/

እውን አማርኛ፤ ከኦሮምኛ የመጣ ቋንቋ ነውን? (ለበፍቃዱ ዘ. ኃይሉ በኩል)

ከሁለት ሳምንት በፊት እንደ አውሮፓ አቆጣጠር የካቲት 1፥ 2017፤ የፌስቡክ ጓደኛዬ በፍቃዱ ዘ. ኃይሉ በፌስቡክ ገጹ ላይ “ይህንን በድጋሜ ማጋራት አስፈላጊ ይመስለኛል” ከሚል ማሳሰቢያ ሥር የሚከተለውን አስፍሮ ነበር፡፡

«…ዶናልድ ሌቨን (ዶ/ር) በሠራው አንድ ጥናቱ ‹አማርኛ የተፈጠረው የኦሮሞ ተወላጆች ግዕዝ ለመናገር ሲሞክሩ ነው› በማለት ያትታል፡፡ የመርጌታ ግሩም ተፈራን ትርክት ማመን ከቻልን ይህ እውነት ሊሆን ይችላል፡፡ ዶናልድ ሌቪን የአማርኛ ቋንቋ ቅርፅ (Syntax) የኩሽ ቋንቋዎች ባሕሪ ያለው መሆኑን ጠቅሶ ነው እንዲያ ያለው፡፡ ባሕሩ ዘውዴም ‹‹[አማርኛ] ተገንጥሎ ወጥቷል ተብሎ በጥቅሉ ከሚታመንበት ሴማዊው ግዕዝ ይልቅ ከኩሻዊው ኦሮምኛ ጋር ብዙ የሚጋራው ጠባይ አለው›› ብሎ ጽፏል፡፡…»

oromo and a mharicገና ጽሑፉን እንዳየሁት ድካም ተሰማኝ፡፡ ለምን ማለት ጥሩ ነው፤ ገና ሳየው የሆነ ነገር ማለት እንዳለብኝ ስለገባኝ እና ማለት ያለብኝንም ዝም ብዬ በግምት እና በመሰለኝ መወርወር ሳይሆን እውነትን ብቻ ይዤ ማቅረብ ስለሚገባኝ፤ እውነትን የያዘ ነገር መጻፍ ደሞ ቀላል ባለመሆኑ ገና ከመጀመሪያው አድካሚ ሥራ  እንደሚጠብቀኝ በመረዳቴ ነበር መድከም ግድ የሆነብኝ፡፡ በመጨረሻ ግን የጻፍኩት ጽሑፍ አማርኛን በተመለከተ መታወቅ ካለባቸው ጉዳዮች ዋና ዋናዎቹን በጥቂቱም ቢሆን የሚዳስስ በመሆኑ ድካሜ ወደ ብርታት ተቀይሮ ደስ ብሎኛል፡፡

በነገራችን ላይ እኔ አይደለም የኢትዮጵያ፤ የዓለም ቋንቋዎች ግንኙነት እና ዝምድና የሚስበኝ እና የሚያስደንቀኝ ሰው ነኝ፡፡ ሌላው ይቅርና “ምስጢር” የሚለው የግእዝ ቃል፤ በአማርኛ “ሚስጥር”፣ በግሪክ “ሚስቲሪዮ”፣ በላቲን “ሚስትሪዮ/ሚስተሪዩም”፣ በሮማንያ “ሚስጤር”፣ በጣሊያንኛ “ሚስተሮ”፣ በእንግሊዝኛ “ሚስትሪ” ከመሆኑም ሌላ በብዙ የአውሮፓ ቋንቋዎች ተቀራራቢ ቃል መያዙ ራሱ ባሰብኩት ቁጥር ያስደንቀኛል፣ ያስደስተኛል፡፡ ክርስትና ሲጀመር መለኮታዊውን ሚስጥር ወይም ሚስጥረ ስላሴ የምንለውን  ጉዳይ ለመግለጽ ስለተጠቀሙበትና ያኔ ክርስትናን የተቀበሉ ሁሉ ቃሉን ስለተጋሩት ይሆንን የሚል ሃሳብም ይመጣብኛል፡፡

ወዳገራችን ቋንቋዎች ስንመጣም፤ አማርኛና ኦሮምኛ ይቅርና ግእዝ እና ኦሮምኛ ብዙ የጋራ ቃሎች እንዳሏቸው አምናለሁ፡፡ ለምሳሌም ቁር (ብርድ)፣ ፈውስ፣ እምነት፣ባቄላ/ቡቃያ እና ሌሎችም አያሌ ቃሎች በግእዝና በኦሮምኛ አስገራሚ ተመሳሳይነት/አንድነት እንዳላቸው ተገንዝቤአለሁ ይሁንና ሰዎች የዘመኑን የታሪክ እና የፖለቲካ እብደት ተከትለው ስለቋንቋዎቻችን የሚጽፉትን ውሸት መቀበል አይሆንልኝም፤ ከመኮነንም ወደኋላ አልልም፡፡ ይህ ጽሑፍም የዚህ አስተሳሰቤ ነጸብራቅ እንደሆነ ይያዝልኝ፡፡

በመጀመሪያ በፍቃዱ የቋንቋ ቅርፅ (‘ሲንታክስ-syntax’) ሲል በአንድ ቋንቋ ዐረፍተ ነገር ውስጥ ያሉ ቃሎችን የአደራደር ቅደም ተከተል ሊል ፈልጎ መሆኑን ማረጋገጥ ነበረብኝ፡፡ በፍቃዱ የቋንቋ ቅርፅ (‘ሲንታክስ-syntax’) ሲል የጠራው ቃል በቋንቋው ዓለም ያለውን ትርጉም ለማየት ሞከርኩ፡፡ የአንድን ቋንቋ የዐረፍተ-ነገር አወቃቀር ሥርዐት በተለይም ቃሎች በዐረፍተ-ነገሩ ውስጥ ያላቸውን አደራደር (ቅደም ተከተል) እንደሚያመለክት ተረዳሁ፡፡ ታዲያ እንደዚህ ከሆነ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በአፍ መፍቻነት ከሚያገለግሉ ሴማዊ ቋንቋዎች ውስጥ የዐረፍተ ነገር አወቃቀር ሥርዐቱ ከኦሮምኛ የተለዬ ቋንቋ አለን? አማርኛን ብቻ ለይቶ መጥቀስ ለምን አስፈለገ? ጉዳዩ የዐረፍተ ነገር አወቃቀር ሥርዐት ከሆነ አማርኛ ብቻ ሳይሆን ከግእዝ ውጪ ያሉት የኢትዮጵያ ሴማዊ ቋንቋዎች በሙሉ ኦሮሞዎች ግእዝ ለመናገሩ ሲሞክሩ የተፈጠሩ ናቸው መባል አለበት ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም በቋንቋ ሳይንስ መሠረት የኢትዮጵያ ሴማዊ ቋንቋዎች በመባል ከሚታወቁት 15 ቋንቋዎች ውስጥ ከኩሽ ቋንቋዎች የተለዬ የዐረፍተ ነገር አወቃቀር ያለው ግእዝ ብቻ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ለምን “ግዕዝ” ሳይሆን “ግእዝ” ብዬ እንደምጽፍ ሌላ ግዜ አብራራለሁና ላሁኑ ሳትቀየሙኝ እንዳላያችሁ እለፉት፡፡

ዝርዝሩን በሰፊው ማየታችንን እንቀጥል፡፡ በዓለማችን ላይ ሰባት ሺ የሚሆኑ ቋንቋዎች ይገኛሉ። በነዚህ ሁሉ ቋንቋዎች ዐረፍተ ነገሮች የሚዋቀሩባቸው ስድስት ዋና ዋና የሚባሉ የቃል አደራደር መንገዶች አሉ። ይህ ክፍፍል የተዘጋጀው በዐረፍተ ነገር ውስጥ ያሉት ዋና ዋና የንግግር ክፍሎች ማለትም የድርጊት ባለቤት (አድራጊ)፣ ድርጊት ተቀባይ (ተደራጊ) እና ግስ ያላቸውን ቅደም ተከተል መሠረት በማድረግ ነው። ለምሳሌ “አበበ በሶ በላ” የሚለው የአማርኛ ዐረፍተ ነገር ‘አድራጊ-ድርጊት ተቀባይ-ግስ’ የሚለውን የአደራደር ሥርዐት የተከተለ ነው። የመጀመሪያው ቃል “አበበ” አድራጊውን ያመለክታል። ለጥቆ ያለው “በሶ” የሚለው ቃል ድርጊት ተቀባዩን ሲያመለክት “በላ” የሚለው ደሞ ግስ ሲሆን ድርጊት አመልካች ነው።

 

ያለማችን ቋንቋዎች የሚጠቀሟቸው ዋና ዋናዎቹ የዐረፍተ-ነገር አደራደር ሥርዐቶች የሚከተሉት ናቸው።

 • አድራጊ — ድርጊት ተቀባይ — ግስ (ምሳሌ ዐ.ነገር በአማርኛ-አበበ በሶ በላ፤ ቋንቋ-ኦሮምኛ)
 • አድራጊ — ግስ —ድርጊት ተቀባይ    (ምሳሌ ዐ.ነገር በአማርኛ-አበበ በላ በሶ፤ ቋንቋ-እንግሊዝኛ)
 • ግስ — አድራጊ — ድርጊት ተቀባይ (ምሳሌ ዐ.ነገር በአማርኛ-በላ አበበ በሶ፤ ቋንቋ-ግእዝ)
 • ግስ — ድርጊት ተቀባይ — አድራጊ (ምሳሌ ዐ.ነገር በአማርኛ-በላ በሶ አበበ)
 • ድርጊት ተቀባይ — ግስ — አድራጊ (ምሳሌ ዐ.ነገር በአማርኛ-በሶ በላ አበበ)
 • ድርጊት ተቀባይ — አድራጊ— ግስ    (ምሳሌ ዐ.ነገር በአማርኛ-በሶ አበበ በላ)

ከዓለማችን ቋንቋዎች ውስጥ፤ አርባ አምስት ከመቶ የሚሆኑት አንደኛውን መንገድ (አበበ-በሶ-በላ)፣ አርባ ሁለት ከመቶ የሚሆኑት ደሞ ሁለተኛውን መንገድ (አበበ-በላ-በሶ) ይከተላሉ።

የኩሽ፣ የኦሞ፣ እና በኢትዮ-ሴማዊ መደብ የሚካተቱት 14 ቋንቋዎች እንዲሁም ጥንታዊ ግሪክ እና አርመንያ ከላይ በቁጥር አንድ የተመለከተውን (አበበ-በሶ-በላ) የዐረፍተ ነገር አደራደር ሥልት ይጠቀማሉ፡፡ ከነዚህም በተጨማሪ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ3000 እስከ 1000 ዓመተ ዓለም በሜሶፖታሚያ ይነገር የነበረው አካዲያን የተባለው ሴማዊ ቋንቋ ይህንኑ መንገድ ይከተል እንደነበር ይታወቃል፡፡

የሴማዊ ቋንቋዎች መሠረታዊውና ዋናው የዐረፍተ-ነገር አደራደር መንገድ ሥወስተኛው (በላ-አበበ-በሶ) እንደሆነ የቋንቋ ሊቆች ይስማማሉ። ይሁንና ዛሬ ይኸን መንገድ የሚከተሉት ሴማዊ ቋንቋዎች ግእዝ እና ዐረብኛ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ሌሎቹ ሴማዊ ቋንቋዎች ልክ እንደ ኩሽና ኦሞ አንደኛውን መንገድ (አበበ-በሶ-በላ) እንደሚከተሉ እስቲ በምሳሌ እንመልከት፡፡ በአማርኛ “እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” ብንል፤ “እግዚአብሔር” ባለቤት፣ “ሰማይና ምድር” ተደራጊ ወይም ድርጊት ተቀባይ ሲሆን “ፈጠረ” ደሞ ግስ (ድርጊት አመልካች) ነው፡፡ ይኸንኑ ዐረፍተ ነገር ወደ ትግርኛ ስንወስደው፤ “እግዚአብሔር ሰማይን ምድሪን ፈጢሩ” ይሆናል፡፡ በኦሮምኛ ደሞ “ዋቀዮ በንቲዋን ዋቃ ፊ ላፋ ኡሜ” ልንል እንችላለን፡፡ “ዋቀዮ” የዐረፍተ ነገሩ ባለቤት ሲሆን “በንቲዋን ዋቃ ፊ ላፋ” የሚለው ሐረግ “ሰማይንና ምድርን” ይወክላል፡፡ “ኡሜ” ማለት ደሞ “ፈጠረ” ማለት ነው፡፡ ይኸው ዐረፍተ ነገር በግእዝ ሲቀመጥ፤ “ፈጠረ እግዚአብሔር ሰማየ ወምድር” ወይም “ገብረ እግዚአብሔር ሰማየ ወምድር” የሚል ይሆናል፡፡ ወደ ዐረብኛ ሲተረጎም ደሞ “ኸለቀ አላህ ሰማዋህቲ ወአል ኧርደ” የሚል ይሆናል፡፡በዐረብኛ “ኸለቀ” ማለት “ፈጠረ” ማለት ሲሆን፤ “ሰማዋህቲ ወአል ኧርደ” የሚለው ሐረግ “ሰማያትንና ምድርን” የሚል ትርጉም አለው፡፡ ጥንታዊው ዕብራይስጥ እንደ ግእዝና እንደ ዐረብኛ ይኸንኑ መንገድ ይከተል እንደነበር ይታወቃል፡፡ የዛሬው ዘመናዊው ዕብራይስጥ ግን ልክ እንደ ዘመናዊው ግሪክ እና እንደ እንግሊዝኛ በሁለት ቁጥር የተመለከተውን (አበበ-በላ-በሶ) መንገድ ይጠቀማል፡፡

እዚህ ላይ፤ ሌሎች ኢትዮ-ሴማዊ ቋንቋዎች በሙሉ (ዳሃላክ፣ ትግረ፣ ትግርኛ፣ አማርኛ፣ አርጎባ፣ ሐረሪ፣ ስልጤ፣ ወለኔ፣ ክስታኔ፣ ኢኖር፣ ሜስሜስ፣ መስቃን፣ ሰባት ቤት ጉራጌ እና ዛይ) ከግእዝ ተለይተው እንዴት የኩሽና የኦሞ ቋንቋዎችን መንገድ ሊከተሉ ቻሉ የሚል ጥያቄ መነሳቱ ተገቢ ነው፡፡ ብዙ የቋንቋ ሊቆች በኩሽ ቋንቋዎች ተጽዕኖ ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ፡፡ ይሁንና ይህ ሐቅ በራሱ፤ አማርኛ፣ ትግርኛም ሆነ ሌሎች ዛሬ በኢትዮጵያ በአፍ መፍቻነት በማገልገል ላይ ያሉ ሴማዊ ቋንቋዎች ከኦሮምኛ ወይም ከሌሎች ኩሽ ቋንቋዎች የመጡ ናቸው ሊያሰኘን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ከላይ እንደተጠቆመው ዕብራይስጥ ራሱ ጥንት ይጠቀምበት የነበረውን “ግስ-ባለቤት-ድርጊት ተቀባይ (በላ-አበበ-በሶ)” ሥርዐት ትቶ በዘመን ሂደት “ባለቤት-ግስ-ድርጊት-ተቀባይ (አበበ-በላ-በሶ)” ወደሚለው ሥርዐት እንደተቀየረ ይታወቃልና፡፡ ዘመናዊው ግሪክም ጥንት የነበረውን የዐረፍተ-ነገር አወቃቀር ዘዴ ለውጧል፡፡ ዕብራይስጥና ግሪክ የዐረፍተ ነገር አወቃቀር መንገዳቸውን ቀየሩ ማለት የጥንቱ ዕብራይስጥ እና ዘመናዊው ዕብራይስጥ እንዲሁም የጥንቱ ግሪክኛ እና ያሁኑ ግሪክኛ የተለያዩ ቋንቋዎች ሆኑ ማለት አደለም፡፡ እነዚህ ሁለት ቋንቋዎች ያደረጉት የዐረፍተ-ነገር አወቃቀር ለውጥ ጥንት ከነበራቸው የዘር ግንድ አላወጣቸውም፡፡ ዕብራይስጥ እንደገና ከሌላ ቋንቋ መጣ አልተባለም፡፡ ግሪክም፤ የጥንቱ ግሪክ አልን የዛሬው ግሪክ ያው አንድ ቋንቋ ነው፡፡

እናም ምናልባት የኛም ሴማዊ ቋንቋዎች በተመሳሳይ መንገድ ባሳለፉት ዘመን ውስጥ የአወቃቀር ለውጥ አድርገው ሊሆን ቢችልስ? በነገራችን ላይ ግርማ አውግቸው ደመቀ “የአማርኛ አመጣጥ (The Origin of Amharic)” በሚል በጻፈልን የቅርብ ግዚ ሥራው ላይ ቀደም ባሉ ዘመናት የነበሩ የአማርኛ ጽሑፎችን በማጥናት የጥንቱ አማርኛ ልክ እንደ ግእዝ እና እንደ ዐረብኛ የ “ግስ-ባለቤት-ድርት ተቀባይ (በላ-አበበ-በሶ)” የዐረፍተ ነገር አወቃቀር ሥርዐትን ይከተል እንደነበር መስክሮልናል፡፡ መጽሐፉን በሙሉ የማንበብ ዕድል ባላገኝም ዕድሜ ለኢንተርኔት ዘመን ከላይ የጠቆምኩትን ሐቅ በመግቢያው እተሰጠ አስተያየት ላይ ተመልክቻለሁ፡፡ ለማንኛውም ስለ ዓለማችን ቋንቋዎች አመዳደብ እና የዐረፍተ ነገር አደራደር ሥርዐት ተጨማሪ ዝርዝር ማብራሪያ የፈለገ ሰው ‘ኢትኖሎግ (ethnologue)’ የተባለውን ድረ ገጽ መመልከት ይችላል፡፡

“አማርኛ ከኦሮምኛ መጣ ወይም አማርኛን ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ግእዝ ለመናገሩ ሲሞክሩ ፈጠሩት” የሚለው በዶናልድ ሌቨን ተደርሶ በበፍቃዱ ዘ. ኃይሉ የቀረበው ቀልድ ባያስቀኝም አንድ አሳዛኝ ነገር አስታውሶኛል፡፡ ዛሬ ግዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች አማርኛን እና ሌሎችን ቋንቋዎች የሚያዩበት መንገድ የአራምባና የቆቦ፣ የመቀሌ እና የሞያሌ ብቻ ሳይሆን የሰማይና የመሬት ያህል ተራርቆ ይታየኛል፡፡ ብዙ ሰዎች ከአማርኛ ውጪ ያሉትን የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በተመለከተ ትክክል ያልሆነ እና የመሰላቸውን ነገር ለመጻፍ ወይም አስተያየት ለመስጠት ይቅርና የቋንቋዎቹን ስም ለማንሳት እንኳ የብሔረ ብሔረሰቦች አምላክ እባክህ ይቅር በለን የሚል ልመና እንደሚያቀርቡ ሳንታዘብ ቀረን ብላችሁ ነው! ታዲያ አማርኛ ላይ ሲሆን ሰው ሁሉ ከመሬት እየተነሳ እንዴት ደፋር ይሆናል? ምክንያቱ ምን ይሆን ብዬ ስጠይቅ፤ ከጀርባ የሚያሸልም ያልተጻፈ ስምምነት አለ የሚል መልስ የሰማሁ መሰለኝና መላሹ ሰይጣን እንደሚሆን በመገመት ወግድልኝ፣ አርባ ክንድ ራቅ ብዬው ቀጠልኩ፡፡

ለማንኛውም አማርኛን በተመለከተ የሆነ ያልሆነውን ማለት ልክ እንደመተንፈስ ከመቆጠሩ የተነሳ ስለሱ የሚያወራው እና የሚጽፈው ሰው ቁጥር ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦቸ ብዛት በልጦ ጠቅላላ የኢትዮጵያን ሕዝብ ብዛት እንዳያክል እና ለአቆጣጠር እንዳያስቸግር መስጋቴን ልደብቅ አልችልም፡፡ ብዙ ሰው ስለ አማርኛ መጻፉ ባልከፋ ነበር ከእውነት የራቀና መሠረት የሌለው ሲሆን ግን ያስጠይፋል፡፡ በተለይ ፌስቡክ ላይ አማርኛን ከሌሎች ቋንቋዎች ጋር እያነጻጸሩ የሚጽፉ አንዳንድ ሰዎች አማርኛን በተመለከተ  የሚሰነዝሩት አስተያየት የኢትዮጵያን ቋንቋዎች “ሀ- ሁ” ሳይቆጥሩ በባዶው ሜዳ የሚደነፉ አላዋቂዎች መሆናቸውን ይመሰክራል፡፡

በፍቃዱ ዘ. ኃይሉ ከዐረፍተ-ነገር አወቃቀር ሥርዐት ጋር አያይዞ “አማርኛን ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ግእዝ ለመናገር ሲሞክሩ ፈጠሩት” ሲል ያቀረበልን አስተሳሰብ ይሰራል ቢባል እንኳ ለአማርኛ ብቻ ተለይቶ እንደማይሠራ ለማረጋገጥ ከፈለገ ከአማርኛና ከኦሮምኛ ዘለቅ ብሎ የሌሎችን ቋንቋዎችም “ሀ-ሁ” እንዲቆጥር በወንድምነት እንመክረዋለን፡፡ ይኸ ሃሳብ ባጠቃላይ ከግእዝ ውጪ ያሉትን ሴማዊ ቋንቋዎች በተመለከተም እንደማያስኸድ እንዲሁም አማርኛ የቋንቋ አወቃቀሩ ሴማዊ እንደሆነ ለመገንዘብ የሴማዊ ቋንቋዎችን ወሳኝ ባህሪዎች መመልከት ግድ ይለናል፡፡

ሴማዊ ቋንቋዎች አንድ የጋራ የሆነ ባህሪ አላቸው-ከግስ ይነሣሉ (ግስን መሠረት ያደረጉ ናቸው)፡፡ በሴማዊ ቋንቋዎች ውስጥ ከንግግር (ከዐረፍተ-ነገር) ክፍሎች እንደ ግስ ወሳኝ ነገር የለም፡፡ በሴማዊ ቋንቋዎች ሌላ ምንም ቃል ሳይጨመርበት ግሱ ብቻ በቅጥያዎች መልኩን እየለዋወጠ የድርጊቱን ባለቤት፣ የድርጊቱን ጊዜ፣ አዎንታዊ/አሉታዊ መሆኑን ወዘተርፈ የማመልከት ብቃት አለው፡፡ “በላ” የሚለውን መነሻ ግስ ወስደን የሚከተሉትን መመልከት ጥሩ ፍንጭ የሚሰጥ ይመስለኛል፡፡

 • በላ = እሱ በላ፤ ባይገለጽም ባለቤቱ “እሱ” መሆኑን በግሱ ብቻ እናውቃለን
 • በላች= እሷ በላች
 • ልትበላ= እሷ ልትበላ፤ “ልትበላ” የሚለው ቃል የድርጊቱ ባለቤት “እሷ” መሆኗን ብቻ ሳይሆን ድርጊቱን ለመፈጸም ተቃርባ እንደነበር የሚያመለክተን ነገር አለ፡፡
 • ላይበላ፣ ሲበላ፣ እያበላ፣ በልተው፣ አባላ፣ ተበላላ……….

ሌላው የሴማዊ ቋንቋዎች መለያ ደሞ ብዙዎች ግሶች ባለ ሥወስት ሆሄ/ፊደል መሆናቸው እና በብዙዎች ሴማዊ ቋንቋዎች ተመሳሳይነት ያላቸው መሆኑ ነው፡፡ በአማርኛ ቋንቋም ባለ ሥወስት ፊደል ግሶች እጅግ በጣም የተለመዱ ናቸው፡፡ በ “ቀ” ፊደል ከሚጀምሩ ባለ ሥወስት ሆሄ ግሶች መካከል ልጥራ ብል፤ ቀበጠ፣ ቀበለ፣ ቀበረ፣ ቀደደ፣ ቀደመ፣ ቀደሰ፣ ቀወረ፣ ቀወጠ፣ ቀወሰ፣ ቀዘነ፣ ቀዘፈ፣ ቀጠጠ፣ ቀጠለ፣ ቀጠነ፣ ቀጠፈ፣ ቀጠረ፣ ቀጨጨ፣ ቀጨመ፣ ቀየሰ፣ ቀየረ፣ ቀየደ፣ ቀየጠ፣ ቀለለ፣ ቀለመ፣ ቀለደ፣ ቀለበ፣ ቀለዘ፣ ቀለጠ፣ ቀለሰ፣ ቀመመ፣ ቀመሰ፣ ቀመረ፣ ቀመለ፣ ቀነሰ፣ ቀነፈ፣ ቀነተ፣ ቀሰፈ፣ ቀሰረ፣ ቀሠሠ፣ ቀሰተ፣ ቀሸረ፣ ቀፈፈ፣ ቀፈተ፣ ቀሰጠ፣ ቀሰመ፣ ቀቀለ፣ ቀረረ፣ ቀረበ፣ ቀረጠ፣ ቀረፈ፣ ቀተለ፣ ቀተረ እያለ ይቀጥላል፡፡ አይበቃኝም? በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ ያሉትን ባለ ሥወስት ሆሄ ቃሎች በሙሉ ልዘርዝር ብል እስክሪብቶና ወረቀት ብቻ ሳይሆን ዕድሜዬም ላይበቃኝ ይችላል፡፡

ይኸም ብቻ አደለም፤ ሴማዊ ቋንቋዎች ከግስ ተነስተው የሚራቡ እጅግ ብዙ ቃሎች አሏቸው፡፡ ለምሳሌ በአማርኛ ቋንቋ “በላ” ከሚለው ግስ በመነሳት አንድ ሺ የሚሆኑ ርቢ ቃሎችን ማግኘት እንችላለን፡፡ በዚህም መሠረት ከአንድ ቃል ተነስቶ በመራባት አማርኛ በጣም የታወቀ ሲሆን ግእዝ “እነሱ” በሚለው ተውላጠ ስም ለወንዶች እና ለሴቶች የተለያየ አጠቃቀም ቢኖረውም በጠቅላላ የርቢ ቃሎቹ የተወሰኑ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህልም “አበላ“ እና “አስበላ” የሚሉ ቃሎች “አብልዐ” በሚል አንድ ቃል ብቻ ይወከላሉ፡፡

አማርኛና ኦሮምኛ ልክ ዕቃ እንደሚዋዋሱ ጎረቤታሞች ግንኙነታቸው ቃሎችን በመዋዋስ ላይ የተመሰረተ ሲሆን አማርኛ እና ሌሎች ሴማዊ ቋንቋዎች ግን አንድ ቤት ውስ ያለውን ተካፍሎ በጋራ እንደሚበላ ቤተሰብ ከመዋዋስ የዘለቀ መሠረታዊ የቋንቋ ዝምድና አላቸው፡፡ ይኸንንም ለመረዳት ግእዝን፣ አማርኛን እና ዐረብኛን እንደ ምሳሌ በመውሰድ ቀጥለን እንመለከታለን፡፡ እስቲ፤ ከበረ፣ ወለደ፣ ፈታ፣ ተዋሐደ፣ ሰማ እና ከተበ የሚሉት ቃሎች በግእዝ፣ በአማርና እና በዐረብኛ የሚያስተላልፉልንን መልክት እንከታተል፡፡ የሚነግሩንን በጥሞና እናዳምጣ!

የግእዝ እና የአማርኛ አረባብ (በቅንፍ ውስጥ ያለው አማርኛ ነው)፡-

 • ከብረ (ከበረ)፤ ተከብረ (ተከበረ)፤ አክበረ (አከበረ/አስከበረ)፤ ክቡር (የተከበረ)፤ ክብርት (የተከበረች)፤ ክብር (ክብር)፤ አክባሪ (አክባሪ/አስከባሪ)
 • ወለደ (ወለደ)፤ ወላዲ (ወላጂ)፤ አውለደ (አዋለደ/አስወለደ)፤ መወልድ (አዋላጂ)፤ ሙላድ (መውለጃ)፤ ተወልደ (ተወለደ)፤ ውሉድ (የተወለደ)፤ ተወላዲ (ተወላጂ)፤ ወለድ/ወለት (ሴት ልጅ)፤ ወልድ (ወንድ፣ ልጅ)፤ ወልድና (ልጅነት)፤ ልደት (ልደት)፤ ትውልድ (ትውልድ)
 • ፈትሐ (ፈታ)፤ ፈታሒ (ፈቺ)፤ መፍትሕ (መፍቻ፣ቁልፍ)፤ፍትሕ (ፍትሕ)፤ ፍትሐት (አፈታት)፤ ተፈትሐ (ተፈታ)፤ ፍቱሕ (የተፈታ)
 • ዋሐደ (ተዋሐደ)፤ አውሐደ (አዋሐደ፣ አንድ አደረገ)፤ መዋሕድ (የሚያዋሕድ)፤ ውሑድ (የተዋሐደ)፤ ዋሕድና (ውሕደት፣ አንድነት)፤ ተዋሕዶ (አንድ የሆነ)፤ ዋሕድ (አንድ)
 • ሰምዐ (ሰማ)፤ ሰማዒ (ሰሚ፣ የሚሰማ)፤ ተሰምዐ (ተሰማ)፤ ስሙዕ (የሰማ፣ የተሰማ)፤አስምዐ (አስሰማ፣ አስደመጠ)፤ መስምዕ (አስሰሚ)፤ምስማዕ (መስሚያ፣ ማሰሚያ)፤ ተሳምዐ (ተሰማማ)፤ ስምዕ (ስሞታ፣ ስሙልኝ)፤ ስማዔ (ስመ-ጥር፣ ዝነኛ፣ የተመሰከረለት) ፤ ስሙዓት (ዝና)፤ ስምዓት (ዝነኛነት፣ መስማት)
 • ከተበ (ከተበ፣ ጻፈ)፤ ከታቢ (ጸሐፊ)፤ ክታብ (ጽሕፈት)፤ ተከትበ (ተጻፈ)፤ ክቱብ (የተጻፈ)

ከላይ የተጠቀሱት ስድስት ቃሎች የዐረብኛ አረባብ ደሞ እንደሚከተለው ይሆናል (በቅንፍ ውስጥ የአማርኛው ትርጉም ተመልክቷል)፡፡

 • ካቢር (ክቡር)፤ አክባር (ክቡር፣ ኃያል)፤ ታክቢር (ከበሬታ)
 • ወለደ (ወለደ)፤ መውሊድ (ልደት)፤  ማውሉድ (ልጅ)፤ ዊላዳ (ውልደት)፤ ዋላድ (ልጅ)፤ ታውሊድ (ትውልድ)
 • ፈትሓ (ፈታ፣ ከፈተ)፤ ሚፍታሕ (መፍቻ፣ ቁልፍ)፤ ፈቲሓ (መግቢያ፣ መክፈቻ)፤ ሊፈታሕ (መፍታት፣ መክፈት)፤ ፈታሓ (ፈቺ፣ ከፋቺ)
 • ወሕዳ (ውሕደት)፤ ተዋሐድ (ማዋሐድ፣ አንድ ማድረግ)፤ ዋሒድ (አንድ)፤ ሙዋሐድ (የተዋሐደ)፤ ታውሒድ (አንድነት)
 • ሳማ (መስማት)፤ ሳሚ (ዝነኛ)፤ ኢስማ (መስማት)፤ ሰምዔተ (ሰማ)፤
 • ከተበ (ጻፈ)፤ ያክቱቡ (ይጽፋል)፤ ይክቱብ (መጻፍ)፤ ካቲብ (ጸሐፊ)፤ ኪታባ (አጻጻፍ)፤ ኪታብ (መጽሐፍ)፤ ማክቱብ (ደብዳቤ)፤ ማክታብ (ቢሮ፣ ጽሕፈት ቤት)፤ ኢክቲታብ (ምዝገባ)

እንደተባለው አማርኛን ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ግእዝ ለመናገር ሲሞክሩ ከፈጠሩት ከመጀመሪያው ቋንቋቸው (ከኦሮምኛ) ወደ አማርኛ ያመጡት መሠረታዊ የቋንቋ ባህሪ ምንድነው ነው? ለመሆኑ የአማርኛ እና የኦሮምኛ ግንኙነትስ ምን ዐይነት ነው?  እንደኔ እንደኔ መሠረታዊ ግንኙነታቸው ቃሎችን መዋዋስ ነው፡፡ ይኸ ደሞ የቋንቋዎቹ ተናጋሪዎች በነበራቸው ግንኙነት የተፈጠረውን ቁርኝት እንጅ ከአንድ ቋንቋ ቤተሰብ መምጣታቸውን ወይም አንዱ ከሌላው መምጣቱን አያሳይም፡፡ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ተዋደው ቢጋቡ እና አንድ ቤት ውስጥ ቢኖሩ ወደላይ ዘራቸው አንድ ሆነ ወይም ከአንድ ቤተሰብ የመጡ ናቸው ማለት አይደለም፡፡

ግሪክ እና ግእዝ የቃል መዋዋስ ሲነሳ በጣም ጥሩ ምሳሌዎች ሊሆኑን ይችላሉ፡፡ ግእዝ በሕንዳዊ-አውሮፓዊ የቋንቋ መደብ ከሚካቱት ከግሪክ፣ ከሮማይስጥ እና ከላቲን የሚዛመዱ አያሌ ቃሎችን ይዟል፡፡ ስኳር፣ ነጭ ሽንኩርት፣ በርበሬ እና ጠረጴዛ በግሪክ እና በግእዝ ተመሳሳይነት ካላቸው ቃሎች መካከል ሲሆኑ፤ ደባል፣ ክብሪት እና ባንዲራ ደሞ ግእዝ ከሮማይስጥ የተዋሳቸው እንደሆኑ የሚጠቁሙ መረጃዎች አልጠፉም፡፡

የግእዝና የግሪክ የጋራ የሆኑ ቃሎችን መዘርዘር ራሱን የቻለ ሥራ ቢሆንም ጥቂት ቃሎችን በመመልከት ግንዛቤአችንን መገምገም እንችላለን፡፡

ግሪክ……ግእዝ………አማርኛ………..ትግርኛ……..ላቲን………ሮማኒያ……ጣሊያንኛ……እንግሊዝኛ

ፒፔሪ……ፕፕሬ………በርበሬ…….……በርበረ…….…ፒፔሪስ……..ጲጴር………….ፔፔ……….…..ፒፐር

ሳካሪ………ሶከር……….ስኳር/ሽኳር…….ሽኮር…………ሰካሮ…..……ሱከር……..……ዙገሮ……….…ሹገር

ላምፓስ……ለምፓ………ላምባ…………ላምባ………..ላምፓስ…..….ላምፐ…..ላምፓዳ/ላምፓዲና….ላምፕ

ሩዚ……….ሩዝ….….…ሩዝ……………ሩዝ…………..ሪቼ……………ኦሬዝ……….ሪዞ…………..ራይስ

ፓፓስ………ጳጳስ………ጳጳስ……………ጳጳስ…..…….ፖፔ…………..ጳጰ…………..ፓኣፓ………ፖፕ

ኦክያኖስ…ውቅያኖስ.…ውቅያኖስ…..……ውቅያኖስ……፤ኡቺያኑስ………ኦቺያን………ኦቺያኖ………ኦሺን

ሰጠናስ…..ሰይጣን .…..ሰይጣን……….ሰይጣን………….ሳታን………….ሳጣና………ሳተና………ሴተን

ዲፕሎ….ደባል…….…ደባል…..………ደባል…………..ዱፕሉስ………….ዱብሉ………ዱፕሊካቶ….ደብል

ፓስካ…ፓሲካ/ፋሲካ…ፋሲጋ/ፋሲካ…..ፋሲጋ/ፋሲካ.……ፓዚካ………….ጳሲቃ……….ፓዚካ……………….

ስጎርዶ……ስጒርድ…..(ነጪ)ሽንኩርት….(ጸዓዳ)ሽጉርቲ……………………………………………………………………….

ዲያቮሎስ….ዲያብሎስ……………………………………ዲያቦሊ……………ዲያቮል………………….ዴቭል

ግእዝና ግሪክ፤ በግዜው በነበረው ግንኙነት ምክንያት በተለይም ከክርስትና አመጣጥ እና የሃይማኖቱ መረጃዎች ከግሪክ ወደ ሌሎች ቋንቋዎች መስፋፋታቸውን ተከትሎ በግእዝና በግሪክ መካከል የቃሎች መወራረስ ተፈጠረ እንጅ ሰዋሰዋዊ ሥርዓታቸውም ሆነ አገሳሰሳቸው እና የቃል አረባባቸው የተለያየ ነው፡፡ በቅርቡ ዘመን እንኳ አማርኛ ከፈረንሳይኛ ሹፌር፣ ፓርላማ፣ ዳንቴል፣ ዲስኩር፣ አምፖል፤ ከጣሊያንኛ ፋብሪካ፣ ካልቾ፣ አልቤርጎ፣ ፌርማታ፣ ኩሽና፣ አውቶቡስ እና ባልኮኒ እንዲሁም ከእንግሊዝኛ፤ ደርዘን፣ ኮምፒውተር፣ ሶፋ፣ሆቴል የመሳሰሉትን ቃሎች ተውሷል፡፡ ይሁንና ሰው ሁሉ የአዳም ዘር ነው ወይም ቋንቋዎች ሁሉ መጀመሪያ አንድ ነበሩ የሚለውን ድፍን ያለ ሃሳብ እናራምድ ካላልን እና በዛሬው የቋንቋዎች አመዳደብ መንገድ መሠረት አንሂድ ካልን አማርኛ ከፈረንሳይኛ፣ ከጣሊንኛም ሆነ ከእንግሊዝኛ ጋር የቅርብ ዝምድና እንደሌለው የምንጠራጠር አይመስለኝም፡፡

የአማርኛ እና የኦሮምኛ ጉዳይም ይኸው ይመስለኛል፡፡ በነገራችን ላይ ሰዎች አማርኛ ከኦሮምኛ ስለተዋሳቸው ቃሎች እንጅ ኦሮምኛ ከአማርኛ ስለተዋሳቸው ሲያወሩ ብዙ ስላላጋጠመኝ ኦሮምኛ ከአማርኛ ስለተዋሳቸው ቃሎችም ጥቂት ማለት እፈልጋለሁ፡፡

“ኦሮምኔት” የተባለ ድርጅት በቁቤ መንገድ ያዘጋጀውን ኦሮምኛን ወደ አማርኛ የሚተረጉም የቃሎች ዝርዝር መዝገብ ለማየት ሞክሬ ነበር፡፡ በዝርዝሩ ካገኘኋቸው ቃሎች መካከል የሚከተሉት ከአማርኛ የተወረሱ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከአማርኛ እንዳልመጡ የሚያሳይ አሳማኚ መረጃ የሚያመጣ ሰው ካለ ሃሳቡን ከመቀበል ወደኋላ አልልም፡፡ ቃሎችን አንያቸዋ! ከኦሮምኛው ቃል ቀጥሎ ለዚሁ ቃል መሠረት የሆነው ቃል እና ርቢዎቹ በግእዝ እና በአማርኛ (አማርኛው በቅንፍ ውስጥ) ተቀምጠዋል፡፡

 • ማረሻ (maarashaa)- ሐረሰ(አረሰ)፤ተሐርሰ (ታረሰ)፤ሐራሲ (አራሺ)፤ሕርስ (እርሻ)፤ማሕረስ (ማረሻ)
 • ኬላ (kellaa)- ከልአ(ከላ፣ከለከለ፣አገደ)፤ተከልአ(ተከለከለ)፤ከላኢ (ከልካዪ)፤ምክላእ (ኬላ፣ መከልከያ)
 • ፍልጥ (falaxa)- ፈለጸ (ፈለጠ)፤ ፈላጺ(ፈላጪ)፤ፍልጽ (ፍልጥ)
 • ክብሪት (kibriitii)-ክብሪት (ክብሪት)……..ችብሪት (ሮማይስጥ)
 • መለኩሴ (moloksee)- መንኰሰ(መለኮሰ፣ተለየ)፤መነኰስ (መለኩሴ)፤ ምንኩስና (ምልኩስና)
 • ርካሽ (rakasa)- ረኲሰ (ረከሰ፣ ዋጋ አጣ)፤ርኩስ (የረከሰ)፤ ርኲሰት(ርካሽነት፣ ርኩስነት)
 • ሚዛን (mizaana)-መዘነ(መዘነ)፤ መዛኒ (መዛኚ)፤ ሚዛን (ሚዛን)
 • ፈላስፋ (falaasama)- ፈልሰፈ (ፈለሰፈ፣ፈለሰመ)፤ ፍልሱፍ (ፈልሳፊ፣ ፈላስማ)፤ ፍልሳፌ (ፍልስፍና፣ ፍልስምና)…..ፊሎሶፊያ (ግሪክ)
 • በተስኪያን (bataskaana)- ቤተ-ክርስቲያን፣በተክሲያን፣በተስኪያን (“ቤት” የሚለው ቃል በዕብራይስጥ፣ በግእዝ እና በአማርኛ አንድ ሲሆን፤ የግሪኩ ሁለተኛ ፊድል “ቤታ”፣ የዕብራይስጡ ሁለተኛ ፊደል “ቤት” እና የግእዙ ሁለተኛ ፊደል “በ” (መጀመሪያ ላይ ግእዝ አ፣ በ፣ ገ፣ ደ የሚል አደራደር እንደነበረው ልብ ይሏል) አመጣጣቸው “ቤት” ከሚለው ቃል ጋር የተገናኘ ሲሆን የ “በ” ቅርጽም የቤት ወይም የቤት መግቢያ በር ቅርጽ እንዲመስል ተደርጎ መቀረጹ በኔ በኩል ከግምትነት ያለፈ ጉዳይ ነው፡፡
 • መርፌ (marfe)- ረፍአ (ሰፋ፣ጠቀመ)፤ ረፋኢ (ሰፊ)፤ ርፍእ (ስፌት)፤ መርፍእ (መስፊያ፣ መርፌ)
 • ገበያ (gabaa)- ጋብአ (ሰበሰበ፣አከማቸ)፤ ተጋባአ (ተሰበሰበ)፤ መስተጋብእ (መሰብሰቢያ)፤ ጉባኤ (ጉባዬ፣ ገብያ፣ መሰብሰቢያ)
 • በርበሬ (barbaree)- በርበሬ (አማርኛ)፤ ፕፕሬ (ግእዝ)፤ ፒፔሪ (ግሪክ)
 • አረም (aramaa)-አረመ (አረመ)፤ አረም (አረም)
 • ባህር (baarii)-ብሕረ (ተንጣለለ፣ ተዘረጋ)፤ ብሔር (አገር፣ ምድር)፤ ባሕር (ባሕር፣ የውሀ መከማቻ፣ ውሃማ ምድር)
 • አበባ (abbaaoo)- አበበ (አበበ)፤ አበባ (አበባ)
 • መቀስ (maaqassi)-መቈሰ (ቆረጠ፣ቀጠፈ)፤ መቀስ (መቀስ፣ መቁረጪት)

አትደክሙም፣ እንቀጥል? በቃ፤ እኔን ደከመኝ፡፡

 

ሲ. ፉት የተባለው እንግሊዛዊ እንደ አውሮፓዊዎቹ አቆጣጠር በ1913 በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ባሳተመው የኦሮምኛ-እንግሊዝኛ የቃል መፍቻ መጽሐፍ ላይ በጣም ብዙ የአማርኛ መሠረት ያላቸው የኦሮምኛ ቃሎች ሠፍረዋል፡፡ እነዚህን ቃሎች እዛሬው ኦሮምኛ-እንግሊዝኛም ሆነ ኦሮምኛ-አማርኛ ቃል መፍቻ ላይ ሳጣቸው “አዲሱ የቁቤ ትውልድ እነዚያን የነፍጠኛ ቃሎች የት አደረሳቸው?” የሚል ተንኮለኛ ጥያቄ መጣብኝና ሰይጣንና ክፉ ነገር እንዲርቁ በሚል ጸሎት አደረስኩ፡፡

አማርኛ ከኦሮምኛ ከተዋሳቸው ብዙ ቃሎቸ መካከል ለዛሬው ጉዳያችን “አንጋፋ”፣ “ጨፌ” እና “አዱኛ” የሚሉትን እንመልከት፡፡ በነገራችን ላይ ድሮ “አዱኛ” ኦሮምኛ ቃል መሆኑን አላውቅም ነበር፡፡ በአማርኛ ግን ቃሉን ከልጅነቴ ጀምሮ ዐውቀው ነበር፡፡ ለምሳሌ ያላገባ ልጅ ሲሞት ገና አዱኛውን ሳያይ ተቀጬ ይባላል-ደስታን፣ የሕይወትን ጣም፣ ባጠቃላይ ዓለምን ሳያይ ለማለት ነው፡፡ በኋላ “አዱኛ” በኦሮምኛ “ዓለም” ማለት እንደሆነ ለማወቅ ችያለሁ፡፡ እነዚህ ቃሎች በተለመደው የአማርኛ አረባብ መንገድ ሲራቡ አይታይም፡፡ ከሮማይስጥ/ጣሊያንኛ የመጣው “ፋብሪካ” የሚለው ቃል እንኳ ባቅሙ፤ “ፈበረከ”፣ “አፈበራረክ” ለማለት ሲሞክር እንታዘባለን፡፡  “አንጋፋ” ከሚለው “አነገፈ”፣ “አነጋገፍ” ፣ “ንጋፌ”፣ “መንገፍ” እና “መናገፊያ” የሚሉ ቃሎችን እንደርድር ብንል ትርጉም የላቸውም፡፡  አንድን ቃል ነጥሎ መዋስማ በማንኛቸውም ቋንቋዎቸ መካከል ሁልግዜ ያለ ነው፡፡ ከእንግሊዝኛ የመጣው “ኮምፒውተር” የሚለው ቃልም እንዲሁ ነው፡፡ “ኮምፒውተር” ከሚለው ቃል ውጪ ያሉት ተዛማጅ ቃሎች በእንግሊዝኛ እና በአማርኛ የሞያሌ እና የመቀሌ ያህል ይራራቃሉ፡፡ “ኮምፒውተር” የሚለው ቃል እናት፣ አባት፣ እህቶች እና ወንደሞች በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ አይገናኙም፡፡ የእንግሊዝኛወ “ኮምፒውቴሽን” እና የአማርኛ ትርጉሙ “አቀማመር” አንድ ሊሆኑ ቀርቶ አይመሳሰሉም፡፡ ይኸም የሆነው አማርኛን እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች ስላልፈጠሩት ብቻ ሳይሆን አማርኛ እና እንግሊዝኛ በቋንቋ ቤተሰብ ዝምድና ስለሌላቸው ነው፡፡ የኦሮምኛና የአማርኛ ጉዳይም ተመሳሳይ ነው፡፡ ትናንት ከኦሮምኛ ወደ አማርኛ የመጣው “አንጋፋ” ይቅርና ጥንት ከግሪክ በግእዝ በኩል ወደ አማርኛ የመጣው “በርበሬ” ም እንዲሁ ነው፡፡ “በረበረ”፣ “ብርበራ”፣ “አበራበር” እያልን በግድ እናራባ ብንል ከ“በርበሬ” ጋር ሊገናኙልን አይችሉም፡፡ ከመሠረቱ ባድ ቃል ስለሆነ እና አመጣጡ አንድን ነገር ወክሎ (ቀይ የሆነውን የሚያቃጥል ነገር) ስለሆነ አማርኛ ውስጥ ከጎኑ የሚሆን ዘመድ አጥቶ ብቸኝነት ሲሰማው ይታያል፡፡

“ወደላ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ከሌሎች ትንሽ የተለየ ነገር ይታይበታል፡፡ “ወደላ” በኦሮምኛ “ወንድ አህያ” የሚል ትርጉም አለው፡፡ አማርኛ ይኸን ቃል ከኦሮምኛ የወሰደው ይሆን? እኔ ርግጠኛ አደለሁም ሆኖም ግን “ወደል/ወደላ” በአማርኛ “ትልቅ/ግዙፍ” የሚል ትርጉም ሲኖረው “ወደለ”፣ “መወደል” እና “አወዳደል” የሚሉ ርቢዎችም አሉት፡፡ “ወደለ” ሲባል “አጠበደለ፣ ጠብደል ሆነ” ማለት ነው፡፡ ይኸ ልጅ እንዴት ወደለ እባካችሁ አቤት መወደሉ ሲባል እሰማ ነበር ድሮ-እንደዛሬው አዲስ አበባ ላይ በሚታወቁ የአማርኛ ቃሎች ብቻ በተወሰነ አማርኛ ከመታጠሬ በፊት፡፡ እናም አማርኛ ከኦሮምኛ ከወሰደው በኋላ ራሱ አራብቶት ይሁን አይሁን አላወቅኩም፡፡ በኦሮምኛ ግን ወደላ ከሚለው ቃል ጋር የሚዛመድ እና ወንድም፣እህት ፣ አባት ወይም እናት ነኝ የሚል ቃል አላጋጠመኝም፤ ከቤተሰብ ተለይቶ እንደጠፋበት ያመለከተም አልተመዘገበም፡፡

አማርኛ በወጣትነቱ ወይም በጎልማሳነቱ ዘመን የተዋሳቸው እና ራሱ ያሳደጋቸው እልቆ መሳፍርት የሌላቸው የግእዝ መሠረት ያላቸው ቃሎች የሚያሳዩን ሐቅ ግን ከኦሮምኛው እጅግ የተለየ ነው፡፡ የግእዝ መሠረት ያላቸው፤ “ገዛ”፣ “ገደለ”፣ እና “ተጓዘ” ከኦሮምኛዎቹ “አንጋፋ”፣ “ጨፌ”፣ እና “አዱኛ” እንዴት እንደሚለዩ ቀጥላችሁ ተመልከቱልኝ፡፡

 • አንጋፋ (ኦሮምኛ)-›አንጋፋ (አማርኛ)፤ አንጋፉታ (ኦሮምኛ)-›………
 • አዱኛ (ኦሮምኛ)-› አዱኛ (አማርኛ)…… አበቃ፣ ሌላ ቃል የለም
 • ጨፌ (ኦሮምኛ)-›ጨፌ (አማርኛ)
 • ገዝአ (ገዛ)፤ ገዛኢ (ገዢ፣ የሚገዛ)፤ አግዝአ (አስገዛ)፤ እግዚእ (ገዢ፣ ጌታ፣ አዛዢ)፤ እግዝእት (ሴት ገዢ፣ እመቤት)፤ እግዚኦ (ገዥ ሆይ፣ ጌታ ሆይ)፤ ተገዝአ (ተገዛ)፤ ግዙእ (የተገዛ)፤ ግዝአት (ግዛት፣ መገዛት)፤ እግዚአብሔር (የአገር ጌታ፣ የዓለም ጌታ፣ የዓለም ገዢ)
 • ገደለ (ገደለ)፤ ገዳሊ (ገዳዪ)፤ አግደለ (አስገደለ)፤ ተገድለ (ተገደለ)፤ ግዱል (ግዳይ፣ የተገደለ)፤ ገደላ (ሬሳ)፤ ገደል (ገደል፣ መጣያ)፤ ተጋደለ (ተጋደለ)፤ ተጋዳሊ (ተጋዳዪ)፤ ገድል (ገድል፣ ውጊያ)፤ አስተጋደለ (አጋደለ)፤ አስተጋዳሊ (አጋዳዪ)
 • ግዕዘ (ተጓዘ)፤ ገዓዚ (ተጓዢ)፤ ገዓዝ (ጉዞ)፤ ግዑዝ (የተጓዘ)፤ ግዕዘት (ግዞት፣ መጓጓዝ)፤ ምግዓዝ (መጓጓዣ)፤ ጋዕዝ (ጓዝ)፤ አግዐዘ (አጓዘ)፤ አግዓዚ (አጓዢ፣ አጓጓዢ)

 

ማጠቃለያ

የአማርኛ ቤተሰባዊ ዝምድና ከግእዝ ወይም ከኦሮምኛ እንደሆነ ለማሳየት የተቻለንን ሞክረናል፡፡ አማርኛን ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ግእዝ ለመናገር ሲሞክሩ ከፈጠሩት ከድሮ ቋንቋቸው  (ከኦሮምኛ) የተወሰኑ ቃሎችን ከቤተሰቦቻቸው ነጥለው ከመዋስ ሌላ መሠረታዊ የቋንቋ ባህርይ ወደ አዲሱ ቋንቋ (ወደ አማርኛ) ያላመጡ ይልቁንም ገና መናገር ከሚሞክሩት ከግእዝ ለአማርኛ ብዙ ነገር ያወረሱት ለነፍሳቸው ብለው ነው? እስቲ እዚህ ላይ ጥቅሱን እንደገና እናምጣው፤ “…. አማርኛ የተፈጠረው የኦሮሞ ተወላጆች ግዕዝ ለመናገር ሲሞክሩ ነው” የኦሮሞ ተወላጆች ሲባል ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ለማለት እንደሆነ እገምታለሁ- የሚወራው ስለ ቋንቋ እንጅ ስለሰው ዘር ስላልሆነ፡፡ ይታያችሁ እንግዲህ ኦሮምኛ የሚናገሩ ሰዎች (የኦሮሞ ተወላጆች) ከሚናገሩት ከራሳቸው ቋንቋ ሳይሆን ገና ለመናገር ከሚሞክሩት ከግእዝ ብዙ ነገር አውርሰው አማርኛን ፈጠሩት! “ልሳቅ ባይኔ ጥርሴስ ልማዱ ነው” አለ ያገሬ ሰው፡፡

መቼም የመሰለንን መጻፍ ቀላል ነውና እኔም ኦሮምኛ ከአማርኛ የተዋሳቸው ቃሎች ስላሉ እና የአማርኛ እና የኦሮምኛ የዐረፍተ-ነገር አወቃቀር ሥርዐት ተመሳሳይ ስለሆነ ብቻ፤ ኦሮምኛ ከአማርኛ የመጣ ቋንቋ ነው ብዬ ብጽፍ ካስፈለገም እከሌ የተባለው ጸሐፊ እንደዚህ ብሏል፣ አለቃ እንተና ይኸን ጠቅሶታል እያልኩ ብደረድርስ? ያኔማ ብዙ ሰዎች ሲሳደቡ፣ ሲንጫጩ፣ ሲጮሁ ወይም ሲያለቅሱ ይታየኛል፡፡ ለማንኛውም ውሸት መጻፍ እና  መተረክ ገደብ እና ለከት ቢኖረው መልካም ነው በሚል ሃሳቤን እደመድማለሁ፡፡

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.