“ያሳምራል ያሉት ኩል ዓይን አጠፋ” (በምዕራብ ወለጋ በአማሮች ላይ የተካሄደውን ጭፍጨፋ በጥብቅ እናወግዛለን!)

ጥቅምት ፳፫ ቀን ፪ ሺህ ፲፫ ዓ. ም

EPRP 3 “ያሳምራል ያሉት ኩል ዓይን አጠፋ”  (በምዕራብ ወለጋ በአማሮች ላይ የተካሄደውን ጭፍጨፋ በጥብቅ እናወግዛለን!)ምነው እንደዚህ ከሰብአዊነት ተራ ወጣን? እስከመቼስ ይህ ዓይነቱ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ይፈጸማል? ኢትዮጵያስ እስከመቼ የደም መሬት ሆና ትቀጥላለች? እኛስ እስከመቼ የሀዘን መግለጫ እያወጣን እንዘልቃለን? በምእራብ ወለጋ የተከሰተው የሰሞኑ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሕይወታቸውን ለነጠቃቸው ኢትዮጵያውያን የአማራ ተወላጆች የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለጽን በአገራቸው ላይ በተለያዩ አካባቢዎች ግፍ እየደረሰባቸው ካሉ የአማራ ተወላጆች ጎን ሁሉም የኢሕአፓ አባላት እንደምንቆም በአንክሮ እንገልጻለን፡፡ ፓርቲያችን፣ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ሰሞኑን በአማራ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው አስከፊ ጭፍጨፋ እጅግ ያሳዘነውና ያስቆጣው መሆኑን በመራር ሁኔታ ይገልጻል።  ኢሕአፓ በጭፍጨፋው ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለጸ፤ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውም መጽናናቱን ይመኛል።

የሟቾች ቁጥር የጥቃቱን ግዝፈት ያመላክት እንደሆነ እንጂ የወንጀሉ መፈጸምና ያለመፈጸም ሊጠቀስ የሚገባው ጉዳይ አይደለም፡፡ መንግሥት ግፍ ለሚፈጸምበት አንድ ዜጋውም ቢሆን ተቆርቋሪነትን ማሳየት ግዴታው ነው፡፡ እየሆነ ያለው ግን፣ እጅግ የተለየ ነው፤ ያለፈውን ሁሉ ትተን በወራት ውስጥ የተከሰተውን ሰቆቃ ማሰብ ብቻውን ኢትዮጵያዊነታችንን እንድንጠራጠር አድርጎናል፡፡ ከሰብአዊነት ውጭ የሆነው ክስተት አብሮ የመኖርንና የመዋለድን ታሪክ የፋቀ መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡ ለመሆኑ ይህ ሁሉ ሲሆን መንግሥት ምን እያደረገ ነው? በቃል ከመናገር የዘለለ የሕግ የበላይነትን የማስጠበቅ ግዴታውን ሲፈጽ የማይታይ መንግሥትስ ምን ስም ይሰጠዋል?

ይህንን መሠል ግፍና እልቂት አንድ ቦታ ላይ “በቃ!” ማለት ይገባል፡፡ “ሳይርቅ በቅርቡ መመለስ፣ ሳይደርቅ በእርጥቡ ማቃናት” ሲገባ፣ “በእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽን” እንደተባለው ተመጣጣኝ ርምጃ ወስዶ ወንጀልን በጅምሩ ማስቆም ሲገባ፤ በቸልተኝነት ማለፍ አሁን ለደርስንበት ቅጥ-ያጣ ሁኔታ እንዳደረሰን መቀበል ግድ ይሆናል፡፡ በወለጋ ይህ ጥቃት የተፈጸመው ዛሬ አይደለም፣ በባሌና በአርሲ፣ በቤኒሻንጉልና በጉራፈርዳ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ዜጎች በዘራቸው የተነሳ ሲጨፈጨፉ ዓመታትን እያስቆጠረ ነው፡፡ እነዚያ ሁሉ ጥቃቶች ግን ይኸ ነው የሚባል ምላሽ አልተሰጣቸውም፡፡  የሕግ የበላይነትም በአግባቡና በትክክለኛው መጠንና ልክ ሲከበርም አላዬንም፡፡

ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና ሕዝቡ ተቃውሞአቸውን በተደጋጋሚ ቢያቀርቡም፣ በርካታ መግለጫዎችን ቢሰጡም፣ መንግሥት ጆሮ መስጠቱን ያመላከቱ ተግባራትን ሲፈጽም አልታየም፡፡ ይህ ጆሮ-ዳባ ልበስ አካሄድም የፖለቲካ ፓርቲዎች ተፎካካሪነታቸው የቃላት መሆኑንና ሃሳባቸው የሚደመጥ ለመሆኑን እንዲገነዘቡና ሕዝብም በለውጡ ላይ ያለው አመኔታ እየቀነሰና እየተሟጠጠ እንዲሄድ ከማድረጉ በስተቀር ያስከተለው ፋይዳ የለም፡፡

ችግሩ በቀጣይነት እየከፋ የሄደባቸው የኦሮሞና የአማራ የፖለቲካ ድርጅቶች አስር ወር ሙሉ ሲሰበሰቡ ቢቆዩም ያመጡት ውጤት የለም፡፡ ይልቁንም በእነዚህ አስር ወራት ውስጥ፣ ሕዝቡ በዘሩ ምክንያት እየተገደለና እየተፈናቀለ፣ ብሎም እየተሰደደ ነው፡፡ በመንግሥት በኩል፣ በሽፍንፍን ለማለፍ የሚቻል ችግር ያለመኖሩን መረዳት የተቻለ አይመስልም፤ ፍርጥርጥ ያለው እውነት እንዲወጣም “አካፋን አካፋ፣ ዶማንም ዶማ” ማለት አልተቻለም፡፡ አንዳንድ የመንግሥት አካላት ችግርን ከማቃለል ይልቅ የችግሩ አካላት፣ የፍጅቱ አራጋቢዎች ሲሆኑ መስተዋላቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ታዲያ ይህ በሆነበት እውነታ መንግሥት በቆራጥነት የሕዝቡን ደህንነት ይጠብቃል ብሎ ለማመን እንዴት ይቻላል? ለመሆኑ ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲን ሊያመጣ ተስፋ የተጣለበት ለውጥስ “ያሳምራል ያሉት ኩል ዓይን አጠፋ” እንዲሉ ለምን ሆነ?

ኢሕአፓ በተደጋጋሚ ባወጣቸው መግለጫዎች የዜጎችን መጨፍጨፍና መሰደድ ተቃውሟል፡፡ መንግሥት ትክክለኛ ሚናውን እየተጫወተ ሳይሆን በአንዳንድ ሁኔታዎች በሚነደው እሳት ላይ ቤንዚን የመጨመር ክስተቶችን ሊያቆም እንደሚገባና የሕግ የበላይነትን ማስከበር እንደሚገባው አሳስቧል፡፡ ሆኖም ሁኔታዎች እየተሻሻሉ ሳይሆን እየከፉ መሄዳቸው ይስተዋላል፡፡ የዜጎችን ሰቆቃ እያዳመጡ ትርጉም አልባ ጩኸት መጮህ ይሰለቻል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ውግዘትና ሱባኤ የሕዝብ ጸሎትና ምህላም እነሆ የኢትዮጵያን ስቃይ ለፈውሱ እንዳልቻሉ ተመልክተናል፡፡ እናም እሹሩሩ ሊበቃ ይገባል! ጥፋተኞች ተገቢውን ቅጣት ሊያገኙ፤ ሕዝቡም እፎይ ሊል ያስፈልገዋል፡፡

በትናንትናው ዕለት የተፈፀመው ፍጅት በዓይነቱ ለየት ያለ መሆኑ ታውቋል፤ ሕዝብን ከቤቱ ለስብሰባ አስወጥቶ በቦንብና በጥይት ማጋየቱ፤ ቤትና ንብረት ማቃጠሉ… በርካቶች መግለጫ እንዲያወጡ አድርጓል፡፡ ሆኖም ይህ ቋት አይሞላም፤ ከዚህ ቀደም የተከሰቱ እልቂቶችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ከንግግር ያለፈ ትሩፋት አላመጡም፡፡ ይልቁንስ ሁኔታውን ከስሩ መመርመርና በዓይነቱ ለየት ያለው ዘር-ተኮር ጭፍጨፋ (የዘር-ማጥፋት) እንዲከሰት ያደረገው ሁኔታ ምን እንደ ነበረ እውነተኛውን ምክንያት ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ ሕዝብ “ትታችሁን አትሂዱ! ሊጨርሱን ነው!…” ወዘተ እያለ ሲማጸን “ታዝዣለሁ…አልቆይም!” በማለት አካባቢውን የለቀቀው የሀገር መከለካከያ ሠራዊት ሃላፊነቱን መወጣት ለምን አቃተው? ተዕዛዙን ያስተላለፈውስ ማነው? የመከላከያ ሠራዊቱን እግር ተከትሎ የታጣቂው ሃይል ህዝብን ስብሰባ ጠርቶ የመፍጀት ግጥምጥሞሹስ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? የቦንብና የመሳሪያ እሩምታ ሲወርድና የሕዝብ ሰቆቃ አየሩን ሲሞላው የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይል ለምን አልሰማም? የትስ ሄዶ ነበር? …. ለሚሉት ጥያቄዎች ትክክለኛውን መልስ በመፈለግ እውነተኛ ፍርድ መስጠት እና የሕግ የበላይነትን ለዘሌቄታው ለማስከበር ይቻል ዘንድ የማያወላዳ ውሳኔ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

ኢሕአፓ ይህ የግፍ ተግባር በአስቸኳይ መቆም ይኖርበታል የሚል ጽኑ አቋም አለው፡፡ ወንጀለኞችም ታድነው ለፍርድ እንዲቀርቡ ጥሪውን ያስተላልፋል። ሀገራችን ኢትዮጵያም አሁን ከምትገኝበት አስከፊ የጸጥታ ሁኔታ ወደተሻለና ወደተረጋጋ ሁኔታ እንድትመጣና ሰላም እንዲሰፍን ኢሕአፓ የሚከተሉትን ሰባት ነጥቦች ወይም የመፍትሔ ሃሳቦች ያቀርባል።

  1. ኢሕአፓ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ከምንጊዜውም የጠነከረና የሕዝብ ወገናዊነቱን የሚያስመሰክር አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ ያሳስባል፡፡ መንግሥት ያለ ምንም ማወላወል የሕግ የበላይነትን እንዲያረጋግጥና በወንጀለኞች ላይ ያለማመንታት እርምጃ እንዲወስድ በአንክሮ ያሳስባል፡፡
  2. ጽንፍ በረገጠ የዘረኝነት አመለካከት እና ጥላቻ የተነሳ ለተሰዉ ኢትዮጵያን መንግሥት የሀዘን ቀን እንዲሰይምም ኢሕአፓ ይጠይቃል፡፡ በሀገራችን ውስጥ ሰላም እንዳይሰፍን፣ ኢትዮጵያን ደካማ ሀገር እንድትሆን ያላሰለሰ ሚና በሚጫወተው ሕወሃት መራሹ ኃይል ላይም የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድ እንጠይቃለን፡፡
  3. በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉና የአንድን ብሔር የበላይነት መልሰው ለማስፈን የሚጥሩ አክራሪ “የተረኝነት ስሜት” ከተጠናወታቸው ብሔርተኞች ራሱን እንዲያጸዳ እያሳሰብን፤ ከዚህ ቀደም እንደሚደረገው በሕግ ማስከበር ሥርዓትና ሂደት በማሳበብ አጥፊዎች ምንም ሳይደርስባቸው ለዓመታትና ለወራት የዘለቀ የፍትሕ መጓተት በፍጹም ሊኖር እንደማይገባ ኢሕአፓ ለመግለጽ ይገደዳል፡፡
  4. የኢትዮጵያ ሁኔታ እንዲህ ከድጡ ወደ ማጡ እያሽቆለቆለ እና ወደየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል መንቀሳቀስ አስጊ በሆነበት ወቅት፣ የሰላም እጦት አንገብጋቢ በሆነበት ነባራዊ ሁኔታ ላይ፣ አገራዊ ምርጫ የሚደረግበትን ምህዳር ማሰብ እጅግ ከባድ በመሆኑ ሊታሰብበት እንደሚገባ በአንክሮ ይገልፃል፡፡
  5. በሀገራችን ውስጥ ለተከሰቱት በርካታ ችግሮች ምንጩና መሠረቱ በሥራ ላይ ያለው ሕገ-መንግሥት በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ ሕዝቡን ያሳተፈ የሕገ-መንግሥት ጉባዔ በመጥራት ሠረታዊ ማሻሻያ እንዲደረግ በድጋሚ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
  6. የሀገራችንን ምስቅልቅል ችግሮች ፈር ለማስያዝና ዘላቂ ሰላምን እውን ለማድረግ ባለድርሻዎችን የሚያሳትፍ ሃገራዊ ውይይት በአስቸኳይ እንዲጠራና የብሄራዊ መግባባት ሂደትም እውን እንዲሆን አበክረን እንጠይቃለን።
  7. መንግሥት አስቸኳይ እርምጃ የማይወስድ እና ጉዳዩን በማለባበስ ለማለፍ የሚሞክር ከሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቆመናል የሚሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገራችን የመንግሥትን ያህል ሃላፊነት ያለብን መሆኑን በመገንዘብ ግዴታችንን ለመወጣት መምከርና የጋራ ጠንካራ ሕብረ-ኃይል ማቋቋም እንዳለብን ኢሕአፓ ያሳስባል፡፡

በመጨረሻም፣ በዚህ አጋጣሚ፣ በተደጋጋሚ የአብረን እንሥራ መልዕክታችንን ኢትዮጵያ እንደ አገር መኖርና መቀጠል እንዳለባት ከሚያምኑ አገር ወዳድ ኃይሎች ጋር በመሆን፣ አክራሪ ብሔርተኞችን መታገል የሚችል ጠንካራ ኃይል (የጋራ ንቅናቄ ወይንም መድረክ) መመሥረት አስፈላጊነቱንና ወቅታዊነቱን በማመን ጥረቱንም በመጀመር ሀገርና ሕዝብን በጋራ እንድንታደግ ኢሕአፓ ጥሪውን ያቀርባል።

ኢትዮጵያ አንድነቷ ተከብሮ ለዘላለም ትኑር!

ኢሕአፓ ለተሻለ ነገ!

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም…. አዲስ አበባ!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.