ሱሪ (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

 

የወልቃይት ነገር ሲነሣ ለአሠርት አመታት ስንሰማ የኖርነው ሕወሃት በወልቃይት ያካሄደው ግፍ እጅግ ስለሚከነክነኝ አንዳንድ ታሪካዊ ጽሑፎችን ለማንበብ እሞክር ነበር። የመጀመሪያ ደረጃ ግርምቴ ወልቃይት ውስጥ አገዎች ይኖሩ ነበር የሚሉ ጽሑፎች ስላገኘሁ የአማራ ነው/ የትግሬ ነው የሚለው ክርክር ጭራሽ በሦስተኛ ሕዝብ በአገው ርስት ላይ ነው እንዴ? የሚል ነበር። ከብዙ ንባብ በኋላ ያገኘሁት እውነት የሚያሳየው ወልቃይት አገዎችም ኖሩበት ፈላሾችም ኖሩበት፣ አማሮች የሚተዳደረው በስሜን ክፍል ነበር (ሰሜን ሳይሆን ስሜን)። ይህም የዛሬው ጎንደር የጥንቱ የበጌምድርና ስሜን አንዱ ክፍል መሆኑ ነው። የሆነ ሆኖ እየዋለ እያደረ ወልቃይት የትግራይ ነው የሚለው የሕወሃታውያን መከራከሪያ በመጀመሪያ ሲሰማ ከነበረው ሕዝቡ ትግሪኛ ተናጋሪ ሕዝብ ነው ከሚለው መከራከሪያ ወጥቶ በታሪክ ወልቃይትን በትግሬ ግዛትነት አስተዳድረነው ነበር የሚል መከራከሪያ እየተጨመረበት ሲመጣ በታሪክ የትግሬ አስተዳዳሪዎች ተከዜን የተሻግረች “ትግራይ” ያስተዳደሩበትን ዘመን ፍለጋ ብሞክር ማስረጃ አላገኘሁም።

welkeit 768x597 1

 

ይልቁንም ወልቃይት ምናልባት አንድ የነበሩት የሰሜን እና መካከለኛ ኢትዮጵያ የግእዝ ተናጋሪ ማሕበረሰቦች ሁለት ሦስት የተለያዩ ቋንቋዎችን ተናጋሪ በሆኑበት ታሪካዊ ክሥተት አማርኛ ተናጋሪ ሕዝብ (የአማርኛ ቋንቋ) የተፈጠረበት ቦታ ሳይሆን አይቀርም የሚል አስተሳሰብ ሰረጸብኝ።  ይህንን ያሰኘኝ አንዱ ነገር ብዙ የወልቃይት አማሮች ስም አወጣጥን ስታዘብ፣ በሌላው የጎንደር የወሎና የሸዋ ክፍል እንኳን እየጠፋ የመጣውን የልጅና የአባት ስም  መግጠም (ዋና የአማራ ባሕል አሁን አሁን ጥቂትም ቢሆን በጎጃም ብቻ ቅሪቱ የሚገኝ) በወልቃይት በመታዘቤ ነው።  ሕወሃት አፍና ደብዛቸውን ያጠፋቻቸው የወልቃይት ሰዎች ስም ዝርዝር በከፊል የዛሬ 3 አመት ተለቅቆ ነበር። የትግሪኛና የክርስትና ስሞች አልፎ አልፎ ቢኖሩባቸውም ያለማጋነን ከሲሶ በላይ የሚሆኑት ሰዎች ስማቸው ይህ ነባር የአማራ ባሕል (የልጅና የአባት ስም መግጠም) በወልቃይት የጸና መሆኑን ያመለክታል። ቢጠና ጥሩ ነው። ትልቅ ወንዝ ወይም ሌላ የተፈጥሮ አጥር ደግሞ ቋንቋን የመለያየት ሚና እንዳለው የብዙ ቋንቋዎች አፈጣጠር ታሪክ ያስረዳናል። ስለዚህ ፊት አንድ የነበሩ ግእዝ ተናጋሪ ሕዝቦች በወንዙ በተከዜ ምክንያት ቋንቋቸው እየተለያየ መጥቶ ሊሆን ይችላል። በተለይም ወንዞች እንደዛሬ ባልኮሰሱበት በቀላሉ መሻገሪያ ድልድዮችም ባልነበሩበት በሩቁ ዘመን። ይህ ሰፊና ተጨማሪ ምርምር የሚያሻው ጉዳይ ሲሆን በአስተዳደር  ደረጃ የነበረው ታሪክ ግን አሁን ግልጽ እየሆነ መጥቷል።

334wወልቃይት ከሺ አመታት በላይ ባለው የኢትዮጵያ ታሪክ አንዴም በትግሬ ውስጥ ተካትታ እንደማታውቅ፣ ትግሬ የሚባለውም ግዛት ምጽዋና ከረን ድረስ የዘልቀበት ዘመን ቢኖርም በምእራብ ግን ተከዜን አልፎ እንደማያውቅ በዝርዝር ማስረጃ አቻምየለህ ታምሩ ማስረዳት ከጀመረ ወዲህ እነዚህን መከራከሪያዎች ይዤ የትግራይ ተወላጅ ወዳጆቼን መሞገት ቀጠልሁ። በነገራችን ላይ እነዚህ የአቻምየለህ ማስረጃዎች አሁን ተወዳዳሪ በሌለው መልኩ በመጽሐፍ ታትመው ለአንባቢ ቀርበዋል። 1600 አመታትን የዳሰሱ ከ700 የማያንሱ መረጃዎችን ያካተተ ድንቅ ሥራ ነውና ሁሉም የኢትዮጵያ ታሪክና ፖለቲካ ያገባኛል የሚል ሊያነበው ይገባል።

ወልቃይት ይገባናል ባይ ሕወሃታውያን ቀደም ሲል በነበሩት ክርክሮቻችን ለወልቃይት ትግሬነት ሕወሃት የምታቀርባቸውን ውሃ የማይቋጥሩ ቅጥፈቶች በመከራከሪያ ያቀርቡ ነበር። ከአቻምየለህ ማስረጃዎች በኋላ ግን ሁሉም ዝንባሌያቸውን ቀይረው በቃ በሱሪ ይዘነዋል። የቻለ በሱሪ ማስመለስ ነውየሚል ድርቅና ነበር የሚያሰሙት። በኢትዮጵያውያን መካከል የቀን ማጋደል ልዩነት እንጂ የሱሪ ልዩነት እንደሌለ እየታወቀ እንዲህ ዐይነቱ የትእቢት ቃል አሳዛኝ ነው።

ያንን ሕወሃታውያን የተኩራሩበት ሱሪ የጎንደር ወጣት በወልቃይት አስወልቋቸዋል። የዘመን ጉዳይ ሆኖ። ይሁን እንጂ የሱሪ ጉዳይ ብቻ ቢሆን ርስቱን አስመለሰ ተብሎ ያለቀ የደቀቀ ጉዳይ ይሆን ነበር። ነገር ግን ሕወሃት የተባለችው ዘንዶ ጨርሳ ብትወድቅ እንኳን እልፍ ዘንዶዎች ፈልፍላ ያደረች በመሆኑ እንደምናየው የወልቃይት ሰቆቃ የሚቀጥል እንጂ የሚያበቃ አይመስልም።

አንዳንድ ሰዎች “እኔ በግሌ ወልቃይት በትግራይ፣ ይሁን በአማራ አልፎም በደቡብ ክልል ስር ቢተዳደር ብዙም ግድ የለኝም” ይላሉ። ነገር ግን በብሄር ነጻነት ስም ሥልጣን ላይ የወጣ ወገን ወልቃይት ላይ የማንነት ጭፍለቃ፣ የርስት ቅሚያ እንዲሁም የአስተዳደር በደል ለማካሄድና ያደረበትን የአማራ ጠልነት ስሜት ለመበቀያ እንዲጠቀምበት መፍቀድ ሁሉም ሊታገለው የሚገባ የግፍ ጥግ ነው። ለብሔር ማንነት ነጻነት ታግያለሁ የሚለው የብሔርተኞች የትግል አሻራ የአማራ ማንነት ላይ ሲደርስ በጭፍለቃ የማለፉ ነገር የትግሉን እውነተኛ ዓላማ የከሠተ የታሪክ ጉድፍ ነው። ወይ ይሄንን አውዳሚ የብሔር ፖለቲካዊ ሥርዓት ማፍረስ፣ ያለ እሱ አንኖርም ካሉ ደግሞ ሁሉንም የማንነት ጥቅያቄዎች በፍትሕ ማስተናገድ።

የወልቃይት ግፍ እኔ እንዳየሁት በስሱ

ያየነውን  እንመሰክራለን። ካየነው ጥቂት ተነስተን ያላየነውን ግን የሰማነውን ብዙውን እውነትነቱን ለመገመት እንችላለን።

ሕወሃት ትግራይን በመገንጠል ጉዞ እየገሰገሰ መሆኑ ስላስደነገጠን የኤርትራው ታሪክ ሳይደገም፣ ታሪካዊ ቦታዎችንና በተለይም ታላላቅ ገዳማትን በመጎብኘት መንፈሳዊ በረከትም ለማግኘት ሰሜን ኢትዮጵያን ትግራይን ጭምር ጎብኝተን ነበር። ከጥቂት አመታት በፊት። የቤተሰብ አባላትና ጓደኞቻችን ሆነን። በራያ ገብተን ምሥራቅና ማእከላዊ ትግራይን ጎብኝተን በተከዜ በኩል ወደ ደባርቅ ተሻግረናል።  ትግራይ በፊት ከማውቃት የደኸየችና የቆረቆዘች (እንደዛሬው ጎጃም የመሰለች ) ሀገር እጅግ በጣም ተሻሽላ፣ አድጋ ሰዉም በአለባበሱና በቁመናው እጅግ የተሻለ ሆኖ ነበር የጠበቀኝ። እርግጥ በአንዳንድ ገበያዎች የድህነት ወለል ላይ ያለ ሕዝብም አስተውለናል። ቢሆንም ከሰቆጣና ሌሎች የአማራ አካባቢዎች ጋር የሚወዳደር ከቶውንም በዚያ ደረጃ የከፋ አልነበረም።  ትምህርት ቤት እና ክሊኒክ በየገጠሩ ተከፍቷል። የደን ሽፋን እጅግ ተስፋፍቷል። በዚህ በደን መስፋፋት ነገር በጣም እገረም ስለነበር ሹፌራችንን ጠየቅሁት። ምክንያቱም በልጅነቴ የማውቀው የትግራይ ገበሬ ብዙ ጊዜ መጥረቢያ ይዞ (ለማንኛውም በእግረ መንገዱ የሚቆረጥ ዛፍ ከተገኘ ለመቁረጥ) መጓዝ የሚያዘወትር ነበርና።

ሹፌሩም በትግራይ ከወያኔ ወዲህ ዛፍ መቁረጥ ሰው እንደመግደል መታየቱን ነገረን። ከጥቂት ቀናት በኋላ የታሪካዊውን ምእራብ ትግራይ ተከዜ ላይ ተሰናብተን ወያኔ ምእራብ ትግራይ እያለ ወደተስፋፋበት የጎንደር ክፍል ገባን።  ቆላማ በሆነው በዚህ አካባቢ ሶስት ታዳጊ ሴቶች በእግር ሲጓዙ አገኘንና አነጋገርናቸው። ሀገሩ ገደላማ መንገዱ ደግሞ ጠመዝማዛ ነበር።

ሰላም ልጆች ወዴት እየሄዳችሁ ነው። አልመሸም? አልናቸው። ከትምህርት ቤት እየተመለሱ እንደነበር ነገሩን። እንዴ የእህል ከረጢት እያመላለሳችሁ ነው የምትማሩት? ስንላቸው። ጠዋት እህል ተሸክመው እንዲሸጡላቸው ለዘመድ አድርሰው በዚያው ወደ ትምህርት ቤት እንደሄዱና አሁን ያልተሸጠውን ተቀብለው ወደቤት እየተመለሱ መሆኑን ነገሩን። መኪናው ውስጥ ተጠጋግተን ጥቂት መንገድ እንድንገፋቸው ብንለምናቸውም እምቢ አሉ። የት ነው ቤታችሁ? ስንላቸው በእጅ ያመለከቱን መንደር ርቀት በጣም ነበር ያስደነገጠን። ለምን እምቢ እንዳሉን ስንጠይቃቸው በመኪናው መንገድ ብዙ ብንጓዝም አስፓልቱ ከመንደራቸው ያለው ርቀት እንደማይቀንስ አስረዱን። እንዲሁ ሰአት ማባከን ነው የሚሆነው፣ ከዚህ ጥቂት ከፍ ብለን ሰብረን በእግር መንገድ ነው የምንጓዘው አሉን። በግምት ከዚህ በኋላ ስንት ጊዜ ይወስድባችኋል? ብለናቸው ሁለት ሰአት ያህል ተጉዘናል፣ ከአንድ ሰአት የበለጠ አይወስድብንም አሉ። አብረውን የነበሩት የቤተሰብ ልጆች በድንጋጤ ክው ነበር ያሉት። በቀን ስድስት ሰአት ጉዞ ለትምህርት! አስተዳደር ተከዜን ቢሻገርም ፍቅርና ፍትሕ አብረውት አልተሻገሩም።

ልጆቹን አለፍ እንዳልን ተራራው በየቦታው እሳት ተለቆበት ቆረቆር የሚባል የራስ በሽታ ጸጉሩን ቡጭቅጭቅ ያደረገበት ሕጻን ልጅ ይመስላል። በጣም ደንግጠን ሾፌራችንን

ከባድ የቋያ እሳት አደጋ ተከሥቷል፤ መንገዳችን አያሰጋም ወይ? ስንለው

ይሄማ ሆን ብሎ የሚነድ እሳት ነው አለን።

እንዴት? ስንለው

ለከሰል አለ።

ይሄስ አካባቢ በትግራይ ሥር አይደለም ወይ? አሉት ከልጆቹ አንዳቸው።

አዎ።

ታድያ ዛፍ መቁረጥ በሚከለከልበት ጭራሽ በቋያ እሳት ደኑን እያነደዱ ማክሰል ከባድ ወንጀል አይሆንም?

ይሄ ታሪካዊ ይዞታው የጎንደር የሆነ ቦታ ነው። እንደምታዩት መንገዱ ዳር ዳር የተኮለኮለው ከሰል ወደ ሽሬ ባለው በኩል እንጂ ወደ ጎንደር ባለው መንገድ በኩል አይደለም። ለትግራይ የማገዶ ፍጆታ እንዲወድም የተፈረደበት ደን ነው ማለት ነው። አለን። አይ ድንቁርና! በሰሃራ በረሃና በትግራይ መሃከል ያለው የደን ሽፋን ሲጋለጥ ትግራይ ውስጥ በመከራ የሚያሳድጉት ደንም አደጋ እንደሚገጥመው አልተረዱም? ብለን አዘንን።

እንግዲህ ሰዉንም አገሩንም በሁለት አይነት በተከፈለ አፓርታይዳዊ ሥርዓት የሚገዛ ወራሪ ብቻ ነው። ያልጨቆነው የሀገሩ ባለቤት ነገ ተንስቶ ርስትና መብቱን ይጠይቀኛል ብሎ በሰቀቀን ስለሚኖር።

ዛሬ በሱሪ ነጻ የወጣው ወልቃይት እጣ ምን እንደሚሆን በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። በድሮ ጊዜ መሳፍንት ወይም ንጉሦች ሲያምጹና ጦርነት ሲቀሰቅሱ ከጦርነቱ በኋላ ቢያንስ በቅጣት የተወሰኑ አውራጃዎች ወይም ግዛቶች ተቀንሰው ሌላ እንዲያስተዳድራቸው ይደረግ ነበር። በተለይም ተበደልሁ የሚል ስሞታ የቀረበ ሲኖር። ሰባተኛ ንጉሥ ነኝ እያሉ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ የሚያላግጡት 230 ምናምነኛው ንጉሠ ነገሥት ዐቢይ አህመድ ምን እንደሚወስኑ፣ ሕዝቡስ ምን እንደሚቀበል አብረን የምናየው ይሆናል።

ትግሉ ራያና ማይጨውን ሲያልፍ ደግሞ የዚያን ትዝብት በስሱ አካፍላችኋለሁ።

ሰላሙን ያውርድልን። ወያኔን እስከ ገጀራዋ (ሕገ መንግሥቷ) ይቅበርልን።

መጽናናትን ለማይካድራ ተጭፍጫፊ ንጹሐን ቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ወገኖቻችን እመኛለሁ።

 

ማሳሰቢያ

ሕወሃት ከዚህ በፊት በተናጠል ውጊያዎች እንጂ በጦርነት ተሸንፋ አታውቅም። ትልቁ ጥንካሬዋ ደግሞ መናቋ (ዝቅ ተደርጋ መገመቷ)፣ ምስጢራዊነቷ፣ ከፍተኛ ዝግጅቷ እና ድንገተኝነቷ ነው። ሕውሃት ተሐትን፣ ኢዲዩን፣ ኢህአፓን፣ ደርግን፣ ሻዕቢያን አሸንፋለች (ጉንጭ አልፋ የሽንፈት የምክንያት ድርደራው ውጤቱን አይለውጠውም)። ያንን የአሸናፊነት ታሪክ መሠረታዊ ምክንያቶች አለመመርመር ተጨማሪ ዋጋ ያስከፍላልና የምር ሕወሃትን እደመስሳለሁ ብሎ የተነሳ ካለ በጥልቅ እንዲያስብና እንዲዘጋጅበት ለማሳሰብ እወዳለሁ።

በተጨማሪ ልብ ሊባል የሚገባ ጉዳይም አለ። ሕወሃት በመጀመሪያ ያሸነፈችው የትግራይን ሕዝብ ነው። የትግራይን ሥነ ልቡና አንበርክካለች።  በጭራቅ ተረቶች፣ በከረሜላ እና በአለንጋ። ያንንም በጥልቀት ማወቅ ያስፈልጋል። ምናልባትም ጠ/ሚ ሰሞኑን “ምዕራብ ትግራይ” የሚሉት አገላለጽ ይህንን ቀዳዳ በከፊል የመድፈን ስልታዊ አካሄድ ይሆን?

እሷም ምን ብልጣ ብልጥ ብትሆን፣ እኛም መተባበር አቅቶን እድሜ ልካችንን ምን በእንከፎች ብንመራ፣ ከደደቢት ጀምሮ ያለመታከት ያፈሰሰችው የንጹሐን ደም ሕዋሃትን ጠርቷታልና፣ ጽዋዋ ከሞላ ውሎ ያደረ ነው። መጥፋቷ አይቀርም። አብራ እንዳታጠፋን፣ ይዛን እንዳትሞት ግን ከፍተኛ ብልሃት ይጠይቃል። የፈጣሪ እርዳታም እንዲሁ።

 

እግሩ ሥር አትቁሙ

የታረደው በሬ  የፈሰሰው ደሙ
ሊሞት ሲንጠራወዝ እግሩ ሥር አትቁሙ
በመጨረሻ ኃይል በጣረሞት አቅሙ
በኋሊት እርግጫ አመድ እንዳትቅሙ።

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.