መዘግየቱ ወይስ መዋጋቱ?? – በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)

124418944 3771137276241206 1916458257079906990 n መዘግየቱ ወይስ መዋጋቱ??   በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)
ትህነግ ከጦርነት በስተቀር ለመንግስት ምንም የሰላም መንገድ አልተወለትም፡፡ መንግስት መጠየቅ የሚገባው አሁን ወደ ጦርነት በመግባቱ ሳይሆን፣ እስከዛሬ በመዘግየቱ ነው፡፡ እነዚህ ማፍያዎች ከምስረታ ጀምሮ ከመግደል፣ ከመዝረፍና ከመዋጋት በስተቀር ታሪክ የላቸውም፡፡ የመንግስትነት ታሪካቸውም ቢሆን ከዚህ የራቀ አይደለም፡፡ በታሪካቸው አንድም በድርድር የፈቱት ችግር፣ ያሰፈኑት ሰላም የለም፡፡ አሰብና በድርድር ማስቀረት ሲቻል ለመደራደር ሳይፈቅዱ ሰጡት፡፡ ለድርድር አንዴ ቢቀመጡ ባድሜን አስረክበው መጡ፡፡
.
ጠቅላይ ሚንስትሩ የሚጠየቁት፣ ማፍያነታቸውን ከማንም በላይ እያወቁ፣ እድሜያቸው ያልደረሰ ህጻናትን ሳይቀር የሚያሰለጥኑበት፣ መሳሪያ የሚሰበስቡበት፣ ምሽግ የሚቆፍሩበት፣ ሰላዮቻቸውንና አሸባሪዎቻቸውን በመላው ሀገሪቱ የሚያሰማሩበት ጊዜ በመስጠታቸው፤ ሀገር እስኪያተራምሱና የንጹሀንን ደም እስከሚያፈሱ፣ በመጨረሻም የመከላከያ ሰራዊቱን እስከሚያጠቁ በመጠበቃቸው ነው፡፡
.
አንዳንዶች ‹‹ሰላም ከጦርነት አይገኝም፤ ሞት እንጂ›› ሲሉ እሰማለሁ፡፡ ይህ አባባል ሚዛናዊነት የጎደለው፣ ለትህነግ የሚሰጥ አይንአፋር ድጋፍ ነው፡፡ ላለፉት ሁለትና ሶስት አመታት በሀገሪቱ ጭራሽ አንድ ሰው ሞቶ የማያውቅ፣ ሞት የተጀመረው ትላንት ከጦርነቱ ጋር ይመስል፡፡ እስቲ 2013 ከገባ እንኳን የሞተውን እናስብ! እና ያለ ጦርነት እየቀበሩ መኖር ሰላም ነው?
.
ለማንኛውም ሰላም በሁለት መንገድ ሊገኝ ይችላል፤ ከድርድርና ከጦርነት፡፡ ጦርነት ለሰላም የሚከፈለው ከፍተኛ ዋጋ ነው፤ ህይወት ይጠፋል፣ ኢኮኖሚ ይወድማል፡፡ #ከትህነግ ማፍያ መሪዎች ጋር በድርድር ሰላም ማምጣት እንደማይቻል ከእኛ በላይ እማኝ የለም፤ የሀይማኖት አባቶችና ሽማግሌዎች በተደጋጋሚ ተልኮባቸዋል፡፡ ሰላምን ከድርድር ለማግኘት መንግስት ያሳለፈውን ሁለት አመት፣ የተጠቀሙበት ጦር ለማሰልጠንና ሀገር ለማተራመስ ነው፡፡ ከልደታቸው ጀምሮ እዚህ ያደረሳቸውን፣ አሁንም እስከወንጀላቸው መሸሸጊያ የሆናቸውን የትግራይ ጭቁን ህዝብ ውለታ በምን እንደከፈሉት ለመገንዘግ፣ ከጉያው መንጭቀው ክላሽ ያሸከሟቸውን ህጻናት ማየት በቂ ነው፡፡
.
ይህን ጦርነት በተቻለ መጠን ሲቪሉን እየጠበቁ፣ ባነሰ ጥፋትና ባጭር ጊዜ በድል መወጣትና እነዚህን ለሀገርና ለህዝብ ደንታ የሌላቸው ማፍያዎች ሴራ ማምከን፣ የሀገራችንን የውስጥ ሰላም ለማምጣት መሰረታዊና የመጀመሪያ እርምጃ ነው!!!!
በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)

2 Comments

  1. ዶ/ር በድሉ ሰማኸዉ አይደል ህወአትን ሳይሆን ጁንታ ህዋቶችን ነዉ ብሎሀል ::ጠ/ሚኒስተሩ አንድ 5 ገመምተኛ አዛዉንትን ከ ጌታቸዉ ረዳ ጋር ዘብጥያ ጥሎ የተቀሩ ትግሬዎችን እስከ መርዛቸዉ ትቶ ሀገር ሊያበጣብጥ ነዉ እንደገና ::እነሱ ጀምረዉ አጥፉን ያሉትን ጥሪ ትቶ ሌላ ነገር ይቀበጣጥራል። አሁን አረጋዊ በርሄ ከመለስ ዜናዊ አብረሀ ደስታ ከስብሀት ነጋ ገብሩ አስራት ከአቦይ ስብሀት ማን ከማን ይለያል ታች ያለዉ ትግሬ ምንም ሳያገኝ ትግሬ ገዥ ነዉ በሚል እሳቤ የህወአት ደጋፊ ነዉ። ስለዚህ የጠፋዉን መሳሪያችንን ከነዚህ ወንጀለኞች ከግል ሂሳብ ንብረታቸዉ አንድ በአንድ ተሺጦ ወደ መንግስት የሚገባበት መንገድ ተፈልጎ ሂሳቡ መወራረድ ያስፈልገዋል። የህዝብ ገንዘብ ነዉ። እስከ ዛሬ ለፍርድ ይቅረቡ ስንል አብይ አባዱላን ለማዳን ብሎ ይህ ሁሉ ጥፋት እንዲፈጸም ምክንያት ሆነ። እግዚአብሄር አገራችንን ይጠብቅ ሰዉየዉ ረብሻ ሳይወድ አልቀረም ይህ ሁሉ ሰራዊት ኦነግ ሸኔን ማጥፋት ከብዶት ነዉ የወለጋን ህዝብ ቁም ስቅል የሚያሳየዉ ባንክ የሚዘርፈዉ? ለማንኛዉም ስለ ጥረትህ ሳናመሰግን አናለፍም።

  2. አሁን እነዚህ የትህነግ መሪዎች እጃቸውን ለመንግስት ቢሰጡ እንደ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ከእስክንድር ነጋ እኩል በአሸባሪነት ክስ ሊከሰሱ ነውን?
    ወይንስ እንደ ልደቱ አያሌው ህገ ውስጥ ጦር መሣርያ ይዘው ህገ መንግስት በመጣስ ሊከሰሱ ነው?
    ወይንስ እንደ ድንበር ጠባቂ ወታደር ተቆጥረው በመከላከያ ህግ በዝግ በወታደራዊ ፍርድ ቤት Court Marshall በግድያ ክስ ሊከሰሱ ነው?

    መቼም ከሶስት አመታት በፊት በኃይለማርያም ደሳለኝ እና በመለስ ዜናዊ ጊዜያት የሠሩት ወንጀል እንዳልሆነ ያሁኑን ግጭት ያስነሳው ግልጽ ነው። ስለዚህ በቅርብ በአብይ አህመድ ጊዜ ስለጣሱት ህጎች እነ መአዛ አሸናፊ እና የአቃቤ ህጉ እና ተመስገን ጥሩነህ የደህንነት መረጃ ሰብሳቢ እና የህግ መዋቅሩ ጭምር ወንጀለኞቹን በመመርመር ዝግጅት በማድረግ ወያኔንን ለመዳኘት የሚያስችል መዋቅራዊ ብቃት ማጎልበት ይገባቸዋል።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.