የፌዴሬሽን ም/ቤት በትግራይ ጊዜያዊ መንግስት እንዲቋቋም በሙሉ ድምጽ ወሰነ

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ጣልቃ እንዲገባ እና ጊዜያዊ መንግስት (አስተዳደር) እንዲቋቋም ያቀረበው የውሳኔ ሃሳብ በሙሉ ድምጽ ፀደቀ፡፡
Parlama 1ምክር ቤቱ በዛሬው እለት አስቸኳይ ስብሰባውን አካሄዷል፡፡
በስብሰባውም በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

ጊዜያዊ አስተዳደር ለክልሉ ከፍተኛ የሕግ አስፈፃሚ አካል የተሰጡትን ተግባሮች እንደሚኖሩት ተገልጿል።

በተለይም ደግሞ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፦

ሀ) አስፈፃሚ አካሉን ይመራል፣ ያስተባብራል፤
ለ) የጊዜያዊ አስተዳደሩን ኃላፊዎች ይመድባል፤
ሐ) ሕግና ሥርዓት መገበሩን ያረጋግጣል፤
መ) አግባብ ባለው ህግ መሰረት በክልሉ ምርጫ የሚከናወንበትን ሁኔታ ያመቻቻል፤
ሠ) የክልሉን እቅድና በጀት ያፀድቃል፤
ረ) በፌዴራል መንግስቱ ሚሰጡ ሌሎች ተግባሮችን ያከናውናል ተብሏል።

የምክር ቤቱን ውሳኔ

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግስቱና በአዋጅ ቁጥር 359/1995 በተሰጠው ስልጣን መሰረት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋምና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ውሳኔዎችን ወሰነ፡፡
ሕገወጡ የትግራይ ክልል መንግስት ወደ ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱ እንዲመለስ የተሰጠውን በቂ እድል መጠቀም ባለመቻሉ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌዴሬሽን ም/ቤት ዛሬ ጥቅምት 28 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔ በሕገ መንግስቱና በአዋጅ ቁጥር 359/1995 በተሰጠው ስልጣን መሰረት ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋምና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ውሳኔዎችን ወስኗል፡፡
ህገወጡ የትግራይ ክልል መንግስት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ በክልሉ በሚገኘው ጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ አስነዋሪ ጥቃት ፈጽሟል፡፡ በተጨማሪም በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ጥቃት በመፈፀም በንፁሃን ዜጎችና ንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡
የፌዴራል መንግስት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 359/95 አንቀጽ 12 በአንድ የክልል መንግስት ተሳትፎ ወይም ዕውቅና ሕገመንግስቱን ወይም ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን ባለማክበር የሚደረግ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት በተለይም፡
(1) በትጥቅ የተደገፈ የአመጽ እንቅስቃሴ ማድረግ፤
(2) ከሌላ ክልል ወይም ከሌላ ክልል ብሔር፣ ብሄረሰብ ወይም ሕዝብ ጋር የተፈጠሩ ችግሮችን ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ መፍታት፤
(3) የፌዴራሉን ሰላምና ጸጥታ ማናጋት ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት እንደሆነ እንደሚቆጠር ተደንግጓል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ አንጻር ሕገወጡ የትግራይ ክልል መንግስት የፈጸመው እና እየፈጸመ ያለው ድርጊት ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ ተጨማሪ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡
በዚሁ መሰረት የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ም/ቤት በሕገመንግስቱ አንቀጽ 62 (9) ማንኛውም ክልል ሕገመንግስቱን በመጣስ ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌዴራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ የማዘዝ ሥልጣን እንዳለው የተደነገገ በመሆኑ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር ለመዘርዘር በወጣው አዋጅ ቁጥር 251/93 አንቀጽ 36 (1) የፌዴሬሽን ም/ቤት በአንድ ክልል ውስጥ ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ወድቋል ብሎ ሲያምን የፌዴራሉ መንግስት ተገቢና ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ማዘዝ እንደሚችል እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 359/95 አንቀጽ 13 (4) ም/ቤቱ የፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ መግባት አስፈላጊ ሆኖ ያገኘው እንደሆነ ጣልቃ እንዲገባ ሊያዝ እንደሚችል በመደንገጉ ሕገወጡ የትግራይ ክልል መንግስት ሕገመንግስታዊ እና የፌዴራል ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት በመፈጸም የፌዴሬሽኑን ህልውና አደጋ ላይ የጣለ ስለሆነ ይህንን ድርጊት ማስቆም ተገቢ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በመሆኑም የፌዴሬሽን ም/ቤት በሕገመንግስቱና በአዋጆቹ የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት በመጠቀም ሕገመንግስታዊ መፍትሔ መስጠት ያለበት ሆኖ በመገኘቱ ዛሬ ጥቅምት 28 ቀን ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የሚከተሉትንን ውሳኔዎች አሳልፏል፡፡
1. ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለውን ድርጊት ለማስቆም የፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ እንዲገባ ትዕዛዝ ሰጥቷል፤ እንዲሁም ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች በተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 359/95 አንቀጽ 14 (2) መሰረት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተጣጣመ መልኩ አደጋውን ለማስወገድ እንዲቻል የፌደራል ፖሊስን ወይም የሃገር መከላከያ ሠራዊትን ወይንም ሁለቱንም በክልሉ እንዲያሰማራ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፤
2. ሕገወጡን የክልሉ ምክር ቤት እና የክልሉ ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ አካል ታግዶ ለፌደራል መንግስቱ ተጠሪ የሆነና በአዋጅ 359/1995 አንቀጽ 15 ላይ የጠቀመጡት ሥልጣንና ተግባራት የሚኖሩት ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ወስኗል፡፡ በዚሁ መሰረት የሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ከሌሎች አግባብነት ካላቸው መንግስታዊ አካላት ጋር በመተባበር ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለውን ሁኔታ ለማስወገድ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ይወስዳል፡፡ በተጨማሪም ለክልሉ ከፍተኛ የሕግ አስፈፃሚ አካል የተሰጡትን ተግባሮች ይኖሩታል፡፡ በተለይም ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤
ሀ) አስፈፃሚ አካሉን ይመራል፣ ያስተባብራል፤
ለ) የጊዜያዊ አስተዳደሩን ኃላፊዎች ይመድባል፤
ሐ) ሕግና ሥርዓት መገበሩን ያረጋግጣል፤
መ) አግባብ ባለው ህግ መሰረት በክልሉ ምርጫ የሚከናወንበትን ሁኔታ
ያመቻቻል፤
ሠ) የክልሉን እቅድና በጀት ያፀድቃል፤
ረ) በፌዴራል መንግስቱ ሚሰጡ ሌሎች ተግባሮችን ያከናውናል፡፡
3. ከፍ ብሎ የተጠቀሱትን የምክር ቤቱ ውሳኔዎች አፈጻጸምና ክልሉ ሰለሚገኝበት ሁኔታ በተመለከተ ክቡር የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደ አስፈላጊነቱ ለፌዴሬሽን ም/ቤት በየሦስት ወሩ ሪፖርት እንዲያቀርብ በማለት ወስኗል፡፡
በመጨረሻም መላው የትግራይ ሕዝብና የአገራችን ሕዝቦች ሕገወጡ ቡድን የፈፀመውን ኢ-ሕገመንግስታዊና አስነዋሪ ድርጊት በማውገዝ የሀገርን ሉዓላዊ ክብር ለማስጠበቅ ከራስ በፊት ለሕዝብና ለሀገር በሚል መርህ እስከ ህይወት መስዋእትነት እየከፈለ ካለውና የኩራታችን ምንጭ ከሆነው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ጨምሮ ከፌደራሉ መንግስት እና ከሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ጎን እንዲቆም የፌዴሬሽን ም/ቤት ጥሪውን ያቀርባል፡፡ በተጨማሪም መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በመተሳሰብ፣ አንዱ ለሌላው ጠበቃና ዋስትና በመሆን እኩይ አላማ ይዘው እርስ በርሳችንን በማጋጨት አገራችንን ለመበታተን ሌትተቀን የሚሰሩ ሀይሎችን ነቅተን በመጠበቅና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር ረገድ ሁሉም ዘብ እንዲቆም የፌዴሬሽን ም/ቤት ጥሪውን ያቀርባል፡፡
የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት
ጥቅምት 28/2013 ዓ/ም

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.