ግልጥ ደብዳቤ: ይድረስ የአዲስ አበባን አስተዳደር በተመለከተ ለመነጋገር የተሰበሰባችሁ ድርጅቶች – አንዱ ዓለም ተፈራ

ሐሙስ፣ ጥቅምት ፲ ፪ ቀን፣ ፳   ፫ ዓመተ ምህረት

32 ግልጥ ደብዳቤ: ይድረስ የአዲስ አበባን አስተዳደር በተመለከተ ለመነጋገር የተሰበሰባችሁ ድርጅቶች   አንዱ ዓለም ተፈራ

ውድ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሕብረት አመራርና አባላት

ውድ የኢትዮጵያ ተራማጅ ፓርቲ አመራርና አባላት

ውድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ አመራርና አባላት

ውድ የጋምቤላ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ አመራርና አባላት

ውድ አብሮነት ፓርቲ አመራርና አባላት

ውድ ትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትኅ አመራርና አባላት

ውድ ማራ ሔራዊ ቅናቄ አመራርና አባላት

ውድ አሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራርና አባላት

ውድ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ አመራርና አባላት

ውድ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ውስጥ ባለ ጉዳይ ተቆርቋሪ ሆናቸው የተሰየማችሁ ድርጅቶች፤

ሰሞኑን የአዲስ አበባን አስተዳደር በተመለከተ ያደረጋችሁትን ስብሰባና የደረሳችሁበትን ውሳኔ ተከታትያለሁ። አሁን አገራችን ባለችበት ሁኔታ፤ ጊዜያችሁንና ገንዘባችሁን ለአገራችን ዕድገት፣ ልማትና ደህንነት ለምታደርጉት ጥረት፤ እኔ ከፍ ያለ ክብርና ምስጋና አቀብላችኋለሁ። ይሄን የምጽፍላችሁ፤ ከኔ በኩል ይረዳል ብዬ የታየኝን ላካፍላችሁ ስለወደድኩ ነው።

ቀደም ሲል ጠባብና ትክክለኛ ባልሆነ የቋንቋና የአካባቢ ተወላጅነት የተመረኮዘ የፖለቲካ ቅኝት፤ ራሳቸውን የቻሉ ክልሎችን እንዲፈጠሩ በማድረግ፤ አገራችንን የሚበታትን የአስተዳደር ስሪት ተገፍቶ ነበር። በመካከል ግን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ “አትከፋፍሉን!” ብሎ ተነስቶ፤ ያንን አስተዳደር አስወግዶታል። በዚያ በተፈጠርው ሂደት፤ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማቋቋም፤ የፖለቲካ ተሳትፎ የሚደረግበትን መንገድ ተከፈተ። ይህ አጋጣሚ፤ የእናንተንና የእናንተን የመሰሉ ድርጅቶች እንዲመሠረቱ ዕድሉን ሠጥቶናል። እናም እጅግ የበዙ የፖለቲካ ድርጅቶች ተቋቁመዋል። በአሁኑ ሰዓት፤ የያንዳንዳችሁ ድርጅት የራሱ የሆኑ መርኀ-ግብርና መተዳደሪያ ደንቦች አሉት። ልዩነቶች ስላሏችሁም፤ ራሳችሁን ችላችሁ ቆማችኋል።

እኔ በዚህ መስክ ከተሠማራችሁት የበለጠ አውቃለሁ ብዬ፤ ለናንተ ትረካ አልይዝም። ነገር ግን፤ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ፤ ተግባራችሁን ከመከታተልና በጎውን ከመደገፍ ያለፈ፤ በኔ በኩል ይሄ ቢደረግስ ብዬ ላማክራችሁ ነው። የተነሳሁት ከዚህ ነው። በርግጥ፤ እያደረጋችሁት ያለው በሙሉ፤ መሠረታዊ መብታችሁ ነው። በፅንፈ ሃሳብ ደረጃም ተገቢ ነው። የፖለቲካ ድርጅትን መሥርቶ ተሳትፎ ማድረግ፤ ሁለት ጎኖች አሉት። የመጀመሪያው ድርጅቱን ለመመሥረት የሁኔታው መሟላት ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ፤ የድርጅቱ ሕያውነትና ስኬታማነት ነው። ሕያውነትና ስኬታማነት፤ በተጨባጩ የአገራችን ሁኔታና በአመራሩ ችሎታ ለግብ ይበቃሉ። ታዲያ የኔ ሃሳብ ተጨባጩን የአገራችን ሁኔታን የተመለከተ ነው።

ባለፈው መንግሥት፤ አገሪቱ በክልል ተሸንሽና፣ እያንዳንዱ ክልል የራሱ የሆነ መንግሥታዊ ይዘት ኖሮት፣ አንዱ ከሌላው ጋር ተወዳደሪ ሆኖ፤ የአገራችንን ጥሪት ለመከፋፈል ብቻ የተገናኙ እስኪሆኑ ድረስ የተዋቀሩበት አሰራር ነበር። ለዚህ መነሻውና መድረሻው፤ የተደነገገው ሕገ-መንግሥትና ያን ለመተግበር የተዘረጋው መዋቅር ነበር። በሂደቱ ኢትዮጵያ የምትባል አገር እየጠፋች እንድትሄድ፤ የነበረው መንግሥት ይሄኑ ያራግብ ነበር። ያ፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ጥረት፤ ከጀመረው መንገድ በጊዜው ተሰናክሏል። ከዚያ የሚያቀና መንገድ እንድንይዝ ሽግግር ያስፈልግ ነበር። አልተደረገም። አሁንም የክልል መንግሥታት እንዳሉ ናቸው። ብልፅግና ከዚያ ውጪ ሕልውና የለውም። ያ ብቻ ሳይሆን፤ ብልፅግና ተወዳዳሪ አይፈልግም። ውሎ አድሮ፤ እያንዳንዱ የክልል ብልፅግና ድርጅት፤ “ከኔ ሌላ፤ በኔ አካባቢ፤ ተንቀሳቃሽ ድርጅት አልፈቅድም!” የሚልበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። ስለዚህ፤ ዛሬ እያንዳንዳችሁ ድርጅቶች የምታደርጉት እንቅስቃሴ፤ ለነገ ዋስትና የለውም።

እንዳልኩት የምነሳው ከዚህ ነው። እናንተ ያላችሁበት የፖለቲካ ሀቅ፤ በናንተ ፈቃድ ሳይሆን፤ በሥልጣን ላይ ባለው ክፍል ፍላጎትና ውሳኔ የተመሠረተ ነው። እናም ሕልውናችሁን ከዚህ አንጻር እንድትመለከቱት እፈልጋለሁ። የአዲስ አበባ በዚህ መንገድ ወይንም በዚያ መንገድ መተዳደር፤ በአገራችን ካሉት ብዙዎች ጉዳዮች አንዱ ነው። በአንድ ጉዳይ የተመሠረተ ስምምነት፤ ያ ጉዳይ ቢሳካም ባይሳክም፤ ጊዜያዊ ስምምነት ነው። ከድርጅቶቻችሁ ሕልውናና ከአገራችን የፖለቲካ እውነታ አንጻር ሲታይ፤ ብዙ የምትስማሙባቸው ጉዳዮች አሉ። ምንም እንኳን በነበረው የፖለቲካ ሀቅ ምክንያት አመሠራረታችሁ ባመቻችሁና ጊዜው በጠየቀው ሁኔታ ቢሆንም፤ አገራችን እንደ አገር እንድትቀጥል ሁላችሁም ታምኑበታላችሁ። ቀጥሎ፤ የያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ትፈጋላችሁ። በዚህ ውስጥ፤ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ፤ የፖለቲካ ተሳትፎውን በአስተሳሰቡና በኢትዮጵያዊነቱ ብቻ እንጂ፤ በፆታ፤ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በሀብት ክምችት፣ በትምህርት ደረጃ፣ በአካባቢ እንዳይሆን ትስማማላችሁ። በሶስተኛ ደረጃ፤ ሙስናና ወገንተኝነት በፖለቲካ ምሕዳሩ ቀርቶ፤ በኅብረተሰባችን እንዳይኖር ትፈልጋላችሁ። በአራተኛ ደረጃ፤ ሁላችሁም ትሕነግ ያሰነበተውን የፖለቲካ ሂደት፤ ሕገ-መንግሥት፣ የፖለቲካ መመሪያ አስተዳደራዊ መዋቅር ታወግዛላችሁ። መቀጠል እችላለሁ፤ ነገር ግን ነጥቤን ላማሳየት ይሄ ይበቃኛል። እኒህ የአገራችን የመሸጋገሪያ ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው።

አገራችን በትክክል መሸጋገር ትችል ዘንድ የግድ መደረግ ያለባቸውን ወደ ጎን አድርገን፤ ዓይኖቻችንን ጨፍነን ወደፊት ብንሸመጥጥ፤ ተመልሰን፤ ይሄን ብናደርግ ኖሮ! የሚያስብል ጊዜ አናገኝም። አሁን ባለው ተጨባጩ የአገራችን ሁኔታ፤ ዋና ዋና ጉዳዮች ካላይ የሰፈሩት ናቸው። እኒህ ከተተገበሩ በኋላ ነው፤ ሌሎች በመካከላችሁ ያሉት መለያያ ነጥቦች ብቅ የሚሉት። እንደልባችሁ ልትወዳደሩና ሃሳቦቻችሁን ከሕዝብ ፊት ልታቀርቡ የምትችሉት። እያንዳንዳችሁ ድርጅቶች ስትመሠረቱ፤ መንግሥት ሆናችሁ አገራችንን ለማስተዳደር እንጂ፤ ለስሙ ድርጅት አለን ለማለት አይደለም። እናም በትክክል ለስኬት ተነስታችሁ ነው። በተጨባጩ የአገራችን ሁኔታ ደግሞ፤ ለስኬት የሚያበቃው፤ ከብልፅግና የበለጠ የተደራጀ፣ ከብልፅግና የበለጠ መዋቅሩን የዘረጋ፣ ከብልፅግና የበለጠ አባላትን የያዘና ያዘጋጀ፣ ባጠቃላይም ከብልፅግና የበለጠ የዳበረና የሰላ ሲሆን ነው። በኔ እምነት፤ ዋና ዋና በሆኑ፤ የአሁን የአገራችን ወሳኝ ጉዳዮች ላይ፤ አንድነት አላችሁ። የልዩዩነቶቻችሁን ጉዳዮች አንስተኛነት በአንድነት ብትቆሙ ከሚገኘው አገራዊ ጥቅም አንጻር ብታዩት፤ ሀቁን ትቀበሉታላችሁ። ለየብቻችሁ ከምትከፍሉት መስዋዕትነት ያነስ ትከፍሉ ይሆናል። እናም አገላብጨ ሳየው፤ አንድ ድርጅት ሆናችሁ ብትቆሙ፤ እናንተ ብቻ ሳትሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠቀማል እላለሁ።

በእርግጥ ይሄን ማድረጉ፤ እንዳጻጻፌ ቀላል ነገር አይደለም። እያንዳንዳችሁ ድርጅቶች፤ የየራሳችሁ የሆነ ታሪክ አላችሁ። የየራሳችሁ የሆነ መነሻ አላችሁ። የየራሳችሁ የሆነ ሀብት አላችሁ። በናንተ ላይ ብቻ እምነታቸውን የጣሉ፤ የየራሶቻችሁ አባላት አሏችሁ። ሌላም፣ ሌላም፣ ሌላም። ግንኮ፤ የማንኛውም ድርጅት ዓላማ፤ ካቀደው ግቡ መድረስ ነው። በኔ እምነት፤ የሁላችሁም ድርጅቶች እምነት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱ የሆነ መንግሥት በራሱ ፈቃድ መመሥረት እንዲችል ማድረግ ነው። አሁን ትክክለኛ ውድድር ተደርጎ፣ ትክክለኛ ውጤት ተገኝቶ፣ ትክክለኛ መንግሥት በቦታው ይቀመጣል ብሎ ማመን፤ በአእምሯችንና በምኞት ብቻ ነው የሚቻለው። በእውነቱ መገዛት ያስፈልጋል። ምኞታችሁን በየግላችሁ በተግባር ላይ ልታውሉት አትችሉም። በትብብርም ልታደርጉት አትችሉም። የምትችሉት፤ ከብልፅግና አንጻር የሚያስቆም አንድ የሆነ ራዕይና ጥንካሬ ሲኖራችሁ ነው። ግባችሁ እንጂ፤ የግድ የኔ ድርጅት ለብቻው ካልሆነ የሚል ግትርነት የላችሁም ብዬ አስባለሁ። ታዲያ እንዲያ ከሆነ፤ እኔ ብቻ ሳልሆን፤ ብዙ ሊተባበሩና ከአንድነታችሁ የሚመነጨው የድምር ጉልበታችሁ የውጤት ኡደት፤ ለየግል ተደምራችሁ ከምትስገኙት የበለጠ እንደሚሆን አትዘነጉትም። በተጨማሪ፤ ይሄ በሌሎች ኢትዮጵያዊያን ዘንድ የሚፈጥረውን ስሜትና የሚያስገኘውን ድጋፍ፤ ከወዲሁ በቁጥር ማስቀመጥ ቢያስቸግርም፤ ከመቼውም የበለጠ እንደሚሆን ምንም ጥርጣሬ የለኝም።

ስለዚህ፤ እንድትመለከቱት የምፈልገው፤ የአዲስ አበባ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ፤ ያንን ልታሳኩት የሚቻለው፤ በቂውን ተፅዕኖ ለማድረግ የሚያስችል ጥንካሬ ሲኖራችሁ እንደሆነ ተቀብላችሁ፤ ለሁሉም መሳካት ጉልበታችሁን ታዳብሩት ዘንድ፤ በአንድ ድርጅትነት እንትቆሙ ነው። ለዚህ ስኬት የምችለውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ ነኝ። ተባባሪዎችም እንደሚመጡ ባስተማማኝ ልገልጥላችሁ እወዳለሁ።

አክባሪያችሁ

አንዱ ዓለም ተፈራ

2 Comments

  1. የሃጫሉን ግድያ ተከትሎ በተከሰተው አለመረጋጋት ለወደሙ ኢንቨስትመንቶች መንግሥት የሚከፍለው ካሳ የለም::

    “ክልልም ራስገዝም ሆነን ብዙ አመታት አይተነዋል ለህዝብ ጥቅም ፍትህና ዕኩልነት ያመጣ አደረጃጀት አላየንም” – ናትናኤል ፈለቀ የኢዜማ ህዝብ ግንኙነት

  2. አቶ አንዷለም፡
    ለኢትዮጵያ ቅን ሃሳብ እንዳለህ እና ጨዋ ሰው መሆንህ አሁን የበለጠ ግልጽ ሆኖልኛል፡፡ ባለፈው ስለ “ሽግግር መንግስት” ጽፈህ እኔም ኮሜንት አድርጌ ነበር፡፡ በሃሳብ ላንስማማ እንችላለን፡፡ ችግር የለውም፡፡ ምናልባት ቅር አስኝቼህ ከሆነ ግን ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡
    መልካሙን ሁሉ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.