በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞን ቡለን ወረዳ በኩጂ በተባለች ቀበሌ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ከ90 በላይ ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀረ የአካባቢዎው ነዋሪዎች ተናገሩ

OLF and Benshangulጥቃቱ በቀበሌዋ ዛሬ ማለዳ መፈጸሙን የተናገሩት ነዋሪዎቹ ከሀምሳ በላይ የመኖርያ ቤቶችም መቃጠላቸውን ገልጸዋል። ዛሬ ሲነጋጋ አሰራ አንድ ሰዓት አካባቢ ተጎጂዎች ተኝተው ባሉበት ቤታቸው ከውጭ እየተዘጋ እንዲቃጠልባቸው እና ሌሎች ደግሞ ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ መገደላቸውን ከአካባቢው መስማታቸውን አንድ የቡለን ወረዳ ነዋሪ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። በጥቃቱም ሕጻናትን ጨምሮ 96 ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀረም ገልጸዋል።
«በዓይኔ እንኳ አላየሁም ቢያንስ ጥዋት 11 ሰዓት አካባቢ ሰዎች ተኝተው ባለበት ሰዓት ቡለን ወረዳ በኪጂ በምትባል ቀበሌ ማኅበረሰቡ በድንገት ታፍኖ ብዙ ጥቃቶች ደርሷል። ሰዎች ሳር ቤት ውስጥ በተኙበት በራቸው ከውጭ እየተቆለፈ ሕጻናት፣ እናቶች እና ብዙዎች ሞተዋል። እስካሁን ባይረጋገጥም እስከ 96 ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀሩ መረጃዎች አሉን።»
በመተከል ዞን የግልገል በለስ ከተማ ነዋሪ እና መምህር እንደሆኑ የነገሩን ሌላው ምስክር ደግሞ የጥቃቱ ሰለባዎችን ቁጥር 106 ያደርሱታል ። በተጨማሪም በጥቃቱ ከተገደሉት ውጭ ከ50 በላይ መኖርያ ቤቶች መቃጠላቸውንም ይገልጻሉ።
« በመተከል ዞን ዋና ከተማ ግልገል በለስ ነው ያለሁት። በአንድ ወረዳ ከ106 በላይ ሰው ነው የታረደው እና የተገደለው። እና በጣም ዘግናኝ እና በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ እና ተሰምቶ የማይታወቅ ድርጊት ነው የተፈጸመው። በተጨማሪም ከ50 በላይ ቤቶችም ተቃጥለዋል። በዚህ ድርጊት እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ 96 ሰዎች ነበር አሁን እየተፈተሸ እየተፈተሸ ሄዶ ወደ 106 ሰዎች ደርሷል።»
ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅትም የመከላከያ ሠራዊትም ሆነ ሌሎች የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በአቅራቢያ እንዳልነበሩ እና ዘግይተው መድረሳቸውንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። በመተከል ዛሬ ተፈጸመ የተባለውን ጥቃት በተመለከተ የክልሉን መንግሥት አስተያየት ለማካተት ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጋሹ ዱጋስ ብንደውልም ስልካቸውን ባለማንሳታቸው አልተሳካም። የክልሉ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ ደግሞ ስብሰባ ላይ መሆናቸውን ነግረውናል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ በመተከል ዞን ተገኝተው በአካባቢው ባለው የጸጥታ ሁኔታ ላይ የነዋሪዎች ተወካዮችን ያነጋገሩት ትናንት ማክሰኞ ነበር።
DW

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.