ክረምት እና በጋ በጎጃም መተከል – ማላጂ         

metekel ክረምት እና  በጋ በጎጃም  መተከል     ማላጂ         በሩብ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያዉያን የጥልመት እና ሞት ዓመታት የዜጎች ደም ያልፈሰሰበት ፣ህይዎታቸዉ ያላለፈበት ፣ ሠላማቸዉ ያልደፈረሰበት እና ማንነታቸዉ  የጥቃት ኢላማ በመሆን ለማያባራ መከራ እና ፍዳ ያልተዳረጉበት ዓመታት አይደለም ቀናት እንዳልነበሩ የገሀዱ ዓለም ዕዉነታ ነዉ ፡፡

በኢትዮጵያችን በቋንቋ የአገር አስተዳደር ፈሊጥ የቡድን እና የግል ስልጣን እና ጥቅም ከመረጋገጥ አልፎ ተንሰራፍቶ ካልሆነ በቀር ለዜጎች የአጋም እና ቁልቋል ቅርበት እና ጉርብትና በመትከል አገራዊ መረጋጋት ሊኖር እና ላይኖር  በግል እና ቡድን  በጎ ፈቃድ እና ችሮታ እንጅ በዜግነት የሚጠየቅ እና የሚጠበቅ አልነበረም ፡፡

በተለይም በአሁኑ ጊዜ አንጻራዊ ሠላም እና መረጋጋት የሚታይባቸዉ የአገራችን ክፍሎች ማለትም ምስራቅ ፣ደበቡብ ምዕራብ  ከመሳሰሉት ዉጭ አሁንም በሰላም ዉሎ በሠላም መግባት ህልም የሆነባቸዉ የሞት ጠረን ሽታ የሚሰማቸዉ በገዛ እናት አገርምድር ተወልደዉ ባደጉበት ፣ ወልደዉ በከበሩበት ፣በክብር ከኖሩበት መጻተኛ መባል ከምንም በላይ የሚያቆስላቸዉ ዜጎች አሁንም ብዙ ናቸዉ፡፡

ከሚጠቀሱት እና ጆሮ ዳባ ልበስ ከሚባሉት አካባቢ አንዱ እና ወነኛዉም መተከል አዉራጃ ነዉ ፡፡ መተከል ከአካባቢዋ እና ከራሷ ልጆች አልፋ ለመላዉ ኢትዮጵያ እና አፍሪካ ሲሳይ የምትሆን ናት ፡፡

ነገር ግን በጥላቻ እና በምቀኝነት የፖለቲካ ቅኝት ከጎጃም ክፍለ ሀገር ተነጥላ በክልል አደረጃጀት ባለቤቱን ባይታዋር ወንጀለኛ እና ቀማኛን አገልጋይ በማድረግ ለታሰበ ሴራ ወደ ቤኒ ሻንጉል ከተካለለ ጊዜ አንስቶ ዕድለኛ ሆኖ በሰደት እና በጥገኝነት ህይወቱን ለማቆየት ከቻለዉ ህዝብ በቀር ብዙዉ በሞት፣ በማስፈራራት፣ በዱር በገደል መኖር ከጀመረ ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ መቆጠሩን ባለቤቱ ህዝቡ እንጅ ማንም ሊናገር አይችልም፡፡

ሆኖም ከቅርብ ዓመታት በኋላ በክልሉ በተለይም በመተከል አዉራጃ እየደረሰ ላለዉ ከፍተኛ እና ጭካኔ የተሞላበት የዜጎች ኣሳር በሚመለከት የሚሰጠዉ ምክነያት እና ምንም ዓይነት ህዝባዊም ሆነ መንግስታዊ አላፊነት የሚወስድ አካል አለመኖር ሳያንስ የ20 ዓመት ተደጋጋሚ እና አገር አዉዳሚ ሰበብ መስማት ለሰዉ ልጅ ቀርቶ ለዱር አራዊት እንኳን ሠላም የሚነሳ ነዉ ፡፡

በመተከል በሰዉ ልጅ ህይዎት ፣ ደህንነት ፣ በአገር ዕድገት እና በዐጠቃላይ የአስተዳደር እና ብሄራዊ ቀዉስ ላይ የነበረዉ ችግር እና ችግሩን ምንጭ መጥቀስ ለቀበሪ ማርዳት እና ጊዜ ማጥፋት ይሆናል፡፡

ሆኖም በተለያ ጊዜ የአካባቢ የመንግስት መስተዳደር አካላት  በመተከል አዉራጃ በሚኖሩ እና ነባር ዜጎች ላይ የሚደርሰዉ ሁለገብ የማሳደድ ጥቃት መንስኤ እና መፍትሄ የሰጡትን እና ዕየሰጡ ያለዉን ለማስታወስ ይህም በተለያየ ጊዜ የሚገለጥ ሆኖ ፡-

፩) ከሱዳን ሰልጥነዉ የሚገቡ ለወጡን ለማደናቀፍ  ከፀረ ለዉጥ አካላት የሚለላኩ፣

፪) የመተከል አካባቢ መሰረተ ልማት አጠር በመሆኑ እና ይህም ጥቃት ለማድረስ እና ለመደበቅ ምቹ ለመሆኑ፣

፫) ባልተዘጋጀንበት ጊዜ ስለመጡ፣

፬) በለሊት እና ምሽት ስለመጡ  ወዘተ ሲሉ አንድም ቀን በአቅም እና ፍላጎት ማነስ ለተከሰተ ተደጋጋሚ በህዝብ እና አገር ላይ ለደረሰ ጥፋት ኃላፊነት መዉሰድም ሆነ ይቅርታ ለመጠየቅ አልተፈለገም ፡፡ እዚህ ጋ ይቅርታ ማን ለማን ለሚል  የ3000 ሽ ዓመት የአገረ ምድር ታሪክ ባላት አገር የአገር እና የዳር ድንበር ምስረታ እና ጥበቃ ባለቤት የሆነዉን ህዝብ ከአራቱም የአገሪቷ አቅጣጫ እንደ ዱር አዉሬ የማሳደድ ሴራ አካል ሆኖ በለዉጥ ጊዜም መቀጠሉን የሚያዉቅ በተለይም የአካባቢ መንግስት በይፋ ይቅርታ ለመጠየቅ፣ ለደረሰዉ ጥፋት እና ሞት ኃላፊነት ለመዉሰድ ብሎም ግንባር ቀደም ህዝብ እና አገር ከመከላከል በዜጎች ላይ ሞት እና እንግልት  እንዲቀጥል መፍቀድ ነዉ ፡፡

ከላይ የተጠቀሱት እና ለሌችም ሸንጋይ ምክነያቶች ከ20 ዓመት በላይ አካባቢዉን እና አገሪቷን የሞት እና የስጋት ቀጠና በማድረግ የስልጣን ዘመን ማራዘሚያ እና ማድለቢያ የተሰጡ እና የሚሰጡ  ርሃብ ሲባል  ጥጋብ የሚል ትርጉም የሚሰጥበት ነዉ፡፡

ይህ ሁሉ ሳይበቃ ሰሞኑን ከቀናት በፊት ከአካባቢዉ መስተዳደር ድንበር አልፎ ለደረሰ ጥቃት የተሰጠ መልስ በአጥፊዎች ላይ እርምጃ ለመዉሰድ በጋ እንጠብቃለን ማለታቸዉን ከአንድ የቤንሻንጉል ቃል አቀባይ መስማታችን የሚያሳየን በህዝብ እና አገር ላይ ለዓመታት የደረሰዉ እና አምሳያ ለሌለዉ የግፍ አስተዳደር የማን አለብኝነት ማሳያ ነዉ ፡፡

በጋ እና ክረምት ዓለም ሲፈጠር እኛም እንደ አገር ኢትዮጵያ  ከተመሰረተችበት እና ከኖረችበት ጀምሮ ክረምት እና በጋ ነበር ግን አንድም ቀን ላለፉት ሀያ አምስት ዓመታት የሠዉ ህይወት ያልጠፋበት ፣ደም ያልፈሰሰበት ፣ ስደት ያልነበረበት ፣ህዝብ ቤቱን ትቶ በዱር በተራረዉ ያልባዘነበት የመተከል አዉራጃ መሬት እና ዓመታት አልነበረም፡፡

የህዝብ አስተዳደር ኃላፊነት ባለመወጣት  በህዝብ እና አገር ላይ ለሚደርስ መጠነ ሰፊ ጥቃት እና ዉርደት በለሊት እና ማዕልት ፣ በበጋ እና ክረምት  የሚመካኝባት ብቸኛዋ እና ጥንታዊት አገር ኢትዮጵያ እና ጎጃም(መተከል) መሆኑ ግን የ21ኛዉ ክፍለ ዘመን “አሳዛኝ ቀልድ እና ጭካኔ ” ብሄራዊ እፍረት   ነዉ ፡፡

ይኸ ምን ቸገረኝ የምትሉት ሀረግ  እርሱ ነዉ አገሬን ያረዳት እንደበግ  ፣

የምትሰኝ ስንኝ ልፅፍ አሰብኩ እና ፣

       ምን ቸገረኝ  ብየ ቁጭ አልኩ እንደገና፡፡(ነስርዲን ሙሳ- ነባር ታጋይ የነበሩ )                                                                                               

                                                             ማላጂ                                                                                                     

                                                       “ምንጊዜም  እናት አገር” !!!

 

1 Comment

  1. የሚገርመው የክልሉ ፕሬዜዳንት ተብየው ለምን በጊዜው እርምጀ አልተወሰደበትም፡፡ ሌላውስ ወንጀለኛ ህዝብ ስንት ሲጮህ፡፡

    በኢሰባዊነት የሰውን ልጅ ያለአግባብ የጨፈጨፉ በአደባባይ በሞት ፍርድ መቀጣት አለባቸው፡፡ የሞት ፍርዱ ህግ በአፋጠኝ መቀየር አለበት፡፡ እንደው የሰውልጅ እንደቀልድ በየሜዳው፡፡ ነግ በኔ ማለት ጥሩ ነው፡፡ አትፍረድ ይፈርድብሃል ነው ነገሩ የጊዜ ጉዳይ ቢሆንም፡፡

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.