” ሀገር መምራት በግ እንደመጠበቅ አይቀልም ” አብርሃም አለኸኝ ጥሩነህ

abrhamአጼ ኃይለስላሴ ስዩመ እግዚአብሄር ዘእምነገደ ይሁዳ፤ ንጉሰ ነገስት ዘ ኢትዮጵያ እንደተናገሩት።
አምባሳደር ብርሀኑ ድንቄ በኢትዮጵያ ፖለቲካ አንጻራዊ ምቾት ማግኘት ያልቻሉ የቅኔ ሰው ነበሩ። ታማኝ ፣ ታታሪ ፣ ድሀ
ተበደለ ፍትህ ተጓደለ ብለው አብዝተው የሚጮሁ አዋቂና ተመራማሪም ነበሩ። ” አልቦ ዘመድ / ቄሳርና አብዮቱ ” በሚል ባለሁለት መልክ ርዕስ ባበጁለት መጽሀፋቸው ስለ ንጉሰ ነገስቱ ገራምነት ፣ አዋቂነት ፣ አድማጭነት ፣ ፍትሀዊ ውሳኔ ሰጭነት ተርከውልናል።
” ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚል ስያሜ በወጣለት ባለጌ ወንበር ተቀምጠው ኢትዮጵያንና የአዲስ አበቤን ሰው ይመሩ የነበሩ የዘመኑ ሰው ደጋግመው ሲረብሿቸው ንጉሰ ነገስቱ ፊት እየቀረቡ ይሞግቱና መፍትሔ ያገኙ ነበር። አምባሳደር ብርሀኑ ድንቄ ከመጮህ ንጉሰ ነገስቱ መፍትሄ ከመስጠት አልተቆጠቡም።
ይሁን እንጂ ” የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል” እንዲሉ ደጋግመው የሚከሷቸው ሰውና አምባሳደሩ የአዲስ አበባ ከንቲባና ፀሀፊ ሆነው ተገናኙ። በዚህ ጊዜ አምባሳደር ብርሀኑ ድንቄ የሰውየው አይን ያወጣ ሙሰኝነት እየከነከናቸው ቢቸገሩ እንደልማዳቸው ማጀስቲ ፊት ቀርበው መደመጥ ፈለጉ። ጥያቂያቸው ተቀባይነት አግኝቶ ንጉሰ ነገስቱ ፊት ቀርበው ጉዳዬቸውን አስረዱ። የአምባሳደር ቅንነትና የሰውየው መሰሪነት በንጉሰ ነገስቱ በኩል የተሰወረ አልነበረም።
ይሁን እንጂ ንጉሰ ነገስቱ ሁሉን ቻይ አልነበሩም። ምንም እንኳ የአምባሳደርን ቅንነት በውል ቢረዱም ፍጹም ስልጣናቸውን ተጠቅመው የአዲስ አበቤውን ከንቲባ ዳግም ማስቀየም አልፈለጉም።
ታዲያ ከብርሀኑም ጋር ቀረቤታ ስላላቸው ግራ ተጋቡ። በመጨረሻ ግን ” ብርሀኑ፤ አገር መምራት በግ እንደመጠበቅ አይቀልም ” ሲሉ ለዛሬ ጦማሬ መነሻ የሆነችኝን ተግሳፅ ሰነዘሩ። አምባሳደሩም እያዘኑ ወደመጡበት ተመለሱ።
እኔ የምለው የወገኖቻችን ሞት የማይገደን ከንቱዎች ነን እንዴ ? በወንድሞቻችን ሞት የማናዝን ፣ የማናለቅስ ፣ የማንነፈርቅ ፣ ደማችን የማይፈላ እርባና ቢሶች ነን እንዴ ? አገር መምራትን በግ ከመጠበቅ አሳንሰው መመልከት የሚፈልጉ ጦማርያን በደም ፍላት የሚነግሩንን ተግሳጽና ዘለፋ የማንረዳ ቀርፋፋዎች አይደለንም። አስተዳደጋችንም ቢሆን የህዝባችንን ህመምና ቁስል በቅጡ እንድንረዳ ያግዘናል እንጂ እንድንለግም አያደርገንም። በጥቅሉ በአማራ ወግ ተኮትኩተን ያደግን የልጅ ጉዳት የሚጎዳን ፣ የእናትና የአባት ሞት የሚሰቀጥጠን ፣ ልጀ ልጀ ፣ ወንድሜ ወንድሜ ፣ እህቴ እህቴ ፣ እናቴ እናቴ ፣ አባቴ አባቴ ብለን ማልቀስ የምናውቅ ፣ ደረት በመድቃት ፣ ሙሾ በማውረድ ለሟች ወገንና ለሟች ቤተሰብ የሚሰጥ አክብሮት እንደሆነ የምንረዳ በአማራ ባህል ያደግን የአማራ የቁርጥ ቀን መሪዎች ነን።
የሟች አስከሬን ግብአተ መሬት ባልተፈጸመበት እህል ውሀ የማንቀምስ፣ በሟች የቀብር ስነስርአት ላይ ተገኝተን አፈር ዘግነን ሟች ወደአረፈበት የመቃብር ጉድጓድ የምንበትን ፣ በሟች ቤተሰቦች ፊት ቁመን ጎንበስ ቀና እያልን ፣ እጃችን ከትክሻቸው አስጠግተን መፅናናትን የምንመኝ ፣ ሥሦት ፣ አስራ ሁለት ፣ ሠላሳ ፣ አርባ ፣ መንፈቅ ሙት አመት እያልን ለሟች ነፍስ ክብር የምንሰጥ ፣ እየተመላለስ ለእጓለ ሙታንና ለመበለቷ የሞራል ድጋፍ የምንሰጥ በህይወት ላለ ሰው ቀርቶ ለሟች በድነ ስጋ ፣ ነፍስና ቤተሰብ ኃላፊነት በሚወስድ የአማራ ማህበረሰብ ጥብቅ አጥር ውስጥ ያደግን መሪዎች ነን።
በመተከል፣ በኦሮምያ ክልልና በሌሎች ክልሎች በየቀኑ የሚሞቱ ወገኖቻችን የማያሳስበን ከየትም የተሰባሰብን በአማራ ህዝብ ጫንቃ ላይ የወደቅን ወፍ ዘራሾች አይደለንም። ወፍ ዘራሽ ለምንመስላቸውና ወፍ ዘራሽ ሊያደርጉን ለሚሞክሩ የብዕር ተመጻዳቂዎችም ከበቂ በላይ መልስ አለን። ሞተንም ቢሆን ህዝባችንን ነጻ ለማውጣት ፣ የህዝባችንን ስነልቦና ከፍ ለማድረግ ፣ ስብራቱን ለመጠገን መክፈል የምንችለውን ሁሉ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን። ይህንን ስናደርግ ብዕራችንን ኢትዮጵያ ውስጥ አካላችንን አውሮፓ ፣ አሜሪካ ፣ ደቡብ አፍሪካ አላደረግንም። ትላንትም ከሞት ጋር ተፋጠን ለህዝባችን ወግነናል። ዛሬም ከህዝባችን ውጭ የምናስቀድመው አጀንዳ የለንም።
እርግጥ ነው የአሁኗ ኢትዮጵያ ከንጉሰ ነገስቱ ኢትዮጵያ ትለያለች። የትላንቱ ሙሌት ዛሬ ጎድሏል። የትላንቱ ጎደሎ ዛሬ ሞልቷል። ህዝብ መምራት ግን ያውና ተመሳሳይ ነው። ማጀስቲ እንዳሉት ” ህዝብ መምራት በግ እንደመጠበቅ አይቀልም ” ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከጊዜ ወደጊዜ እየከረረ፣ እየተወሳሰበ እና እየተወጠረ እንጂ እየረገበ አይመጣም። ምክንያቱም የትህነግ ፍርስራሾች ፍርስራሽ ብቻ ሆነው አይቀሩም። የእነሱ መፈራረስ እየተቃረበ ሲመጣ ላለመፈራረስ የሚያደርጉት መፍጨርጨር እኛን ደግሞ ደጋግሞ ማንጨርጨሩ አይቀርም። ይኸም ቢሆን ለጊዜው ይወሳሰብ እንጂ መስተካከሉ አይቀርም።
ችግሩ የአብርሀም ሊንከንን ያህል ፖለቲካውን አውቆ በቁርጠኝነት መምራት ያስፈልጋል።
የጥቁሮች መብት ይከበር ሲል እንዴት ተደርጎ የሚል የኃይል አሰላለፍ እንዳለ መረዳት ያስፈልጋል። የባርያ ንግድን ስትቃወም በባርያ ንግድ ዳጎስ ያለ የካፒታል ክምችት የሚሰበስቡ ኃይሎች በሌላ መስመር ግጭት መቀስቀሳቸው ይታወቃል። በመጨረሻም ህልሙን መግደል ባይችሉ ፕሬዝዳንት አብርሀም ሊንከንን በጥይት ገድለውታል።
ህዝብ መምራት በባህርይው አስቸጋሪ ቢሆንም በለውጥ ጊዜ የሚኖረው የአመራር ባህርይ ደግሞ የበለጠ አስቸጋሪ ይሆናል። ትህነግ ፣ ኦነግና የሰብአዊ አእምሮ የእድገት ደረጃውን ገና ያልጨረሰው የቤጉህዴን አማፂ ቡድን በሀገራዊ የለውጥ ነፋስ ላይ ሲጨመርበት ትግላችንን ከድጡ ወደማጡ አድርጎታል። ይሁን እንጂ ትህነግ በኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ወደፍርስራሽነት ተቀይሯል። ለመከላከያ ሰራዊታችን ፣ ለልዩ ኃይላችን ፣ ለሚሊሻችንና ለመላው ህዝባችን ምስጋና ይድረሳቸውና ትህነግን ወደፍርስራሽነት ከቀየሩ በኋላ በምንም ተአምር ርዝራዥ ፍርስራሾች ሊያሸንፉን አይችሉም።
አንድ ነገር ግን መታወቅ አለበት። የትህነግ ፍርስራሾች በውለታ የሚታሰሩ፣ በምስጋና የሚሳከሩ አይደሉም። ስላመሰገናቸው ለህዝባችን ፈጽመው አይራሩም። ስለረግማናቸው ህዝባችንን አይጨፈጭፉም። ጨፍጫፊነት ፣ አራጆነት ፣ ሰው በላነት (Cannibalism) ቃል ኪዳን የፈጸሙበት ባህርያቸው እንጂ እኛ ስለተናገርን ፣ ስለፃፍን ፣ መግለጫ ስለደረደርን ጉልበት የሚጨምሩ የርህራሄ ነቁጥ የተፈጠረባቸው ሰዎች አይደሉም። ስለሆነም እንደወትሮው ሁሉ እየተመካከርን የምጽአት ቀናቸውን ማፈጠን ይኖርብናል።
ትህነግ፣ ኦነግም ሆነ ሰው በላው የቤንሻንጉል ጭራቅ ቡድን የአማራ ህዝብ ዘላለማዊ ጠላት ይሁን እንጂ የኢትዮጵያም ተፈጥሯዊ ጠላት ነው። ይህ የጋራ ጠላት በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የጋራ ትብብር ዳግም ላይነሳ መቀበር አለበት። ለዚህ ደግሞ የፌዴራል መንግስቱን ጨምሮ ሁሉም ክልሎች በጋራ መረባረብ አለባቸው። ቤንሻንጉል ስለቀረበንና ሰለተጎራበትን ኃይል ይዘን እንግባ ብንል መግቢያ በር የሌላቸው የህዝባችን መዳረሻ የሆኑ በብዙ መቶ ኪሎሜትሮች ሬድየስ ውስጥ የሚገኙ አካባቢዎች ብዙ ናቸው።
መውጫ መንገድ!
1. ውስጣዊ አንድነታችንን እንጠብቅ ። መደጋገፍና መተባበር ለህዝባችንና ለክልላችን አጠቃላይ እድገት የምናበረክተው ዝቅተኛው መስዋዕትነት አንጂ አንዳችን ለሌላችን የምንሰጠው የማይተካ አበርክቶ (exclusive gift) አይደለም።
በዚህ አገር የፖለቲካ ሁኔታ እርስ በእርስ የምንተጋገዘው ችሮታ ለመስጠትና ችሮታ ለመቀበል መሆን የለበትም። ለጋራ አገራችንና ህዝባችን ብለን መናበብ እየተገባን እርስ በእርስ መናበብን ለገዥው ፓርቲ የተደረገ ዳረጎት አድርጎ በመውሰድ ጥፋት በተከሰተ ቁጥር የወዮላችሁ ዛቻ ማዥጎድጎድ “የማይተማመኑ ባልንጀሮች በየወንዙ ይማማላሉ ” አይነት ተራ ጉድኝት ነው የሚሆነው።
ሁሉም ዜጋ በአገሩ ጉዳይ ያገባዋል። የአገሩም ሆነ የህዝቡ ባለቤት ነው። አንዳችን ለሌላችን ባለቤት እንጂ ጌታና ሎሌ መሆን የለብንም። ጌታ ስንሆን እንናጥጣለን ፤ ሎሌ ስንሆን እንፈረጥጣለን። መናጠጥም መፈርጠጥም ባለቤትን አይተካም። ስለሆነም በባለቤትነት ስሜት መተጋገዝ ለህዝባችንም ለክልላችንም ሊተካ የማይችል ዘላቂ ትሩፋት አለው።
2. የዜጎችን ሰብአዊ መብት (በህይወት የመኖር መብት) አክብሮ ማስከበር ዝቅተኛው የመንግስት ተፈጥሯዊ ግዴታ ነው። የኛ ሚና መንግስት ግዴታውን በሚወጣበት ሂደት የሚታዩ ክፍተቶችን እንዲያርምና እንዲያስተካክል ገፊ አቅም የመሆንን ኃላፊነት ሳንሰስት እንጠቀም።
በየትኛውም አለም መንግስት ምሉዕ ሊሆን አይችልም። በሁሉም አካባቢ ወቅታዊና ቅጽበታዊ አደጋዎች ያጋጥማሉ። የኛን ሀገር ለየት የሚያደርገው አመታት የፈጀ የዜጎች ህይወት መቀጠፍ ነው። በተለይም አማራን ለይቶ የማጥቃት ዘመቻ ዘግናኝ በሆነ መልኩ መቀጠሉ በእርግጥም ያማል። እንደአመራር አይደለም እንደሰው ለመኖር አያስመኝም።
በዚህ ጉዳይ የአማራ ክልል ብቻውን የቱንም ያህል ቢደክም የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አይቻልም። በክልሉ ለሚታይ የሰላምና ጸጥታ ችግር የክልሉ አመራሮች ሙሉ ኃላፊነት መውሰድ አለባቸው። ወሰን ተሻጋሪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አማራዎችን በማንነታቸውና በሚከተሉት እምነት ለይቶ የሚፈጸምን ጥቃት ሁሉም ክልሎችና መላ ኢትዮጵያውያን በጽናት ሊታገሉት ይገባል። በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ጥቃት የዘር ማጥፋት ወንጀልና የጅምላ ጭፍጨፋ የኢትዮጵያ መለያና ዋነኛ መታወቂያ ሆኖ መቀጠል የለበትም። ይህ ሁኔታ ባለበት ከቀጠለ ለብልጽግና ፓርቲም ሆነ ለገዥው ፓርቲ ትልቅ ሽንፈት ነው።
በክልሎች መካከል እየታየ ያለው የብሽሽቅ ፖለቲካ ስንጥቅ ሊደፈን የሚችለው ኃላፊነት የሚሰማው ውሳኔ እስከተወሰነ ድረስ ብቻ ነው። ቃላትን ከሰው ህይወት መጥፋት በላይ በሚመነዝር የፖለቲካ ገበያ ውስጥ ቀውስ መቆጣጠር የሚችል ገለልተኛ የአመራር አቅምና አሰላለፍ ይኖራል ብሎ ማሰብ ከብሳና ዛፍ አፕል ለመቁረጥ መሞከር ነው። ስለሆነም የፌዴራል መንግስት የቀውስ ጊዜ አስቸኳይ አመራር ካላረጋገጠ በስተቀር ማንነትን ለይቶ የሚፈጸም ጥቃት ድህረ ትህነግ አገሪቷን የማትወጣበት ቅርቃር ውስጥ ሊያስገባት እንደሚችል ማወቅ አለበት።
3. ብልጽግናን ከኢህዴግ ፍጹም የተሻለ ፓርቲ በማድረግ በህገመንግስትና በፌዴራሊዝም ሽፋን እንዲረዝም የሚፈቀድለት ስንፈተ አመራር እንዳይኖር ማድረግ ያስፈልጋል።
ብልጽግና የወርቃማ መርሆዎች ባለቤት መሆኑ ላይ ጸሀፊው አይጠራጠርም። በፕሮግራም ፣ በመተዳደርያ ደንብ ፣ በርዕዮተ ዓለምና በስትራቴጂ ደረጃ ፍጹም እንከን የለበትም ባይባልም ኢትዮጵያንና ህዝቧን የሚመጥን መሰረተ ሀሳብና የወትሮ ዝግጁነት ባለቤት ነው። ይሁን እንጂ ሀገርና ህዝብ መምራትን በግ እንደመጠበቅ አቅለው የሚያዩ ፣ ከዙርዮሽ የፖለቲካ አዙሪት መላቀቅ የማይፈልጉ ፣ በስንፈተ አመራር ባህል ተተብትበው በቀይ መስመር የለውጥ ተቃርኖ ውስጥ የሚዳክሩ ፣ በብልጽግና ውስጥ እየኖሩ የብልጽግናን አስተሳሰብ እንደጦር የሚፈሩ ፣ የመደመርን ፍልስፍና ከተራ የሂሳብ ስሌት በዘለለ መረዳት የማይፈልጉ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በወሰነላቸው የሀሳብ መስመር እየማሉና እየተገዘቱ ባላመኑበት የብልጽግና ጎዳና ተደባልቀው መጓዝ የሚፈልጉ የኔ ቢጤ ካድሬዎች ላይ ቆፍጠን ያለ እርምጃ መወሰድ አለበት። ድህረ ትህነግ በሚኖረው አገራዊ የፖለቲካ ሁኔታ ብልጽግና የትህነግ ፍርስራሾችን ለቃቅሞ ራሱን ማጥራት ካልቻለ ለዜጎች አጠቃላይ ክብር ለሀገር ብልጽግናና ለህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝም ቆሚያለሁ የሚለው ፖለቲካዊ ትልም የሆነ ቦታ ተንገራግጮ ይቆማል። ምንአልባትም እንደአገር በጽናት መቀጠል የሚቻልበትን ምርጥ አጋጣሚ መጠቀም አለመቻል ለብልጽግና ውርደትም ቅሌትም ነው።
ኢትዮጵያንና ህዝቧን ፈጣሪ አብዝቶ ይባርክ !!!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.