ከህሊና ቢሱ ፖለቲካችን መቼ ነው የምንፋታው ? – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

abiy 1

ጥቂት ሆዳ አደር እና ከራስ በላይ ነፋስ ባዮቹ  የኢትዮጵያ ምሁራንና ሊሂቃን ፣ የጎሣ ፖለቲካ አሳብዷቸዋል። የጎሣና የቋንቋ ፖለቲካ በህዝብ ሥም ለጥቂት ጥቅመኛ ቡድኖች የሚያሳብድ የደም ገንዘብ አቅራቢ ነው። እያንዳንዱ ሰው የሆነ የጎሣ ቡድን፣ ሰውነትን አሥረሥቶ ቆዳን በማዋደድ አምሳያውን ሰው እንደሰው እና እንደዜጋ ያልቆጠረው፣ ህሊናውን በሆድ በመቀየር በመቀወሱ ነው።

ይህ ህሊናውን ሽጦ የበላ፣ ሞራለ ቢስ ሰው ህዝብ፣ ህዝብ እያለ ” በሰፊው ህዝብ ሥም ”  እንደትናንቱ ይሸቅጣል።በህዝብ ሥም መሸቀጥ የተጀመረው በማርኪሲስቱ ደርግ ዘመነ መንግሥት ነው። የማርኪሲዝም ሥርዓት ፈጣሪን ያሥካደ ሥርዓት በመሆኑ ህሊናን ቢያቃውሥ አይገርምም።  በወቅቱ የነበረው ፖለቲካ በደንብ ባልገባን የማርክስ ቲዎሪ ያበደ ነበርና፡፡ (…)

በህዝብ እየነገዱ ሥልጣንን ለማራዘመ የሚደረግ ሸፍጥ  እና የፍየል ወጠጤ ፉከራና ፍትህን የረገጠ ነፃ እርምጃ ደርግ የሚከተለው   የፖለቲካ ሥርአት የበደ እንደነበር የሚያሳይ ነበር፡፡ ዛሬም ” ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ” እያለ ያለፍርድ በፈጣጣ የሰው ህይወት እንደሚገድለው ደርግ ፣ አንድ አንድ  ፖለቲከኞችም በህዝብ ስም አጥፊ የሆነውን ፖለቲካ አልሚ እንደሆነ በመስበክ” ያበደው የዘር ፖለቲካ ” እንዲቀጥል ይሻሉ፡፡ይህ ፍፁም ኋላ ቀር የሆነ ለዘመኑ የማይመጥን የድሮ የባርያ አሳደሪዎች አግላይ የዘር  ሥርአት ዛሬ በዘመናዊው የፊደራል ሥርዓት ካልተቀየረ በአገር ላይ የሚየስከትለው አደጋ ፣ አሁን ካጋጠመን  አደጋ እጅግ የከፋ ይሆናል፡፡

ዛሬ፤ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ሲባል ሳይሆን “ለብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ፣ ለጎሳችን  እና ለቋንቋችን ጥቅም ሥንል ማንኛውንም መስዋትነት እንከፍላለን  እየተባለ አደጋ አምጪ ስብከት እየተሰበከ፤ ፖለቲካዊ እብደቱ መፋፋሙን እያስተዋልን ነው፡፡   “ቅንጦት አሥገኚው የጎሣ ፖለቲካ ወይም ሞት ! ” በማለትም መፈክር የሚያሰማው እብድ  የፊሥ ቡኩ የዘር አርበኛ ና ሥልጣን እንጂ የሰው ልጅ እኩልነት የማይታየው ፣ በባለአምስት ኮኮብ ላይ  እበላባይ ተምነሽናሽ ፖለቲከኛ በእብደቱ እንደገፋበት እያስተዋልን ነው።

ህሊና ቢሱ ፖለቲከኛ ሰውን በቋንቋው በመከፋፈል፣ በአንድ አገር ውሥጥ ያሉ ዜጎችን ” ይሄ መሬት የዚህ ጎሣ ነው፡፡ያ ደግሞ የአንተ ዘር ብቻ ነው፡፡ ”  እያሥባለ ሰውን እና ዜጋን “ፈርጆ” በባላንጣነት እንዲተያይ ማድረጉን እነደቀጠለበት እያስተዋልን ነው፡፡

ይህ በዘር እና በቋንቋ ላይ የተመሠረተ ፊደራሊዝም ከሰው ልጅ የዛሬ አኗኗር ጋር ፍፁም የተራራቀ ነው፡፡የመጣንበት ከፋፋይ የተገንጣይ አስተሳሰብን አራማጅ ስርዓት ለኢትዮጵያ ጠላቶች እንጂ ለብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ የሚጠቅም ከቶም አያደለም ፡፡  የዘር እና የቋንቋ ፖለቲካዊ አሥተዳደር ፣ኢትዮጵያዊ ዜግነትን ፈፅሞ የካደ ነው፡፡በተከለለት ክልል ሳቢያ ራሱን እንደ አንድ ነፃ አገር የሚቆጥረው ጥቂት ድሎተኛ ህሊና ቢሥ የክልል እና የፊደራል ሹም ና ፓርቲና ደርጅት መስርቻለሁ ባይ ፣በህዝብ ስም የሚነግድ ሁላ፣ ያለሀፍረት በአደባባይ ውህዱን ኢትዮጵያዊ እንደዜጋ እንደማይቆጥር እየተናገረ ነው።የሚያሳዝነው ግን ራሱ ውህድ መሆኑንን ያለመገንዘቡ ነው፡፡ዘርህን ቁጠር ቢሎት እስኪ እስከ አስር ቤት በትክክል ለመጥራት ቀርቶ እስከ ሰባት የሚጠራ የትኛው ነው ???

እርግጥ ነው ይህ ዘር ቆጠራ ከፈጣሪ ጋር የሚያጣላ መሆኑን እነዚህ እብድ ፖለቲከኞች አይገነዘቡም፡፡ ኃይማኖተኛ ነኝ ቢሉም እንደሚሞቱ እንኳ የዘነጉ ናቸው፡፡ጭፍን  ደጋፊያቸውም በየእምነቱ ሲታይ ኃይማኖተኛ ይመስላል እንጂ ፈፅሞ በፈጣሪ እንደማያምን የጥላቻ ተግባሩ ያሳብቅበታል፡፡ሁሌም ለሥጋው ጥቅም ብቻ ነው ጥላቻን ሰንቆ ሲባዝን የሚታየው፡፡…በተግባር የሚታይ እምነት ከቶም የለውም፡፡ፈፅሞ እምነት እንደሌለው ግብሩ ይመሰክራል፡፡እምነት ቢኖረውማ ” ኢትዮጵያ አገሬ ናት። ” ብሎ፣ከአካባቢው ና ከክልሉ ህዝብ ጋር አብሮት የሚኖረውን ዜጋ በህሊና ቢስነት  ” በነፍሥህ ጭምር የማዘው እኔ ነኝ።”  በማለት፣ ሰብአዊ፣ ዴሞክራሲያዊ ና ህጋዊ መብቱን አየነፍገውም ነበር። የዜግነት መብቱንም በመነፈግ ፣የህግ ጥበቃ እንኳ እንዳያገኝ በማድረግ በአሰቃቂ ሁኔታ ፣ከውሻ የባሰ ሞት እንዲሞት ከነፍሰ ገዳዮች ጋራ አይመሳጠርበትም ነበር።

ዛሬ በምእራብ ወለጋም ሆነ በቤንሻጉል (በመተከል) እየተፈፀመ ያለው በሰው ዘር ላይ የሚፈፀም አረመኔያዊ ግፍ፣ ከየአካባቢው የክልሉ የመሥተዳድርና የፀጥታ አካላት ጋር በመመሳጠር የሚፈፀም መሆኑ ታውቋል።

የየአካባቢው ነዋሪ  ህዝብ በዚህ ግፍ እጁ የለበትም።ምናልባትም ይህንን ሴጣናዊ የጭካኔ ድርጊት የሚፈፅሙት ፣ መሐል አገር ድረሥ ህቡ መዋቅር አበጅተው ለኢትዮጵያ  ውድቀት ሌትና ቀን የሚሰሩ የታሪካዊ  እና የጂኦ ፖለቲካዊ ጠላቶቻችን ቅጥረኞች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

እነዲህ አይነት በስውር የተደገሰለን የጥፋት ድግስ እንዳለ ከተገነዘብን ቆም ብለን ንዋይ ያሳበዳቸውን ጉያችን ውስጥ ያሉ የራሳችን የምንላቸውን ሰዎች በቅጡ መመርመር ይገባናል፡፡(ከወዳጅ ጠላት አድነኝ ብሎ መጸለይን ወቅቱ ይጠይቃል፤፤) ይህንን ስናደርግ ብቻ ነው ሰንኮፉን ለመንቀል እና በአገር አስተማማኝ ሰላም ማስፈን የምንችለው፡፡እነዚህ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች በድንበር በኩልም በሥውር የሎጀሥቲክ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚችሉ የታወቀ ነውና ጓዳችንን እስቲ እንፈትሽ። ምናልበትም እኮ አገር አተራማሹ ኃይል ከህሊና ቢሶቹ  የየአውራጃው፤ወረዳውና ቀበሌው  መሥተዳድሮች ጋር በመመሳጠር  በየከተማው በመመሽገ በሌሊትና በአሳቻ ሰዓት፣ አዘናግቶ ሰብአዊ ፍጡራንን ጨፍጭፎ ወደተዘጋጀለት መሸሸጊያ ይገባ ይሆናል።ማንያውቃል ???

ልብ በሉ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ዜጎች፣ በህዝብ ደረጃ ሆ ብለው ሌላውን ዘር ለማጥፋት አልተነሱም። በህዝብ ላይ የተነሱት ፣ወያኔ ያፈራልን ፣በብር የተገዙ ፣የጊዜው የቋንቋና የዘር ፖለቲካ አራማጆች ናቸው፡፡እነዚህ ሰዎች ከግብር አባታቸው የተማሩት ስግብግብነትን ብቻ ነውና ለሰው ዘር አንዳችም ርህራሄ የላቸውም፡፡ሆኖም ግን ህዝብን እንደ ሰብአዊ ጋሻ በመጠቀም ተንኮላቸውን መደበቅ ይችሉበታል፡፡

ትላንትም ሆነ ዛሬ ፣በከተማም ሆነ በገጠር የሚኖረው ህዝብ ፣ኢትዮጵያዊነቱን እና ኢትዮጵያዊነታቸውን ክዶ በሌሎች ኢትዮጵያውያን ወድሞቹ እና እህቶቹ ላይ ቃታ አልሳበም። ካራ አልመዘዘም። ካራ የመዘዘው ተከፋዩ የዘረኞች አሽከር ወይም ባርያ ነው። ይህ ታዛዥ ሎሌ ትላንት “የንጉሥን ግብር በግዴታ እንጂ በውዴታ አትበላም ፡፡ “እያለ እየገረፈ የሚያሥበላ ነበር። በደርግም ተኩሶ ከገደለ በኋላ “ቁም” የሚል እንደነበረ አንዘነጋም። በወያኔም የጤነኛ ሰውን እግር የሚያሥቆርጥ ግብረ ሰዶማዊነትን በእሥር ቤት ያሥፋፋ ሞት የሚገባው የሴጣን ልጅ ነበር። ዛሬም በኋላ ቀር የሥለት መሣሪያዎች በካራ ና ቀሥት እያሳደደ የሚገድልው የዚህ የሴጣን ልጅ ሽንት ነው።

ይህ እውነት ከታወቀ ዘንዳ የኢፊድሪ መንግሥት ከምርጫው በፊት፣ የአጭር ጊዜ እቅድ በማውጣት የማያዳግም እርምጃ  መውሰድ በጣም አስፈላጊ ይመስለኛል። የህግ ማሥከበሩ ቆራጥ እርምጃ እንደ ተጠበቀ ሆኖ የነዚህ ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች የፋይናሥ ምንጭ መታወቅ ይኖርበታል።ይህንንም ለማወቅ የኢትዮጵያ ደህንነት ወይም የኢተለጀንሥ ተቋም፣ ከምንጋዜውም በላይ በቤንሻጉል እና በኦሮሚያ ክልል፣ጊዜ ሳያባክን በጥልቀትና በስፋት መቀሳቀሥ ይኖርበታል።

ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ዛሬ በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ በተቀናጀ መልኩ የተደቀነባትን ሴራ ፣ በጥበብ  ፣ በዘዴ ና በትግስት እንዲሁም በቋራጥ እርምጃ በመበጣጠስ ይህንን የፈተና ጊዜ እንድታልፍ አገር ወዳዶች ሁሉ በጋራ ሊቆሙ ይገባቸዋል፡፡በተለይም የግብጾችን የሸር መንገድ ቀድሞ በማወቅ እኩይ ዓላማቸው እንዳይሳካ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

እንደሚታወቀው ፣ ግብፅ ከልማታችን የምንደናቀፈው በጦርነት እንደሆነ አሳምራ ታውቃለች እና ትላንት ደጋግማ እንደወረረችን እና ከልማት እንደጎተተችን ሁሉ ዛሬም ከሱዳን ጋር በድንበር ምክንያት እንድንፋለም ትፈልጋለች። ይህንን የግብፅ ዓላማ ማክሸፍ ይጠበቅብናል።በኢትዮጵያ ውሥጥ እድገትና ብልፅግና እንዳይኖር ትላንት በመሳፍንቶች የእርሥ በእርሥ ጦርነት ግብፅ በሚገርም ፣ማንም ሌላ አገር በማያስበው መልኩ ኢትዮጵያን ዜጋዋን ኢትዮጵያዊ ንጉሥ በማድረግ  ለመቆጣጠር የዛሬ 388 ዓመት በፊት አቅዳ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል  ።እጠቅሳለሁ።

 

   1622__1625 በወቅቱ የአገሪቱን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ የሃይማኖት ፣ማህበራዊ ቀውሥና ሽብር በመየት፣ አንድ ግብፃዊ ግለሰብ በአምባ የልዑላን ግዞት የነበርሁ የአፄ ሠረፀ ድንግል ልጅ ነኝ  በማለት በሻዋ ተነሳ። እሱም በመነኮሳት ልብስ ተሸፍኖ በቀረበ ጊዜ ሰዎች የፊቱን ቅላት ባዩ ጊዜ  እውነትም በአምባው ግዞት ከሚኖሩት ልዑላን ነው።  ብለው ተቀበሉት። የኢትዮጵያ ሰዎች መልከ ቀና ባዩ ጊዜ በልማዳቸው የእሥራኤል ልጅ (ልዑል) ይመሥላል ይላሉና ፤እሱም ይህን ሰምቶ  አዎን የንጉሥ ሠርፀ ድንግል ልጅ ነኝ አላቸው።ተክለ ሥላሤ የግቦፁን ወንበዴ ወልደቅብርያል በማለት በአባቱ ሥም ብቻ ይጠራዋል።

    ከከረዩ ጎሣ ሀያ ሉባዎች ማለትም የጎሳ መሪዎች ወንበዴውን የቅብርያል ልጅ ወደ ጦርነት የሚመራን የንጉሥ ልጅ ነው  በማለት ንጉሣቸው አደረጉት። የዙፋን ሥሙንም  ቴዎድሮስ ፀሐይ አሉት። አፍሮ አይገባ የተባለ የጨዋ ጦርም ንጉሥ ቴዎድሮስ ፀሐይን  ተከተለው ፡፡ከአማራ በታች የመንዝ የግሼ፣ የመርሐ ቤቴ ፣የግድምና የተጉለት ህዞቦችና ጭፍሮች ከአካባቢው የእሮሞ የተለያዩ ጎሳዎች ጋር የቅብርያልን ልጅ ንጉሥ ቴዎድሮስ ፀሐይን በአፄ ሱስንዮስ መንግሥትና ጦር ላይ (ተቃዋሚ በማድረግ ) እንደንጉሣቸው መከተልና መታዘዝ ጀመሩ።ንጉሥ ቴዎድሮስ ፀሐይ 1622 እሥከ 1625 ድረሥ ለሦስት ዓመታት የየአካባቢውን የኦሮሞና የአማራ ሰዎች አሥተባብሮ በሸዋ የራሱን መንግሥት መሠረተ።

   1622 እሠከ 1625 ድረሥ በሦሥት ዓመታት ውሥጥ በራስ ሥዕለ ክርሥቶሥ፣ በራስ የማነ ክርስቶስ ፣በደጃዝማች ሠርፀ ክርስቶስ ዘማርያም፣ በደጃዝማች ቦኩ አዝማችነት የዓፄ ሱስንዮስ ወታደሮች በመንዝ ፣በግሼ በመርሐ ቤቴ፣ በገድም በተጉለት ፣በየፋት ፣በሸዋና በአምባሰል በንጉሥ ፀሐይ ቴዎድሮስ ተከታዮች ላይ ከሰበት በላይ ዘመቻዎችን አካሄዱ። በመጨረሻ 1625 ራስ ስዕለ ክርስቶስ ወምበዴውን በቅጥረኛ ገዳይ እጅ በፈጠጋር አስገደለው።

(የኢትዮጵያ ረጅም የህዝብና የመንግሥት ታሪክ አንደኛ መፅሐፍ ዶ/ር ላጵሶ ጌ. ድሌቦ ገፅ 229)

ይህ እውነት የሚያመለክተን ፣ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያዊያንን ለመከፋፋል፣ ግብፆች ምን ያህል ርቀት መሄድ እንደቻሉ ነው።  ግብፆች በትግራይ በነፃ ድንበር ተሻጋሪ ባለሀብቶቻቸው ሥም ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ለምን አፈሰሱ ? ዛሬሥ በሌሎቹ የኢትዮጵያ ክልሎች በእውነት የንግድ ሥራ ብቻ ነው ወይ የሚሠሩት ? …በበኩሌ ግብፆች እንኳን የአፍሪካን ህብረትን ሊፈልጉ ይቅርና የሱዳን ፣የግብፅና የኢትዮጵያ ህዝቦች ተደጋግፈው ባለፀጋ እንዲሆኑ አይሹም። ሱዳንም ሆነች ኢትዮጵያ እንዲበለፅጉ ከቶም አይፈልጉም። ይህ የለ መሻታቸው ግን በ16 ኛው ክ/ዘመን እንጂ በዚህ የሰው አእምሮ እጅግ በተራቀቀበት በ21 ኛው ክ/ዘ ተገባራዊ ሊሆን ከቶም እንደማይችል ቢገነዘቡ መልካም ነው። የሱዳን እና የኢትዮጵያ ህዝቦችም በግብፅ ተንኮለኛ መሪዎች ሴራ አይጠፋፉም፡፡ ዛሬ ጦርነት በዘመናዊ ጦር መሣሪያ የተደገፈ በመሆኑ ግብፆችም የጦርነት አማራጭ ዋጋ እንደሚስከፍላቸው ከወዲሁ መገንዘቡ የሚበጃቸው ይመስለኛል፡፡ ሚዳ ሲቃጠል ተራራ መሳቅ የሚችለው እሳቱ እስከሚደርስበት ጊዜ ድረስ ብቻ ነውና?

ኢትዮጵያውያንም ቆሞ ቀር ከሆነው የግብፅ መንግሥት እኩይ ፍላጎት አንፃር የአንድነት ወይም የዜግነት ፖለቲካ በአገራችን አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ በብርቱ በመታገል ይህንን ህሊና ቢስ የሚያደርግ የዘርና የቋንቋ ፖለቲካ በዘመነኛው በዜጎች ግለሰባዊ መብት፤በፍትህ ፣በኩልነትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መከበር ላይ ባተኮረ  ፌደራሊዝም መቀየር ይኖርብናል። የዘር ፖለቲካ እንደማያዋጣ ባለፉት 27 ዓመታት ታይቷል።የዘር ፖለቲካ የሚያዋጣው፣ ለአገርና ለዜጎች ግድ ለማይሰጣቸው እብዶች ብቻ ነው።ህሊና ቢሶቹ  ደግሞ የአገርን ሀብት እየሰረቁ እውጪ አገር በማሸሽ ፣ወደ ፊት የልጅ፣ ልጆቻቸው ተንቀባረው እንዲኖሩ የሚያልሙ እንደሆኑ በወያኔ ቁንጮ አባላት ተረገግጦል፡፡ እነሱ ጠግበው ቆመንለታል የሚሉት ጠኔ የያዘው ደሃ  የሚያገሳ የሚመስላቸው  ህሊና ቢስ  ከንቱዎች ሁሉ በስልጣን ወንበር ላይ መቀመጥ የለባቸውም፡፡ አገርና ህዝብ ከፍ እንዲሉ ከተፈለገ  ከግል ጥቅማቸው ይልቅ የሀገርን እና የህዝብን ጥቅም የሚያስቀድሙ ወደ ከፍተኛው አመራር መምጠት አለባቸው፡፡ይህ የሚሆነው ደግሞ ፣በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የዘርና የቋንቋን ፖለቲካ የሙጥኝ ያሉት ሲፋቱን ብቻ ነው፡፡

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.