አብን በመላ አገሪቱ የሚገኙ የዞንና የወረዳ አመራሮቹን አቅም መገንባት የሚያስችል ሰፊ ሥራ እየሰራ መሆኑን ገለፀ

Abnየአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ከአማራ ክልል ለተውጣጡ 275 የወረዳና የዞን አመራሮቹ ታኅሳስ 3 እና 4 ቀን 2013 ዓ.ም ለሁለት ቀናት በባሕርዳር የአማራ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት የሰጠውን ስልጠና አጠናቋል።
የሥልጠናው ዓላማ በአማራ ክልል በወረዳና በዞን የሚገኙ የንቅናቄው አመራሮች በድርጅታዊ ርዕዮተዓለም፣ በወቅታዊ ፖለቲካና የትግል ስትራቴጅ ዙሪያ መሰረታዊ ግንዛቤና የተሻለ መረዳት ለመፍጠር ብሎም ንቅናቄው ከምሥረታው ጀምሮ እስካሁን የተጓዘባቸውን የፖለቲካ ትግሎችን በመገምገም በቀጣይ ግለቱን የጠበቀ ትግል ለማድረግ፣ አመራሩ የድርጅቱን ተልዕኮ በተሻለ መንገድ እንዲፈፅም ብሎም ወቅቱ በሚጠይቀውና ሕዝባችንን በሚመጥን ቁመና ልክ እንዲገኝ ለማስቻል መሆኑን የአብን ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላ ተናግረዋል።
አቶ በለጠ አክለውም አብን የአማራ ሕዝብን መሰረታዊ ጥያቄዎች ለማስመለስና አንድነቷ የተጠበቀ አገር ለመገንባት በሚያደርገው መንታ ትግል ስልጡን ፖለቲካ የሚያራምድ መሆኑን በመጥቀስ መሰል ስልጠናዎች በየደረጃው ለሚገኘው አመራር ወጥ በሆነ መንገድ በመስጠት የወቅቱን አገራዊ ፖለቲካ ታሳቢ ባደረገ መልኩ የአብንን ትክክለኛ ገፅታ ለሕዝቡ በማሳየትና በማንቀሳቀስ የአማራ ሕዝብን ትግል በሰከነ መንገድ ለማካሄድ ሚናው የጎላ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
በሥልጠናው የተካፈሉ አመራሮችም ስልጠናው የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታና የኃይል አሰላለፍ በሚገባ ተረድቶ ድርጅት ዘለል አማራዊ ትብበርን በማሳደግ ወጥ የተግባርና የአመለካከት አንድነት በመፍጠር የአማራን ሕዝብ የዘመናት የእኩልነትና የፍትኅ ጥያቄዎችን ለማስመለስ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልፀዋል።
በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአብን ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላ ሥልጠናው ንቅናቄው በብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚና በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ የሚሰራቸውን የፖለቲካ ስራዎች የወረዳና የዞን አመራሩ በምን መልኩ ተረድቶ ሥራዎችን እየሰራ እንዳለና በቀጣይ በምን መልኩ መስራት እንዳለበት ግንዛቤ የፈጠረ ነው ብለዋል።
አክለውም የአብንን አቋሞች ለአባላቱ፣ ለድርጅቱ ደጋፊዎች እና ለምልአተ ሕዝቡ ግልጽነት ለመፍጠር የወረዳና የዞን አመራሮች ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመረዳት በመላ አገሪቱ ለሚገኙ አመራሮቹ ቀጣይነት ባለው መልኩ የተለያዬ የአቅም መገንቢያና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።
አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ፥ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!

1 Comment

  1. “አቶ በለጠ አክለውም አብን የአማራ ሕዝብን መሰረታዊ ጥያቄዎች ለማስመለስና አንድነቷ የተጠበቀ አገር ለመገንባት በሚያደርገው መንታ ትግል ስልጡን ፖለቲካ የሚያራምድ………..”። …..”ስልጡን ፖለቲካ” የሚለው ይሰመርበታል፡፡
    አብኖች፤ የልጅ አዋቂዎች! ደጋፊያችሁ ባልሆንም፤ “እኛ ተጎድተን ኢትዮጲያ ትትረፍ” ብላችሁ፤ ጽንፈኞች “ከመስከረም በኋላ መንግስት የለም!” ብለው ህዝቡን ግራ ባጋቡበት ወቅት የምርጫውን መራዘም በመደገፍ የወሰዳችሁት አቋም ሁሌ ሲታወስ ይኖራል፡፡ አሁን በትህነግ ላይ ለተገኘው አንጸባራቂ ድልም የእናንተ አስተዋጾ ከጅማሮው እንዳለበት ያለምገንዘብ ድንቁርና ይሆናል፡፡ በስልጡን ፖለቲካችሁ ግፉበት!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.