” በጫርከው እሳት ትቃጠልበታለህ ። በቆፈርከው የተንኳል ጉድጓድም  ራሥህ  ትገባበታለህ ። ” መኮንን  ሻውል  ወልደጊዮርጊስ

ኢትዮጵያዊነትን ለመገንባት እና ዳር ድንበሯን ላለማሥደፈር ፣ከወራሪዎች ፣ከዘራፊዎች ፣ከሽፍቶች ፣ከወንበዴዎች እንዲሁም ከተንኮለኞችና ከእሣት ጫሪዎች ጋር ፣ አባቶቻችን ፣ፍፁም በማይመች ሁኔታ ፣ በባዶ እግራቸው ፣ በእራፊ ጨርቅ፣ከርሃብ ና ከውሃ ጥም ብቻ ሳይሆን ከተፈጥሮ ጋራ እየታገሉ ዕድሜ ልካቸውን ያለፋታ ተፋልመው ፣በደምና በአጥንታቸው ይህቺን ውብ አገር በክብር አቆይተውልናል። ለራሳቸው ሳይሆን ለሀገር ብልፅግና ፣ክብር እና  ለኢትዮጵያዊነት ከፍታ ሲሉም ፣በበረሃው፣በዱር በገደሉ  የቀሩ ፣ ዛሬም  እሥከቅርብ ጋዜ ድረሥ እየተሰው ያሉ ፣ነገም ለመሰዋትነት የተዘጋጁ የኢትዮጵያ ጀግኖች ክብር ይገባቸዋል።

125025105 1432883130237610 178304440615977363 n

እነዚህ የኢትዮጵያ ማህፀን ያፈራቻቸው ፣በታሪክ ውሥጥም በተደጋጋሚ የተዘመረላቸው እና ገና የሚዘመርላቸው ቆራጥ፣ አርቆ አሥተዋይ፣ “አገሬን አትንኩ !” ፣ባይ ፣የጀግኖች ጀግና የሆኑ   ውድ አሌንታ ና ኩራቶቻችን፣ የማር እና ወተት፣የአልማዝ ና እንቁ  ባለቤት የሆነችውን  እናት አገራቸውን ለመዝረፍ የመጣውን የውጪ ጠላት ያለማቅማማት ፣ በፍፁም ፍቃድ ና ቃላት ሊገልፀው በማይችለው ጀግንነት ሲፋለሙ ደማቸው ከእናት አገር መሬት ጋር ተቀላቅሎ በክብር አርፈዋል። አጥንታቸውም በመላ ኢትዮጵያ ጠረፍ ከጥር ሆኗል።

ለምንድነው የትላንትኖቹ ምንጅላቶቻችን በመላው አገራችን ዳርድንበሮች ደማቸውን ያፈሰሱት?ለምንድነው፣ቅድም አያቶቻችን፣ አያቶቻችን፣ አባቶቻችን ትላንትና  ለዚች አገር ሥም ዘላለማዊነት ና ለሉአላዊነቷ  መከበር ፣  ያለሥሥት ህይወታቸውን የገበሩት? ይህ ትውልድ በባርነት እንዳይኖር፣ ፍፁም ሳያፍር የበታችነት ሥሜት ሳይሰማው፣ከቶም  ሳይሸማቀቅ አንገቱን ቀና አድርጎ ፣ደረቱን ነፍቶ በዓለም ህዝብ ፊት  በኩራት እንዲራመድ አይደለምን?

በሥራ አጋጣሚ እና በጉብኝት አገሬን እንደቃኘኋት እና ከአገር አሳሾች ታሪክም እንደተረዳሁት ፣  ይህቺ አገር በማር እና በወተት ፣በበዙ የተለያዩ አዝርቶች የተሞላች ካብታም አገር በመሆኗ ለባእዳን ምራቅ የምታሥውጥ አገር ናት።በልዩ፣ልዩ የቤት ና የዱር  እንሥሣት፣እዋፋት ና የዱር አራዊትም ደን እና ዱሩ የተሞላ ተፈጥሮ የታደለች  ናት።  ያልተነካው የከርሰ ምድር  ሐብቷ  ለበለፀጉት አገሮች በሣተላይት ሲታይ ለኃጭ የሚያዝረበርብ ሆኖ አግኝተውታል። በወንዝ፣በኃይቅ፣አና በምንጮችም እጅግ በመባረኳ በበረሃ ውሥጥ የሚኖሩ አገራት በእጅጉ ይቀኑባታል።ይህቺ እናት ምድራችን ኢትዮጵያ፣ በተፈጥሮ የበለፀገች፣ የሰው እግር ባልነካቸው ለም መሬቶችና የተፈጥሮ ደኖች የተሞላች ውብ ምድር  ናት።ለዚህ እውነት ሲሉ ነው አባቶቻችን ትላንት ለሀገራቸው ያለሥሥት ግንባራቸውን ለጥይት ደረታቸውን ለጦር በመሥጠት በጀግንነት ኢትዮጵያን ሲጠብቁ የኖሩት።…

ዛሬ ግን ሲፈጠሩ ፣ለፈጠሯቸው የኢትዮጵያ ጠላቶች  በገቡት ቃል መሠረት፣  ከታላላቅ ጀግኖቻችንን መካከል ሥመጥር የሆኑትን ፣ የዓፄ ዮሐንሥን እና የአሉላን መሠዋትነት በመናቅ፣ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ፣ሥውር ምኞት አሳኪ ና አመቻማች  በመሆን ፣ወደ እርሥ በእርሥ ጦርነት አገሪቱ እንድትገባ ና እነዛ ታሪካዊ ጠላቶቻቸው በሚፈልጉት ና፣ባቀዱልን የመበታተን አደጋ ውሥጥ እንድንዘፈቅ በማድረግ፣  ለብዝበዛ እንድንመቻች ግልፅ ጦርነት በመክፈት ኢትዮጵያን ወግተዋታል።

ኢትዮጵያን ወግተዋታል ሥንል፣አጠቃላይ የአገሪቱን ዜጎች ወግተዋል ማለታችን ነው። ከታራክ እንደተገነዘብነው የአያሌ ጦርነቶች አውድማ የነበረችው ትግራይ ነበረች። በትግራይ ምድር ኢትዮጵያዊያን ለአገር ክብር ሲዋደቁ አያሌ ባንዶች ከትግራይ ምድር ተፈጥረው ኢትዮጵያን እንደወጉ የአድዋ ታሪክ ምሥክርነት ብቻ በቂ ነው።…

ዛሬም ይኸው የባንዳ ተልኮ እንዲቀጥል    ፣የትግራይን ክልል  ሥልጣን በመሣሪያ ወይም በወታደር ኃይል የተቆጣጠሩት ” ጁንታዎች” በአሳፋሪ እና በወራዳ መንገድ በአገራችን የመከላከያ ኃይል ላይ ሰይፍ መዘው ጥቃት አድርሰዋል።ከሬሳ ላይ ልብሥ ገፋዋል።መርኮኛን መለመላውን በማሥቀረት ኢሰባዊ በሆነ መንገድ አዋርደዋል።ይህንን ኢ ሰብአዋ ድርጊት የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅር አይለውም።እነዚህ አረመኔዎች የእጃቸውን ሲያገኙ ማየት የፈልጋል።

የእነዚህ የጀግኖች ኢትዮጵያዊያን መሥዋትነት ከንቱ ለማድረግ የሚጥሩት የዛሬዎቹ ” ያበዱ ጁንታዎች ” የእጃቸውን ማግኘት አለባቸው።እነዚህ ጥቂት ሆነው በእጃቸው ባለው ገንዘብ ፣ቅጥር ነፍሰ ገዳይ ቀጥረው አገርን የሚያተራምሱ ሴጣናት በህይወት እንዲኖሩ ሊፈቀድላቸው አይገባም።

ትላንት ሲፈጠሩ ፀረ ኢትዮጵያ ሆነው ነውና ዛሬም የሚያቀነቅኑት ይህንኑ በመሆኑ ከታሪክ መዝገብ ሙሉ ለሙሉ መፋቅ ይኖርባቸዋል።

እነዚህ እብዶች እኮ፣ ገና ከፍጥረታቸው “ነፃ አውጪ ድርጅት ነን። “ሲሉ፣እና ትግራይን ለመገንጠል ሲጥሩ ፀረ አንድነት አቋም እንዳላቸው አሥመሥክረዋል። ገና ከፍጥረታቸው ፀረ ኢትዮጵዮ ሆነው በመፈጠራቸው ፣ የተነሳ ከኢትዮጵያዊ አሥተሳሰብ በማፈንገጥ ፣ፍፁም ኢትዮጵያዊ አሥተሳሰብ የነበረውን ጥቂት የማይባለውን ትግሪኛ ተናጋሪ ምሁር በጠባብ ብሔርተኛ ሃሳብ ህሊናው እንዲበረዝ በማድረግ ሆዳም ፣ሥግብግብና ሆድ አደር አድርገውታል።

ይህንን የጎሳ ና የቋንቋ  ከፋፋይ አሥተሳሰብም በሌሎች ቋንቋ ተናጋሪ ምሁራን ጭንቅላት ውሥጥም ለመፍጠር ችለዋል። …

እርግጥ ነው፣ከዚህ እንደአውሬ ከሚያሥብ ምሁር በተቃራኒ የቆሙ ቁጥራቸው እጅግ ብዙ የሆነ ምሁራንን የትግራይ መሐፀን እንዳፈራች ይታወቃል። ዛሬም እነዚህን የበሉበትን ወጪት ሠባሪውች የሚገባቸውን ቅጣት ለመሥጠት ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብና ከመከላከያ ኃይላችን ጎን የተሠለፉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች አሉ።ዛሬም እንደ አሉላ አባነጋ አይነቶች እልፍ ትግራዊያን ኢትዮጵያችን እንዳላትም በዚህ የታሪክ አጋጣሚ ተረጋግጧል።

ይህ የቅጥረኞች  ጦርነት እንደሆነ የገባቸው የትግራይ ተወላጆች ከመከላከያ ጋር ሆነው በጀግንነት እየተዋጉ ነው።የኢትዮጵያ  ወታደር ጎሳ ና ቋንቋ እንደሌለው ይታወቃል። ” የጁንታው ቡድን”   ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች    በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈሪ በትር ሠንዘረው ፣በአሠቃቂ ፣በአሣፋሪ ና በሚያሥቆጭ ሁኔታ  የጀግኖቹን ህይወት ማጥፋታቸውም እጅግ አሣዝኗቸዋል።በቁጭትም ከመከላከያ ሠራዊት ጋራ እንዲሠለፉ አድርጓቸዋል።

ይህ ነውረኛ እና አፀያፊ የጥቂት “እብድ ጁንታዎች “ድርጊት፣ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ  የማንቂያ ደውል መደወሉን መላው ኢትዮጵያዊያን እንድንገነዘብም አድርጓናል።

ይህ የዘር፣የጎሣ ና የነገድ ለ21ኛው ክ/ዘ የማይመጥን እጅግ ኋላ ቀር ፖለቲካዊ  መንገድ  በቋንቋ ሥም ለተደራጁ፣ለሆዳም ፣ለሥግብግብ ና ለአግበሥባሽ  ፖለቲከኞች ሥጋዊ ጥቅም ፣ምቾት ና ድሎትን ያበረክታል እንጂ ፣ለዜጎች እልቂትና ሞትን እንደሚያሥከትል በአምሥቱ አመት የኢጣሊያ አገዛዝ ወቅት ታይቷል።(1928 __1933)

ይህ የከፋፍለህ ግዛ የፖለቲካ ሥርዓት በአብዮታዊ ዴሞክራሲ እና በብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ሽፋን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ መጫን የለበትም።ይህ በማር የተለወሰ መርዝ በውሥጡ የያዘ ሥርዓት  የአንድነታችን፣ የፍቅራችን ፣የጋብቻችን ፣የልጆቻችን፣ የትውልዳችን ጠላት ነው በማለት ፣ከ1984 ዓ/ም ጀምሮ አያሌ የሀገር ፍቅር ያላቸው ምሁራን በፅሑፍ፣በንንግግር፣በተቃውሞ ድምፅ የዛሬውን  አደጋ አሥቀድመው አሣውቀዋል።

ዛሬም ይናገራሉ።ወደፊት ግልፅ የሆነ ወቅታዊ አደጋ፣   በነፃ አውጪ ሥም በተደራጁ ኃይሎች ሁሉ  እንደሚደርሥብን ከወዲሁ መታወቅ አለበት። ።ነፃ አውጫ ብሎ ፓርቲ ከአንድ አገር ህልውና ጋር ብቻ ሳይሆን ፣ ከራሱ ከፓርቲ ሥያሜ ጋርም እርሥ በእርሱ የሚጋጭ ነው።ለመግደል አነጣጥረህበት አልገድልህም ዝም ብለህ ቁም እንደማለትም በመሆኑ ፣ሥያሜው ወደእውነተኛ ሠላማዊ ሥም፣   መቀየር ይኖርበታል።

ወደፊት እንደ ህወሓት  ዓይነት ጁንታ ከመከሰቱ በፊት   እነዚህ ኢትዮጵያዊ ሆነው ፣በፀረ ኢትዮጵያዊነት ሥም የተደራጁና፣አገርን ለመቆራረሥ የሚያሥችል፣ የነፃ አውጪ ሥም ያላቸው ሁሉ ፣ ሥማቸውን ካልቀየሪ፣ በሙሉ ከፓርቲነት መሠረዝ አለባቸው። ሥማቸውንም ከግንባር ወይም ከተዋጊነት ወደ ዴሞክራሲያዊነት ወይም ንቅናቄነት ወይም ወደህብረት ና አንድነትነት እንዲቀይሩ የሚያሥገድድ ህግ መውጣትም አለበት።የሚል እምነት አለኝ።

ይህ እምነቴን የሚያረጋግጥልኝ ደግሞ የኦነግ ፀረ ኢትዮጵያ ሥያሜ ነው። የኦነግ ሥያሚ በግብፅ የተሠጠ  መሆኑ ይታመናል።የተቋቋመውም ሥልጠና የተሠጠውም ግብፅ ውሥጥ እንደሆነ ታሪክ ይመሠክራልና። እናም አላማው ኢትዮጵያ የምትባልን አገር ማፈራረሥ ነው።

እርግጥ ነው፣ይህ በፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች የተሠጠው ተልእኮ በመላው ኢትዮጵያውያን  ቅቡልነት የለውም።

ቅቡልነት እንደሌለው የምንገነዘበው    ኦሮሞ እንደተባለ ጎሣ ፍፁም ኢትዮጵያዊ እንደሌለ ሥንገነዘብ ብቻ ነው።አሥረዳለሁ።

የኦሮሞ ጎሣ፣  ከ1520__1620   በመላው ኢትዮጵያ፣በደፈጣ ውጊያ የበዙ የኢትዮጵያ ክፍለ አገሮችን ይዞ፣   በሞጋሣና በጉዲፈቻ ” ኗሪዎቹን በራሱ ባህል በግድ አጥምቋል።ተጋብቷል።ተዋልዷል። እናም ነፁህ የኦሮሞ ዘር ብሎ ነገር በኢትዮጵያ የለም።  ።ነፁህ ኢትዮጵያዊ ሰው እንጂ።

ዓፄ ሶሥኒዮሥ 1605 __1632  የኦሮሞ ገዳ ሥርዓትን ወደ ባላባታዊ ሥርዓት ፣የመለወጥ ሂደትን የጀመረ የጎንደር ንጉሥ ነው።ይህ ንጉሥ የአፄ ልብለድንግል የልጅ፣ልጅ ነው።የተወለደውም በ1565 ዓ/ም እንደሆነ ይታመናል። “በ1580  ኦሮሞዎች በጎንደር ባደረጉት ወረራ በልጅነቱ   በምርኮ ወሥደውት ፣ቡኮ ለተባለ ኦሮሞ የጉዲፈቻ ልጁ አደረጉት።”ይለናል ታሪክ።

ሶስኒዮሥ በምርኮ ዘመኑ ከቡኮ ፣የኦሮሞን ቋንቋና የገዳን   ሥርአት ጠንቅቆ በመማር ና የጦር አደረጃጀትና ሥልትን በሚገባ ተምሮ ካጠናቀቀ በኋላ፣በ1886 ወደ ሠረፀ ድንግል ቤተመንግሥት መለሱት። እዛም የቤተመንግሥቱን ወግና ሥርዓት ተምሮ በ1605  ዓ/ም  ለንግሥና በቃ።

ከ1605__1632 ዓ/ም ባለው የንግሥና ግዜው የኦሮሞ ገዳ ሥርዓትን ወደ ባላባታዊ ሥርዓት የመለወጥ  ሂደትን የጀመረ ሰው ነው።

( በነገራችን ላይ የገዳ ሥርዓት በማለት በኋላ ቀር ሥርዓት እንመራ የሚሉት እጅግ ጠርዘኛ የሆነ ቆሞ ቀር አሥተሳሰብ ያላቸው ከመሆናቸውም በላይ ፣የ21ኛው  ክ/ዘ ሥልጣኔ ፈፅሞ ያልገባቸው ናቸው።  የገደ ሥርዓት እንከኑ ብዙ ነው። ከመብት አንፃር ለሴቶች አንዳችም መብት የማይሰጥ ጨቆኝ ና አምባገነን ነው።የገዳ ሥርዓት በእርግጥ ለ15ኛው ክ/ዘ የሚመጥን ነው።ለ21ኛው ክ/ዘ  ፈፅሞ የማይመጥን መሆኑ መታወቅ አለበት።)

ከዚህ እውነተኛ ታሪክ ተነሥተን፣ ኢትዮጵያዊያን በዘመን ሂደት የተዋሃድን ነን። ደማችን ተቀላቅሏል።ባህላችን ተደባልቋል።ቋንቋችን ተወራርሷል።…እናም የኘፃ አውጪ ሥም አያሥፈልገንም።… ማንን ከማን ነፃ እናወጣለን?…የታራካዊ ጠላቶቻችንን በነፃ አውጪ ሥም አደራጅተው እርሥ በእርሥ ሊያጫርሱን የሸረቡትን ድብቅ ሤራ ዛሬ ለአንዴና ለመጨረሻ ጋዜ መበጣጠሥ ይገባናል።

ዛሬ በነፃ አውጪ ሥም  ግብፅ ከጅምሩ  ያደራጀቻቸው በዕድሜ የገፉ  ፣ጉድጎዳቸው የተማሰ ልጣቸው የራሰ፣ግለሰቦች ፣በባዮሎጂ ሞት ተሠንገው እንኳን የደሞዝ ከፋያቸውን ተልእኮ  ለመፈፀም የነፃ አውጪ ስማቸውን የሙጥኝ ሲሉ እናሥተውላለን።ይህ አሥተሳሰባቸው የደለቡ የሰው ጅቦችን የሚገባቸውን ቅጣት ከሰጠናቸው በኋላ እንዲታረም ማድረግ ይገባናል።

“  በኢትዮጵያ ውሥጥ እየኖሪ፣ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በአንድ ማዕድ እየተቆደሱ ፣ከኢትዮጵያ ነፃ አወጣችኋለሁ ብሎ ፣በባርነት ውሥጥ የሌለን ህዝብ ፣ባርያ ወይም ቅኝ ተገዢ ሆነሃል ብሎ መቀሥቀሥ እንደማይቻል ፣በህግ ሊደነገግ እና በቅኝ ገዢዎችና በታሪካዊ ጠላቶቻችን የተመሠረቱ ሥሞች ሁሉ በህግ እንዲሠረዙ ማድረግ ለዘላቂ ሠላማችን አሥፈላጋ ነው። “ ብዬ አምናለሁ ።(በአሸባሪነት መፈረጀ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነታቸውን እሥካላመኑ   ና የነፃ አውጫ ሥማቸውን እሥካልሠረዙ ጊዜ ድረሥ  ከፖለቲካ ጫወታው መውጣት አለባቸው።)

ያለአንዳች የፖለቲካ ሣይንሥ እውቀት ፣ የአንድ  የፖለቲካ ቡድንን ሥያሚ በመገንዘብ ብቻ ማንነቱን መረዳት ይቻላል።ህውሃት ከሻቢያ ወይንም ከኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባር ሥምን በመኮረጅ ብቻ ሳይሆን ሥልጠና እና ትጥቅ አግኝቶ በጣት በሚቆጠሩ ግለሰቦች የተመሠረተ መሆኑን ።( በ1962 ዓ/ም።) በመገንዘብ ብቻ ዓላማውን፣ራእይና ግቡን መረዳት አያዳግትም።

ከዚህ መረዳታችን ተነሥተንም፣ “ ህወሓት   ከምሥረታው ጀምሮ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደረውን  የትግራይ ህዝብ የካደ ነው።” ለማለት እንችላለን። ትግራይን ነፃ አወጣለሁ ሲል እገነጥላታለሁ ማለቱ ነው።ይህንንም በማለቱ እና የኢትዮጵያ መንግሥትን በመውጋቱ ከግብፅ ና ከአንዳንድ የአረብ አገራት ከፍተኛ ድጋፍ እና እንደልብ መውጫና መግቢያ ፓሥፖርት ማግኘቱም ይታወቃል።

በወቅቱ የነበረውም የዓለም አይዶሎጂ እና ሁለት ጎራ ለኢትዮጵያ ያለመረጋጋት ከፍተኛ አሥተዋፆ አድርጓል።በየዋህነት ና በቅንነት በፍፁም የሀገር ፍቅር ሥሜት ለአገሩ፣ ማለትም ለኢትዮጵያ ህዝብ ሠላም፣ብልፅግና እና ክብር ሲል የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ያለሥሥት በጀግንነት ከተገጣዮች ና አሥገጣዮች ጋር ተፋልሞ በጀግንነት መውደቁ ይታወቃል።

ወያኔም በኢሳያሥ አፈወርቂ ሙሉ እገዛ ትግራይን ሳይሆን ኢትዮጵያን ይዞ እንደጅብ በልቷታል።ጥቂት ግብራ አበሮቹም ድርጓቸውን አግኝተዋል።አጫፋሪዎቹም ሞልቶ ሲፈሥ ፍጪጭ ያለውን ልሰው እያጣጣሙ ተኝተዋል።

ቀን፣ቀንን ወልዶ የሚያሥብ ትውልድ ተፈጠረ።ጠያቂ ትውልድ የለም።ኢህአዴግንም የሚገዳደር ፓርቲ አልተፈጠረምና ገና አርባ ዓመት እንገዛለን ሲሉ  ያ ጠንቋይ ተሥፋዬ ገ/አብ በጋዜጠኛው ማሥታወሻ ላይ ከ27 ዓመት አያልፉም የሚል ንግርት አለ እንዳለው በ27 ዓመታቸው ተንኮታኮቱ።

እነሱ ተንኮታኩተው ወደመቀሌ ቢመሽጉም የትላንት የፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎችን የውጪ ጠላቶቻችንን “ የጌቶቻቸውን “ ሴራ  አልረሱም ነበርና በእነሱ ቅኝት ፣የማረጃ ቢላቸውን ከደበቁበት አንሥተው፣ሰውን በጭካኔ ማረድ ጀመሩ።ከአልሻባብ እና ከአይስስ ብቻ ሳይሆን ከሴጣን የበለጡ ጨካኝ መሆናቸውንም በማሳየት ከዳቢሎሥ የወርቅ ሽልማት አገኙ።

በዚህ ድርጊታቸው ኃይማኖተኛው ፣ የትግራይ ህዝብ በእጅጉ አዝኗል።አልቅሷል።” ምን ዓይነት ጉዶች ከከኃይማነተኛዋ እና ፈሪሃ እግዛብሔር ካላት ትግራይ በቀሉ?!”  በማለትም አውግዟቸዋል።…

የትግራይ ህዝብ ፣እንደኢትዮጵያዊነቱ፣መተከዝ ማዘን ፣መቆጨት፣ እና እነዚህን ጠብደል ጀቦች መጠየፍ ብቻ ሳይሆን ፣ከእኩይ አላማቸው ጋር አልሰለፍም ብሏል።ለእንጀራው __ለደሞዙ ሲል ከእነዚህ የሰውን ደም ከሚጠጡ የሤጣን አልቆች ጋር የተሰለፈም አለ። ጥቂቱም በቀቢፀ ተሥፋ ነገ ኢትዮጵያን ቅኝ እገዛለሁ ብሎ ፣ለፍርፋሪ ሥልጣን የቋመጠም ፣በአዝማችነት ተሠልፎ ከአበዱት ሴጣኖች ጋር አብሮቸው የንፁሐን ኢትዮጵያዊያንን ደም የሚጣውንም አሥተውለናል።

ዋ! ሀገሬ፣ሥንቶቹ ለአንቺ ክብር በጉንደት፣በሰናኤ፣በጉዳጉደት፣ በአባላጌ በማጨው፣በመቀሌ ፣በመተማ፣ ወደቁ ?

በሚያሰዝን መልኩስ ፣ እነሥዩም መሥፍን በዓለም አቀፉ ፍርድ  ቤት ባድሚን ለኤርትራ አሥረክበው ሲያበቁ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ በመዋሸት ፣”የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ባድሜን ለእኛ ወሰነልን።” በማለት በተለመደው ቀጣፊነታቸው ገፍተውበት አደባባይ ወጥተን እንድንጨፍር ካደረጉን በኋላ ፤ በተፈረደለት የኤርትራ መንግሥት (ለሀገርነቱ መጀመሪያ እውቅና የሠጠው የወያኔ አመራር መሆኑ አይዘንጋና)  ጥቂትም ሳይቆዩ ፣ ተወረርን በማለት ጮኹ።መላው ኢትዮጵያኖችም እንደ አድዋ ለሀገራቸው ለመዋደቅ ሆ ! ብለው በመነሳት ድል እንዳደረጉሥ ይዘነጋልን???

ልብ በሉ የዓለም አቀፍ ፍርድ ቤትን ውሳኔ እሥተተቀበሉ ድረሥ ፣ሌላውን ጉዳይ በውይይትና በሰጥቶ መቀበል ይፈቱት ነበር።ይህ አሳብ የመጣው  ግን ጦርነቱ ከሁለቱም ወገን የደሃ ልጆችን ከበላ በኋላ ነው።  ድንበርተኛውና የሁለቱ አገር መንግሥታት በጠረጴዛ ዙሪያ የሚፈቱትን ፣በመገዳደል ቂም እንዲረገዝ አድርገዋል።…

ሲጀመር ከኤርትራ መንግሥት ጋር የተጣሉት ፣የግል ሃብት ማከማቸት በመጀመራቸው የተነሳ፣የኤርትራን ባለሀብቶች እኩል ተጠቃሚነት ባለመፈለጋቸው ነው። ቀድሞውንም ለአጠቃላይ ዜጎች እድገት አያሥቡም ነበርና  ቅን ያልሆነው ምኞታቸው ሁሉ በየጊዜው ሲከሽፍ ተሥተውሏል።

ዛሬም በተጠና ታላቅ ሴራ ፣ያላቸውን ገንዘብ ሁሉ አውጥተው ቅጥር ነፍሰ ገዳይ በመቅጠር ፣ከአይስስ፣ከአልሻባብ፣ በመቶ እጅ የበለጡ ፣ ቁጥር አንድ የዓለም አሸባሪዎች መሆናቸውን ቢያስመሰክሩም እኩይ ውጥናቸው ከሽፏል።

በልዩ ኃይል ሥም በሥውር አደገኛ  ሽፍታ፣ማጅራት መቺ፣ሌባ፣ወሮበላ፣ ሠርቆ ከመብለት ውጪ ህልም የሌለው ሆድ ብቻ የሆነ ጭንቅላት አልባ አውሬ አደራጅተው ፣ አገራችንን እያደሟት ፣እያቆሰሏት እዛና እዚህ የሤጣን ብትር እየሰነዘሩባት ቢገኙም ፣ ዛሬ ራሳቸው የጫሩት እሳት እየፈጃቸው ነው።

በጫሩት እሳት እሥከሚጠፉ ድረሥ በእኩይ ድርጊታቸው እቅድ መሠረት በአሥደንጋጭ ና በሠቅጣጭ ድርጊታቸው መቀጠላቸው ግን አይቀርም። ጭንቅላት ስለሌላቸው ማሠብ አይችሉምና በአእምሮ ቢሥ ድርጊታቸው ይቀጥላሉ።

የእነዚህ ጭንቅላት አልባ ፣ሆድ ብቻ የሆኑ አእምሮ ቢሶች መጨረሻቸው እንደማያምር የታወቀ ነው።የሚሊዮን እናቶች እንባ እንዲሁ ፈሶ አይቀርም። ቀና ብለው ወደ ፈጣሪያቸው የረጩት እንባ በከንቱ ይቀራል ብሎ የሚያሥብ ካለ እሱ ከታሪክ መማር የማይችል የፈጣሪን የየእለት  ፍርድ ያላሥተዋለ ግብዝ ብቻ ነው።

እውነት አውነት እላችኋለሁ ፣በጭካኔ ተነሣሥቶ ወንድሙን በሠይፍ የሚገድል በሠይፍ መሞቱ አይቀርም።ማንም ሰው በሰፈረው መሥፈሪያ እንደሚሠፈርለት ይወቅ።ገዳይ ቢዘገይ ሟች ገሥግሶ ወደ ገዳዩ መሄዱ ለምን ይመሥላችኋል? ….አትጠራጠሩ እነዚህ አሣፋሪ የበሉበትን ወጪት ሰባሪ ፣ያጎረሳቸውን ጣት ነካሽ ፣ እነዚህ አእምሮ ቢሥ  ባንዳዎች ፣በጫሩት እሣት እራሳቸው ተቃጥለው ያልቃሉ።

እሥከፍፃሚያቸው  ድረሥ፣

“ሎጋው ሽቦየ ! ሎጋው ሽቦየ  !

የጫረው እሣት ሲፈጀው ታየ  !” እያለን ፣ ወደማይቀረው የኢትዮጵያውያን አኩሪ ድል እንገሠግሣለን ።

 

ኮንን  ሻውል  ወልደጊዮርጊስ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.