የወልቃይት፣ የጠለምትና የራያ አወሳሰን፤ የሕገ-መንግሥት ጉዳይ አይደለም! – አንዱ ዓለም ተፈራ

አንዱ ዓለም ተፈራ
ሰኞ፣ ሕዳር  ፳ ፰  ቀን ፳ ፻ ፲ ፫ ዓመተ ምህረት  12/7/2020

Welkait Tegede 1

የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ለመጀመሪያ ጊዜ ተከዜን ተሻግሮ ወደ ወልቃይት ሲገባ፤ በቦታው ነበርኩ። ለምን እንደገባና ገብቶ ምን እንዳደረገ የነበረውን ሀቅ ከተረዳን፤ ዛሬ በቦታው መደረግ ስላለበት የአስተዳደር ውሳኔ፤ ትክክለኛ ግንዛቤ ይኖረናል። የዚህ ጽሑፍ መልዕክት ይሄው ነው።

የዛሬ አርባ ዓመት፤ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ሠራዊት፤ ወልቃይትን ተቆጣጥሮ፤ ሕዝቡ ራሱን አደራጅቶ እንዲያስተዳድር አድርጎ ነበር። ይህ አካባቢ ከአራቱ በቤጌምድርና ስሜን ክፍለ ሀገር ካሉት ዞኖች አንዱ ነበር። የወልቃይት ወይንም አራተኛው ዞን ተብሎ ይጠራ ነበር። በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የሚመራው ይህ ሠራዊት፤ እያንዳንዳቸው በሶስት ቡድኖች የተደራጁ፣ ሶስት ኃይሎች ነበሩት። የጠቅላላ ታጋዮች ድምር ቁጥር፡ ወደ አንድ መቶ ሃምሳ ይጠጋ ነበር። በወቅቱ በበለሳ ያለው የዞን ሁለት ክፍል ላቀደው የጥቃት ዘመቻ ዕርዳታ ስለጠየቀ፤ ሁለቱ የወልቃይት ኃይሎች ወደዚያ ተልከው ነበር። በቀሪው ኃይል የነበሩት ሶስቱ ቡድኖች፤ አንደኛው ክፍል ወደ ቆላው ወርዶ፣ መዘጋ ባለው መሬት እንዲንቀሳቀስ ተመደበ። ሁለተኛው ቡድን እዚያው ደጋው ላይ በደቡብ በኩል፤ ወደ ጠለሎ እንዲሄድና የጠገዴን ሁኔታ እንዲከታተል ተመደበ። እኔ የነበርኩበት ሶስተኛው ቡድን፤ አሁንም በደጋው ምዕራብ በኩል፤ ወደ ቀብትያ በመሄድ፤ ከዚያ ሆኖ ከጎንደር ወደ ሁመራ በሚወስደው መንገድ ያለውን የደርግ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዲከታተል ተመደበ። እኔ የዚህ ቡድን የፖለቲካ ኃላፊ ነበርኩ።

የኛ ቡድን፤ የቀብትያ ዋና ከተማ አዲ ሕርፃን ደረስን። በዚያ ትንሽ ቅይታ ካደረግን በኋላ፤ ወደ ምዕራብ የደጋው ጫፍ በመሄድ፤ ቁልቁል የቆላውን መሬት ከምናይበት ቦታ ደረስን። እግረ መንገዳችን ሾኔ የሚኖሩቱን ፊታውራሪ የሺወንድም አግኝቼ አነጋግሬያቸው ነበር። የደጋው ጫፍ ስንደርስ አንድ አራት ጓዶችን የያዘ ቡድን ወደ ቆላው ወርዶ፤ በሃከር አካባቢ ተጠግቶ፤ በዚያ የሰፈረውን ጦር ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዲከታተል ላክን። ሌሎቻችን በዚያ አካባቢ እንደምንጠብቃቸው ተነጋግርን። በስተሰሜን የተከዜ ወንዝና ኤርትራ፣ በስተምዕራብ ቆላውና በሩቅም የሱዳን ምድር ተንጣሏል። ከከብት ጠባቂ ወጣቶች ጋር እየተነጋግርኩ ባለሁበት ወቅት፤ አንድ ያካባቢው ነዋሪ ተጠጋኝና፤ “አያ ጓዱ! በስተአዲ ረመጥ የሚነፍሰው ጥሩ አይደለም!” አለኝ።

ከእረኞቹ ለይቼ ወደ ጎን ወሰድኩና፤ “ምንድን ነው?” ብዬ ጠየኩት። “ኧረ! እቺ የከብት ሌባ አዲ ረመጥ ገብታለች። ደሞ በጣም ብዙ ናት! ሁለት በጣሊዎን ናት! ገበያ ውዬ መምጣቴ ነው።” አለኝ። ያካባቢው ሕዝብ ለኛ ያለውን ፍቅር ስለማውቅ፤ ያለ ምንም ሌላ ጥያቄና መልስ፤ አመስግኜ አሰናበትኩት። በእረኞች በኩል መልዕክት ቆላ ለወረዱት ተልኮ፤ የቡድኑን አባላት ጓደችን በመሰብሰብ ስለሁኔታው ገለጥኩላቸው። በቀጥታ ወደ መዘጋ ወርደን፤ በወልቃይት ካሉትና ጠለምት ካሉት የሠራዊቱ አባላት ጋር ግንኙነት መፍጠር እንዳለብን ተረዳን። የአሁኑ ተልዕኳችን ይህ እንደሚሆንና፤ ወደ ቆላው የተላኩት ጓዶች፤ ወደ ደጋው ሳይወጡ፤ በሰሜን በኩል ቆላውን ይዘው በአዲ ጎሹ በኩል ወደ መዘጋ በመምጣት እንደሚያገኙን ተወስኗል። ወዲያው ተሰባስበን፤ በቀጥታ ወደ አዲ ሕርፃን የሚወስደውን መንገድ ትተን፣ በደቡብ በኩል ዳር ዳሩን በመጓዝ ከከተማው ለመግባት ወሰን። ከፊት ትግርኛ ተናጋሪ የሁኑ ሁለት ፈታሽ ጓዶችን አስቀድመን፤ ዝርዝር በማለት በፍጥነት ተጓዝን። አዲ ሕርፃን ደቡብ ምዕራብ ጫፍ ላይ ቀጥ ብሎ የወጣ አንድ ኮረብታ አለ። ሁላችንም አጣጥፈን በመታጠቂያን ላይ በጀርባችን የያዝናትን የመኝታ ልብሳችንን አውጥተን፤ እንደ አገሩ ሰው ነጠላ ለብሰናል። ጠመንጃዎቻን በዚችው ጨርቃችን ሸፍነናል። አንድ ግሬኖቭ ዲ ነበረንና እሱን መደበቅ ስለማይቻል፤ በመጨረሻ ከቡድኑ ወታደራዊ መሪ ኋላ ሆኖ፤ በትከሻው እንዲይዘው ተደርጓል። አንድ ማስ ጠመንጃ የያዘ ጓድ፤ ከመትረየሱ ኋላ ተመድቧል።

በዚህ የመስመር አሰላለፍ ስንገሰግስና ወደ አዲ ሕርፃን ስንጠጋ፤ “ጠጠው በል!” – ቁም ማነህ! የሚል ትዕዛዝ ከኮረብታው ላይ ተሰማ። ከፊት የነበሩት ጓዶች፤ የአጠቃላዩን ሁኔታ ስለተረዱ፤ የከብት ሌባዋ እዚህ እንደደረሰች አወቁ። “ንእና ኢና!” – እኛ ነን! በማለት አዘናግተው፤ ወደኋላ ላለነው ምልክት ሠጡን። በያለንበት ቁጭ አልን። እነሱ በቀስታ ወደኋላ መጥተው ወደኛ ሲጠጉ፤ ትንሽ ወደኋላ ተመልሰን ወደ ዘባጣው ገብተን፣ ራቅ ብለን ወደ አዲ ሕርፃን የሚወስደውን የመኪና መንገድ አቋርጠን ወደ ሾኔ አመራን። አሁን ፍጥነታችን ጨምሯል። ጥንቃቄ የሰዓቱ ጥሪ ነው። አስልተን ወደ ፊታውራሪ የሺወንድም ቤት ተጠጋን። ጠባቂዎችን አስቁመው ስለነበር፤ ሰላም መሆኑን አረጋገጥን። እሳቸው ሲያዩን ደስታቸው በጣም ጥልቅ ነበር። “እንኳን መጣህ! ካባቴ ጋር ልጅ ሆኜ ጣሊያንን እዚህ ሳናስገባ ተዋግተናል። ይሄ የቆላው ጥቅጥቅ ጫካ አለልን! እንኳን የናንተን መሣሪያ ይዘን፤ በጥቂት ነፍስ ወከፍ ነበር ጣሊያንን ያጠቃነው!” በማለት የሳቸውን ዕቅድ ደረደሩልን። እኔም ተልዕኳችን ሠራዊቱን ማግኘትና ሁኔታውን እኛም ማስረዳት ከነሱም መረዳት እንደሆነ ገለጥኩላቸው። እሳቸው ግን አይሆንም አሉ። ዘመዶቻቸውን አሰባስበው ሠራዊት እንደሚያቋቁሙና እኛ ከፍተኛ ሚና እንዳለብን ነገሩኝ። አንድ ቀን የግድ አሳደሩን። በበነጋታው ግን፤ እንደማያቆሙን ሲረዱ፤ ሸኚ መድበው በሰሜን በኩል ቆላ ወርደን፤ ብላምባ ላይ ወደ ደጋው ወጥተን በበሩ በኩል ወደ መዘጋ እንደምንወርድና ጓዶችን እንደምናነጋግር፤ የሳቸውንም ሁኔታ እንደምናስረዳላቸው ነግረናቸው ተሰናበትን።

ደጋው ደርሰን ከማውቃቸው ሰው ቤት ስጠጋ፤ ተደናግጠው ወጥተው፤ “ኧረ ታስፈጁናላችሁ! ቶሎ ይሄን ቦታ ልቀቁልን! በዚህ እኮ ነው የመጡትና የሚተላለፉት!” በማለት የድንጋጤና የፍርሃት ሁኔታቸውን ነገሩኝ። ሴቶቹን ቶሎ ምግብ አዘጋጅተው እንዲሠጡን አዘዙልን። ሴቶቹ “ዚአቶምስ . . . ” እኒህስ የኛዎቹ ናቸው – አሉና ምግብ ለማዘጋጀት ተጣደፉ። ትልቋን ሴትዮ ቀረብኩና፤ “ምን ሆነ?” አልኳቸው። “ኧረ! ምኑን ብየህ!” ብለው ባጭሩ አስቀመጡልኝ። ካዚያ ቀን በፊት በነበረው ዕለት ስብሰባ ገበያ ላይ ጠሯቸው። በስብሰባው የነገሯቸው፤ ከዚያች ዕለት ጀምረው ትግሬዎች እንደሆኑ፣ አማራ ትግሬነታቸውን እንደቀማቸው፣ ከዚያች ዕለት ጀምረው በትግርኛ ማልቀስና መዝፈን እንዳለባቸው፣ አቤቱታቸውን ጽፈው ለነሱ ማቅረብ እንዳለባቸው አዋጅ ነገሯቸው። እሳቸውም ለኔ፤ “እና ማን እኛን ምን እንደሆን ነግሮን ያውቃል! ደሞሳ እኛ ራሳችንን የማናውቅ ሆነን ነው እነሱ ሚነግሩን! በማንውቀውስ ይትባሕል እንዴት አርገን ነው የምንዘፍነውና የምናለቅሰው! ኧረ ጉድ ነው! መንግሥት ተሆኑ ደርግን አቸንፈው ከተማ ይግቡና ግብሩን እንልክላቸዋለን እንጂ፤ ተኛ መሃል ገብተው ይሄን አርጉ ያን አታድርጉ ምንድን ነው!” ብለው ምሬታቸውን ገለጡልኝ።

በጠለምትና በራያ የሆነውም ይሄው ነው። በሁለተኛው ቀን፤ በለሳ የሄዱት ኃይሎች ተመልሰው ሸረላ ላይ ከባድ ጦርነት አደረግን። አሰላለፉ አንድ ከአስር በላይ ነበር። በኛ በኩል አንድ መቶ ስድሳ የሚሆን ሲሰለፍ በትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር በኩል ከሁለት ሺህ በላይ ነበር። ጦርነቱን አቸናፊ ሳይኖርበት መሽቶ ሁለታችንም በያለንበት ቆምን። ስለ ጦርነቱና የአሰላለፍ ስልታቸው በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ። ባጭሩ፤ ከኛ በኩል አስራ ሰባት ቁስለኞች ነበርን። የሞተ አልነበረብንም። እኔ ከባድ ቁስ ከደረሰባቸው አንዱ ነበርኩ። አሁንም ሰባራ የቀኝ ክንድና ሰባራ የአጥንት መጋጠሚያ ይዤ እኖራለሁ። ከነሱ በኩል ሬሳቸውን ትተውት፤ የአካባቢው አራሾች ሬሳውን ማየት ስለከበዳቸው፤ ከሶስት ቀን ቆይታ በኋላ ሰማንያ አንድ እንደቀበሩ ነግረውኛል። በወልቃይት ካደረግናቸው ከባድ ጦርነቶች አንደኛው ይህ ነበር።

ከዚህ የተረዳሁት፤ ወልቃይት መግባታቸው የትግላቸው አካል እንጂ የሕዝቡ ወይንም የአስተዳደር ጉዳይ አይደለም። በየትኛውም ሕግ ተመርተው አይደለም። ሕዝቡን አስገድደው ትግሬ ለማድረግ ነው የዘመቱት። ይህ የሕገ-መንግሥት ጉዳይ አይደለም። በጉልበት የተወሰደ ቦታ ነው። ሁለተኛ ህዝቡ የኛ አላላቸውም። እኛን ሲያዩ፤ “እኒህስ የኛዎቹ ናቸው!” በማለት፤ ፍራቻቸውን ገልጠውልኛል። በአዋጅ ሕዝቡን ትግሬ፣ አካባቢውን የትግሬዎች ሊያደርጉ ነው ወልቃይት የገቡት። ከሁሉ የሚያስከፋው ደግሞ፤ ያካባቢውን ሕዝብ በመግደል፣ በማሰር፤ አስገድዶ አማራነቱን እንዲጥል በማድረግና አሳዶ ከአካባቢው በማስለቀቅ መሬቱን ወደ ትግራይ አጠቃለዋል። ከመሬቱ ጥቅም ጋር የተያያዘው የፖለቲካ ውሳኔያቸው፤ የሱዳን በርነቱና የመሬቱ ለምነት ዋናዎቹ ናቸው። ከትግራይ እየመጡ የሚሠሩና ገንዘባቸውን ይዘው ወደ ትግራይ የሚመለሱ ትግርኛ ተናጋሪዎች በየጊዜው መመላለሳቸው፤ በአካባቢው ትግርኛ እንዲነገር ረድቷል። ይሄንን መሠረት አድርገው ነው የትሕነግ መሪዎች ሕዝቡን ትግሬ፣ መሬቱን የትግራይ ለማድረግ የጣሩት።

ምን ጊዜም ቢሆን አንድን አካባቢ ለማስተዳደር፤ ሕገ-መንግሥቱ በሚፈቅደውና ሕዝቡና ፓርላማው በሚስማማበት መንገድ ማዋቀር ይቻላል። የወልቃይት፣ የጠገዴና የራያ አወቃቀር ከዚህ የተለየ ነው። እኔ የአማራ ወይንም የትግሬ መሬት የሚለው ትርጉም አይሠጠኝም። መሬቱ የኢትዮጵያ ሆኖ፤ የቀደም ነዋሪዎቹ ንብረት ነው። ሁሉም ባለቤት ነዋሪዎች መሬታቸውን ተነጥቀዋል። ከፊሎቹ ተገድለዋል። ከፊሎቹ ታስረዋል። ከፊሎቹ ተሰደዋል። ባለቤትነታቸውን ግን የሚሰርዝ ሕግም ሆነ አግባብ የለም።

በኔ እምነት፤ መልስ የሚሆነው፤ አገራችንን በጋራ አሁን ሕዝቡ እንደታደጋት ሁሉ፤ ባለቤትነቱንም በጋራ የምናደርግበት ሕገ-መንግሥት እንዲኖር ነው። ኢትዮጵያዊነት ወሰን የለውም። ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያዊት የትም ቦታ ኢትዮጵያዊነታቸው ነው ምልክታቸው። በኢትዮጵያዊነታቸው የትም ሊኖሩ ይገባል። የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ድርጅት ያስቀመጠው የክልል አስተዳደር የኢትዮጵያዊነት ጠር ነው። የተለየ የአስተዳደር መዋቅር ሊዘረጋ ይገባል፡፡ የአገራችን አንድ መቶ አስር ሚሊዮን ሕዝብ፤ በአስራ አንድ ክፍለ አገራትና በአንድ መቶ አስር አውራጃዎች ሊስተዳደር ይችላል። እያንዳንዱ አውራጃ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ እንዲኖርበት፤ የሕዝቡን እንቅስቃሴ፣ የገበያውን ሁኔታ፣ የመልክዓ ምድሩን አቀማመጥና ኩታ ገጠምነት በሚመለከት ሊጠናና ሊዋቀር ይችላል። ክልል የአስተዳደር አመቺ መዋቅር እንጂ፤ ከማንነት ጋር የተያያዘ መግለጫ አይደለም። ማናችንም ብንሆን የምንስተዳደረው በኢትዮጵያዊነታችን እንጂ ከወላጆቻችን በወረስነው የደም ምንጭ መሆን የለበትም። አለዚያማ ኢትዮጵያዊነታችንና ጀግኖች የሕዝቡ ፋኖና ወታደሮች ትግራይ ውስጥ የከፈሉት መስዋዕትነት የማን ተብሎ ሊፈረጅ ነው!

እዚህ ላይ መልሱ ያለው ከሕገ-መንግሥቱ ላይ ነው። ሕገ-መንግሥቱ ደግሞ ሁሉን ገዥ ሰነድ ነው። ይህ ሰንድ የያዛቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ። አሁን አገራችን የምትስተዳደርበት ሕገ-መንግስት፤ ያለ ምንም ጥያቄ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ሕገ-መንግሥት ነው። በውስጡ ጥሩ ነገሮች የሉት ማለት አይደለም። አሉት። መሠረታዊ ሂደቱና ግቡ ግን፤ የዚህን የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ዓላማ ማሟላት ነው። ለውጡ ግቡን የሚመታው ይሄን ሕገ-መንግሥት ትክክለኛ አለመሆን መቀበልና በዚህ ላይ ለውጥ እንደሚያስፈልግ አምኖ፤ ይሄን ለመተግበር መንገድ ሲጀመር ነው። የዓይን ምስክር ነኝ።

8 Comments

 1. ሕገ – መንግሰቱ ችግር አለበት ከተባለ ቆይቷል፡፡ ከምርጫ በኃላ ይታያል የሚባል ከሆነ እንኳን አሁን ያሉትን መሰረታዊ ግጭቶች፣ የመሬት ይገባኛል እና ማንነት ጥያቄ ለጊዜውም ቢሆን አፋጣኝ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል፡፡ በተለይ አማራ ክልል ያስመለሳቸው ቦታዎች በዚሁ ሊቆዩ ይገባል፡፡ አሁን በብልፅግና ፓርቲዎች ውስጥ ያሉ ባለስልጣናት የሚወራወሩት የቃላት ምልልስ አንደ አገር አስተዳዳሪ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ በውሰጥ ያለ ስሜትን በማንፀባረቅ ህዝብን ሊያበጣብጥ ወደሚችል ሁኔታ መገፋፋት ቢታገድ ጥሩ ነው፡፡ ከትህነግ ለመለቃቅ ስንት ተጋድሎ ሲያደርግ የነበረ ሰራዊት እና ህዝብ ይህንን አይጠብቅም፡፡ እንደ አገር /ኢትዮጵያዊነትን/ የማያንፀባርቅ ሃሳብ ነገ ተጠያቂነትን እንደሚያመጣ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

  ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!

 2. ዝባዝንኬህ ሰልችቶኝ እስከ ‘ “ጠጠው በል!” – ቁም ማነህ! የሚል ትዕዛዝ ከኮረብታው ላይ ተሰማ።’ እስከሚለው ብቻ ካነበብኩኝ በኋላ:

  አንተ ምላስህን ቆልፈህ አዲ … የምትላቸውና እንዲሁም ማይ…..፣ ለምሳሌ (ማይ ፀብሪ) በኦርጂናላቸው እና እንዲሁም ጥራት ባለው የትግርኛ ምላስ፣ ዓዲ … እና እንዲሁም ውሃ ጠብሪ ሳይሆን፣ ማይ ፀብሪ የሚባሉት ቦታዎች ሁሉ፣ ያኔ እኛ ከኮሎኒያሊስቶች ጋራ ወደ ባህር አካባቢ ስንዋደቅ፣ ከኋላ በኩል በአባትህ ምኒልክ ከእኛ ተነጥለው ወደ ሌላ አስተዳደር የተለጠፉ ነበሩ፣ ምናልባት አታውቅም ይሆናል እንጂ በንግስት ዘውዲቱ ዘመንም፣ ጎንደር የንጉስነት ማእረግ በተሰጠው ያጎትዋ ልጅ፣ ምንትሴ ጊዮርጊስ በሚተዳደርበት ጊዜም የአክሱም ከተማም ሳትቀር ለሶስት ቀናት ያህል በጎንደር ትስተዳድር ውላና አድራ ነብር:: ሃይለስላሴም ቢሆን በሌላዎች አቅጣጫዎች አካባቢ ተመሳሳይ ተግባራትን አካሂዷልና፣ እኛ አሁን እየሞከርን ያለነው እናንተን ዘላለማችሁን ከአጥር ገፊነት ነፃ ለማውጣት ነውና፣ ይልቁንስ መንፈሳዊ ቸሮታችንን አሜን ብላችሁ ተቀበሉ……….!

 3. አንአንዱ አለም አራጌ እናመሰግናለን እንዴት ጎትተዉ ኢዜማ እንዳስገቡህ ሲታሰብ ያሳዝናል ብርሀኑ በቀጥታ አንዳርጋቸዉ በተዘዋዋሪ ከዚያ ቦታ ቢገለሉ ምናልባት ኢዜማ ጥሩ አማራጭ ሊሆን ይችል ነበር ነገር ግን እነዚህ መርዘኞች ቀድመዉ ገብተዋል ድርጅቱንም መርዘዉታል ፈራ ተባ እያልክ ብዙ ከምታዉቀዉ ጥቂቱን ቀንጨበህልናል። ቦታዉ የተወረረ ነዉ የተወረረን ንብረት ለወራሪዉ ያጸና ህግ የለም እንደዉም በብዙ አገሮች እንደተደረገዉ የትግሬ ድርጂት አማራ ላይ ባደረሰዉ በደል እንደ ካሳ የሚሆን ተከዜን አልፎ ለአማራዉ ሊሰጥ በተገባ ነበር ይህ በሌሎች አገሮች ላይ ሁኗል ወደፊት በጽሁፍ እመለስበታለሁ።
  እናዉቃለን ይህ ጽሁፍህ እነ ብርሀኑንና አንጋቾቻቸዉን አይመቻቸዉም ያንተ ኢዜማ ዉስጥ መኖር ካንተ በላይ ጠቀሜታዉ ለነሱ ስለሆነ ግምባርህን አትጠፍ። እናመሰግናልን

  • ውድ ሰመረ
   እኔ አንዱ ዓለም አራጌ አይደለሁም። እኔ አንዱ ዓለም ተፈራ ነኝ። በብዙ ነገር እንለያያለን። ከብርሃኑ ነጋም ሆነ ከኢዜማ ጋር ፍጹም ግንኙነት የለኝም።

 4. Mr. Andu Alem – – I think there were some fighters among you I want to know about their whereabouts. They were killed in action during those days.
  Please send me your email so we can talk about it.

 5. ወያኔ የጫነብን የፓለቲካ ስርአት ቅኝ ገዢዎች የሚገዙዋቸውን ህዝቦች ህብረት ኖሮአቸው እንዳይነሱባቸው የተገበሩት ስርአት ነው። አባቶቻችን ምስጋና ይድረሳቸውእና፣ ፋሺስት ጣሊያን የዘር ፓለቲካ ብሎም ክፍፍል ሊጭንብን ሲሞክር ያገኘው ምላሽ ፍፁም አሉታዊ ነበር። የኛው ወገኖች ግን ቀባብተው በህገ መንግስት ደግፈው ክልል በሚል የዘር ክፍፍል ሀገራችንን ሸንሽነው አንዱ ወገን ተጠቃሚ ፣ ሌላውን ተጎጂ አርገው ሁሌ በጥቅም እንዱጣሉ ፣ ህብረት እንዳይፈጥሩና ገዢውን መደብ ያለ ሀይ ባይ እዲገዛን እርገዋል።
  ህዝበ ቀርቶ መሬቱ የዘርማንነት ተሰጥቶታል። ኬኛ፣ የኛ የደናቁርት ጨዋታ ሰፍኖአል። ድምር ውጤቱ ሀገራችን እንዳ ትለማ ፤ለጠላቶቻችን ምቹ ምሆን ነው። በባንዳነት የሚገኝ ጥቅማ ጥቅምን መቃረም ነው።
  አሁን ትህነግ ተቀብሮአል ፣ በግፍ የተገደሉ የመከላከያ አባላት ፣ የታረ ዱ ንፁሀን አማ ሮች ደም ሳይደርቅ የወያኔ ሌጋሲ አስቀጣዬች በመንግስት ሀላፊነት ቦታ ተቀምጠው የወያኔ ወራሾች አለን እያሉ ነው። እነኝህን እና መሰሎቻቸውን፤ትናት ለውድ ሀገራችን የተዋደቃችሁ ፣ በተኛችሁበት የተረሸናችሁ ፤ ኢስባዊ ድርጊት የተፈፅመባችሁ የመከላከያ ሰራዊትና የአማራ ልዩ ሀይል በቅንጅት በአብያችን መሪነት ይህን ፅረ ኢትዬይያ የሆነን ግልገል ጀንታ አደብ ሳታስገዙ ወደ ካምፓችሁ እድዳትመለሱ በኢትዬጽያ ስም እማፅናችሁዋለሁ።
  መደረግ ያለበት ሁሉም ነገር ወያኔ ከመምጣቱዋ በፊት ወደ ነበረው ሁኔታ/Status quo ante / እንዲመለስ ተደርጎ የኢትዮጵያን አንድነት ማእከል አድርጎ በአዲስ መልክ በዘር ላይ ያልተመስረተ ፌደራላዊ ስርአት መርዘትጋት ነው።
  ይሄን በእንጭጩ ካላጠፋችሁት ሌላ ዙር ምልናባትም ከአሁኑ የባሰ ክህደት እንደ ሚጠብቃችሁ አስተውሉ።
  God bless Ethiopia !

 6. ፋሽሽታዊዉና ጉግማንጉጉ ትሕነግ /ሕወሀት ምዕራብ ትግራይ ብሎ ሰይሞት የነበረዉ ዞን የሚያጠቃልለዉ ወልቃይትን ፤ጠገዴን ፤ሁመራንና ጠለምትን ነዉ፡፡ይህ ሰፊ አካባቢ ከ 320 ዓ.ም.ጀምሮ አስከ 1968 ዓ.ም.ብሎም 1983 ዓ.ም. ድረስ ይተዳደር የነበረዉ በጎንደር ጠቅላይ ግዛት ነበር፡፡በመሰረቱ የጎንደርና የትግራይ ወሰን የሚለየዉ የተከዜ ወንዝ ነዉ፡፡ይህንንም ታሪካዊ ሂደት “የወለቃይት ጉዳይ” የሚለዉን መጽሀፍ ደርሶ ታሪካዊዉን ዳራዉን አቶ አቻምየለህ ታምሩ አፍታቶታል ፡፡ ለዚህም ሊመሰገን ይገባዋል፡፡
  ወያኔ ትግል ሲጀምር በ 1968 ዓ.ም. ባወጣዉ ማኒፌስቶ አካባቢዉን የትግራይ አካል ነዉ በማለት ተሸቀዳድሞ ጠቅሶታል፡፡ በማስቀጠልም ቀስ በቀስ አካባቢዉን በመሳሪያ ሀይል ከ1971 ዓ.ም. ጀምሮ ተቆጣጠረዉ፡፡
  አካባቢዉ የትግራይ ያለመሆኑን እያወቀ፤ ሆን ብሎ ተከዜን በመሻገር ይህን ያደረገበት ምክንያት የሚከተሉት ናቸዉ፤
  • ትግሉን ሲጀምር ከመንግስት የሚደርስበትን ዉጊያ ለመከላከል ወደ ሱዳን ለመሸሽ ማፈግፈጊያ በመፈለጉ፤
  • ለትግሉ የሚያስፈልገዉን ስንቀና ትጥቅ ከሱዳን ለማጉዋጉዋዝ እንደ ኮሪደር ለመጠቀም፤
  • አካባቢዉ በጣም ለም በመሆኑ ለወደፊት የገቢ ምንጪ ያስገንልኛል በሚል እሳቤ በመያዙ፤
  • ከትግራይ ሪፑብሊክ ምስረታ በሁዋላ ከዉጪ ሀገራት ጋር ለመገናኘት፤
  • አካባቢዉ በጣም ለም በመሆኑ “ከትግሉ ድል” በሁዋላ ለታጋዮች እንደዉለታ ለም መሬት በመስጠት ለማስፈር በማሰቡ ናቸዉ፡፡

  በትግሉ ጂማሪ ይቃወሙናል ተብለዉ የታሰቡ ባላባቶችና ተወላጆች አንድ ባንድ እየተለቀሙ ተገድለዋል፡፡
  ከዚያም በመቀጠል እስከ 2013 ዓ.ም. ድረስ ማይካድራ ላይ እንደተፈጸመዉ ሁሉ የአካባቢዉ ተወላጆች ሲታሰሩና ሲገደሉ ኖረዋል፡፡ በመካከለኛ ግምት ወደ 15 ሺህ በላይ አካባቢዉ ተወላጆች ተገድለዋል፡፡ከዚህ ድርጊት በመለስ የአፓርታይድ አገዛዙ የዘር መድሎዉና ማሸማቀቁ ላለፉት 45 ዓመታት የቀጠለ ነበር፡፡በዚህም ተነሳ የአካባቢዉ ተወላጅ የትዉልድ አከባቢዉንና ቦታዉን ጥሎ እንዲሰደድ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ተግባራዊ ተደርጉዋል፡፡
  በ1984 ዓ.ም. ከትግሉ ፍጻሜ በሁዋላ 85 ሺህ(በመጀመሪያ 50 ከዚያም 35ሺህ) ታጋዮችን እስከነመሳሪያቸዉ በአካባቢዉ አስፍሮአል፡፡
  ከዚህም በተጨማሪ ወደ ሁለት ሚሊዎን የሚጠጋ ህዝብ ከትግራይ በማምጣት በተለያየ ጊዜ አስፍሮአል፡፡ ሌሎችም በራሳቸዉ ፈቃደኝነት ሰፍረዋል፡፡
  በመሀሉም አንዳንድ ቆራጥ አካባቢዉ ተወላጆች በህግ ይመለስልናል በሚል እሳቤ ለተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አቤቱታ ያቀረቡ ቢሆንም ጀሮ ዳባ ከመባላቸዉ ባለፈ ተሳደዋል ፤ታስረዋል ፤ተገድለዋል፡፡
  ከሁለት ዓመት በፊትም የተቁዋቀመዉ የወሰንና ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ግዳዩን ይፈታዋል ተብሎ ቢታሰብ አንድም ነገር ጠብ አላለም፡፡ይህም፤ የወሰንና የማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ማየት የሚችላቸዉ ጉዳዮች በሕገመንግስቱ የተካለሉትን እንጅ ከዚያ በፊት በግዳጅና በሀይል የተነጠቁትን አይመለከትም፡፡ የተቁዋቀመበት ሕጉም አይፈቅድም፡፡ ይፍታዉ ተብሎ ቢታሰብ እንኩዋን ሂደቱ ትግራይን ክልል ዉሳኔ የሚጠይቅ በመሆኑ ሂደቱ በፍጹም የሚቻል አይደለም፡፡
  እንደሚታወቀዉ በአሁኑ ወቅት አካባቢዉ በአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሸያ ተጋድሎ ከአረመኔዉ እጅ ነፃ ወጥቶዋል፡፡ በሀይል የተነጠቀዉን በሀይል አስመልሱዋል፡፡
  ስለሆነም ትህነግ በጦርነቱ ሰለተሸነፈ የትግራይ ሕዝብ በማኩረፉ ብልጽግናና የፌደራሉ መንግስት እንደገጸበረከት በመስጠት ለማባበል እንደ ፖለቲካል ኢንትሪግ ለመጠቀም ያሰበዉ አካባቢዉን እንደነበረዉ ማስቀጠል ነዉ፡፡
  በመሆኑም፤ለመላ ወልቃይት፤ጠገዴ፤ሁመራና ጠለምት ሕዝብ ሆይ !!!!!
  ትግልህ ላለፉት 45 ዓመታት በትህነግ/በሕዉሀት የደረሰብህን የአፓርትይድ አገዛዝ ለማስወገድ ተጠናክሮ መቀጠሉ አይዘነጋም፡፡በዚህ ጊዜ ዉስጥ ቁጥራቸዉ የበዛ ወገኖችህ በገዛ ትዉልድ ሀገራቸዉ ተገልለዋል፤ታስረዋል፤ተሰደዋል፤ተገድለዋል፡፡ ሌላዉን ለጊዜዉ ብንተወዉ እንኩዋን በቅርቡ ማይካድራ ላይ ደረሰዉን ጭፍጨፋ መላዉ ዓለም አስተጋብቶታል፡፡ በዚህ ምድር ናዚዎች በአይሁዶች ላይ ያደረሱት ግፍና በደል በአንተም ላይ ደርሶብሀል፡፡የግፍ ጽዋዉ ሞልቶ በመፍሰሱ በአለማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሺያ ተጋድሎ ነጻነትህን ለመቀዳጀት በቅተሀል፡፡ ይሁን እንጂ የተቀዳጀኸዉን ነጻነት ነጥቀዉ፤ በነበረዉ መልክ ተመልሰህ ወደባርነት እንድተገባ የሚመኙና የሚያመቻቹ እንዳሉ መዘንጋት የለብህም፡፡በህግ ስም በሚደረግ የማታለያ ዘዴ በምንም ዓይነት እነዳትታለል፡፡የብልጽግና ፓርቲ -የፌዴራል መንግስት ሆነ የአማራ ብግጽግና የሚያቀርቡልህን መንገዶች በሙሉ እንዳትቀበል፡፡በመሸንገያ ሊቀርቡህና ሊያታልሉህ ይችላሉ፡፡በምንም መልኩ እምቢይ በላቸዉ፡፡ነጻነት እጅህ ዉስጥ ስለገባች አሳልፈህ እንዳትሰጥ!!!!!!!!
  ስለሆነም ፤ይህ የአፓርትይድና ባርነት ሁኔታ ተመልሶ እንዲመጣ እንደማትፈልግ ከፈለግህ ተደራጅ፤ንቃ፤ታጠቅ ከዚያም ሌት ተቀን ነቅተህ የተቀዳጀኸዉን ድል ጠብቅ፡፡
  በጊዜያዊ ፈንጠዝኛና የመደለያ ንግግር እንዳትታለል፡፡እሱን ድልህን ስታረጋግጥ ትደርስበታለህ፡፡
  በመጨረሻም ፤ አካባቢዉ መፍትሄ አስኪሰጠዉ ድረስ እንደነበረዉ ይካለላል በማለት ብልጽግና እያሾፈ በመሆኑ ጉዳዩ የሚመለከተዉ ሁሉ በማንኛዉም ዓይነት መንገድ አምርሮ ሊታገለዉ ይገባል፡፡የማዕከላዊዉን መንግስት ስልጣን የተቆናጠጠዉ አብይ አህመድ የሚጨነቀዉና ሙሉ ጊዜዉን ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራዉ ስልጣኑን ለማደላደልና ለማስጠበቅ ነዉ፡፡ ኢትዮጵያ፤ኢትዮጵያ በማለት ሲዘላብድ ልትታለል አይገባም፡፡የእሱም አጎብጎብጉቢ ተከታዮች እንደሱ ሁሉ በሚሰጡት አስመሳይ ንግግር ልንታለል አይገባም፡፡
  ይህ የአስመሳይ ፖለቲከኞች ዘዴ ነዉ፡፡ወቅቱን ጠብቀዉ መገለባበጥ የተለመደ ባህሪያቸዉ ነዉ፡፡
  የአንድን ፖለቲከኛ ሀቀኝነት መመመዘን ያለብህ በሚወስዳቸዉ ተጨባጭ እርምጃዎች ነዉ፡፡
  አብይ ለፓርላመዉ ንግግር ለማድረግ በቀረበበት ወቅት ከፓርላማ አባላት ከቀረቡለት ጥያቄዎች መሀከል ስለ ወልቃይትየቀረበዉአንዱ ነበር፤ሆኖም ዝባዝንኬ በሆነ ንግግር አለባብሶ አዘናግቶና አድበስብሶ አልፎታል፡፡ ከዚህም በጣም ጠቃሚ ትምህርት ዉሰድ !!!!!!!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.