ከታሪክ ማህደር: ከባለቤቱ አንደበት  –  አገሬ አዲስ

ጥቅምት 11 ቀን 2013 ዓም (21-10-2020)

ሎርድ ማኩላይ የተባሉት የእንግሊዝ ባለስልጣን በፍብሩዋሪ  2 ቀን 1835 እ.አ.አ አፍሪካን ፣ኢትዮጵያን ዞረው ካዩ በዃላ ለእንግሊዝ ፓርላማ አባላት የሰጡት ማብራሪያ ይህን ይመስል ነበር።   “ በአፍሪካ ከዳር እስከዳር ተጉዣለሁ፤በዚህ አገር ግን አንድም ለማኝ ሆነ ሌባ አላጋጠመኝም፣አላዬሁም።ሃብታምና የሞራል ልእልና ያለው ፣ብልህ የሆነ ሕዝብ የሚኖርበት  አገር ነው።ይህንን አገር በቀላሉ  ለማንበርከክና በቁጥጥራችን ሥር እናስገባለን ብዬ አልገምትም።ይህ ሊሳካ የሚችለው የአገሩን የጀርባ አጥንት የሆነውን የእምነትና የባህል ጠንካራ እሴቱን ስንሰባብር ብቻ ነው።ስለሆነም ነባሩን የትምህርትና የባህል ተቋሙን በእኛ በመለወጥ የራሱን እንዲንቅና ኩራትና ክብሩን ጥሎ የእኛን እንዲያከብርና እንዲቀበል ስናደርግ ብቻ ነው በመዳፋችን ሥር ሊወድቅ የሚችለው ”በማለት ምክርና አስተያየታቸውን ሰጡ።ያንን ተከትሎ የሆነውን ነገር ታሪክ የሚያውቀው ሲሆን  አሁን ያለንበት ሁኔታም የዚያ ቅጥያ ነው።

34

የፈረንሳይ ፕሬዚዴንት የነበሩት ዣክ ሺራክ ደግሞ ስለአፍሪካ  እንዲህ ብለው ነበር-

“ ለአራት ተኩል ዘመን( 450 ዓመታት) አለብናት፤የተፈጥሮ ሃብቷንና ማዕድኗን በዘበዝናት፣ዘረፍናት።ቀጥለንም አፍሪካውያን የማይረቡና ዋጋ ቢሶች መሆናቸውን አምነው እንዲቀበሉ አደረግን።በሃይማኖት ስም ባህላቸውንና እምነታቸውን አጠፋን።አሁን ደግሞ የስልጡን ትህትናና አሳቢ   በሚመስል መንገድ ብቃት ያላቸውን በትምህርት ዕድል(ስኮላርሽፕ) ሰበብ እያወጣን የምሁር ደሃ አደረግናት።የቀረውን ያልታደለ ምስኪን ሕዝብ ብቃት የሌለው ፣እርስ በርሱ እንዲጋጭና አንድነቱ እንዲላላ፣ለአገሩ ልዑላዊነት እንዳይቆም በማድረግ  በእርሱ ድህነት ጀርባ እራሳችንን አበልጽገን በባዶ ቃላት እንሸነግለዋለን”

Jacques Chirac did say this about Africa!

PARU LE LUNDI, 06 AOÛT 2018 17:32

In these statements attributed to the 22 French president by social media users, it is

said :

“We drained Africa for 4 and a half centuries. Next, we plundered its raw materials. After

that, we said: they (Africans) are good for nothing. In the name of religion, we destroyed

their culture and now, as we have to act with elegance, we are picking their brains with

scholarships. Thereupon, we are claiming that the unfortunate Africa is not in a brilliant

condition, and is not making elites.We divide them to fight to each other and make them unable to defend their sovereignty. Having enriched on its back, we are now lecturing”

ሁለቱም የአገር መሪዎች የተናገሩትን የታሪክ ምስክርነት በሰነድ መልክ ያቀረቡልን ዶር.ጥላሁን ይልማ ሲሆኑ ከሌላ በኩል ያገኘሁትንና ያልተካተቱትን በመጨመር ብዙሃኑ እንዲረዳው በአጭሩ ተርጉሜዋለሁ።በቅድሚያ ለዶር.ጥላሁን ይልማ ታላቅ ምስጋና እያቀረብኩ በትርጓሜው ላይ ግድፈት ቢኖር ከወዲሁ ይቅርታ እጠይቃለሁ።

ይህንን የታሪክ ሰነድ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ለማካተት ያነሳሳኝ አሁንም ቢሆን በነዚህ መመሪያዎች በመመርኮዝ በአፍሪካ በተለይም በአገራችን ኢትዮጵያ የሚካሄደውን ሴራ ለማመልከት ይረዳል በሚል እምነት ነው።አሁን ያለንበት የጎሳ ፖለቲካና የክልል አገራዊ አወቃቀር የዚሁ ንድፈሃሳብ ውጤት መሆኑን  በግልጽ እንደሚያሳይ አልጠራጠርም።በሃይማኖት በኩል የካቶሎክስና የፕሮቴስታንት መስፋፋት አገር ወዳዱን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እንዳዳከመው ሁሉ ኦሮሞኛ  ቋንቋ ተናጋሪው ሕዝብ አገር በቀሉን  ከብዙሃኑ ጋር ሲግባባበት የኖረውን የአማርኛ ቋንቋና የራሱን የግእዝ ፊደል ጠልቶ በላቲን ፊደል የመጻፉ ፍላጎት ለዚሁ ነጮች ለዘሩት  በእራስ ጠልነትና አለመተማመን ብሎም የባርነት ምርጫ ለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም።ለብዙ አገሮች የነጻነት አርማና ምልክት የሆነውን አረንጓዴ ቢጫና ቀይ  ሰንደቅ ዓላማ ጠልቶ የአረቦችና የጀርመኖችን የሚመስል ባንዲራ ማውለብለቡ የባዕዳኑ ጥረት ፍሬ እንዳፈራ የሚያሳይ ነው።

ሌላው የሴራው አካል የሆነው ደግሞ  ያለው  የጎሰኞች ሥርዓትና የክልል አወቃቀር ነው።ይህም እንዲወገድ ነው የብዙሃኑ ትግል።ሆኖም ግን የግለሰቦች የስልጣንና የጥቅም ማስከበሪያ የሆነው የክልል እንሁን ጥያቄ እያደገ መምጣቱ አይካድም።ሌላው ቀርቶ አዲስ አበባን ክልል የማድረግ ፍላጎትም ብቅ ብቅ እያለ መጥቷል።ይህ  ፍጹም አደገኛና ያለውን ስርዓት የመቀበል ዝንባሌ ስለሆነ ሁሉም ሊያወግዘው ይገባል።በተለይም አዲስ አበባ የአንድ ነጠላ ጎሳ ወይም ስብስብ ንብረት ሳትሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ ከተማ በመሆንዋ ለሌሎቹ ኢትዮጵያውያኖች የተነፈገችና በጎሳ አጥር የተከለለች መሆን አይኖርባትም። ከሌሎቹ ክፍላተ ሃገር ወደ መንግሥት ካዝና  የሚፈሰው የግብር ገንዘብ የሁሉም እንደሆነ ሁሉ፣የሁሉም ከተማ በሆነችው በአዲስ አበባ የሚገባው ገቢም የሁሉም ክፍላተሃገር የጋራ ሃብት ነው።አዲስ አበባ ክልልን ለማፍረስ ግንባር ቀደም ሚና ልትጫወት ይገባታል እንጂ የክልል አወዳሽና ተከታይ መሆን አይኖርባትም። በዚህ የክልል እንሁን ጥያቄ ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባል።

አሁንም የምዕራቡ ፣ቻይናና የአረብ አገራት ለአፍሪካ በተለይም ለአገራችን ያሰቡ መስለው የራሳቸውን ጥቅም በማስጠበቁ ላይ እንደተሰለፉ አገር ያወቀው ፀሃይ የሞቀው ሃቅ ነው።በተለይም ላለፉት 30 ዓመታት በወያኔ መራሹ ኢሕአዴግና  አሁን ባለው ኦሕዴድ መራሹ ብልጽግና  የሥልጣን ዘመን ከመንግሥት ባለሥልጣናት  ጋር የመቀራረብና የመቆላለፍ  ጥምር የዘረፋ ክንዋኔ  አገራችንንና ሕዝቡን ለበለጠ አደጋና ችግር አጋልጧል።አንዱን በሌላው እዬተኩ፣በሥልጣን ላይ ማስቀመጥ፣በብድርና በእርዳታ ብሎም በኢንቨስትመንት ስም የአገር ሃብት በቁጥጥራቸው ስር ማድረግ፣ዋናውን ሳይሆን የብድሩን ወለድ የመክፈል አቅም ሲጠፋ  አገራትን በወለድ አገድ የመያዙ አዝማሚያ እየጎላ መጥቷል። ያገር ተቋማትን በዚህም በዚያም ብሎ መያዝ  የወለድ አገድ አንዱ አካል መሆኑ መዘንጋት የለበትም።ለመሻሻልና ለማደግ ይረዳል የሚለው ፕሮፓጋንዳ የማጭበርበሪያ ዘዴ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል።አገር ይሻሻል ከተባለ ምንም ያህል አዳጋች ቢሆን በራሱ ዜጎች እውቀትና ሃብት ማሻሻል ይቻላል።ዋናው ቁም ነገር ለዚያ የሚያበቃ  አገር ወዳድነትና ቁርጠኝነት ያለው ስርዓት ማስፈን ነው።

ከላይ በታሪክ ሰነዱ ላይ እንደታዬው የተማረውን በስልጠናና በሥራ ዕድል ሰበብ ከአገሩ እንዲወጣ የማድረጉም ስልት እንደቀጠለ ነው።ለአሜሪካም ሆነ ለአውሮፓ የመኖሪያ ዕድል(ሎተሪ) ከሁለተኛ ደረጃ በላይ ትምህርት ያለው እንጂ ከዚያ በታች ያለው ለማመልከት አይፈቀድለትም።ገና ከጅምሩ ያንን ካላሟላ ተቀባይነት አይኖረውም።እንግዲህ ከዚያ ደረጃ ለመድረስ አገርና ቤተሰብ ያወጡት ወጭና ያሳለፉት ድካም ለአገር ጥቅም ሳይሰጥ ለባዕዳን የርካሽ ጉልበት ምንጭ ይሆናል ማለት ነው።የተማረው እዬወጣ ሲሄድ አገር ሊያሳድግ የሚችል ሃይልና ትውልድ አይኖርም ማለት ነው። ይሆናል፣ሆኗልም።ሥራ በማጣትና በድህነት ኑሮ አዳጋች የሆነበት ወጣት ትውልድ ከአገሩ ይልቅ የሌላው አገር ኑሮ ቀልቡን እዬሳበው አገሩን ለባዕዳን እያስረከበ ስደት የኑሮ ዘይቤ ሆኖት ይቀራል ማለት ነው።ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት እግሩ እንዳደረሰው ብዙ አደጋዎችን አልፎ የሞተው ሞቶ የተረፈው በዬአረብ አገራቱ በግርድናና በአሽከርነት እዬተሰማራ የስቃይ ኑሮ ሲገፋ ጥቂቱ በላስቲክ ጀልባ ተሳፍሮ ሜዲትራኒያን ባህርን ለማቋረጥ የቻለው ለአውሮፓ መሬት ይበቃል።በዚህ ሁሉ መከራና ውጣ ውረድ ያለፈው ሁሉም ኑሮ ይሳካለታል፣ የሚሻውን ያገኛል ማለት አይደለም።

አሁን የተያዘው ሌላው ዘዴ ደግሞ በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ያለው ግለሰብ በአውሮፓ አገሮች  የመኖሪያ ፈቃድ እንደሚያገኝ የወጣው መመሪያ ነው።የተማረው እውቀቱን፣ ገንዘብ ያለው ገንዘቡን ይዞ ሲኮበልል አገር ባዶውን ይቀራል፤ለወራሪዎች አመቺ ይሆናል ማለት ነው። ሃብታም ሃብቱን ይዞ ሲፈረጥጥ የአገር ኤኮኖሚ እዬገደለ የውጭ አገር ኤኮኖሚ እንዲያድግ ይረዳል ማለት ነው።የሚጠዬቀውን ያህል  ገንዘብ የሚይዙት ደግሞ አብዛኞቹ ባለሥልጣኖች፣ የባለሥልጣኖቹ ዘመድ አዝማዶችና የጥቅም ተባባሪዎቻቸው ናቸው።በአጭሩ አባባል አገር የዘረፉ ሌቦች ናቸው።

አገርን ለመታደግና የእራስን ክብር ለማስጠበቅ ለችግር እጅ ሳይሰጡና ለሚዘረጋው ወጥመድ ሳይመቹ በኢትዮጵያዊነት ኮርቶ የችግሩ ምንጭ የሆነውን ማድረቅ ይገባል።

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ለዘለዓለም ተከብረው ይኑሩ!!

አገሬ አዲስ

3 Comments

  1. ማኮሌይ ስለ ኢትዮጵያ አለ የሚባለው ሃሰት ነውና ይታረም፡፡ ጽሑፉ ብዙ ቁም ነገር ይዟልና በዚች ስህተት እንዳይመዘን ያሰጋል፡፡

  2. ሎርድ ማኳይ የሰጠዉ አስተያየት ከዚህ በፊት ወገኖች ተቀባብለዉት ወደ እኔ አድርሰዉት ነበር በሀገር ቁጭት ሰሜት ለመመርመር ሞክሬ የተሰጠዉ አስተያየት ለእኛ ሀገር ሳይሆን ለህንድ እንደነበረ ነዉ የተረዳሁት። ይህ ነገር የአኖሌ ታሪክ እንዳይሆንብን አቅሙ ያላቸዉ ዜጎች አንጥረዉ ቢልኩልን መልካም ይመስለኛል ኢትዮጵያዉያን የነጠረ ነገር ካልሆነ አይመቸንም ጤናም ይነሳናል በዚህ አይነት እኛስ ከነህዝቅኤል ጋቢሳ በምን ተለየን?

  3. የአዲስ አበባን የክልልነት ጥያቄ ምንም አደገኛ አይደለም። አንድ ካለመረዳት ወይም ደግሞ የአዲስአበባ መጠንከር የማይፈልግ ካልሆነ በስተቀር። አዲስ አበባ በአዲስ አበቤ ማንነት ክልል ቢሆን እራሱን የማስተዳደር መብቱን ያገኛል።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.