“ስደትና ድህነት የዜጎችን ክብር ዝቅ ሊያደርጉ አይገባም”… አቶ ሙስጠፌ መሐመድ

Mustefeስደትና ድህነት የዜጎችን ክብር ዝቅ ሊያደርጉ አይገባም ሲሉ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ተናገሩ።
ስደተኞችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ የሰብዓዊነት ግዴታ መሆኑንም አንስተዋል።
በሁለተኛው ዙር የከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔት ረጅም ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ የቆዩ ስደተኞች በአካባቢ ልማት ስራዎች ተሳትፈው ህይወታቸውን በዘላቂነት እንዲያሻሽሉ የሚደረግ መሆኑም ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ በሶማሌና ጋምቤላ ክልል የሚገኙ 30 በመቶ ስደተኞችን ተጠቃሚ በማድረግ የሚጀምር ቢሆንም በሌሎች ክልሎችም ቀጣይነት ይኖረዋል ተብሏል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ለኢዜአ እንዳሉት ስደተኞች ከህብረተሰቡ ጋር ያላቸው ማህበራዊ ግንኙነት እንዲጠናከር በአካባቢ ልማትና በሌሎች ስራዎች ላይ ማሳተፍ ያስፈልጋል።
ማንም ሰው ችግር ውስጥ ካልገባ በቀር ተረጂነትን እንደማይፈልግ ገልጸው፣ስደትና ድህነት የዜጎችን ክብር ዝቅ ሊያደርጉ አይገባም ነው ያሉት።
እንደ አቶ ሙስጠፌ ገለጻ፣ኢትዮጵያ በርካታ ስደተኞችን እያስተናገደች እንደመሆኗ ለስደተኞቹ ሰብዓዊ ድጋፍ የማድረግ ግዴታ አለባት።
ስደተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ተግባራዊ መደረጋቸው የስደተኞችን ህይወት ከመለወጥ ባለፈ የመንግስትንም ጫና ይቀንሳል ነው ያሉት።
ስደተኞችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ ከተጀመረው ፕሮጀክት ተሞክሮ በመውሰድ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ዜጎችንም ለመርዳት ያስችላል ብለዋል።
የስራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረጉ ሰብዓዊ ግዴታ መሆኑን ያነሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ኢትዮጵያዊያን ካላቸው ላይ ለሌሎች የማካፈል የቆየ ባህላቸውን ማስጠበቅ አለባቸውም ብለዋል።
በኢትዮጵያ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ከተለያዩ አገሮች የመጡና በመጠለያ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል።
ኢዜአ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.