በሰሜን ዕዝ 4ኛ ሜካናይዝድ ላይ ጥቃቱ እንዴት ተፈጸመ? – የሻለቃ አምሳሉ ደመቀ የዓይን እማኝነት

end
በአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ 4ኛ ሜካናይዝድ ላይ ጥቃቱ እንዴት ተፈጸመ? በእለቱ ድባቡ ምን ይመስል ነበር? – በስፍራው ከነበሩት ሻለቃ አምሳሉ ደመቀ የአይን ምስክር ሆነው ሁኔታውን በአንደበታቸው ይነግሩናል።
“ባለብዙ ገድል ወራሪን ድባቅ መምታት እንጂ ሌሎቹን በግፍ የመውረር ታሪክ የሌለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ባልተጠበቀው፤ ጌታውን እንደሸጠው ይሁዳ፣ በገዛ ወገኔ ተከዳ” በማለት ንግግራቸውን ጀመሩ።
“የቅርብ ጠላቴን እንጂ የሩቁን እጠብቀዋለሁ’ እንዲል አገሬው፤ ሰራዊቱ አገር አማን ባለበት ወቅት በወዳጁ ጥቃት ተከፈተበት።
“ጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የኖረበት ወታደራዊ ስነ ስርዓትና ክብር “የእኔው ናቸው” ብሎ ያምናቸው በነበሩ ከሃዲያን ተደፈረ” በማለት ንግግራቸውን ይቀጥላሉ።
እለቱን እንዲህ ያስታውሱታል ሻለቃ አምሳሉ፤ ጥቅምት 24 ቀን 2013 አመሻሽ ላይ።
ለሩብ ክፍለ ዘመን አገሩን በጠበቀበት፣ ወልዶ ከብዶ፣ ከማህበረሰቡ ጋር ተላምዶና ተጋምዶ፣ ቤተሰብ መስርቶ በቆየበት ሰፈር ሲጠብቀው በኖረውን ቀዬ አገር አማን ብሎ ተቀምጧል። ሰዓቱም ውድቅት ሆኗል – ልክ 5 ሰዓት ተኩል።
በትግራይ ክልል ኩይሃ ከተማ በሰሜን ዕዝ ውስጥ በሚገኘው 4ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር የእናቶች ሲቃ፣ የህጻናት ሰቆቃ ይሰማል።
ሰራዊቱን ለ32 ዓመታት ያገለገሉት፣ ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ ደግሞ በስፍራው ለ20 ዓመታት ያሳለፉት የክፍለ ጦሩ አመራር ሻለቃ አምሳሉ ደመቀ የጥቅምት 24ን አጋጣሚ መናገራቸውን ይቀጥላሉ።
ከህዲዎች እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት የ4ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር አዛዥ ኮሎኔል ገብረስላሴን ጨምሮ በሰራዊቱ ያሉ አዛዦች በመመሳጠር ሰራዊቱ ካለትጥቅ እንዲቀመጥና መጋዘኑን እንዲቆለፍ ቀድመው አሲረዋል።
“ባደራጇቸው ሰዎችና በልዩ ሃይል አማካኝነትም በመጀመሪያ የጦር መሳሪያና ንብረት ዘረፋ ገብተዋል፤ ከቀላል አስከ ከባድ መሳሪያ እየጫኑ ወስደዋል” ይላሉ።
ከሃዲዎች በካምፕ ውስጥ የሚገኙ ከቀላል እስከ ከባድ መሳሪያ እየጫኑ ከወሰዱ በኋላ ከ400 በላይ ሰው መያዝ በሚችል አዳራሽ እንዲገባ አድርገዋል።
“በድርጊቱ ያልተስማሙትንም ከዋርድያ (ከተረኛ የካምፑ ዘብ) እስከ የሬዲዮ መገናኛ ባለሙያዎች መግደል ጀመሩ” ይላሉ-ታዛቢው ባለታሪኩ።
ለመሆኑ ሻለቃ አምሳሉ ደመቀ እንዴት ተረፉ?
“ከግድያ እርምጃቸው ፋታ ወስደው መሳሪያውን ዘርፈው ጀሌውን ያስቀመጡትን ሰራዊቱን ሰብስበው ሁለት አማራጭ ብቻ አቀረቡ” ይላሉ ሻለቃ አምሳሉ።
በከሃዲዎቹ የቀረበው አማራጭ አንድ ከራሳቸው ወገን በማሰለፍ መከላከያ ሰራዊቱን መውጋት ሲሆን ሌላው አማራጭ ለሞት (ለመረሸን) ዝግጁ መሆን ብቻ ነው።
ከሃዲዎቹ የሰራዊቱን አባላት ለእኩይ አላማቸው አብረዋቸው እንዲሰለፉ ማድረግ ካልሆነም በአሰቃቂ ሁኔታ የጅምላ ግድያ ለመፈፀም የተጠና ዝግጅት አድርገዋል።
በዚህ ቅፅበት ነበር ሻለቃ አምሳሉ የከሃዲዎቹን ትእዛዝ ተቀብለው የራሳቸውን አባሎች አልወጋም በሚል ያፈተለኩት።
አሁን ሻለቃ አምሳሉ “ውጥረት በነገሰበት በዚያ የሲኦል ምሽት” አምልጠው በቅፅበት አዲ ጉዶም ላይ በመኪና ተሳፍረው አላማጣ ደረሱ።
ከዚያም ከሰይጣኖቹ መዳፍ የሾለኩት ሻለቃ አምሳሉ ከአላማጣ የክልሉ ልዩ ሃይል እንደማያሳልፋቸው ሲረዱ በማሽላ አዝእርት ውስጥ ለውስጥ በማቆራረጥ ወታደራዊ ጥበባቸውን እየተጠቀሙ በማለፍ ቆቦ ከተማ መድረስ ችለዋል።
ሰራዊቱ ለዚህ የከሃዲዎች ጥቃት ምላሽ በመስጠት የህግ ማስከበር ዘመቻውን ጀምሮ በርካታ ድሎችን አስመዝግቧል።
አዲስ አድማስ
ተጨማሪ ያንብቡ:  ”ቢቢሱ ሃርድ ቶክ” ቆይታ ህወሃትና እና “የብሄራዊ ጥቅም” - ነአምን ዘለቀ

1 Comment

  1. ይህ ባንድራ ህወአት ለኢትዮጵያ የሰጠዉ ነዉ ክልላቸዉ ዉስጥ ይህ ባንድራ አይሰቀልም አይዉለበለብም ወዲያ ቀዶ ጥሎ ትክክለኛዉን የሀገራችንን ባንድራ መስቀል ነዉ። ይህ ባንድራ የኢትዮጵያ ባንድራ አይደለም። ጎበዝ ያረዷችሁ ሰዎች እኮ የዚህ ባንድራ ሰዎች ናቸዉ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.