የዐማራው ሕዝብ እልቂት በትእግስት ሊቆም አይችልም – አክሎግ ቢራራ (ዶር)

አክሎግ ቢራራ (ዶር)
October18, 2020

“ዐማራን እየገደሉ ኢትዮጵያን መግዛት የከሰረ ፖለቲካ ነው”

                    የጎንደር ሕዝብ በሰላማዊ ሰልፍ ያሰማው መፈክር

“በእኔ ዘመን አሳዳጅና ተሰዳ አይኖርም”

                    ጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ አሕመድ አሊ

ክፍል ሶስት

በመናገር እና የተናገሩትን ወደ ተግባር በመለወጥ መካከል ሰፊ ልዩነት አለ። መናገር ቀላል ነው። የተናገሩትን በመሬት ላይ ስኬት ለማድረግ ግን ልዩነቱን ለማወቅ መስፈርቱ ጉዳዩ የሚመለከተውን ወገን መጠየቅ አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ፤ የዐማራው ሕዝብ በተከታታይ በማንነቱና በእምነቱ ብቻ እየተለየ ሲጨፈጨፍ ጭፍጨፋው ምን ያህል ነው? ከማለት ይልቅ የተጎዱትን ሂዶ ማነጋገርና ጭፍጨፋው ወደፊት እንዳይደገም እርምጃ መውሰድ የባለሥልጣናት ሚናና ሃላፊነት መሆኑን መቀበል ነው። ለተጎዱት ሃዘንና ቁጭትን መግለጽ አግባብ አለው። የሰው ህይዎት ብርቅ ነው የሚለውን እሴት ከተቀበልን– እኔ አምንበታለሁ–ይህን እሴት በተግባር ማሳየት ግድ ይላል። የሚደረገው ግን ግራ የሚያጋባና ወደ ተሳሳተና ወደ የተባባሰ እልቂት የሚያመራ ሁኔታ ነው።

ለምሳሌ፤ ስንት ሰው ተጨፈጨፈ ወደሚል የሂሳብ ቆጠራ እየገቡ አሳሳቢነቱን በቸልታ የሚመለከቱ ባለሥልጣናትና ተመልካቾች አያለሁ። እኔን በተለየ ደረጃ የሚዘገንነኝ፤ ይህን የሂሳብ ቆጠራ የሚናገሩ ኢትዮፕያዊያን ነን የሚሉና በተለይ ዐማራዎች መኖራቸው ነው። ሰው ክቡር ነው፤ አንድም ሰው ቢሆን በማንነቱና በእምነቱ ብቻ ተለይቶ ሲገደል የዚህ ህይወት ያገባኛል የሚል እንዴት ሊጠፋ ቻለ? የዐማራው ህይወት ከማን ይለያል? ዐማራው ሆነ አገውው በቤኔ-ሻንጉል ጉሙዝ በተደጋጋሚና በሚዘገንን ደረጃ፤ ዐማራውና ኦሮሞ አይደለህም ተብሎ፤ ኦሮሞም ቢሆን ሌላ በእምነቱ መስፈርት እየተለየ እየተፈረደበት ደግሞ በኦሮምያ በተከታታይ ተጨፍጭፏል፤ ታርዷል፤ ተባሯል፤ ከንብረቱና ከቤቱ ተፈናቅሏል፤ ንብረቱ ተቃጥሏል።

ብንቀበልም፤ ባንቀበልም፤ የዐማራ ሕዝብ እልቂት (ጀኖሳይድ) ተካሂዷል።

ዘውግንና ኃይማኖትን ለይቶ ማንንም ሰብአዊ ፍጡር መጨፍጨፍ የሕዝብ እልቂት ወይንም ጀኖሳይድ ነው። ሌላ ትርጉም የለውም። ጀኖሳይ (Genocide) የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመው የፖላንዱ ተወላጅ ራፋኤል ሌምኪን ነው። በ 1944 genos የግሪክ ቋንቋ ማለትም ዘር ወይንም ነገድ እና የላቲኑን ግድያ (cide) አጣምሮ ጀኖሳይድ የሚለውን ዓለም የተቀበለውን ጽንሰ ሃሳብ ፈጠረ። ይህን ቃል ተጠቅሞ ናዚስቶች አይሁዶችን የጨፈጨፉትን ወንጀል አብራርቶ ለዓለም ሕዝብ አቀረበው። ናዚስቶች ብዙ ሚሊየን የሚገመቱ አይሁዶችን በዘውጋቸው (በማንነታቸው) እና በእምነታቸው እየለዩ ጨፈጨፏቸው።

ይህን ጭፍጨፋና ወንጀሉን የፈጸሙትን ናዚዝቶች ቅጣት ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ በ 1946 ዓ.ም. ረቂቅ አወጣ። በ1948 ዓ.ም. ጀኖሳይድን ወንጀል ያደረገው ሕግና መመሪያ “የጀኖሳይድ ደንብ (The Genocide Convention)” ጸደቀ፤ እስከ 2019 ድረስ ባለው ጊዜ 149 አገሮች ተቀብለውታል። ይህን የዓለም ሕግ በፍርድ ቤት የሚያስተዳድረውና የሚተረጉመው የዓለም አቀፍ የእልቂት ፍርድ ቤት (The International Court of Justice (ICJ) ይባላል። የዓለም ሕግ አለ ማለት ነው። ደንቡን የፈረሙ አገሮች ሁሉ ይህን ሕግ ተግባራዊ የማድረግ ግዴታና ሃላፊነት አለባቸው። እልቂት ከፈጸመ፤ ማንም ሰው ቢሆን ከሃላፊነት ነጻ ሊሆን አይችልም።

የዐማራው ጭፍጨፋ ወንጀል ነው።

ትርጉሙን ባጭሩ ላቅርበው። የእልቂቱ የወንጀል ስምምነት ትርጉም አንቀጽ ሁለት እንዲህ ይላል። ጀኖሳይድ ወይንም የሰው እልቂት ማለት “በአንድ ዘውግ ወይንም ዘር ወይንም የእምነት ተከታይ ላይ፤ በከፊል ሆነ በሙሉ የአካል ጉዳት ወይንም የአእምሮ ጉዳት መፈጸም፤ ልጅ እንዳይወልድ መበከል ውይንም ማምከን፤ የወለደውን ወደ ሌላ ዘውግ ወይንም ኃይማኖት ማቀላቀል” በዓለም ሕግ የተከለከለ ወንጀል ነው።

ይህን ድንጋጌ ለመቀበል የቻለ ግለሰብ ወይንም ባለሥጣን ወይንም ሌላ ተመልካች ህሊናው የሚያስገድደው ጭፍጨፋውን መካድ ሊሆን አይችልም። ከካደ ግን በሌሎች አገሮች የተፈጸሙትን ወንጀሎች ስከታተላቸው፤ ለምሳሌ በቀድሞዋ ዩጎስላቭያ፤ በካምቦዲያ፤ በሯዋንዳና በሌሎች እልቂት በተካሄደባቸው አገሮች ሲገመገም፤ በተባባሪነት እና በሃላፊነት ሊያስጠይቀው ይችላል።

ለዐማራው ሕዝብ እልቂት ሌላ መገምገሚያ ወይንም መስፈርት ሊፈጠርለት አይችልም።

የዐማራውን ሕዝብ እልቂት፤ ግፍና በደል በሚመለከት የዛሬ አምስት ዓመት በመረጃ ተደግፎ ሞረሽ ወገኔ የተባለው ተቋም ለተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ኮሚሺን የላከውን መረጃ ከታች ባለው ሊንክ እንድትመለከቱት አባሪ አድርጌዋለሁ።

https://mail.google.com/mail/u/0/?tab=wm&ogbl#inbox/FMfcgxwKhqmkdTBrgjMjQGdrFJhQcWpq?projector=1&messagePartId=0.1

በተጨማሪ፤ በ2015 ዓ.ም፤ ልኡል ሃሰን የተባበሩት መንግሥታት ሰብአዊ ኮምሺን ከፍተኛ ኮሚሺነር በነበሩበት ወቅት 127 ገጽ የተጨፈጨፉ ዐማራዎችን የስም ዝርዝር የያዝ ሰነድ ከመሸኛ ደብዳቤ ጋር አያይዠ ልኬ “ክስ ለማቅረብ ከፈለጋችሁ የሚሞሉትን ሰንዶች ሞልታችሁ አቅርቡ” የሚል መልስ ከሳቸው ቢሮ ደርሶን ነበር። ባለሞያዎች ያስፈልጉ ስለነበርና ብዙ ወጭ ስለሚያስከትል ጉዳዩን ለመከታተል አልተቻለም።

ቁም ነገሩ፤ በዐማራው ሕዝብ ላይ ጭፍጨፋ የተጀመረው ዛሬ አለመሆኑን ለማስታወስና የዐማራው ሕዝብ ተቆርቋሪ ወገኖችም ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ እንደ ነበርና አሁንም እንድሚያደርጉ ላሰምርበት ስለፈለግሁ ነው።

ወጣቱ ትውልድ እንዲያውቀው ለናሙና ያህል በዐማራው ሕዝብ ላይ ከ1991-2015 ዓ.ም ድረስ የተካሄደውን የእልቂት ቦታዎች ላቅርብ፤

 1. በምእራብ ሃረርጌና በአሩሲ በተደጋጋሚ ከ1991-2015 እና ከዚያ ወዲህ ደግሞ በተከታታይ፤
 2. በወለጋና በመተከል (ቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ ከ1999-2001 በተከታታይ፤ ከዚያ ወዲህ በመተከል በተደጋጋሚ፤
 3. በጉራ ፈርዳ ከክ2012-2014 በገፍ ማፈናቀል፤
 4. በጅማ ከ2004-2005 በገፍ ማፈናቀልና መግደል፤
 5. በወለጋ ከ1999-2001 በገፍ ማፈናቀል፤ መግደል፤
 6. በአምቦ፤ ጂማ፤ ጉራ ፈርዳ ከ2014-2015 በገፍ ማፈናቀል፤ መግደል፤

ለተባበሩት መንግሥታት አቤቱታ ስናቀርብ የተጨፈጨፉ ስሞችንና ቦታዎችን መረጃ አባሪ አድርገን ነው፤ ከላይ የተጠቀሱትን ጨምረን። አቤቱታውን ካሰማን ወዲህ ያለው ሁኔታ ቀደም ሲል በወልቃይት ጠገዴ፤ ሰቲት ሁመራና ሌሎች የዐማራ ሕዝብ አንጡራ መሬቶች ነዋሪዎች ላይ ህወሓትና ሌሎች ጽንፈኞችና ብሄርተኞች የፈጸሙት ወንጀል፤ በተለይ ህወሓት በበላይነት ይመራው የነበረው የኢህአዴግ መንግሥት ስልጣን ከያዘ በኋላ ደግሞ ኦነጋዊያንና ጅሃዲስቶች በህወሓት አጋርነት በሃረር፤ በድሬ ዳዋ፤ በአሩሲና በሌሎች በኦሮሞ ክልል በሚገኙ ቦታዎች ላይ በተከታታይ ያካሄዷቸው እልቂቶች በድምራቸው ያሳዩት ገጽታ፤ ከቁጥሩ ልዩነት በስተቀር በአይነቱና በካኔው በአይሁዶች ላይ ከተካሄደው አይለይም።

ለየት የሚያደረገው ግን፤ እናት በልጇ ሬሳ ላይ እንድትቀመጥ መደረጉ፤ የሰውን እሬሳ እንደ ከብት እየቆራረጡ ትእይንት እንዲታይበት መደረጉ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን በዘውግ የሰብአዊ መብት ጥብቅና ስም በኢትዮጵያ የሚካሄደው እልቂት ከእንስሳ በታች ዝቅ ያደረገን መሆኑን ያሳያል።

ህወሓት የፈጸመው ግፍና ወንጀል እንዳለ ሆኖ፤ በተለይ ይህ ጠባብ ብሄርተኛና ዘረኛ ቡድን በወልቃይት ጠገዴ፤ ጠለምት፤ ሰቲት ሁመራ ያካሄደው ግፍ፤ በነዋሪዎቹ ላይ ያካሄደው ጭፍጨፋ፤ በደልና በተለይ የትግራይን ክልል ለማስፋፋት ያካሄደው በሚቀጥለው ገጽ የቀረበው የመሬት ነጠቃ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊተላለፍ የሚችል ወንጀል ነው።

የወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምት፤ ሰቲት ሁመራ፤ ራያና አዜቦ የዐማራ ሕዝብ ይህ ሁሉ ግፍና በደል ከተካሄደበት በኋላም እንኳን በማያሻማ ለህወሓት የሰጠው መልስ አንድ ብቻ ነው። ይኼውም፤ ከአያትና ከቅድመ አያት ጀምሮ አካባቢውና የአካባቢው ሕዝብ የትግራይ አካል ሆኖ አያውቅም የሚል ነው። በባህሉ፤ በስነልቦናው፤ በታሪኩ፤ በሽለላው፤ በእምነቱ፤ በወግ በማእረጉ፤ በጋብቻው፤ በቀብር ስነስርዓቱ፤ በቋንቋው፤ በሰርጉና በሌላው ሁሉ በማያሽማ ደረጃ ከዐማራው ዘውግ ጋር የተቆራኘና በምንም ሊለይ የማይችል መሆኑን አስመስክሯል፤ አቤቱታውን ለዐማራው ክልልና ለፌደራሉ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ አቅርቧል;፡

የወልቃት አስመላሽ ኮሚቴ የተቋቋመበትና ለህወሓት ሳይምበረከክ እስካሁን የሚታገለው አላማውን ስኬታማ ለማድረግ ነው።

ህወሓት ሊነጥቀውና ወደ ታላቋ ትግራይ ሊያቀላቅለው የሚፈልገውን የመሬቱን ስፋትና ጂኦፖለቲካዊ አቀማመጥ በጥሞና ማየት አስፈላጊ ነው። መሬቱ ለልማት ወሳኝ ስለሆነ ይህን መሬት መንጠቅ ማለት፤ ባለፈው ሃተታየ እንዳሳየሁት የዐማራውን ጉረሮ እንደማነቅ ነው።

የወልቃይት ጠገዴ፤ ጠለምት፤ ሰቲት ሁመራ፤ ራያና አዜቦ ነዋሪ ሕዝብ “መጤ” ነው ብሎ የሚከራከር የህወሓት ደጋፊ ምሁር የለም። ቢያንስ ቢያንስ፤ የአካባቢው ሕዝብ ከትግራይ ሕዝብ ጋር ተስማምቶ፤ ብዙ ጊዜ ተጋቦቶ በሰላም የሚኖር ስለሆነ፤ የሚያዋጣው መፍትሄ ዘረኛነትን፤ ጠባብ ብሄርተኛነትን፤ ጎጠኛነትን አስወግዶ ከጥንት ጀምሮ እንደተለመደው በስምምነት መኖር ብቻ ነው።

ኦነጋዊያን፤ ጃዋራዊያንና ጅሃዲስቶች ግን ይህንንም መፍትሄ ለማስተናገድ ፈቃደኛ ሆነው አይታዩም። ይህ ግትርና ኋላ ቀር አስተሳሰብ ለማንም አይበጅም፤ መለወጥ አለበት።

የኢትዮጵያ የድህነት መሰረታዊ ምክንያት ወይንም መንስኤ የዐማራው ሕዝብ አይደለም። ከጥቂት ዓመታት በፊት አልጀዚራ የዐማራውን ክልል የልማት መጠን ከሌሎቹ ክልሎች ጋርና ከዓለም ድሃ ህዝቦች ጋር አነጻጽሮ የዐማራው ሕዝብ በመላው ኢትዮጵያና ጥቁር አፍሪካ፤ ከዚያም አልፎ በመላው ዓለም ከሚገኙ ተነጻጻሪ በድህነት ከሚሰቃዩ ህዝቦች መካከል አንደኛውን ደረጃ የያዘ ነው ብሎ ደምድሟል፤ ለምሳሌ በአይን ስውርነት፤ በመጠጥ ውሃ አቅርቦት ዝቅተኛኘንት፤ በኤሌክትሪክ መብራት አቅርቦት ማጣት፤ በንፅህና መጓደል፤ በምግብ እጥረትና እጦት፤ በትምህርት ቤት ኋላ ቀርነት፤ በስራ እድል አጥነት ወዘተ የሚሰቃየውን በብዙ ሚሊየን የሚገመት ሕዝብ ዘገባ አድርጎ።

የዚህ ድሃ ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ እስካሁን አልተሻሻለም።

welkeit

የኦነግ ሽኔ ሆነ የጅሃዲስት አባል ኦሮሞ ያልሆነውን ወይንም ኦሮሞም ሆኖ የክርስትና እምነት ተከታይ የሆነውን፤ በተለይ ደግሞ በተከታታይ ዐማራና የተዋህዶ እምነት ተከታይ የሆነውን ክፍል ለይቶ ስም አውጥቶለታል።

“መጤን” እንደመለያ እንውሰድ፤ ምን ማለት ነው? መብት የሌለው፤ ሊወገድ የሚችል ማለት ነው። በአሜሪካ ፕሬዝደንት ትራምፕ እንዲህ ብለው ነበር። “ከሜክሲኮ የሚመጡት ሜክሲካኖች ሁሉ በጀምላ ወንጀለኞች፤ ሴቶቻችን የሚደፍሩ፤ መወገድ ያለባቸው ናቸው” ብለው ወነጀሏቸው። ትራምፕ በምንም የማይቀበሉት ነጮች አሜሪካን ከመውረራቸው በፊት ነዋሪዎቹ “ህንዶች” መሆናቸውንና ነጮች እነዚህን ጥንታዊ ነዋሪዎች (Indigenous people) እንደ ጨፈጨፏቸው ነው። አሁንም ሃብቱና መሬቱ ሁሉ የነጭ እንጅ የጥንታዊዎቹ ህንዶች፤ አሜሪካን በላቫቸው የገነቧት የጥቁር አሜሪካኖች፤ የሂስፓኒኮች ወዘተ አይደለም የሚል የፈጠራ ትርክት በግልጽ ይሰማል።

በተመሳሳይ፤ ኢትዮጵያ ቢያንስ የሶስት ሽህ ዓመታት ታሪክ አላት። አሜሪካ መንግሥት ከመመስረቷ በፊት ኢትዮጵያ የታወቀ ሥልጣኔ፤ አስተዳደር፤ ፊደል፤ የቀን መቁጠሪያ፤ የባህር በር፤ ዳር ድንበር፤ እስከ ሕንድ አገር ድረሥ የንግድ መስመር ዘርግታ ነበር  ወዘተ የሚለውን ሁሉ ጠባብ ብሄርተኞችና ጽንፈኞች ይህችን ጥንታዊት አገርና መላውን ህዝቧን አንቀበልም ብለው በአሁኑ ወቅት ሌላው ቀርቶ አዲስ አበባን ለማጠርና የዐማራው ሕዝብ በመሰረታትና በሞተላት ኢትዮጵያ እንዳይንቀሳቀስ እያደረጉ ነው። “መጤ ነህ” እና ወደ መጣህበት ሂድ፤ መብት የለህም  የሚለውን የተሳሳተና አደገኛ ብሂል ከፍ አድርገውታል (Have escalated the level of polarization and conflict to the edge).

ፕሮፌሰር ሃብታሙ በቅርቡ በጻፈው የታሪክ መጽሃፍ፤ በራራ፤–ቀዳማዊት አዲስ አበባ እንዳሳሰበው፤ የዛሬይቱ አዲስ አበባ የምትገኘው በአጼ ዳዊት ዘመነ መንግሥት (1380-1413) ተመስርታ በወቅቱ የዘመናዊነት ተምሳሌት ሆና የአስተዳደር፤ የንግድ፤ የውጭ ግንኙነት ወዘተ ማእከል በነበረችውና እስከ አጼ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት ድረስ (1508-1540) የኢትዮጵያ መንግሥታት ዋና ከተማ ሆና ያገለገለችው ጣሊያኖች፤ ፈረንሳዮች፤ አረቦችና ሌሎች ይኖሩባትና ይነግዱባት የነበረች በጥቁሩ ዓለም ከፍተኛ እውቅና የነበራት ከተማ ናት። ኢትዮጵያ በዚያ ወቅትና ከዚያ በፊት፤ ጥናትና ምርምር ያደረጉ ምሁራን የሚያስተምሩን ከግብጽ ጋር ተወዳዳሪ የሆነ ሥልጣኔ እንደ ነበራት ነው። ላሰምርበት የምፈልገውና ወጣቱ ትውልድ እንዲያውቀው የምመኘው ሃሳብ፤ ይህችን ጥንታዊ ከተማ የመሰረቷት ኢትዮጵያዊያን ስለሆኑ “መጤዎች” ሊሆኑ አይችሉም፤ ጥንታዊ ነዋሪዎች ናችው የሚለውን ነው።

የበረራ ከተማ ወይንም ጥንታዊ አዲስ አበባ የሚከተሉትን ስኬታማ አድርጋ ነበር።

 • ዲፕሎማቶች ውይይት ያደርጉባት ነበር፤ የውጭ አምባሳደሮች ያዘወትሯት ነበር፤
 • ጉባኤዎችና ልዩ ልዩ ስብሰባዎች ይካሄዱባት ነበር፤
 • የእደጥበብ ባለሞያዎች መናኸሪያ ነበረች፤
 • ሶሪያዊያንና ሌሎች ይነግዱባት ነበር፤ የአካባቢው ገበሬ ምርቱን ለገበያ ያቀርብባት ነበር፤
 • በአጭሩ በራራ ቋሚ መዲና ነበረች። **

** ለተጨማሪ መረጃ፤ የሃብታሙ መንግሥቴ ተገኝን “በራራ—ጥንታዊት አዲስ አበባ (1400-1887) ይመልከቱ። ከአማዞን ለማዘዝ ይቻላል፤ አዲስ አበባም ይሰራጫል።

እድገትና ልማት ተከታታይነት ከሌለው ድህነትና ኋላ ቀርነት አይቀርም። በራራ ስትወድም አብሮ የወደመው እድገትና ልማት ነው። ባለፈው ሰኔ በሻሻመኔ ከተማ የተካሄደው ውድመት ተመሳሳይ ነው። እያወደሙ መልማት አይቻልም።  መሰረታዊው ጥያቄ በራራን ማን አወደማትና ለምን? የሚለው ነው። በራራ የወደመችው የእስልምና ኃይማኖትን መለያና ያማከለ ባደረገው በግራኝ ሞሃመድ ወረራ፤ ጦርነትና አጥፊነት ምክንያት ነው። ግራኝ ሞሃመድ ለ14 ዓመታት ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያዊነትን ተቋማት በሙሉ በሚባል ደረጃ አውድሟቸዋል። ሲያወድም፤ ንጽሃንን ማረድ ብቻ አልነበረም፤ አንድም የተቋም፤ የታሪክ፤ የባህል ምልክት እንዳይኖር ባደረገ ደረጃ ነው። ሌላው ጥንታዊ ነዋሪዎቹን ሲጨፈጭፍና ተቋማቶቻቸውን ሲያቃጥል፤ አብሮ ያመቻቸው “የኦሮሞዎቹን ወረራና መስፋፋት ነው።”

ፕሮፌሰር ሃብታሙ በመረጃ ተደግፎ እንዳሳየው ከ1529-1543 ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ ግራኝ ሞሃመድ ሆነ ብሎ አብያተ ክርስቲያናትን፤ ገዳማታን፤ ጽሁፎችን አውድሟል፤ የልማት መሰላሎችን አቃጥሏል። ዛሬ በየአካባቢው፤ በተለይ በቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝና በኦሮምያ በዐማራው፤ በአገው፤ በጉራጌውና በሌላው ንጹህ ሕዝብና በተዋህዶ እምነት ተቋማት ላይ በተቀነባበረ ደረጃ የሚካሄደው እልቂት፤ የተቋማት ውድመት የሚያስታውሰኝ በግራኝ ሞሃመድ ዘመን የተካሄደውን ውድመት፤ እልቂትና ድክመት ነው። ኢትዮጵያ ለምን ድሃና ኋላ ቀር ሆነች? ለሚለው መሰረታዊ ጥያቄ መልስ ለማግኘት የሚቻለው የውስጥ ጽንፈኞችና ጀሃዲስቶች ክውጭ ኃይሎች ጋር ተባብረው የሚያካሂዷቸውን ግፍና በደሎች በአንክሮ ስናጤናቸው ብቻ ነው።

በግራኝ አጥፊ ወቅት ምን ሆነ? ምን ለመማርና ለማድረግ እንችላለን?

ኢትዮጵያን ያዳከሟትና ያፈራረሷት ሶስት ኃይሎች ናቸው፤ ተቀነባብረው፤ እነዚህም፤

 1. በግራኝ የተቀነባበረው፤ በተለይ ኢትዮጵያን የእስልምና እምነት ተከታይ አገር ለማድረግ የተቀናጀው አጥፊ ኃይል፤

 

 1. በእስልምና እምነት ዙሪያ የተሰበሰቡት የጂሃዲስቶች ኃይል ስብስብና ቅንብር፤ የግራኝ አጋሮች የምላቸው፤ አል ሻባብ፤ አልኬይዳ፤ ቦኮሃራም፤ “የኦሮሞ እስልምና እምነት” አክራሪዎች የሚያደርጉትን ግፍና በደል ማየት በቂ ነው፤

 

 1. የመአከላዊ መንግሥት ድክመት መኖሩን ከግምት ውስጥ ያስገቡት የኦሮሞ ዘውግ ተስፋፊነትን የተቀበሉ የጽንፈኞችና ብሄርተኞች ኃይል፤
 2. በብሄር፤ ብሄረሰብና ሕዝቦች እየተመካኘ የሚካሄደው የእምቢተኞችና እኛ ካልገዛን በስተቀር ኢትዮጵያ “ትውደም (Down, Down Ethiopia and Down, Down Abiy”) የሚሉት ኃይሎች ቅንጅት።

ለማስታወስ መለስ ዜናዊ በበላይነት ኢትዮጵያን ሲመራ በጻፍኩት መጽሃፌ እንዳሳየሁት የገጠርና የከተማ መሬት በገፍ ከነዋሪዎቹ እየተነጠቀ፤ እንደ ካራቱሪ፤ አላሙዲ ለሆኑ፤ በዝቅተኛ ደረጃ ሲገመት ከ36 አገሮች ለመጡ ባለኃብቶችና በሚዘገንን ደረጃ ለትግራይ ተወላጆች ይቸረቸር ነበር። ዛሬ ደግሞ ህወሓትን የተካው “የኦሮሙማ” ቡድን የሚባለው ቅርምቱን ተያይዞታል።

የመሬት ነጠቃና መስፋፋት ከሕዝብ ስርጭት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው። በወልቃይት ጠገዴ፤ በጠለምት፤ በሰቲት ሁመራ፤ በራያና አዘቦ አካባቢዎች የሆነውን ማስታወስ አስፈላጊ ነው።

ምን ሆነ? ህወሓት በእነዚህ አካባቢዎች ነዋሪውን ሕዝብ በገፍ እያስለቀቀ፤ እየገደለ፤ እያሰረና እያሳደደ የራሱን የዘውግ አባላት ትግራዮችን አስፍሯል። የትግራይ ሕዝብ በየትኛውም ኢትዮጵያ የመኖርና ኃብት የመያዝ መብት አለው፤ ግን ህወሓትም ሆነ ኦነግ ሌላውን ኢትዮጵያዊ ከኃብትና ከመኖሪያው የማስለቀቅ መብት የለውም። በመሬት ላይ የሚታየው ግን ከዚህ የተለየ ነው።

በተጨማሪ፤ የፌደራሉ መንግሥት የሕዝብ ቆጠራ የዐማራውን ሕዝብ ቁጥር የመቀነስ መብት የለውም። ግን ሆኗል። ለምሳሌ፤ የዐማራው ሕዝብ በሁለት ሚሊየን አምስት መቶ ሽህ ቀንሷል የሚለው ዐማራውን ከመጉዳትና ክማጥፋት ሴራ ጋር የተያያዘ ሆኖ አየዋለሁ። ሌላው ልጠቅሰው የምገደደው ከዐማራው ክልል ውጭ የሚኖረው በብዙን ሚሊያን የሚገመተው የዐማራ ሕዝብ እንደ ሌላው ዘውግ የማንነት መብቱ ለምን አይከበርም? ለምን ማንነቱ እንዲጠፋ ይደረጋል? የሚለውን ነው። ዐማራው ለመኖር ራሱን እንዲክድ ማስገደድ ራሱ ወንጀል ነው።

በኦሮምያ ክልል ለመኖር ዐማራው ኦሮሞ መሆን የለበትም። በተመሳሳይ፤ በባህር ዳር ወይንም በጎንደር ለመኖር ኦሮሞው ዐማራ መሆን የለበትም፤ ትግራዩ ማንነቱ ተከብሮ የሚኖርባቸው ከተማዎች መሆናቸውን ከልጅነቴ ጀምሮ አውቃለሁ። ሁሉን አስተናጋጅ የሆነ አገዛዝ እና (All inclusive governance) የሁሉም ኢትዮጵያዊያን አገር አለችን ለማለት የምንችለው እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በየትኛውም ኢትዮጵያ የመኖር መብቱ/መብቷ ሲከበር ብቻ ነው። የብሄር ተኮሩ ፌደራል ሕገ መንግሥትና የክልሉ አስተዳደር ማነቆ መሆኑን ካልተረዳን ግን ሁሉን አቀፍ አገዛዝ ለመመስረት አንችልም።

ጠባብ ብሄርተኛነትንና የብሄር ጽንፈኛነት ማነቆነትን በተናጠል አላያቸውም። ከላይ ያቀርብኳቸው አራት አድካሚ ተግዳሮቶች የሚሰሩት በመናበብ ነው። ጅሃዲስቶች ወንፊት ይፈልጋሉ፤ መግቢያ ቀድዳዳ ማለቴ ነው፤ ግብጾችም እንደዚሁ።

በሃያኛውና በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ጅሃዲዝም ተብሎ የተሰየመው፤ የአሜሪካን የኢኮኖሚ እምብርት ኒውዮርክን ለጥቃት ያበቃው የአመጸኞች እብሪት በተቀነባበረ ደረጃ የተጀመረው በኢትዮጵያ ነው ብል የተሳሳኩ አይመስለኝም። የዛሬ 400 ዓመት ማለት ነው።

በአሁኑ ወቅት የጸረ-ኢትዮጵያና ጸረ-ኢትዮፓጵያዊነት ኃይሎች የሚያካሂዷቸው፤ በተለይ ለዘላቂ እርጋታ፤ ለሰላምና ለልማት ተግዳሮት የሆኑት ምልክቶች ምን ይመስላሉ?

 • የእርስ በእርሥ ግጭትና ጦርነት እንዲነሳ ማድረግ፤
 • የስርዓት አልባነት፤ የውንብድና፤ የሌብነት፤ የሙስና፤ ህገወጥ የሆነው የመሳሪያ ንግድ፤ የመሬት ነጠቃና መስፋፋት፤ የተተኪነትና የሽብርተኛነት ጥልቀትና ስፋት መከሰት፤
 • የጠባብ ብሄርተኛነትና ጽንፈኛነት ሴረኞች ከውጭ ኃይሎች ጋር ትሥስር መፍጠራቸው፤ ለምሳሌ ህወሓት፤ ኦነጋዊያን፤ የጃዋር ደጋፊዎችና የአገር ውስጥ ጅሃዲስቶች ከግብጽ ጋር መተባበራቸው፤
 • የአገር ውስጥ የፖለቲካ ውድድር ራስንና ቡድንን ከማገልገል፤ ማለትም፤ ከካድሬነት ባሻገር አገራዊ፤ ብሄራዊ ጥቅምንና ኢትዮጵያዊነትን የሚያንጸባርቅ አለመሆኑ፤
 • የፖለቲካውን የማህበረሰባዊው ባህል ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት አለመቻሉ። አንድ ቀላል ምሳሌ ልስጥ፤ ህጻናት በጥላቻ አይወለዱም። ጥላቻን የሚማሩት ከወላጆቻቸው፤ ከትምህርት ግብአት፤ ከስልጠና፤ ከጎረቢት፤ ከጓደኛ፤ ከፖለቲካ ልሂቃን ወዘተ ነው። ከልዩ ልዩ ዘውጎች ህጻናትን በአንድ ላይ እየዋሉ ተመሳሳይ እሴትና ትምህርት ቢሰጣቸው የሚኖረው ውጤት የተለየ እንደሚሆን ጥናቶች ያሳያሉ።

“መጤ፤ ነፍጠኛና ትምክህተኛ” የሚሉት የዐማራ መለያዎች ለይቶ ለማጥቃት፤ ለመጨፍጨፍና ለማባረር፤ በኣጭሩ ለእልቂቶች መሳሪያ ሆነዋል። በቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ ሌላም ተጨማሪ የዐማራ መለያ አለ፤ ይኺውም “ቀይ” የሚል ነው፤ ከጉሙዙና ከሌላው ኢትዮጵያዊ ለመለየት መሆኑ ነው። ዓለም በተሳሰረበት ባአሁኑ ወቅት፤ እኛ “ቀይ፤ መጤ፤ ነፍጠኛ” ወዘተ እያልን ኢትዮጵያን እያዳከምናት ነው። ለመሆኑ 109 ፓርቲ መስርቶ ይህን ችግር ለመፍታት ይቻላል? አይቻልም። ኢትዮጵያ ፓርቲ እንደ ቁብ የሆነባት አገር ሆናለች።

በእኔ እምነት፤ ኢትዮጵያ ከሁሉም በላይ የሚያስፈልጋት የፓርቲ ጋጋታ አይደለም። በዘውግ በተበከለች አገር ዲሞክራሲን ስኬታማ ለማድረግ ያስቸግራል። ተግዳሮቱ እንዳለ ሆኖ፤ ኢትዮጵያዊያን ለፍትህና ለዲሞክራሲ አዘውትረን መታገል አለብን። ፍትህ ወሳኝ ቢሆንም ዲሞክራሳዊ ስርዓት ከሌለ ፍትህ ስኬታማ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም፤ ፍትህ ከሕግ የበላይነት ጋር የተገናኘ ጉዳይ ነው።

እኔን የሚያሳዝነኝ፤ ከመቸውም በባሰ ደረጃ በአሁኑ ወቅት የምናስተጋባው እሲት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ የፖለቲካ ደዌ መሆኑ ነው። ልዩነቶችን በማባባስ፤ ኢትዮጵያዊነትን በማሳነስ፤ አማራ፤ ትግሬ፤ ጉራጌ፤ ኦሮሞ ወዘተ እያልን ህብረ-ብሄራዊነትን ዝቅ አድርገን አገራችን ድሃ፤ ኋላ ቀር፤ ተጠቂና ዝቅተኛ እያደረግናት ነው። በማህበረሰባዊ ልማት ከ187 አገሮች 173ኛ ናት ኢትዮጵያ።

የማህበረሰባዊ ልማት እርከን ዝቅተኛኘነት ምን ማለት ነው? እንዴት ሊቀረፍ ይችላል?

የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት የአገሮችን የማህበረሰባዊ ልማት የሚገመግምባቸው ሶስት መሰረታዊ መስፈርቶች አሉ። እነዚህም፤

አንደኛ፤ የእያንዳንዱ ዜጋ የኑሮ ሁኔታና መጠን ( Standard of living)

ሁለተኛ፤ የትምህርት አቅርቦት (Access to education)

ሶስተኛ፤ የጤና አገልግሎት አቅርቦት (Access to health services)

እነዚህ ሶስት መሰረታዊ የሕዝብ ፍላጎቶች ግንኙነት አላቸው፤ አንዱ ሌላውን ያጠናክራል። የገቢ መጠን ከፍ ያለ ሲሆን ወላጆች ልጆቻቸውን የማስተማር እድላቸውም ከፍ ይላል ወዘተ። ሰላምና እርጋታ ከሌለ፤ የሕዝብና የመዋእለ ንዋይ፤ የእውቀትና የሌሎች ግብዓቶ እንቅስቃሴ አስተማማኝ ካልሆነ (Social and capital mobility)፤ ኢንቬስትመንት አስተማማኝ ጥበቃ ካልተደረገለት ልማት አስተማማኝ በሆነ ደረጃ ስኬታማ ሊሆን አይችልም።

በልማቱም መስፈርት ስገመግመው የዐማራውን ሕዝብ ማዳከም፤ መጨፍጨርና ማሳደድ ድህነትንና ኋላ ቀርነትን አባብሶታል።ለምሳሌ፤ የሃሰት ትርክት ዐማራውን፤ “መጤ፤ ነፍጠኛ፤ ቀመኛ፤ ቅኝ ገዢ፤ ጡት ቆራጭ” ወዘተ በሚል ልብ ወለድ ትርክት ለጥቃት አጋልጠነዋል። የተጠቃ ሕዝብ ምርታማ ሊሆን አይችልም። ይህ አገር አፍራሽ ትርክት በአስቸኳይ መታረም አለበት። የክልልና የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ጉዳዩን እየሸነገሉ ችላ ከማለት ፋንታ፤ የማያሻማ አቋም መውስድ አለባቸው። “ነፍጠኛ” እያሉ ልማት ስኬታማ ሊሆን አይችልም።

“ነፍጠኛ” የሚለውስ መለያ ምን ማለት ነው? ባጠቃላይ ስገመግመው የዘውድ ስርዓትን ሙሉ በሙሉ የሚኮንን ብሂል ነው። የዘውድ አገዛዝ ወድቋል፤ በሌለና ባለፈ ጉዳይ ዐማራውን ማውገዝ ህሊና ቢስ ነው። ይህን ያለፈ የዘውድ ስርዓት ደግሞ አጣምረው የሚያዩት ከዐማራው ዘውግና እምነት ጋር ነው። የተዋህዶ እምነትን፤ ዐማራውን በጀምላ፤ አማርኛ ተናጋሪውን በጥቅል የሚያካትት እየሆነ ይተረካል። ክዚህ ጋር ተያይዞ አጼ ምኒልክ ለመላው የኢትዮጵያና የጥቁር ሕዝብ ነጻነትና ክብር ያበረከቱትን አስተዋጾ ወደ ጎን ትተው “ወራሪ” አድርገው ይወነጅሏቸዋል። ጸረ-ኢትዮጵያና ጸረ-ኢትዮጵያዊነት የሆነው የመለያያ ሕገመንግሥት “ነፍጠኛን” ለማዳከምና ለማክሰር የተፈጠረ የሚመስለው ለዚህ ነው። ይህ ሕገመንግሥት “እኛ የኢትዮጵያ ዜጎች” አይልም። የሚለው “እኛ የኢትዮጵያ ብሄር፤ ብሄረሰብና ሕዝቦች” ነው የሚለው ። ስለሆነም፤ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለመሸከምና ለማስተጋባት አይችልም።

ብዙ ተመልካቾች ያላጤኑት ተጨማሪ ክስተት አለ። ዶር ባሽር የሚባል የሱዳን ባለሞያ ስለ ሕዳሴ ግድብ ሲከራከር እንንዲህ ብሏል። “ዐብይ አህመድ እኮ ግማሹ ዐማራ ነው፤ ኦሮሞዎች አይወዱቱም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተከፋፍሏል፤ ዐብይ ደካማ መንግሥት ነው የሚመራው” ወዘተ የሚል ትርክት። ምንም ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌለው ሃተታ ነው የተናገረው። ቁም ነገሩ ግን ጠቅላይ ሚንስትሩን ልክ “የነፍጠኛው ዐማራ” ተወካይ አድርጎ መተቸቱ ነው። ይሄ የህወሓትና የኦነግ፤ በተለይ የነጃዋር/በቀለ ገርባ “ፌደራሊሥት ኃይሎች” ቅንብር ከሚሰብከው ሃተታ የተለየ አይደለም። በባሽር አነጋገር አገር ወዳዱ ሁሉ “ነፍጠኛ” መሆኑ ነው።

ሌላው የኦሮሞ ጽንፈኞችና ጅሃዲስት ምሁራን የሚናገሩት እጅግ በጣም የሚያሳፍርና አደገኛ ጸረ-ኢትዮጵያና ጸረ-ኢትዮጵያዊነት ትርክት በሕዝብ ቆጠራ ወይንም ሴንሰስ የሚሳራጩት ትርክት ነው። በዐማራው ሕዝብ ላይ ያላቸውን ሴራ ለማጠናከር የዐማራውን ሕዝብ ቁጥር ዝቅ አድርገው የኦሮሞውን ሕዝብ ቁጥር ግን ተሰምቶና ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ከፍ አድርገውታል።  ለምሳሌ፤ በዶር አሰፋ ጀለታ “ጥናትና ምርምር መሰረት” የኦሮሞው ሕዝብ ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አምሳ በመቶ ነው ወይንም በጠቅላላ አምሳ ሚሊየን ደርሷል የሚል ትርክት። አሁንም ወደ ግብጾች ምሳሌ ልውሰዳችሁ። ተመሳሳይ ትርክት ስለሆነ።

ግብጾች የህዳሴ ግድብ “አስተማማኝ አይደለም፤ ይናዳል፤ ግድቡ ሲያልቅ ብዙ ሚሊየን ግብጻዊያን ይጎዳሉ፤ ካርቱም በውሃ ጎርፍ ትጥለቀላቃለች” ወዘተ የሚሉ ትርክቶች በተደጋጋሚ ያስተጋባሉ። ሳይንሳዊ መረጃ ግን አቅርቡ ብለን ስንጠይቃቸው እመኑን ነው የሚሉን። በተመሳሳይ፤ የኦሮሞ ጽንፈኞች መረጃው የታለ? ተብለው ሲጠየቁ ጠያቂዎችን ይሳደባሉ። ትርክትን እንደሟያ ማስተጋባታችው ግን ለኦሮሞም ሕዝብ አይጠቅምም። የትርክቱ ዓላማ ግን የኦሮሞ ሕዝብ አንድ አገር ይሆናል ለማለት ነው። ጽንፈኞቹ ከህወሓት የተማሩት ሌላው ነገር መዋሸት መሆኑን አሰምርበታለሁ።

ትህነግ/ህወሓት እና ኦነግ አሁንም ራሳቸውን የሚለዩት በሚወክሉት ዘውግ ነው። የክልሉ አስተዳደር ተወካዮች ነን ለሚሉት የፖለቲካ ልሂቃን ገቢና ኑሮ አመች ሁኔታዎችን ፈጥሮላቸዋል፤ ስርዐቱ እንዲለወጥ የማይፈልጉት ለራሳቸው የበላይነትና ጥቅም አገልጋይ ስለሆነ ነው።

ይህ የልዩነት አስተዳደርና ስርዓት የፈጠረው ምንድን ነው? ብባል፤ መልሴ ያጠናከረው የአስተሳሰብ ግድፈትን ነው የሚል ይሆናል። ሰው እንደ በግ ሲታረድ የሚያሳየውን ጠቅሻለሁ። ሰውን እንደ በግ የሚያርድ አይሲስ ነው!!

ሌላው ላልፈው የማልችለው ሁኔታ አለ። ይኼውም፤ ከህሓወታዊያንና ከኦነጋዊያን የወረስነው የፖለቲካ አደረጃጀት ባህል ነው። በዐማራው ስም ጽንፈኛ፤ ብሄርተኛ፤ መንደርተኛ ወዘተ የሆኑ ስያሜዎችና አደረጃጀቶች ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት ምንም ፋይዳ የሌላቸው መሆናቸው ነው። ከማንኛውም ክፍል ቢሆን፤ በዘውግና በኃይማኖት መደራጀት ሌሎች አገሮች ንቀዋቸው የሄዷቸውን  አፍራሽና አተራማሽ አደረጃጀቶችን ነው። በዘውግና በኃይማኖት ለፖለቲካ ሥልጣን መደርጃት መከልከል አለበት።

እኛ ወደ ውጭ በገፍ እየተሰደድን ከሌሎች ለመማር አለመቻላችን ያሳፍራል። አማራ፤ ኦሮሞ፤ ትግሬ፤ ጉራጌ ወዘተ በሚል የፖለቲካ ድርጅት ስናቋቁም የምናዳክመው ማህበራዊና ኢትዮጵያዊነትን የሚያንጸባርቅ ትሥስርን ነው። ወጣቱ የሚከተለው ወገን ለወገኑ እንዲቆም ሳይሆን በዘውግና በእምነት የወረሰውን እሴት ይሆናል። በዘውግ እና በእምነት ጥላቻ የተማረውና ያደገው ወጣት ትውልድ ነው በጠራራ ጽሃይ  ወገኑን በሜንጫ የሚያርደው።

ህጻን ሽብርተኛ ሆኖ አይወለድም። ተምሮም ልክ እንደ እንሥሳ ወገኑን እንዲያርድ የሚደረገው በጥላቻ እንዲያድግና እንዲሰለጥን ስለተደረገ ነው። ሸብቶም፤ ዶክተሬትም ኖሮት ጥላቻን እንደ መብትና እንደ መፍትሄ የሚያይ የተማረ እብድ በገፍ ከፈጠሩ አገሮች መካከከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗ የስርዓት ፈጠራ እንጅ ወገን ለወገኑ ጨካኝ እንዲሆን ያደረገች ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ወይንም ተራው የኢትዮጵያ ሕዝብ አይደለም። በቀለ ገርባ በወያኔ ተገርፎ ነበር። ግን የወያኔ ደጋፊ ከመሆኑ ባሻገር በዐማራው ሕዝብ ላይ በጀምላ ከፍተኛ ጥላቻ ከሚያሳዩት መካከል ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። ዐማራውን እንዲጨፈጨፍ አመቻችቷል።

ማን ይግዛ? ችሎታ ያለው ብቻ።

በነገራችን ላይ፤ የዐማራው ሕዝብ ማንም ይግዛ ማን በዘውጉ ወይንም በእምነቱ አይለይም።  መብቱ፤ ማንነቱና እምነቱ እስካልተደፈሩ አና ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት እስከተከበሩ ድረስ ደንታ የለውም። ዐቢይን በገፍ እልል ብሎ የተቀበለው በተናገረውና በእሴቶቹ ነው። መለስን የተቃወመው በትግሬነቱ አይደለም፤ በባህሪው፤ በሚያደርጋቸው ነገሮች፤ በጠባብ ብሄርተኛነቱና በአድላዊነቱ ነው። ዐማራው የሚመኘው በበላይ ሆኖ ለመግዛት ሳይሆን አብሮና ተባብሮ ጠንካራ፤ በሉዐላዊነቷ የተከበረች፤ የሰለጠነችና የሁሉም ዜጎቿ ምቹ የሆነች ኢትዮጵያን መመስረት ነው።

ህወሓታዊያን፤ ኦኖጋዊያን፤ ጃዋራዊያን፤ ጅሃዲሶቶች የሚያስተጋቡትን ቀረብ ብየ ስመለከተው ግብጾችና ወዳጆቻቸው የመላው አረብ አለም ጋዜጠኞችና ምሁራን ከሚሉት የተለየ አይደለም። ስለ ሕዳሴ ግድብ ሲነጋገሩ አብረውና ለእነሱ በሚረዳ መልኩ የሚሉትን ተከታተሉ። ባጭሩ ላስቀምጥላችሁ። “የዐብይ መንግሥት እጅግ በጣም ተዳክሟል። ያዳከሙት በሰሜን ህወሕቶች፤ በደቡብ ደግም ኦነጎችና የጃዋር ደጋፊዎች ናቸው” ይላሉ።

ግብጾችና ደጋፊዎቻቸው በሕዳሴ ግድብ ላይ፤ እኔንም ጨምሮ፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ብሄራዊ አቋም ይዟል ለማለት አይደፍሩም። የሚናገሩት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመኙትን ነው። የሚመኙት ደግሞ በዘውግና በእምነት የተከፋፈለች፤ ደካማና ድሃ ኢትዮጵያን ነው።

በተመሳሳይ ከላይ የጠቀስኳቸው ጠባብ ብሄርተኞችና ጽንፈኞች የኢትዮጵያን ታላቅ መሪዎች የሌለ ስም ይሰጧቸዋል፤ ዐማራ በመሆናቸው ብቻ። ለምሳሌ ታላቁን የኢትዮጵያን መሪ መይሳው ካሳን (አጼ ቴዎድሮስን) የሌለ ስም የሚሰጧቸው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አድርገው ለብሄራዊ አንድነትና ለአገራችን ዘመናዊነት ስለተዋጉ ነው።

ታላቁን የጥቁር ሕዝቦችን ነጻነት አባት መሪ አጼ ምኒልክንም የሌለ የፈጠራ ታሪክ ተሸካሚ አድርገው የአኖሌን ሃውልት የሰሩት በተመሳሳይ ትርክት ነው፤ ዐማራ ስለሆኑ ብቻ። በተመሳሳይ፤ ግብጾችና ሱዳኒሶች በአሁኑ ጊዚ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶር ዐብይን የዐማራው ሕዝብ (ነፍጠኛና ትምክህተኛ ወዘተ) ተለጣፊና የእሴቶቹ ደጋሪ አድርገው ይተቻሉ። ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት የቆመ ሁሉ እንደሚተች ላሰምርበት እፈልጋለሁ።

ለማጠቃለል፤ የዐማራው ሕዝብ ባለፉት 40 ዓመታት ተከታታይ ግፍ፤ በደል፤ እልቂት፤ መፈናቀል የደረሰበት “መጤ፤ ነፍጠኛ፤ ትምክህተኛ፤ ሰፋሪ፤ ወራሪ” ወዘተ የሚሉ መለያዎች እየተሰጡት ነው። ባለፈው ሰኔ ከ 200 በላይ ንጹህ ወገኖቻችን ተጨፍጭፈዋል። በቅርቡ በተከታታይና በሚዘገንን ደረጃ በቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ፤ በአንድ ሰሞን ብቻ ከ 80 የማያንሱ፤ ከዚሃ በኋላ ሌሎች ተጨፍጭፈዋል። ከ300 ቀናት በላይ የሆነው በደምቢ ዶሎ ዩንቨርስቲ በዐማራነታቸው ምክንያት የተነጠቁት (Abducted) 17 ወጣት ሴቶች ተማሪዎች እስካሁን ድረስ ይሙቱ፤ በህይወት ይኑሩ ሳይታወቅ ወላጆቻቸውና ዘመዶቻቸው በማልቀስ ላይ ይገኛሉ።

ክፍል አራት በኢትዮጵያ የሚታየውን የአስተሳሰብና የፖለቲካ ግብግብ ይገመግማል።

October 18, 2020

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.