በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አማራዎች ላይ ጥቃቱ በርትቷል

131889150 4002260809806985 4086047162538332254 n
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ውስጥ ነዋሪ የሆኑ የአማራ ተወላጆች፦ «ምንነቱን ባላወቅንበት ኹኔታ አማራ በመሆናችን ብቻ እየተገደለን ነው፤ ጭንቀት ላይ ነው ያለነው» ሲሉ ለአማራ መገናኛ ብዙኃን ገለጡ። ነዋሪዎቹ ጥቃት የሚደርስባቸው በዋናነት፦ «በካራ እና በገጀራ» እንደሆነም ተናግረዋል። ጥቃት የሚያደርሱት ደግሞ የጉሙዝ ታጣቂዎች እንደሆኑ ነዋሪዎቹ አክለዋል። የቀበሌ ሚሊሺያ ብቻ ነው ያለው እነሱም ስጋት ላይ ናቸው ብለዋል።
ተደጋጋሚ ጥቃቱ በተለይ በአማራ እና በአገው ተወላጆች ላይ እንዳነጣጠረም ነዋሪዎች ገልጠዋል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞን ቡለንና ድባጢ ወረዳ ነዋሪዎች ታጣቂዎች በተደጋጋሚ ጥቃት እያደረሱባቸው መሆኑን ከትናት በስትያ ዶይቸ ቬለ (DW) መዘገቡ ይታወሳል።
በተያያዘ ዜና፦ የሰላም ሚንሥቴር፦ «በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን የዕለት ደራሽ ርዳታ እየተዳረሰ ይገኛል» ሲል በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሩ ገልጧል። የሠላም ሚንስቴር እንዳለው ከሆነ፦ በመተከል ዞን «ማንዱራ፣ ጉባ፣ ድባጤ፣ ጋሊሴ፣ ቡለን፣ ዳንጉር እና ወንበራ ውስጥ ለተፈናቃዮች መጠለያ ሰፈሮች ተመስርተው የዕለት ደራሽ ርዳታ በመከፋፈል ላይ ይገኛል።»
131424582 4002889136410819 6297393835317455964 n
በቤንሻንጉል ክልል በጉሙዝ ሸማቂዎች እና በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)ታጣቂዎች እንደተፈናቀሉ የተነገረላቸው ከ30 ሺህ በላይ የአማራ ተወላጆች አስቸኳይ ርዳታ እንዲደረግላቸው መጠየቃቸውን የአማራ መገናኛ ብዙኃን ዛሬ ዘግቧል።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ በተደጋጋሚ ስለሚደርሰው ጥቃት ከነዋሪዎች እና ከሚመለከታቸው አካላት ተጨማሪ መረጃ ለማሰባሰብ ጥረት እያደረግን ነው።
DW

1 Comment

  1. ካንጀት ካለቀሱ ይባላል፡፡ እንደው የመተከልን ችግር መንግስት መቆጣጠር አቅቶት ነው፡፡ በየተራ በየክልሉ ከሚያበጣብጡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ለመስጠት አይሞከርም፡፡

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.