ንገረኝ ጀግናዬ! – ከራሔል አሸናፊ መንገሻ

125428040 2766635163551841 251458235549591768 n 1

ንገረኝ ጀግናዬ!

አንተ ቃል አክባሪ ከድል ያልጎደልከው
አንተ ብርቱ ጀግና አገር ያቀናኽው
የተዋደቅክለት ሲጥልህ መልሶ
የተጋደልክለት ሲገድልህ ተኩሶ
በስተመጨረሻው የነፍስህ ህቅታ
ጸጥ እረጭ ሳትል የልብህ ትርታ
ምን ብለኽው ይሆን? ይህን ነብሰ-በላ
የሀገር አደራን ቀርጥፎ ሲበላ
ንገረኝ እባክህ አንተ ክንደ-ብርቱ
ምንኛ ደለቀ የልብህ ምታቱ?
ንገረኝ ጀግናዬ ስትስመው ነክሶ ስታነሳ የጣለህ?
ሞቱን ስትሞትለት መልሶ የገደለህ
ምን ቢሰፍርበት ነው እንደዚህ የከፋው
ውለታህን ሁሉ በግፍ አለቅልቆ ከመሬት የደፋው
ንገረኝ በሞቴ መለዮህን ወስዶ ካናቱ አጠለቀ?
ለዶሮ ጭንቅላት እንደማይሆን ሲያውቀው መልሶ አወለቀ?
ንገረኝ በሞቴ ዝናርህን ወስዶ ላይሆን ሞካከረው?
ወንድነት ይቀማ ይነጠቅ መሰለው?
ጀግና ልጅ እንዳለህ ማንም አልነገረው?
መቼም አያርመው ንገረኝ እባክህ
እጀ-ጠባብህ ላይ እጣ ተጣጣለ?
ስጋህን ላሞራ ከዛፍ ላይ ሰቀለ?
ያንገብግባት ብሎ አንተን ሳሰላስል
የምኮራበትን ገላህን ስመስል /ጠበረቆ ይነበብ/
ሬሳህን ለአውሬ በአውሬነት ሰጥቶ
ከፊትህ ሲሰወር ከጨለማ ገብቶ
ከናትህ አፈር ላይ በጀርባህ ተንጋለህ
ከምሽት ጨረቃ ሰንደቅህን ስለህ
የገዛ ቀኝ እጅህ ወሽመጥክን ሲቆርጠው
ኢትዮጲያዊነቱን ድንጋይ ላይ ሲያፈርጠው
ምን ነበር ህቅታህ ንገረኝ በሞቴ
እንዲያቆፈጥነኝ እንዲሆን ብርታቴ
መቼም አትደብቀኝ
በኔና አንተ መሀል ስውር ምስጢር የለ
የአብራክህ ክፋይ ብሎ ሲጠየቀኝ አባዬ ምን አለ
እንድተርክለት ያንተን ወኔ ጀብዱ
ላገር እንደጨከንክ እንዲጨክን ሆዱ
ንገረኝ ጀግናዬ
ላላለቅስ ምያለሁ ጠብቋል መቀነቴ
ደምክን ተነቅሼው ካንገት ከደረቴ
ሞትክን ላጌጥበት ንገረኝ በሞቴ
ቃሌን አላፈርስም አይፈስም እንባዬ
ገደልነው ቢሉኝም አልሞትክም ጀግናዬ
ንገረኝ ግድ የለም
በየቱ ቢላ ነው በየትኛው ስለት የገዛ ቀኝ እጅህ እጁን የቆረጠ
የዘመን ይሁዳ ለረከሰ ዲናር ለሆዱ የሸጠህ
ንገረኝ ጀግናዬ የዘለባበዳው ልጅ የቆላው ገበሎ
የትኛው ጋኔል ነው እርቃን ያጋደመህ ዝናርክን ገንጥሎ
ንገረኝ ጀግናዬ ንገረኝ ጎበዜ
ገድልህን ለትውልድ ከትቤ ልያዘው ማለፉ አይቀር ጊዜ
ይህን የሰው ጭራቅ እንድዘብትበት
ያረገህን ሁሉ የሆነውን ሁሉ ተው አትደብቅለት
ንገረኝ ግዴለም በጻድቃን ጉባኤ አንት አትወቀስም
ደምህ ያቤል ደም ነው ዝም ብሎ አይፈስም
ቃሉን ያከበረ ስሙም አይኮስስም
አትደብቅለት ጉዱን አፍረጥርጠህ ግለጠው ልረዳ
ለልጅህ ነግሬ እንዲጀግንልኝ እንዲቀለኝ እዳ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለቆጠራ ዬተቀመርን - ሥርጉተ©ሥላሴ

ከራሔል አሸናፊ መንገሻ


 

ምን ሆነሽ ከሳሽ ይሉኛል

ምን ሆነሽ ከሳሽ ይሉኛል
ጥያቄው ራሱ ያመኛል
ምን ሆኜ ነው ልበላቸው
ፍርሀቴ ላያስፈራቸው
ስጋቴ ላያሰጋቸው
ችግሬ ላይቸግራቸው
ነገሬም ላይታያቸው
ምን ሆነሽ ከሳሽ ይሉኛል ምን ሆኜ ነው ልበላቸው?
እኔ ችጋሬን በስንጥር
ከ-ደረቅ አፈር ስቆፍረ
ካሸዋው ጥሬን ስለቅም
የኑሮ እራፊን ለብርዴ ግራና ቀኙን ስጠቅም
ከቅንጦት ቅንጦት አማርጠው
ካማረ ቪላ ተቀምጠው
ጥጋባቸውን በሹካ ካናቱ እየቧጠጡ
የጎረሱትን ሊውጡ ከወይኑ እያጫለጡ
ምን ሆነሽ ከሳሽ? ይሉኛል እንደምን ልግለጥላቸው?
የኔኑ መሆን ሆነውት መሆኔ እስኪገባቸው
ምናል ህመሜን ጉዳቴን ለጊዜው ለኔው ቢተውት
አጉል ወጌሻ ባይመስሉ መልሰው ቅስሜን ሊሰብሩት
ስጋዬን ግጠው ገሽልጠው – ለምን አጥንትሽ ገጠጠ
ዋዲያት ሌማቴን ገልብጠው – እንዴት ጎተራሽ ታጠጠ
በጥፍሬ የለቀምኳትን ስጤን ከደጄ እየደፉ
ፈካች ያልኳትን አበባ ካይኔ ስር እየቀጠፉ
እቀና ያለች ማጀቴን ከርስቷ እየነቀሉ
ኩራዜን በግፍ ደፍጥጠው ብርሀኔን እየገደሉ
ደሀ ሰፈሬን አቃጥለው ጥግ ይዘው እያላገጡ
አሳሬን ሲጨፍሩበት ላዝማሪ ዜማ እየሰጡ
እዩልኝ ሲሸቃቅጡ፤ ነጩን መሀረብ ሲያመጡ
ራሳቸው እያስለቀሱ – ገላጋይ መስለው ሲደርሱ
ሬሳ ላይ እየደነሱ – የነብሴን ጩኅት ሲያብሱ
እንደው እፍረትም የላቸው?
ምን ሆነሽ ከሳሽ ይሉኛል?
ጥያቄው ራሱ ያመኛል!
ምን ብዬ ምላሽ ልስጣቸው?
ተረፈ-ምርቴን ላራግፍ ከጂም መዋሌን ላውጋቸው
አቋሜን ለማስተካከል የምጥ ሩጫዬን እሮጬ
እሮጬ፤ ሮጬ፤ እሮጬ አ-ለ-ቅ-ጥ ተንቆራጥጬ!
የደም ላብ አላበኝ ብዬ
እሬቱን በማር ጠቅልዬ
የመሰሉትን መስዬ
በ-አሽሙር ላላግጥባቸው?
ያኔ ነው የሚገባቸው?
ወይስ ጤናዬን አስቤ
ሆዴን ከእህል ቆጥቤ
ምሳዬን ግማሽ ከፍዬ
እራቴን በጁስ ጭማቂ – ለጥቂት ቀናት ዘልዬ
ዳ-ይ-ት – ገብቼ ል-በ-ላ-ቸ-ው
እንደዚ ብናዘዝ ይሆን ብሶቴ የሚገባቸው?
እስቲ ንገሩኝ በሞቴ
ከራብ ከእርዛት ተርፌ በስጋት እየባነንኩኝ
ህልሜና ውኔ ተምታትተው አለሁ የለሁም እያልኩኝ
ወልዶ ማሳደግ ምጥ ሆኖ ወልዶ መሳቀቅ ሲመጣ
ወላጅ በውላጅ ሲረገጥ አባት በልጁ ሲቀጣ
ጭንቀት ከጭንቁ ሲማማጥ ስጋት ስጋትን ደርቦ
ም-ነ-ው- ከ-ሳ-ሽ ብሎ አግቦ!
አ-ይ-ገ-ር-ም-ም!
አሽሙሩስ አጥንት አይሰብርም
ከልካይ ገላጋይ ሲጠበኝ ላፍታ እንኳ አለሁ ያላለ
የሀገር ድንጋይ ሲያልቅብኝ ገዳዬን ያልሸመገለ
አይኑን በጨው እያጠበ
ድርቀቱን እያረጠበ ስስ ልቤን ከሚሞግተው
ምነው የቤቴን ለቤቴ ክሳቴን ለራሴ ቢተው?
ስለምን ይጠይቀኛል መልሱስ ከላዬ ተጽፎ
እያየው የጎን ውጋቴን ግራና ቀኜን ቀስፎ
የሙዚቃቸው ግምግምታ የዳንኪራቸው ርግደቱ
የፈንጠዝያው ብርቅታ የድሎታቸው ስባቱ
ብርሀናቸውን ካልነሳ ያይናቸው ሞራ ተጋግሮ
መስሚያቸው ካልደነቆረ በትእቢታቸው ከበሮ
እስቲ ፍረዱኝ እናንተው በህይወት መኖሬ ሳይደንቀው
አስሬ ከሳሽ የሚለኝ ብከሳስ ምን አስጨነቀው
ቢጠይቅ እንኳ ሚያምርበት ብወፍር ነበር ብወዛ
ቢመቸኝ ብደላደለው ነብሴ እንደነብሱ ደንዛ
የውስጥ የውጪው እሪታ ሌሊቴን እያስጨነቀው
የቅርብ የሩቁ መርዶዬ ስጋዬን እየቦጨቀው?
ምን ሆነሽ ከሳሽ ይባላል? ወገኔ ነዶ እየጋየ
ም-ድ-ሬ በደም አበላ ሌት ተቀን እየጨቀየ
ይህንን ሁሉ ህቅታ ህ-ቅ-ቅ! እያለው ደረቴ
ምን አ-ግ-ኝ-ቶ-ሽ ነው? ይባላል ንገሩኝ እስቲ በሞቴ?
መ-ኖ-ሬ* ነበር ግርምቱ! ያላሳብ መሽቶ ቢነጋ
ህሊናን ለሆድ ገብሬ ስጋ ካጥንቴ ቢጠጋ
እና ባካችሁ እንዳዛኝ የማይሆን ቅቤ አታንጉቱ
ተዉኝ ዝም ብዬ ልክሳበት ከላዬ እስኪገኝ ብልሀቱ
ምን ሆነሽ ከሳሽ አትበሉኝ ጥያቄው ራሱ ያመኛል
የወዳደቁት አጥንቶች ቢያምርብኝ ይሞግቱኛል
እና ባካችሁ ዝም በሉኝ ጽዋዬን እኔው ልጠጣ
ብሞት ብሽርም ማራዬን እስኪያጣፍጠው ልቀጣ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  እንኳን መሞት አለ ማርጀት (ዘ-ጌርሣም)

ከራሔል አሸናፊ መንገሻ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.