እጅግ አስደንጋጭና ልብ ሰባሪ ሰበር ዜና! – አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ)

“ካለበት የተጋባበት” ነው ነገሩ፡፡ ዜናን ለማጋነን ወይም የፈጠራ ዜናን በግነት አስውቦ ለማቅረብ እኔስ ከማን አንሳለሁ?

ወያኔ በዚያ በተረገመ ግንቦት 20/83 ሀገራችንን እንደተቆጣጠረች ለተወሰኑ ዓመታት አንጻራዊ የሚዲያ ነፃነት ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ታዲያ እንደአሸን የፈሉት የግል ጋዜጦች የአንባቢን ቀልብ ለመሳብና ገበያን ለመቆጣጠር በማሰብ የፊት ገፃቸውን በሚጮሁ ርዕሶች ያጭቁ ነበር፡፡ በሃቅ ይሠሩ የነበሩት የተወሰኑት ብቻ ነበሩ፡፡ ለምሣሌ እኔ እሠራበት የነበረው እንትና የሚባል የግል ፕረስ፡፡

“ጎንደር በተኩስ ስትናጥ አደረች!” ይልህና በጉጉት ወደ ውስጥ ገብተህ ስታነብ በአንድ ቡና ቤት ውስጥ በተነሣ አነስተኛ ግጭት አንድ ሰው ቆስሎ፣ አሥር የቢሮ ጠርሙስና አምስት ብርጭቆዎች እንደተሰበሩ ልታነብ ትችላለህ፡፡ ጎዳናው፣ ገናናው፣ መብረቅ፣ ሠይፈ ነበልባል፣ …. በሚሉ ስያሜዎች ሣምንቱን ሙሉ ሕዝብን ያወናብዱ የነበሩ ጋዜጦች ዜናን በማጮህ ወደር አልነበራቸውም፡፡

ወያኔ በጫካ ሳለችም እንዲሁ ነበረች፡፡ ሴኩቱሬና ሐመልማል የሚባሉ የወያኔ በቀቀኖች “ጀግናው የኢሕአዲግ ሠራዊት በወሰደው መብረቃዊ የማጥቃት እርምጃ በዛሬው ዕለት ብቻ ከ50 ሽህ በላይ የደረግ ሠራዊት ሙትና ቁስለኛ ሲሆን ከ25 ሽህ በላይ ወታደሮች ደግሞ ከነሙሉ ትጥቃቸው ተማርከዋል” ይሉህና በነሱ በኩል ደግሞ “በዛሬው ቀን በተደረገው ጦርነት የደርግ የጦር ጀቶች በጣሏቸው ቦምቦች ሦስት አህዮችና ሁለት ዶሮዎች ከነጫጩቶቻቸው መስዋዕት ሆነዋል፡፡ ይሁንና ይህን የአየር ጦርነት ሲያካሂዱ የነበሩት አሥራ አምስቱም ጀቶች በጀግናው የአየር መቃወሚያ ክፍላችን ተመትተው  የዶጋመድ ሆነዋለደ” ትባላለህ፡፡ አንተ ያለብህ ማድመጥ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያሏትን ጀቶች በሙሉ ወያኔ በሦስት ቀናት ተከታታይ ዜናዎቿ ከአየር በሚሳይል አፈንድታ ልትጥላቸው ትችላለች፡፡ ውሸታም ደግሞ መዋሸቱን እንጂ እውነታዎችን የማገናዘብ ፍላጎትም ሆነ ችሎታ የለውም፡፡ ወያኔ የውሸት መምህር ብትሆን በዓለም የሚስተካከላት የለም፡፡ ታማኝ በየነ አንድ ወቅት ወያኔዎች ገደልን ያሉትን የኢትዮጵያ ሕዝብ ደምሮ 52 ሚሊዮን እንደደረሰና ከወቅቱ የሀገራችን አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር በ2 ሚሊዮን መብለጡን በመግለጽ ሁለት ሚሊዮኑን ከወደፊቱ ትውልድ ተበድረው እንደገደሉ መድረክ ላይ ቀልዶባቸው ነበር፡፡ ታማኝ እንዳለውም ባለፉት 30 ዓመታት 2 ሚሊዮን ብቻ ሣይሆን 20 ሚሊዮንም የማይጠቅመው ሕዝብ ከኢትዮጵያ ሕዝብ በግድያና በመሳሰለው ከሕይወት ወደ ሞት ተለውጧል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ቻይናን አርሂቡ እንበላት - በስንታየሁ ግርማ

በነገራችን ላይ በዘመናችን የተከሰቱ ዩቲዩበሮችም አድማጭን ለመማረክ የሚያደርጉት ነገር በጣም አሳዛኝ እየሆነ ከመምጣቱ የተነሣ ብዙዎቹን የሚከታተላቸው እየጠፋ ነው፡፡ ርዕሳቸውና ዝግጅታቸው የማይገናኝ ብዙ የዩቲዩብ ሚዲያዎች መኖራቸው በታሳቢነት ተይዞ የርዕሱ ግነትና የውስጥ ይዘቱ ቀደም ሲል የጠቀስኩትን የወያኔ ዘመን ጋዜጦች የሚያስታውስ ነው፡፡ ሳይበላስ ቢቀር!

ዛሬ ደግሞ የወያኔው ደብረ ፅዮን ከአሥር ሽዎች በላይ ወታደሮችን ከኤርትራና ከኢትዮጵያ መከላከያ መማረካቸውንና በ“ትግራይ ሪፓብሊክ ጦር ሠራዊት” እጅ መግባታቸውን በኩራት ሲገልጽ ሰማን፡፡ ማንን እንደምናምን አስቸጋሪ ቢሆንም ወያኔ ባላት “ትራክ ሪከርድ” መሠረት ያላት የታማኝነት ደረጃ ከዜሮ በታች በመሆኑ ይህንን ዜና ገልብጠን ምናልባት በሽዎች የሚገመቱ የጦር ሠራዊት አባሎቿ በመከላከያ ተይዘውባት ሊሆን እንደሚችል ብንጠረጥር ብዙም አንኮነንም፡፡

መጨረሻውን አይቼ፡፡ “የቡዳዎቹ መንደር የትኛው ነው” ብሎ መንታ መንገድ ላይ ያገኘውን ሰው አንድ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው መንገደኛ ቢጠይቀው – ያ ተጠያቂ በቡዳነት ከሚታማው መንደር ነዋሪዎች አንዱ ኖሮ ለካንስ – “እነሱም እኛን ይላሉ፤ እኛም እነሱን እንላለን” በማለት መንገደኛው በራሱ ውሳኔ መርጦ በአንደኛው እንዲሄድ በሾርኒ ጠቁሞታል፡፡

ውሸት ከሀገራችን እንዲጠፋ እንጸልይ፤ ምቀኝነትና መናናቅ ከኢትዮጵያ እንዲጠፉ አንድዬን እንማጠን፤ ዘረኝነትና ማይምነት፣ ድንቁርናና ሆዳምነት፣ አድርባይነትና መሀል ሰፋሪነት ከሀገራችን እንዲጠፉ ምህላ እናድርግ፤ እውነተኛ ሙሤ እንዲላክልን ወደላይ አንጋጠን አቤት እንበል፡፡ የመከራው ዘመን እንዲያጥርልንና ወርቃማው ዘመን በቶሎ እንዲብትልን ሁላችንም በየእምነታችን እንጸልይ፡፡ ከአሜን ብቻ ሣይሆን ካለመጸለይም ይቀራልና በዚህ አንዘናጋ፡፡

ለነገሩ እግዚአብሔር ጓዙን ጠቅልሎ አሁን የሚገኘው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ እግዚአብሔርን የማያምን ምድረ “ኤቲይስት” ሁላ አሁንና ዛሬ የፈጣሪን መኖር ካላመነ መቼም አያምንም፡፡ 45 ዓመት ሙሉ ሕዝብ ላይ የተጸዳዳ ሕወሓት የሚባል ሽፍታ በስማም እንደተባለበት ሰይጣን በሰዓታት ውስጥ ወልቃይትን የመሰለ የደምና የዕንባ ምድር ለቅቆ መውጣት ማለት የእግዜር ፍርድ እንጂ የጀግንነትና የወኔ ጉዳይ አይደለም፡፡ “ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር” የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ገና መፈጠራቸውን ይረግማሉ፤ ገና “ለምን ወያኔ አድርገህ ፈጠርከኝ!” ብለው ፈጣሪያቸውን አምርው ይወቅሳሉ፡፡ ገና ገና ገና … ምን አየንና፡፡ “ለለአሃዱ በበምግባሩ” እንዲል መጽሐፉ፡፡ “ነገር ቢበዛ በአህያ አይጫንም” ይላል ያገሬ ሰው፡፡ ቀሪውን አንተው ጨማምርበት፡፡….

ተጨማሪ ያንብቡ:  "ኢሕአዴግን ጥለን እኛ እዚህ የምንቧቀስ ከሆነ ኢሕአዴግ ባይወድቅ ደስ ይለኛል" - ግርማ ሰይፉ (የፓርላማው አባል)

martyrof2011@gmail.com

2 Comments

  1. አምባቸዉ እነሱ ለቀዉ ቢወጡም አብይ ለወንጀላቸዉ ካሳ የተመለሱትን የአማራ መሬት ሊሰጣቸዉ ዳር ዳር ይላል። እስከ ዛሬ ለተጸዳዱበት በቂ ሁኖ በዚያ አካባቢ ያለ ወገን ከዚህ የሚብስበት ነገር ስለሌለ በደሙ ያስመለሰዉን መሬት የኢትዮጵያን ባንዲራ ገጥግጦ ተክሎ ላንዴና ለመጨረሻ የነገዱን ጭፍጨፋ አስቁሞ ላገሩ አጥር እንዲሆን እናሳስባለን።

    የአብይ የተንኮል አካሄድ ጤና አይመስልም ሰዉዬዉ የልብ ቅንንት የለዉም እነ አረጋዊ በርሄን፤ ሌንጮ ለታን፤ አቡ በከርን መሰለኝ አስመላሺ ኮሚቴ ዉስጥ የደነቀረዉ። አሁን ኢትዮጵያን መናቅ ካልሆነ አረጋዊ በርሄ አሁን የያዘዉ ሹመት ይገባዋል? ከህወአት አባላት ጋር ሁኖ ጦር ፍርድ ቤት መቅረብ ሲገባዉ እሱን መሾም ምን ማለት ነዉ? በሱ ቤት የትግሬን ልብ የገዛ መስሎታል እነሱም ይስቁበታል አረጋዊም ይስቅበታል።

  2. BBC.com › news-48957925
    “አገሪቷ አሁን ለምትገኝበት የፖለቲካ ብልሽት ህወሓት ተጠያቂ ነው” አዴፓ – BBC News አማርኛ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share