ሁለተኛው እድል እያመለጠ ነው ሦስተኛ እድል ይኖራቸው ይሆን?

abiy ሁለተኛው እድል እያመለጠ ነው ሦስተኛ እድል ይኖራቸው ይሆን?ሰርፀ ደስታ

ዛሬ በለውጥ ሥም የወያኔ ማደጎዎች ከአሳዳጊያቸው የወረሱትን የሴራ ፖለቲካ ቁማር የተረከቡት ራሳቸውን የለውጥ አራማጅ አድርገው ይሄው አገርን ወደለየለት አደጋ እየመሩ ያሉት የዛሬ ሁለት ዓመት ተኩል በፊት ሕዝብ 27 ዓመት የደለበን የዘረኝነት ጥላቻ ወላጅ ዓባታቸው ወያኔን ገፍትሮ ከአዲስ አበባ ባስወጣ ጊዜ የለውጥ መሪ ነን ብለው የተሰየሙ ለጊዜው ሕዝብን ቢሸውዱም ከቀን ወደቀን ማንነታቸው ጥርት እያለ እየወጣ ነው፡፡ ከወያኔ ጋር በነበራቸው ዘመን የሰሩትን ኃጥያታቸውን ሕዝብ ይቅር ብሎ በመሪነት እንዲቀጥሉ እድል መስጠት ብቻም ሳይሆን ሙሉ ድጋፍም አድርጎላቸው ነበር፡፡

ወያኔን ለማስወገድ በነበረ ትግል ሕዝብ 27 ዓመት የተሰራበትን የዘረኝነትና የጥላቻ ግንብ አፍርሶ ከምርም ኢትዮጵያዊነቱን አጉልቶት ነበር፡፡ ያኔ ነበር 27 ዓመት በኦሮሞና አማራ መካከል ወያኔ የሰራቸውን ሴራና ዘረኝነትን ሰብራው ኦሮማራ የሚል ለወያኔ አስፈሪ የሆነው የኦሮሞና አማራ ሕብረት የተፈጠረው፡፡ ቀጥሎም በአገሪቱ ወዳሉ ሕዝቦች ሁሉ ተቀጣጥሎ አንድ ኢትዮጵያዊ የሆነው፡፡ ይሄን ማንም ፖለቲከኛ አላገዘውም፡፡ ማንም ምሁር ንድፍ አላወጣለትም፡፡ ሕዝብ በራሱ ያደረገው እንጂ፡፡ እርግጥ ነው በወቅቱ የዛሬን አያድርገውና እነ ለማ መገርሳ ከዚሁ የሕዝብ አንድነት ጋር ቆመው ነበር፡፡ እንግዲህ የቱንም ያህል ወያኔ 27 ዓመት በሕዝቦች መካከል ጥላቻንና ዘረኝነትን ብትሰራም ሕዝብ ግን በአንዲት ሰሞን ነበር አንድ ሆኖ ከዳር እስከዳር ትግሉን ያቀጣጠለውና በእርግጥም የአንድነትን ትርጉም በተግባር ያየው፡፡

ዛሬ በለውጥ ስም ወደሥልጣን የመጡት የወያኔ ወራሽ ልጆች ይሄን ሕዝብ በራሱ ጊዜ ከ27ዓመት በኋላ ያመጣውን እንድነት ነው አፍርሰው ዛሬ የምናየውን ከወያኔም ጊዜ የከፋ የዘረኝነትና ጥላቻን በአገሪቱ ላይ ዳግም የመሠረቱት፡፡ ግልጽ ነበር፡፡ የወያኔ መወገድና የሕዝብ በአንድነት በዛ መልኩ በራሱ ጊዜ መጥቶ በሙሉ ልብ ለወጥ እናራምዳለን ላሉት ደጋፊ የሆነበት እውነት ከመንም አገርን ወደሠላም ለመመለስና ሁለተኛ በወያኔ ያየንው እንዳይደገም ትልቅ እድልና አጋጣሚ ነበር፡፡ የለውጥ አራማጅ ነን ያሉት ግን ከአሳዳጊያቸው የተጠመቁትን ሴራ እንጂ በፍጹም መሆን የሚገባውን ማሰብ አልወደዱም፡፡ ነገሩ በሴራ የኖረ አእምሮ መልካም ነገርን ማድረግ ያስፈራዋል፡፡ ያን የመሠለ እድል ነበር በፍጥነት በኦሮሞ ተረኝነት ተክተው ይሄው አሁን ላለንበት ደረጃ የደረስንው፡፡  ብዙዎች ኢትዮጵያዊ ነው ሌሎች አስቸግረውት ነው እንጂ እያሉ የሚወሩለት አብይ አህመድ ነበር ዋናው ያንን የመሠለ አድል ዳግም ላይመለስ በኦሮሙማ ስግብግብነት፣ ዘረኝነት፣ ጥላቻና የበታችነት ስሜት ለመቀየር ዋነኛ ተዋናዩ፡፡ ሌላ ሌላውን ትተን በራሱ ፊርማ የሆኑትን ብናይ የኢትዮጵያን ንግድ ባንክ አፍርሶ በኦነጋውያን አስወረረ፣ ታከለ ኡማን ከአዲስ አበባ ሰው (ኦሮሞም ከተፈለገ) እንደሌለ ብጤ ከኦሮሚያ አምጥቶ ሾመ፡፡ በፍጥነት የአዲስ አበባና ወሳኝ የፌደራል መዋቅሮችን በኦሮሞ እንዲያዙ አደረገ፡፡  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከገንዘብ አክሳሪነቱ በላይ ዛሬ በየቦታው እየሆኑ ላሉ የሕዝብ እልቂቶች ዋና የገንዘብ ማስተላለፊያ ሆነ፡፡ የሚገርም ነው የዚህ ባንክ የዛሬ ሥራ አስኪያጆች የተመደቡት ከራሱ ከባንኩ እንኳን አደለም በፊት ከአዋሽ የመጣ በባንክ አስተዳደር ምንም ልምድ የሌለው በጴንጤነትና በኦሮሞነት መስፈርተ ቢቻ የገባ ሲሆን የአሁኑ ደግሞ የሙያ ብቃቱ ባያጠያይቅም የመጣው ከኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ነው፡፡ ልብ በሉ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ሲጀምር ዘረኛና በኢትዮጵያ የኮሜርሽያል ኮድ ሕግን በሚጣረስ ሁኔታ የተመሠረተ ባንክ ከመሆኑም በላይ ዛሬ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥራ አስኪያጅነት የተመደበው ግለሰብ በቀድሞ ባንኩ ከፍተኛ ባለድርሻ የሆነ ነው፡፡ እንግዲህ ይሄ ግለሰብ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስኪያጅ እንጂ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ነው ቢባል ቀልድ ነው፡፡ እንግዲህ ይሄ እየሆነ ያለው ስንት የባንከ አስተዳደር ሙያ ያላቸውን ባለሙያዎች ያሉት ባንክ ነው፡፡ ታከለ ኡም በሁለት ዓመት ውስጥ አዲስ አበባን ምን እንዳደረገ አይተናል፡፡

ከላይ እንደጠቀስኩት እንደምልክት ነው፡፡ ብዙ ብዙ ሴራ ተሰርቷል፡፡ አብይ አህመድ ከዚህ ሌላ የሐይማኖታዊ ሴራ ቁማርም ቆማሪ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ዛሬ ብልጽግና የተባለው ቡድን ማኒፌስቶ የኦርቶዶክስንና እስልምናን ሥም ጠርቶ ሲኮንን ፕሮቲስታንቲኒዝምን ያበረታታል፡፡ ይሄ ለብዙዎች እንደዋዛ ታይቶ እየተዘነጋ ይሚስላል፡፡ የግዜው ግዜ ግን ይሄ ነገር ይዞት የሚመጣውን አደጋ አብረን እናየዋለን፡፡ ቀጥሎም የኦሮሞ ጽንፈኞችን ከለላ በመሆን በአገሪቱ የለየለት ሥራዓተ አልበኝነትንና የዜጎችን ፍጅት ከለላ እየሰጠ ማከናወኑን ቀጠለ፡፡ አብይ አሜሬካ ሄዶ ከእነ ጀዋር ጋር ከተገናኘ በኋላ ይሄን በስፋት ከኋላ ሆኖ ሲመራው ነበር፡፡ በመጨረሻም ለሚያሴረው የኦሮሞ-ኦነግ/ኦፒዲ የሴራ ጉዞ እንቅፋት ይሆናሉ ብሎ ያሰበውን የአማራ ክልል ባለስልጣናትን አስደለ ከእሱ ጋር የሚተባበቱትን ለራሱ አስቀረ፡፡ ሳዕረም የዚሁ ሰለባ ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜ አብይና ወያኔ በጥምረት ይሰሩ ነበር፡፡ የዛሬን አያድርገውና፡፡  የማነሳቸው ጉዳዮች በተግበር ሆነው የታዩትን እንደሆነ ግን ልብ በሉ፡፡

ቀጠለ ነገሮች ከምርም እየተበላሹ መጡ ወያኔም እየቆየች ጉልበትም ሞራልም አገኘች፡፡ የወያኔዎች ጥያቄ እኛ ከዚህ የከፋ ምን አድርገናል በሚል ነበር፡፡ ከዛ መናናቁም መተዋወቁም ስላለ ወያኔ ትግራይ ሄዳ ያደረገኝውን ሁሉ አድርጋ በቅርብ ያየንው ጠርነትን እስከመክፈት እድል አገኘች፡፡ ያ ጦርነት ዛሬ እነ አብይ እንደሚያወሩት ሳይሆን በግልጽ የመከላከያው ድክመት እንደሆነ እንታዘባለን፡፡ ወያኔ ያንን ሁሉ የሰሜን እዝ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጋ በአንድ ጊዜ ስትይዝ መረጃ በመለዋወጥ ነበር፡፡ ይሄ የመረጃ ልውውጡ አዲስ አበባ ውስጥ ላሉ የወያኔ ሴራ አስፈጻሚዎች ሳይቀር ደርሶ እነሱ ቤተሰባቸውን ወደመቀሌ ልከው አዲስ አበባ ላይ ጦርነት ለመክፈት ዝግጅት አድርገው ነበር፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን የመከላከያው እዝም ሆነ የአገሪቱ ደህንነት አናውቅም ነበር እያሉን ነው፡፡ አስገራሚ ነው፡፡ አሳሳቢም ነው፡፡ እንኳንስ ይሄን የሚያህል ሰንሰለት ሲዘረጋ ይቅርና መከላከየው እንደ ተቋማዊ ባህሪው የሆነ ቦታ አጠራጣሪ የሆነ ክፍተት እንኳን ቢያይ እርምጃ ለመውሰድ የነቃ መሆን አለበት፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ ነበር የሰሜኑ ጦርና አረመኔዎች ተጋልጦ መሳሪያውም በወያኔ የተቀማው፡፡ ይሄን እውነት ሳሰብ አሁንም አጅግ ያሳስበኛል፡፡ መከላከያን የሚያህል ተቋም በዚህ ያህል ክፍተት ሲገኝ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን የአብይ ደህንነቶች የግለሰቦችን ቲዊተርና ፌስቡክ አካውንት እየሰበሩ ነበር፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ የተራ ግለሰቦችን የግል መረጃ ልውውጥ ሳይቀር እያወጡ ግለሰቦችን ሲያስፈራሩ ነበር፡፡  ይሄ ሁሉ ከሆነ በኋላ ነበር መከላከያው  ልዩ ኃይል አጋዥነት ራሱን መልሶ  በማደራጀት ወያኔን ዛሬ የሆነችውን ያደረጋት፡፡ ለዚህ ደግሞ ከልባቸው ኢትዮጵያዊ የሆኑ የጦር መሪዎችና ተዋጊዎች ታላቅ ምስጋና ይድረሳቸው፡፡ እግዚአብሔርም የልባቸውን አይቶ የወያኔንም የዘመናት ግፍና እብሪት ለመበቀል ደል በእጃቸው አደረገ፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን አብዝቶ ሲወራ የነበረው የድሮን ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ይሄም የፕሮፓጋንዳው አካል እንጂ ጦርነቱ የድሮን አልነበረም፡፡ ቆይታችሁ ሁሉንም ትረዱታላችሁ፡፡ በድሮን እየተከታተልናችሁ ነው እያለ ሲያውጅላቸው የነበረው አብይ ይሄው ዛሬ ደግሞ ለጠቆመኝ 10 ሚሊየን እሰጣለሁ ይላል፡፡ እውነታው የአይ ኃይሉ እገዛ እያደረገ የቀጥታ ተዋጊዎች ናቸው ይሄን ድል ያመጡት፡፡ በዚህ ሂደት የአማራ ልዩ ኃይልና ፋኖ ታላቅ አስተዋጾ አደርገዋል፡፡ የኣር ልዩ ኃይል በክልሉ ወያኔዎች እንዳያመልጡ የራሱን ኃላፊነት ተወጥቷል፡፡

ይሄ የጦርነት ከጦርነቱ ድል ባሻገር ዳግም ለሁለተኛ ጊዜ ለእነ አብይ እድል የሚሆን የሕዝብን እንድነትና ሕዝብ ከእነ አብይ ጎን በመቆም ለሚቀጥለውም የሄዱበትን የተሳሳተ መንገድ እንዲያስተካክሉ እድል ሰጠ፡፡  ነገሮ ያዳቆነ ሰይጣን ሆነና ገና ጦርነቱ ሳያልቅ ነበር በዘረኝነትና ጥላቻ የተመረዙት የኦሮሞ ባለስልጣናት  በአማራ ላይ ማሴር የጀመሩት፡፡ የአማራ ልዩ ኃይል በቀጥታ ተሳትፎ በግፍ ከአማራ ተቀምተው ለወያኔ ባለስልጣናት ወደ ትግራይ የተካለሉ ቦታዎቹን ማስመለስ ብቻም ሳይሆን መከላከያውንም በመታደግ ትልቅ ድርሻውን በማበርከቱና ሥሙ መጠራቱ የኦሮሞ ባለሥልጣናትን እብድ አደረጋቸው፡፡ ባለስልጣናትን ብቻ አደለም ሁመራና ራያን ወደ ባለቤቶቹ መመለሳቸው ቀለም የቆጠረ ብዙ ኦሮሞን ነበር ያቀወሰው፡፡ ያሳዝናል፡፡ በእነዚህ ቦታዎች የመሬቶቹ ባለቤቶች ከቦታቸው እየተገደሉና እየተሰደዱ ኖረዋል፡፡ በመጨረሻም በማካድራ የሆነውን አይተናል፡፡ ይሄ ሁሉ በዘረኝነትና ጥላቻ እንዲሁም የበታችነት ስሜት ለተጎዳው የኦሮሞ ኦነጋውያን ሊታያቸው ቀርቶ ጭራሽ ያ ሰቆቃ ቢቀጥል ደስታቸው ወደር የለውም፡፡ ከእነዚህ ቦታዎች በግፍ የተፈናቀሉ ዛሬ በየአገሩ ተሰደው ይኖራል፡፡ በብዛት የቀናቸው አውስተራሊያ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ አብዛኛው ግን ዛሬም በሱዳን በስደት እየተንከራተተ ያለ ነበር፡፡ አሁን ወደ ቦታው እየተመለሰ ነው፡፡  ይሄ ሁሉ ሕዝብ አፈናቅለው የወያኔ ባለስልጣናትና ቤተሰቦቻቸው ነበሩ እነዚህ መሬቶች በስፋት ወሰዱት፡፡ አሁንም ስለእነዚህ መሬቶች በድፍረት ሊየወሩ የሚሞክሩ የትግራይ ባለስልጣናት አሉ፡፡ ዳግም ሕዝብ ለአራጆች ተላልፎ አይሰጥም ራሱን የመከላከል አቅም እንዲኖረው ይደረጋል፡፡ ቦታዎቹ ዳግም ትግራይ በሚባል ግዛት ሊገቡ የሚችሉበት ምንም አይነት ሕጋዊ በሉት ሞራላዊ አሰራር የለም፡፡ ብዙ ማይካድራዎችን የተፈጸመበት ሕዝብ ቅዱስ እግዚአብሔር የግዜው ጊዜ ጠላቶቻቸውን በአይናቸው ፊት አዋረዶ ለግፉዓኑ ፈርዷል፡፡ ይልቅ ሁንም ጤነኛ የሆነ ግንኙነት እነዲኖር ቢሰራ ጥሩ በሆነ፡፡  እየሆነ ያለው ግን ይሄ አደለም፡፡

አብይ ምን ያለበት ምን ኤችልም እንደተባለው ከጦርነቱ በኋላ መከፋፈል እንዳይኖር ሲል ነበር፡፡ ከኋላ የመከፋፈልን ሴራ እያሴሩ አትከፋፈሉ ይገርማል? ይሄ ጦርነት እድል ነበር፡፡ ሁለተኛ የተገኘ አጋጣሚ፡፡ ይሄው የተፈጠረውን እድል ወዴት እየመሩት እንደሆነ ገና ጦርነቱ ሳያልቅ ጀምረው አሁን እያየን ነው፡፡ እንግዲህ መከላከያው ውስጥ ያሉት በሳል ሆነው ይሄን የእነ አብይን ቁማር አደብ እንዲያዝ አድርገው አገርን ወደማዳን አሰራር ሕዝብን መመለስ ካልተቻለ እየሆነ ያለው ሶስተኛ እድል በማይፈጠርበት ሁኔታ ትልቅ አደጋ ነው፡፡  በቀደም አብይ ወደ ቤኒሻንጉል የሄደበት ሁኔታና ከሄድም በኋላ በዛ ያደረገውን ብዙዎች አስተውለውታል፡፡ አልደግመውም፡፡ ከምንም ነገር በላይ ግን አሳኙ አብይ እዛ የሄደው የለመደውን ሴራ ለማሴር መሆኑ ነው፡፡ ሲጀምር አብይ አዛ ቦታ የሚሄድበት አንዳቸውም ምክነያት አልነበረም፡፡ ከሄደም በቦታው ተገኝቶ አካባቢውን ለሚያስተዳድሩት ማስጠንቀቂያ መስጠት ሲገባው በግልጽ ቀድሞውንም ተነጋግረው የጨረሱትን ጉዳይ በፊልምና ፎቶ ለማሳየት ነበር አብይ የሄደው፡፡ በቦታው ላይ ኢቲቪና ኦቢኤን አሉ፡፡ ሌላ ፋና አለ መሰለኝ፡፡ ሌላ ማየት አልቻልኩም፡፡ በዚህ ቦታ ላይ ከኦቢኤን የአማራ መገናኛ ብዙሀን ይቀርባል፡፡ እነአብይ ኦቢኤንን የኢስት አፍሪካ እናደርጋለን የሉናል (አዲሱ አረጋ) በቀበሌ ከቀበሌ ባነሰ የአስተሳሰብ ልኬታቸው፡፡ ይሄን ሰምቶ ነው መሰለኝ የአማራው ክልል መሪ አገኘሁ ሰሞኑን እንዲሁ የአማራ መገናኛ ብዙሀንን እናሳደጋለን አዲስ አበባ ስቲዲዮ እንከፍታለን ሲል የነበረው፡፡ ሁለቱም ያው የአሳዳጊያቸውን የወያኔን ባህሪ ይዘው ስለአደጉ የሕዝብ ቀልብ ይስባል ብለው የሚሉትን ሕዝብን ለመሸወድ የማያረጉት የለም፡፡ የሆነ ሆኖ አብይ በዚህ ቦታ በተገኘ በሰዓታት  የሰማንውን አይነት አረመኔያዊ ግፍ መፈጸሙ ብቻም ሳይሆን ለዚህ አረመኔያዊ ድርጊት አንዱ ዋነኛ ምክነያትም ነው፡፡ ሲጀምር አብይ ጋር ይሄዳሉ የተባሉ ባለስልጣናተን እናጅባለን ብሎ መከላከያ ከቦታው ሲለሄደ ዜጎች ታረዱ፡፡ ሲቀጥል አብይ በቦታው በመገኘት ለአራጆች የልብልብ የሚሆናቸውን እድል ነበር የሰጠው፡፡

አዝናለሁ ሶስተኛ ጊዜ ሌላ እድል ያለ አይመስለኝም፡፡ የሚገርም ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን ይሄን አረመኔ ደርጊት ያወገዘ ተቋም አላየንም፡፡ ኢሰመጉ ሥራው ቢሆንም እሱም የሰጠው መረጃ የተዛበ ነበው፡፡ ለመሆኑ ግን በሕዝብ እንመረጣለን አገር እንመራለን የሚሉት የት ናቸው? እነ አብይ ጭራሽ አሁን አገርን ወደለየለት ማፈረስ ለማድረስ በዚህ ሁኔታ ወደምርጫ እንሄዳለን ብለው ወስነዋል፡፡ ለነገሩ እዛም መድረሳቸውን እንጃ፡፡  ብዙ የታመንባቸው ዛሬ ላይ ማንነታቸውን ለውጠው ታይተዋል፡፡ በሕዝብ ዘንድ ትልቅ ከበረታ የነበራት ብርቱካን ሚደቅሳ ዛሬ እንደወያኔው ዘመን የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች ሆኗል ንግግሯ፡፡ ከምርጫ በፊት አስተማማኝ ሕግና፣ ሠላም ሊፈጠር ሲገባው ይሄው ወደ ሶስት አመት የተጠጋ ጊዜ አገርን በሕግና በፖሊሲ መገንባት ሲቻል ወደለየለት አደጋ እየከተቷት ነው፡፡ ማንም የሕዝብን ድምጽ ለመስማት ፍቃደኛ አደለም፡፡ በአሳዳጊያቸው በወያኔ ሥርዓትና ሕግ ለመቀጠል ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ እንግዲህ የት ድረስ እንደሚደርሱ አናውቅም፡፡ ነገሩ እያንቀዠቀዣቸው ያለው ሲሰሩት የኖሩት ግፍና በደል ዛሬ ሕዝብ ይቅር ቢላቸው የተሸወደላቸው መስሏቸው መሰለኝ፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ግን ስለተሰፈረ ምን ዓልባትም እንደፈርኦን መጥፊያቸውን በፍቃዳቸው እያፈጠኑት ይመስላል፡፡ ገደልንው ከአሉት ከአሳዳጊያቸው ወያኔ እንኳን መማር አልፈለጉም፡፡ አዝናለሁ፡፡ እግዚአብሔር ሁሉም ነገር ጠርቶ እስኪታይ ያያል፡፡ በዚህ አጋጣሚ አሁንም እላለሁ መከላከያው ከእነዚህ የጥፋት ዘሮች እራሱን አግሎ ለአገርና ሕዝብ ይቁም፡፡ በወያኔ ሥርዓትና ሕግ በመቀጠል አገርን ወደ ሌላ ቀውስ እየከተቱ ምርጫ የሚሉትን ከወዲሁ አደብ እንዲገዙ ሁሉም እንዲያሳሰብ እላለሁ፡፡  ተመከሩ ቢባሉ ሊመከሩ አልቻሉም፡፡ ደብረጽዮንም ሲያመነታ ነው ዛሬ የደረሰው እጣ የደረሰው፡፡ እነዚህም ወደው አይመስልምና ሕዝብም ሆነ ሌላ የሕዝብ አገራር ከእነሱ በመለየት አገሩንና የራሱን ደህንነት ይጠብቅ፡፡

ቅዱስ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ! አሜን!

ሰርፀ ደስታ

1 Comment

  1. ድሮ ድሮ ት/ቤት እያለን የበሬ የዘር ፍሬ ከረጢት ይወድቅልኛል ብላ ዘመኗን ሙሉ ስለምትጠብቅ አንዲት እንቁራሪት ተረት ይነገረን ነበር፤ ፤ አንተም እንቁራሪቷን መሰልክኝ! “አንድ ሁለት ዕድል” ያንተ አቆጣጠር ነው፤ ምናባዊ! እሱን ተወው እና ይህን ተቀበል፤ አቢይ ከምርጫ ዉጭ በምንም ተአምር አይወርድም፤፤ እደግመዋለሁ በምንም ተአምር፤ ተለማመድ! አብዛኛው ህዝብ ዲያስፖራውን ጨምሮ ቢያንስ ቅንነቱን እና ለኢትዮጵያ በጎ አሳቢ መሆኑን ተቀብሏል፤፤ ያለዚያማ ስቴት ዲፓርትመንት ፊት ለፊት በየሳምቱ ሰልፍ ይሆን ነበር እኮ፤፤ አንተና የአንተ አይነቶች (በኢትዮ360 የምትመሩ) በጣም MINORITY መሆናችሁም ይታወቃል፤፡ እኔ በግሌ አቢይን አፍቅሬው ወይም በጥቅም ተደልዬ እንዳይመስልህ፤፤ Far from it!! የምነግርህ ግን እንዳንተ ሁለት አገር እንደሌለኝ ነው፡፡
    To make matters worse and for your disappointment በሚቅጥለው ምርጫ ብልጽግና ከፍተኛ ድምጽ የሚያገኘው ክአማራ ክልል ነው፤፤ ዝቅተኛው ክኦሮሚያ፤፤ አይገርምህም? አንተ ችግርህ አቢይ ስለሆነ አይደለም፤ ክዴይ ዋን ጀምሮ የሱ ጠ/ሚ መሆን አልተዋጥልህም፤፤ ለምን እንደሆነ እንጃ፤ ሳስብህ ምንም ነገር የማይጥምህ ሁሉን ነገር ተጠራጣሪ ድሮ ድሮ “አኞ” የምንለው አይነት ትመስለኛለህ፤፤ በቃ መቃወም ካልሆነ የሰውን ምንም ጥሩ ነገር ማየት አትችልም፤፤ እስቲ እንደው ስለ አቢይ አንድ ጥሩ ነገር፤ እንደው አንድ ንገረን እና እኔ ዉሸታም ልሁን እና ይቅርታ ልጠይቅ፤፤
    እንግዲህ Abiy is there to stay, till the ballot box says otherwise, ተለማመድ አባቱ፤ ቻለው!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.