/

በጀርመን የገባውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በተመለከተ ያለው ቴከኒካዊና ተቋማዊ ልምድና አስተያየት – ክፍል 10

ለተከበራቹህ ወገኖች                                                                           

ሁለተኛው ዙር ሙሉ ሎክ ዳውን  – 13.12.2020

German Covidሁኔታዎች በቅፅበት በመቀያየራቸው ከአለፈው በመቀጠል ስለ ኮቪድ-19  ወረርሽኙ 2ኛ ማዕበል የተወሰነውን ሎክዳውን የያዘውን ክፍል አስርን አቀርባለሁ።

በዛሬው ዕለት ቻንስለር አንጌላ ሜርክል ከፌዴራል መንግስታት ርዕሰ መስተዳድሮች ጋር በመመካከር  ከዚህ በፊት በ9ኛው ገለፃ እንዳስቀመጥኩት የነበርውን ግማሽ ሎክ ዳውን በመቀየር ከታህሳስ 16 እስከ ጥር 10 ቀን 2021  በጀርመን የሚቆይ ሙሉ በሙሉ ሎክዳውን ጥለዋል።

የሮበርት ኮህ ኢንስቲትዩት እንደዘገበው በየቀኑ 24 ሰዓታት ውስጥ ወደ  ከ20ሺ በቫይረሱ ሰዎች የሚያዙ ሲሆን እና ይህም በተመሳሳይ የናሙና ምርመራ መጠን ከአለፉት ጊዜያቶች ምንም መሻሻል አላሳየም። በአውሮፓም ሆነ በጀርመን ሁኔታው በጣም እየከባደ የመጣ ነው። ጀርመን ላይ እስካሁን ከ1.3 ሚሊዮን በላይ በወረርሽኙ ሲያዙ፣ ከ950ሺ በላይ አገግመዋል። ከ22 ሺ በላይ ህይወታችወ አልፏል። አሁን በህዳር/ታህሳስ ወቅት በአረጋውያን እና በእንክብካቤ መስጫ ቤቶች ውስጥ በወረርሽኞች የተያዙት በእጥፍ ጨምሯል። ቫይረሱ በአጠቃላይ ህዝብ ውስጥ እና በአደጋ ተጋላጭ ቡድኖች ውስጥም በፍጥነት በመሰራጨት ይገኛል፡፡ከዚህ በመነሳት ከላይ የተጠቀሰው እርምጃ በአስቀድሞ መከላከያ እቅድ መሰረት ተወስኗል።


  1. የዕለታዊ ፍጆታ ጅምላ ሻጮች እና ቸርቻሪዎች፣

የዕለታዊ ፍጆታ ከሚሸፍኑ በስተቀር ሁሉም ሱቆች፣ ገበያ ቦታዎች ከታህሳስ 16 እስከ ጥር 10 2021 ድረስ ይዘጋሉ። የገና ስጦታ መግዛት ያለበት ሰው እስከ መጪው ረቡዕ ድረስ መፍጠን ይኖርበታል። ይህ እገዳ የማይመለክታቸው የምግብ ቸርቻሪዎችን፣ ሳምንታዊ ገበያን እና አካፋፍዮች፣ ሸቀጣሸቀጦችን፣ የፖስታ እና የእቃ የመሰብሰብ እና የማድረስ አገልግሎቶችን፣ የመጠጥ ገበያዎችን፣ የጤና ምግብ መደብሮች እና ፋርማሲዎችን ነው።፡ በአለፈው የተላለፈው የሆቴሎች እና ሪስቶራንቶች መዘጋት ይቀጥላል።


  1. ትምህርት ቤቶች እና መዋለ ሕጻናት፣

በዚህ ጊዜም ትምህርት ቤቶች እና መዋለ ሕጻናት ይዘጋሉ። የመቀራረብ ገደቦች ተፈጻሚ ይሆናሉ። ልጆች በተቻለ ሁሉ በቤት ውስጥ ትምህርት መከታተል አለባቸው። ጀርመን አገር አንድ ሰው በአካል ተገኝቶ ትምህርትን የመከታተል ግዴታ በድጋሜ ለጊዜው የተነሳ ሲሆን አስቸኳይ የርቀት ትምህርትን ይመከራል። ወላጆች በተጠቀሰው ጊዜ ልጆቻቸውን ከቤት ሆነው ለመንከባከብ የደሞዝ፣ ክፍያ የማይቀይርበት ፈቃድ መውሰድ እንዲችሉ ተጨማሪ ዕድሎች ይፈጠራሉ።


  1. የገና ቀናት አካባበር፣

ከታህሳስ 24 እስከ 26 ባለው የገና ቀናት ውስጥ ከ“የቅርብ የቤተሰብ አባላት” ከአራት ሰዎች ጋር በተጨማሪም እስከ 14 ዓመት ዕድሜ ያላቸውን ጨምሮ መገናኘት ይፈቀዳል። ይህም በጣም የቅርብ የቤተሰብ ማለት የትዳር አጋሮች እና ሳይጋቡም በአንድ ቤት የሚኖሩ ጥንዶች እንዲሁም የቅርብ ዘመድ እና የቤተሰብ አባሎቻቸውን ያጠቃልላል። በውሳኔ ሃሳቡ መሠረት ከሁለት ቤተሰቦች በላይ ወይም እድሜያቸው ከ14ዓመት በላይ የሆኑ አምስት ሰዎች አብረው የሚደርጉት መሰባሰብም ይፈቀዳል።

  1. የዘመን መለወጫ ዋዜማ እና የአዲስ ዓመት ዋዜማ

የዘመን መለወጫ ዋዜማ እና የአዲስ ዓመት ዋዜማ በአገር አቀፍ ደረጃ በመሰባሰብ ማክበር የታገዱ ናቸው። በአደባባይ ቦታዎች ላይ ርችቶች የሚተኮሱበት ቦታዎች በማዘጋጃ ቤቶች የሚወስኑት ብቻ ይሆናል። የርችቶች ሽያጮች በአጠቃላይ በዚህ ዓመት የተከለከሉ ናቸው።


  1. የአልኮል መጠጥ

ከታህሳስ 16 እስከ ጥር 10 በአደባባይ አልኮል መጠጣት ክልክል ነው። ይህንን የሚጥስ ይቀጣሉ።


  1. የእምነት ቦታዎች

በአብያተ-ክርስቲያናት፣በምኩራቦች እና በመስጊዶች እንዲሁም በሌሎች የሃይማኖት ማህበራት አገልግሎቶች የሚፈቀዱት የ1.5 ሜትር ርቀት መተግበር ከቻሉ ብቻ ነው። የአፍ እና የአፍንጫ መከላክያ ማድረግ ግዴታ ሲሆን፣ በእነዚህ ስነስርዐቶች ላይ የጋራ መዘሙሮች የተከለከሉ ናቸው። ተሳታፊዎችም አስቀድመው መመዝገብ አለባቸው።


  1. ለቤተ አረጋውያን

ለቤተ አረጋውያን የጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚሰሩ እና ተንቀሳቃሽ የህክምና ሰራተኞች በሳምንት ብዙ ጊዜ የግዴታ የናሙና ምርመራ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የበሽታው መጠን እየጨመረ በሄደባቸው ቦታዎችም ጎብኝዎች አዲስ የኮሮና ኔገቲቭ ናሙና ማቅረብ አለባቸው።


  1. የመዋቢያ ስቱዲዮዎችን እና የመታሻ ቤቶች፣

የግል እንክብካቤ የሚሰጡ ይዘጋሉ። እነዚህም የፀጉር አስተካካዮች ፣ የመዋቢያ ስቱዲዮዎች ፣ የጤና መታሻ ቤቶች እና የንቅሳት ስቱዲዮዎች ይገኙበታል። እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ሕክምናዎች  ማለትም የፊዚዮቴራፒ፣ የኤርጎ እና ሎግቴራፒ እንዲሁም የእግር እንክብካቤ ሊፈቀድላቸው ይችላል።


  1. ኢኮኖሚያዊ ድጎማ እና ክትባት፣

የኮሮና ቀውስ ኢኮኖሚን ክፉኛ ቢመታውም እ.ኤ.አ. በ 2020 የመጀመሪያ አጋማሽ ከነበረው ከባድ ውድቀት በኋላ የጀርመን ኢኮኖሚ የወረርሽኝ ከሚያስከትለው ውጤት በተሻለ እየተቋቋመ የመጣው ይመስላል። በሎክ ዳውን ለተጎዱ ኩባንያዎች፣ ተቁማት የኢኮኖሚ ድጋፍ እፎይታ ይደረግላቸዋል። “መሸጋገሪያ እርዳታ 3” ከዚህ በፊት 200,000 ዩሮ የነበርው እስከ 500,000 ዩሮ ከፍ ብሏል። ከፍተኛው መጠን በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ስራቸውን በመዘጋት ለሚጎዱ ተቋማት የታሰብ ነው። በአሁን ሰዓት የተዘጋጀው ክትባት እስከ 29 ታህሳስ 2020 ፈቃድ እንደሚያገኝ ይጠበቃል። ባዮንቴክ የሚባለው ኩባንያ ያዘጋጀው ክትባቱን በቅርቡ ማቅረብ ይጀመራል። የባዮንቲከ ባልቤት እና መሪ ሳይንቲስት ከቱርክ ወደ ጀርመን በልጅነት የመጡና እና ለተሳልጦ መኖር ትልቅ ተምሳሌት የሆኑ ናቸው። ለመከተቢያ የሚሆኑ ቦታዎች በየስቴቶቹ እየተዘጋጁ ነው፣ ለምሳሌ በርሊን ወስጥ ወደ 15 መከተቢያ ቦታዎች ላይ ዝግጅት እየተደረገ ነው።

ለመደምደሚያ በዚህ አጋጣሚ ኢትዮጵያ ስርጭቱ ቢቀንስም፣ ህግ እና ደንብ ማስከብር ላይ ብትገኝም ብዙ የሚታዩ መዘናጋቶች ለምሳሌ ያለ አፍንጫ እና አፍ መከላከያ በማስ የሚደርጉ እንቅስቃሴዎች እና ስብስቦች ይታያሉ። እንደ ጀርመን አብዝቶ እንዳይመለስ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

መልካም የፈርንጆች ገና እና የአዲስ አመት እንዲሁም ሰላም እና መርጋጋትን እመኛለሁ።

ከመልካም የጤንነት ሰላምታ ጋር
ፀጋዬ ደግነህ (ዶ/ር)

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.