ምዕራብ ወለጋ፡ ግድያው የተፈጸመው ስብሰባ ተብለው በተጠሩ ሰዎች ላይ ነው ተባለ

abiyየኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ባልቻ በምዕራብ ወላጋ ትናንት የተገደሉት ሰዎች ለስብሰባ በተጠሩበት ስፍራ ነው አሉ።

የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ጉሊሶ ወረዳ፣ ጋዋ ቃንቃ ቀበሌ በሰላማዊ ዜጎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት የሰዎች ሕይወት ማለፉን አስታውቆ ነበር።

አቶ ጌታቸው ለቢቢሲ እንደተናገሩት በሐሰተኛ መልኩ ነዋሪዎች ለስብሰባ ከሰበሰቡ በኋላ በተወረወረባቸው ቦምብ ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል።

“በኦነግ ሸኔ ስም የሚንቀሳቀስው ቡድን ትናንት በስበሰባ ስም ሰዎችን ከሰበሰቡ በኋላ ቦምብ ወርውረውባቸው ጉዳት መድረሱን የሚጠቁም መረጃ ነው ያለን” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ሕዝብ በአንድ ቦታ ሰብስቦ በቦምብ ማቃጠል ለምን እንዳስፈለገ ግልጽ አይደለም። ጥቃቱ እጅግ ጭካኔ የተሞላበት ነው” ብለዋል።

ጥቃቱ የተፈጸመው ከምሽቱ 12 ሰዓት አከባቢ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ጌታቸው፤ “ቦምቡን የወረወሩት ሐሰተኛ ስበሰባ የጠሩት ናቸው” በለዋል።

አቶ ጌታቸው በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው መረጃ አጣርቶ የሚልክ ቡድን ወደ ሥፍራው ተልኳል በማለት በጥቃቱ የተገደሉ ሰዎች አሃዝ ከመጥቀስ ተቆጥበዋል።

“የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ እየተጠቀሰ ነው። ነገር ግን ትክክለኛውን ቁጥር ለማወቅ በአካባቢው ያለው አካል አጣርቶ እስኪልክልን እየተጠባበቅን ነው” ብለዋል አቶ ጌታቸው።

የኦሮሚያ ክልል መግለጫ

የኦሮሚያ ክልል ዛሬ ጠዋት ላይ ባወጣው መግለጫ፤ “ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ሕይወታቸው እንዲያልፍ ባደረገው የኦነግ ሸኔ ቡድን ላይ እርምጃ ይወሰዳል” ሲል አስታውቆ ነበር።

“ትናንት በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ጉሊሶ ወረዳ፣ ጋዋ ቃንቃ ቀበሌ ጨለማን ተገን በማድረግ በተፈጸመው የሽብር ጥቃት ሰላማዊ ዜጎች ጭካኔ በተሞላበት መንገድ በአንድ ስፍራ ሕይወታቸው እንዲያልፍ ተደርጓል” ይላል የክልሉ መግለጫ።

ለግድያው ተጠያቂ ነው ያለው ቡድን በሕዝቡ ላይ አሰቃቂ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ የክልሉ መግለጫ ይጠቁማል።

ክልሉ በመግለጫው ምን ያክል ሰዎች በምን አይነት ሁኔታ እንደተገደሉ ያለው ነገር የለም።

“የጥፋት ኃይሎቹ መንግሥት የፖለቲካ እና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት እየሠራ ባለበት ወቅት በተቃራኒው በመቆም ጭቃኔ የተሞላበት ተግባር በሕዝቡ ላይ እየፈጸሙ ነው” ብሏል።

ክልሉ በመግለጫው፤ “የኦነግ ሸኔ ሽፍታ ህወሓት ጋር በመሻረክ በኦሮሚያ ክልል እና በአገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት እንዳይኖር ሲሰሩ ቆይተዋል” ብሏል።

የገቡ የጦር መሣሪያዎችን በመጠቀም በጸጥታ ኃይሎች፣ በመንግሥት ሠራተኞች እና በማኅበረሰቡ ላይ ግድያ መፈጸሙን የኦሮሚያ ክልል ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ድርጊቱ ሕብረተሰቡ ላይ የሥነ ልቦና ጫና እንደፈጠረ እንዲሁም የማኅበረሰቡ የእለት ከእለት ሕይወት በስጋት እንደተሞላም ተገልጿል።

በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ ሕፃናት፣ ሴቶች፣ አረጋውያን እና ወጣቶች መገደላቸውን እና የአካል ጉዳትም እንደደረሰባቸው በመግለጫው ተጠቅሷል።

ቡድኑ፤ ሰዎችን ጠልፎ በመውሰድ ጉዳት ሲያደርስ መቆየቱን የጠቀሰው መግለጫው፤ “በተለያዩ ጊዜያት የጸጥታ እና የአስተዳደር አካላት በተመሳሳይ መንገድ ጫካ ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸው እንዲያልፍ ሲያደርግ ቆይቷል” ብሏል።

የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የሕዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ፤ ሕዝቡን ባሳተፈ ሁኔታ የሕግ የበላይነትን የማስከበር ሥራ እያከናወነ መሆኑም ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ እርምጃ ይወሰዳል ስለማለታቸው

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ማንነትን መሠረት ባደረጉ ጥቃቶች ማዘናቸው በፌስቡክ ገፃቸው ገልፀዋል።

“የኢትዮጵያ ጠላቶች፤ “ወይ እኛ እንገዛለን፤ ወይ ሀገር አትኖርም” ብለው ተነሥተዋል። ለዚህም የጥፋት ዐቅማቸውን ሁሉ እየተጠቀሙ ነው። አንደኛው ዒላማቸውም የሕዝባችንን ቅስም መስበር ነው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

“ግራ ቀኝ የሚያውቁ ሰዎችን እየሰበሰቡ በማሠልጠንና በማስታጠቅ በየአካባቢው ማንነትን መሠረት ያደረገ አረመኔያዊ ጥቃት ማድረስ” ጠላቶች ያሏቸው ሰዎች አላማ ነው ሲሉ በመግለጫቸው አትተዋል።

“መንግሥት በተለያዩ ቦታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ ያላቸውን ጥፋቶች በቅድሚያ መረጃ ሰብስቦ ርምጃ በመውሰድ ሲያከሽፍ ቆይቷል። ነገር ግን ያለፈው ሥርዓት ያወረሰንን ቀዳዳዎች ሁሉ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ደፍኖ መጨረስ አልተቻለም” ይላል የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ኦፊሴላዊ ገፅ ላይ የሰፈረው መልዕክት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጥፋት ኃይሎች ያሏቸው ከውጭና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ከሚገኙ ሰዎች ትብብር እየተደረገላቸው ነው ሲሉም ወቅሰዋል።

አክለውም “የጸጥታ አካላት ጥቃቱ ወደተፈጸመበት አካባቢ ተሠማርተዋል። ርምጃም እየወሰዱ ነው። በቀጣይም የሕዝባችንን ደኅንነት ለማስጠበቅ መንግሥት የመንግሥትነቱን ሥራ በቁርጥና በጽናት ይሠራል” ብለዋል።

የክልሉ ፕሬዝደንት መልዕክት

የክልሉ ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳም በዜጎች ላይ ለደረሰው ጥቃት “ጥልቅ ሃዘኔን እገልጽለሁ” ያሉ ሲሆን “በኦነግ ሸኔ አሸባሪ ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለው ውጤታማ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ላረጋግጥ እወዳለሁ” ብለዋል።

ፕሬዝደንት ሽመልስ “እንደዚህ አይነት የፈተና ወቅት የሕዝቦችን ወንድማማችነትና በጽናት አብሮ በመቆም ፈተናን የማለፍ ልምድን ያጠናክራል እንጂ ጠላት እንደተመኘው ሕዝቦችን የሚያባላ ፈጽሞ አይሆንም” ብለዋል።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ መግለጫ

የአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ባወጣው መግለጫ፤ ትላንት ምሽት የተፈጸመው ጥቃት መጠን እና ዝርዝር ሁኔታዎችን ከፌደራልና ከክልሉ መንግሥት ጋር በመተባበር እየተጠራ ነው ብሏል።

“በዚህ ጭካኔ በተሞላበት ድርጊት የአማራ ሕዝብና ድርጅታችን የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ክፉኛ አዝኗል፤ ተቆጥቷል። ይህን ድርጊት የሚያወገዝ ከመሆኑም በላይ አጥፊዎቹ እንደየሥራቸው በሕግ አግባብ ሊዳኙ ይገባል ብለን እናምናለን” ሲልም መግለጫው አክሏል።

BBC

1 Comment

  1. አረ ተዉ አትቀልዱብን ሺመልስ አብዲሳ አዛኝ ሁኖ ነዉ መግለጫ የሰጠዉ ወይስ ኮንፊዩዝ በሚለዉ ዘዴዉ ኮንፊዩዝ ሊያደርገን ነዉ ጠ/ሚኒስተሩም እንዲሁ ቀልዳችሁን ተዉና እናንተም በስልጣን እንድትቆዩ ኢትዮጵያዊም እንዳይታረድ የተግሬዎችን ህገ መንግስት ቀዳችሁ ጣሉ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.