በወቅታዊ ጉዳዮች ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የተሰጠ መግለጫ

Abnድርጅታችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ትህነግና ያደራጃቸው ፅንፈኛ የጥፋት ሀይሎች የሚፈፀሟቸውን የዘር ማጥፋት ወንጀሎች በተመለከተ መረጃዎችን ያሰባስባል፣ ያጠናቅራል እንድሁም ሪፖርቶችን እያዘጋጀ ያቀርባል።

አብን በማያቋርጥ ሽሽት ውስጥ ያለው የትህነግ ሰራዊት በማይካድራ ከተማ በንፁሀን በተለይም በአማራዎች ላይ በፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ዙሪያ ዝርዝር ማስረጃዎችን ከማሰባሰብ ጎን ለጎን የወንጀሉን አንድምታና ይዘት በተመለከተ ለአለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት፣ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ሚዲያዎች፣ ለኤምባሲዎችና ለድፕሎማቲክ ተቋማት ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል።

በማይካድራ ከተማ የፈፀመው ጅምላ ዘር ተኮር ጥቃት እየታወቀ መምጣቱን ተከትሎ የትህነግ ሀይል ራሱን ከተጠያቂነት ለማሸሽ ያስችሉኛል ያላቸውን የማድበስበስና መረጃ የማዛባት እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ቆይቷል።

በዚህ ረገድ በመጀመሪያ አካባቢ ጥቃቱን ያደረሱት የመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሀይልና ሚኒሻ እንደሆኑ አድርጎ ትህነግ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ለመስራት የሞከረ ቢሆንም በተለይ የጥቃቱ ሰለባዎች በዋናነት አማራዎች መሆናቸው ሲጋለጥ የማደናገሪያ ስልቱን በቅፅበት በመቀየር “ለመዋጋት ወደ ጦርነት የገቡ ሰዎች ናቸው” የሚል በሬ ወለደ ለማሰራጨት ሞክሯል።

በማይካድራ ከተማ የተጨፈጨፉት ወገኖች የከተማዋ ነባር ኗሪዎች መሆናቸው፣ ጥቃቱ የተፈፀመው በሽማግሌዎች፣ በእናቶችና በህፃናት ላይ ጭምር መሆኑና ጥቃቱ የተፈፀመው የመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሀይልና ሚኒሻ ከተማውን ከመቆጣጠራቸው በፊት መሆኑ፣ በዋናነት ጥቃቱ የተፈፀመው በገጀራ፣ በቢላ፣ በመጥረቢያና በስለት መሳሪያዎች መሆኑ የትህነግን ወንጀለኝነት በሁሉም ረገድ ያረጋገጡ ናቸው።

ይሄን ጉዳይ ከጠባቡ የህወሀትና የቅጥረኞቹ አለም ውጭ ያለው ሰፊው የአለም ማህበረሰብ ባግባቡ ተረድቶ ተቀብሎታል።

የህወሀት ሀይል በማይካድራ ከተማ የፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ከተጋለጠበት እለት ጀምሮ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እያጋለጡትና እያወገዙት ይገኛል። አለማቀፍ ታዋቂ የሚዲያ አካላትም በሰፊው እየዘገቡት ነው።

በርግጥ የትህነግ ቋሚ መርሆች ሴራ፣ ክህደት፣ ጥላቻና ውሸት መሆናቸው ይታወቃል።

ጦርነቱ የተከፈተው በትህነግ በኩል መሆኑ እየታወቀ በአማራ ሀይሎችና በመከላከያ ሰራዊት እንደሆነ ተደርጎ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ሲሰራጭ ቆይቷል።

ትህነግ በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ የተቀነባበረ ጥቃት ከመክፈቱ ባለፈ በአማራ ህዝብ ላይ በቅራቅር አካባቢ ጥቃት ከፍቶ ነበር። የዚህ ጥቃት አላማ የአማራን ህዝብ ለመጨፍጨፍና ኢትዬጵያን ለማፍረስ ነበር። በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ድነገተኛ ጥቃት ከፍቶ በመደምሰስ፣ ትጥቁን በመቀማት፣ በርካቶችን በግፍ ገድሎና ዩኒፎርማቸውን አስወልቆ ርቃናቸውን በትኗቸዋል። አስክሬኖችን በመርገጥ ሲጨፍሩ ቆይተው እንዳይቀበሩና በአሞራና በአውሬ እንዲበሉ አድርጓል።
ይህ የትህነግ የተሸከመውን አጠቃላይ ጥላቻ፣ ክህደትና ፍርሀት ፍንትው አድርጎ አሳይቷል።

ያልተሳካው የትህነግ ቀጣይ አላማ በቀናት ውስጥ በቅራቅር በኩል ወደ መሀል ጎንደር በመግባት የተለያዩ የአማራ ከተሞችና አካባቢዎች ላይ መጠነሰፊ ጥቃቶችን ለመክፈት ነበር።

ሀ/ ትህነግ በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በመክፈት ጦርነቱን እንደጀመረ በይፋ አምኗል።

ለ/ በትላንትናው እለት በአማራ ከተሞች ላይ ተወንጫፊ ሮኬቶችን በመተኮስ በሲቪልና የማህበረሰብ የልማት አውታሮች ላይ ጉዳት አድርሷል። በጦርነቱ ውስጥ ያልተሳተፉ ንፁሀን ግለሰቦችን በማጥቃት ገድሏል።

በትናንትናው እለት ከምሽቱ 5 :00 አካባቢ ትህነግ ባስወነጨፈው ሮኬት በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ በዉራባ ቀበሌ ጣብላ በሚባለው ልዩ ቦታ ኗሪ የነበሩትን ገቢያነሽ ዘዉዱ(እናት)፣ ባንቺ እሸቴ- (ልጅ)፣ ተሾመ እሸቴ፣ ማስተዋል እሸቴና ባዜ እሸቴ የሚባሉትን የአማራ ንፁሀን ገበሬዎችን ህይወት ማጥፋቱ ተረጋግጧል።

ይህ ድርጊት የትህነግ ስምሪት አማራ ጠል መሆኑን ገሀድ ያወጣ ሲሆን ጦርነት ተከፈተብኝ በሚል ያስተጋባው ፕሮፖጋንዳ ሀሰት መሆኑን አጋልጧል።

መግደል የትህነግ ሞኖፖል መሆኑ ካቆመበት እለት ጀምሮ አጠቃላይ የትህነግ መጥፋት በቅርብ ርቀት መሆኑን ሲገነዘብ ከመጨረሻ ሞቱ በፊት የንፁሀን አማራዎችን ህይወት አብሮ ማጥፋት አላማ እንዳደረገ መገንዘብ ይቻላል።

በተለይ በጦር ግንባሮቹ ተሸንፎ የተበተነው የትህነግ ሰራዊት ቀድሞ ካሰማራቸውና ካስታጠቃቸው ኢመደበኛ የጥፋት ሀይሎች ጋር ተቀላቅሎ በመመሸግ የመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሀይልና ሚኒሻን ከጀርባ ለማጥቃት እየተንቀሳቀሰ ከመሆኑም በላይ በንፁሀን አማራዎች ላይ ግድያዎችን እያቀነባበረ ይገኛል።

ትህነግ ቦታዎቹን ለቅቆ ሲሸሽ በርካታ አማራዎችን በተለይም ታዋቂ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ ነጋደዎችንና ኢንቬስተሮችን አግቶ መሰወሩ ተረጋግጧል።

በዚህ ረገድ:-

1/ ህወሀትን እንደድርጅት የሚዘውሩት ጥቂት ግለሰቦች ቢሆኑም በዘረኝነትና በጥላቻ የታወሩ በርካታ ሲቪልና ሚሊታሪ አመራሮችና አባላቶች ያሉት መሆኑን፤

2/ ህወሀት በጦር ግንባሮች እየተሸነፈና እየሸሸ ቢሆንም በርካታ ታማኝ ባለሟሎቹን በሰርጎ ገብነት ማሰማራቱን፤

3/ በተለይም በጦርነት ተሸንፎ በለቀቃቸው አካባቢዎች ከሸሸው ሀይል የማይተናነስ አደገኛ ሀይል ከኋላና ከጀርባ የቀረ መሆኑን፣

4/ ከጀርባ የቀረው ሀይል ከትህነግ ጋር በጥቅም የተሳሰረ፣ በጥቅምና ጥላቻ መስፈርት የተመለመለ መሆኑን፣

5/ ከጀርባ የቀረው ሀይል በሰፊው የታጠቀ መሆኑና የግለሰብ ግድያዎችን ጨምሮ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ውስጥ በቀጥታ መሳተፉን፣

6/ እነዚህ በትህነግ የሰፈራ ፕሮግራም በየከተሞቹ ውስጥ የተነጠለ አሰፋፈር ያላቸውና ለበርካታ ንፁሀን ዜጎች አፈናና ስቃይ፣ ለግድያና መሰወር፣ ለህገወጥ የሰዎች፣የጦር መሳሪያዎች፣ የገንዘብና የእፅ ዝውውሮች አመች ተደርገው በካምፕ መልክ የተዘጋጁ ቀጣናዎች መሆናቸውን፤

7/ ወደፊት አልፈው እየገሰገሱ ያሉትን የመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሀይልና ሚኒሻ ከጀርባ ለማጥቃት ፍቃደኛና ዝግጁ መሆናቸውን ባግባቡ በመገንዘብ እየፈፀማቸው ያሉትንና ለመፈፀም ያቀዳቸውን ጥቃቶች በዘላቂነት ማክሸፍ ያስፈልጋል።

በመሆኑም በመንግስት በኩል ትህነግ ያሰማራውን መደበኛ ተዋጊ ሀይል ከማሸነፍ፣ እንዲሸሽ ከማድረግና በህግ የበላይነት ማእቀፍ ስር ከማዋል ጎን ለጎን ሰርጎ ገቦችንና የታጠቁ ኢመደበኛ ሀይሎችን በፍጥነት በቁጥጥር ስር በማዋል የታጠቋቸውን መሳሪያዎች በማስወረድ ህግ ለማስከበር እየተንቀሳቀሰ ያለውን የመንግስት ሀይል ከጥቃት መከላከልና በንፁሀን ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችንና አጠቃላይ የደህንነት ስጋቶች መቅረፍ ይገባል።
በሽሽት ላይ ያለው የወንበደ ሀይል አፍኖ የሰወራቸውን ንፁሀኖች ለማስጣል ርብርብ ማድረግም ይገባል።

በተለይ ገና በትህነግ ያልተለቀቁና በስሩ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ንፁሀን ኢትዬጵያውያንን በተለይም ተጨባጭ የዘር ማጥፋት ያንዣበባቸው አማራዎችን ለመታደግ መንግስት ታሪካዊ ሀላፊነቱን እንዲወጣ ለማሳሰብ እንወዳለን።

በሌላ በኩል በቤኒሻንጉል ክልል ውስጥ ድባጤ በሚባለው አካባቢ አማራጠል ፅንፈኛ ሀይሎች በስፍራው ሲጓዝ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ መኪና ላይ ጥቃት በመክፈት በተሳፋሪዎቹ ላይ ዘግናኝ ግድያዎችን መፈፀማቸው ታውቋል።

የፅንፈኞች ስንቅ አቀባይ የሆነው ትህነግ እየተደመሰሰና በህግ ጥላ ስር እየወደቀ ባለበት ወቅት የቅጥረኞቹ መወራጨት በሀይል አሰላለፍ ረገድ አንዳችለውጥ እንደማያስከትልና የህግ ማስከበሩ ሂደት በነሱም ላይ የሚቀጥል መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል።

በዋናነት የቤኒሻንጉል ክልላዊ መንግስት ችግሩን የመፍታት ሀላፊነት እንዳለበት ሊገነዘብ ይገባል።

የአማራ ህዝብ ሀገራችንን ለማፍረስ ዝግጅቱን አሰናድቶ ጦርነት የከፈተውን የትህነግ ሀይል በመግጠም እየተዋደቀ ባለበት በአሁኑ ጊዜ በየስርቻው የተወሸቁ አልባሌ ፅንፈኞች ጉዳት እንዲያደርሱበት ሊፈቀድ አይገባም።

የፌዴራል መንግስት፣ የቤኒሻንጉል ክልላዊ መንግስትና የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በቤኒሻንጉል ክልል ውስጥ በአማራ ህዝብ ላይ የተከፈተውን ያልተቋረጠ ዘር ተኮር ጥቃት በዘላቂነት ለማስቆም አስቸኳይ የሆኑ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አስቀምጠው ተግባራዊ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን። በፅንፈኛ ሀይሎች በተደጋጋሚ በተከፈቱ ዘር ተኮር ጥቃቶች የደረሱትን ጉዳቶች በማጣራት ጥፋተኞችን በዘር ማጥፋት ወንጀል ማእቀፍ ስር ተጠያቂ ማድረግ ይገባል።

አጠቃላይ የትህነግን በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወድህ ያለውን ስምሪት ስንመረምር ግልፅ የሆነ ሀገር በቀል የሽብር ድርጅት መሆኑን እንረዳለን። በርግጥ አሁን ትህነግ ከአለማቀፍ የሽብር ድርጅቶች ጋር በከፍተኛ ቅንጅት እንደሚሰራም ይታወቃል። ቤኒበሻንጉልና ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ካሉ ፅንፈኛ ሀይሎች በተጨማሪ አልሸባብና አይ ኤስ አይ ኤስ ጋር ጭምር በትብብር እየሰራ ስለመሆኑ ማስረጃዎች እየወጡበት ይገኛል።

አብን ድህረ ትህነግ የኢትዬጵያ የፖለቲካ ብሩህ እንደሚሆንና ለረጅም ዘመን መንበሩን ተቆናጥጦ የቆየውን የጥላቻ ድባብ በመግፈፍና በምትኩ ፍቅር፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣ዴሞክራሲና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ለሚንቀሳቀሱ በጎ ጥምረቶች መንገድ እንደሚጠርግ ይገነዘባል።

1 Comment

  1. የትህነግን ህጢያት መዘርዘሩን ጋብ አርጋችሁ ነገ ስጋት እንዳይሆን ትህነግ ትናንት እነ ግንቦት ሰባት አሸባሪ ተብለው እንደተፈረጁ ሁሉ ይህን ግፈኛ ድርጅት በአሸባሪነት ፈርጆ እንዲፈርስ ማደረግ ተቀዳሚ ስራችሁ ሊሆን ይገባል። እላይ ያሉት የጅንታው ማእከል / Top leadership /መውደም፣ የጅንታው ሀሳብ ወደቀ ማለት አይደለም፣ ከታች የአፈሩዋቸው ” ጎጃም ከሚለማ፣ሲናይ በረሀ ቢለማ እመርጣለሁ ” የሚሉ ደቀ መዝሙራን እንዳሉአቸው ለአፍታም ችላ ልትለት አይገባም። ወያኔ እነ መንግስቱን እና አመራሩን አውርዶ ኢሰፓን ባያፈርስ የዚህን ያህል እድማ ይኖረው ነበር ???
    ጊዜው ለአማራው መልካም አጋጣሚም ወይ ስጋት የሚሆንበት መስቀለኛ መንገድ ላይ በመሆነ ማስተዋልን እና አማተር ሳይሆን ፕሮ ፌሽናል ፓለቲክኛነትን ይጠይቃል። ወያኔ ለስልጣን የበቃው አባላቱ የሙሉ ጊዜ ፓለተከኛ እና ጠንካራ ድርጅት መፍጠር በመቻላቸው ነው።
    ሌላው ማየት ያለባችሁ ብቻችሁን ብዘም ልትራመዱ አትችሉም፣ ህብረት፣ ግንባር፣umbrella…etc ለመፍጥጠር ሞክሩ ፣ኢዜማ፣ አብሮነት፣ብልጽግና፣ የቀድሞ ወታደሮች ማህበር፣ የምሁራንማህበር……ወዘተርፈ under the umbrella of Ethiopian Sovereign ity and territorial integrity.
    የወያኔ ሰንኮፍ ያለው በህገ መንግስቱ ስለሆነ በቁዋሚነትም ይሁን በጊዚያዊነት እን ዲቀየር መታገል የግድ ነው።
    God bless Ethiopia !

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.