በህዝባችን አልቂት ጉዳይ የክልሉ መሪዎች ስራና የመንግስታችን ዓላማ ግልጽ ኣይደለም – ከገብረ አማኑኤል፣

የመሪዎች ዋና ሚና የዜጎችን ደህንነትና ሰላም ማስጠበቅ መሆኑ ግልጽ ነው። መሪዎቻችን ይህንን ጉዳይ አንደትርፍ ሰዓት ሥራ ያዩት ይመስላል። ምክንያቱም የዜጎች ደህንነት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በከፍተኛ አደጋ ላይ የወደቀ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር በመሆኑ ነው።

113757ለበርካቶች ህይወት መጥፋት ዋነኛው ምክንያት የለውጡ ሃይል የሚከተለው የአመራር ስልት ወይም የያዘው ዓላማ ይመስላል።

ተጠቂው ህዝብ እየተካሄደ ባለው ጭፍጨፋ ራሱን ለመከላከልም ሆነ ለመቃወም አንኳን አልቻለም። ትጥቁንም በተለያየ መንገድ አጥቷል። ስለዚህ አሁን የሚታየው ሁኔታ ዜጎች በማንነታቸው ዘራቸው እንዲጠፋ ተፈርዶባቸዋል፣ አንዳይንቀሳቀሱ በሃይል ተረግጠው የተያዙ መሆኑን ነው። ምንም በማያደርጉበት ሁኔታ ላይ የመንግሥት አካል በሆኑም ሆነ ራሳቸውን ባስታጠቁ ሃይሎች እጅና እግራቸው ተይዞ እየተጨፈጨፉ ይገኛል። እጅግ የሚያሳስበው እንዲጠፉ የተፈረደባቸው ዜጎች በኣገራችን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መሆናቸው ነው። ለዜጎች ህይወት ዋጋ የሚሠጥ ስርዓት ቢሆን ኖሮ በክልልላቸው የዚህ ሁሉ ሰው ህይወት ሲጠፋና ቤት ንብረታቸው፣ አንዲሁም ቤተ ክርስቲያኖች  ሲቃጠሉ፣ ይህንን ሁኔታ ያልተቆጣጠሩ የክልል መሪዎች ምንም እንዳልተፈጠረ  ለችግሩ መፍትሄ ሳይሰጡ ባሻቸው ጊዜ ብቻ መግለጫ እያወጡና ያዞ እንባ እያፈሰሱ በስልጣናቸው ላይ ተደላድለው ባልተቀመጡ ነበር። ስለዚህ ይህ የሚያሳየው የዚህ ዘር የማጽዳት ተልዕኮ አጠያያቂ መሆኑን ነው። ”የመፍትሄው አካል ካልሆንክ የችግሩ አካል ነህ።” አንደሚባለው ማለት ነው።

ሃላፊነት የሚሰማው መንግሥት የዜጎቹን ሰላምና ደህንነት ከመጠበቅ የበለጠ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ሊኖር አይችልም።  ሆኖም መሪዎቻችን የሚውሉበትን ስንመለከት እየታየ ያለው ከሰው ህይወት የበለጠ በአገሪቱ ቅድሚያ የሚሰጧቸው ብዙ ሌሎች ጉዳዮች እንዳሉ ነው። ይህ ደግሞ በምንም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም። ፈጣሪ አክብሮ የፈጠረው የሰው ልጅ ዛሬ ሰዎች ለራሳቸው ጊዜያዊ ጥቅም ሲሉ በፈጠሩት ሰው ሰራሽ ምክንያት ምንም የማያውቁ ሰዎች፣ ምናልባትም የዘመኑ ፖለቲካ የማይገባቸው ሰዎች፣ ህጻናት፣ እናቶችና አባቶች ህይወታቸው አንዳልባሌ ማለፉ ህሊና ያለውን ዜጋ በጅጉ ያሳዝናል።

የወያኔ መንግስት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ህዝቦችን ፈርጆ ሲያጠቃና የሃሰት ምክንያቶችን እያቀረበም ዜጎችን ሲገድል ኖሯል። አሁን የሚታየው ደግሞ እጅግ ያልተለመደ ነው። በአገር ውስጥ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ ወንጀልን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ የሚፈጽሙ በከፍተኛ ደረጃ የታጠቁ ሃይሎች እንዳሉ ይታያል። መንግስት እነዚህን የተደራጁ ሃይሎች የራሱንም ጭምር ሙሉ ለሙሉ የሚቆጣጠራቸው አይመስልም ወይም ይቆጣጠራቸዋል፣ ይህ ሁሉ ሰቆቃ ሲወርድ ግን ለምን ዝም አንደሚል አኛ  ኣናውቅም። ቀና መሪዎች አሉን ብለን ብናስብም አንኳን፣ የዜጎቹን የመኖር መብት ለማስከበር ለምን አንዳልቻለ ግልጽ አይደለም ወይም ፍላጎታቸው ኣይደለም።

በመሆኑም በማዕከል ቀና አመራርና የዜጎች ህይወት ግድ የሚለው አመራር ካለ ሃይሉን አስተባብሮ ችግሩን ማቃለልና በቁጥጥሩ ስር ማዋል የማይቻልበት መንገድ አይታይም። ህዝቡ ተባባሪ ነው ስነልቡናውም ይታወቃል። ለመንግስት ይታዘዛል፣ የሚያስተባብረው ከተገኘ ለዚህ ጉዳይም መፍትሄ ለመስጠት ይችላል ብዬ አምናለሁ ግን የሚያስተባብረው የለም ድርጊቱን አንኳን መቃወም አልቻለም።

የዘር ማጽዳት ከሌሎች አገሮች ልምድ አንደታየው ያለመንግስት ድጋፍ ሊካሄድ አይችልም። ይህንንም የክልል ባለሥልጣኖች የተሳተፉበት መሆኑን መንግስትም በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው ተነግሮናል። በተለይ በኦሮሚያ ክልል ለህዝቡ ብዛትና አስተዋይነት የሚመጥን አመራር አለ ለማለት ያስቸግራል። ዓላማቸው ፍጹም ኢትዮጵያዊነት ኣይደለም። ስለዚህ በመጀመሪያ ችግሩ በተስፋፋባቸው ክልሎች ያሉ ዋና ዋና መሪዎች ሥልጣናቸውን መልቀቅ ያለባቸው ይመስለኛል። ነዋሪዎቿን በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ባንድ ጀምበር የሚገደሉባት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሪ በስልጣናቸው መቆየታቸው ትርጉሙ ምንድነው? መልካም በማይሰሩበት ወይም አኩይ በሚሰሩበት ወንበራቸው ላይ ክዚህ ሁሉ ጭፍጨፋ በኋላ ምን ያደርጋሉ? ? ? የዲሞክራሲው አልዘልቀን ስላለ አንጂ በተደጋጋሚ በሚያስተዳድረው ክልል ውስጥ ህዝብ ሲጨፈጨፍ ቀርቶ፣ ትንሽ ጎላ ያለ ስህተት ሲታይ መሪዎች ሥልጣናቸውን አንደሚለቁ የታደሉት አገሮች ልምድ ያሳየናል። ይህን ያላየነው ጉዳዩ ሌላ ስለሆነ ነው። ከሰዎች አልቂት በኋላ በስልጣን ላይ ኢንደድል ኣድራጊ መንደላቀቅ አየተለመደ ሆኗል።

አገራችን በተወሳሰበ ሁኔታ ውስጥ መሆኗ ግልጽ ነው። ከተወሳሰበ ችግር ውስጥ ለመውጣት ሁሉም ዘዴ ከመሪዎች ሊመነጭ አይችልም። በመሆኑም፣ መንግሥት የጠራ ዓላማ ካለው፣ መፍትሄውን ከራሱ ከህዝቡ ጋር መፈለግ ያገባዋል። ይህን ለማድረግ ህዝብን ለማስተባበር መንግስት ኣቅም አንዳለው በተነካና በተደፈረ ጊዜ ባደረገው ጦርነት ኣይተነዋል። በዘር ማጽዳት ጭፍጨፋ ላይ ግን የመንግስት ዓላማ ግልጽ ኣይደለም። መንግስት ሆይ የእግዚኣብሄር ፍርድ ሳቀድም ዓላማህን ኣስተካክል። ክቡሩ የወገኖቻችን ደም ኣይፍሰስ፣ ህይወታቸው በከንቱ ኣይጥፋ!

‘ፍላጎት ካለ መንገር አለ።’

እግዚአብሄር ኢትዮጵያንና ህዝቧን ያድን!

ገብረ አማኑኤል

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.