“ልክን ማወቅ ከራስ ጋር መታረቅ” ዶክተር መላኩ ተገኝ

<<ዶክተር መላኩ ተገኝ የኢሕአፓ አባል (አመራር) የነበሩ አባይ ሜዳያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ የተሰጠ የግል አስተያየት>>

በዚህ አጋጣሚ ቃለ መጠይቁን ያዘጋጁትን አቶ ኤሊያስ አወቀን ሳላመሰግን አላልፍም። ሙሉውን ቃለ መጠይቁን ለመገምገም ፍላጎትም ችሎታም የለኝም። ሆኖም ግን ከቃለ መጠይቁ ውስጥ ዶክተር መላኩ  ሕይወት ተፈራንና ታደለች ኃ/ሚካኤልን የተመለከቱበትና የገለጹበት  ትምክህት አዘልና ንቀት የተመላበት እንደሆነ ተመልክቼ አዘንኩ፡፡ አባባላቸው ከሳቸው የማልጠብቀው ሆኖ በማግኘቴ ምናልባትም አንዳይደግሙት በመፍራት አንድ ነገር ማለት ወደድሁ፡፡ እግረ መንገዴን ከእሳቸው የምጠበቀው ሙሉ ትንታኔ እንጂ የማይረባ  ሽሙጥ አለመሆኑንም ለማሳስብ ጭምር ነው ።

በወቅቱ ከነበረው የትግል ባህሪና ትግሉ ከጠየቀው መጠነ ሰፊና ትልቅ የሕይወት መስዋዕትነት አኳያ የታዬው የትግል ቁርጠኝነት ፣ ዛሬም ድረስ ዘመን ተሻጋሪ ሆኖ የሚወሳ ተምሳሌታዊ እውነት ነው፡፡ የመብትና የነጻነት ትግልን ባህሪ፣ጥንካሬና የዓላማ ጽናት፣ ለድርጅት ፍቅር የተከፈለን ክቡር የህይወት መስዋዕትነት በታሪክ አስረጅነት የሚጠቀስ ኑባሬ ነው፡፡ በተለይም ከትግልና ከጓዳዊ የትግል መንፈስና የዓላማ ትስስር አኳያ ሲመዘን ፣ የዶ/ር መላኩ አነጋገር ከሚዛን የቀለለ ጉድፍ እሳቤ የተቀላቀለበት ሆኖ በማኘቴ አደብ ገዝቼ  ለማለፍ አልወደድኩም፡፡

እኔ ባለኝ ግንዛቤ እነዚህ ከላይ የተገለጹት ሶስት ግለሰቦች በኢሕአፓ ውስጥ በተለያየ የትግል እርከንና ቦታ የተሳተፉና የተለያየ ልምድ ያላችው ናቸው። ዶክተር መላኩ ተገኝ በትግሉ ወቅት ብዙውን ጊዜ በውጭ ሃገር በሆላንድ ይኖሩ የነበሩ ሲሆን  የፓርቲው ምስርታ ላይ የተገኙና በሁዋላም ከፍተኛ አመራር እርከን ላይ የደረሱ ሰው ናቸው። ከዚህም በላይ ከሰንጋተር እስክ አምስተርዳም የሚል መፀሃፍ መጻፋቸውም ይታወቃል። ወይዘሮ ታደለች ኃ/ሚካኤል ሲዊዘርላንደ ሲኖሩ የቆዩና ትግሉን ለማስቀጠል ወደ ሃገር ውስጥ ተመልስው ገብተው በትግል ላይ ሳሉ በደርግ እጅ ወድቀው ከ12 ዓመት በላይ በስር ሲማቅቁ የኖሩ ናቸው ። ከዚም በላይ ያላቸውን የትግል ተመክሮና ትውስታ ዳኛው ማነው በሚለውን መጸሃፋቸው ለንባብ አብቅተውልናል። ሕይወት ተፈራ የወጣት ሊጉ ከፍተኛ አመራር የነበሩ ሲሆን  እሳቸውም እንዲሁ በደርግ ታስርው ከስምንት አመት በላይ በወህኒ የተንገላቱ ሲሆን ማማ በሰማይ የሚል በአንባቢ ዘንድም በተወደደላቸው መጽሐፍ ከትግል ማህደራቸው አውጥተው አካፍለውናል።

በዶክተር መላኩ አገላለጽ እነዚህ ሁለት ሰዎች ካላችው „ስልጣን“ አንጻር ስለኢሕአፓ መተረክ አይችሉም ወደሚል ድምዳሜ ሊያደርስ የሚችል ገለጻ ሲሰጡብ ተደምጧል። ይህንን በምን ምክንያት እንደሆን ሲያብራሩ  የግለሰቦቹን ጉልህና ቀጥተኛ የትግል  ተሳትፎ ወደ ጎን በመተው  ያላቸው መረጃ ሁሉ ከፍቅረኞቻችው ያገኙት ብቻ ነው በማለት  እንደ ታጋይ ጓድ ግለሰቦቹ የከፈሉትን መሰዋትነት አጣጥለውታል። በተለይ ሕይወት ተፈራ የወጣቱ ሊግ አባል በመሆኑዋ ምንም መጸፍ አትችልም ማለታቸው ዛሬም በምናብ የትምክህት ማማቸው ላይ ተኮፍሰው እያላዘኑ መቀጠል እንደሚሹ  አይነተኛ ማሳያ ነው፡፡

ዶክተር መላኩን እንደ ሌሎች ሁሉ የውጭ አርበኛ እንደነበሩ እናውቃለን፡፡ ትግሉ ደግሞ የሕይወት ዋጋ ያስከፈላቸው ውስጥ ሆነው የታገሉትን ነው፡፡ ስለሆነም ዶክተሩ በቅርብ ስላላዩት ለወጣት ሊግ አባላት ንቀት ቢያሳዩ አይደንቀንም፡፡ በዛ አፍላ ዘመን አያሌ ወጣቶች የከፍሉትን የህይወት መሰዋትነት በውል ሊገነዘቡት ከቶ አይችሉም፡፡ የመከራው ስፋት ከዩንቨርስቲ ተማሪነት እስከ አራሽ ቅጥረኛ ምንደኛ ገበሬነት፣ ከእስራት እስከ ሞት፣ ከግራፋት እስከ አካለ ስንኩልነት ያበቃቸው እሳቸው የሚኮፈሱበትና የሚመጻድቁበት የመብትና የነጻነት ትግል ፋና ሆነው ያለፉበትና ለድርጅት ያደረጉት ተጋድሎ መሆኑን ሊገነዘቡ እንዳልቻሉ ይህ  ምልክታቸው በጉልህ ያሳያል፡፡ ክልምድ አንጻር በዚህም እሳቤ ስህተት ላይ የወደቁ እሳቸው ብቻ እንዳልሆኑ እረዳለሁ፡፡

ከዶ/ር መላኩ አባባል እንደተረዳሁት እንኳን ለአስራ ሁለት አመታት ለአንድ ወርም ያህል ጊዜ ከዛሬ ነገ እገደላለሁ እያሉ በጭንቀት እስር ላይ የሰቆቃ ኑሮ መግፋት ምን ያህል የውስጥ ህመም እንደ ሆነ ሊርዱት እንዳልቻሉ ነው። ሌላው ቢቀር እነዚህ ሁለት ሴቶች የከፈሉትን መስዋዕትነትን ብቻ እንኳን በመመልከት  ለትግላቸው እውቅናና ክብር መስጠት መንፍጋቸው ምን ያህል ጥላቻና ንቀት በታችኛው እረከን አመራርና አባላቱ ላይ እንዳላቸው በገሃድ የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን የህሊናቸው ሚዛን መዛባቱንና የስልጣን ፍቅር ከአባላቱ መስዋእትነት እንደተነጠላቸው ጉልህ ማሳያ ነው፡፡ የአባላቱ ታሪክ የድርጅቱን ታሪክ ሚዛናዊነት ይጠብቅ እንደሁ እንጅ እንደድሮው  እኔ ብቻ አዋቂነኝ እኔ ያልኩትን ተቀበል የሚለን ሚዛን የጎደለው ስንክሳር እንዲነግሩን አያስፈልግም፡፡ ደግሞስ በ50 ዓመት ታሪኩን መሰነድ ያልቻለ ድርጅት አመራር የበታች እርከን አባላቱ የሚያውቁትን የትግል ተመክሮ ለንባብ ቢያበቁ ማናናቅና ማንቋሸሽ የሚችልበት የሞራል ብቃት አለውን?  እዚህ ላይ እተወዋለሁ፡፡

ዶክተር መላኩ እርስዎ አንደሚያስቡት የሊግ አባላት ፓርቲያችን ብለው መሰዋታቸው የጭዳ ዶሮ ያደርጓቸው ይመስላል?  የወጣት ሊጉስ የፓርቲው ሌላ ክንፍ መሆኑን መካድና ማጣጣል፣ ብሎም ዋጋ ማሳጣት ያስቻልዎ ምን እንደሆነ በውል ባላውቅም ሊያዩ የሞከሩበት ለራሳቸው ልዩ ክብርና ቦታ ለማግኘት የሚፍገመገሙ አስመስሎዎታል። እንደሚታወቀው የወጣቱ ሊግ ትግልና አባላቱ የከፈሉት መስዋዕትነት እሳቸው ቢክዱትም በሕብረተሰቡ ልብ ውስጥ በማይፋቅ ቀለም በክብር ቦታ ተፅፏል። የኢሕአፓ ታሪክ በከፍተኛ አመራሮች ብቻ ነው መጻፍ ያለበት የሚለውም እሳቤም ቢሆን እሳቸው ጥልቅና ውስብስብ ታሪክ አለው ለሚሉት ትግል ፡ አባላቱን የነበራቸው ድርሻና የትግል ተመክሮ ታሪካቸውን በነጻነት መጻፍ አይችሉም የሚል “ከእኛ ወዲያ ላሳር” እይነት ድምዳሜ የሚያሰጠው ከቶ አይሆንም፡፡ እርሶ እንደሚያስቡትም የተወሰነ ስው ብቻ መረጃ ያለውም አይደለም ። ግን ልክ ነዎት ብዙዎቻችንን “የጭፍን“ ደጋፊዎች ነበርን። ስለ አመራሮቻችንን የማንጠይቅ በእምነት ላይ ብቻ የተመሰረተ መተማመን ስለነበረን ነው እንጅ እንዲህ አይነት ወግ አጥባቂዎችና ግብዝ መኖራቸሁን ላፍታ አስበን ብናውቅ ኖሮ የተከፈለው መስዋዕትነት ያን ያህል ባልሆነ ነበር፡፡

ፅሁፌን ከማጠቃለሌ በፊት እዚህ አውሮፓ ውስጥ በሆላንድ ሃገር የተፈፀመ አነስ ያለ ጉዳይ መጥቀስና ግለሰቦችን ማመስግን

እፈልጋለሁ። የከፍተኛ አመራር የነበረ ግለሰብ የፓርቲውን ቁልፍ ሰነዶች በሙሉ ጥሏቸው ይሄዳል ። እነዘህ ዶክመንቶች ይጠቅማሉ

በማለት የሰበሰቧቸውን ብስራትንና ጎሳዬን በዚህ አጋጣሚ ሳላመሰግን አላልፍም ። የምስጋናው መለዕክት ይድርሶታል ብዬ አምናለሁ።

ቃለ መጠይቁን ለመስማት ለምትፈልጉ ከዚህ በታች ያለውን አስፈንጣሪ ይጠቀሙ፡፡

https://www.youtube.com/watch?v=x36NoISB8U0

 

ለሕዝብ ሲሉ መስዋትነት የከፈሉ ሁሉ በሰላም ይክርሙ

3 Comments

  1. ዶክተሩ ለወቅቱ ባላንጣችው ኃይሌ ፊዳ ያላችው ጥላቻ እስካሁን የወጣላችው አይመስልም፡፡ የተበሳጩት ደግሞ እትዬ ታደለች በአንድ ስብሰባ ላይ “ኃይሌ ፊዳ ይቅርታ ስለጠየቀ አደነቅሁት” ስላለች ይመስለኛል፡፡ በህይወት የሌለውን ኃይሌ ፊዳን “እንዲወገዝ አደረኩ” ብለው ዶክተሩ በኩራት ሲነግሩን ትንሽ እንኳ ቅር አላላችውም፡፡ ቢጠሉት እንኳ ቢያንስ “ሙት ወቃሽ አያድርገኝና” ይባላል፡፡
    እንደው ለመሆኑ “ኢህአፓ ተሳክቶለት ስልጣን ይዞ ቢሆን ኖሮ” ብሎ የተመራመረ የለም?

  2. ከድር ሰተቴ ከዋናዉ ከድር ሰተቴ አትሻልም ሂትለርን የምናወግዘዉ በህይወት ኑሮ ነዉ እንደዉ ይሄ የዘር ልክፍት መች ይሆን የሚያበቃዉ? ሀይሌ ፊዳና ዋለልኝ መኮነን ካልተተቹ ማን ይተች?

    • አመጣጥህ ገባኝ፤ አቤት የጥላቻህና ክፋትህን መጠን! የት እንደተማርከውም ገባኝ፤ አሁንም አልወጣልህም ፤እስቲ በምን ሂሳብ ነው ኃይሌ ፊዳ እና ሂትለር የሚወዳደሩት? ጨካኝ ነህ አይሳካልህም፡፡ ጫጫታው ለጊዘው ነው፡፡

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.