“ወደ ሱዳን ከተሰደዱ ወጣቶች መካከል ማይካድራ ላይ በተካሄደው ጭፍጨፋ ላይ የተሳተፉ ይገኙበታል የሚል ጥርጣሬ አለን” – አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

128725483 3009231205980858 4839906457070914738 n “ወደ ሱዳን ከተሰደዱ ወጣቶች መካከል ማይካድራ ላይ በተካሄደው ጭፍጨፋ ላይ የተሳተፉ ይገኙበታል የሚል ጥርጣሬ አለን”   አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን
ወደ ሱዳን ከተሰደዱ ወጣቶች መካከል ማይካድራ ላይ በተካሄደው ጭፍጨፋ ላይ የተሳተፉ ይገኙበታል የሚል ጥርጣሬ በመንግሥት በኩል ያለ መሆኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን አስታወቁ።
አምባሳደር ሬድዋን ይህን ያስታወቁት የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ከሬውተርስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ነው።
በትግራይ ክልል ከተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ እስካሁን ከ40 እስከ 43 ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ድንበር ተሻግረው ሱዳን መግባታቸውን አምባሳደሩ ተናግረዋል።
አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ለስደት የበቁት በተለይ ወደ 700 ሰዎች ከተጨፈጨፉበት የማይካድራው ክስተት ጋር ተያይዞ መሆኑንም ገልጸዋል።
በግጭቶች ወቅት አብዛኛውን ጊዜ ለስደት የሚዳረጉት ሴቶች፣ ሕፃናት እና አረጋውያን ናቸው ያሉት አምባሳደር ሬድዋን፣ ከማይካድራው ክስተት ጋር በተያያዘ ግን የሴቶች እና የሕፃናት ቁጥር አነስተኛ መሆኑን፣ የወጣቶች ቁጥር በተቃራኒው እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
በማይካድራው ጭፍጨፋ ከሕወሓት ጁንታ ልዩ ኃይል እና ሚሊሺያ በተጨማሪ መደበኛ ያልሆነ አደረጃጀት ውስጥ የነበሩ ወጣቶች የተሳተፉበት መሆኑን በዓለም አቀፍ እና በሀገር ውስጥ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት መረጋገጡን ገልጸዋል።
“ማይካድራ ለሱዳን ቅርብ በመሆኗ ወደ ሱዳን ከገቡት ስደተኞች መካከል በዚህ ድርጊት ላይ የተሳተፉ ወጣቶች ይገኙበታል የሚል ጥርጣሬ አለን ብለዋል” አምባሳደሩ።
ስለዚህ የእነዚህን ስደተኞች ማንነት እና ምንነት በመለየት ሥራ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሱዳን ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
“አሁን ላይ የመንግሥት ወታደሮች ማይካድራን የተቆጣጠሩ በመሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የተፈጠረውን ሁኔታ መናገር ጀምረዋል፤ በዚህም የጭፍጨፋው ተሳታፊዎች ማን እንደሆኑ በስም ሊነግሩን ይችላሉ” ሲሉም አክለዋል።
በስም ከሚዘረዘሩት ውስጥ ምናልባት ወደ ሱዳን ከተሰደዱት ወጣቶች መካከል ሊሆኑ እንደሚችሉ እና እነዚህን የማጣራት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰዓት ሱዳን ውስጥ በሚገኙ እነዚህ ስደተኞች መካከል አልፎ አልፎ ግጭት እየተፈጠረ ነው ያሉት አምባሳደር ሬድዋን፣ ምናልባት ጅምላ ጭፍጨፋው ላይ ከተሳተፉት ወጣቶች ውስጥ 10 ወይም 12 የሚሆኑ ስደተኞቹ ውስጥ የሚገኙ ከሆነ እዚያ ያለውን ሁኔታ ሊያደፈርሱ እና ብጥብጥ እንዲከሰት ማድረግ እንደሚችሉም አውስተዋል።
ሱዳን የኢትዮጵያ መንግሥት እየወሰደ ያለውን የሕግ ማስከበር እርምጃ እየደገፈች መሆኑንም ነው የገለጹት።
በአሁኑ ሰዓት መቀሌን ጨምሮ አብዛኛው የትግራይ ክልል አካባቢ ከጁንታው ነፃ በመሆኑ እነዚህ ዜጎች ወደ ሀገራቸው ተመልሰው እንዲገቡ የማሳመን ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.