ዉርደት እና ሞት በተባበረ ኃይል ይሰባበር፤ይቀበር  –       ማላጂ

Maykadra 2በዚህች አገር እና ህዝቦች ላይ በኢትዮጵያ እና ኢትዮጵዊነት ላይ የጥፋት ሴራ ተልዕኮ አስፈጻሚዎች ምኞት የተጀመረዉ ዛሬ ሳይሆን ከ18ኛዉ ክ/ዘመን የሚነሳ እንደሆነ  ዛሬም በእኛ ዘመን የሚታዩ እዉነታወች አሉ  ፡፡

የዘመናችን ታሪካዊ  እና ወደር የለሽ የጥፋት መልዕተኞችን ድብቅ ሴራ በቀደሙት የመንግስት ስርዓቶች በግልጽ እና በማያሻማ ሁኔታ ለኢትዮጵያ እና ለዓለም ህዝብ ተነግሯል ሰሚ ባያገኝም ፡፡

ህዝብም ለዘመናት ስጋቱን ከእዉነት ጋር እያጣቀሰ የሰሚ ያለህ ብሎ ሳይሰላች ጮኋል ፤ አድማጭ ቢያጣም ፡፡

በእኛ አገር  ከጥንት አስከ ዚች ዕለት እየሆነ ያለዉ ከቅርብ አስከ ሩቅ ፤ከዉስጥ አስከ ዉጭ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ከብሄራዊ እና ዓለማቀፋዊ ጠላቶች ጋር  በትብብር የሚሰሩት የዉስጥ እና ቅርብ ብሄራዊ ጠላቶች ከሀረር አስከ ጎንደር ፣ ከጉራ  ፈርዳ አስከ ስማዳ ፣ ከደራ አስከ ማይካድራ ፣ ከአርሲ አስከ ጎሊሶ …..በተለይም ከ 1985 ዓ.ም. ጀምሮ እየፈፀሙ ያሉትን መጠሪያ የማይገኝለት ግፍ እና በደል አስቀድሞ የተገለፀ እና የሚጠበቅ መሆኑን እና በተደጋጋሚ የታየ ዕኩይ ተግባር መሆኑን መርሳት ዕዉነተኛ የዚህችን አገር ታሪክ አለመረዳት ወይም ዕዉነትን ክህደት ነዉ ፡፡

ትናንት የኢትዮጵያ ሠባዊ መብት ተቋም(ኮሚሽን) በጎንደር ማይካድራ የሆነዉ አንድን ማህበረሰብ  በማንነት ላይ የተለየ ገድያ ወይም ዘር ማጥፋት (Genocide )ሊሆን እንደሚችል አዝማሚያ ሰጥቷል፡፡

ይህ አስመልክቶም ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ይህን ለይቶ የማጥፋት “ ዘር ማጥፋት ” መሆኑን እንዲስማማ ፣እንዲኮንን ብዙዎች አስተያየት ሲጠይቁ ይስተዋላል ፡፡ ይህ ግን ታሪክን አለማዎቅ ወይም ጠላት እና ወዳጅ አለመለየት እንደሆነ ይገባኛል፡፡

ዓለም ዞትር ከአሸናፊወች እና ድል አድራጊዎች ጋ ናት እና እኛ የማንደፈረዉን ዓለም እንዲመሰክር መጠበቅ ግን ጊዜ ማጥፋት እና የነጸነት ትግሉን መጥለፍ ነዉ ፡፡

በዚህች አገር ለዘመናት ታፍራ እና ተከብራ የራሱ የሆኑ ድንቅ መገለጫዎች ባሏት አገር የቅኝ ገዥነት ልክፍት ያላቸዉ ጠላቶቻችን በቀጥታ ባርነት ባያስተዳድሩንም በአድር ባይ አገልጋይ እና ጥገኛ መልዕክተኞች በኩል ከ20 ዓመታት በላይ በአገራችን የተከሉት የርስ በርስ ባርነት ስነልቦና በህዝብ ዕቢተኝነት ሲመክን በ19 ክ/ዘ መባቻ የተጠቀሙበትን የዉክልኛ ጦርነት ስለመለሱት ነዉ የነጻነት ትግል ያልኩት ፡፡

ጠላቶች ስለ እኛ ምን ቢያሳስባቸዉ ነዉ የርስ በርስ ጦርነት የሚሉት የርስ በርስ ጦርነት ማለት በጦር አበጋዝ ለይቶ እና ጎራ ፈጥሮ ለስልጣን መራኮት ነዉ ፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ በጉልበት የሚገኝ ስልጣንም ሆነ በኃይል ስልጣን ኮርቻ ለመፈናጠጥ ጠበንጃ አያነሳም ፣ቃታ አይስብም ነጻነቱን ግን ሞቶ ያረጋግጣል  እንጅ እየሞተ መኖር እምነቱም ማንነቱም አይፈቅድለትም ፡፡

ስለዚህ የማይካድራ ሞት ፡

የህዝብ እና የአገር ብሎም የዓለም ነዉ ዓለም ሠባዊ መብት ይላል በተግባር ግን ጨካኞችን ያደልባል ፤ይንከባከባል ይህም በዕኛ አገር ሁኔታ ለአለፉት 27 ዓመት የሆነዉን ማሳየት ይቻላል፣

የሠባዊ መብት ያሳስበናል የሚሉት ሁሉ ከማይካድራ በባሳ በአገራችን ለሆነዉ ነገር አንድም ዕልባት የሰጡበት ካለ ያሳዩን፣

በአገራችን በቋንቋ እየተለየ አንድን ህዝብ ከሌላዉ ማሳደድ በህግ እና በዕምነት የሚፈቀድ አስኪመስል ያልተደረገ የ21ኛዉ ክፍለ ዘመን ሰቆቃ በዓለም ሌላ ምድር እንጅ ኢትዮጵያ ላይ የሚል ካለ መኖሩን አንጠራጠርም ማን እንደነበር እና እንደሆነ የሚያሻማ አይደለም እርሱ “በብሄረሰብ የንግድ ስያሜ ” የራሱን እና ቤተሰቡን ህይወት በህዝብ እና አገር ሀብት የቀየረ የዘመናችን አሊባባ ነዉ ፡፡

እናም ከማይካድራ ተነስተን ጉም ጉም፣ መረዶ እና ዋይታ ለዓለም ማሳማት ማን እንዲያስብልንይሆን ፡

  • ኢጣሊ በግፍ አገራችንን ለቅኝ ግዛት ወረራ እንድትሰናዳ ያበረታታት ማን ነበር ፣
  • በጊዜዉ ንጉሰ ነግስት አፄ ኃይለስላሴ በጀኔቭ ለተባበሩት መንግስታት (League of nation )ፀጥታ ምክር ቤት ሲያስረዱ ምን መልስ ተሰጣቸዉ  ፣
  • ለዓመስት ዓመት በዱር በገደል ከፍተኛ ላአገር አንድነት እና ህዝብ ልዕልና የተዋደቁትን እነዚያ የቁርጥ ቀን ጀግኖች ( አቡነ ጴጥሮስ፣ ደጃች በላይ ዘለቀ……..) ሞት መንስኤ እነማን ነበሩ፣
  • ኢጣሊ በቅኝ ግዛት ዘመን በተለያዩ የቅኝ ግዛት አገሮች ላደረሰችዉ የሠዉ ልጅ ሞት እና ለአገራት ድቀት ካሳ ስትከፍል ለምሳሌ ዝቅተኛ በሚባል በደል ለደረሰባት ሊቢያ ስትከፍል ለኢትዮጵያ ግን ያን ያህል ዘግናኝ እና አሳዛኝ ተደራራቢ በደል አድርሳ  በመንግስት ደረጃ እንኳን ለድርጊቱ ዕዉቅና መስጠት አልተፈለገም ፡፡

ለዚህ እና ለመሳሰሉት የጠላት ልብ በትዕቢት እና ክፋት መሞላት የህዝብ እና መንግስት ትስስር አለመጠናከር ነዉ ፡፡

ከዚህ ጋር ፅዮናዊት አገር አስራኤል እና የአሜሪካኖች የነፃነት ትግል ማስታወስ ግድ ይላል፡፡

ከታረክ ድረሳናት እንደምንማረዉ አስራኤላዉያን  በ 1940 ዎች እንደ አገር ለመቋቋም የዓለምን ድጋፍ ስትጠይቅ (በተባበሩት መንግስታት) ዕዉቅና ለመስጠት ካቅማሙት ወይም እምቢተኛ ከሆኑት አንደኛዋ አገር የዛሬዋ አሜሪካ ነበረች ፡፡

ዛሬ ግን ዓለም ወደ አለበት ነዉ እና የሁለቱን ግንኙነት እና ምንነት ዓለም ይናገር ፡፡

አሜሪካ ከአንድ ክ/ን አስቀድሞ ከቅዥ ገዥዋ ታላቋ እንግሊዝ ነጻ ለመዉጣት በነበር የነጻነት ተጋድሎ በአስተሳሰብ የበታችነት እና የተገዥነት ስሜት ባህር ዉስጥ ተዘፍቆ የነበረዉ ብዙ አሜሪካዊ የነበረዉን ትግል የቁም ቅዠት እና የማይቻል በማለት ወደ ካናዳ እና ሌሎች ዓለማት ስደትን ሲመርጥ ጥቂቶች እና ቻዮች የዛሬን የኣለም ምኞት እና መዳረሻ ዓለም ከቅኝ ገዥዎች መንጋጋ አላቀዉ ለዚህ አድርሰዋታል ፡፡

ስለዚህም  ከእኛ በላይ ለእኛ ከሌላዉ ዓለም መጠበቅ ከላይ በጣሊያን ወረራ እና እንዲሁም ላለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት የበሩትን እዉነታ መርሳት፣ መካድ ወይም አለማወቅ ይሆናል፡፡

ከታሪክ አለመማር ሆነ ታሪክን አለማወቅም (መራሳት፣ መካድ እና እያወቁ አለማወቅ)የሞ የሞት ሞት ነዉ ፡፡

ለመጪ ትዉልድና እና ለዓለም አስተማሪ ማድረግ ይቻል ዘንድ በራሳችን ከራሳችን እዉነታ ጋር የሚሄደዉን እና ለደረሱት ክስተቶች መገለጫ ይሆን ዘንድ ፡-

፩) ላለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት በራሳቸዉ ህዝብ እና አገር ላይ በደል ያደረሱ ሁሉ ለሰሩት ስራ ህዝብን እና አገርን በይፋ ጥፋተኝነታቸዉን እንዲያምኑ፤እንዲቀበሉ ማድረግ፣

፪) የበደሉትን አገር እና ህዝብ እንዲክሱ ፣

፫) በአገር እና ወገን ላይ ላደረሱት ጥፋት፣ ዉርደት እና ሞት በህግ የሚጠየቁበት ፣

፬) ለማይካድራ እና ሌሎችም ለዘመናት በራሳቸዉ አገር ምድር እና ወገን በግፍ መሞት በማያወላዳ አኳኋን  የዘር ፍጅት መሆኑ በግልፅ መረጋገጥ የሚቻልበት ሁኔታ  ፣

፪) ኢትዮጵያዊ እና ሠባዊ ፍጡር በመሆናቸዉ በግፍ ፣በአድሎ እና መድሎ በመገለል በደል ለደረሰባቸዉ እና ለሞቱት የ ሠማዕትነት መታሰቢያ እንዲደረግላቸዉ፣ እንዲቆምላቸዉ ማድረግ ይደር የማይባል የህዝብ እና መንግስት ኃላፊነት መሆን አለበት ፡፡

አበዉ “ባለቤት ያቀለለዉን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለዉም ” እንዲሉ እኛ ለእኛ የማንሰጠዉን ክብር ዓለም እንዲሰጠን ፣ እኛ የማንደፍረዉን ዕዉነት እንዲመሰክርልን መጠበቅ ምኞት እንጅ  እዉነት አይሆንም ፡፡  ይህም የራስን እና የአገርን ሚስጥር ሌላዉ እንዲጠበቅ ማሰብ ነዉ ፡፡

በዓለም ፍላጎት እና ምኞት ቢሆንስ ኖሮ እንደ ዓለም ፍረደ ገምድልነት ዓለም ራሷ ጠፍታ ነበር ፡፡

ዛሬ የኢትዮጵያ ጉዳይ (የዉስጥ ጉዳይ) ያሳስበናል የሚሉት ኢትዮጵያን ለዚህ ያደረሳት ማን እንደነበር ስለማያቁ ነዉ  ፤ ለዓመታት ከፍተኛ የመከራ ነዶ እንድንሰበስብ በዘረኝነት ማዕበል እና ጎርፍ  (ግጭት፣ ድህነት ፣መፈናቀል፣ ስደት እና ሞት ) አገሪቷን እና ህዝቧ ሲማቀቁ ፣ ወደብ አልባ ሆና ዜጎች በድህነት አንገታቸዉን ሲደፉ ሰባዊነት ተከብሯል ፤በምግብ ራስን ማረጋገጥ ተችሏል እያሉ ሲያላግሉ ከነበሩት እና በበላይነት የዚህችን አገር እና ህዝብ ዉድቀት ከሚያስተባብሩት  እና ከሚመሩት ሀዘኔታ ሆነ ይሁንታ መጠበቅ በራስ ከመሳለቅ አያንስም፡፡

እኛ ለዕኛ ካልሆን ጠላት የዕኛን ቤት እንዲያድስ ሳይሆን የጀመረዉን የጥፋት ጎዳና እንዲጨርስ ፤እንዲያፈርስ ከዳር እንዲያደርስ  የጥፋት ዱላ ማቀበል ነዉ ፡፡

ባለቤት ካልጪኸ ገላጋይ አይደርስም ፤ክብራችንም ሆነ ዉርደታችን ፣ ህይወታችንም ይሁን ሞታች በዓምላክ ቸርነት እና  በእኛ እጅ ብቻ ነዉ ፡፡

እኛ ኢትዮጵያዉያን ሞተንም ተዋርደንም ዓለምን አይተንዋል ፤ ዓለም ከእኛ ጎን እንዲቆም  እኛ ለራሳችን ራሳችን የቁርጥ ቀን ልጆች ጋር እንደ አንድ ህዝብ እና ብቸኛ አገር ባለቤቶች ሆነን በተግባር እንሰለፍ ፣እንቁም  ይህን ለወዳጅም ለጠላትም በገቢር እናሳይ ፤

ያኔ የሚጠሉን ይወዱናል፤ ያነቁን ያከብሩናል ፤ ቆመዉ የሚያከብሩን የሚመስሉንን የወዳጅ ጠላቶች አንገታቸዉን ማስደፋት እንችላለን ፡፡

በመጨረሻም የኢትዮጵያ እና ህዝቧ (ልጆቿ) መከራ በማይካድራ  ይብቃ በማለት ዉርደት እና ሞት በቃ በማለት በህብረት አንድነት  ይሰበር ፤ይቀበር ከእኛ በላይ ለዕኛ ይቅር ፡፡

 

እናት አገር ለምንጊዜም ትኑር !!!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.