የአረና መሪዎች እና አባላት ወዴት አላቹህ? (ዳዊት ከበደ ወየሳ)

በትግራይ ምድር ላይ የነጻነት ጎህ ሲቀድ፤ በህሊናችን ብዙ ነገር ይመላለሳል። እነዚያ የግፍ በትር በህዝብ ላይ ያወረዱ አረመኔ የህወሃት ሰዎች በተፈለፈሉባት ምድር እነአረጋዊ በርሄ መፈጠራቸውን አንዘነጋም። በቅርብ ከማውቃቸው የሙያ ባልደረቦቼ መካከል ጋዜጠኛ አርአያ እና ጋዜጠኛ አብርሃ በላይ (ኢትዮ ሚዲያ) ይታወሱኛል። እነዚህና ሌሎችም የትግራይን አምባገነን በግልጽ ሲቃወሙ የነበሩ የትግራይ ወንድም እና እህቶቻችንን አንዘነጋም። ከምንም በላይ ደግሞ በዚያው በትግራይ ምድር ላይ ህወሃትን በሃሳብ እና በሰላማዊ መንገድ ይፋለሙ የነበሩ የአረና ፓርቲ አባላትን ከቶውኑም አንዘነጋቸውም። ለመሆኑ እነዚህ የአረና ሰዎች አሁን የት ነው ያሉት?
128605487 1653093018227172 8855943045166152257 n
በሰሜን ዕዝ መከላከያ ሃይል ላይ ጥቃት ከመፈጸሙ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ፤ የህወሃት ተቃዋሚ የነበሩ ሰዎች ከየቤታቸው እየተወሰዱ ይታሰሩ ነበር።
ብዙዎች የምናውቃቸው አብርሃ ደስታ እና አምዶም ገብረስላሴ ድምጻቸው ጠፍቷል። በአሁኑ ወቅት የት እንዳሉ አናውቅም። ላለፉት 25 ቀናት የግል ማህበራዊ ገጾቻቸው ምንም እንቅስቃሴ የላቸውም። አሁን በዚህ የድል ደወል ከዳር እስከዳር በሚሰማበት ወቅት ደግሞ ጭራሽ ደብዛቸው ጠፍቷል። “በኔትወርክ ምክንያት ነው የጠፉት” እንዳንል፤ ሁለቱም ጓዶች ኔትወርክ ከመቋረጡ አንድ ሳምንት በፊት ነው። ሌላው ቀርቶ በዚህ ወቅት ከፊት ረድፍ መሰለፍ የነበረባቸው አረናዎች ምንም ነገር ላይ አይታዩም። እናም መከላከያ ሰራዊት ነጻ ባወጣቸው ከተሞች ጭምር የአረና አባል እንቅስቃሴዎች አለማየታችን ጥርጣሬያችንን አጎልብቶታል።
አብርሃ ደስታ እና አምዶም ገብረስላሴ ከመጥፋታቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ የአረና አባላት የነበረው፤ ሃይለኪሮስ ታፈረ በድጋሚ ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ የት እንዳሉ አልታወቀም። እነአብርሃ ደስታ በጠፉ ሰሞን እጅግ ብዙ የህወሃት ተቃዋሚዎችም ታፍነስ ጠፍተዋል። ከነሱ በፊትም የታሰሩ ነበሩ።
1. ዮሃንስ ግርማይ (ዓይናለም እንደርታ)
2. ሃይለኪሮስ ታፈረ (ውቅሮ)
3. ስሙር አባዲ (ተምቤን ዓብይ ዓዲ)
4. ይርጋ ገብረ (አይናለም)
5. ሃፍቶም ደስታ (መቀለ)
6. ማርቆስ ፀጋይ (መቀለ)
7. ገብረመድህን ተኽለአብ (ተምቤን)
8. አልጋነህ ወልደጀወርግስ (ተምቤን)
9. ሙሉ ግርማይ (ኩሓ)
10. ፅጋቡ ቆባዕ (ኩሓ) (እነዚህ እንደምሳሌ የሚነሱ እንጂ በርካቶች የታሰሩ መሆናቸው ይታወዋል)
በነዚህ እና በሌሎችም የህወሃት ተቃዋሚ ትግራዋይ መታፈን ምክንያት፤ አብርሃ ደስታ እና አምዶም ገብረስላሴ የህወሃትን አምባገነን መንግስት ፊት ለፊት ሲሞግቱ ነበር። ህወሃት በትግራይ ምድር ላይ ያደረገውንም ህገ ወጥ የምርጫ ሂደት በመቃወም፤ እራሳቸውን ከምርጫው ያገለሉ ቆራጥ የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ናቸው።
እናም ዛሬ ላይ ሆነን… የትግራይን ነጻ መውጣት ስንሰማ፤ ከማንም በፊት አናንተን እና የአረና ጓዶችን “እንኳን ደስ ያላቹህ” ለማለት ወደድን። ነገር ግን ከወዴት እንዳላቹህ ግራ እንደተጋባን ነው። እነሆ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ፍልሚያ እንዳለ ሆኖ፤ በ’ናንተም ትግል ጭምር ትግራይ ነጻ ወጥታለች። ከዚህ በኋላ የጨበጣችሁትን ነጻነት ይዛቹህ፤ የትግራይን ህዝብ በትጋት እንደምታገለግሉ ተስፋ አለን… ነገር ግን ድምጻቹህ ቢጠፋብን ጨነቀን።
128821446 1653093228227151 7663698313599470869 nጎበዝ! አብዛኛው የትግራይ ህዝብ በዝምታ ድባብ በታፈነበት ወቅት፤ እዚያው በትግራይ ምድር፤ የወያኔን ጫና ተቋቁመው በድፍረት የህዝብ ድምጽ ሆነው ነበር። በአንጋንድ ጉዳዮች… የሃሳብ ልዩነት ሊኖረን ይችል ይሆናል። ነገር ግን የህወሃት እሳት እንዲበላቸው ፈጽሞ አንመኝም። ይልቁንም “ጥቂት ነበራቹህ፤ ሚሊዮን ትሆናላቹህ።” እንላቸዋለን። እናም በዚህ ወቅት እነዚህን ትንታጎች አለማመስገን ንፉግነት ነውና ባሉበት ልናመሰግናቹህ ይገባል።
ይህን ጽሁፍ የምታነቡ ሰዎች፤ ‘ለመሆኑ አረና ምንድነው? መሪዎቹስ እነማናቸው?’ ትሉ ይሆናል። እናም ለአይን መግለጫ ይሆናቹህ ዘንድ፤ ከአረና መሪዎች አውራ የነበረው አብርሃ ደስታ በመጨረሻዎቹ ቀናት የተናገረውን ላጋራቹህ። እንዲህ ነበር ያለው።
ህወሓት “ዶር ዐብይ የትግራይ ህዝብ ጠላት ነው” ብላ የምታምን ከሆነ ለምንድነው ሊቀ-መንበር (ጠቅላይ ሚኒስተር) አድርጋ የመረጠችው? ለኔ ግን አንድ መሪ የህዝብ ጠላት ነው የሚባለው ህዝብ ሲያፍንና ሲጨቁን ነው። እስካሁን ድረስ የትግራይ ህዝብ እየተገዛም እየተጨቆነም ያለው በህወሓት መሪዎች ነው።
በማለት እቅጩን ተናግሮ ነበር። አሁን ድምጹ ጠፍቶብናል። እሱን እና ሌሎች ታፍነው የጠፉ ወንድም እና እህቶቻችንን ድምጽ በድጋሚ እንሰማ ይሆናል።
በክፉ ቀን ከትግራይ ህዝብ ጎን ቆማችኋልና፤ በዚህ መልካም ዘመን የናንተ ድምጽ መጥፋት ደስ አላለንም። ስጋት አድሮብናል። የአረና ሰዎችን አፋልጉን። ስለአብርሃ ደስታ፣ ስለአምዶም እና ሌሎችም የአረና አባላት መሰወር የምታውቁ ካላቹህ፤ እባካችሁን አሳውቁን። እስከዚያው ግን የናንተን ክፉ መስማት አንሻም፤ ባላችሁበት “እንኳን ለዚህ ቀን አበቃቹህ” እንላለን። ደህና ሁንልን።

1 Comment

  1. የህዋሃት ህይወት ታሪክ career ጥሩ አሳይትሃል፡፡ ግን

    ከመቀሌ ወደ ደደቢት/ዋሻ/

    ከደደቢት/ዋሻ ወደ ከርቸሌ ቢባል የተሻለ ነው፡፡

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.