/

የኢትዮጵያ ኅብረሕዝብ ብሔራዊ ንቅናቄ (ኅብረሕዝብ-ኢትዮጵያ) የተሰጠ የአቋም መግለጫ

hibrehizb 2በሕወሓትና በማዕከላዊ መንግሥት መኻል ከተፈጠረው ችግርና ካስከተለው ጦርነት ምን ትምሕርት ተቀሰመ?፣ አገርን የሚታደግ መፍትኄውስ?

ከኢትዮጵያ ኅብረሕዝብ ብሔራዊ ንቅናቄ (ኅብረሕዝብ-ኢትዮጵያ) የተሰጠ የአቋም መግለጫ፤

ኅዳር ፳፫ ቀን ፪ ሽህ ፲፫ ዓ/ም

ምንም እንኳ ሕወሓት ለሃያ-ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያን በበላይነት ሲመራ ከቆየ በኋላ በሕዝብ ትግል የነበረውን ሥልጣን ካጣ ጀምሮ ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር ያለው ግንኙነት ከጊዜ-ወደ-ጊዜ እየሻከረ መሄዱና ልዩነቱንም በሰላማዊ መንገድ በውይይት ለመፍታት የማይቻልባቸው ምልክቶች እንደነበሩ ቢታወቅም፣ ከጥቅምት ፳፬ ቀን ፪ ሽህ ፲፫ ዓ/ም ጀምሮ በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን-ዕዝ ጦርና በትግራይ በሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ላይ የፈጸመው አሳፋሪ የክኅደት ወንጀል ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የነበረውን ተስፋ ጨርሶ እንዳከሰመውና ማዕከላዊ መንግሥትም የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ እንዲገደድ አድርጓል።

ይኽ በሕወሓት ጽንፈኛ አመራር የተወሰደ አስነዋሪ እርምጃ ተራ ወንጀል ሣይሆን፣ ማንም ሉዓላዊ አገር ሊቀበለው የማይችልና በምንም መንገድ ሊታለፍ የማይገባን ቀይ-መሥምር የጣሰ ፀያፍ ድርጊት፣ እንኳን ኢትዮጵያችን ለባዕዳን የጥቃት አደጋ ተጋላጭ በሆነችበትና የዜጎቿን አንድነት አጥብቃ በምትሻበት ቀርቶ በማንኛውም ጊዜ ቢሆን በአገር ኅልውና ላይ የተፈጸመ ከፍተኛ የክኅደት ወንጀል በመሆኑ፣ ልዩነቱ በገዥው ፓርቲና በሕወሓት መኻል ከመሆን እንዲያልፍና በኢትዮጵያ ሕዝብና በሕወሓት መኻል እንዲሆን አድርጎታል።

በሕወሓት ልዩ-ኃይልና በሠራዊቱ ውስጥ በነበሩ ተባባሪዎቻቸው በተወሰደ ይሆናል ተብሎ በማይታሰብ የአገር ክኅደት የወንጀል ድርጊት ቁጥራቸው ለጊዜው ያልታወቀ በርካታ የጦሩ አባላት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፣ ብዙዎች ለከፍተኛ ጉዳት፣ ውርደትና እንግልት ተዳርገዋል፣ የጦሩ ንብረትም ተዘርፏል፣ ወድሟል። ሕወሓት ባደራጀውና በሚመራው ገዳይ ቡድን ማይ ካድራ ላይ ከሽህ በላይ የሚገመቱ ሰላማዊ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት በአሰቃቂ ሁኔታ ተጨፍጭፈው አስክሬናቸው በጅምላ መቃብርና የትም እንዲጣል ሆኗል። ይኽ አረመኔኣዊ ግድያ መሠረታዊ ወታደራዊ የመለዮ ሥነ-ምግባርና ሥነ-ሥርዓትን የጣሰ፣ በማይ-ካድራም ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት የጥቃት ዒላማ ሆነው በዘግናኝ ሁኔታ የተጨፈጨፉበት በመሆኑ ከጦር-ሜዳ ወንጀልና በሰው-ዘር-ፍጅት የሚያስጠይቅ ይሆናል። እነኝኽ የወንጀል ድርጊቶች ከዚያ በታች የሚታዩ አይሆኑም።  ድርጅታችን ይኽንን አስነዋሪና አሸባሪ አረመኔኣዊ የአገር-ክኅደት የወንጀል ተግባር አጥብቆ ያወግዛል፤ የድርጅቱ መሪዎችና በጦሩ ውስጥ ሆነው የድርጊቱ አስተባባሪና ፈጻሚ የሆኑት ለፍርድ እንዲቀርቡ ይጠይቃል። ሕወሓት በእነዚኽ የወንጀል ድርጊቶቹ ምክንያት የድርጅቱን ሕጋዊ ኅልውና ቢያንስ ጥያቄ ውስጥ አስገብቷል ማለት ይቻላል።

በመንግሥት በኩል እየተወሰደ ያለው አጸፋዊ እርምጃ በተቻለ መጠን ከ፵ ዓመታት በላይ በሕወሓት ጭቆና ሥር ታፍኖ በኖረው ሰላማዊ የትግራይ ወገናችን ላይ ጉዳት በማያደርስ መንገድ ወንጀለኞችን ለፍርድ በማቅረብ፣ ሰላምና መረጋጋት እውን እንዲሆንና ሕዝብ አስተማማኝ መሠረታዊ አገልግሎቾችን እንዲያገኝ እና በነፃነት በመረጣቸው መተዳደር እስከሚችል ድረስ፣ በቀጥታ በገዥው ፓርቲ (ብልጽግና) በሚሾሙ ሣይሆን ከአገር መከላከያና ከኅብረተሰቡ ልዩ-ልዩ ክፍሎች የተወከሉ አባላትን ባቀፈ ጥምር አካል በጊዚያዊነት (ከሦስት እስከ ስድስት ወር ላልበለጠ ጊዜ) እንዲተዳደር በማድረግ እንዲጠናቀቅ ያስፈልጋል የሚል እምነት አለን።

አገራችንን ለዚኽ የዜጎችን ደም-አፋሳሽ ችግር እንድትዳረግ ያደረገ ዋነኛና መሠረታዊ ምክንያት ምንድን ነው? ከሚለው ከባድ ጥያቄ ቀጥሎ ምላሽ የሚያስፈልገው እንደ-አገርም፣ እንደ-ሕዝብም ከዚኽ እሳዛኝ ሁኔታ ምን ትምሕርት ተቀሰመ? የሚለው ይሆናል። ለእነዚኽ ጥያቄዎች ከግልም ሆነ ከቡድን ወገንተኝነት-ባለፈ ቀና አስተሳሰብ የምር ውስጣችንን ፈትሸን፣ የአገርንና የሕዝብን ዘለቄታዊ ጥቅም ባስቀደመ የኃላፊነት መንፈስ መልስ መስጠት ይኖርብናል። ዞሮ-ዞሮ የፈሰሰው የወገኖች ደም፣ የጠፋው የራሣችን ዜጎች ሕይዎት ነው። ይኽንን ካደረግን ውርደት፣ መከፋፈል፣ የችግር አዙሪት ተቸናፊ፣ እውነት፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አቸናፊዎች ይሆናሉ።

ይኽ የዜጎችን ሕይዎት ያጠፋ እና የአገርን ንብረት ለውድመት የዳረገ መሠረታዊ ችግር በጥሞና ሊጤን ይገባል። ሕወሓት ጥቅምት ፳፬ ቀን የፈጸመው ድርጊት የፖለቲካ ችግሩ ውልድ እና ነፀብራቅ እንጅ መሠረታዊ ምክንያት እንዳልሆነ ሊጤን ይገባል። በመሆኑም፣ መንግሥት ‘ሕግ-የማስከበር’ ተልዕኮ ብሎ በሰየመው በዚኽ ዘመቻ ሕወሓት በጦር-ሜዳው የሚገጥመው ሽንፈት የሚያጠራጥር ባይሆንም፣ አገራችንን ለዚኽ ደም-አፋሳሽ ችግር እንድትዳረግ ያደረገው ፖለቲካዊ መሠረት ያለው ችግር በቅጡ ካልታወቀና መፍትኄ ካልተገኘለት ውጤቱ የተከፈለውን መስዋዕትነት የማይመጥንና አገርም ለተመሣሣይ ችግር እንዳትጋለጥ ማድረግ እንደማይቻል መታወቅ ይኖርበታል።

ስለሆነም፣

ሀ. ገለልተኛ አካል ማቋቋም፡-

የዚኽን ጦርነት መሠረታዊ መንስዔ የሚያጠና ልዩ ገለልተኛ የሙያተኞች አካል (ኮሚቴ) በማቋቋም ጥናት እንዲደረግና ውጤቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር-ቤትና ለኢትዮጵያ ሕዝብ በይፋ እንዲገለጥ ማድረግ ያስፈልጋል።

ለ. አጣሪ ኮሚሽን መሰየም፡-

ይኽ ጦርነት በሕዝብ ላይ ያስከተለውን ጉዳትና በንብረት ላይ ያደረሰውን ኪሣራ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመሆን የሚያጣራ አጣሪ ኮሚሽን መንግሥት እንዲሰይም እና ውጤቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር-ቤትና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይፋ እንዲደረግ።

ሐ. አገራዊ (ብሔራዊ) የእርቅና የሰላም ጉባዔ

ለአገራችን ውስብስብ ችግሮች ዘለቄታዊነት ያለው ሰላማዊ መፍትኄን ለማስገኘትና ወደ-ዴሞክራሲያዊ-ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ግንባታ የሰከነ ሽግግር ማድረግ ይቻል ዘንድ፣ አገርአቀፍ የሰላምና እርቅ ጉባዔ ማካሄድ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ዴሞክራትና አገር-ወዳድ ኃይሎችና መልካም-አሳቢ ግለሰቦች ከሦስት-አሥር-ዓመታት በላይ ለዘለቀ ጊዜ ያለመታከት ሲወተውቱ እንደቆዩ ይታወቃል። በሕዝብ ግፊት ከኢሕአዴግ መኻል በወጡ በዶ/ር ዐብይና በአጋሮቻቸው የተመራው ለውጥ ሲከሰትም ድርጅታችን ኅብረሕዝብ ለውጡ ሕዝብ የታገለለትና መስዋዕት የከፈለለት መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጥያቄ ዳግም እንዳይቀለበስና እውን እንዲሆን ይኽን የአገራዊ (ብሔራዊ) የእርቅና የሰላም ጉባዔ እና ቅድሚያ ሊሰጣችው የሚገቡ ሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮች ተግባራዊ እንዲሆኑ በጽሑፍ ማቅረቡ ይታወቃል።

አሁንም ቢሆን ወደ-ምርጫ ከመኬዱ በፊት በ ‘ሀ’ የተመለከተው ገለልተኛ የሙያተኞች አካል የሚያቀርበውን የጥናት ውጤት መሠረት በማድረግ በአገራችን ውስብስብ ችግሮች ላይ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖርና ዘለቄታዊነት ያለው መፍትኄ ለማስገኘት አገራዊ መግባባት ላይ መድረስ ይቻል ዘንድ ሁሉን-አቀፍ አገራዊ/ብሔራዊ የእርቅና ሰላም ሸንጎ (ጉባዔ) እንዲጠራ ከገዥው ፓርቲ፣ ከተቃዋሚ ድርጅቶች፣ ከተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት፣ የማኅበራዊ ድርጅቶችና የአገር ሽማግሌዎች የተውጣጣ ወይም የእነዚኽን ይሁንታ ባገኘ ገለልተኛ አካል እማካይነት እንዲዘጋጅና በአገርና በሕዝብ የወደፊት ዕጣ-ፈንታ ላይ ወሣኝነት ባላቸው ዐበይት ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል። ድርጅታችን የዚኽን ተግባራዊነት በተመለከተ መሰል አመለካከትና አቋም ካላቸው ወገኖች ጋር ለመተባበርና የበኩሉን አስተዋጽዖ የማድረግ ግዴታውን ለመወጣት ያለውን ዝግጁነት ሲገልጥ ጥሪ በማቅረብ ጭምር ነው።

መ. ሕወሓትን በተመለከተ፤

መ-1. ሕወሓት በእነዚኽ የወንጀል ድርጊቶቹ ምክንያት የድርጅቱን ሕጋዊ ኅልውና ቢያንስ ጥያቄ ውስጥ አስገብቷል የሚል እምነት አለን። የድርጅቱን ሕጋዊ ኅልውና የመንፈግ እርምጃ በሕግ ባለሙያዎች ታይቶና በሕዝብ ተወካዮች ምክር-ቤት ቢወሰን የተሻለ ይሆናል።

መ-2. በትግራይ ሕዝብ ስም ለጥቂት የድርጅቱ አመራር አባላትና ቤተሰቦቻቸው ጥቅም የዋለው ንብረት ከድርጅቱ ይዞታ ወጥቶ ሕዝብን በሚጠቅሙ ተቋማት ላይ፣ በአሥራ-ሰባት ዓመት ትግሉ ጉዳት ለደረሰባቸው አባላቱና በሕይዎት ለሌሉ አባላት ቤተሰቦች መጦሪያ እና በሕግ በተረጋገጠ ሁኔታ ድርጅቱ ኢ-ሰብዓዊ ግፍ ለተፈጸመባቸውና ከፍተኛ በደል ለደረሰባቸው ዜጎች ተገቢ ካሣ እንዲሆን ለማስቻል በሚቋቋም ገለልተኛ አካል አማካይነት ተፈጻሚ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል።

ሠ. ቀጣዩን አገር-አቀፍ ምርጫ በተመለከተ፣ (በዚኽ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ ድርጅታችን ያለውን አቋም ከዚኽ ጋር በአባሪነት የቀረበውን ሰነድ ይመለከቷል።)

በ፪ ሽህ ፲፪ ዓ/ም ይካሄዳል የተባለው አገር-አቀፍ ምርጫ በኮቪድ -19 ሣንባ-ቀስፍ ወረርሽኝ ምክንያት የአስቸኳይ-ጊዜ አዋጅ በመታወጁ የበሽታው አደጋ ስጋት እስከማይሆንበት ጊዜ ድረስ እንዲተላለፍ መወሰኑ ይታወቃል። ይኽ ውሣኔ በወቅቱ የሕገ-መንግሥት ክርክርና ውዝግብ ቢያስነሳም ምርጫውን ማስተላለፍና የተወካዮች ምክር-ቤትም መንግሥትም ባሉበት እንዲቀጥሉ ሆኗል። በበሽታው ላይ ያለው ስጋት ጨርሶ ተወግዷል ባይባልም፣ የተላለፈው ምርጫ በዚኽ ዓመት (፪ ሽህ ፲፫ ዓ/ም) እንደሚደረግ በምርጫ ቦርድና በመንግሥት ተነግሯል።

ምርጫ ለሕዝብ የተሻለ ሁኔታን ለመፍጠርና መልካም ዕድልን ለማስገኘት እንጅ፣ በራሱ ለምርጫ ሲባል ለይስሙላ የሚደረግ ተራ ጨዋታ እንዳልሆነና መሆንም እንደሌለበት ይታወቃል። ማንኛውም ምርጫ ትርጉም የሚኖረው ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ፍትኃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ርቱዓዊ ሲሆን ብቻ ነው። ምርጫ በአገራችን ከአፄ ኃይለ-ሥላሴ ዘመነ-መንግሥት ጀምሮ ሲካሄድ መቆየቱ የታወቀ ነው። ምናልባት በ፲፱፻፺፯ ከተደረገውና የሕዝብን ትክክለኛ ፍላጎት ካስመሰከረው ታሪካዊ ምርጫ ውጭ ሌሎቹ ይስሙላዊ ወይም የሕዝብን ፍላጎት ያላንጸባረቁ እንደነበር አሌ አይባልም። ያ የሆነበት ምክንያት ሕዝብ የሚፈልገውን ስላላወቀ ወይም ሳይፈልግ ቀርቶ ሣይሆን፣ መሠረታዊ ችግሩ ከዝግጅት እስከ ድምፅ ቆጠራ ያለውን የምርጫ ሂደትና ምሪት (አስተዳደር) ሙሉ-በሙሉ የሚቆጣጠረው ገዥው ክፍል በመሆኑና የምርጫውም ዓላማና ግብ ሥርዓቱን ለማስቀጠል ታስቦ የሚደረግ እንጅ የሕዝብን የሥልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ ስላልነበረ ነው።

ዴሞክራሲ ከምርጫ የሚመነጭ አለመሆኑ አጠያያቂ ባይሆንም፣ በምርጫ የሚቋቋም መንግሥት በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረውና ሕዝብም በመንግሥት አመሠራረት ተሣታፊ፣ መንግሥትም ለሕዝብ ተጠያቂ እንዲሆን በማድረጉ ረገድ ያለው ጥቅም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ሆኖም፣ ምርጫ ማካሄድ ብቻውን በቂ እንደማይሆን፣ ምርጫ ስለተካሄደም ዴሞክራሲያዊ አለ ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል። ዲሞክራሲ የሚባለው ፅንሰ-አሣብ ነፃና ፍትኅዊ ምርጫን ከማካሄድ በላይ ስለሆነ፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመሥረት የሚደረግ ምርጫ የተለያዩ ዴሞክራሲያዊ ተቋሞች እንዲኖሩ የግድ ይላል።

ማንኛውም ምርጫ ነፃ፣ ፍትኃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የሚከተሉት መሟላት ይኖርባቸዋል።

ሠ-1. የአገራዊ ሰላምና መረጋጋት መረጋገጥ፡-

አገራዊ አንድነትና አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት በሌሉበት ሁኔታ ምርጫም ሆነ ዴሞክራሲ የሚታሰቡ አይሆኑም። ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ሕዝብ ያለ ስጋት ወጥቶ መግባትና ሳይሳቀቅ አሳቡን በነፃ መግለጽ የሚችልበት አገራዊ ሰላምና መረጋጋት ሊኖር ይገባል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ከሦስት ሚሊዮን በላይ የሚቆጠሩ ዜጎች በማንነታችው የመንግሥት ዋና መቀመጫ ከሆነችው የአገራችን ዋና ከተማ ከአዲስ-አበባ አካባቢ በሚገኙ ወገኖች ሣይቀር ‘ቦታችሁ አይደለም፣ መጤ ናችሁ’ እየተባሉ በግፍና በገፍ ከመፈናቀልና ሰብዓዊ መብቶቻቸው ብቻ ሣይሆን መሠታዊ ሰብዓዊ ክብራቸው ተገፍፏል፣ በሚከተሉት ሐይማኖት ምክንያት ጭምር ለአሰቃቂ ጭፍጨፋ ተዳርገዋል። ይኽንን በዜጎች ላይ የተፈጸመ ሰቆቃ፣ ኢትዮጵያውያን በመረረ ሃዘኔታና በሃፍረት፣ የዓለም ሕዝብም በመገረም ተመልክተውታል። ከዚኽ አይቀሬ የክልል-ሥርዓት-ወለድ ሰቆቃ መንግሥትም፣ ሕገ-መንግሥትም ለሕዝባችን ዋስትና ሆነው አልተገኙም። ይኽ ሥርዓት እንዲቀጥል እስከተፈቀደለት ድረስ ደግሞ ሁለቱም ዋስትና ሊሆኑ አይችሉም። አሁን ያለው የአገራችን ሁኔታ ከዚኽ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት የአረመኔኣዊ ጥቃትና የጅምላ ጭፍጨፋ ሰለባ እየሆኑ ያሉበት ስለሆነ ምርጫ ከመታሰቡ በፊት አገራዊ ሰላምና መረጋጋት በተገቢ ሊረጋገጥ ያስፈልጋል።

ለዚኽም ነው የአገርን አንድነትና የሕዝብን ዘለቄታዊ ሰላም፣ አስተማማኝ እድገትና ብልጽግና፣ እውነተኛ የፍትኅና የእኩልነት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ እውን እንዲሆኑ ሁሉም፣ በተለይም የመንግሥት ሥልጣን የያዘው ክፍል፣ ሰላምና መረጋጋት በአገር-አቀፍ ደረጃ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲኖር የቅድሚያ-ቅድሚያ በመስጠት ሊረባረብ ይገባል የምንለው። እርብርቡ አዎንታዊ ውጤት እንዲያስገኝ ግን የጥረቱ ዒላማና ንጥጥር ምርጫ ላይ ሣይሆን ከሱ በፊት መሆን ስለሚገባው ሕዝባችንንና አገራችንን ለዚኽ አደጋ ያጋለጠውና ያመቻቸው የልዩነት ሥርዓት ላይ ሊሆን ይገባል።

ሠ-2. የድርጅቶች ነፃነት መከበር፡-

የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ የግል ተወዳዳሪዎች ያለ ገደብ ለሕዝብና ለአገር ይበጃሉ የሚሏቸውን አማራጭ አሳቦች በሰላማዊ መንገድና በነፃነት ባመቻቸው መንገድ ለመራጩ ሕዝብ ማቅረብና ሕዝብም የመስማት መብቱ በተግባር ሊረጋገጥ ይገባል። በአሁኑ የአገራችን ሁኔታ በተለይም አገር-አቀፍ አደረጃጀት ላለን ድርጅቶች በገጠሩ የአገራችን ክፍሎች ቀርቶ በከተሞች ሣይቀር ስብሰባ ለማድረግ እንኳ የማይቻል እንደሆነ ይታወቃል። በዚኽ ሁኔታ ትርጉም ያለው ሰላማዊ፣ ነፃና ፍኃዊ ምርጫ ማድረግ እንደማይቻል ግልጥ ስለሆነ ይኽ ሁኔታ ከወዲሁ አስተማማኝ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል።

ሠ-3. የዜጎች ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች መረጋገጥና እና የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ፡-

ነፃና ፍታኅዊ ምርጫ ለማካሄድ የዜጎች ሰብዓዊ፣ ፖለቲካዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሊከበሩ እና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ቁልፍ ሚና ያላቸው ዴሞክራሲያዊ ተቋማት በአስተማማኝ እውን ሊሆኑ ያስፈልጋል። ዴሞክራሲ ዜጎች በየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች በመረጡበት ቦታ በነፃነት የመዘዋወር፣ የመኖርና ሃብት የማፍራት፣ በሚኖሩበት አካባቢ በሚደረግ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የመሣተፍ ሙሉ መብት ካልተከበረ ዴሞክራሲ አለ ማለት አይቻልም። የኅትመትና ሌሎች የመገናኛ ብዙኀን፣ የተለያዩ የሙያና ማኅበራዊ ተቋማት ሕጋዊ እንቅስቃሴ ሊከበርና ለተቋቋሙበት ዓላማ በነፃነት እንዲሠሩ ማድረግ ያስፈልጋል። የፍትኅ ሥርዓቱ በየደረጃው ከማንኛውም ተጽዕኖ ነፃ ሊሆን ይገባል። ዳኞች የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡና ውሣኔአቸው እንዲከበር፣ የፍርድ-ቤት ትእዛዝ ተፈጻሚ እንዲሆን የግድ ነው። በአሁኑ ጊዜ የዳኞችን ፍርድ ፖሊስ የሚሽርበት ዓይን-ያወጣ ሥርዓት-አልበኝነት የሚታይበት አሣፋሪ ሁኔታ መከሰቱ እየተስተዋለ ነው። በምንም መንገድ ተቀባይነት ሊኖረው የማይገባ ይኽ ነውረኛ ተግባር ሊወገድና የፍርድ-ቤት ትዕዛዝን የሻሩ ሕግ-ተላላፊዎች ሊጠየቁ ይገባል። በዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታና ነፃነት ዙሪያ እና የዜጎች መሠረታዊ ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች ያለመከበርን ዐብይ ጉዳዮች በተመለከተ አሁን ያለው አሉታዊ የአገራችን ሁኔታ ከምርጫ በፊት መስተካከል ይኖበታል።

-4. የሕዝብ ቆጠራ፡

በኮቪድ ፲፱ አደገኛ ወረርሽኝ ምክንያት በ፪ ሽህ ፲፪ ዓ/ም ሊካሄድ የነበረው አገራዊ-ምርጫ መተላለፉና ያም ሕገ-መንግሥታዊ-ቀውስና ውዝግብ ማስከተሉ ይታወሳል። ውዝግቡን እንተወውና ምርጫው መተላለፉ እውነተኛ ነፃ፣ ፍትኅዊ፣ ርቱዓዊና ዴሞክራሲያ ምርጫ ለማድረግ መሟላት ያለባቸው የቅድመ-ሁኔታ መብቶችና አስፈላጊ መዋቅራዊ አደረጃጀቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ፣ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጅቶችም በምርጫ-ቦርድ የሚጠየቁትን ለማጠናቀቅና በበቂ ለመዘጋጀት ያልታሰበ መልካም አጋጣሚን ፈጥሯል።

አገራዊ-ምርጫ ከመደረጉ በፊት መሟላት ካለባቸው ዓይነታ ጉዳዮች ውስጥ በአገር-አቀፍ ደረጃ ተኣማኒነት ያለው የቤትና የሕዝብ ቆጠራ ሊደረግ ይገባል። በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 103 (5) እንደተጠቀሰው የምርጫ ክልሎች አከላለል የሚወሰነው የሕዝብ ቆጠራውን ውጤት መሠረት አድርጎ ስለሆነ፣ በአንቀጽ 54 (3) የሕዝብ ቁጥር የተወካዮችን ቁጥር ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ መሆን ስላለበት፣ ከምርጫ በፊት መደረግ ከነበረበት ሦስት ዓመታት ያለፈው የቤትና የሕዝብ ቆጠራ ተግባራዊ መሆን ይኖርበታል። የሕዝባችንን ቁጥርም ከደፈናዊ ግምት ባለፈ በትክክል ማወቁ የተሻለ ተኣማኒነት ያለው አገራዊ ምርጫ ለማካሄድም ሆነ ለበጀት አመዳደብና ለሌሎች አስተዳደራዊ ጉዳዮች አስፈላጊ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

ሠ-5. ገለልተኛ የምርጫ አስተዳደር፡-

ምርጫንና የምርጫ ውድድርን የማዘጋጀት፣ የማደራጀት፣ ሂደቱንና አፈጻጸሙን የማስተናገድና የመወሰን ኃላፊነት ያለበት የምርጫ አስተዳደር በሁሉም እርከኖች ከተፅዕኖ ነፃና ገለልተኛ ሊሆን እና ድርጅታዊ ብቃት ሊኖረው ይገባል። ይኸም ማለት መንግሥት በተቋሙ ላይ አንዳችም ተፅዕኖ ማድረግ አለመቻሉ ሊረጋገጥ፣ ተቋሙ ለማንኛውም ተፎካካሪ ፓርቲም ሆነ ግለሰብ ምንም ዓይነት አድልዖ የማያደርግ፣ እንዲሁም የራሱ የሆነ የገንዘብ አቅም ያለውና የሥራ-ማስኬጃ ተመኑም (በጀቱም) በአስፈፃሚው ክፍል የማይወሰን ሊሆን ይገባል። ምርጫ አስተዳድሩ (ቦርዱ) በምርጫ ጉዳይ ተወዳዳሪ ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦች እንዲያከብሩና እንዲገዙበት አስፈላጊ ሆነው ያገኛቸው አዳዲስ መመሪያዎች ከመውጣታቸው በፊት በተቻለ መጠን ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ተወዳዳሪዎች ጋር መመካከሩና ያሏቸውን አሳቦች ማስተናገዱ በሂደቱ የተሻለ ኣመኔታ እንዲኖር ይረዳል።

ሠ-6. ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሕግ መኖር፡-

የአንድ አገር ፖለቲካዊ ሥሪት ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን መንግሥታዊ ተቋማት ዴሞክራሲያዊ ይዘት ሊኖራቸው ይገባል። ዴሞክራሲ ፖለቲካዊ ብቻ ሣይሆን ማኅበራዊና ኤኮኖሚያዊ ይዘት እንዳሉት ግልጥ ነው። ምርጫ ዴሞክራሲያዊ መሆን የሚኖርበትም ኅብረተሰቡ በፖለቲካዊ፣ በማኅብራዊና ኤኮኖሚያዊ ዘርፎች ያሉትን ፍላጎቶች ሊያስከብሩልኝ ይችላሉ ብሎ ያመነባቸውን ተወካዮችና መሪዎች በሚሰጠው ድምፅ መሰየምና የኔ ነው የሚለው መንግሥት የሚኖረውን ሥልጣን ለመቆጣጠር ስለሚያስችለው ነው።

እንደሚታወቀው ተዓማኒነትና ሕዝባዊ ተቀባይነት ያለው ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ለመመሥረት የተለያዩ መሠረታዊ ሁኔታዎች መሟላት አለባቸው። ከእነዚኽ ሁሉ ግብዓቶች እጅግ አስፈላጊና በቅድሚያ ሊሟላ የሚገባው ሁኔታ የምርጫ ሥርዓቱ ነው። ነፃና ፍትኅዊ ምርጫ እንዲኖር ለማድረግ ደግሞ ቀዳሚ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ የምርጫ ተቋም ነው። የምርጫ ተቋም መኖር ብቻውን አንድን ምርጫ ነፃና ትክክለኛ ያደርገዋል ባይባልም፣ አስፈላጊነቱ ግን ጥያቄ ውስጥ ሊገባ ከቶ አይችልም።

ማንኛውም ሰው ወይም ዜጋ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ለነፃና ፍትኃዊ ምርጫ አስፈላጊ የሆኑና መሟላት ያለባቸው የቅድመ-ሁኔታ መብቶች በተረጋገጡበት ሁኔታ በሚደረጉ ምርጫዎች ከመንግሥት ይሁን ከማንኛውም አካል ምንም ዓይነት ተጽዕኖ ሣይደርስባቸው፣ በቋንቋ ይሁን በሚከተሉት መንፈሣዊ ሕይዎት፣ በኑሮ ደረጃቸው ይሁን በፖለቲካ አቋማቸው ልዩነት ሳይደረግባቸው፣ ለመምረጥም ይሁን ለማስመረጥ በሚደረግ ሂደት ከቦታ-ቦታ ያለ ችግር የመዘዋወርና የመንቀሳቀስ፣ ከምርጫ አስፈጻሚ አካላት መረጃ የመጠየቅና የማግኘት፣ ለመምረጥም ሆነ ለመመረጥ እንዲችሉ የመመዝገብና አስፈላጊውን ትብብር የመጠየቅና የማግኘት፣ ለማን እንደሚመርጡ በማንም ሳይጠየቁ ያለ ምንም ፍራቻ፣ ልዩነትና ባልተገደበ ነፃነት ድምፃቸውን በምስጢር ለፈለጉት በመስጠት አስተዳዳሪዎቻቸውን የመምረጥ፣ እንዲሁም የሰጡት ድምፅ በአግባቡና በትክክል መቆጠሩን የማረጋገጥ መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል።

ዜጎችም ሆኑ ድርጅቶች የምርጫና የፖለቲካ መብቶቻችው መከበር በነጠላው የቆመ መብት ሣይሆን ሊያከብሯቸውና ሊወጧቸው የሚገቡ ኃላፊነቶችና ግዴታዎች እንዳሉባቸው ግልጥ ነው። ለምርጫ በሚደረግ ሂደትም ሆነ በምርጫ ጊዜ፣ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች የኅብረተሰብን ሰላም ከሚበጠብጥና አደጋን ከሚጋብዝ ማንኛውም ዓይነት ሕገ-ወጥ ቅስቀሳ፣ ባኅሪና ተግባር ሊቆጠቡ ይገባል። በአኳያው የመንግሥት ሥልጣን በያዘው ክፍል በኩል ምርጫው ዓለም-አቀፍ መሥፈርትን ባሟላ መልኩ ነፃና ፍታኃዊ እንዲሆን በአንድ በኩል ለሥርዓቱ ጥቅም ሲባል ወይም ለተወሰኑ ወገኖች በሚያዳላ መልኩ ሂደቱንም ሆነ ውጤቱን የሚያደናቅፉና የሚያሰናስክሉ ተጽዕኖዎች ባለማድረግ፣ በሌላ በኩል አስፈላጊ የሆኑት ተቋማት ተልዕኳቸውን በበቂ እዲወጡ የሚያስችል አቅም በመፍጠርና ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅበትን ግዴታ መወጣት ይኖርበታል። የምርጫ ሕጉ ሁሉንም ተወዳዳሪዎች አድልዖ በሌለው በእኩል የሚያይና የምርጫ ዝግጅት፣ አደረጃጀትና አፈጻጸም፣ በምርጫ ታዛቢዎች አመዳደብና በሌሎች ተዛማች ጉዳዮች መብታቸው እኩል እንዲከበር፣ ወዘተ.. ያስፈልጋል።

በአሁኑ ጊዜ ያለው የአገራችን ፖለቲካ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአብዛኛው ቋንቋን መሠረት ባደረገና እርስ-በርስ በሚገፋፉ ክልሎች እንዲወሰን በመሆኑ እና የአንዲት አገር ዜጎች ዘርን፣ ጎሣን፣ ቋንቋን፣ ወዘተ… የመሳሰሉ ልዩነቶችን መሠረት ባደረገ አግላይ አደረጃጀት እንዲከፋፈሉ በመደረጉ ዓለም-አቀፍ የሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች ድንጋጌዎችን የሚጻረርና ርቱዓዊነቱ አጠራጣሪ ስለሚሆን፣ ቢያንስ በዚኽ ሁኔታ የሚካሄድ ምርጫ፤ ነፃ፣ ፍትኅዊ፣ ርቱዓዊና ዴሞክራሲያዊ የመሆን ተኣማኒነቱን ሊቀንስበት ይችላል። ዞሮ-ዞሮ የምርጫ ሕጉ የአገሪቱን ሕገ-መንግሥት ጠገግ ተከትሎ የሚወጣ በመሆኑ፣ የምርጫ ሂደቱንና ነፃ፣ ፍትኃዊ፣ ርቱዓዊና ዴሞክራሲያዊ መሆን አለመሆኑን ከወዲሁ የሚወስነው ይኸው በአገሪቱ ላይ ያለው ሕገ-መንግሥት ይሆናል። ስለሆነም፣ ሕገ-መንግሥቱ የተሻለ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ማድረጉ ምርጫው ፍትኃዊ፣ ርቱዓዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የተሻለ ዕድል ይኖረዋል።

ሠ-7. ገለልተኛ ቅሬታ ሰሚና የሚዳኝ አካልና ደንብ፡-

ከምርጫ ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ቅሬታዎችና ክሶች ከአድልዖ ነፃ ሆኖ የሚዳኝ ተኣማኒነት ያለው አካልና ሥነ-ሥርዓት ሊኖር ይገባል። ይኽም ምርጫ ከመደረጉ በፊት መረጋገጥ ያለበት ጉዳይ ነው።

ሠ-8. ዴሞክራሲያዊ ሕገ-መንግሥት፡-

ለአንድ አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን ዴሞክራሲያዊ ሕገ-መንግሥት ሊኖር የግድ ይላል። በአገራችንም ይኽ እንዲኖር ያስፈልጋል። ያ ከሌለ የሕገ-መንግሥታዊ-ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለቤት መሆን አይቻልም። ላለፉት ሃያ-ስድስት ዓመታት በሥራ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ከአረቃቀቅ ሂደቱ ጀምሮ ችግሮች እንዳሉበት በተለያዩ ጊዜዎች ትችቶች ሲቀርቡበትና የመፍትኄ አሳቦች ሲለገሱት ቆይቷል። ይሁንናም አሳቡን ከአገርና ከሕዝብ ዘለቄታዊ ጥቅም አኳያ ሣይሆን ጽንፈኛ ከሆነ ጊዚያዊ የፖለቲካ ትርፍ-አስገኚ ማዕዘን እየታዬ ጉዳዩን በቀና መንፍስ ለማስተናገድ እንኳ ዕድል ሳይሰጠው ቆይቷል። በዚኽ የአገርና የሕዝብ ዕጣ-ፈንታ ላይ ወሣኝነት ያለው አንገብጋቢ የሕገ-መንግሥት ጉዳይ ላይ ጥያቄ ማንሳቱ መብት እንደሆነ ተረስቶ እንደ አገር-አፍራሽ ወንጀል እስከመቆጠር መድረሱ፣ ፖለቲካችን ምን ያኽል ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ያሣያል።

በማንነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ቅኝትና የአደረጃጀት ዘይቤን በሚከተሉ ድርጅቶች በኩል የሚሰማው አሳብ ግትርነት የሚንፀባረቅበት ሆኖ ይገኛል። ምንም ዓይነት ምክንያት ሊደረደር ቢችል አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ-መንግሥት ችግር የለውም፣ አይነካ አልፎም ችግር እንኳ ቢኖር አተገባበር ላይ ነው የሚለው ደፈናዊ ሙግት ከሌላ ሣይሆን በራሣችን አገርና ሕዝብ ላይ ያስከተለውን ጦስ የዘነጋ፣ አሳማኝነት የሌለውና ኃላፊነት የጎደለው ከመሆን አያልፍም። ይኽ የሚሆነው ምናልባት በምልዓተ-ሕዝቡ ኪሣራ በዚኽ ሕገ-መንግሥት ተጠቃሚ የሆኑ ክፍሎች እንዲነካ ስለማይፈልጉ ነው ሊባል ይችላል። ከሚያቀርቧቸው መከራከሪያዎች ውስጥ አንደኛው “ሕገመንግሥቱን መንካት አገር ያፈርሳል” የሚለው የተዛባ አስተሳሰብ ነው። ይኸን መሟገቻ የሚያቀርቡ ወገኖች የሳቱት ቁም-ነገር ይኽችን የረጅም ጊዜ የተመዘገበ መንግሥታዊ የአስተዳደር ታሪክ ያላት፣ በዜጎቿ ደምና አጥንት የቆመችና በልጆቿ የተባበረ ትግል ነፃነቷንና ሉዓላዊነቷን አስከብራ የቆየች ጥንታዊት አገር ይኽ ሠላሣ ዓመት ያልሞላውና ዴሞክራሲያዊ ባልሆነ መንገድ የተወሰኑ ቡድኖችን ጥቅም ለማስከበር ሲባል በሕዝብ ላይ የተጫነ ሕገ-መንግሥት የፈጠራት አድርገው መቁጠራቸው የሙግቱን ግልብነትና ግብዝነት የሚያሣይ ነው። ዴሞክራሲያዊ ሕገ-መንግሥት እንደ ሙሴ ጽላት ከመለኮት የተሰጠና እንዴ ከተጻፈ የማይነካ ሣይሆን በየጊዜው ሊለዋወጡ የሚችሉ የኅብረተሰብ ፍላጎቶችን እንደየሁኔታው ሊያሟላ የሚችልና አግባባዊ በሆነና ሥርዓትን በተከተለ መልክ አስፈላጊ የሆኑ ለውጦች ሊደረጉበት የሚችል ሕይዎት ያለው፣ የሚገዛበት ሕዝብ አስፍላጊ ሆኖ ሲያገኘውም ጨርሶ የሚቀየር የመተዳደሪያ ሰነድ ነው።

ስለሆነም፣ ባለፉት ሠላሣ ዓመታትና በተለይም ያለፉት ሦስት ዓመታት በሕዝባችንና በአገራችን ላይ ለተከሰቱ ችግሮች ይኽ ሕገ-መንግሥት ያለውን አስተዋጽዖ ረጋ ብሎ ከልብ መመርመርና እንዳለ ይዞ መቀጠሉ የሚያስከትለውን ጦስ ማጤኑ አስፈላጊ ይሆናል። ሰላምን የሚያደፈርሰው፣ ሕዝብን ለእልቂት የሚጋብዝና አገርን የሚያፈርሰው ይኽን ማድረጉ ሣይሆን፣ እንዲሁ በጭፍን “አይነካም፣ በዚኽ አንደራደርም” የሚለው ደረቅ ሙግትና ይኽንኑ ጠንቀኛ ሕገ-መንግሥት ይዞ ለመጓዝ መከጅሉ ይሆናል። ይኽቺ አገር ከዚኽ ሕገ-መንግሥት በፊትም ነበረች፣ ወደፊትም ትኖራለች። ለአገራችን አንድነት፣ ለሕዝባችን አስተማማኝ ሰላምና እድገት የተሻለውና ተመራጭ የሚሆነው ግን ይኽን ጉዳይ ከምርጫ በፊት መልክ ማስያዝ ይሆናል።

በዚኽ ረገድ አንዳንድ ወገኖች የሚሻሻልም ካለ ከምርጫ በኋላ በሚሰየመው አዲስ የተወካዮች ምክር–ቤት ይታያል የሚል አሳብ ሲሰነዝሩ ይሰማል። እዚኽ ላይ መጠይቅ ያለብን፤ ለዚኽ ሕገ-መንግሥት የመፈተሽ እንኳ ዕድል ሣይሰጥና ቢያንስ አስፈላጊ የሆኑ መሻሻያዎች ሣይደረጉ በሚካሄድ ምርጫ የተሰየሙ የተወካዮች ምክር-ቤት አባላት በምን አሳማኝ ምክንያትና በምን አስገዳጅ ሁኔታ ነው የተወከሉበትንና ለዚያ ወንበር ያበቃቸውን ሕገ-መንግሥት እንዲሻሻል የሚፈልጉት? ያኔ ማድረግ ይችላሉ ተብሎ ከታሰበስ አሁን ያለው ምክር-ቤት ለምን ተግባራዊ ማድረግ ተሣነው ወይም አልፈለገም? አሁን ያለው የተወካዮች ምክር-ቤት አባል ያላደረገውን በተመሣሣይ ሁኔታ የሚመረጠው ያደርገዋል ብሎ ማሰብ ላም አለኝ በሰማይ አጉል ምኞት ይሆናል። ሕገ-መንግሥት እኮ በአጭሩ ዜጎች ለሚያስተዳድሯቸው ኃላፊዎች ሥልጣናቸውን ገድበው የሚሰጡበትና እነሱም ግዴታቸውን ወድደው የሚወስኑበት ሰነድ ነው። በአመጽ ሣይሆን ሕግን ተከትሎና በሰላማዊ መንገድ የሕገ-መንግሥት ጥያቄን ማንሳት ደግሞ የዴሞክራሲ መብት ነው። አይነካ የሚሉ ወገኖች ምን እንደሚያስፈራቸው ግልጥ አይደለም። አገርና የአገር ጉዳይ የጋራ እንጅ ለተወሰኑ ክፍሎች ብቻ ተወስኖ የተሰጠ የግል ጥሪት አይደለም። ጥያቄ ማንሣት ሊፈራ ሣይሆን ሊደፋፈር ይገባል። የሕገ-መንግሥት ባለቤት ደግሞ ምልዓተ-ሕዝቡ ነው። የሕዝብን ፍላጎት ማወቁ ተገቢ ስለሚሆን፣ በሕዝብ ስም በደፈናው ጥግ-የያዘ ሙግት ውስጥ ከመግባት ባለፈ የጉዳዩ ባለቤት በሆነው ሕዝብ ፊት ግልጥ ውይይት ይደረግና ቢያንስ ሁኔታዎች ተስተካክለው ለውሣኔ-ሕዝብ ይቅረብና ውጤቱ ይታይ።

ይኽ የዜጎችን ጥቅምና ፍላጎት በክልል ማንነት የገደበ የፖለቲካ ሥርዓት በተፈጥሮ ባኅሪውም ይሁን በዓይነቱና በይዘቱ፣ እንዲሁም በውጤቱ በቁጥር አናሳ የሆኑ ነጮችን የበላይነት ለማረጋገጥ ታስቦ በብዙ እጥፍ አብላጫ ቁጥር ያለውን የአገሪቱ ሕዝብ፣ በተለይም ቱባውን አፍሪቃዊ፣ ለጭቆና ከዳረገው የደቡብ አፍሪቃ ዘረኛ የአፓርታድ ሥርዓት የተለየ ነው ማለት አይቻልም። ኅብረተሰብን በዘርና በጎሣ በከፋፈለ በዚያ አስከፊ የአፓርታይድ ሥርዓት ሥር የማቀቀው የደቡብ አፍሪቃ ሕዝብ ፍትኅንና እኩልነትን ማስገኘት የሚችል ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ እንዳልቻለ የታወቀ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የደቡብ አፍሪቃ ሠፊ ሕዝብ ይገኝ በነበረበት ተመሣሣይ የልዩነት ሥርዓት ሥር ሆኖ ምርጫ በማካሄድ የተለየ ውጤት ይገኛል ብሎ ማሰብ ከንቱ ምኞት ይሆናል።

የዜጎች እኩልነትን፣ ዴሞክራሲና ፍትኅን ከፈለግን ዴሞክራሲያዊ ሕገ-መንግሥት እንዲኖር የግድ ይላል። ስለ ሕገ-መንግሥት የሚነሳው ጥያቄ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር፣ የአገር አንድነት ለአደጋ እንዳይጋለጥና ተስፋ ላለው አዲስ ዴሞክራሲያዊ-ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት እውን መሆን አስፈላጊ ነው። ስለሆነም፣ የሕገ-መንግሥት ጉዳይ አንድም ምርጫ ከመደረጉ በፊት እንዲታይ፣ ካልሆነም ቀጣዩ ምርጫ ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚቆይ መደበኛ ተወካዮች የሚመረጡበት ሣይሆን የሕገ-መንግሥት ሸንጎ የሚሰየምበት ቢሆን የተጀመረው ለውጥ ሂደቱን የተሳካና ታሪካዊ ውጤት እንዲኖረው ያደርጋል የሚል እምነት አለን። ሕዝባችን ዘለቄታዊነት ለሚኖረው ዴሞክራሲያዊ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ባለቤት እንዲሆንና አገራችን የሚገባት ከፍታ ላይ እንድትደርስ ይኽን ለማድረግ ድፍረቱና ቁርጠኝነቱ ሊኖረን ይገባል። የችግራችን ምክንያት የሆነውን ሣይሆን ችግር ፈጻሚውን (መልዕተኛውን) ብቻ በማስወገድ ዘለቄታዊነት ያለው መፍትኄ ይገኛል ብሎ ማሰብ፣ ‘አህያውን ፈርቶ፣ ዳውላውን’ እንደሚባለው ይሆናል።

ስለሆነም፣ ምርጫን ከአጠቃላይ የአገራችን ውስብስብ የፖለቲካ ሁኔታ ለይተን በተናጠል የምናየው ሊሆን አይገባም። አሁን በሚንጸባረቀው ‘በክልሌ አትድረሱብኝ’ መንፈስና ሥነ-ልቦና የተቃኘ የፖለቲካ ይዞታ ባለበት ሁኔታ ምርጫ ይካሄድ ከተባለ፡ ተሣትፎውም አገራዊ ሣይሆን ዓይን ባወጣ መልክ አግላይና የተለያዩ ሉዓላዊ አገሮች የሚያደርጉትን ነው ሊመስል የሚችለው። በዜጎች መኻል፣ ያውም በቡድን (በወል) ፍረጃ፣ የተተከለና የሚገፋ የፖለቲካ ቅኝትና ያንንም መሠረት ያደረገ አግላይ የአደረጃጀት ሥርዓት፣ የልዩነት አጥርን የሚያደነድን ብቻ ሣይሆን በኅብረተሰብ መኻል ቀውስን የሚጋብዝና ያም የእርስ-በርስ ትርምስንና አይቀሬ እልቂትን ስለሚያስከትል፣ በጋራ መስዋዕትነት የቆመችና የነፃነት አርኣያ ሆና የቆየችውን ኢትዮጵያችን ኅልውና ከፍተኛ አደጋ ላይ እንደሚጥል አጠራጣሪ አይሆንም።

ይኽ የፖለቲካ ሥሪት ክልሎች እራሣቸውን እንደ-ሉዓላዊ አገር እንዲቆጥሩ የፈቀደ በመሆኑ፣ አሳዛኝና አሣፋሪ ውጤቱንም ዜጎችን እንደ-ባዕድ ቆጥሮ ከማፈናቀልና አሰቃቂ የጅምላ ጭፍጨፋ ከማድረግ ጀምሮ እነሆ አገራችንን ከውጭ ወራሪ ጠላት ጋር የሚደረግ እስከሚመስል ለደረሰ የእርስ-በርስ ደም-አፋሳሽ ጦርነት ዳርጓል። ይኽ ሕገ-መንግሥት ላለንበት አስቸጋሪና ኀልውና-ተፈታታኝ ከባድ ችግር እንደዳረገን ከዚኽ የበለጠ ማሣያ ሊኖር አይችልም። ይኽንን እውነታ እያዩ እንዳላዩ መሆንና እዝነ-ኅሊናን በጊዚያዊ ጠባብ የፖለቲካ ትርፍ ግርዶሽ ሸፍኖ ለማለፍ መከጀል፣ የጋራ ውድቀትን ሆን ብሎ ከማስተናገድ የተለየ አይሆንም። ያ ደግሞ ተራ የፖለቲካ ስህተት ሣይሆን፣ በአገርና በሕዝብ ዕጣ-ፈንታ ላይ አክሣሪ ቁማር ከመጫዎት፣ የበደል-በደል እና የአገርና የሕዝብ ጠላትነት ከመሆን አያልፍም። ለዚኸ አንገብጋቢ ጉዳይ የሚገባውን ትኩረት አለመስጠትና መልካምን እየተመኙ ብቻ ባለበት ለመቀጠል ማሰብ ምናልባት የሚጠቅመው የአገራችንን ሰላም፣ አንድነትና እድገት እንደ ስጋት ለሚመለከቱ ታሪካዊ ጠላቶች እንጂ ለኢትዮጵያዊያን የሚያተርፈው በፀፀት የማይመለስ ጉዳት ብቻ ይሆናል።

ማንኛውም መጥፎ ሁኔታ ላወቀበት በውስጡ በጎ ነገርን ይዞ ስለሚመጣ፣ ከዚኽ ክቡር የሆነውን የዜጎች ሕይዎት ከበላውና አገራችንን ለአደጋ ካጋለጠ ችግር በቂ ትምሕርት ልንቀስምና ኢትዮጵያችንን ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ መሠረት ላይ ለማቆም፣ ለሕዝባችንም ዘለቄታዊነት ያለው ሰላም ለማስገኘት ቁርጥኝነቱ ሊኖረንና ጊዜውን በተገቢ ልንጠቀምበት ይገባል። የጧት ፀሐይ ሲነካው እንደሚረግፍ ጤዛ ብን-ብሎ ለሚጠፋ ጊዚያዊ ሥልጣንና ከሱም ጋር ተያይዞ ለሚመጣ ጥቅማ-ጥቅም እና ከጥቅሉ ኢትዮጵያዊነት ይበልጥ ለክፍፋዩ ሣይሆን፣ የአገርንና የሕዝብን ጥቅሞች በማስቀደም፣ ለዛሬ ሣይሆን ለነገና ተነገ-ወዲያ ትውልዶች በማሰብ፣ ከልዩነት ይልቅ አንድነትን ከመረጥን ኢትዮጵያችንን ልትደርስ ከምትችልበትና ከሚገባት የእድገትና የብጽግና ከፍታ፣ ዜጎቿም ወደ-ባዕድ አገር የሚስደዱ ሣይሆን የወጡ በጉጉት የሚመለሱባት ታላቅ አገር ማድረግ እንችላለን፣ ይገባልም።

ሠ-9. የዜጎችን መፈናቀልና ጭፍጨፋዎችን በተመለከተ፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈጸሙ የሕዝብ መፈናቀሎችንና ማንነትን መሠረት ያደረጉ ዘግናኝ የጅምላ ጭፍጨፋዎችን በተመለከተ ዝርዝር ጥናትና ምርመራ የሚያደርግ ገለልተኛ ልዩ አጣሪ አካል (ኮሚሲዮን) እንዲሰየምና ውጤቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር-ቤት ሊቅርብና የኢትዮጵያ ሕዝብ በይፋ እንዲያውቀው ሊደረግ ይገባል። የምርምሩ ዘገባም የሕግ-አስከባሪው ከደረሰበት ጋር ተዳምሮ ወንጅለኞች ከያሉበት ታድነው ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ ያስፈልጋል።

ሠ-10. የክልል ልዩኃይልን በተመለከተ፡

በ ‘ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች’ ስም በአገራችን ላይ የተጫነውና በዜጎች መኻል ልዩነትን መሠረቱና መርኆው ያደረገ ከፋፋይ የፖለቲካ ሥሪት በሕዝባችን የጋራ ኢትዮጵያዊ የወል እሴቶችና ማንነት ላይ የዘመተ፣ በተፈጥሮው ወደ-ውስጡ ብቻ የሚያይና ሌላውን ወገኑን እንደ-ባዕድ እንዲመለከት የሚያደርግ በመሆኑ፣ ወደ አንድነት ሣይሆን አገራችንንና ሕዝባችንን ወደ ከፋ የቀውስ አዙሪት ውስጥ የሚያስገባ አደገኛ፣ መዘዘ-ብዙ እና ጠንቀኛ መሆኑን ከአርባ ዓመታት በላይ የተሟገትንበትና ሕወሓት ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ደግሞ ጎጅነቱን በተግባር ያየነው ጉዳይ ነው። ይኽ ጦሠኛ የፖለቲካ ሥሪት በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሕዝባችን ላይ ያስከተላቸውን ዘግናኝ የወንጀል ድርጊቶች ተመልክተናል። ‘በደንባራ በቅሎ ቃጭልም ታክሎ’ እንዲሉ፣ ይኽ ከፋፋይ የፖለቲካ ሥሪት ለብቻው በአንዲት-አገር ዜጎች መኻልና በአገር ላይ የሚያስከትለው ጦስ ሣያንስ፣ እነሆ ልዩኃይልበሚባል ከአገር መከላከያ ሠራዊት የሚገዳደር ታጣቂ ክፍል እንዲታጀብና እንዲጎለብት ሆኗል።

በአገራችን በየአካቢው የሚገኝ መለስተኛ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት ያለው ታጣቂ ኃይል ድሮም እንደነበር ይታወቃል። በንጉሡ ዘመን ቀደም-ሲል ‘ነጭ-ለባሽ’ የሚባልና በኋላ በአገር ደርጃ የተሻለ አደረጃጀት ይዞ ‘ብሔራዊ-ጦር (ሕዝባዊ-ሠራዊት}’ የሚባል ታጣቂ ኃይል ነበር። የዚኽ ታጣቂ ኃይል የግሉን የነፍስ-ወክፍ የቃታ-ጠመንጃ የታጠቀና ከመደበኛ ፖሊስ ጋር በመተባበርም ይሁን ለብቻው በአካባቢው የሚገኝ ቀማኛና ሽፍታን በማደን ለፍርድ የማቅረብ፣ የውጭ ጠላት ሲኖርና ክተት ሲታወጅ ደግሞ የሚዘምት የአርሶ-አደር ጦር ነበር። ይኸ ኃይል በደርግ ጊዜ ሥልጠናና ትጥቅ እየተሰጠው ከመደበኛው እግረኛ ሠራዊት ጋር በመዝመት ለአገሩና ለሕዝብ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጓል። የዚያ ሕዝባዊ ጦርና የአሁኑ ልዩ-ኃይል በሚባለው ታጣቂ መካከል ያለው መሠረታዊ ልዩነት የትጥቅ ብቻ ሣይሆን መሠረታዊ አደረጃጀቱና ዓላማው ነው። የብሔራዊው (የሕዝባዊው) ጦር ተኣማኒነትና ተጠሪነት ለአንዲት አገሩ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ብቻ ነው። የአሁኑ የክልል ልዩኃይል ቀጥታ ተጠሪነት፣ ተጠያቂነትና ተኣማኒነት ግን ለክልሉ ሕገመንግሥት ነው።

በአገራችን ላይ ያለው ልዩነትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ርዕዮትና አደረጃጀት ያለው አሉታዊ ተጽዕኖ በክልል በተዋቀረውና ተኣማኒነቱ ለክልል በሆነው ታጣቂ ኃይል ላይ ብቻ ሣይሆን በጽንሰ-አሳብ ደረጃ ተኣማኒነቱ ለአገሪቱ ሕገ-መንግሥት በሆነው የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ እንደሆነ በሰሜን-ዕዝ ሠራዊት ውስጥ በጄኔራል ማዕረግ በጦሩ ላይ የአመራር ኃላፊነት ከነበራቸው ጀምሮ እስከ መሠረታዊ ወታደር ባሉ እርከኖች የነበሩ የሕወሓት አባላት ለአገራቸው ለኢትዮጵያ በመሃላ የገቡትን የተኣማኒነት ቃል ሽረው ለክልላቸው ድርጅት ቅድሚያ በመስጠት በራሣቸው የጦር ጓደኞች ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ በማካሄድ ጭምር ታሪክ ይቅር የማይለው ከፍተኛ የአገር-ክኅደት ወንጀል ሊፈጽሙ ችለዋል። አሁን በሚደረገው ፍልሚያም በጡረታ የተገለሉት ሣይቀሩ ከድርጅታቸው ጎን ተሠልፈው የአገራቸው መከላከያ ኃይል ላይ በመዝመት ተቀዳሚ ተኣማኒነታቸው የት ላይና ለማን እንደሆነ እየታየ ነው። አገርንና መንግሥትን ወክለው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ዜጎች ሣይቀሩ በሚያሣፍር መልኩ ታማኝነታቸውን ከአገራቸው አስበልጠው ለጎሣቸው ሲሰጡ እያየን ነው። በዚኽ ጠባብ የማንነት እሳቤ የተበከለ ፖለቲካችን ምክንያት፣ ለአገር ሙሉ ተአዓማኒነትን፣ ብቃትና ችሎታን በሚጠይቀው የዲፕሎማሲ መስክ በኃላፊነት የሚደረገው ምደባ ይኸንኑ የማንነት መመዘኛን የተከተለ መሆኑ የሚያስከትለው ችግር በተግባር ታይቷል። ይኽ መቸም ቢሆን መሆን ያልነበረበት፣ ወደፊትም መደረግ የማይኖርበት አሣፋሪ ተግባር ነው።

ከሁሉም መንግሥታዊ መዋቅሮች መኻል ዜጎች ከቋንቋ፣ ከሐይማኖትም ሆነ ከአካባቢ ማንነት በላይ በወንድማማች/እህትማማች መንፈስና በማይበጠስ የአንዲት አገር ቃል-ኪዳን ትሥሥር የተጋመዱበትና መታወቂያቸውና የማንነታቸው መገለጫ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ብቻ በሆነው የመጨረሻ አይነኬ የአንድነት ጎራ የአገር መከላከያ ሠራዊት መኻልና ውስጥ ይኽ መከሰቱ በአገራችን እንዲሰፍን የተፈቀደለት መርዘኛ የፖለቲካ ሥርዓት ምን ያኽል እኛነታችንን እንደተፈታተነንና አደገኛነቱን ሁላችንም የምር ልንረዳ ይገባል። ይኽ መቸም ቢሆን በአንድ አገር የሠራዊት ተቋም ውስጥ ሊኖር የማይገባው አሣፋሪና እጅግ አደገኛ ሁኔታ ነው። ይኽ ሁኔታ በሠራዊቱ ውስጥ ሊኖር የሚገባውን መሠረታዊ የሆነና ጨርሶ ጥያቄ ውስጥ የማይገባ ፊጹም የመተማመን ይዞታ (Esprit de corps) በእጅጉ የሸረሸረ በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረትና አስቸኳይ መፍትኄ ሊሰጠው ይገባል።

በአገራችን እንዲሠፍን የተፈቀደለት የፖለቲካ ሥርዓት በመከላከያ ሠራዊታችን ሣይቀር በመንግሥታዊ መዋቅሮች ውስጥ ምን-ያኽል ሰርጾ እንደገባና ያም በአገርና በሕዝብ አንድነትና ደኅንነት ላይ የሚኖረው አደገኛ ተጽዕኖ በተገቢ ሊጤንና እንደ-አገር ከእነዚኽ በተግባር ከታዩ ኩኔቶች በቂ ትምሕርት ሊቀሰም ይገባል። ምንም-እንኳ በአሁኑ ጊዜ የሕወሓትን ያኽል በመሣሪያ ኃይል የተጠናከረ ክልል ባይኖርም፣ የክልል አስተዳደር አደረጃጀቱም ይኸንኑ በአብዛኛው ማንነትንና ቋንቋን መሠረት ባደረገ መሥፈርት የተዋቀረና ታማኝነቱ ለክልሉ በሆነ የታጠቀ ኃይል የታጀበ በመሆኑ፣ በክልል አመራሮችና በማዕከላዊ መንግሥት መኻል የሚፈጠር አለመግባባት እንዲሁ በሰላማዊ መንገድ ይፈታል ብሎ ማሰብ እንደማያዋጣና በሠራዊቱ ውስጥ ባሉ አባላት ዘንድ ሊያሳድር የሚችለውን አሉታዊ የሥነ-ልቦና-ጫና-ለወለደው አለመተማመን እንደሚዳርግ፣ ለውጭ ጣልቃ-ገብነት በር እንደሚከፍትና ያም ምን ያኽል አገርን ለአደጋ ሊያጋልጥ እንደሚችል በጥሞና ማስተዋሉ ተገቢ ይሆናል።

ታላቂቱንና ታሪካዊቷን ኢትዮጵያ ለዚኽ አሣፋሪ የእርስ-በርስ አለመተማመን የዳረገንን ይኽ መዘዘ-ብዙ የፖለቲካ ቅኝት እስካሁን ድርስ በአገርና በሕዝብ ላይ ያስከተለውን ችግር በመረዳት ሰላማዊ መፍትኄ ሊገኝለት ይገባል። በቅድሚያ ግን ማንኛውም ክልል በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 52 ቁጥር 2 (ሰ) እንደተፈቀደው ከሕግ አስከባሪ ፖሊስ ውጭ ታጣቂ ኃይል በዚኽ ደረጃ የሚያስፈልግበት ምክንያትም ሆነ ሕጋዊ መሠረት ስለማይኖር አፋጣኝ መፍትኄ ሊፈለግለት ይገባል። ሌላው ቢቀር፣ እስካሁን እንደሚታየው የክልል አወቃቀር ከተፈጠረ ጀምሮ ሁሉንም ክልሎች የሚያስተዳድሩት ተመሣሣይ የየክልሉ ገዥ-ፓርቲ አባል ወይም ተባባሪ የሆኑ ድርጅቶች ብቻ ስለሆኑ፣ ሌሎች ድርጅቶች የመወዳደር ዕድል ቢኖራቸውም እንኳ ቀጣሪና አባራሪ ሆኖ የቆየውና ከሞላ-ጎደል ሁሉንም አስተዳደራዊ-መዋቅሮች የሚቆጣጠረው ገዢ ድርጅት በሥልጣን ላይ ለመቆየት ሲል በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ይኽን ታጣቂ ኃይል ጫና ለማሳደርና ለአፈና ሊጠቀምበት ስለሚችል፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚኖረው አሉታዊ አስተጋብዖ በቀላሉ የሚገመት አይሆንም።

ስለሆነም፣ አገራዊ ምርጫ ከመደረጉ በፊት ይኽንን የክልል ልዩ-ኃይል የሚባል ታጣቂ ክፍል ቁጥሩንና የትጥቁን (የመሣሪያውን) ዓይነት በሕግ ከመገደብ ጀምሮ የተወሰኑትን አነስ-ያለ ቁጥር ያለው ፈጥኖ-ደራሽ ክፍል በማቋቋምና በዚያ ውስጥ እንዲያገለግሉ በማድረግ፣ የተወሰኑትን ወደ-ክልሉ ፖሊስ በማዛወር፣ ፍላጎትና ብቃት ያላቸውን በአዲስ መልክ በቂ ሥልጠና (በተለይም ረዘም ያለ በአገራዊ ሥነልቦና ሊታነጹ የሚችሉበት ትምሕርት እየተሰጣቸው) የአገር መከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀሉ፣ የቀሩትን ከክልላቸው ውጭ በሚገኙ የሥራ መስኮች እንዲሠማሩ በማድረግ ደረጃ-በደረጃ ማፍረስ ያስፈልጋል። ለተሟላ መፍትኄ ግን ልዩ የጥናት አካል ቢሰይም መልካም ይሆናል።

ሠ-11. አገራዊ የምክክር ሸንጎ፡-

ድርጅታችን ከአሁን በፊት በተደጋጋሚ እንዳሳሰበው ሁሉ፣ የአገርና የሕዝብ ጉዳይ ለገዥው ፓርቲ ወይም ለተወሰኑ ክፍሎች ብቻ የሚተው ሣይሆን ሁሉንም በየደረጃው፣ በተለይም የፖለቲካ ድርጅቶችን በቀጥታ የሚያገባ ስለሆነ፣ በተበታተነ መልክ ሣይሆን በተሰባሰበና በኃላፊነት መንፈስ በጋራ መምከር የሚችሉበት መድረክ ሊኖር ይገባል። የአገርና የሕዝብ አንገብጋቢ ጉዳዮች አልፎ-አልፎ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎ-ፈቃድ በሚጠሩም ይሁን በምርጫ-ቦርድ አማካይነት በሚካሄዱ ውሱን ስብሰባዎች ላይ በሚደረጉ ከጥያቄና መልስ ያልዘለሉ የአጭር-ጊዜ የአሳብ ልውውጦች ብቻ ሊስተናገዱ እንደማይችሉ ሊታወቅ ይገባል። በሸንጎ መልክ በድርጅቶች መኻል የሚደረጉ ውይይቶችና የአሳብ ልውውጦች፣ በአገራችን ባሉ መሠረታዊ ችግሮች ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝና ከዚያም ተነስቶ ለችግሮቻችን ዘለቄታዊነት ያላቸው መፍትኄ-አስገኚ ስምምነቶችንና እነዚያም ተግባራዊ ስለሚሆኑበት ሁኔታና መንገድ የጋራ መግባባት ለመያዝ የተሻለ መድረክ ይሆናል። በተጨማሪም፣ በመንግሥት በኩል ለተሠሩ በጎ ተግባራት ድጋፍ መስጠት ብቻ ሣይሆን ጉድለቶችና ግድፈቶች ሲከሰቱ ሰብሰብ ያለ ትችትና የተሻሉ አማራጭ አሳቦችን በማቅረብ ያለባቸውን ኃላፊነት መወጣት ያስችላቸዋል፣ ይገባቸዋልም።

ይኸን ማድረጉ አንደኛ ድርጅቶች በአገርና በሕዝብ ጉዳይ የመገልል ስሜት እንዳያድርባቸውና ከተናጠል አሳባቸው ወደ-አገራዊ ጉዳዮች እንዲያተኩሩ፣ የሩቅ ተመልካችና ባይተዋር ሣይሆኑ የራሣቸውን የኃላፊነት ድርሻ እንዲወጡ ዕድል ይሰጣል። ሁለተኛ ድርጅቶች በርቀት ሆነው በተገቢ ሳይተዋወቁ እንደ-ባዕድ ከመተያየትና አንዱ በሌላው ላይ ካለው የራሱ ግምት በመነሣት እርስ-በርስ ከመጠራጠር አባዜ ለመላቀቅና የተሻለ በመቀራረብ በአቋሞቻቸው ዙሪያ ከግንባር እስከ ውኅደት ለመሄድ የተሻለ ዕድል ስለሚፈጥር የድርጅቶችን ቁጥር በእጅጉ እንዲቀንስ ለማድረግ ይረዳል፣ አለመግባባቶችንም በሰለጠነና በሰከነ ሁኔታ በውይይት የመፍታት ባኅልን ለማዳበር ይጠቅማል። ሦስተኛ፣ የታላቁ ኅዳሴ ግድባችንን በመሣሰሉ አገራዊ ጉዳዮችና ከባዕዳን የሚሰነዘሩ የጥቃት ሙከራዎችን ሆነ አገራዊ አንድነትን በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ እያንዳንዱ ድርጅት የየራሱን አቋም በተናጠል በሚሰጥ መግለጫ ከማቅረብ ይልቅ በአንድነት ቢገለጥ በመንግሥት በኩል ለሚወሰድና ሊያዝ ለሚገባ አገራዊ አቋም የተሻለ አጠናካሪ ድጋፍና ጉልበት ይሆናል። አራተኛ፣ በመንግሥት በኩል በውጭ ግንኙነት ይሁን በአገር ፖሊሲዎች ላይ ግድፈቶች ሲታዩ ድምፅን በጋራ በማሰማት ስህተቶች እንዲታረሙ ያግዛል። አምስተኛ ለአገራዊ የሰላምና የእርቅ ጉባዔ መልካም መንደርደሪያ ይሆናል። ስድስተኛ በገዥው ፓርቲና መንግሥት እና በተቃዋሚው ጎራ ለሚገኘው ክፍል የተሻለ መቀራረብና መተማመንን ይፈጥራል። ሰባተኛ የዚኽ ዓይነት የድርጅቶች መቀራረብ የተበከለውን የፖለቲካ አየር ሊያሰክነውና ለመድብለ-ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ መልክ መያዝ ይረዳል፣ ድርጅቶችም ከተስፈንጣሪ አቋማቸው ወደ መኻል ለመምጣት ዕድል ይስጣቸዋል።

ስለሆነም፣ ይኽ አገር-አቀፍ የምክክር ሸንጎ በአመራር ደረጃ ያሉ የድርጅት ተወካዮችን ያቀፈና ከሐይማኖት ተቋማት፣ ከሙያ ማኅበራት፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከወጣቶች፣ ከሴቶች፣ ከምሑራን፣ ወዘተ. የተወከሉ በታዛቢነት የሚሣተፉበት ሲሆን፣ በክብርት ፕሬዝደንቷ የበላይ ሰብሳቢነትና ከድርጅቶቹ በሚመረጡና በየሦስት ወሩ የሚቀየሩ ሰባት ሥራ-አስኪያጆች የሚመራ ይሆናል። (ስለ አደረጃጀቱና አሠራሩ ዝርዝር በድርጅታችን በኩል ለማቅረብ ፈቃደኞች ነን።)

አንድነታችን የጋራ ኅልውናችን መሠረት ነው!

አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ ይጠብቅ!!

ኢትዮጵያ በልጆቿ አንድነት ታፍራና ተከብራ በነፃነት ትኑር!!!

(*) የኢትዮጵያ ኅብረሕዝብ ብሔራዊ ንቅናቄ (ኅብረሕዝብ-ኢትዮጵያ)

ኅዳር ፳፫ ቀን ሽህ ፲፫ ዓ/ም

(*) የኢትዮጵያ ኅብረሕዝብ ብሔራዊ ንቅናቄ (ኅብረሕዝብ-ኢትዮጵያ) ከተለያዩ አውራጃዎች የመጣ ሕዝብ በተገኘበትና ከኅዳር ፲ እስከ ፲.፪ ቀን ፲፱፻፸፩ ዓ/ም (1978) ጎንደር (ፉጨና ማርያምአርማጭሆ) በተደረገ ጉባዔ ላይ በአገር-ወዳድ ኢትዮጵውያን ከተመሠረተው ‘የኢትዮጵያ ዴሞክሲያዊ አገር-ወዳዶች ድርጅት (ኢዴአድ)’፣ ጀምሮ በተለያዩ ጊዜዎች ተመሳሳይ አቋም ካላቸው ልዩ-ልዩ ድርጅቶች ጋር ውኅደት በመፍጠር በ፲፱፻፹፭ ዓ/ም ‘የኢትዮጵያ ሕዝብ ፌዴራል ዴሞክራሲያዊ አንድነት ፓርቲ (ኅብረሕዝብ-ኢትዮጵያ)’፣ ከዚያም ‘የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኅብረሕዝብ የአንድነት ንቅናቄ (ኅብረሕዝብ-ኢትዮጵያ/ በመጨረሻም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ብሔራዊ ፓርቲ ጋር በመዋኀድ ‘የኢትዮጵያ ኅብረሕዝብ ብሔራዊ ንቅናቄ (ኅብረሕዝብ-ኢትዮጵያ)’ በሚል ስያሜ የሚገኝ፣ በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ በመታገል ላይ ያለና እረጅም የትግል ታሪክ ያለው ድርጅት ነው።

hibrehizb

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.