ከመቀሌ በስተጀርባና ከመቀሌ ወዲያ ማዶ – ዶ/ር መኮንን ብሩ

Mekelle Airstrike VOA Amharicአንዳንዴ ለአፍታም ቢሆን ቆም ብሎ ግራ ቀኙን መመልከት መጪዉን ለማስተካከል ይረዳል። ትናንት ዛሬ እና ነገ ሊንጣጠሉ የማይችሉ በመልካም የሰዉ ልጅ ገቢር የተዋቡ አልያም በክፋትና በከንቱነት የጨለሙ የጊዜ ፍሰቶች ናቸዉ። ወንድሙን ከበላዉ ከቃዬል የኃጥያት ጡንቻ ጀምሮ እስከ ጥልቁ የመወርወር ፍርድ ድረስ ዘመን በዘመን እየተተካ መጓዙ መለኮታዊ ግዴታ ነዉና እየተጓዝን እንዳለን እራስን መታዘቡ ለነፍስም ለስጋም የሚበጅ ይመስለኛል።

ትናንትን አለማስታወስ የትናንትን ኃጥያት የመድገም እርግማን መሆኑን ስፔናዊዉ ፈላስፋ ጆርጅ ሳንታና እና ሌሎች ብዙዎች ደጋግመዉ የተናገሩት እዉነታ ነዉና ትናንትን መመርመር ግድ ይለናል።

አሁን በጭንቅ ዉስጥ ካለች መቀሌና ኢትዮጵያ በፊት የነበረችዉን መቀሌንም ሆነ ኢትዮጵያ በአንክሮ ማስታዎሱ ያስፈልጋል። ከሳምንት ከወራት ከዓመታት እና ከሺህ ዘመናት በፊት መቀሌም ሆነች ኢትዮጵያ የት ነበሩ? ….. እንዴት በየት ወደዛሬዉ የጭንቅ ሰዓታት ደረስን? …. ከዛሬዉ ጭንቀትስ በኋላ ጉዟችን ወዴት ነዉ? ይህን ቆም ብሎ በመጠየቅና በአግባቡ በመመለስ የቃዬልን ጡንቻ በመግራት የኖህ መርከብን ይሰራ ዘንድ ለማድረግ ይረዳል ብዬ አምናለሁ። አልያ ከትናንት መማር ተስኖን የተቅበዘበዘና የማይደማመጥ የባቢሎን ትዉልድ በመሆን እርስ በእርስ መጠፋፋታችን ከመቀሌም በኋላ ይቀጥላል።

በአክሱም ዘመነ መንግስት  በአራተኛዉ ክፍለ ዘመን ክርስትናን እስከተቀበለዉ ንጉስ ሂዛና ….. ለጥቆም የዛግዌ ዘመነ መንግስትና አያይዞም እስከ አስረኛዉ ክፍለ ዘመኑ ሰለሞናዊዉ ይኩኑ አምላክ ድረስ ኢትዮጵያ ይብዛም ይነስም እራሷን እየፈለገችና ማንነቷን በዓለም ታሪክ ዉስጥ እየፃፈች የነበረችበት ወርቃማ ጊዜዋ ነበር። ቀጥሎ የመጣዉ ግን የምድሯ ቡቃያዎች ሲጨራረሱ በሰቆቃ የታዘበችበትና እስካሁን በሚመስል ሁኔታ እርስ በእርስ ሲሳደዱ የታዘበችበት ዘመነ መሳፍንት ነበር።

ኢትዮጵያ ከአርመንያ ቀጥላ ክርስትናን በመቀበል ድንቅ የዕምነት ገድል የፃፈች ጥንታዊ ሀገር መሆኗን የሚመሰክር የቁሳቁስ ቅሪት ተገኝቶ በሳይንስ ተረጋግጧል። በሰባተኛዉ ክፍለ ዘመንም እስልምናን ፈቅዳ የእራሷ ያደረገች የታሪክ ፀጋ ባለቤት ነች።ይሁን እንጂ በዘመኗ እንደ ጥቁር እንግዳ ሳይጠበቁ ብቅ በማለት ዉበቷን የሚያኮስሱ …. ቅድስናዋን የሚያረክሱ ….. ቤተ-ዕምነቷን የሚያልከሰክሱ እባቦችም ተፈራርቀዉባታል።

ዮዲት ጉዲት እንደ ወያኔ ለአርባ ዓመታት የተጠጋዉን የሰቆቃና የግፍ የንግስና ዘመኗን በዘጠነኛዉ ምዕተ ዓመት ከአክሱሞች ተቀብላ ክርስትናን ለማጥፋት ጦሯን በመስሰብቅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንን ለማጥፋ ዘመተች። ከዚያም ቤተ ክርስትያን አቃጠለች፣ ምህመናንን አሳደደች፣ ቅዱሳንን አረከሰች፣ ቤተ መቅደስን በጫማዋ እረገጠች፣ በመጨረሻም የቅድስቲቷን ምድር ትዉልድ አልከሰከሰች። ወያኔም ቤተክርስቲያኗን ጠላቴ ብሎ እንደ ብል ከዉስጧ ለአርባ ዓመታት ስታኝክና ስትቦረቡር ከረመች።ጳጳስ በጳጳስ ላይ ሾመች። ከተማ መንደሩን የሴት ልጅ ገላ በገንዘብ የሚቸበቸብበት የሶዶምና የጎሞራ ምድር ፈጠረች።

በኋላ ግን ቀናተኛ ነኝ የሚለዉ አምላክም በዘጠኝ መቶ አስራ ሁለት (912) ዓመተ ምህራት ዮዲት ጉዲት ወደ መቀመቅ ትወረወር ዘንድ ፈቀደ። የገባችበት ገብተዉ ምሷን ይሰጧትም ዘንድ ላሊበላን የመሰለ ድንቅ ተዓምር የሰሩትን የወሎና የጎንደሮቹ የዛግዌ መኳንንትን ነበር የመረጠዉ። ልክ ከአንድ ሺህ ዓመታት በኋላም ዛሬ እንደ ዮዲት ጉዲት አንቺ ብለን የምንጠራት ወያኔ  በተራዋ ወደ መቀመቅ ለመግባት በመቀሌ ከተማ ዉስጥ ታጥራ ወደ መቀመቋ ለመዉረድ እያጣጣረች ትገኛለች። ከታሪክ የማይማር ታሪክን ይደግማል ይሉሃል ይሄ ነዉ።

ዶ/ር መኮንን ብሩ።

1 Comment

  1. በኢትዮጵያ በቀይ ሽብር ጊዜ የተለኮሰው እሳት እስካሁን ድረስ ሙሉ በሙሉ አልተዳፈነም። እሳቱ ፍም ሆኖ ይቆይና ፍሙ እንደገና እሳት እየሆነ ሲያቃጥለን እስከአሁን ድረስ አለ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.