“የትህነግን ትርክት አስቀጥላለሁ የሚል መንደፋደፍ የፖለቲካ ኳራንታይን ከማስቀጠል የተለየ ውጤት አይኖረውም።” ሲሉ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ የአብን ም/ሊቀመንበር አቶ የሱፍ ኢብራሂም ገለፁ

አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ
የአብን ም/ሊቀመንበር አቶ የሱፍ ኢብራም በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት በትግራይ ውስጥ ቀላል የማይባል ድጋፍ የነበረው ትህነግ በአማራ ህዝብ ላይ እስከዘር ማጥፋት የደረሱ ወንጀሎችን ፈፅሟል ብለዋል።
“አሁን ድህረ ትህነግ በትግራይ ውስጥ የተደራጀ ፖለቲካ እመራለሁ የሚል ማናቸውም አካል ትህነግ ካነገበው አማራ ጠል ትርክት ራሱን አርባ ክንድ ማራቅ አለበት!” ያሉት ም/ሊቀመንበሩ እስካሁን በአማራ ህዝብ ላይ ለተፈፀመው ጥፋት እውቅና መስጠትና ይቅርታ መጠየቅም ይኖርበታል ሲሉም አክለዋል።
129955353 116150223654572 798405031834258288 n
“የትህነግን ትርክት አስቀጥላለሁ የሚል መንደፋደፍ የፖለቲካ ኳራንታይን ከማስቀጠል የተለየ ውጤት አይኖረውም።” ብለዋል አቶ የሱፍ ኢብራሂም በመግለጫቸው።
   አያይዘውም “የአማራ ህዝብ በፅኑ ተደራጅቷል፤ ጠላቱን ለይቷል፤ የጥላቻ ትርክቱን ይዘትና አንድምታ ባግባቡ ተረድቷል!” ብለዋል።
አቶ የሱፍ ኢብራሂም “በፅኑ ጉዳዬቻችን ላይ የሀሳብ ጥራት!” በሚል ባስተላለፉት መልዕክታቸው የአማራ ህዝብ ትግል የፍትህ፣ የነፃነትና የእኩልነት መሆኑን አስምረዋል።
እኛ እኩልነትን መሰረት ባደረገ ስርዓት ውስጥ የምናጣው ነገር እንደሌለ እንረዳለን ያሉት አቶ የሱፍ አንዳንድ ሰዎች የራሳቸውን ቅዠት አስፍረው የእኛ ሀሳብ አስመስለው ለመተቸት የሚያደርጉት መራወጥ እብቅ አመክንዬ ላይ የተመሰረተ ስሁት ሀሳብ ብቻ እንደሆነ ልናስረግጥላቸው ይገባል ነው ያሉት።
ይሄን ስልት ለሌላ ፅንፈኛ ጎራ ምሽግ ለማድረግ መሞከር አደገኛ መሆኑን ማስገንዘብ ያሻል ብለዋል።
ሲቀጥሉም የወልቃይትና የራያ ጉዳዬች በህግ አግባብ ሊታዩ ይችላሉ፤ ሆኖም አሁን የአማራ ህዝብ በአካባቢዎቹ ላይ አካላዊ ቁጥጥር ስላለው ይገባኛል የሚል አካል ካለ አቤቱታውን የሚያቀርብ ይሆናል፤ አማራው አካባቢዎቹን የማስተዳደርና በነባራዊ ስነህዝብ ጉዳዬች ላይ ጭምር ፍትሀዊ የምልሰት ስራዎችን እንደሚያከናውን ይጠበቃል ሲሉ አስፍረዋል።
129721510 116150270321234 5866316838769102372 n
ነጻ በወጡ በአማራ አፅመ እርስቶች ዙሪያ ያለ ህዝብ ስለአማራነቱ በነቂስ አደባባይ ወጥቶ እየተናገረ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
ከሁሉም አካላት በላይ ትህነጋውያን ወልቃይትና ራያ አማራና የአማራ መሆናቸውን ያውቃሉ፣ በተግባር አረጋግጠዋል ሲሉም አክለዋል።
ትህነጋውያን አብዛኛውን አማራ ገድለውና አፈናቅለው ሲያበቁ ቀሪውን ህዝብ በጅምላ ጨፍጭፈው ከማይገባቸው ቀጠና ለቀው ወጥተዋል ያሉት አቶ የሱፍ ለትህነግ እና ለኢመደበኛው ሳምሪ የወንጀል ቡድን ነፃ የጥብቅና አገልግሎት ለመስጠት ለሚደክሙትም ዋናው የእኩያን የመንፈስ አባት ትህነግ በጫማ ስር በዋለበት ወቅት ትርፉ ትዝብትና ድካም ብቻ ነው እንላለን ነው ያሉት።
ዙሪያ ገባውን በንቃት መቃኘት አስፈላጊ ቢሆንም ትግላችን በይሁንታ ላይ ሊንጠለጠል እንደማይገባ ማወቅ የግድ ነውም ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በተያያዘ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አብን የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት “የሕግ ማስከበርና የአገር ሉዓላዊነት ዘመቻው መቋጫ ትሕነግን በአሸባሪነት ፈርጆ ዳግም እንዳያንሰራራ አድርጎ መደምሰስ መሆን ይኖርበታል” ብለዋል።
ትሕነግን በአሸባሪነት ፈርጆ ዳግም እንዳያንሰራራ አድርጎ አለመደምሰስ ማለት ለትሕነግ የዘር ፍጅት ሽብርና አገርን የማፍረስ እኩይ ምግባር ፈቃድ እንደመስጠት የሚቆጠር ነው ብለዋል አቶ ክርስቲያን ታደለ በመልዕክታቸው።
የአብን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጣሂር መሀመድ ከደደቢት እስከ ደደቢት (አዲስ አበባ ደርሶ መልስ) ለግማሽ ምዕተ ዓመት ገደማ የቆየው ትህነግ የያዘው የጥላቻ ትርክት ከፓርቲ አስተሳሰብነት አድጎ እነሱን የመሰሉ “ልሒቃን”ም ሃሳባቸውን ገዝተውታል ብለዋል።
እንዲያውም አሉ አቶ ጣሂር “አንዳንዶች ይህ የትህነግ አስተሳሰብ ከዚህም አልፎ ወደ አዲሱ ትውልድ ሁሉ ተሸጋግሯል የሚል መከራከሪያ ያመጣሉ።” ሲሉ ጠቅሰዋል።
129638446 116150276987900 7507503890972220261 n
የሆነው ሆኖ ግን ችግራችን ከአስተሳሰቡ እንጅ ከሰዎቹ ጋር አለመሆኑን ማወቅ ግድ እንደሚል ያሰመሩት አቶ ጣሂር ይህ አስተሳሰብ በደብረፂዮንም መጣ በአረጋዊ ፣በጌታቸውም አልነው በነብዩ …ወደ ኋላ ሳንል የምንታገለው ብቻ ሳይሆን ዋጋ የምንከፍልበት መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል ነው ያሉት።
የእኛ ትግል በወረራ የተበተነውን የአማራ ሕዝብ እና ግዛት አንድነት ማረጋገጥ ነው ያሉት ደግሞ የአብን የም/ቤት አባል አቶ መልካሙ ሹምዬ ናቸው።
አቶ መልካሙ ይህ ትግል የአማራ ሕዝብ አሁን ሥራ ላይ ባለው “የፌዴራል” ሥርአት መሰረት በአንድ ግዛት ስር መተዳደር እስካለበት ድረስ መተዳደር አለበት ከሚለው መርህ የመነጨ ብቻ ሳይሆን በኃይል የተወሰደው ሕዝባችን ማንነቱን የመደምሰስ እና ይህን የሚቃወመውን ለመሬቱ ሲባል መጠነ ሰፊ ጥቃት የደረሰበት እና እየደረሰበት ያለ ስለሆነ ፈፅሞ ሳይጠፋ ከእልቂት መታደግን ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል።
የአማራ ሕዝብ አንድን አካባቢ በርስት መልክ የሚገልፅ መሆኑ ይህን ሃቅ የሚቀይር ጉዳይ ተደርጎ መወሰድ የለበትም ያሉት አቶ መልካሙ ጉዳዩን የመሬት ጉዳይ ብቻ አታስመስሉት ነው ያሉት።
አያይዘውም “እርግጥ ነው መሬትም ቢሆን በወረራ ተነጥቆ መወሰድ የለበትም፤ በኃይል የተወሰደን ግዛት እና በግዞት የተያዘን ሕዝብ በኃይል ማስመለስ ጥፋት ሊሆን አይችልም፤ በተለይ በጉልበት ወሳጁ ከጉልበት ውጭ ሕግ የሚባል ነገር የማያውቅ ሲሆን ምን አማራጭ ሊኖር ይችላል?” ሲሉ ጠይቀዋል።
“የሕዝባችን እና ግዛት አንድነቱን አረጋግጠናል፤ የቀረውን ሕዝባችንን እየተካሄደ ካለ የዘር ጭፍጨፋ እና ፈፅሞ መጥፋት አትርፈናል፤ ይህ በየትኛውም መለኪያ ተቀባይነት ያለው ነው፤ ሌላው ሁሉ ትህነግ የዘራው የአማራ ጥላቻ ፍሬ ውጤት ነው።” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
129722246 116150230321238 4572712405521056538 n
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አብን እንደ ፓርቲ በተደጋጋሚ:_
1) ትህነግ ሊድን በማይችል የጥላቻ ደዌ የተጠቃ፣ ከምስረታው ጀምሮ በርካታ ወንጀሎችን ሲፈፅም የቆየ ሽብርተኛ ድርጅት በመሆኑ ከሰላማዊ ፖለቲካ ፖርቲዎች ዝርዝር እንዲሰረዝና በሽብርተኝነት እንዲፈረጅ፣
2)ይህ የሀገራችንና የአማራ ህዝብ ቀንደኛ ጠላት በሆነው ትህነግ ላይ የሚያዘው አቋም ፍፁም የማያወላዳ መሆን እንዳለበት፣ አብን ከትህነግ ጋር ምንም አይነት ግንኙነትና ውይይት እንድሁም ድርድር እንደማያደርግ ወስኖ እሳቤው የፓርቲው ቋሚ መርህ ሆኖ በድርጅቱ ስትራቴጂክ የሀይል አሰላለፍ ትንተና ሰነድ ላይ ጭምር በግልፅ እንዲቀመጥ ማድረጉን፣
3)ትህነግ ከሀገራችንና ከህዝባችን የዘረፋቸው አንጡራ ሀብቶች ተወርሰው በደል ለተፈፀመባቸው ወገኖች ካሳ ለመክፈል እንዲውል፣
4) ትህነግ በአግላይነት የጻፈውን ህገ መንግስት፣ ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች እንዲሁም የዘረጋቸው መዋቅሮች እንዲከለሱ የሚሉ ሀሳቦችን በግልፅ አቅርቦ እንደነበር ተገልጧል።
ተጨማሪ ያንብቡ:  በመርሳ ከተማ በህዝብ ላይ የሚፈጸመው ጥቃት እንደቀጠለ ነው

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.