የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የተጀመረውን ጦርነት አስመልክቶ ከኢሕአፓ የተሰጠ መግለጫ

EPRP 3 የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የተጀመረውን ጦርነት አስመልክቶ ከኢሕአፓ የተሰጠ መግለጫጦርነት በወንድማማች እና እህትማማች ሕዝቦች መሀል የተከሰተ ልዩነትን ለመፍታት ተመራጭ መንገድ ባይሆንም ሁኔታዎች ወደተካረረ ደረጃ ላይ ሲደርሱ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ከውጭ ከሚመጣ ወራሪ ጦር ጋር የሚደረግ ጦርነት የቱንም ያህል የሰውና የንብረት ኪሳራ ቢያስከትልም ውጤቱ ነፃነት ሲሆን ተጋድሎው ለትውልድ የሚተላለፍ ኩራት ይሆናል፡፡ የእርስ-በእርስ ጦርነት በምንም መመዘኛ ቢታይ የኩራት ምንጭ አይሆንም፡፡

እንዲያውም አንገት የሚያስደፋ እና  ጸጸትን የሚወልድ ተግባር ነው፡፡ እንግዲህ ኢትዮጵያ ወደዚህ መራር እውነታ ጫፍ ተገፍታለች፤ የጦርነት መጀመርን ዜናም ሰምተናል፡፡ ጦርነቱ በትዕቢተኛው ሕወሃት ታጣቂ ሃይሎች ትንኮሳ የተጀመረ መሆኑም ታውቋል፤ በዚህ ጦርነት የሚወድቁት ሁሉ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡

እንደሚታወቀው በጦርነት የሚጎዱት ጦርነት ናፋቂዎችና ለኳሾች አይደሉም፤- ሕዝቡ እንጂ! የመከላከያ ሠራዊት አባላትም ይሁኑ ሕወሓት ያሰለፋቸው ሃይላት የኢትዮጵያ ሕዝብ ልጆች ናቸው፤ የሚጎዱትም እነርሱና በጦርነቱ ቀጠናዎች አካባቢ ያለው ንፁህ ሕዝብ ነው፡፡ እንግዲህ የመጀመሪያዋ የጦርነት ማስጀመሪያ ጥይት ስትተኮስ ሁኔታው ፈሩን ስቶ ሰላም ደፍርሷል፤ የደፈረሰ ነገር ደግሞ ካልጠራ ሰላም የለም፡፡

ሰላማችን ሕገ-ወጡ ቡድን ባሰማራቸው ታጣቂዎች በየአካባቢው በሚተኮሱ ጥይቶችና በሚወረወሩ ቦንቦች ምክንያት በተፈጠሩ ትናንሽ ጥቃቶች ከደፈረሰ ረጅም ጊዜ አስቆጥሯል፤ የበርካታ ዜጎቻችንን ሕይወት ቀጥፏል፤ የሕዝቡም ሕይወት ተበጥብጧል፤ ዛሬ ግን ለይቶለት ወደ መደበኛ ጦርነት አድጓል፡፡

በወንጀለኛው ቡድን የተጀመረው ጦርነት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ኪሳራ ሳያበዛ መጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡ እስከአሁን የተደረገው ጦርነት የቀጠፋቸውን ኢትዮጵያውያንን ማሰብ ያማል፤ በጦርነቱ ድምጸት የደነገጡ ልጆችን ማሰብ ያሳዝናል፣ የእናትና የአባቶቻቸውን ጭንቀት አረጋውያኑንና ህሙማኑን ማሰቡም ይከብዳል፡፡

በአጠቃላይ ጎስቃላው ሕዝብ የሚካፈለው ኢትዮጵያ አስመዘገበች ከሚባለው ዕድገት ሳይሆን ከችግሯ በመሆኑ እንደሀገር እንድናፍር ያደርገናል፡፡ ያም ሆነ ይህ፣ ወደድንም ጠላን፣ ፈለግንም አልፈለግን ጦርነቱ ተጀምሯል፡፡ ጦርነቱ ብዙ ጉዳት ሳያስከትል ማለቅ አለበት፡፡ የውስጥ ችግራችንን ውጠን እና ሁልጊዜም የምናሰማቸውን ብሶቶች ያዝ አድርገን ከመንግሥትና ከሕዝብ ጎን መቆም ግድ ይለናል፡፡ ከዚህ ክፉ አጋጣሚ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረግን ሩጫ በፍጹም ማየት አንፈልግም፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! ጦርነት የሚካሄደው በጦር ግንባር ብቻ ያለመሆኑን በማሰብ ከማንኛውም ከይሲ እንቅስቃሴ ራስህን ልትጠብቅ ይገባል፡፡ አሁን ጦርነቱ በተጀመረበት ቀጠና አካባቢ የምትገኙ የትግራይና የአማራ ሕዝብ ሆይ፤ መተሳሰብና አብሮነታችሁን ለሚፈትን እኩይ ቅስቀሳ ሳትበገሩ መንፈሳዊ አንድነታችሁን ጠብቁ፡፡ የዘርና የሃይማኖት ጥቃት በሚዘወተርባቸው አካባቢዎች የምትገኙ ኢትዮጵያውያን በአካባቢያችሁ ከሚገኙ የመንግሥት ሃይላት ጋር በመሆን አካባቢያችሁን የመጠበቅ ሃላፊነት አለባችሁ፡፡

ኢሕአፓ ይህ አስከፊ ጦርነት በአጭሩ እንዲገታ ይመኛል፡፡ ኢሕአፓ ሕዝብን እና ሀገርን ለመታደግ ለመከላከያ ሠራዊትና ለመንግሥት የሚያስፈልገውን ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን እየገለጸ በየአካባቢው ያላችሁ አባላቱ ሁሉ ከሕዝብ ጋር እንድትቆሙና የበኩላችሁን ሃላፊነት ሁሉ እንድትወጡ አደራ ይላል፡፡

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥቃት መካችነት ከአስከፊ ጦርነት ትወጣለች ! ኢትዮጵያ አንድነቷ ተከብሮ ለዘላለም ትኑር! ኢሕአፓ ለተሻለ ነገ! ጥቅምት 26/2013 ዓ.ም…. አዲስ አበባ! Phone :0911405427/0946240724/0911393535 Email:eprp@eprp-ihapa.com

3 Comments

  1. “የተጀመረው ጦርነት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ኪሳራ ሳያበዛ መጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡” ማለትም ቁጠባዊ ጦርነት!
    እንዲህም አርጎ “ምክር” የለ፣ In TIGRIGNA we say, ኣበያሎኻ ዘይበልዎስ፣ ኣብዙይ ኣሎኹ ይብል…!

  2. ኢህአፓ እናመሰግናለን፤፡
    ግጭትም ይሁን ጦርነት እያደር ሲመጣ ሌሎች መዘዞች ይዞ መምጣቱ አይቀርም፡፡ አሁን አሁን አሳሳቢው ጉዳይ የሚመስለኝ ይቺን “የግጭት” አጋጣሚ በመጠቅም የክልል አስተዳደር ወሰን በጉልበት ለመቀየር ፍላጎቶች መታየት ጀምረዋል፤፤ እጂግ አደገኛ ነው! እደግመዋለሁ እጅግ እጅግ አደገኛ! You know what I mean?

  3. I beg to differ, this is not a war between brothers and EPRP should know that given its experience with EPLF. One look at the hundreds thousands innocent Amharas that were murdered and still being murdered by the policies of EPLF is proof enough it is not. One can only be brother if the other considers you a brother and treats you as such. If the other believes you are the enemy there is no one sided brotherhood. It is one of the defeatist and stupidest beliefs that characterizes some Ethiopians and certainly EPRP. EPLF and its supporters have always regarded Amharas and genuine Ethiopians as the enemy as everyone should know unless they are in denial. So have some guts and call it as it is, a war between two bitter enemies intent on advancing there benefits. Sorry to hear EPRP which its members were brutally murdered by EPLF call EPLF brothers. The blood of your members which were your brothers should choke you.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.