ፍርድ ቤቱ ሻለቃ አዲስ ተድላ እና ሻለቃ ብርሃኑ ባየህ ከጣሊያን ኤምባሲ እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ሰጠ

132826749 10219263611442866 5179201574902013368 o
 የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሻለቃ አዲስ ተድላ እና ሻለቃ ብርሃኑ ባየህ ከጣሊያን ኤምባሲ እንዲለቀቁ ለጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እና ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ትዕዛዝ ሰጠ።
በእነ ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም መዝገብ የተከሰሱት የቀድሞ ፍርደኞች ሻለቃ አዲስ ተድላ እና ሻለቃ ብርሃኑ ባየህ ላይ የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ዘርፍ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት አስተዳደር የአመክሮ አቤቱታ ከአስተያየት ጋር አቅርቧል።
በዚሁ መሰረት አቤቱታውን የመረመረው ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል።
በጣሊያን ኤምባሲ ላለፉት 30 ዓመታት ተጠልለው የሚገኙት ሁለቱ ተከሳሾች ካሉበት የተከለለ ውስን ስፍራ ሊላቀቁ ይገባል ሲል ፍርድ ቤቱ አቤቱታውን መርምሮ በአብላጫ ድምጽ ብይን ሰጥቷል።
በዚሁ መሰረት “ሻለቃ አዲስ ተድላ እና ሻለቃ ብርሃኑ ባየህ ከጣሊያን ኤምባሲ እንዲለቀቁ” ሲል ለጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እና ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ትዕዛዙ በቀጥታ ለጣሊያን ኤምባሲ ሳይሆን በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ለጣሊያን ኤምባሲ እንዲሁም ለቀድሞ ፍርደኞች ሻለቃ አዲስ ተድላ እና ሻለቃ ብርሃኑ ባየህ እንዲደርስ ይደረግ ዘንድ አዟል።
ሻለቃ አዲስ ተድላ እና ሻለቃ ብርሃኑ ባየህ የቀድሞ ፍርደኞች አሁን ግን በአመክሮ በፍርድ ቤት የተለቀቁ መሆኑን አውቀው መብታቸውን ለማስከበር ጥበቃም ሆነ ክትትል እንዲያደርጉ ለሚመለከተው አካል እንዲጻፍ ፍርድ ቤቱ አዟል።
በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ላይ በተራ ቁጥር ሁለት የተሰየሙት ዳኛ ተከሳሾቹ በኤምባሲ በስደተኛነት ተጠልለው ነበር እንጂ ፍርድ አግኝተው ቅጣታቸውን በማረሚያ ቤት ያልተቀበሉ በመሆናቸው ከመደበኛው የአመክሮ ስርዓት ውጭ የአመክሮ ጊዜያቸው እንደደረሰ በመቁጠር እንዲለቀቁ ከውሳኔ መደረሱ ላይ በልዩነት ወጥተዋል።
ላለፉት 30 አመታት አዲስ አበባ በሚገኘው የጣሊያን ኤምባሲ ተጠልለው በቁም እስር ላይ የቆዩት ሁለቱ ከፍተኛ የደርግ
በኤምባሲው ተጠልለው የሚገኙት የ85 ዓመቱ ሻለቃ ብርሃኑ ባየህና የ77 አመቱ ሻለቃ አዲስ ተድላ ናቸው።
ሻለቃ ብርሃኑ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ያገለገሉ ሲሆን የ77 ሻለቃ አዲስ ተድላ ደግሞ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሆነው ያገለገሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ነበሩ።
እነዚህ ሁለት ከፍተኛ የቀድሞ ሹማምንት ከጣሊያን ኤምባሲ የቁም እስር እንዲወጡ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስን ጨምሮ በርካታ አካላት ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር ኢዜአ ዘግቧል።
ላለፉት 30 አመታት አዲስ አበባ በሚገኘው የጣሊያን ኤምባሲ ተጠልለው በነበሩት የደርግ ባለስልጣናት ላይ ተላልፎ የነበረው የሞት ፍርድ ወደ እድሜ ልክ እስራት ማሻሻያ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በፊርማቸው ማጽደቃቸው ይታወሳል።
ኤፍ ቢ ሲ

1 Comment

  1. የደርግ አስር አለቆች እጅ እያወጡ በድምጽ ብልጫ በተለምዶ “ስልሳዎቹ ባለስልጣኖች” ላይ ሞት ፈርደው ነበር የረሸኗቸው፤፤ በዚያች ቀውጢ ምሽት “ጉዳዩ በህግ ስለተያዘ፤ ለምን በህግ አያልቅም?” ብለው ለታሪክ የምትሆን በብችኝነት የተለየ ሃሳብ ያቀረቡት ኮሎኔል ብርሃኑ ባየህ ነበሩ፤፤ ምናልባትም በጣት ከሚቆጠሩት የኮሌጅ ዲግሪ ከነበራቸው አንዱ እሳቸው ነበሩ፤ ከዚህ በኋላ እንግዲህ የቀሩት ቁንጮው መሪ ራሳቸው ኮ/ል መንግስቱ ናቸው – የሞት ፍርድ በአናታቸው ላይ ይዘው ወደ መቃብር የሚወርዱ ብቸኛው የደርግ አባል! ብቸኛው መሪ? እንደው ንስሃ ገብተው ይሆን?

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.