ሽሬ ያፈራችው ዳግማዊ ሀየሎም!

HH
የአገርንና ህዝብን ጡት ከነከሱና ካስለቀሱ ጁንታዎች በተቃራኒ የትግራይ ምድር ለአገርና ለህዝብ የታመኑና ህይወታቸውን ሳይሳሱ የሚሰጡ ጀግኖችን ማፍራት ታውቅበታለች። ለኢትዮጵያና ለክብሯ ሲሉ ውድ ህይወታቸውን የሰዉና የእነአሉላ አባነጋን ፈለግ የተከተሉ ብዙ ጀግኖችም ከትግራይ ማህጸን ፈልቀዋል፤ አሁንም በመፍለቅ ላይ ናቸው።
ይህን ጉዳይ ስናነሳ በቅድሚያ ወደ አዕምሯችን ከሚመጡት አንዱና ቀዳሚው በጁንታው ሴራ ህይወቱን የተነጠቀው ሜጀር ጀኔራል ሓየሎም አርአያ ነው። ለዴሞክራሲና ለህዝቦች አኩልነት በተደረገ ትግል አኩሪ ገድል የፈጸመውና በብዙዎች ልብ ውስጥ በጀግነንት ታሪኩ የተጻፈው የሽሬው ሜጄር ጀኔራል ሓየሎም አርአያ፤ የሃሳብ ልዩነት ስላንጸባረቀ ብቻ ግፍና ሴራ ኑሯቸው ባደረጉት የጁንታው አባላት በግፍ ህይወቱን እንደተነጠቀ ብዙዎች የሚናገሩት ሀቅ ነው።
ይህን በቅርበት ከሚያውቁት እና ጉዳዩን አስመልክቶ ሃሳባቸውን ለአዲስ ዘመን ከተናገሩት መካከል አቶ ሊላይ ኃይለማርያም አንዱ ናቸው። አቶ ሊላይ በአንድ ወቅት ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ስለ ግድያው ሲያስረዱ፣ “ሓየሎምን ጁንታው እንደገደለው እርግጠኛ ነኝ። ሓየሎም በሰራዊቱ በጣም ተወዳጅ ከመሆኑም በላይ በአንዳንድ ጉዳዮች ከእነሱ ጋር አይስማማም ነበር። በትጥቅ ትግሉ ወቅት በረሃ ላይ እንዳይገድሉት ከአጠገቡ ሰው ስለማይጠፋ አልተመቻቸውም። በተገደለበት ወቅት ከእሱ በታች ያሉ ጄኔራሎች እንኳን በጥበቃ ነበር የሚሄዱት። እሱ ግን ጥበቃ አልነበረውም። እናም እነዚህን ሁሉ ስታይ እና ማን ገደለው ብለህ ስትጠይቅ እነሱ እንደሆኑ ትረዳለህ” ብለው ነበር።
አገራችን ኢትዮጵያ ጀግኖችን ለመውለድ ማህጸነ ለምለም ናትና ዛሬም የሓየሎምን የጽናት ታሪክ የደገመ አንድ ጀግና ከሽሬ አፍርታለች። ይህ ጀግና ሃምሳ አለቃ ሓየሎም ነጋ ይባላል። ሽሬ ዞን አዲዳዕሮ በተባለ የትግራይ አካባቢ የተወለደው ሃምሳ አለቃ ሓየሎም፣ የመከላከያ ሰራዊት የ23ኛ ክፍለጦር አባል ነው። ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ሓየሎምና ጓደኞቹ በሱዳን ጠረፍ ሁመራ አካባቢ የሀገር ድንበር በመጠበቅ ላይ እንደነበሩያስታውሳል። ሀገር አማን ብለው አረፍ ባሉበት ምሽት ግን ጁንታውና ተላላኪዎቹ ጥቃት በመፈጸም እርሱንና ሌሎች የሰራዊቱ አባላትን አፍነው ወሰዱ።
ከሁመራ ሉግዲ ወደ ሽሬ እና አክሱም ከተሞች ታፍነው በሚወሰዱበት ወቅት ሓየሎምና ሌሎች የሰራዊቱ አባላት መከራቸውን ሲያዩ እንደነበር አይዘነጋውም። ምግብና መኝታ እንኳን ሳይመቻች በአድዋ እና በጉዊሃ አካባቢዎች በአንድ ክፍል ታጉረው ቆይተዋል። ከዚህ ባለፈ ከቦታ ወደቦታ በተሽከርካሪ ሲያንቀሳቅሷቸው ሰው በሰው ላይ አነባብረው ያጓጉዙ እንደነበር ሓየሎም በኀዘን ያስታውሰዋል።
ለ21 ቀናት በተለያዩ አካባቢዎች ታፍነው ሲቆዩ በየቀኑ አንድ አንድ የማታጠግብ ዳቦ እና አልፎ አልፎ ገንፎ እየበሉ ህይወታቸውን ለማትረፍ መታገላቸውንም ነግሮናል። የጁንታው ቡድን አባላት የትግራይ ተወላጆችን አስገድደው በመውሰድ ለራሳቸውም እኩይ ዓላማ እንደሚያሰልፉ ሓየሎም አጫውቶናል።
እርሱ ግን አገሩን መክዳት ስለማይፈልግና በኢትዮጵዊነት ላይ ጽኑ አቋም ስለነበረው ከጁንታው ታጣቂዎች ጋር ላለመሰለፍ የትውልድ ቦታውን ቀይሮ የደቡብ ተወላጅ ነኝ በማለት ለአፋኙ ቡድን ታጣቂዎች ተናገረ። ይህን ዘዴ የተጠቀመውም ከመከላከያ ሰራዊት ጓዶቹ ጋር አብሮ ለመቆየት መሆኑን ይናገራል።
ሓየሎም የትግራይ ተወላጅ መሆኑን በማሳወቅ ብቻ ከታፈኑት መካከል መውጣት እንደሚችል ቢያውቅም፤ አብረውኝ ከበሉ እና ከጠጡ ጓደኞቼ የሰራዊት አባላት አልለይም ብሎና አብሯችው እንደሚሆኑ እሆናለው የሚል ውሳኔ ላይ መድረሱን ይናገራል። በሌላ ጎኑም ታላቅ ክቡር ነውና ሀገር መክዳትን ፈጽሞ አልመረጠም።
በአፈናው ወቅት ጓዶቹን አይዟችሁ ከሞትንም አብረን ነው የምንሞተው እያለ ያበረታታ እንደነበር አይዘነጋውም። በወቅቱ የጁንታው ታጣቂዎች አብረህ ከእኛ ጋር ሂድ ቢሉኝ እንኳን ዓላማ ስለነበረኝ ግደሉኝ እንጂ አይሆንም እንደምላቸው እርግጠኛ ነበርኩም ይላል።
እንደሌሎች አይደለሁም ክደው የሄዱ ቢኖሩም እኔ ሰራዊቱን ክጄ አልሄድም፤ ሁለት መለዮ አልለብስም ብዬ ነው ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጋር የቆየሁት ማለቱን ሓየሎም ነገሮናል። ጓደኞቼንና አገሬን አልዋጋም የሚል የጸና አቋም እንዳለው የነገረን ሃምሳ አለቃ ሐየሎም፤ እኔ ሀገሬ ኢትዮጵያ ነችና ለሀገሬ ክብር ብዬ ነው የተነሳሁት፤ ለብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቆምኩ እንጂ፤ ለአንድ የጁንታ ቡድን ፍላጎት ብቻ አይደለም የሚል የጸና ሃሳብ በአዕምሮው መያዙንም ነግሮናል።
በመጨረሻም የመከላከያ ሰራዊት ደርሶ የጁንታው ታጣቂዎች ላይ እርምጃ ሲወስድ አፋኞቹ ሓየሎምን እና ሌሎች የሰራዊት አባላትን ከተከዜ ወንዝ ድንበር አካባቢ ወስደው ለቀቋቸው። ሓየሎምም ከጓደኞቹ ጋር ወደአማራ ክልል በእግሩ ተሻገረ። በአማራ ክልል የነበረው አቀባበል ጥሩ ነበር፤ ምግብ፣ አልባሳት እና የሞራል ድጋፉም አስደሳች እንደነበር ሓየሎም በኩራት ይነገራል።
በአስቸጋው ቆይታ ወቅት የሰራዊቱ አባላት ሓየሎም ንጹህና ከእኛ ጋር አብሮ ሲታገል የቆየ ታማኝ ወታደር ነው በማለት በሙሉ ልብ አብረውት እንደተሰለፉ ያስታውሳል።
በጁንታው ቡድን አማካኝነት ታፍነው የቆዩ የሰራዊቱ አባላት ጎንደር ላይ ተመልሰው ከተደራጁ በኋላ፤ ዳግም ወደግዳጅ ሲሰማሩ ሓየሎምም በትልቅ የሀገራዊ ስሜት አብሮ ወደትግራይ ክልል ተመለሰ። ጓደኞቹ አድናቆታቸውን በመግለጽ ያንተ ታማኝነት እና ተወዳጅነት ከፍተኛ ነውና፤ የያዝከውን መስመር ቀጥልበት ብለው በምላሹ ማበረታቻ ሰጥተውታል።
“እኔ ህዝብን ወክዬ ቃለመሃላ የገባሁለት ጉዳይ አለኝ፤ ብሔር ብሔረሰቦችን በአጠቃላይም ኢትዮጵያን መጠበቅ አለብኝ ብዬ ነው ቃለመሃላ የገባሁት። በማንም ይሁን በማን ላይ በሀገሬ ኢትዮጵያ ጉዳይ ህግን የማስከበር ተግባር ሲያጋጥመኝ ወደኋላ አልልም። አሁንም ቢሆን ከጓደኞቼ ጋር ግዳጄን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ሀገራችንን የበለጠ ሰላም እንደምናደርግም ተስፋ አለኝ” በማለት ለሀገሩ ያለውን ታማኝነት በገሃድ አሳይቷል።
ከምንም ነገር ቅድሚያ ለአገር የሚለው የሽሬ ዞን ተወላጁ ሓየሎም ነጋ፤ ከአጥፊው ቡድን የሴራ ፖለቲካ ይልቅ ለህዝብ መወገኑ ብቻ ሳይሆን ለህይወቱ ሳይሳሳ ሀገሩን ያስቀደመ የሰራዊቱ አባል መሆኑንንም ጭምር በዳግማዊ ሓየሎምነቱ ሥራው ሲያስታውሰው ይኖራል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 7/2013

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.