የወልቃይትና የራያ ጉዳይ የማንነት፣ የፍትህና የዴሞክራሲ ጥያቄ ነውና የእርስትና ጉልት የማስመለስ እንቅስቃሴ አድርጎ ማቅረብ በሰው ቁስል እንጨት ከመስደድም የከፋ ግፍ ነው!!!

ከመሰረት ተስፉ

welkeitየኢህዴን ሊቀመንበር የነበረው አቶ ታምራት ላይኔና ሌሎችም ነባር የኢህዴን ታጋዮች እንዲሁም እነአቶ አብርሃም ያየህና ገብረመድህን አርዓያ በተለያዩ ጊዚያት ካደረጓቸው ንግግሮችና ካሰፈሯቸው ፅሁፎች እንደተረዳሁት የህወሓት ሰዎች በረሃ እያሉ ጀምረው ወልቃይትን ከጎንደር ራያን ደግሞ ከወሎ ቆርጠው ወደ ትግራይ ክፍለሃገር ለማካተት እቅድ የነበራቸው መሆኑን ነው። እንዲያውም እነአቶ አብራሃም ያየህስ የህወሓት ሰዎች ስግብግብ አላማ “ከአልውሃ ምላሽ” ያሉትን ቦታዎች ሁሉ ወደ ትግራይ ክፍለሃገር ማካለል ነው ብለው ቃለመጥይቅ ሲሰጡ አስታውሳለሁ። በዚህ መሰረትም የህወሓት ሰዎች አህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ ጀምሮ እስከ 1984 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ከላይ የተጠቀሱትን ቦታዎች ወደ ትግራይ እንዲካለሉ አድርገዋል። ከዚህ መረዳት የሚቻለው ቦታዎቹ የተካለሉት በህገመንግስቱ መሰረት ሳይሆን በህወሓት ሰዎች በመሳሪያ የፈረጠመ ክንድና ጡንቻ መሆኑን ነው። ፤ ምክንያቱም ህገመንግስቱ የፀደቀው 1987 ላይ ነውና።

የህወሓት ሰዎች በዚህ መልክ የመስፋፋት ፍላጎትቸውን እውን ካደረጉበት ጊዜ ጀምሮ በተጠናና በታቀደ መንገድ ከትግል የተቀነሱ ታጋዮችንና ሌሎችን ሰዎች ሲያሰፍሩ የየአከባቢዎቹ ነዋሪዎች ቅሬታ ሲያቀርቡ፣ ተቃውሞ ሲያሰሙና አለፍ ብለውም በመሳሪያ የታጀበ ትግል ሲያደርጉ ቆይተዋል። በተለይ ደግሞ ከተጠቀሱት ቦታዎች የተውጣጡ የማንነት አስመላሽ ኮሚቴዎችን አቋቁመው ተነጠቅን ያሉትን ማንነት ለማስመለስ እልህ አስጨራሽ ትግል አድርገዋል። በዚህ ረገድ እነዚህ የማንነት አስመላሽ ኮሚቴዎች በህጋዊ መንገድ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀረቧቸው ተደጋጋሚ አቤቱታዎች መልስ ተነፍገው መቆየታቸው ተጠቃሾች ናቸው። ይልቁንም ማንነታችን ይመለስ ብለው ይታገሉ የነበሩትን የየአከባቢዎቹን ተወልጆች በማፈን፣ በማሰር፣ በማሰቃየትና አልፎም በመግደል የመብት ትግሉን ለማኮላሸት የተደረገው ጥረት በቀላሉ የሚታይ አልነበረም።

ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ይህ የህወሓት ሰዎች ድርጊት ፍትሃዊ አይደለም ብለው ያምኑ የነበሩ ከወልቃይትና ከራያ ውጭ ያሉ አማራዎችና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ድርጊቱን ያወግዙና በፅናት ይታገሉም ነበር።  እነዚህ ኢትዮጵያውያን በተላያዩ ጊዚያት በነበሩ ድርጅታዊና መንግስታዊ መድረኮች ላይ ወልቃይትና ራያ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ወደ ትግራይ የተካለሉበት አግባብ ኢ-ፍትሃዊና ፀረ-ዴሞክራሲያዊ በመሆኑ ነዋሪዎቹ በግልፅ ተወያይተው ከተፀዕኖ ነፃ በሆነ መንገድ ማነታቸውን በራሳቸው ፍላጎት ይወስኑ የሚሉ ጠንካራ ትግሎች ያደርጉ እንደነበር እኔ ራሴ የምመሰክረው ሃቅ ነው። እየቆየም ማንነታችን ይመለስ የሚለው ህዝባዊ ትግል እየተጠናከረ ሄዶ በ2008 ዓ.ም እነ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ለመያዝ ወደ ጎንደር የተላከውን ቡድን መመከት ችሏል። ይህ ትግል የህወሓት ሰዎች መቀሌ እንዲወሸቁ ላደረገው ህዝባዊ እንቅስቃሴ እርሾ ሆኖም አገልግሏል።

በወቅቱ እኔም በበኩሌ የማንነት ነጠቃው ኢ-ፍትሃዊና ፀረ-ዴሞክራሲያዊ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የኋላ ኋላ በሃገር አንድነት ላይ አደጋ ይጋርጣል የሚል ስጋት ስላደረብኝ የችግሩን ክብደትና መፍትሄ ይሆናል ብየ የገመትኩትን ሃሳብ በፅሁፍ ገልጨ ነበር፤ እንደሚከተለውም ይነበባል፤

“…ለማንም ግልፅ እንደሚሆነው የህወሃት ሰዎች የሃገሪቱን ስልጣን ከተቆጣጠሩ ጀምሮ ያላቸውን በሴራ የታጨቀ የትግል ልምድና በመሳሪያ የተደገፈ ጡንቻ ተጠቅመው በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው እንዲሁም በማህበራዊ ጉድዮች ላይ በርካታ ግፎች ፈመዋል። እነዚህ ሰዎች በሰብአዊ መብቶች ጥሰት፣ በሙስና እና አድሎዋዊ በሆኑ አሰራሮቻቸው ወደር የለሽ መሆናቸውን ከኢትዮጵያ ህዝብ መደበቅ አልቻሉም። ይህ ትግራይን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በህወሃት ሰዎች አጋፋሪነት የተፈፀመ ግፍና መከራ ሊካድ የማይችል ሃቅ ቢሆንም በተለይ ደግሞ ከአማራ ክልል ባሉ አዋሳኝ ቦታወች የፈፀሙት ተጨማሪ ደባ [አይን ያወጣ] ስግብግብነታቸውን ያሳዩበት አሳፋሪ ድርጊት መሆኑ ግልፅ ነው። ገና ከበርሃ ትግላቸው ጀምረው የትግራይ ድንበርከአልውሃ ምላሽነው የሚል እቅድ ነድፈው ሲንቀስቀሱ ከቆዩ በኋላ ልክ የሃገሪቱን ስልጣን በተቆጣጠሩ ማግስት የወልቃይትንና የራያን አካባቢዎች ነዋሪዎቹ ሳይወያዩበትና በአግባቡ ሳይወስኑ የኛ ነው ወደሚሉት የትግራይ አስተዳደር እንዲካለሉ አደረጉ። ይህን ሲያደርጉ በየአከባቢው የነበሩ ነዋሪዎች ተቃውሞ ሲያሰሙ እንደነበር በግልፅ ይታወቃል። ግን በጥቅም የታወሩት የህወሓት ሰዎች የነዚህን ነዋሪዎች ጩኸት የሚሰሙ ጆሮዎች አልነበሯቸውም።

በእኔ እይታ ከላይ ለተገለፀው ችግር እልባት በመስጠት ረገድ ለጊዜው የሚታየኝ መፍትሄ በነዚህ በተጠቀሱ አካባቢዎች ህዝበውሳኔ ሊካሄድ ይችል ዘንድ  ሰላማዊ፣ ፖለቲካዊና ህጋዊ መንገዶችን ሁሉ ተከትሎ መታገል ነው።

እዚህ ላይ ህዝበውሳኔ ሲባል የትኛው ህዝብ የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። ምክንያቱም ቦታወቹ ወደትግራይ ከተካለሉ በኋላ በታቀደ ሰፈራና በሌላ መንገድ እንደ አዲስ መኖር የጀመሩ ሰዎች አሉና ነው። በእኔ እምነት በህዝበውሳኔው ሊሳተፉ የሚገባቸው ሰዎች ቦታወቹ ወደትግራይ ከመካለላቸው በፊት ይኖሩ የነበሩ ብቻ ሊሆኑ ይገባል እላለሁ። ይህ ሂደት ሁኔታዎችን ወደነበሩበት ስለሚመልሳቸው የተፈጠሩ ችግሮችን ሊያርም እንደሚችል መገንዘብ ይቻላል። ጉዳዩ ከመቶ ወይም ከሁለት መቶ አመታት በፊት ተፈፀመ የሚባል አፈታሪካዊ ውንጀላ ሳይሆን በኛው ትውልድ የታዘብነው ስለሆነ ተጨባጭ ማስረጃ ለማቅረብም የሚያዳግት አይደለም።

ከዚሁ ተያይዞ እነዚህን ነዋሪዎች እንዴት ማወቅና መለየት ይቻላል የሚል ጥያቄ ቢነሳ ስህተት አይሆንም። በርግጥ ነዋሪዎቹን ለመለየት ብዙ ስራ ሊጠይቅ ይችላል። ይሁንና ካለው ጠቀሜታ አንፃር የወሰደውን ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ ወስዶ ከዚህ በፊት የተደረጉ የህዝብ ቆጠራ ሰንዶችን፣ የግብር ከፋይ ደረሰኞችን እንዲሁም በየአካእባቢው የሚገኙ መዛግብቶችን በማገላበጥ የሰዎቹን ማንነት መለየት ይቻላል። የህወሓት ሰዎች ይህን መንገድ አንቀበልም ካሉ ማንነታችን ተነጥቀናል የሚሉት የየአከባቢዎቹ ነዋሪዎች፣ ደጋፊዎቻቸው፣ የአማራ ክልል ገዥ ፓርቲና ክልላዊ መንግስቱ ሊኖራቸው የሚገባው ሚና ፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ እንዲገባ ግፊት ማድረግ ብቻ ይሆናል።

አለመታደል ሆኖ ግን ባለፉት ሰላሳ አመታት ይህ ሲሆን አልታዘብኩም። ምክንያቶቹ ደግሞ የፌዴራል መንግስቱ ችልተኝነትና የህወሃት ሰዎች እብሪት ናቸው ብየ አምናለሁ። ይህ በመሆኑም ሰሞኑን እየታዘብነው እንዳለነው ሃገሪቱ ብዙ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ እየደረሰባት ይገኛል። አሁን ግን እብሪተኞቹ የህወሃት ሰዎች ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በመፈፀማቸውና አማራ ክልልንም ለመውረር እንቅስቃሴ በማድረጋቸው ምክንያት በመከላከያ ሰራዊቱና በአማራ ህዝባዊ ሃይል ጥቃቱ ተቀልብሶ እነሱም ሸሽተው የቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ እንዲደበቁ፤ በአንፃሩ ደግሞ ማንነታችን በሃይል ተነጠቀናል የሚሉት የወልቃይትና የራያ ነዋሪዎች (እደግመዋለሁ: የወልቃይትና የራያ ነዋሪዎች) ከባቢያቸውን ተቆጣጥረው ድሮ ወደየነበሩበት የጎንደርና የወሎ አከባቢዎች መቀላቀላቸውን በደስታ እየገለፁ ይገኛሉ። አሁን ዋናው ነገር ከዚህ በኋላ ሁኔታዎች ምን መልክ ይኑራቸው የሚለው ፍሬ ነገር ስለሆነ በጉዳዩ ላይ የግሌን ሃሳብ እንደሚከተለው ለማቅረብ እሞክራለሁ።

በእኔ እምነት አሁንም መፍትሄው የህዝብን ጥቅም ያማከለ መሆን አለበት እላለሁ። ይህ ማለት ምን ማለት ነው?

1ኛ) የህወሓት ሰዎች ወልቃይትና ራያ ላይ ያደረጉት የመሬት ማካለል ከመሰረቱም ፉርሽ (void ab initio) መሆኑን በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል። ምክንያቱም በወቅቱ ቦታዎቹ ላይ ይኖሩ የነበሩ ዜጎች አልተወያዩም፤ አግባብ ያለው ነፃና ገለልተኛ የሆነ ህዝበ-ውሳኔም አላደረጉም። ሌላ ህጋዊም ሆነ ሞራላዊ መሰረትም አልነበረም። ነበረ ከተባለም የህወሓት ሰዎች በመሳሪያና ከህዝብ በተዘረፈ የገንዘብ ሃይል የፈረጠመ ጡንቻ ብቻ ነው። በመሆኑም ፈረንጆቹ Restitution እንደሚሉት የወልቃይትና የራያ ነዋሪዎች በሙሉ ፍላጎታቸው ተመስርተው ቀድመው ወደነበሩበት ከባቢዎች መመለሳቸው ተፈጥሯዊ መብታቸው ነው። ስለዚህ ይህን አስጠብቆ ሊያስቀጥል የሚችል ህጋዊና ሰላማዊ የሆነ ጠንካራ ትግል ማድረግ የመጀመሪያው ተግባር ሊሆን ይገባል።

2ኛ) የወልቃይትና የራያ ነዋሪዎች በራሳቸው አነሳሽነት ሆ ብለው ወደጎንደርና ወደወሎ በመመለሳቸው ምክንያት ሌላ የሚገፈፍ ማንነት አለ ከተባለ ጥያቄው በግልፅ እንዲቀርብ ተደርጎ ነፃና ግልፅ በሆነ ህዝበ-ውሳኔ እልባት ማግኘት ይኖርበታል። በህዝበ-ውሳኔው እነማን እንደሚሳተፉና በምን መንገድ እንደሚለዩ ከላይ ስለገለፅኩት እዚህ ላይ አልደግመውም።

3ኛ) ህዝበ-ውሳኔው ነፃና ግልፅ በሆነ መንገድ ተካሂዶ የወልቃይትና የራያ ነዋሪዎች ባብላጫ ድምፅ እንደየአግባባቸው ወደጎንደርና ወደወሎ መካለል አለብን የሚሉ ከሆነ ውሳኔያቸው ሊከበርላቸው ይገባል። ነዋሪዎቹ አሁንም በአብላጫ ድምፅ መካለል የምንፈልገው ወደትግራይ ነው የሚሉ ከሆነም በተመሳሳይ መንገድ ውሳኔቸው ተፈፃሚነት ማግኘት ይኖርበታል። በህዝበ-ውሳኔው አነስተኛ ድምፅ ያገኙት ደግሞ በየአከባቢዎቹ የመኖር ህጋዊ መብታቸው መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።

4ኛ) ህዝበ-ውሳኔው ከተደረገ በኋላም የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ያለው አካል ካለ ታሪካዊም ሆኑ ሌሎች ማስረጃዎችን በማቅረብ ህጋዊ  ስርዓቱን ተጠቅሞ ፍትህን የመሻት መብቱ መከበር አለበት።

ከዚህ በላይ ያሉትን ሁኔታዎች ጠቅለል አድርጌ ስመለከታቸው ነው እንግዲህ የወልቃይትና የራያ ነዋሪዎች ጥያቄ የማንነት፣ የፍትህ፣ የዴሞክራሲና የሚዛናዊነት እንጅ በደረቁ የእርስትና ጉልት ማስመለስ ተደርገው ሊቆጠሩ አይችሉም የሚል ጠንካራ እምነት ያደረብኝ። አይ ጥያቄዎቹ በእርስትና ጉልት ማስመለስ መልክ መታየት አለባቸው ብሎ የሚነሳ ሃይል ካለ በሰው ቁስል እንጨት ከመስደድ የከፋ ግፍ እየፈፀመ መሆኑን መረዳት ይኖርበታል።

 

3 Comments

 1. በ ወረራ የተወሰደ መሬት ለ ባለቤቱ መመለስ አላበት። ምንም የሚያወላዳ ጉዳይ አይደለም። ቅኝ ግዛቶች ነጻ ሲወጡ ለ ቅኝ ገዢዎች ርዝራዦች መብት አይሰጡም። ወያኔዎችም ቅኝ ገዢዎች ነበሩ። ከ ሌሎች ቅኝ ገዢዎች የሚለዩት ጥቁር መሆናቸው ብቻ ነው። ወንጀላቸው ከ ሌሎች ይበልጣል እንጂ አያንስም። ስለዚህ አማራ እና አፋር የተነጠቁትን መሬት ስለአስመለሱ ሌላ ምንም አይነት አስተዳደራዊ ጥያቄ መቀበል የለባቸውም። የጸሃፊው ሃሳብ ፍትሃዊ ቢሆንም ብዙ ውጣ ውረድ ስላለው አግባብ አይመስለኝም። በ ጉልበት የተወሰደብንን መሬት ህይወት በ መክፈል አስመልሰናል። ከዚህ ወዲያ በ ህይወታችን ማስከበር ብቻ ነው። በ እጅ ያለን ነገር ለቆ ማሳደድ እንዳይሆን።

 2. ዘረ-ያዕቖብ
  says:
  November 28, 2020 at 8:07 pm
  በምንም ጥንቆላም ሆነ ወይንም በምንም Dialectic, In case ካርታው ከምብሓድሽ የመበወዝ እድል ከገጠመው፣ የድሮ ጥያቄአችን ከም ብሓድሽ ለትግሉ መስክ ይቀርባል::
  ዘላለማዊ ሰላም ይሰፍን ዘንዳ፣ ባንዳው መለስ ዜናዊ ያጨናገፈብንን ስርመሰረታዊ አላማችን ዘንዳ መድረስ አለብን፣ ‘እምነ-ፅዮነይ ተደጊፈስ እንታይ’ዶ ከይከውን እየ’ እንዳሉት ንጉሰ ፅዮኑ፣ ግዛታቸው ከአለውሃ እስከ ባፅዕ ድረስ ነበርና፣ በሚቀጥለው የፋሲካ ቅርጫ ክፍፍል ጊዜ ከዚህ የቀነሰ ድርሻ እንደማንቀበል እወቁት::
  Vernunft የሰው ልጆችን በሙሉ globally ካላስተዳደረ በስተቀር፣ ታሪክ መጨረሻ አይኖረውምና፣ እንዲሁም ተጋዳላይ ይሞታል እንጂ ትግል አይሞትምና…..!! እነ የመን እና እነ ቬትናምም በትግል የሚገባቸውን አስመልሰዋና::
  በየቦታው ሆነሽ ሳንቲም እየተወረወረልሽ፣ ‘ኮሎኒያሊስቶቹ ሳይነግሩት፣ ኮሎኒያሊስቶቹ የሚፈልጉትን አዋቂና ሳያዙትም አስተግባሪን’ ሚና ከመጫወት አልፎ Principe የሚባል ተስፋ ተቀዳጅቷችሁ የማታውቁ ባንዳ ሁሏም አፋችሁንና ለንጨጫችሁን ሰብሰብ ማድረግን ተማሩ::
  Unity in diversity, ኢትዮጵያ ታበፅህ ኢደውሃ ሃበ መላ ልጆችዋ…….!

 3. ፋሽሽታዊዉና ጉግማንጉጉ ትሕነግ /ሕወሀት ምዕራብ ትግራይ ብሎ ሰይሞት የነበረዉ ዞን የሚያጠቃልለዉ ወልቃይትን ፤ጠገዴን ፤ሁመራንና ጠለምትን ነዉ፡፡ይህ ሰፊ አካባቢ ከ 320 ዓ.ም.ጀምሮ አስከ 1968 ዓ.ም.ብሎም 1983 ዓ.ም. ድረስ ይተዳደር የነበረዉ በጎንደር ጠቅላይ ግዛት ነበር፡፡በመሰረቱ የጎንደርና የትግራይ ወሰን የሚለየዉ የተከዜ ወንዝ ነዉ፡፡ይህንንም ታሪካዊ ሂደት “የወለቃይት ጉዳይ” የሚለዉን መጽሀፍ ደርሶ ታሪካዊዉን ዳራዉን አቶ አቻምየለህ ታምሩን አፍታቶታል ፡፡ ለዚህም ሊመሰገን ይገባዋል፡፡
  ወያኔ ትግል ሲጀምር በ 1968 ዓ.ም. ባወጣዉ ማኒፌስቶ አካባቢዉን የትግራይ አካል ነዉ በማለት ተሸቀዳድሞ ጠቅሶታል፡፡ በማስቀጠልም ቀስ በቀስ አካባቢዉን በመሳሪያ ሀይል ተቆጣጠረዉ፡፡
  አካባቢዉ የትግራይ ያለመሆኑን እያወቀ፤ ሆን ብሎ ተከዜን በመሻገር ይህን ያደረገበት ምክንያት የሚከተሉት ናቸዉ፤
  • ትግሉን ሲጀምር ከመንግስት የሚደርስበትን ዉጊያ ለመከላከል ወደ ሱዳን ለመሸሽ ማፈግፈጊያ በመፈለጉ፤
  • ለትግሉ የሚያስፈልገዉን ስንቀና ትጥቅ ከሱዳን ለማጉዋጉዋዝ፤
  • አካባቢዉ በጣም ለም በመሆኑ ለወደፊት የገቢ ምንጪ ያስገንልኛል በሚል እሳቤ በመያዙ፤
  • ከትግራይ ሪፑብሊክ ምስረታ በሁዋላ ከዉጪ ሀገራት ጋር ለመገናኘት፤
  • አካባቢዉ በጣም ለም በመሆኑ ከጻነት በሁዋላ ለታጋዮች እንደዉለታ ለማስፈር በማሰቡ ናቸዉ፡፡
  በትግሉ ጂማሪ ይቃወሙናል ተብለዉ የታሰቡ ባላባቶች አንድ ባንድ እየተለቀሙ ተገድለዋል፡፡
  ከዚያም በመቀጠል እስከ 2013 ዓ.ም. ድረስ ማይካድራ ላይ እንደተፈጸመዉ ሁሉ የአካባቢዉ ተወላጆች ሲታሰሩና ሲገደሉ ኖረዋል፡፡ ከዚህ ድርጊት በመለስ የአፓርታይድ አገዛዙ የዘር መድሎዉና ማሸማቀቁ ላለፉት 45 ዓመታት የቀጠለ ነበር፡፡የዘርማጥፋት ወንጀል በተደጋጋሚ ተፈጽሞአል፡፡በዚህም ተነሳ የአካባቢዉ ተወላጅ የትዉልድ አከባቢዉንና ቦታዉን ጥሎ እንዲሰደድ ተደርጉዋል፡፡በእርሱ ምትክ የዴሞግራፊ ቅያሬ ተከናዉኖአል፡፡
  በ1984 ዓ.ም. ከትግሉ ፍጻሜ በሁዋላ 85 ሺህ ( መጀመሪያ 50 ሺህ ቀጥሎ 35 ሺህ )ታጋዮችን እስከነመሳሪያቸዉ በአካባቢዉ አስፍሮአል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ወደ ሁለት ሚሊዎን የሚጠጋ ህዝብ ከትግራይ በማምጣት አስፍሮአል፡፡ በመሆኑም፤የአካባቢዉ ነዋሪዎች በመፈናቀላቸዉና በመገደላቸዉ ከፍተኛ የሕዝብ መዛባት ተፈጥሮአል፡፡ ህዝበ-ውሳኔ ለአካባቢዉ ተጨባጭ ችግር እንደ መፍትሄ ሊቀርብ አይችልም፡፡ህዝበ-ውሳኔው ተግባራዊ ሊሆን የሚችለዉ ቀደምት ነዋሪዎች ላይ ችግር ባይፈጠርና ከሌላም አካባቢ ሆን ተብሎ የተፈጸመ የማስፈር ተግባር ባይፈጸም ነበር፡፡አንዳንድ የወልቃይት፤የጠገዴ፤የሰቲት ሁመራ ፤የጠለምትና የራያ ተቆርቁዋሪ በመምሰል ወሳኝ በሆነዉ ነጥብ ላይ መለትም ህዝበ-ውሳኔው የሚል መርዘኛ ተንኮላቸዉን ለማስረጽ እየተፍጨረጨሩ ነዉ፡፡ ማንነታችንን ተነጠቅን፤ የአፓርታይድ አገዛዙ የዘር መድሎዉና ማሸማቀቁ ፤ግድያዉ ለደረሰባቸዉ በፍጹም ተቀባይነት የሌለዉ ማታለያ ነዉ፡፡ ሁላችንም እኔ በእነርሱ ቦታ ብሆን ኖሮ ምን አደርግ ነበር ብለን እራሳችንን በእነሱ ቦታ ተክተን ችግሩን እናጢነዉ፡፡

  በመሀሉም አንዳንድ ቆራጥ አካባቢዉ ተወላጆች በህግ ይመለስልናል በሚል እሳቤ ለተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አቤቱታ ያቀረቡ ቢሆንም ጀሮ ዳባ ከመባላቸዉ ባለፈ ተሳደዋል ፤ታስረዋል ፤ተገድለዋል፡፡
  ከሁለት ዓመት በፊትም የተቁዋቀመዉ የወሰንና ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ግዳዩን ይፈታዋል ተብሎ ቢታሰብ አንድም ነገር ጠብ አላለም፡፡ይህም፤ የወሰንና የማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ማየት የሚችላቸዉ ጉዳዮች በሕገመንግስቱ የተካለሉትን እንጅ ከዚያ በፊት በግዳጅና በሀይል የተነጠቁትን አይደለም፡፡የተቁዋቀመበት ሕጉም አይፈቅድም፡፡ ይፍታዉ ተብሎ ቢታሰብ እንኩዋን ሂደቱ ትግራይን ክልል ዉሳኔ የሚጠይቅ በመሆኑ ሂደቱ በፍጹም የሚቻል አይደለም፡፡
  እንደሚታወቀዉ በአሁኑ ወቅት አካባቢዉ በአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሸያ ተጋድሎ ከአረመኔዉ እጅ ነፃ ወጥቶዋል፡፡ በሀይል የተነጠቀዉን በሀይል አስመልሱዋል፡፡
  ስለሆነም ትህነግ በጦርነቱ ሰለተሸነፈ የትግራይ ሕዝብ በማኩረፉ ብልጽግናና የፌደራሉ መንግስት እንደገጸበረከት በመስጠት ለማባበል እንደዘዴ ለመጠቀም ያሰበዉ አካባቢዉን እንደነበረዉ ማስቀጠል ነዉ፡፡ የወልቃይት፤ጠገዴ፤ሁመራና ጠለምት ሕዝብ ጥያቄ የማንነት እንጅ የወሰን አሊያም የእርስት ማስመለስ ጉዳይ አይደለም፡፡ ማንነታቸዉ ተክዶ ትግሬ ናችሁ ነዉ የተባሉት፡፡
  በመሆኑም፤ለመላ ወልቃይት፤ጠገዴ፤ሁመራና ጠለምት ሕዝብ ሆይ !!!!!
  ትግልህ ላለፉት 45 ዓመታት በትህነግ/በሕዉሀት የደረሰብህን የአፓርትይድ አገዛዝ ለማስወገድ ተጠናክሮ መቀጠሉ አይዘነጋም፡፡በዚህ ጊዜ ዉስጥ ቁጥራቸዉ የበዛ ወገኖችህ በገዛ ትዉልድ ሀገራቸዉ ተገልለዋል፤ታስረዋል፤ተሰደዋል፤ተገድለዋል፡፡ ሌላዉን ለጊዜዉ ብንተወዉ እንኩዋን በቅርቡ ማይካድራ ላይ ደረሰዉን ጭፍጨፋ መላዉ ዓለም አስተጋብቶታል፡፡ በዚህ ምድር ናዚዎች በአይሁዶች ላይ ያደረሱት ግፍና በደል በአንተም ላይ ደርሶብሀል፡፡የግፍ ጽዋዉ ሞልቶ በመፍሰሱ በአለማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሺያ ተጋድሎ ነጻነትህን ለመቀዳጀት በቅተሀል፡፡ ይሁን እንጂ የተቀዳጀኸዉን ነጻነት ነጥቀዉ፤ በነበረዉ መልክ ተመልሰህ ወደባርነት እንድተገባ የሚመኙና የሚያመቻቹ እንዳሉ መዘንጋት የለብህም፡፡በህግ ስም በሚደረግ የማታለያ ዘዴ በምንም ዓይነት እንዳትታለል፡፡የብልጽግና ፓርቲ -የፌዴራል መንግስት ሆነ የአማራ ብግጽግና የሚያቀርቡልህን መንገዶች በሙሉ እንዳትቀበል፡፡በመሸንገያ ሊቀርቡህና ሊያታልሉህ ይችላሉ፡፡በምንም መልኩ እምቢይ በላቸዉ፡፡ነጻነት እጅህ ዉስጥ ስለገባች አሳልፈህ እንዳትሰጥ!!!!!!!!
  ስለሆነም ፤ይህ የአፓርትይድና ባርነት ሁኔታ ተመልሶ እንዲመጣ እንደማትፈልግ ከፈለግህ ተደራጅ፤ንቃ፤ታጠቅ ከዚያም ሌት ተቀን ነቅተህ የተቀዳጀኸዉን ድል ጠብቅ ብሎም ታገል፡፡
  በጊዜያዊ ፈንጠዝኛና የመደለያ ንግግር እንዳትታለል፡፡እሱን ድልህን ስታረጋግጥ ትደርስበታለህ፡፡ የማዕከላዊዉን መንግስት ስልጣን የተቆናጠጠዉ አብይ አህመድ የሚጨነቀዉና ሙሉ ጊዜዉን ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራዉ ስልጣኑን ለማደላደልና ለማስጠበቅ ነዉ፡፡ ኢትዮጵያ፤ኢትዮጵያ በማለት ሲዘላብድ ልትታለል አይገባም፡፡የእሱም አጎብጎብጉቢ ተከታዮች እንደሱ ሁሉ በሚሰጡት አስመሳይ ንግግር ልንታለል አይገባም፡፡
  ይህ የአስመሳይ ፖለቲከኞች ዘዴ ነዉ፡፡ወቅቱን ጠብቀዉ መገለባበጥ የተለመደ ባህሪያቸዉ ነዉ፡፡
  የአንድን ፖለቲከኛ ሀቀኝነት መመመዘን ያለብህ በሚወስዳቸዉ ተጨባጭ እርምጃዎች ነዉ፡፡
  ስለሆነም፤ ወልቃይትን ፤ጠገዴን ፤ሁመራንና ጠለምትን በተመለከተ አብይ አህመድ የሰጠዉን አስተያየት የሰማህ በመሆኑ እንዳትታለል፡፡
  ተዉልድ አገርህን አሳልፈህ ከሰጠህ ለወሬ ነጋሪ እንኩዋን አንድም ሳይቀር ድምጥማጥህን ነዉ የሚያጠፉት፡፡ በዉሀላ ወይኔ ተታለልኩ ብለህ እንዳትቆጭ ፤መሬት ላይ የፈሰን ዉሀ እንደ ማፈስ እንዳይሆንብህ፡፡ ጠላቶችህ አንተን ለማጥፋት ቀን ከሌሊት እያሴሩ መሆኑን ተገንዘብ ፡፡ፋታ ሳትሰጥ ተጠንቅቀህ አካባቢህን ጠብቅ !!!!!!!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.