የሕወሓት ቡድን ከጅምሩ ልዩነቶች በሰላም እንዲፈቱ ምንም አይነት ፍላጎት አልነበረውም – የአገር ሽማግሌዎች

2334የሕወሓት ቡድን ልዩነቶች በውይይትና በሰላም እንዲፈቱ ፍላጎት እንዳልነበረው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ወደ ትግራይ ለሽምግልና ተጉዘው የነበሩ የኃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።
በሱማሌ ክልል የጎሳ መሪ የሆኑት ጋራድ ኩልሚዬ ”ሕወሓት ኢትዮጵያን በመራበት ዘመን ሁሉ ሕገ መንግስቱን አክብሮ አያውቅም” ይላሉ።
እርሳቸው በቅርበት የሚያውቁትን የሱማሌ ክልልን እንደምሳሌ ሲጠቅሱ ክልሉ በሞግዚት አስተዳደር ሲመራ ነበር ብለዋል።
የአገሪቷን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ እሴቶች በሙሉ የናደው የህወሃት ቡድን በሕግ ተመራ ሲባል ወደ ጥፋት መሄዱንም ገልጸዋል።
በብዙ ጥፋት ውስጥ ገብቶ የቆየው ቡድን ከጥፋት እንዲመለስ ለሽምግልና ወደ መቐለ ከሄዱት የአገር ሽማግሌዎች መካከል እንዱ መሆናቸውን ነው የገለጹት ጋራድ ኩልሚዬ።
ጋራድ ኩልሚዬ እንደሚሉት በወቅቱ ከሄድንበት ሽምግልና መታዘብ የተቻለው ሕወሓት ጸረ ሰላምና ለትግራይ ሕዝብም የማይበጅ መሆኑን ነው።
”ምንም ያህል ጦርነት አስከፊ ቢሆንም ከአገር ሕልውና በላይ አይደለም” የሚሉት ጋራድ ኩልሚዬ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቡድኑን ከጥፋቱ መግታት ያስፈልጋል ብለዋል።
የአማራ ክልል የሽምግልና ስርዓት ማህበር ፕሬዚዳንት ሊቀ ሕሩያን በላይ መኮንን ሌላው በወቅቱ ለሽምግልና ወደ ሰፍራው ከተጓዙት መካከል ናቸው።
በወቅቱ ፓትሪያርኩን ጨምሮ ትላልቅ የኃይማኖት አባቶች፣ ኡጋሶች፣ አሚሮችና አባገዳዎችን እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦችን ያከተተ ቡድን ወደ ስፍራው ለሽምግልና ተጉዞ እንደነበር አስታውሰዋል።
አላማውም በሕወሓትና በማዕከላዊ መንግስቱ መካከል እየተካረረ የመጣውን ልዩነት ለማጥበብና በሽምግልና መቀራረብን ለመፍጠር እንደነበርም ይገልጻሉ።
ሆኖም በወቅቱ ወደ መቐለ የተጓዙትን የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች ህወሃት አክብሮት በመንሳት መልካም አቀባበል እንዳላደረገላቸው አስታውሰዋል።
መቐለ ሲደርሱ ከፍተሻ ጀምሮ ብዙ እንግልቶችን አልፈው ሽማግሌዎቹ በስብሰባ አዳራሽ ቢታደሙም የህወሃት ቡድን ለሽምግልና ፍላጎት አለማሳየቱን አረጋግጠዋል።
”አሁን ጊዜው አልፏል፤ ከረፈደ ነው የመጣችሁት” በማለት ለሃይማኖት አባቶችና ሽማግሌዎች ክብር በማሳጣት እንደመለሷቸው ሊቀ ሕሩያን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በወቅቱ ወደ መቐለ ለእርቅ የተጓዙት የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ሰዎች 60 እንደነበሩ ይታወሳል።
EBC
ተጨማሪ ያንብቡ:  (ሰበር ዜና) አንዳርጋቸው ጽጌ ወደ ቃሊቲ እስር ቤት መዛወራቸው ተሰማ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.