አቶ ሰብስቤ ንፃፄ በአማራ ላይ የሀሰትና የጥላቻ ዘመቻ እና የጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ዝምታ – ጌታቸው ሽፈራው

3444አቶ ሰብስቤ ንፃፄ ይባላል። የቤንሻንጉል ጉሙዝ ርዕሰ መስተዳደር እንዲሁም የክልሉ የውሃ ሀብት ቢሮ ኃላፊ ነበር። የሚያሳዝነው እነ አሻድሊ ጋር መክሮ በአማራ ላይ የሀሰትና የጥላቻ ዘመቻውን ማቅረቡ አይደለም። ይህን ችግር እናበርዳለን ብለው የሄዱት ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ዝም ማለታቸው ነው!
1) የትህነግ ወረራ ወቅት በሌሊት በቲቪ ብቅ ብለው የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻን ያመሰገኑት ጠ/ሚ ዐቢይ ናቸው። ሆኖም ይህ ሰው ረዥም ሰዓት ተሰጥቶት የአማራ ልዩ ኃይል በሕግ ማስከበሩ ወቅት ቤት አቃጥሏል እያለ በሀሰት ሲወነጅል ያስቆመው አካል አልነበረም። በዚህ ውንጀላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልስ አልሰጡብትም። ይባስ ብሎ በቲቪ እንዲተላለፍ ተደረገ። የአማራ ልዩ ኃይል የተሳተፈው ጠ/ሚ ዐቢይ በመሩት ሕግን የማስከበር ዘመቻ ነው። ሌሎች ውጭ ሆነው በሀሰት ዘመቻ ሲያደርጉ ውሸት ነው የሚሉ አካላት ፊት ለፊታቸው ቆሞ እሳቸው በመሩት የሕግ ማስከበር ስራ ቤት ሲቃጠል፣ ንፁሃን ሲገደሉ እንደነበር በሀሰት የወንጀለው ማስቆም አልቻሉም። ለሀሰት ወንጀላው ማስተባበያ አልሰጡትም። ጭራሽ ሰፊ ሰዓት ተሰጥቶት ተናገረ። በሚዲያ ተደጋገመ። የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ነው ችግር የፈጠረው ተብሎ በሀሰት ስለተወነጀለ እሳቸው በሀሰት ያልተወነጀሉ የሚመስለው ካለ ተሳስቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህን የሀሰት ወንጀላ ሳያስቆሙ ውስብስቡን የመተከልን ችግር ሊፈቱ አይችሉም።
2) ጠ/ሚ ዐቢይ ለስብሰባ ሲሄዱ የጉሙዝ አመራሮች ሰው አሰልጥነው ሊያስገቡ መሆኑ በተደጋጋሚ ተፅፏል። እነ አሻድሊ ይህንና ሌሎች ሰዎችን እንደሚያስገቡ ይታወቅ ነበር። አንዴ አምነዋቸዋልና ሰላም እሰብካለሁ በሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መድረክና ፊት የለየለት የጥላቻ ቅስቀሳ ተደረገ። ዝም ተባለ። በሚዲያ ተላለፈ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እርቅና ሰላም እናወርዳለን እያሉ ይህን የመሰለው ሰው ግን “እናልቃለን እንጅ” እያለ ሲቀሰቅስ ማስቆም አልተቻለም። መልስ አልተሰጠውም። ጭራሽ ሰፊ ጊዜ ተሰጥቶት በሚዲያ ተላለፈ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህን እነ አሻድሊ ያደራጁት በጥላቻ የሰከረ ቡድን አደራሽ ውስጥ አደብ ሳያስገዙ በርካታ ኃይል ከጀርባው ያለበትን የመተከል ጭፍጨፋ ሊያስቆሙ አይችሉም። መጀመርያ ፊት ለፊት ያገኟቸውን የጥላቻ ብልቃጦች የጥላቻ ቅስቀሳ ማስቆም ነበረባቸው።
3) በብልፅግና ስብሰባ ወለጋና ሸዋ ላይ አማራ በማንነቱ ሲጠቃ ማስቆም ያልቻሉት፣ እንዲያውም በመዋቅር እንዲጠቃ ያደረጉት እነ ሽመልስ አብዲሳ የቤንሻንጉል ጉሙዝን አመራር አሰባስበው፣ ሌላውንም መክረው አማራ በወልቃይትና ራያ ላይ ያለውን አቋም አውግዘው አማራጭ አለን ብለው መጡ። በሚያስተዳድሩት ክልል ንፁሃንን የሚያስጠቁ አካላት በስብሰባ ይሄን ቢሉ አይገርምም በእርግጥ። እነ አሻድሊ አሰልጥነው ያስገቧቸው ሰዎችም የደገሙት ይሄንኑ ነው። የአማራን ሕዝብ እንደ ተንኳሽ፣ አማራ ክልልና የአማራ ሕዝብ ለኢትዮጵያ አደጋ ነው ብለው አቀረቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አላስቆሙም። መልስ አልሰጡም። ጭራሽ በሚዲያ ተላለፈ።
4) ጫካ ገብቶ ሕዝብን እያረደ ያለውን ኃይል “የእኛ ሕዝብ” እያለ ያወራ ነበር። ጭራሽ ተገፍቶ እንደወጣ ሲናገር ነበር። ተገፍቶ ወጣ ያለውን ጨካኝ ኃይል “ይመለስልን” አለ። ይህን ሁሉ ሲል ዝም ተባለ። መልስ አልተሰጠውም። በሚዲያ ተላለፈ። ከዚህ በላይ ለዛ ጨካኝ ኃይል ምን ድጋፍ ሊደረግለት ይችላል? ንፁሃንን በጥይትና በስለት የሚጨፈጭፈው ገዳይ ኃይል ስብሰባ አደራሽ ቢገኝ ከዚህ በላይ ጥላቻውን በምን ቋንቋ ይገልፀዋል?
ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ የመተከልን ጉዳይ እፈታለሁ ብለው ሄደው ችግሮችን አወሳስበው ነው የተመለሱት። የአማራ ሕዝብ፣ ብሎም በእርሳቸው የሕግ ማስከበር ተግባር ተሳትፎ በስርዓት ግዳጁን የተወጣው የአማራ ፀጥታ ኃይል ላይ ያን ያህል የሀሰት ውርጀላ ሲወርድ፣ በአማራ ላይ ጥላቻ ሲሰበክ ምንም አላደረጉም። ስብሰባ ውስጥ ይህን ያህል ጥላቻ ሲሰብክ የዋለ የእነ አሻድሊ ኃይል ለተናገረው ተገቢ መልስ ሳይሰጠው ሲመለስ የልብ ልብ ቢሰማው አይገርምም። ለዛ ነው አብይ እንደተመለሱ ዘግናኝ ጭፍጨፋ የተፈፀመው። እውነቱን ለመናገር ጨፍጫፊው ጫካ ባለው ኃይል ብቻ አልነበረም የሚፈፀመው። አደራሽ ውስጥ በጥላቻ ሲንተከተክ የነበረው የጭፍጨፋው አካል ነው። ጭፍጨፋ የሚመነጨው ያን ከመሰለ ጥላቻ ነው። ያን ጥላቻ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ረዥም ጊዜ ሰጥተው አዳምጠው፣ ለወንጀላው የረባ መልስ ሳይሰጡ፣ በሚዲያ እንዲተላለፍ ሆኗል።
ተጨማሪ ያንብቡ:  ሟች ይዞ ይሞታል

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.