በቀጣይ ቀናት የመጨረሻው ሕግን የማስከበር ተግባር ይከናወናል፡ ጠ/ሚ ዐብይ

125250907 3520021838088530 5101898156027565519 n በቀጣይ ቀናት የመጨረሻው ሕግን የማስከበር ተግባር ይከናወናል፡ ጠ/ሚ ዐብይ

በቀጣይ ቀናት ውስጥ የመጨረሻው ሕግን የማስከበር ወሳኝ እርምጃ በትግራይ ውስጥ ባሉ ኃይሎች ላይ እንደሚወሰድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በትግራይ ክልል ተሰልፈው ያሉ የልዩ ኃይልና ሚሊሻ አባላት ለአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት በሠላም እጃቸውን እንዲሰጡ በፌደራል መንግሥቱ የተቀመጠው የሦስት ቀናት ቀነገደብ መጠናቀቁን ተከትሎ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ዛሬ ጠዋት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቸው ላይ በአማርኛ እና በትግርኛ ባሰፈሩት መልዕክት

የትግራይ ልዩ ኃይልና የሚሊሺያ በሠላም እጁን በመስጠት እራሱንና ሕዝቡን እንዲያድን የተሰጠው ቀነገደብ ማብቃቱን አመልክተዋል።

ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ለሦስት ቀናት ለትግራይ ክልል ኃይሎች ተቀመጠው ቀነ ገደብ መጠናቀቁን ተከትሎም “በቀጣይ ቀናት የመጨረሻው ሕግ የማስከበር ወሳኝ ተግባር ይከናወናል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀናት በፊት የትግራይ ልዩ ኃይልና በሚሊሻ “የስግብግቡ ጁንታ እኩይ ዓላማ ማስፈጸሚያ ከመሆን ይልቅ” እጁን በመስጠት በእራሱ ላይና በሕዝቡ ላይ የሚደርስን ጉዳት እንዲያስቀር ጥሪ አቅርበው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም በተሰጠውን ቀነ ገደብ በመጠቀም እጃቸውን ለመከላከያ ሠራዊት የሰጡ “የትግራይ ልዩ ኃይልና ሚሊሺያ አባላት፣ ለወሰዱት ኃላፊነት የተሞላው ሕዝባቸውን የማዳን ውሳኔ” ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

አስካሁን ምን ያህል የልዩ ኃይሉና የሚሊሻ አባላት ለመከላከያ ሠራዊት እጃቸውን እንደሰጡ የተገለጸ ነገር ባይኖርም የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እጃቸውን የሰጡ ያሏቸውን የትግራይ ልዩ ኃይል አባላት ባለፉት ቀናት ሲያቀርቡ ታይተዋል።

ትግራይ ውስጥ በሚገኘው የሠሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙ ከተገለጸ በኋላ የተቀሰቀሰው ወታደራዊ ግጭት ሁለት ሳምንት ሊሆነው የተቃረበ ሲሆን ትክክለኛ አሃዝ ማግኘት በዚህ ሂደት የሞቱና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች እንዳሉ እየተነገረ ነው።

በግጭቱ ሳቢያም በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን እየሸሹ መሆናቸውን የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች እያመለከቱ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እነዚህ ዜጎች ወደ አገራቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ ለመርዳት መንግሥታቸው አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ትላንት ገልጸዋል።

በፌደራል መንግሥቱና የትግራይን ክልል በሚያስተዳድረው ህወሓት መካከል የተከሰተው አለመግባባት ተካሮ ወደ ግጭት ካመራ በኋላ መንግሥት እየወሰደ ያለው እርምጃ ሕግን የማስከበር በመሆኑ የትግራይ ኃይሎችና አመራሮቹ እጃቸውን እንዲሰጡ ማሳሰቡ ይታወሳል። BBC

1 Comment

  1. በግ ከበረረ ሞኝ ካመረረ መመለሽያ የለውም! የጁንታ ደጋፊ አትሞኝ ። አሁንም በሰላም እጅህን ስጥ።
    ጁንታ ሞኝነታችሁን ተዉት ከአሁኑ መቀሌ ሳትያዝ እጃችሁን ስጡ አልያም እንደ አንዳንዶቻችሁ እንዳደረጉት ወደ ወዳጅ ሀገራት አቅኑ እዛው ወና ጭንቅላት የተሰበሰበበት ምክር ቤት አከባቢ የታጎራችሁም ድርቅ አትበሉ። እስካሁን ካልተገነዘባችሁን ጦርነቱ በጊዜው የሚያበቃው የእናንተ ጁንታዎች በፀጋ ተቀብላችሁ ሆነ አልያም በኃይል ተገዳችሁ የሽንፈት ፅዋን ስትጎነጩ ነው።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.