ወቅታዊ የሐገራችን ሁኔታ አስመልክቶ ከዓለምአቀፍ የጉራጌ ማሕበር (ዓጉማ) የተሰጠ መግለጫ

20201110 002242 0000የሕወሃት-ኢሕአዴግ መራሽ መንግስት በለውጥ ኃይሉ ከተተካ ሁለት ተኩል ዓመታት ጀምሮ በሀገራችን አንጻራዊ የሠላም፣ የዲሞክራሲና የልማት ተስፋ ብልጭ ብሎ ነበር ፡፡ ይሁን እንጂ በለውጡ እዚህም እዚያም ያኮረፉ አካላትና ጥቅማቸው የተነካ የውጪ አካላት ለውጡን ለማኮላሸት በለኮሱት እሳት ለውጡ የታለመለትን ውጤት እንዳያመጣ ብርቱ ትግል ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡
ህወሀትም ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ከለውጥ አደናቃፊ አካላት የመጀመሪያው ረድፍ በመሰለፍ በኢትዮጵያውያን ላይ በሥልጣን ዘመኑ ያደረሰው ጭቆና እና ግፍ ለማስቀጠል ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ከኢትዮጵያውያን ጉሮሮ የዘረፈውን ገንዘብ በመበጀት ከጥፋት ኃይሎች ጀርባ ሆኖ አመራር እየሰጠ በሁሉም ክልሎች ለዜጎች ሞት፣መፈናቀል እና እንግልት ምክንያት ሆኗል፡፡
ይህም አልበቃ ብሎት ሐገራችን የህዳሴ ግድብ ውጫዊ ጫናን፣የአንበጣ መንጋን፣የኮረና ቫይረስና ሌሎችም ችግሮች ውስጥ ባለችበት ባሁኑ ሰዓት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖ፣ ኢትዮጵያውያን ማየትም ሆነ መስማት ወደማይፈልጉት ጦርነት ውስጥ ለማስገባት በመከላከያ ሰራዊታችን ላይ ለመስማት የሚዘገንን ዘር ተኮር ጥቃት ፈጽሟል።
በሁለቱም በኩል የኢትዮጵያውያን ሕይወት ጠፍቷል፤ የሕዝብና የሀገር ንብረት እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ወድሟል፤ ተዘርፏል፡፡
የዓለምአቀፍ የጉራጌ ማሕበር (ዓጉማ) የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴም ጥቅምት 28 ቀን 2013 ዓ/ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ክፍ ብሎ የተመለከቱትን ነጥቦች ከገመገመ በኋላ፡-
§  የሐገር አንድነት እና ሰላም ከሁሉም ጥያቄዎች በላይ መሆኑን በማጤን፤
§  የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ፣ እንዲሁም የልማትና የአንድነት ጉዳዮች በሰከነ መልኩ ሊከናወኑ የሚችሉትም ሀገር ስትኖር መሆኑን በማመን፤
§  መንግሥት በአሁኑ ጊዜ፣ በከንቱ እየጠፋ ያለውን የሰው ሕይወት እና ንብረት እንዲታደግ ድጋፍ መስጠት እንደሚያስፈልግም በማመን፤
§  ሕዝባችን የጥፋት ኃይሎች ሰለባ እንዳይሆን፣ የሕዝብ ግንኙነት ስራዎችን መስራት እንደሚገባ በመገንዘብ፤
እነዚህ አጠቃላይ ሐገራዊ ችግሮች መልክ እስከሚይዙ ድረስ የዓጉማ አባላትና ደጋፊዎች በሙሉ በዚሁ ሐገራዊ አጀንዳ ላይ ትኩረት አድርገው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ተስማምቷል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ፣ እንዲሁም የልማት እና የአንድነት ጉዳዮች ለአፍታም ቢሆን የማይዘነጉ በመሆኑ ከወቅታዊ ሐገራዊ አጀንዳዎቻችን ጎን ለጎን እንዲሰሩ ወስኗል፡፡
በመሆኑም መንግስትና የመከላከያ ሠራዊታችን ሕግን ለማስከበር የወሰዱት እርምጃ በሙሉ የምንደግፍ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ በሕግ ማስከበሩ ሂደት ውስጥ በተቻለ መጠን ሰላማዊ ሕዝብ፣ የሀገር ሀብትና ንብረት ለአደጋ እንዳይጋለጥ መንግስት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ እንጠይቃለን፡፡ በወንጀል ተጠርጥረው እየታደኑ ያሉ የህወሃት ሰዎች በማንኛውም ጊዜ ለፍርድ ለመቅረብ እጃቸው ለመንግስት ከሰጡ የተጀመረው ውጊያ እንዲቆም እናሳስባለን፡፡ ይህ ሕግ የማስከበር ሂደት በመከላከያ ሠራዊታችን፣በልዩ ኃይል፣በሚሊሻ እና በሕዝባችን ተጋድሎ በድል አድራጊነት በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ሀሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም አየር እንዲተነፍስ እንመኛለን፡፡
ድል ለመከላከያ ሠራዊታችን እና ለኢትዮጵያ!
ዓለምአቀፍ የጉራጌ ማሕበር (ዓጉማ)
ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ/ም

1 Comment

  1. ያሁኑ ይባስ! የጉራጌ ኢትዮጵያዊነትም በcondition ሆነ? የምትሉን እኮ “እናግዛለን፤ ግን ከ”ድል” በኋላ ክልል ትሰጡናላችሁ”፤ የጉድ ገንፎ እያደር ይፋጃል አሉ፤ አቢይ መጥኔውን ይስጥህ!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.