ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ በሚመጡ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙት ከኦሮሚያ ልዩ ኃይል የከዱ ፖሊሶች ናቸው ተባለ

(አብመድ) ከጎጃም እና ከጎንደር በደጀን በኩል ወደ አዲስ አበባ የሚንቀሳቀሱ የደረቅ ጭነት አሽከርካሪዎች ኦሮሚያ ክልል ውስጥ መንገድ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑን መናገራቸውን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ ችግሩ የተፈጠረው ከሱሉልታ እስከ ዓባይ በርሃ ድረስ ባለው በኦሮሚያ ክልል በሚያልፍ የፌዴራል መንገድ ላይ መሆኑም ተነስቶ ነበር፡፡ ቀደም ብሎ በየኬላው በሚደረግ ፍተሻ ሕጋዊ ባልሆነ መልኩ ክፍያ ይጠየቁ እንደነበርም ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡ ሥራቸውን ላለማቆም እና ግጭት ውስጥ ላለመግባት ይጠየቁ የነበረውን ሕገ-ወጥ ክፍያ ፈጽመው ሥራቸውን ሲያከናውኑ እንደነበርም አሽከርካሪዎች ጠቅሰዋል፡፡
56 1
ከሰሞኑ ደግሞ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትን የፀጥታ ኃይል መለዮ የለበሱ ታጣቂዎች ጥቃት እየተፈፀመባቸው መሆኑን የአሽከርካሪዎችን ቅሬታ ይዘን ዘግበን ነበር፡፡ በተለይ መስከረም 30/2013 ዓ.ም ምሽት ላይ የመሣሪያ ተኩስ እንደነበር አስተያዬት ሰጪዎቹ ተናግረው ነበር፡፡ በዚህም የሰው ሕይወት ማለፉን፣ የቆሰሉ መኖራቸውን እና መኪናዎች መቃጠላቸውን አስታውቀዋል፡፡ በቅርብ ርቀት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ሲያደርጉ የነበሩ የኦሮሚያ ክልል የፖሊስ አባላትም በወቅቱ እንዳልነበሩ ጠቅሰው ነበር ፡፡ የክልሉ የፀጥታ ኃይል ኃላፊነቱን እንዳልተወጣ ቅሬታ አቅራቢዎች ተናግረዋል፡፡

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ችግሩን ለመንግሥት የፀጥታ አካላት ለማሳወቅ እንደተቸገሩም ነግረውን ነበር፡፡ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ አሽከርካሪዎች ለመንግሥት ግብር የሚከፍሉና የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ በጥቃቱ ምክንያት ግን ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን አለመቻላቸውንና ከባንክ የተበደሩትን ገንዘብ ለመክፈል እንደሚቸገሩ አስተያየት መስጠታቸውም ይታወሳል፡፡

አብመድ በወቅቱ በጉዳዩ ዙሪያ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል መንግሥት አስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ጅብሪል መሐመድን በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡ በተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም ስልክ ሊያነሱ ባለመቻላቸው ሐሳባቸውን ማካተት አልቻለም ነበር፡፡

ዛሬ ጥቅምት 10/2013 ዓ.ም የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ገናናው ጥበቡ በዚሁ ጉዳይ ለኢብኮ ምላሽ ሰጥተዋል፤ እንደ ኮሚሽነሩ መረጃ ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ አሽከርካሪዎች ላይ የተፈፀመው ድርጊት መረጃው ደርሷቸዋል፤ ድርጊቱ የተፈፀመው ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት እንደሆነም አውቀዋል፤ የኦሮሚያ ልዩ ኃይልም ይሁን የኦሮሚያ ፖሊስ የተቋቋመው የሀገሪቱን ሠላምና የሕዝብን ደኅንነት ለማረጋገጥ እንጂ መንገድ ላይ ቆሞ ዘርፎ፣ አካልን ማጉደል ወይም ሕይወት ለማጥፋት አይደለም፤ ድርጊቱን የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አልፈፀመም፤ ከልዩ ኃይሉ በተለያዩ መንገድ የከዱ አባሎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ በየቦታው በሚደረገው ርምጃ የልዩ ኃይሉን ልብስ እየለበሱ መሰል ድርጊት የሚፈፅሙ አሉ፤ ይሄ የሚካድ አይደለም፡፡ ድርጊቱን የሚፈፅሙት በተለያየ መንገድ “ፀረ ሠላም ኃይሎችን” የተቀላቀሉ የፀጥታ አካላት እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ኃይሎች በየቦታው ርምጃ እየተወሰደባቸው መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ልዩ ኃይሉ ግን የተቋቋመበት አላማ አለመሆኑን ምክትል ኮሚሽነሩ አረጋግጠዋል፡፡

“የትራንስፖርቱ ሂደት ለአንድም ቀን አልቆመም” ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፡፡ “ጉዳዩን አስመልክቶ ለፖለቲካ ጥቅም የሚፈልጉት አካላት ሊኖሩ ይችላሉ፤ በእርግጥም የተጎዱና ድርጊቱ የተፈፀመባቸው አካላት አሉ፤ ይሄንን በጋራ ሆነን የምንከላከለው ይሆናል፤ ጉዳዩ ለልዩ ኃይሉ ወይም ለኦሮሚያ ፖሊስ የሚሰጥ አይደለም፤ በጋራ ሆነን የምንከላከለው ነው” ብለዋል፡፡

ሠላምን ለማረጋገጥ ችግር ፈጣሪዎቹን ተከታትለው እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል፡፡

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.