‹‹የክልል ልዩ ኃይል ኢሕገ መንግሥታዊ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል›› ወ/ሮ ሙፈርያት ካሚል የሰላም ሚኒስትር

የሰላም ሚኒትሯ 1024x481 ‹‹የክልል ልዩ ኃይል ኢሕገ መንግሥታዊ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል›› ወ/ሮ ሙፈርያት ካሚል የሰላም ሚኒስትር
ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል

ክልሎች እያደረጇቸው ያሉ የክልል ልዩ ኃይሎች ሕገ መንግሥቱ ከሚፈቅደው የፖሊስ አደረጃጀት ውጪ በመሆናቸው፣ ፓርላማው የአገርን ሰላም ለማስጠበቅ ሲባል የራሱ የሆነ አሠራር ሊያበጅለት እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል አሳሰቡ።

የፖሊስ ሕጉ ክልሎች የራሳቸው ፖሊሶች ይኖራቸዋል ሲል መደበኛ ሥልጠና ያገኘ ፖሊስ እንጂ፣ ከፊል የመከላከያ  ኃይል ባህሪ ይኖራቸዋል ማለት አይደለም ያሉት ሚኒስትሯ፣ የመደበኛ ፖሊስ ሥልጠናው፣ ትጥቁና ሥምሪቱ በግልጽ ምን እንደሆነ ይታወቃል ብለዋል፡፡ በክልሎች እየተደረገ ያለው ያልተገባ እንቅስቃሴ ሊታሰብበት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ምንም እንኳ የተቀመጠው የአሠራር ሥርዓት መደበኛም ሆነ መደበኛ ያልሆነ ፖሊስ ሥልጠናውና ትጥቁ ምን መምሰል እንዳለበት የሚገልጽ ቢሆንም፣ ይህ ጉዳይ ግን ፖለቲካዊ በመሆኑ በየደረጃው ያሉ የፖለቲካ አመራሮች ቢያስቡበት ይበጃል ብለዋል፡፡ አስፈላጊ ከሆነም ፓርላማው ሕግ ሊያወጣለት እንደሚገባ ሚኒስትሯ አሳስበዋል።

‹‹እንደ አገር ለመቆም አቋማችን ግልጽ በመሆኑ ትልቅ ሥራና  ሰፊ ውይይት ያስፈልገዋል፤›› ያሉት ወ/ሮ ሙፈሪያት፣ በየቦታው ለሚታየው የፀጥታ ችግር ሁሉም አመራር ኃላፊነት መወጣት ይገባዋል ሲሉ ጠይቀዋል።

የክልል ልዩ ኃይል አጀማመር ከ2000 ዓ.ም. በኋላ ባሉት ዓመታት የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) ኃይልን ለመቆጣጠር ታስቦ የተመሠረተ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህን ተከትሎም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርከት ያሉ የክልል መንግሥታት፣ ይህን መሰል ኃይል በማሠልጠን ወደ ሥራ ማስገባታቸው ይታወቃል፡፡

በዚህም አብዛኞቹ ክልላዊ መንግሥታት በክልላቸው ከሠፈሩት የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት በተጨማሪ፣ የሚፈቅድ ሕግ በሌለበት የራሳቸው የሆኑና በሺዎች የሚቆጠሩ የልዩ ኃይል ወይም የልዩ ፖሊስ ባለቤት መሆናቸው አነጋጋሪ ነው፡፡

የክልል ልዩ ኃይሎች ተጠሪነታቸው ለክልል ፕሬዚዳንቶች ነው፡፡ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከመከላከያ ሠራዊትና ከክልል ፖሊስ ጋር ያላቸው ግንኙነት በሕግ ምን እንደሚመስልም ግልጽ አይደለም ነው የሚባለው፡፡

ሚኒስትሯ ከላይ የተጠቀሰውን ማሳሰቢያ ያስተላለፉት፣ ፓርላማው የሰላም ሚኒስቴርን የ2013 በጀት ዓመት የሦስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ኅዳር 23 ቀን 2013 ዓ.ም. በገመገመበት ወቅት ነበር።

የፓርላማ አባላት የሰላም ሚኒስቴር የአገርን ሰላም ለማስጠበቅ ዕቅድ ከማዘጋጀት ባለፈ፣ መሬት ላይ የሚታይና ተጨባጭ የሆነ ሥራ በማከናወን እየታየ ላለው የሰላም ዕጦት ችግር ፈቺ መሆን እንደሚገባው አሳስበዋል።

የሰላም ሚኒስቴር፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የተቋቋመ ነው፡፡ የአገሪቱን ቁልፍ የፀጥታና የስለላ ዘርፎች በተለይም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የፋይናንስ ደኅንነትና መረጃ ማዕከል፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮችና ሌሎች ተቋማትን በበላይነት ይመራል፡፡

በተለይም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በውስጡ የያዛቸው የደኅንነት ተቋማት እንደ አገር ሊከሰቱ የሚችሉ ግጭቶችን ቅድመ ማስጠንቀቂያ መስጠት የሚችሉበትን አቅም በመገንባት፣ የሚጠበቅባቸውን አቋም መያዝ አለባቸው ተብሏል።

‹‹የዜጎች ሞት ልብሳችን ሆኗል፣ ብዙ ሀብትና ንብረት ማውደም ሱስ ሆኗል፡፡ ለዚህም  ይነስም ይብዛም በኃላፊነት ላይ ያለን ሰዎች ተጠያቂዎች ነን፤›› ያሉት በምክር ቤቱ የሰላምና የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የሰላም ዘርፍ ንዑስ ሰብሳቢ ወ/ሮ ብርቱካን ሰብስቤ ናቸው።

ሰብሳቢዋ አክለውም እንደ ተቋም  በተዋረድ በሚሊዮኖች ለሚሆኑ ዜጎች  ሥልጠናዎች ተሰጡ መባላቸውን፣ ነገር ግን  ለፖሊስ ኃይሉም ሆነ ለኅብረተሰቡ የሚሰጠው ሥልጠና የሚሞቱ ዜጎችን ካልታደገ፣ የሚወድሙ ሀብትና ንብረቶችን ከላስቆመ የሚኒስቴሩ ሥራ ከንቱ ነው ብለዋል፡፡

የሰላም ሚኒስትሯ በበኩላቸው ዘንድሮ 30 ሚሊዮን ለሚደርሱ ዜጎች ብሔራዊ የሥልጡን የምክክር ውይይት ለማዘጋጀት፣ የሥልጠና ሰነድ ተዘጋጅቷል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከዚህ ጋር በተያያዘ በብሔራዊ መግባባት ላይ ያተኮሩና የጋራ ታሪክና ትርክት እንዲኖር የሚያስችሉ ጉዳዮችን በመለየት፣  ዜጎች በጋራ ጉዳዮች ላይ አንድ ዓይነት ወይም ተቀራራቢ ዕሳቤ እንዲይዙ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልጿል።

በዚህም በዋነኝነት ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከምሁራን ጋር ከአገራዊ ታሪክ ዕይታና ዕሳቤ አንፃር በመነጋገር መግባባት ለመፍጠር እየተሠራ እንደሆነ፣ በተለይም ከአገሪቱ ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ የታሪክ ምሁራንን በማሰባሰብ ለመግባባት የሚያስፈልጉ ጉዳዮች  ምን ምን እንደሆኑ ተለይተዋል ሲሉ ወ/ሮ ሙፈሪያት ገልጸዋል።

በሚኒሰቴር መሥሪያ ቤቱ ሥር ባሉ የደኅንነት ተቋማት ጠንካራ ሪፎረም እየተደረገ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሯ፣ ሥርዓት አገልጋይ የነበሩ የፀጥታና የደኅንነት ተቋማት ወደ ሕዝብ አገልጋይነት እንዲሸጋገሩ እየተሠራ መሆኑን አክለዋል፡፡ ድሮ እንደ ባላንጣ ሲተያዩ የነበሩ የደኅንናትና የፀጥታ ተቋማት አሁን በመነጋገርና በመወያየት በጋራ እየሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በተያያዘ ዜና በሰላም ሚኒስቴር በኩል እየተሠራ ያለው ብሔራዊ የዜጎች መታወቂያ የፕሮጀክት ሥራ ተጠናቆ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ በተያዘው ዓመት 30 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች መታወቂያ ለመስጠት እየተሠራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡

ሪፖርተር

3 Comments

 1. የአማራ ልዩ ኃይል በትግራይ ለህግ ለማስከበር ተሰማርቶ በነበረበት ጊዜ ከጁንታ በመማረክ እና ከመከላከያ ሠራዊት በውሰት ትጥቆች ወስዶ አሻፈረኝ አልመልስም ማለቱ አሳሳቢ ነው።
  ሌሌቹ የኦሮሚያ፣ የትግራይ፣ የሶማሊ፣ የጋምቤላ፣ የአፋር፣ የደቡብ፣ የቤኒሻንጉል፣ የሐራሪ፣ የሲዳማ ልዩ ኃይልም ትጥቅ አይፈታም። ለምሳሌ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል በኦሮሚያ ውስጥ በአሁኑ አደረጃጀቱ መቀጠል አለበት ምክንያቱም የባልደራስ አሸባሪዎች በተደጋጋሚ የመከላከያ ሠራዊትን ተገን በማድረግ የኦሮሚያ ክልል ህዝብ ላይ የሽብር ጥቃት በመሰንዘራቸው ነው።

  በተጨማሪም በአሁኑ የትግራይ ጦርነት እንደተገነዘብነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ልዩ ኃይል ብቻ እንደ ህግ አስከባሪ ሲቆጠሩ በፌደራል መንግስት ፡ የሌሎች ክልሎች ልዩ ኃይሎች ግን እንደ ባዕዶች ወይም እንደ ወንጀለኞች ተቆጥረው የህግ ማስከበር ሥራ ላይ እንኳን በእኩልነት እንዳይሳተፉ መደረጉን ነው። ይህ የሚያሳየው የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ተሽሮ የአማራ ነፍጠኞች አምባገነንዊ ሥርወ መንግስት ሥር መስደዱን ነው። ስለዚህም የክልሎች ልዩ ኃይሎች አደረጃጀትን መነካካት ሰላም እንደሚያሳጣ መገንዘብ ተገቢ ነው።

 2. a)As a matter of both principle and fact that these do called especial forces of ethnocentric and sectarian entities which have caused and continued to cause untold political and social break down , it is the right thing to cal for their abolishment . But the question is are these politicians and officials who have been badly poisoned with all kinds of hypocritical, cynical, dishonest, deceiving behaviors and actions for so long trustworthy or not. The answer is the very horrifying political crimes they have done and continued to do .
  b) Where was this lady who is the fake minister of the fake ministry of peace created for the very purpose of making the so called reform by those very cynical and dishonest politicians of EPRDF , now they renamed themselves Prosperity look good ?
  C) Can she come out and publicly explain what she wanted really to say and why and how?
  D) Does she have a trustworthy political and moral gut to go beyond her cynical rhetoric and to say that the very root cause for all terrible situations we are facing is not a matter of this or that part of the government but the whole system of deadly ethnocentric politics in which she continued to be one of the millions of parasitic cadres ?
  E) or she is making a conspiratorial statement along with he boss , the prime minister about what the Amhara especial forces , militias and other concerned groups did and continued to do in the northern part of the country? Is she or are they scared ?
  No more dirty and deadly political game !!

 3. ትልቁ ነገር በህግ ማዕቀፍ ውስጥ መሆን ሲችል ነው። ምንም እንኳውን ህግ የመጣስ ሁኔታ ቢኖርም ተጠያቂነት ስለሚያመጣ ደንብ ማክበር ይኖራል። ክልሎች ለስልጣን ሲባል misuse የማድረግ ሁኔታ እና የሃሳብ ግጭት ሲፈጠር የአጠቃቀም ችግር ስለሚያመጣ ወጥ ህግ መኖር አለበት። ለማዕከላዊ መንግስት ተጠሪ የሚሆንበት መወቅር እና ደንብ ሊዘጋጅለት ያስፈልጋል። የክልል መንግስት interest እና በ National መንግስት ደረጃ የሚኖረው አገራዊ ፍላጓት ማጣጣም ማስቻል ያስፈልጋል። አለዚያ አደጋ አለው። ይታሰብበት።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.