የአማራን ህዝብ ፀጥታ ሊያውኩ የሚችሉ ሁኔታዎችና መፍትሄዎቻቸው!!! – መሰረት ተስፉ

መሰረት ተስፉ (Meserettesfu4@gmail.com)

13873059 10154337451173232 7520496074197740677 nእንደሚታወቀው ባለፉት ሰላሳና እና አርባ አመታት የአማራ ህዝብ እንደህዝብ በቀደሙት ስርዓቶች ተጠቃሚ፣ ገዥ፣ ጨቋኝ፣ የበላይ፣ ነፍጠኛ፣ ትምክህተኛ፣ ጨፍላቂ፣ አህዳዊና ሌላም እንደሆነ ተደርጎ እንዲታይ በከፍተኛ ሁኔታ የተንቀሳቀሱ በርካታ ልሂቃን ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። በዚህም ምክንያት ይህ ህዝብ እንደህዝብ ትኩረት ተነፍጎትና አልፎም ግፍና መከራ ሲፈራረቅበት ቆይቷል። በዚህ ረገድ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ የስልጣን መንበሩን ከተቆጣጠረ በኋላ የመጀመሪያው የመፈናቀልና የጅምላ ጭፍጨፋ መጥፎ አጋጣሚ ሰለባ የሆነው የአማራ ህዝብ እንደሆነ ማንሳት ለቀባሪ ማርዳት ይሆንብኛል። በማንነቱ ምክንያት እድሜ ልኩን ከኖረበት አከባቢ ሲፈናቀልም እንዲፈናቀል የተደረገው ደን ስለጨፈጨፈ ነው በሚል የተቀለደበትም የአማራ ህዝብ እንደሆነ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

አሁንም በአማራ ህዝብ ላይ እያንዣበቡ ያሉ ከፀጥታ፣ ከህግ የበላይነት፣ ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚና ከማህበራዊ ጉዳዮች ጋ የተያያዙ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን መካድ አይቻልም። በ’ኔ አምነት እነዚህ ችግሮች በተናጠልም ሆነ በመሰናሰል በአማራ ህዝብ ላይ የራሳቸው የሆነ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ቢሆንም የቅደም ተከተል ጉዳይ ነውና ሌሎቹን አበይት ጉዳዮች በሌላ ጊዜ የምመለስባቸው ሆኖ በዚህ ፅሁፌ ላነሳ የፈለኩት ግን ከፀጥታ ጋ የተያያዙ ችግሮችንና መፍትሄ ይሆናሉ ብየ የማስባቸውን ነጥቦች ነው።

ላሁኑ በፀጥታ ጉዳይ ዙሪያ አምስት መሰረታዊ ችግሮችን ማንሳት ተገቢ ነው ብየ አምናለሁ።

  1. የአማራና የቤንሻንጉል ጉሙዝ አመራሮች አተካራ፣

ቤንሻንጉል ጉሙዝ ውስጥ በተለይም መተከል ዞን ላይ በማንነታቸው ምክንያት አማራዎችና አገዎች በስፋትና በተከታታይነት እየተገደሉና ንብረታቸው እየወደመ እንደሆነ ዘገባዎች ያመለክታሉ። እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እየተወሰዱ ናቸው የሚባሉ እርምጃዎችም ብዙ ለውጥ እያመጡ እንዳልሆኑ እየተገለፀ ይገኛል። በተለይ ደግሞ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ አመራሮች ውጭ የሌሎች አካላት ጣልቃ ገብነት አለ የሚለው ስሞታ ጎልቶ እየወጣ መሆኑ ሁኔታዎችን ያባባሰ ይመስላል።

የአማራ ክልል አመራሮች በበኩላቸው መተከል ዞን ላይ የሚኖሩ አማራዎችን በራስችን ሃይል ለመከላከል እንችል ዘንድ የፌዴራል መንግስቱን ፈቃድ እየጠየቅን ነው የሚል ሃሳብ ሲያንፀባርቁ ሰምተናል። ከላይ የተገለፁት እሰጥ አገባዎች ተደማምረው ሲታዩ ችግሩ እየተባባሰ እንጅ እየቀለለ እንዳልሆነ አመላካቾች ናቸው። እዚህ ላይ መነሳት የሚገባው ጥያቄ ችግሩን ለመፍታት ምን ይደረግ የሚል ነው።

በእኔ እምነት ችግሩ በዋነኛነት ሊፈታ የሚችለው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት አመራሮች ሁሉንም ዜጎች እኩል አይተው ለሁሉም እኩል የሆነ የህግ ጥበቃና ከለላ ሲያደርጉላቸው ብቻ ነው። ይህን ሃላፊነት መወጣት ካልቻሉ ያሉት አማራጮች ሁለት ናቸው። አንደኛው አማራጭ አመራሮቹ ራሳቸው ሃላፊነታችን በአግባቡ መወጣት አልቻልንም ብለው ስራቸውን መልቀቅ ነው። ሁለተኛውና የመጨረሻው አማራጭ ደግሞ በስፋትና በተከታታይነት እየተጣሱ ያሉት የዜጎች በህይወት የመኖርና ንብረት የማፍራት መብቶችን ለማስከበር በሚያስችል መንገድ ፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ እንዲገባ ማድረግ ነው። በዚህ ሂደት የአማራ ክልል አመራሮች ሊጫወቱት የሚገባው ሚና ቃላት መወራወርና መግለጫ ማዥጎድጎድ ሳይሆን ህግና ስርዓትን ተከትለው ድርጊቱን ማውገዝና ተጨባጭ ማስረጃዎችን በማቅረብ ፌዴራል መንግስቱ ሃላፊነቱን መወጣት ይችል ዘንድ አስፈላጊውን ግፊትና ትግል ማድረግ ነው። በነገራችን ላይ እነሱም የፌዴራል መንግስቱ አባላት እንደሆኑ መገንዘብ ይኖርባቸዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:   የኢትዮጵያ ታሪክ ጽሁፍ ገና ገና ተጀመረ እንጂ አላለቀም   “ለዶር ጌታቸው ኃይሌና ለዶር ጳውሎስ ሚልኪያስ መልስ ”

በመጨረሻም እንዲታወቅ የምፈልገው የአማራ፣ የኦሮሞና የቤንሻንጉል አመራሮች የሶስትዮሽ ግንኙነት ለአማራ ክልል ፀጥታ መከበርም ሆነ መደፍረስ ያለው ሚና very critical መሆኑ ነው።  በዚህም ምክንያት ሃሳቤን በሌላ መድረክ ለመግለፅ እቅድ ስላለኝ እዚህ ፅሁፍ ውስጥ አላካተትኩትም

  1. በህወሓት ሰዎችና በአማራ አመራሮች መካከል ያለው ፍጥጫ:

እንደሚታወቀው ህወሓቶች አቅደው የጀመሩት የመስፋፋት ፍላጎትና ወረራ ተቀልብሷል። በመሆኑም ባሁኑ ሰዓት በቀጥታ ከነሱ የሚመጣ ከባድ የፀጥታ ችግር አለ ብየ አላስብም። በእርግጥ ተበታትነውም ቢሆን በአንድ ወይም በሌላ ጊዜ ትንኮሳዎችን ሊፈፅሙ የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች ይኖራሉ። እነዚህ ትንኮሳዎች ግን ከአከባቢው ፖሊስ፣ ሚሊሻና ነዋሪ ህዝብ አልፈው ለአማራ ህዝብ እንደ ህዝብ  አደጋ ለመሆን ይችላሉ ለማለት ይከብደኛል። ምን አልባት ወደፊት ሃይላቸውን አሰባስበው የትጥቅ ትግል የሚጀምሩ ከሆነ የመጀመሪያ ታርጌታቸው ምንጊዜም እጅግ አድርገው የሚጠሉት የአማራ ህዝብ መሆኑ አይቀርም። ይህ እንዳይሆን ለማድርገ የአማራ አመራሮች ካሁኑ ህዝቡን በማደራጀትና የአከባቢውን የፀጥታ ሃይል አጠናክረው የማብቃት ስራ በመስራት ራስን የመከላከል ቁመና መገንባት ያለባቸው መሆኑን ላፍታም ቢሆን ሊዘነጉ አይገባም። እነዚህ የህወሓት ሰዎች ሱዳንን እየመሩ ወይም ደግሞ ተባብረው ወረራ ሊፈፅሙ ይችላሉ የሚል ካለ ደግሞ ጉዳዩ የፌዴራል መንግስቱ ስለሚሆን የአማራ አመራሮች ማድረግ የሚጠበቅባቸው ሊቃጣ የሚችልን ቀጥተኛ የሆነ ጥቃትን እየተከላከሉ በዋነኛነት ግን ፌዴራል መንግስቱ አስፈላጊውን ሁሉ አድርጎ የሃገራችን ድንበር ሊያስከብር የሚችል በቂ ሃይል በአከባቢው እንዲመድብ ማስታወስና መታገል ነው።

  1. በአማራ ክልል በኩል ያለው የኢትዮሱዳን ድንበር ውዝግብ፣

በዚህ ዙሪያ በርካታ ሃሳቦች ሲንሸራሸሩ ይደመጣሉ። ብዙ ሰዎች በአማራ ክልል በኩል ያለው የኢትዮጵያ ድንበር የሱዳን መጫወቻ ሆኗል የሚል ስሞታ ያቀርባሉ። የአማራ አመራሮችም እንዲሁ ረዘም ካለ ጊዜ ጀምረው ሱዳን ታሪካዊ ዳራውን ባልጠበቀ መንገድ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በኩል ያለውን ድንበር ጥሳ ወደ ኢትዮጵያ ዘልቃ ገብታለች የሚል ቅሬታ እያቀረቡ እንደሆነ ይታወቃል።

በዚህም አለ በዚያ ግን የድንበሩ “በሱዳን የመጣስ” ጉዳይ የአማራን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ህዝብም ሆነ መንግስት የሚያሳስብና የሚያውክ በጣም ትልቅ የሆነ አጀንዳ ነው። ስለዚህ እንደቀላል ሊታይ የሚገባው ስሞታ አይደለም። ምክንያቱም የአገር ሉአላዊነት ለምንም አይነት ድርድር የሚቀርብ አለመሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በኢንቨስትመንት እንዲሁም  በአከባቢው በሚኖሩ ዜጎች ተረጋግቶ የመኖር መብት ላይም አሉታዊ ተፅእኖው ከባድ ሊሆን እንደሚችል ስለሚገመት ነው። ከዚህ አንፃር ሲታይ በተጠቀሰው አከባቢ ያለው ሁኔታ መሰረታዊ መፍትሄ የሚያስፈልገው ከባድ የፀጥታ ችግር ነው ማለት ይቻላል። በተለይ ደግሞ አሁን ላይ የህወሓት ታጣቂዎችና የጦር አመራሮች ሸሽተው ሱዳን ውስጥ መገኘታቸው ችግሩን ሊያባብስ የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ መገንዘብ ጠቃሚ ነው። የግብፅና የአጋሮቿ ኢትዮጵያን የማተራመስ ፍላጎት ሲጤንም ችግሩን የበለጠ ያወሳስበዋል።

ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ይቻል ዘንድ ፌዴራል መንግስቱ ሊወስዳቸው ከሚችላቸው የማስተካከያ እርምጃዎች ጎን ለጎን የአማራ ክልላዊ መንግስት ተነሳሽነቱን ወስዶ በድንበሩ ጉዳይ ላይ ጥልቅ የሆነ ጥናት እንዲካሄድ ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህን ጥናት በታሪክና በህግ እንዲሁም በህዝብ አሰፋፈር ጥልቅ ሙያ ያላቸው ዜጎች እንዲያካሂዱት ቢደረግ ውጤቱ አመርቂ የመሆን እድል ይኖረዋል። እነዚህ ዜጎች ቢችሉ በትርፍ ጊዚያቸው ያለምንም ክፍያ ካልቻሉ ደግሞ ተከፍሏቸውም ቢሆን ከሱዳን ድንበር ጋ ተያይዞ ያለውን ችግር ከስር መሰረቱ ጀምረው ከታሪክና ከህግ አንፃር እየቃኙ እንዲያጠኑት ማድረግ የመጀመሪያው እርምጃ ነው። ይህን ጥናት መሰረት በማድረግ እንደተባለው ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር መጣሷን መረዳት የሚቻል ከሆነ የአማራ ክልል መንግስት ከሱዳን መንግስት ጋ ሊያደርግ ከሚችለው ሰላማዊ ድርድር በተጨማሪ በተጠናከረ መንገድ ጉዳዩን ለፌዴራል መንግስቱ ማስረዳትና ፌዴራል መንግስቱም አምኖ የራሴ ጉዳይ ነው እንዲል ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የትምህርት ተቌማት የእውቀት ወይስ የፖለቲካ ሜዳ!?

የፌዴራል መንግስት በበኩሉ ከሱዳን ጋር ያለው የድንበር ውዝግብ ጉዳይ የአለም አቀፍ ህጎችን መሰረት አድርጎ ቢቻል በድርድር ካልሆነ ደግሞ በህግ አግባብ እልባት እንዲያገኝ ማድረግ ይጠበቅበታል።  ይህ ሆኖ የሱዳን መንግስት “ከያዛቸው” የኢትዮጵያ ቦታዎች የማይለቅ ከሆነ ኢትዮጵያ ራሷን የመከላከል መብቷን ተጠቅማ ህጋዊ ርምጃ መውሰድ የምትችልበት ሁኔታ ሊታሰብ ይገባል። በዚህ ሂደት የአማራ ክልል መንግስት ሊኖረው የሚገባው ሚና ፌዴራል መንግስቱ አፋጣኝ መልስ እንዲሰጠው በሰላማዊ መንገድ መግፋትና መታገል መሆን ይኖርበታል። ፌዴራል መንግስቱ እገዛ የሚጠይቀው ከሆነ ደግሞ ባለው አቅም መተባበር አገራዊ ግዴታው ይሆናል።

  1. በክልሉ ውስጥ ከሚኖሩ አንዳንድ ከአማራ ብሄር ውጭ ካሉ የብሄርሰብ አባላት ያለ እሰጥ አገባ:

ይህን ጉዳይ በተመለከተ እስካሁን ባለኝ መረጃ መሰረት የሌሎች ብሄር ብሄረሰቦችን እውቅና የሰጠ ክልል ጥራ ብባል ከደቡብ ቀጥሎ ያለው ጥሪዬ አማራ ክልል እንደሚሆን አልጠራጠርም። ይህም ሆኖ ግን በአንዳንዶቹ ብሄረሰቦች ውስጥ ያሉ ሰዎች ጥቅማችን አልተከበረም ወይም ደግሞ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጥያቄያችን በሚገባ አላስተናገደም በሚሉ ምክንያቶች ተፈጥረው በነበሩ ግጭቶች የሰው ህይወት ከመቀጠፉና ንብረት ከመውደሙ በተጨማሪ በክልሉ ነዋሪዎች መካከል ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን አብሮ የመኖርና የመቻቻል ታሪክ ሊያዛንፍ የሚችል ሁኔታ ጥሎ አልፏል።

ይህን ችግር ከመሰረቱ መፍታት የሚቻለው ጥያቄዎች ሲቀርቡ ቅንነት በተሞላበትና ክሴራ ነፃ በሆነ መንገድ ሲሆን፤ እንዲሁም ደግሞ የሚቀርቡ ጥያቄዎች መርህን መሰረት ባደረገ፣ ግልፅነትና ተጠያቂነትን ባሰፈነ እና ሃላፊነት በተሞላበት መንገድ ሲመለሱ ብቻ ነው። በዚህም መሰረት ጥያቄዎች በሚነሱባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ከሁለቱም ወገኖች ያሉ ምሁራን ያገር ሽማግሌዎች የሃይማኖት አባቶችና ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የሚባሉ አካላት እንዲያጠኑት ተደርጎ የመነሻ ሃሳብ ቢቀርብና ጥናቱን መሰረት በማድረግ ደግሞ የክልሉ ም/ቤት ውሳኔ እንዲሰጥበት ቢደረግ የተሻለ ይሆናል። እነዚህን አግባቦች ተከትሎ ክልሉ ጥያቄውን መፍታት ባይችል ወይም ፈቃደኛ ሳይሆን ቢቀር እንኳ ወደ ቃላት ስንዝርና ንትርክ ከመሯሯጥ፤ እንዲሁም አጥፊና ለማንም ጠቃሚ ወዳልሆነ ግጭት ውስጥ ከመግባት ይልቅ የክልሉንም ሆነ የፌዴራሉን ህጋዊ ስርዓቶች በተከተለ አግባብ ጥያቄዎች ቢቀርቡና መፍትሄ የመሻት አቅጣጫ ቢለመድ ሂደቱ ሁሉ የበለጠ ጤናማና ውጤታማ ይሆናል።

ተጨማሪ ያንብቡ:   መሸፈት ደግ ነዉ ለስልጣን ያሳጫል 

ከዚህ ጎን ለጎን የመፍትሄው አካል ሊሆኑ የሚችሉ ነጥቦችንም ልጨምር።  አንደኛ በማንኛውም ጊዜ አንዱ የሌላውን ስሜት ሊጎዳ የሚችል ፀብ አጫሪ የሆነ ንግግርን እንዳያደርግ የሚከለክል ደንብ መመሪያና አሰራር ቢኖር ሁኔታዎች እንዳይጋጋሉ ያግዛል። እነዚህን ደንቦች፣ መመሪያዎችና አሰራሮች ተላልፈው የሚገኙ አካላትም ይሁኑ ግለሰቦች ተጠያቂ እንዲሆኑ ቢደረግ ደግሞ የበለጠ ይሆናል።

ሁለተኛ በማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል የሚቀርቡ ጥያቄዎችና ሃሳቦች የተለያየ ስም እንዳይሰጣቸው ቢደረግ ችግሮች እንዳይሳቀሉ ሊያደርግ ይችላል። ይህም ማለት የሆነ ግለሰብ፣ ቡድን ወይም የህብረተሰብ ክፍል የሻከረውን ጥያቄ ወይም ሃሳብ ባነሳ ቁጥር ከጀርባ እገሌ አለ፣ ሌላ ገፊ ምክኒያት ሊኖር ይችላልና የመሳሰሉ መላምቶች እየተደረደሩ ጥያቄ ያቀረቡትን አካላት ቁስል እንዳይድን እንዲያውም እንዲነፈርቅ የሚያደርግ አካሄድ ሊገታ ይገባል። ከዚህ ይልቅ ገንቢና ሊያቀራርብ የሚችለው መንገድ ጥያቄዎችን ከማንም ጋ ሳያገናኙ ራሳቸውን አስችሎ (On their own merits) ማየትና መልስ ለመስጠት ጥረት ማድረግ ነው።

በዚህ መንገድ ተሂዶ እውነትም ችግሮች ካሉ ቀና፣ በጥናትና በመርህ ላይ የተመሰረቱ መፍትሄዎችን መስጠት ተገቢ ይሆናል። የተባሉት ችግሮች ከሌሉ ደግሞ አለመኖራቸውን በሚያሳይ ሁኔታ በመግለፅ ሁሉም በተገቢው መንገድ እንዲረዳው ማድረግ መተማመንን ይጨምራል የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ። ከኋላ ገፊ ሃይል ወይም አካል አለ የሚል ጥርጣሬ ቢኖር እንኳን ጥናት አድርጎ በተጨባጭ ማስረጃ በማስደገፍ ለህዝብ መግለፅ እንጅ በስሜት መፈረጅ ገንቢና ዴሞክራሲያዊ ሂደት እንዳልሆነ መረዳትም ይጠቅማል። አሁንም በዚህ ረገድ ሊከሰት የሚችለውን ችግር ለመከላከል አሰራር ቢዘረጋለት የተሻለ ይሆናል የሚል ሃሳብም አለኝ።

  1. ስርዓት አልበኝነት፡

ቀበሌም ሆነ ክልል ላይ እንዲሁም በአገር ደረጃ ስርዓት መከበር ያለበት መሆኑ ሁላችንም የሚያስማማ ይመስለኛል። ስርዓት ከሌለ ሰላም የለም። ሰላም ከሌለ ወጥቶ መግባት አይቻልም። ስርዓት በሌለበት አከባቢ ህግ አይከበርም። የህግ አለመከበር በበኩሉ መተራመስን ይፈጥራል። ይህ መተራመስ እንደሰው ሳይሆን እንደ እንስሳ መኖርን ያስከትላል። ከሰወነት የወጣ ባህሪ ደግሞ አገርን በታትኖ ህዝብን ያፋልሳል።

እንዳለመታደል ሆኖ ግን የስርዓት አልበኝነት ችግሮች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሲከሰቱ ቆይተዋል። አማራ ክልልም ቢሆን በተለያየ መንገድ የሚገለፁ የስርዓት አልበኝነት ችግሮች ይስተዋሉ እንደነበረ እናስታውሳለን። እንዲያውም በአንድ ወቅት ስርዓት አልበኝነቱ የከፋ ጫፍ ደርሶ ስለነበር ክልላቸውንም ሆነ ሃገራቸውን ሊጠቅሙ ይችሉ የነበሩ ታጋዮች ህይወታቸውን አጥተዋል።

በእርግጥ አሁን ላይ ብዙ ነገሮች የተስተካከሉ የሚመስልበት ሁኔታ አለ። ህግና ስርዓትም በተነፃፃሪነት እየተከበረ እንደሆነ የሚያሳዩ ምልክቶችም ብዙ ናቸው። ይሁንና ሁኔታዎች ወደኋላ ተመለሰው የክልሉን ፀጥታ እንዳያውኩ የተጀመረው የህግ የበላይነትን የማስከበር እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ጎን ለጎንም የፍትህ አካላት ስለህግ የበላይነት መከበር አስፈላጊነት ትምህርት ቢሰጡ ስርዓትን በማስከበር ረገድ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ ብየ አስባለሁ።

 

ይቀጥላል

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.