ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ /መልክት ቁጥር – 2/

Abiy 7አብይ ተሰማራ – – – አብይ ተሰማራ
እንደ አብርሃም ሊንከን – – – እንደ ቼጉቬራ
ከፍትህ፣ ከአንድነት – – – ከእኩልነት ጋራ
ከዘረኞች ሳይሆን – – – ከሠዉ ልጆች ጋራ
ተረኛ ለመሆን ካደቡት ጋር ሳይሆን – – – ሠላምን ከሚሹ ለፍቶ አደሮች ጋራ

በቅድሚያ በሃገራችን ተንሠራፍቶ የነበረው የዘር ፖለቲካ ጠንሳሽ የነበሩት መሃንዲሶች ድል በመመታታቸው ብቻ ሳይሆን እርስዎን ብቻ ሳይሆን እኔንና መሰል ብዙ ኢትዮጵያዉያንን አሳስቦን የነበረዉ አስፈሪ አደጋ በመስዋዕትነትም ቢሆን በመወገዱ እንኳን ደስአለዎት ለማለት እወዳለሁ:: አዎን በርግጥም ሊደርስ ይችል የነበረው ሰብዓዊ፣ ማህበራዊ፣ ታሪካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ባጠቃላይ በሃገራችን ላይ በተለይ ደግሞ በትግራይ ክልል በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወንድም እህቶ ቻችን ላይ ቢያንስ ባሰብነው መጠን ሳይደርስ ሁኔታዎች በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በስኬት በመጠናቀቃቸው ምስጋናዬ ይድረስዎት። ምክንያቱም አልፎ ሲያዩት ቀላል ቢመስልም ለስኬቱ የእርሶና ኢትዮጵያን ያሉ የጥቂት ጓዶችዎ ትዕግስት፣ ከሃገራችን የመከላከያና ደህንነት ሃላፊዎችና ከአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አመራሮች ጋር ተናቦ የመከወን ብቃት፣ የመከላከያ አባላት፣ የአማራ ልዩ ሃይል የሚሊሽያና ፋኖ አባላት፣ እንዲሁም የአፋር ክልል ልዩ ሃይል አባላትና ሌሎችም በግልም ይሁን በቡድን በትግሉ ዉስጥም ሆነ በደጀንነት ለመሳተፍ ከዳር እስከዳር ለተንቀሳቀሱ ኢትዮጵያዉያኖች ጀግንነት ከዚያም አልፎ የኤርትራ መንግስት ታላቅ ትዕግስት ጉልህ ሥፍራ የሚሰጣቸዉ ናቸው::
እነሱ ባሰቡት ባቀዱትና በፎከሩበት መንገድ ተከናዉኖና ተጠናቆ ቢሆን ኖሮ በአካባቢዉ በሚኖሩ ንጹሃን፣ በንብረት፣ በቅርስና በቤተዕምነቶች ላይ ሊደርስ ይችል የነበረው ያልተፈለገ ዉጤት ወይንም ኮላተራል ዳሜጅ ምን ያህል ከባድ እንደነበር ማሰቡ ራሱ የሚያሳምም ነዉ:: በሂደቱም እርስዎና ጓዶችዎ በምን አይነት ጭንቀትና ጥበት ዉስጥ እንዳሳለፋችሁ መገመት ከባድ አይደለም::
ከዚህ አንጻር አንዱና ወሳኙ ችግር ተፈታ ለማለት ቢያስደፍርም ይህንን ዉጤት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከፊት የሚጠብቅዎትን ቀጣዩንና ምናልባትም ወሳኙን ችግር በፍጥነትና በድፍረት መፍታት አለብዎት ብዬ አምናለሁ፣ ይገባልም:: አሊያ ግን እጅግ እንደ ሚወዷት ደጋግመው የገለጹልንን ሃገርዎንና ህዝቧን ከቀደመው ለከፋ ችግር ሊዳርጓትና ከእርስዎ እንደቀደሙት ሁሉ የታሪክ አጋጣሚ በእጅዎ ላይ ያስቀመጠሎትን ዕድል የማበላሸት አጋጣሚዎ ሠፊ መሆኑን ይጠፋዎታል ብዬ በዚህ ጽሁፍ ለእርስዎ ለመንገር ፈልጌ አይደለም:: በጭራሽ! ይልቁንም ይህንን ታላቅ ገድል በፍጥነትና በድፍረት ሳይፈጽሙ እንደከዚህ ቀደሙ በይደር እንዳያቆዩት በማሰብ ነው:: ምክንያቱም በይደር ካቆዩት ሁላችንም ሠዉ ነንና፣ ነገ ምን እንደሚገጥመን አናዉቅምና በግል አሻራዎን የማኖርያ ዕድልዎን ሳይጠቀሙበት እንዳይበላሽ ለማሳሰብ ከዚያም በላይ ግን ሃገራችን ወደ ዳግመኛ ብቻ ሳይሆን ምናልባትም የከፋ ቀውስ እንዳትገባ ስጋት እርስዎን መወትወት ስለመረጥኩ ነው::
በመሆኑም ሃገራችን ወደ ዳግመኛ ብቻ ሳይሆን ምናልባትም የከፋ ቀውስ እንዳትገባ ከዚህ ቀደም በመጀመሪያዉ መልዕክቴ የተላለፉት መልክቶች *ዋና ፍሬ ነገሮች ማለቴ ነው ዛሬም አጽንኦት ተሰጥቷቸው ተግባራዊ ይሆኑ ዘንድ ከዚህኛዉ መልክቴ ግርጌ በክፍል ሁለት ያስቀመጥኳቸዉ ሲሆን በዚህኛዉ መልዕክቴ በክፍል አንድ ዉስጥ ደግሞ ለቀጣዩ የሃገር ግንባታ ቢያንስ የዉይይት መነሻ ይሆናሉ ያልኳቸዉን እንደ አንድ ዜጋ የራሴን ምልከታ እንደሚከተለዉ ለመሠንዘር ወደድኩ::
እርስዎም ታዲያ ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በመምከርና ከሁሉ ቅድሚያ ሠጥተዉ በፍጥነትና በድፍረት በመከወን ስምዎን በአልማዝ በመጻፍ ቤተሰቦን፣ ዘመዶችዎንና እኛን የሃገርዎን ልጆች ብሎም ዓለምን ሊያኮራና ሊያስደምም የሚችል አሻራዎን የማኖርያ ዕድልዎን በአግባቡ ይጠቀሙበታል ብዬ አስባለሁ::
ክፍል 1
ስለትራይ ማህበረሰባችን
1ኛ/ አሁን በሃገሪቱ ባለዉ ተጨባጭ ሁኔታ በሁሉም ላይ ባይባልም ባብዛኛዎቹ የትግራይ ማህበረሰብ ተወላጆች ላይ ከዉስጣቸዉ የወጡ ነገር ግን የማይወክሏቸው አካላት በሠሩት ታሪካዊ ስህተት ምክንያት ሊደርስ የሚችለዉ የሞራል ስብራት ቀላል እንደማይሆን ይታመናል:: በመሆኑም የዚህ አይነቱን ችግር ሊታደግ የሚችል ሁለገብ ስትራቴጂ /በፖለቲካዉ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎችማለቴ ነው/ ነድፎ በፍጥነትና በድፍረት ተግባራዊ ማድረግ ያሻል::
ስለ ወልቃይትና ራያ ጉዳይ
2ኛ/ የወልቃይትና የራያን ጉዳይ በፍጥነትና በድፍረት ህጋዊ መፍትሄ መስጠት:: ህዝቡ በምን ዓይነት ግፍ፣ በደልና አፈና ዉስጥ እንደነበር በራሱ በህዝቡ አንደበት ከሰሞኑ ግልጽ እየሆነ መጥቷልና:: እስከዚያዉ ግን የአካባቢዉ ህዝብ ቢያንስ ራሱ በመረጠዉ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲተዳደር አለመፍቀድ መዘዙ ዘርፈ ብዙ እንደሆነ መገመት አያዳግትም ::
ስለተረኝነት ትርክቶች
3ኛ/ በእኔ እምነት የዘረኝነቱና የተረኝነቱ መንገድ እንደሃገርም ሆነ በግለሰብ ደረጃ እስከዛሬ ያደረሰብንን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ብቻ ሳይሆን በዚያ አይነት መንገድ ከቀጠልን እንደ ህዝብ ሊያጠፋን እንደሚችል ታይቷል:: ነገሩን አቅልሎ በማየት እኔ ደግሞ በተራዬ ልሞክረው ብሎ ማሰብ ወይንም የችግሩን ደርዝ አለመረዳት የጤነኝነት ሊሆን አይችልም:: በተቃራኒዉ ደግሞ በትብብር በአንድነት እና በፍቅር አንዱ ከአንዱ ሳይበልጥ በእኩልነት መንፈስ እጅ ለእጅ በመያያዝ መጓዝ ከተቻለ ምን አይነት ስኬት መቀዳጀት እንደሚቻል በሰሞኑ ከሆነዉ ነገር ብቻ መረዳት ይቻላል:: ነገር ግን ዛሬም ከትላንት መማር ያልቻሉ ወይንም ያልፈለጉ አካላት መልሰው እኔ ደግሞ በተራዬ ተረኝነቱን ልሞክረው ባዮችን ማየት ያማል:: በተለይ በተለይ ይህንን ጉዳይ ከጉልምስና እስከ ሽምግልና እድሜያቸው በሃገሪቱ ፖለቲካ ዉስጥ በዋና ተዋናይነት የከረሙት ጎምቱ ሠዎች ዛሬ ላይ መስማት ልብ ያደማል:: ለማሳያ ያህል ”ሃገሪቱን ኦሮሞ እየመራ እያለ ሃገር ብትፈርስ ለኦሮሞ ዉድቀት ነው” አይነት በግልብ ሲታይ ጥሩ ሚመስል ነገር ግን ዘረኝነቱን በማር ለዉሶ ከማቅረብ የማይለይ እሳቤ ያሳዝናል ብቻ ሳይሆን ያስተዛዝባል:: ይህ ነገር ከአንዳንድ የኦሮሞ ፖለቲከኞቻችን መስማት ከጀመርን የሰነበትን ቢሆንም ባብዛኛዉ ይህንን እያሉ ያሉት ታዳጊና እንጭጭ ፖለቲከኞቻችን ከመሆኑ አንጻር ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበስላሉ በሚል በተደጋጋሚ በትዝብት ስናልፋቸዉ ሰንብተናል:: ነገር ግን ጎምቱ ፖለቲከኞቻችን በተለይ በሽምግልና እድሜ ህዝብን ወደ መልካም ነገር መምራት ሲገባቸው መልሰዉ ወደኋላ ሊጎትቱን ሲሞክሩ እንዲታረሙ መጠየቅ ተገቢ ነው ከሚሉት ወገን ነኝ:: በዚሁ መሠረት ዋናዉ ፍላጎቴና ምኞቴ ይህ አባባል የአፍ ወለምታ ሆኖ እንዲቀር ነው:: የሆነዉ ሆኖ ግን በመሠረቱ እየመራ ያለው ኦሮሞ ነው እንዴ ? በብልጽግና ሥር የሚመሩት ከሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች የተዉጣጡ ኢትዮጵያዉያን መስሎኝ:: ከላይ የገለጽኩት አባባል የአፍ ወለምታ ካልሆነ በአንድ በኩል እስካሁን ለተፈጠረዉም ሆነ ወደፊት ለሚፈጠረዉ አደገኛ ቀዉስ ካለ ደንታ ቢስነት በሌላ በኩል ደግሞ በብልጽግና ዉስጥ የተሰባሰቡትን ከኦሮሞ ብሄር ዉጭ ያሉ ኢትዮጵያዉያን መናቅ ነው::
ከዚህ አንጻር በተለይ እርስዎ እንደ ሃገር መሪነትዎ ብቻ ሳይሆን በአሁኑ ሰዓት እንዲህ ያሉ ከፋፋይ ሃሳቦች ባብዛኛዉ እየተነሱ ያሉት እርስዎ ከወጡበት ታላቁ የኦሮሞ ህዝብ በወጡ ፖለቲከኞች ከመሆኑ አንጻር ሃላፊነትዎን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል:: ምክንያቱም እነዚህ ሃይሎች ሃገራችንን ወደ ዳግማዊ የፖለቲካ አዙሪት ከመክተት ባሻገር ልክ ከታላቁ የትግራይ ህዝብ መሃል የወጡት ፖለቲከኞች የትግራይን ህዝብ ወክለናል በሚል ሰበብ ህዝቡን የማይመጥን ሥራ ሠርተዉ የፖለቲካ ሞት እንደሞቱት ሁሉ እነዚህኞቹም ታላቁን የኦሮሞ ህዝብ እይወክሉም እይመጥኑምም የሚል እምነት ስላለኝ ነው:: ከዚህ አንጻር ጎጂ የሆነ ሃሳባቸዉን በማምከን ደረጃ የርስዎና እርስዎ የሚመሩት የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሃላፊነት ፈርጀ ብዙ በመሆኑ ይህንን ሃላፊነትዎ በፍጥነትና በድፍረት ተግባራዊ ያደርጉ ዘንድ ላሳስብዎ እወዳለሁ::
ስለሰንደቅ አላማ
እኔ በግሌ የሰንደቅ አላማችን ሊያጣላን ይገባል ብለዉ ከማያስቡት ወገን ስሆን በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩ ሰንደቅ አላማችን መስማማት የማይቻል ሆኖ የግድ ምልክት ይኑረው ከተባለ ግን ለምሳሌ መሃሉ ላይ የኢትዮጵያ ካርታ ሁሉንም ህዝብ ስለሚወክል ማለቴ ነው ወይንም ሠላምን የምንሻ መሆኑን ለማመላከትም ስለሚረዳ ነጭ እርግብ ማስቀመጥ የሚቻል ይመስለኛል:: የሆነዉ ሆኖ ቢያንስ ከዚህ በሗላ የማንቀይረው እንዲሆን ጥረት ማድረግ ግን ይገባል::
ስለኢትዮጵያ የህዝብ መዝሙር
የጥላሁን ገሠሠ ኢትዮጵያ የኛ መመኪያ የሚለዉን መዝሙር የግድ ማስተካከያ ያሻዋል ከተባለ እንኳን በባለሞያዎች ጥቂት ማስተካከያ ተደርጎበት ወርቅ የሆነ የህዝብ መዝሙር ሊሆን እንደሚሆን ይሰማኛልና ቢታሰብበት እላለሁ::
ክፍል 2
ግዜ ሳይሰጣቸዉ ሊከወኑ ይገባል በሚል እኔና ሌሎች ብዙ ሠዎች የምናምንበት የቀደመዉ መልዕክቴ ዋና ጭብጦች የሚከተሉት ናቸው::
1ኛ/ በሃገራችን እንደ ፖለቲካ ፓርቲ በዘር ወይንም በሃይማኖት የመደራጀት መብትን በህግ መከልከል ግድ እንደሚል::
2ኛ/ አሁን ያለዉን የአስተዳደር ወሰን ወይንም የክልል አደረጃጀትን በሚመለከት ፌዴራሊዝምን ማለትም የህዝብን ራሱን በራስ የማስተዳደር
መብትን እንዲሁም ባህልንና ቋንቋን የማሳደግ መብትን በማይጎዳ መልኩ እንደገና መቃኘትና ማሻሻል::

3ኛ/ ብዙሃን በሚኖሩበት ሌሎች ክልል ዉስጥ የሚኖሩ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሌሎች የህብረተሰብ ክፍል አባላት መብትን እንደዜጋ
በተገቢዉ መንገድ ለማክበር እና ለማስከበር የሚያስችል ጠንካራ ህግ ማዉጣት::

4ኛ/ የክልል ልዩ ሃይል አባላት በሚል ስያሜ በየክልሉ እየተሰጡ ያሉ ስልጠናዎችን ማስቆም ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም የሰለጠኑትንም
ቢሆን በመንግስትም ሆነ በህዝብ ላይ አደጋ በማያስከትልና ዉጤታማ በሚያደርግ መንገድ እንደገና ማደራጀት:: ይሄ በመሆኑ እንደሃገር
ያስከፈለንን ዋጋ ከሰሞኑ አይተነዋል::

ሰዉነት ደሃብ
ከሃገረ ስዊድን
ህዳር 20 ቀን 2013 ዓ.ም.

1 Comment

  1. በቀረበው ሀሳብ በአብዛኛው እስማማለሁ።ሆኖም አቢይን በተረኝነት እንቅስቃሴ ውስጥ ካለው ኦህዴድ ለይቶ የሚታይበት ምክንያት አይገባኝም።የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን የዘረፈ ከንቲባ ሌላ ሹመት የሰጠ፣ አዲስ አበባ የኦሮሞዎች ብቻ ነች ብሎ በፓርቲው ያስወሰነ፣ብልፅግና የተቋቋመው ለኦሮሞ ነው ያለ ፣ህገ መንግስቱ የደም ውጤት ነው ያለ፣በኦሮሚያ የተከናወነውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ተራ ግጭት ነው ያለ ወዘተርፈ።ህወሃት ራሱን ትግሬ የሚመራው መንግስት ብሎ አያውቅም።ይሁን እንጂ በተግባር የትግሬ መንግስት ሆኖ እንደ ቆየ የታወቀ ነው።አቢይ የኢትዮጵያ መሪ መሆኑን በተግባር ማሳየት አለበት።ጨው ለራስህ ብሎ ይጣፍጥ።ኢትዮጵያ የሁላችንም እንጂ የቡድኖች ወይም ቡድኖች የሚያጅቡት ግለሰብ አይደለችም።ጊዜና መስዋዕትነት ይጠይቃል እንጂ ህዝብ መብቱን ያስከብራል።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.