የቤኔሻንጉል  በጉራፈርዳና ሌሎችም ቦታዎች  ለምን በተከታታይ በዘር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በረታ?

አክሊሉ ወንድአፈረው ( [email protected] )

ዲስምበር 26፣2020

ባለፈው ጥቂት ወራት በቤኒሻንጉል ነዋሪ የሆኑ የአማራና አገው ማኅበረሰብ አባላት ላይ ሰፊ ጭፍጨፋ ተካሂዷል። ይህን አስቃቂ ግፍ ሰምተንና ዓይተን ሳንውል ሳናድር ጥቅምት 12፣ 2013 ዓ. ም (ኦክቶበር 22፣ 2020)  ደግሞ በቤንች ማጂ ጉራፈርዳ የአካባቢው ባለሥልጣኖች እንደሚሉት  የ18 ሰዎች (በአካባቢው ሌሎች ምንጮች መሠረት እስክ 89 የሚደርሱ)  ህይውት የቀጠፈ ተመሳሳይ ጭፍጨፋና ተዛማጅ ማፍናቀል በአማራ ማኅበረሰብ ተወላጆች ላይ በድጋሚ መፈጸሙ ይፋ ሆኗል። ትላንት ደግሞ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ ውስጥ በተመሳሳይ ጥቃት አሁንም ለስብሰባ በተጠሩ ሰላማዊ የአማራ ማኅበረሰብ አባላት ላይ ጭፍጨፋ ተካሂዶ ብዙዎች አልቀዋል፡ባለፉት ጥቂት ቀናትና ሳምንታት ውስጥ ደግሞ በቤንሻንጉል ተመሳሳይ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ እየተካሄደ ነው።

የሚገረምው ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲሀ የምንሰማው ከነዚሀ ጭፍጨፋዎች ጀርባ የመንግሥት ባልሥልጣናት እጃችው እንዳለበት መንግሥት እያመነ መምጣቱና የተወስኑ ባልስላጣናት መታሰራቸው ነው። ይህ ደግሞ ዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ ብቻ ሳይሆን ከፍትኛ የክልሉ ባለስልጣናትንም ጭምር የሚያካትት እንደሆነ በመንግስትም  የታመነ ነው።

ይህ ከዶክተር አብይ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋም ሆነ ከዚያ በፊት በተከታታይ የሚካሄደው ጭፍጨፋ መሠረቱ ምንድን ነው? ሊያቆም ያልቻለውስ ለምን ይሆን? የሚለውን በአግባቡና በሀገራዊ የሀላፊነት ስሜት መመርመር ተገቢ ነው።

በሽታውን ካልተረዳን ተገቢውንም መድሀኒት ማግኘት አይቻልና በዚህ አኳያ ያለኝን አስተያየት አጠር ባለ ሁኔታ አካፍላለሁ።

ያላቋረጠው ጥቃትና መዋቅራዊ (systemic and structural) መሠረቶቹ

የአንድ ችግር መዋቅራዊ ነው ሲባል በሕግ፣ በአስተሳስብ፣ በተቋም…ወዘተ ተደግፎ የሚነሳና የሚካሄድ ነው ማለት ነው። የአንድ ሀገር የፖለቲካ አወቃቀር፣ የኢኮኖሚ ሥርዓት፣ የሕግ ይዘት መሪው ትርክት ለተጠቃሹ ቀውስ መፈጠርም ሆነ በቀጣይነት መካሄድ የሚያበረክተው አስተዋጻኦጽዖ አለ ማለት ነው። ይህ ሲሆን ቀውሱ በተወስኑ ግለስቦች ፍላጎትና አስተሳስብ ብቻ ሳይሆን በቀጣይነት እንዳያባራ የሚያበረታታ፣ የሚደግፍና የሚያጠናክረው የተዘረጋው ህግ፣ ህጉንም ለማሰፈጸም የሚዋቀሩት ተቋማትና አሠራር መኖሩን ያሳያል።

ይህን ለማወቅም በሕገ-መንግሥቱ፣ በሌሎች ሕግጋት፣ በመንግሥታዊና ሌሎች ተጽዕኖ ፈጣሪ ተቋማት የመንግሥትንና የገዥው ፓርቲ ዕይታ በሚያንፀባርቀው ትርክት ውስጥ የተጠቀሰውን ጥቃት የሚያግዙና የሚያራምዱ ጉዳዮች መኖራቸውን መመርመር ይጠይቃል።

ቤቤኒሻንጉል በጉራፈርዳም ሆነ በመተክል ወይም በኦሮሚያ አካባቢ ለተፈጠረው ጥቃትና ቀውስ ዘርፈ-ብዙ ምክንያቶች መኖራቸው ግልጽ ነው።  በዚች አጭር ጽሁፍ ሁሉንም መነካካት አይቻልምና በተለይም መዋቅራዊ ናቸው  ከዚህም ጋር ተዛማጅነት አላቸው በምላቸው ላይ ትኩረት እስጣለሁ።

ሕገ-መንግሥቱ የቀውሱ መፈልፈያ (መዋቅራዊ መሠረት) ለመሆኑ አንዳንድ ማሳያዎች

ኅዳር 1995 ዓ. ም የጸደቀው “የተሻሻለው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሕገ_መንግሥት”  አንቀጽ ሁለት የሚከተለውን ይላል።

“የክልሉ ባለቤት ብሄረስቦች” በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ሕዝቦች እንዳሉ የሚታወቅ ቢሆንም የክልሉ ባለቤት ብሄረሰቦች በርታ ጉምዝ፣ ሽናሻ፣ ማአኦና ኮሞ ናቸው” ይላል። http://ethcriminalawnetwork.com/system/files/BENSHANGULE%5B1%5D.pdf

በ1999 ዓ. ም የሕዝብ ቆጠራ መሠረት በክለሉ ውስጥ የሚኖሩት የተለያዩ ብሄረሰቦች አባላት አማራ 25.41%፣ በርታ 21.69%፣ ኦሮሞ 13.55%፣  ሽናሻ 7.73% እንዲሁም አገው አዊ 4.22%።   (ethnic groups and others (data from 1999 census) ያጠቃለለ ነው

ከላይ የሰፈረው በግልጽ የሚያሳየው ሕገ-መንግሥቱ በክልሉ የሚኖሩ ኢትዮጰያውያንን ሁሉ፤ በቡድንም ይሁን በግለሰብ፣ በእኩልነት የሚመለከት ሳይሆን  የተለያየ ደረጃ መብት ያላቸው አድርጎ በደረጃ ያስቀመጠ መሆኑን ነው። ይህ ማለት የሁሉም ዜጎች የፖለቲካም ሆነ ተዛማጅ መብቶች አኩል ላለመሆናቸው መሠረቱ ሕገ-መንግሥቱ ነው ማለት ነው።

የአንድ ማኅበረሰብ መንግሥታዊ ተቋሞች የሚዋቀሩትና የሚንቀሳቀሰት “የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ“ የሚባለውን ሕግ-መንግሥቱን መሠረት አድርገው ነው። በመሆኑ በዚህ ክልል የተዋቀሩ የተለያዩ የሕግ፣ የፍትኅ፣ የፀጥታና ሌሎችም ተቋማት የሚዋቀሩትና የሚንቀሳቀሱት አድሏአዊ በሆነው ሕገ-መንግሥት መሠረት በመሆኑ እርሱም በዋናነት አድሏአዊ ያደርጋቸዋል። ስለዚህም የክልሉን ችግሮች የግለሰቦች ፍላጎትና አስተሳስብ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን መዋቅራዊ ያደርገዋል። አድሏአዊነት አንዱ መገለጫው ደግሞ በአካባቢው የፀጥታ ኃይልና የፍትኅ ሥርዓት ላይ ነው።

ተቋሞቹ ሲዋቀሩ የአካባቢውን ነዋሪዎች በእኩልነት ዓይተው ይህንንም ለማስከበር ስላልሆነ “የመጤዎችን” መፈናቀል፣ ማጥቃት፣ የንብረታቸው መዘረፍ፣ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብታቸው መጣስ…ወዘተ እንዲቆም ለማደረግ የሚችል አወቃቀርም ተልዕኮም ግንዛቤ ውስጥ አስግብተው የተደራጁ አይደሉም።  ጭቆናንና አድልዖን ተግባራዊ ለማድረግ ታስቦ የተቀረፀና ተግባራዊ የሆነ ሕግና ተቋማት ከዚህ ውጭ ሊያደርጉ አይችሉም። ይህ ሁኔታ በቤነሻንጉል፣ በኦሮሚያ፣ በቤንች ማጅና በተለያዩ ቦታዎች በይፋ መታየቱ ምስክር ነው።

የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት

ኢህአዴግ ከጅምሩ ስለሀገራችን፣ ስለሕዝባችን፣ ስለታሪካችንና ስለማንናታችን ያለው አመለካከት ሁሉ በአጥፊና ጠፊ፣ በጭቋኘና ተጭቋኝ አንዱ ከተጠቀመ ሌላው ስለሚጎዳበት ሁኔታ ከፍተኛ ትኩረትን የሰጠ ነው።

ይህ ትርክት “ከሌላ ቦታ” የመጣውን የተወስነ የኅብረተሰብ ክፍል በተለይም የአማራውና የአገውን ኅብረተሰብ ለሀገሪቱ ችግሮች ሁሉ ተጠያቂ፣ ለተለያዩ ማኅበረሰቦች በልማት በእድገት…ወዘተ ወደኋላ መቅረት ተጠያቂ የሚያደርግ ሚዛን ያጣ አመለካከት ነው።

ይህ ዕይታ ወደ መንግሥት ርዕዮተዓለም ተሸጋግሮ በሀገሪቱ ገዥ ፖለቲካ ፓርቲ አባሎችና ደጋፊዎቹ፣ በመገናኛ ብዙሃን፣ በትምህርት ተቋሞች…ወዘተ እንደ ብቸኛውና ትክክለኛው አስተሳሰብ እየተነዛ ቢያንስ 27 ዓመት ቆይቷል።የተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍልን በፍራቻና በጥላቻ  ማየትን…ወዘተ እንደ ትክክለኛ አመለካከት፣  በዚህ ክፍል ላይ የሚወሰድ እርምጃንም አግባብ ያለው እንደሆነ  በማድረግ  በ”መጤው” ላይ የሚካሄደውን የማግለል ሂደትና ጥቃት መዋቅራዊ መሠረት ሰጠቶታል። ተገቢ እርምጃም ተደርጎ እንዲወሰድ አድርጎታል።

ይህ ትርከት የሕዘቡን ግንኙነት በአጥፊና ጠፊነት ዓይን እንዲተያይ አድርጎታል፣ከጋራ ተጠቃሚነት ይልቅ ያንዱ ጥቅም የሌላው ጉዳት ተደርጎ እንዲታይ በማድረጉ፣ ለቀጣይ ቀውስና ጥቃትም መሠረት ጥሏል።

የመዋቅራዊው አድልኦና የጥቃት (Violence ) ተያያዥነት

አድልዖ አንድ ግለሰብ ወይም ማኅበረስብ ከሌሎች በተለየ ሁኔታ አሉታዊ በሆነ ሁኔታ የሚስተነገድበትን እውነታ የሚያመለክት ሲሆን ብዙ ጊዜ የሚሆነውም ፆታን፣ የቆዳ ቀለምን፣ ብሄርን፣ ቋንቋን፣ የትውልድ ቦታን…ወዘተ መሠረት በማድረግ ነው።

መዋቅራዊ ጥቃት (institutional/ structural violence) የሚለው ቃል በአንድ ሀገር የሚገኙ ሕግጋትና ተቋሞች የተውስነ የኅብረተሰብ ክፍልን በተለየ ሁኔታ የሚጎዳና እንደሌሎቹ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሕግ ከለላ የሚሰጥ ባለመሆኑ በዚያ ኅብረተሰብ ላይ ሊደርስ የሚችል ሰነልቦናዊ  (psychological)፣ ኢኮኖሚያዊ፣  (Economical) አካላዊ (physical)፣ መንፈሳዊና  (spiritual) ሌሎችም ጎጅ ገጽታዎችን ያመለክታል።

የዚሀ ዓይነቱ መዋቅራዊ አድልዖ አግላይነትን ተግባራዊ ባደረጉ ኅብረተሰቦች ውስጥ ግጭትና ቀውስ በቀጣይ የሚካሄድ ለመሆኑ በአፓርታይድ ሕግ ሥር በነበረችው በድቡብ አፍሪካ፣ በዳርፉር በአየርላንድ…ወዘተ የተከሰቱት ግጭቶች አሳይተውናል;  በተጨማሪም በምዕራቡ ዓለም በጥቁሮችና በሴቶች ላይ ስፍኖ የኖረው መዋቅራዊ አድልዖ እስካሁን ድረስ ያስከተለውንና እያስከተለ ያለውን ጥቃትና አደጋ ሁሉም የሚያውቀው ነው።

በቤኒሻንጉል ጉምዝና በቤንች ማጅ በተወሰኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ አነጣጥሮ የሚካሄደው ተከታታይ ጥቃትም የሚያሳየን ይህንኑ ነው። የየክልሎቹ ሕገ-መንግስቶች አካባቢውን ለሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ሳይሆን ለተወስኑ ብቻ በባለቤትነት የሰጠ ስለሆነ የተወሰኑ ዜጎች በሕግ የተደነገገ አድልዖ ይካሄድባቸዋል። በባለቤትነት ከተሰጣቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የተለየ ቋንቋ ተናጋሪነታቸው የዘር ግንዳቸው እየተቆጠረ ከሌሎች ያነሰ መብት እንዲኖራቸው ተደርገዋል። ይህ  አድልዖ በይፋ የተደነገገውና ተግባራዊ የተደረገውም   የዘረኛው የአፓርታይድ ሥርዓት በደቡብ አፍሪካ በተደመሰሰ ማግሥት የአፍሪካ የነፃነት ቀንዲል በምትጠራው በሆነችው በኢትዮጵያ መሆኑ ውስጥ መሆኑ እጅግ የሚያስገረም ነው።

በሀገራችን ሁኔታ ፖለቲካው ጡዘት እጅግ በተካረረበት ሁሉም ነገር በበዳይና ተበዳይ፣ አጥፊና ጠፊ፣ መጤና ነባር…ወዘተ በሚል ፍረጃ ተከፋፍሎ በሚታይበት አውድ ይህ መዋቅራዊው አድልዖና አግላይነት ማስፈራራትን፣ “ውጡልን ወደመጣችሁበት ሂዱ”  የሚል የማያባራ ሥነሎቦናዊ ጥቃትን፣ ማፈናቀልንና የጅምላ ግድያን ማሰከተሉ አየቀሬ ነው፣ በተግባርም እየታየ ነው።

መዋቅራዊ አድልዖና አግላይነት ተግባርዊ በተደረገበተ ኅብረተሰብ ውስጭ የተገለሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች መሠረታዊ መበታቸውን ለማስከበርና እኩልነትን ተገባራዊ እንዲሆን የሚያደረጉት እንቅስቃሴ ሁሉ በጥርጣሬ የሚታይ ስለሆነ ይህ እውን እንዳይሆነ በየደረጃው በሥርዓቱ ተጠቃሚዎች አፈና ይደረስባቸዋል፣ ቀና ሲሉም ትምህርት እንዲሆናቸው አስከፊ “ቅጣት“ ይሰነዘርባቸዋል፡

ይህ በዋናነት በመንግሥትና በመንግሥታዊ ተቋማት የተደገፈ መዋቅራዊ ጥቃት ኅብረተሰቡን በቅራኔና በውጥረት የተሞላ ብቻ ሳይሆን እጅግ በተካረረ በአጥፊና ጠፊ ግንኙነት እንዲተያይ እርስበርስ ፈጽሞ እንዳይተማመን አድርጎታል።  የዚሀ ምሳሌ በጥቁር አፍሪካውያን ላይ በአፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ፣ በሰሜን አየርላንድ ካቶሊኮች፣ በሱዳን ደግሞ የበዳርፉር ነዋሪዎች በመንግሥት ተቋማትና በተጠቀሱት ማኅበረሰብ አባላት፣ በፀጥታ ኃይሎችና በተጠቀሱት ክፍሎች መሀል በተጨማሪም በአጠቃላይ ኅብረተሰቡ ውስጥ ለዘመናት የቀጠለውን  ሁኒታ መመልከት ትልቅ ተመክሮን  ይሰጣል።

በአጠቃላይ የአጥፊና ጠፊ ስሜትን ለመቀነስም ሆነ የመተባበርና የአብሮነት ሰሜት እንዲዳብር ከተፈለገ በዋናነት ትኩረት ተስጥቶት ሊፈታ የሚገባው ይህንን የሚያራምደውን ሕግ መሻርና በቦታው ደግሞ ሁኔታውን ለመለወጥ የሚየግዝ ሕግ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ የግድ ይላል።  ይህ ሳይሆን የሹማምንት መቀያየርም ሆነ የተለያየ የፕሮፓጋንዳ ሥራ ብቻውን ጊዜያዊ እፎይታን ከማሰገኘት ያለፈ የሚያስገኘው ፋይዳ እጅግ ውሱን ሲሆን ችግሩ መልኩን አየቀያየረ መቀጠሉ አይቀሬ ይሆናል። ጭቆናንና አድልዖን ተግባራዊ ለማድረግ ታስቦ የተቀረፀና ተግባራዊ የሆነ ሕግና ተቋማት ከዚህ ውጭ የሆነ ነገር ሊያደርጉ አይችሉም።

ትግሉ ለ28 ዓመታት በሥልጣን ላይ በቆየው ሥርዓት ተጠቃሚዎችና በለውጥ ፈላጊዎች መካከል ነው

መዋቅራዊ አድልዖ ተግባራዊ በሆነበት ኅብረተሰብ፣ ተጎጂዎች የመኖራቸውን ያክል በሥርዓቱ ተጠቃሚዎችም አሉ። በዋናነት የዚህ አድልዖ ተጠቃሚዎች ሀገሪቱን እንደልቡ ሲያሽከረከር የኖረው ህወሓትና ተባባሪዎቹ የከልሉ ልሂቃን ሲሆኑ ጥቅማቸውም የፖለቲካ የበላይነትን፣ ስፋፊ የእርሻ መሬት በመቀራመት፣ የኩባንያ ባለቤትነትና በመሳሰሉት የተደገፈ የኢኮኖሚና ተጠቃሚነት የሚገለጽ ነው።

ህወሓም ሆነ ጥቅመኛ ልሂቃኑ የሚያንቀሳቅሷቸውን ተቋሞች በመጠቀም ይህንኑ ጥቅማቸውን ለማስቀጠል መጣራቸው የሚጠበቅ ነው።  በተለይም ጥቅማቸውን ያስጠበቀው ሁኔታ ሲናጋ በ”ጠላትነት” የተመደቡት ክፍሎች ላይ እጅግ የባሰ አሉታዊ አመለካክት  እንዲጠናከር አድርጓል፡

በሌሎች ሀገሮችም እንደታየው “መጤዎች” ሥራህን ይውስዱብሃል፣ ንብረትህን ይሻሙሃል…ወዘተ እንደሚባልውና በየቦታው ፀረ-ስደተኛ ተግባሮች እንደሚታዩት ሁሉ በሀገራችንም ሕገ-ምንግሥቱ መሠረቱ ኅብረተሰቡን በዚህ አመልካከት እንዲለከፍ የሚያደርግ ነው፡፡ እኩልነት ከመጣ በሀብት አከፋፈል፣ በፖለቲካ ሥልጣን አያያዝ…ወዘተ ላይ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ የአግላይ ፖሊሲው ተጠቃሚዎች ያውቃሉና፣ ልዩ ጥቅማቸውን ለመከላከልና ሊሎችን በሁለተኛ ደረጃ ዜግንት አፍኖ ለማቆየት የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ።  ከዚህም ውስጥ ዋነኛው ቀጥተኛ በሆነ ጥቃት አለመራጋጋትን ፈጥሮ ለውጥን ማስቆም ሲሆን፣ በኦሮሚያ፣በአማራ፣ ጉራጌ፣ ዶርዜ ወዘት  በቤንሻንጉልና ጉራፈርዳ በአማራና የአገው ማኅበረሰብ አባላት ላይ  የዘር ማጽዳት ጭፍጨፋ ተፈጽሟል።

በሀገራችን ውስጥ የዘረኝነት ፖለቲካን ተግባራዊ እንዲሆን ያደረገው ህወሓት ከማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣኑ ከተወገደበት ጊዜ ጀምሮ ያዋቀረው የአድልዖ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ይናጋል ብለው የሰጉ ተጠቃሚዎች ባሉበት ሁሉ ተከታታይ ቀውስ ታይቷል። የክልል ጉዳይ ላይ ጥያቄ ሲነሳ፣ የዘር ፖለቲካ አስፈላጊነት ላይ ጠንካራ ተቃውሞ ሲነሳ፣ የዘር ፖለቲካ ዋነኛ አራማጅ የሆነው ተቋም ኢሀአዴግን የማፍረስ እርምጃ ሲወሰድ በየቦታው የማፈናቀሉ ተግባር ተጠናክሮ መካሄዱ ይህንኑ እውነታ ያመላክታል።

ምርጫ፣ ፍጥጫና “የመጤው” አበሳ ( ሂድ አትበለው እንዲሄድ አድርገው )

በህወሓት የበላይነት  በ27 ዓመታት ውስጥ ተካሄዱ በተባሉት ምርጫዎች፣ በደርጅታዊ አሠራር የህወሓት ፖሊት ቢሮ የፈለገው ሰው ሥልጣን የሚይዘበት ሂደት ነበር።

ባለፈው ሁለት ዓመታት ህወሓት ከሥልጣን ከመወገዱ ጋር ተያይዞ ተቋማዊና መዋቅራዊ አድልዖው ይበልጥ ራቁቱን የቀረበትና ሕዝብም እኔን የሚወከለኝን መንግሥት በድምፄ እመርጣለሁ ማለቱ እየተጠናከረ የመጣበት ሁኔታ ተክስቷል። ከዚህ ጋር ተያይዞም እነዚህ የአድልዖ አገዛዞች በብዙዎች የተቃውሞ ዒላማ ሁነዋል፡፣ ይህ ብቻ አይደለም የጥቃቱ ዒላማ የሆኑ ማኅበረሰቦችን እንወክላለን የሚሉ የፖለቲካ ደርጅቶችም በነዚህ ማኅበረሰቦች ውስጥ የፖለቲካ ወድድር ለማድረግና በአሽናፊነት ለመውጣት ተዘጋጅተው ይታያሉ።

ይህ ሁሉ እስካሁን በሥልጣን ላይ የቆዩ የፖለቲካ ልሂቃኖችንና የአድሏአዊ ሥርዓት እንዲቀጥል የሚሹትን ሁሉ ያስደነገጠ ሆኗል።  በዚህ ሁኔታ በተለይም “መጤ” የተባሉትን የማኅበረሰብ ክፍሎችንለማሳቀቅና ለውጥ ፈላጊዎች ድምፃቸውን እንዳይሰጡ ከተቻለም በፍራቻ ከምርጫው በፊት አካባቢውን ለቀው  እንዲጣወጡ ጭፍጨፋን የጨመረ ታላቅ ተጽዕኖ እየተደረገ ነው።  ይህ ለውጡን ባለበት የማገት ፍላጎት በ“መጤው” ኅብረተሰብ ላይ በቤኒሻንጉል ፣ በጉራገፍራ፣ በኦሮምያ…ወዘተ ተደጋጋሚና እጅግ አስቃቂ የሆነ ጥቃት መካሄዱ ገደብ የሌለው ጥፋት ለመፈጸሙ አንድ ማሳያ ነው።

እየተጠቁ የሚገኙት ተራ ገበሬዎች ያለውን የአካባቢ ሕግ አክብረውና አንገታቸውን ደፍተው የሚኖሩ ናቸው፡ ”ተነጠሎ የጥቃቱ ዒላማ የሚያደርጋቸው ደግሞ ”መጤ“ ተብለው የተስየሙና በሕገ-መንግሥቱም በክልሉን ባለቤት መብት አንደሌላቸው የተፈረጁ መሆናቸው ነው።  ሟርት አይሁንብኝና ምርጫ እየተቃረበ  ሲሄድ የጥቃት አደጋውም ይጠናከራል።

የመፍትሄ  ሀሳቦች

የህግ የበላይነትን ከማስከበር ጎን ለጎን የሚከተሉት መሰረታዊ ጉዳዮች ሊተገበሩ ይገባል።

መሠረታዊ ሕገ-መንግሥታዊ ለውጥ ማካሂድ

ተቋማዊ ቀውሱ በዋናነት ከሕገ-መንግሥቱ የሚመነጭ በመሆኑ ሕገ-መንግሥት መሠረታዊ በሆነ መልክ በሕዝብ ተሳትፎ ሊሻሻል ውይም ሊቀየር ይገባዋል፣፡  ስፊ ለውጥ ለማካሂደ ጊዜ የሚወስድ ከሆነም አዋኪ የሆኑ የሕገ-መንግሥቱን ከፍሎች ለይቶ ባማውታት ማገደ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ክልልን ለተወሰኑ የማኅበረሰብ አባላት ብቻ ባለቤትነት የሚሰጥውን የሕገ-መንግሥት አካል መሰረዝና የሁሉም ዜጎች እኩል ባለቤትነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል፣ የፖለቲካ ስላጥንን በኮታ ለተውሰኑ የማሀበረስብ ክፍሎች ብቻ የደለደለውናና ሌሎችን ከጭዋት ውጭ ያደረገውን የክልሎች ሀህግጋት ማገድ ያስፍልጋለ።

የሀገሪቱ ፓርላማ ሁለቱም አካሎች በመጭው ጊዜያት ይህ የሀገ መንግስት መሰርታዊ ለውጥ እንደሚካሂደ ውሳኔ ከአሁኑ ሊይስተላልፍ ይገባል።

በየደረጃው የሚገኙ መንግሥታዊ ተቋማት ራሱን ማጽዳት በሁሉም ደረጃ ስብጥራቸው ሕዝቡን እንዲመስሉ ማድረግ፣

ከጥቃት የተላቀቀ ፖለቲካዊና እንቀሰቃሴ እውን እንዲሆን የአካባቢው መንግሥት ነዋሪውን እንዲመስል እንዲወክል፣ ለዝቀተኛ ቁጥር ላላቸው ደግሞ ውል፤ማቸውም የሚያረጋግጭ መሆን ይኖርበታል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዘር ይልቅ በዓላማ ዙሪያ እንዲደራጁ ማበረታታት ያስፈልጋል

ቅራኔን የሚያስራጭ ትርክት አብሮነትን በሚያበረታታ አስተምህሮት መተካት

በሕገ-መንግሥቱና በተቋማት ላይ ከሚደረገው መሠረታዊ ለውጥ ጎን ለጎን በሰው ልጆች እኩልነት፣ በአብሮነት፣ በሰብዓዊ መብት ረገጣ ምንነት ላይ ያተኮረ ትምህርት በሰፊው ሊካሄድ ይገባዋል። ይህ ደግሞ በተለይም በወጣቱ ትውልድ ላይ ያተኮረ ሆኖ የአካብሳቢውን ማኅበረሰቦች ባህላዊ ተቋማት ያማከለ ያሳተፈም ሊሆን ይገባዋል፡

የታሪክንና የዛሬን እውነታ የማሰታረቅ ጉዳዩችን በየፈርጃቸው ይዞ ሚዛናዊ የሆነ ፖሊሲ እንጂ የታሪክ እስረኛ የሆነ ፖሊሲን ተግባራዊ  ለማድረግ ከመሞከር መላቀቅ ያስፈልጋል።

በተለያዩ ማኅበረሰቦች ማካከል ግንኙነትን የሚያጠናክር፣ የተፈጠሩ ቅሬታዎችን የሚፈታ፣ እርቅን እውን የሚያደርግ አሠራርን ተግባራዊ ማድረግ፣

የብዙሀዊነትን አሴት የሚያከብርና አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ማኅበረሰቦችን  እንክብካቤ ተግባራዊ የሚያደርግ ፖሊሲ ማራመድ፣

በተለያዩ ሀገሮች ቁጥራቸው አንስተኛ የሆነ የኅብረተሰብ ክፍሎች የፖለቲካ ተሳትፎ እንዳይታፈን ተግባራዊ የሚደረጉ የተለያዩ አሠራሮቸ አሉ። ከነዚሀም ውስጥ በፓርላማው ውስጥ በቋሚነት የተወሰነ ወንበር መስጠት፣ የተወሰኑ ፖለቲካዊ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዩችን በተመልከተ ለየት ያለ የማማከር፣ ሀሳባቸውን የማዳመጥ ግዴታን በሕግ መደንገግ፣  ባሀላዊና ታሪካዊ እሴቶችን ለማዳበር ልዩ ትኩረት ማደረግና ልዩ ድጋፍ መስጠት…ወዘተ የመሳስሉትን ፖሊሲዎች ተግባራዊ ማደረግ ጥቂቶቹ ናቸው።

በሀገራችን ሁኔታ በሀወሓት ቀያሽነት ተግባራዊ የተደረገው ሕገ-መንግሥታዊ አካሄድ ከዚሀ ጋር የተጋጭና የተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍልን ለይቶ በሀገሩ ውስጥ ባይተዋር የሚያደረግ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ዜግነትንም ተግባርዊ የሚያደርግ የቀጣይ ግጭት መርዝን የዘራ ነው።

ይህ ዕዳ ሁሉንም ከማጠፋት ውጭ ማንንም በቋሚነት ተጠቃሚ አያደርግም፡ ረጅም ጊዜ የሚሹ ተግባሮችንም ለይቶ በማውጣት ሙሉ መውጥ እውን እስኪሆን መደርግ የሚጋባውን መሰረታዊ መሻሻያ በአስቸኳይ ተግባራዊ ማድረግ ጊዜው ይጠይቃል።

ማጠቃለያ

የሀገራችን ችግሮች ምንጩ የጎሳ ፖለቲካን መሠረት ያደረገው ሕገ-መንግሥት ይቀየር ስንል የሽንፈት ለቅሶ ሳይሆን መፃዒውን ጊዜ እኩልነትና አብሮነት የማዳበር ራዕይና ፍኖተ-ካርታ ስለሆነ ነው።

መዋቅራዊና ተቋማዊ መሠረት ያለው አድልዖ የወለደውና እየተንከባከበው የሚገኛውን ተቋማዊ ጥቃት ለማስወገድ መሠረቱ የሆነውን ሕገ-መንግሥትና እርሱንም ለማሰፈጽም የተዋቀሩ ተቋማትን መሠረታዊ በሆነ መልክ መቀየር የግድ ይላል።

እኩልነት ኅብረተሰብን ስላማዊ፣ ያደርጋል፣ ለልማትም ምቹ ሁኒታ ይፈጥራል። ሁሉም የአካባቢው ነዋሪዎች ከጭንቀት ተላቅው የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው ያደርጋል።  እኩልነት የፖለቲካ ሊሂቃን ለሕዝብ ፍላጎት እንዲገዙ ያደርጋል። እኩልነት ማኅበራዊ ትስስርን፣ መከባበርና መዋሀድን ያጠናክራል። በዚህ ደግሞ ተጠቃሚው ሁሉም ነው።

ይህ እስከሚሆን ግን መለኩን እየቀያየረ በሚከሰተው የሀገራችንንና የሀዝባችን መከራ መራዘመ እርግጠኛ መሆን እንችላለን ።

5 Comments

 1. ጥሩ ጅምር ነው፤፤ ሃሳቦችህም መጥፎ አይደሉም፡፤ አየህ አንተ የጻፍከው በቃላት ቃናው (tone) ለውይይት የሚጋብዝ መሆኑ ነው እንጂ በይዘቱ እኮ ሰርጸ ደስታ et al ከሚፎክሩበት በጉልበትና በማሽማቀቅ ስትራተጂ ለማስፈጸም ከሚወተዉቱበት አሰልቺ ጽሁፍ አይለይም፤፤ በፓርቲ ደረጃ ደግሞ ኢዜማ፤ አብን፤ ባልደራስ፤ አቋም ይኅው ነው፡፤ It is not only what you say, it is also how you say it!
  በቅድሚያ ክልል በምንም ይደራጅ ሰውን መጨፍጨፍ በምንም መልኩ ተቀባይነት የለውም፤፤ መቆም አለበት፤
  ምናልባት አጻጻፍህ መፍትሄውን ቀድመህ አስበህ ለሱ ማጠናከሪያ የሚሆኑ ማስረጃዎችን ብቻ ነው በመጠቀም አንዳይመስል ትርታሬ አለኝ፤፤ the end justifies the means!
  ለማንኛውም ጥያቄዎች፡
  1፣ በ1977 በመተክል እና በጋምቤላ ደርግ ስላስፈራቸው ሰዎች ምን ያህል ታውቃለህ? ምናልባት ካላወቅህ መጠለያ ለመስራት ከዩኒቨርሲት በአንድ ክረምት የዘመቱት አሁን ላይ እድሜአቸው በህምሳዎቹ አጋማሽ ነው! አንተ የዚያ ትውልድ ካልሆንክ የሚያውቅ ቅርብ አንድ ሰው አታጣም፤ ደፈር በል ጠይቅ፤
  2። ሟቾች ከአማራና አገው ብቻ ናችው ወይ? (አማራ=ክርስቲያን የሚለውንም አትርሳ)
  3፤ አንተ በምትለው የመፍትሄ ሃሳብ አልስማም፤ ልዩነት አለኝ የሚል ህዝብ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ ካለ ልዩነቱ እንዴት ይስተናገድ?
  4፤ ግድያውን ማነው የሚፈጽመው/የሚያስፈጽመው በሚለው ላይ ስም አልጠራህም? ጨዋነትህ ይደነቃል፡፤ ግን በጣም አሰፈላጊ ነው፤፤ እንደ ቲቸር መስከረም እና ደሳለኝ ጫኔ “ግድያውን አቅዶና አቀነባብሮ ዋናው አስፈጻሚ አቢይ ነው፤ ሥልጣን ይልቀቅ” የሚለውን እያስብክ ከሆነ የጻፍከው፤ – it becomes none starter! በሌላ አነጋገር
  5። የመፍትሄው አፈጻጸም እንዴት እንደሚሆንና ማን እንደሚያስፈጽመው ትንሽ ፈታ አድርገህ ብታስረዳን? እንግዲህ ስታስብ አዲሳባን፤ ባህርዳርን እና ጎንደርን ብቻ እያሰብክ መሆን የለበትም፤፤ ጅግጅጋ፤ ሃዋሳ፤ መቀሌ፤ ስመራ፤ ለቅምት፤ ጨንቻ፤ ወራቤ….እያሰብክ ቢሆን ደግሞ የበለጠ ጥሩ ይሆናል፤፤
  አመስግናለሁ

  • ሰላምታየ ይድረስዎት
   ጊዜ ወስደው ማንበብ ብቻ ሳይሆን ለውይይት የሚጋብዝ አስተያየትና ጥያቄዎችም ሰለሰነዘሩ አመሰግናለሁ። ሃሳቤንም እንደሚከተለው አካፍላለሁ።

   ጥቃቱ ይደረስባቸው አማራና አገው ብቻ አይደለም በዋናነት ግን ያተኮረው በነዚህ ማሀበረስቦች ላይ እንደሆነ መረጃው ሰፊ ነው፣ ይፋዊ የሆነውን የስባዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት ይህንኑ ያረጋግጣል

   3፤ አንተ በምትለው የመፍትሄ ሃሳብ አልስማም፤ ልዩነት አለኝ የሚል ህዝብ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ ካለ ልዩነቱ እንዴት ይስተናገድ?\\

   በኔ አስተያየት የተለየ የመፍትሄ ሀሳብን በተመለክት ዘርፈ ብዙ የአካሄድ ስልት ይኖራል። የመጀመሪያው ሀገ ምንግስቱን በተመለከት ህጸጽንና መፍትሄውን በሀግ ምሁራን በፖለቲካ መሪዎች ወ ዘት ውይይትና ጥናት ለይቶ መቅረብ ተገቢ ይሆናል፡
   ይህ ርጅም ጊዜ ሊወስድ የሚችል የሀገምንግስት መቀየር ወይም መሰረታዊ ማሽሻል እስኪጠናቀቅ መንግስት ሊወስዳቸው የሚቸሉ የአጭር ጊዜ እረምጃዎችም ይኖራሉ፣ ለመሳሌም ለ28 አምታተ ተቋማዊ አድልኦንና ከፋፋይ ትርክትን ለማስቆም አስቸኳይ የህግ ማሻሻያ እርምጃ መውስድ ይችላል፡ ህወሀትንና የትግራይን ክልላዊ መንግስት በፓርላማ አስጸድቆ ማፍረስ እንደተቻለው፣ አድላኦን እና የግጭት መሰረት የሆኑትንም እንዲሁ ማድረግ ይቻላል ብየ አስባለሁ።

   ሀገምንግስቱን መሰረታዊ በሆነ ሁኔታ ለማሻሻልም ይሁን ለመቀየር ህዝብ ድምጽ ሊኖረውም ይገባል
   ከነዚህ ጋር ተያይዞም ብሄራዊ መግባባትን ትርጉም ባለው መልክ ተግባራዊ ማደርግ ለዚህም መንግስት የማያወላውል አቋም መውሰዱ አጅግ አስፈላጊ ይሆናል፡
   ከ2 አመት በፌት ለዚሁ ተግባር የተመሰረተውን ኮሚሽን ሁኒታ እንደገና በአግባቡ መገምገምና ድክመትና ጥንካሬውን ለይቶ ማወቅ ድክመቱን ለማሻሻል የሚያስፈልጉ እርምጃውችን ማከናወንና ትርጉም ያለው መሰረታዊ የብሄራዊ እርቅ ሰራን ተግባራዊ ማድረግ እጅግ ለተወሳሰበው ችግራችን አንድ ትልቅ እርምጃ ይሆናል ብየ አስባለሁ። በዚህ ኧኳያ ሊከናወኑ የሚገባቸው መስረታዊ እርምጃዎች አሉ። ይህ ሲሆን ለወንጅለኞችም በስር አቱ ወስጥ መልሰው መላልሰው ጥፋት እንዳይፈጽሙ ታላቅ አስተዋጻኦ ይኖረዋል። ይህ ግን የመንግስትን ቁርጠኛነትና ወጣቭ የሉ ክፍሎችን በሰፊው ማማከር ይጠይቃል።
   እርስዎም ሌሎችም ይጭምሩበት

   የመፍትሄው አፈጻጸም እንዴት እንደሚሆንና ማን እንደሚያስፈጽመው ትንሽ ፈታ አድርገህ ብታስረዳን? እንግዲህ ስታስብ አዲሳባን፤ ባህርዳርን እና ጎንደርን ብቻ እያሰብክ መሆን የለበትም፤፤ ጅግጅጋ፤ ሃዋሳ፤ መቀሌ፤ ስመራ፤ ለቅምት፤ ጨንቻ፤ ወራቤ….እያሰብክ ቢሆን ደግሞ የበለጠ ጥሩ ይሆናል፤፤
   ከላይ ባሉት አመላካከት አልስማማም የተባለውን የሚያሳይ ተጨባጭ መረጃ አላየሁም እና፡፡ ነገሩን ሁሉ ስልጣን በማስለቀቅ አንጻር ማየት አሁን ካለንበት አረንቋ ለመውጣት የሚያግዝ አይመስለኝም፤ ስልጣንም የሚያከራከረው ሀገርና ህዝብ ሲኖሩ ነው፡፡ ዶክተር አብይም ሆኑ ሌላ ያነሳዃቸውን መዋቅራዊ ችግሮች መፍታት ካልቻሉ ችግሩ እየጎላና እያደግ እንጂ እየቀነሰ የሚሀድ አይሆንም።
   ይህን ካልኩ በኳላ ግን መንግስት ይህን ችግር ለመፍታት ግንባር ቀደምና የማያወላውል ተዋናኝ ሊሆን ይገባዋለ፡ ያነሳዃቸው ማዋቅራዊ ችግሮች የመንግስት ፍጡራን ናቸው በአስቸኳይ ለመቀየርም መፍተሄው በመንግስት እጅ ውስጥ ነው። ይህን ስር የሰደደ ችግር በአዝጋሚ ጥገና ማሻሻል እጅግ አስቸጋሪ ነው። ለስታተስኮው መልሶ ማንሰራራትም ትልቅ እድል ይስጣል። ይህን ፈጠን ባሎ መሰረታዊ እርምጃዎች (ዲስራፐቲቭ አክሽንስ) በመውስድ መቀየር ያሻል፡
   ይህ በቂ ነው ለማለት አይደልም ስፊ ጽሁፍና ውይይት በዚህ ቦታ ማቅረብ ስለሚከብድ ነው አጠር ያሉ ነጥቦችን የማነሳው

   እኔም አመስግናለሁ

   • ጊዜ ወስደህ ቁምነገር ብለህ ለጥያቄዎቼ መልስ ሰልሰጠህ እኔም አመሰግናለሁ፤ ከፍትፍቱ ፊቱ ይባላል እኮ!
    የተመቸኝ
    “ሀገምንግስቱን መሰረታዊ በሆነ ሁኔታ ለማሻሻልም ይሁን ለመቀየር ህዝብ ድምጽ ሊኖረውም ይገባል
    ከነዚህ ጋር ተያይዞም ብሄራዊ መግባባትን ትርጉም ባለው መልክ ተግባራዊ ማደርግ ለዚህም መንግስት የማያወላውል አቋም መውሰዱ አጅግ አስፈላጊ ይሆናል፡”
    ጀምሮታል [ስለ ሺትዮፕያዊነት በመንግስት ሚዲያ] ግን በቁርጠኘት መቀጠል አለበት፤ የግድ ነው፤ ካውንተር ቅስቀሳዎች ስላሉ ትንሽ በተፈለገው ፍጥነት እና ጥንካሬ ማስከድ አልተቻለም፤

    በጣም የተመችኝ፡
    “ነገሩን ሁሉ ስልጣን በማስለቀቅ አንጻር ማየት አሁን ካለንበት አረንቋ ለመውጣት የሚያግዝ አይመስለኝም፤ ስልጣንም የሚያከራከረው ሀገርና ህዝብ ሲኖሩ ነው፡፡”
    ይህንን ካልክ ዶ/ር አቢይን በትንሽ አቅሜ የምደግፈው [የምከላከለው ብል ይቀላል] በግል አውቄው ወይም ጥቅም ደልሎኝ እንዳልሆነ ትረዳኛለህ ብዬ አስባለሁ፤፤ እንዳልከው ፎረሙ አይመችም እንጂ በእርግጠኝነት ለመስማማት ቅርብ እንደሆንን ግን ተረድቻለሁ፤፤ ህሳብህን በግለሰብ ጭውውትም ቢሆን አራምደው፤ አስፋፋው፤፤ ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ከመጡ ሰዎች ጋር ተወያይበት፤ አንድ ሰው ማሳመንም እኮ ትልቅ ነገር ነው፤ እየተባዛ ይሄዳል፤፤
    ሁሉም ነገር ክኢትዮጲያ በታች ነው፤ እናልፈዋለን፤ ኢትዮጵያም ትቀጥላለች፤
    ከወንድማዊ ስላምታ ጋር!

    • ከድር ሰተቴ, ከተወዳጁ ስምዎት ጋር ሰላም ይሁኑ፡
     ሰለምክርና ማበረታቻው አመስግናለሁ
     ብርታቱን ይስጥዎት ፈታኝ ጊዜ ነው

 2. ክብር ለመከላከያ ሰራዊት አንዱን ባንዳና ጁንታ ሲገላገል ወደ ሌላ ኦፕሬሽን ቤኒሻንጉል፣ ሱዳን፣ ወለጋ እንዲህ እንዲህ ብሎ ከጠራ በኃላ ኢትዮጵያ እንደአገር በሰላም የምትቀጥልበት ጊዜ በአምላክ ፈቃድ መምጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ አለአግባብ በግፍ ለተገደሉት ምስኪን ህዝቦች ስትሉ ለምትሰው የሰራዊቱ አባላት ክብር ለናንተ ይገባል፡፡ ዘግይቶ ቢሆንም አሁን ቤኒሻንጉል፣ መተከል፣ ወለጋ ኦነግ ሸኔ ላይ እየተወሰደ ያለ እርምጃ የህዝብን የሁል ጊዜ እሮሮ እና እንባ የሚመልስ ነው፡፡ አሁንም በሚደረገው ኦፒሬሽን የሰንሰለቱ እርዝራዞችን በደንብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከያሉበት ማደን ያስፈልጋል፡፡ ይህን ጊዜ ነው ደማቸው አለአግባብ ለፈሰሰው ካሳ የምትከፍሉት፡፡

  ጀግኖች የኢትዮጵያ ልጆች በርቱ በምታደርጉት ኦፕሬሽን ህዝብ ከእናንተ ጋር ነው፡፡ አምላክም ይረዳችኃል፡፡
  ምንም እንኩዋን የአገር ውስጥ ባንዳዎች እና የቅርብ ጎረቤት ጠላት አገሮች የፈለጉንት ቢመኙም በዚህ ትግላችሁ አገሪቷ ሰላም የምትሆንበት ቀን ሩቅ አይሆንም በውጤቱም የሁሉም ልጆች ሳይሣቀቁ የሚኖሩባት፣ አዛውንቶች ሰላም አግኝተው ምረቃት የሚሰጡበት ሌላውም በዘር፣ ሃይሞኖት፣ ብሔር እንዲሁም አድርባይነትን እና ወገናዊነትን ተላቆ ሰላማዊ አገር እንደሚፈጠር ምኞቱ ነው፡፡

  ክብር ለጀግናው ሰራዊት!!

  ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.