ትግራይ፡ ግጭቱን ፈርተው ወደ ሱዳን የገቡ ተፈናቃዮች ቁጥር ከ30 ሺህ በላይ መድረሱ ተገለፀ

ወደ ሁለት ሳምንት ባስቆጠረው የፌደራል መንግሥትና ትግራይ ክልል ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ30 ሺህ እንደበለጠና ከቀን ወደ ቀንም እየጨመረ መሄዱን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽነር፣ ዩኤንኤችሲአር አስታውቋል።

115526988 gettyimages 1229642997ግጭቱ ያስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ መባባሱን የገለፁት በካርቱም የዩኤንኤችሲአር ድንገተኛ ምላሽ አስተባባሪ ጀንስ ሄዝማን ሁኔታውን “አስጊ ነው” ብለውታል።

በድንጋጤ የተዋጡ፣ እራፊ ጨርቅ ላያቸው ላይ ጣል ያደረጉና በፍርሃት የተሞሉ ተፈናቃዮች ወደ ሱዳን ያቀኑ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት ታዳጊዎች እንደሆኑም መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ኢትዮጵያን በትግራይ ክልል በኩል ከሱዳን ጋር የሚያዋስነው ድንበር የሚገቡ ኢትዮጵያውያን ተፈናቃዮች ሁኔታ እየተከታተሉ ያሉት አስተባባሪው፤ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ በምሥራቃዊዋ የሱዳን ግዛት በሦስት ቦታዎች የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር መጨመር አሳሳቢ ነው ብለዋል።

በተለይም በሃምዳያት በኩል ከፍተኛ የሆኑ ተፈናቃዮች ቁጥርም እየተመዘገበ ነው፤ በየቀኑም “አስገራሚ” በሚባል ሁኔታም እየጨመረ መሆኑን አስተባባሪው ይናገራሉ።

በትናንትናው ዕለት፣ ህዳር 7/ 2013 ዓ.ም ብቻ 2 ሺህ 300 አዲስ ተፈናቃዮች ሱዳን ገብተዋል። ከትናንት በስቲያ እንዲሁም ከ 5 ሺህ በላይ አዲስ ተፈናቃዮች መግባታቸውንም አስተባባሪው አስረድተዋል።

ከዚህ ለየት ባለ ሁኔታም በደቡባዊ ሱዳን በኩል በርካታ ተፈናቃዮች እየገቡ መሆናቸውን ዩኤንኤችሲአር ተመልክቷል።

አካባቢው ከዚህ በከፍተኛ ርቀት ከመገኘቱ አንፃር “ወደ ተለያዩ የድንበር አካባቢዎች እየተስፋፋ ለመሆኑ ምልክት ነው” ይላሉ።

ሃምዳያት የድንበር አካባቢ መሸጋገሪያ ስትሆን በቦታው ያለው የመጠለያ ማዕከል በዩኤንኤችሲአር ቢቋቋምም ትንሽ ቁጥር ያላቸውን ተፈናቃዮች ለማስተናገድ የተከፈተ ነው።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ለማስተናገድ የተቋቋመው ማዕከል በሺህዎች በሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ተጨናንቋል።

ማዕከሉ ማስተናገድ ከሚችለው በላይ በከፍተኛ ሁኔታ ተጨናንቆ የሚገኝ ሲሆን ተፈናቃዮች በአካባቢው እንዲሁም ወደ ሃምዳያት ከተማም ለመሄድ መገደዳቸውንም አስተባባሪው ይናገራሉ።

ተፈናቃዮቹ ባገኟቸው መጠለያዎች ሁሉ ተጠልለው እንደሚገኙም አክለዋል።

የአካባቢው ማሕበረሰብ ለተፈናቃዮቹ ደግነትን በማሳየት ያላቸውንም እያጋሯቸው እንደሚገኙም ይናገራሉ።

የአካባቢው ባለስልጣናት በተመሳሳይ መልኩ ተፈናቃዮቹን በበጎ መልኩ ተቀብለው እያስተናገዱ ሲሆን ስደተኞቹ የሚያርፉባቸው ስፍራዎችን በመለየት ላይ ይገኛሉ።

የተፈናቃዮቹን ህይወት ከማዳንና ድንገተኛ ሥራ ከመስራት በተጨማሪም ዩኤንኤችሲአር በዋነኝነት ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሰራበትም ስደተኞቹ መጠለያ እንዲያገኙ ማድረግም ነው።

“ተፈናቃዮቹ በድንጋጤና በፍርሃት ተውጠው ይገኛሉ። በርካቶቹ ለደኅንነታቸው ይሰጋሉ። ከደረሱም በኋላ ጥላቸውን አያምኑም። ብዙዎቹም እዚህ ደህና ነን ወይ እያሉ ይጠይቃሉ? አሁንም ህይወታችን ከአደጋ ወጥቷል ብለው አያምኑም” ይላሉ አስተባባሪው።

አንዳንዶቹም ቀጥታ ጦርነት ከሚደረግባቸው ቦታዎች የሸሹ ሲሆን ስለደረሰባቸውም ጥቃትና እንግልት ለዩኤንኤችሲአር አስረድተዋል።

በተለይም በአሁኑ ወቅት ለዩኤንኤችሲአር ፈተና የሆነበት የተፈናቃዮቹ ቁጥር ከቀን ወደ ቀን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱ ጋር ተያይዞ በሺህዎች ለሚቆጠሩ ተፈናቃዮች በአፋጣኝ የድጋፍ እርዳታ ማድረግ ነው።

ማዕከሉ በዚህ ደረጃ ስደተኞችን ለመቀበል የአቅርቦት ማዕከል ባለማዘጋጀቱም ጭምር እክል ሆኗል። በሱዳንም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃም እርዳታም ለማሰባሰብ ጥረት እየተደረገም እንደሆነ ይናገራሉ።

የተፈናቃዮቹ ሁኔታ ለዩኤንኤችሲአር እንዲሁም ለአጋር ድርጅቶቹ በዓለም ምግብ ፕሮግራምና በዩኒሴፍ ዋነኛ ኃላፊነት በመሆኑም የድንገተኛ ቡድኖችን በመላክ ይገኛሉ።

የተለያዩ እርዳታዎችንም በማሰባሰብ ጭምር እንደሚገኙ የገለፁት አስተባባሪው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ከሱዳን መዲና ካርቱም እንዲሁም ከውጭ አገራት እየገቡ ነው ብለዋል።

የፌደራል መንግሥት ሕግን የማስከበር ሂደት በሚለው ዘመቻ ከትግራይ ክልል ልዩ ኃይል የተቀሰቀሰውን ግጭት በመሸሽ በርካታ ሰዎች ወደ ሱዳን ለመሰደድ መገደዳቸው ተነግሯል።

BBC

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.