/

የሕግ የበላይነትና የፍትህ ጉዳዮችን ለፖለቲካ መጠቀሚያ አድርጎ መውሰድን የምንፀየፈው ነገር ነው – ናትናኤል ፈለቀ – የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ

ezemaየዛሬ የዜጎች መድረክ ‹‹የቆይታ›› አምድ እንግዳችን የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናትናኤል ፈለቀ ናቸው፡፡ ናትናኤል ፈለቀ ተወልደው ያደጉት በአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዲሁም የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ ዞን ዘጠኝ ተብሎ ይጠራ በነበረው የአራማጆችና የጦማሪያ ቡድን ውስጥ አባል ነበሩ፡፡ በኮንስትራክሽን ቢዝነስ ባንክና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ዘለግ ላሉ ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ሰአት በሙሉ ጊዜያቸው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆነው እያገለገሉ ይገኛል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይ፣ ኢዜማ ሊያደርገው አስቦት በነበረው ውይይት መደናቀፍ እንዲሁም ፓርቲያቸው ላይ ስለሚነሱ ትችቶች በሚመለከት የተለያዩ ጥያቄዎች አንስተንላቸዋል፡፡ ቆይታችንን እንድታነቡት እንጋብዛለን፡፡ መልካም ንባብ!
ጥያቄ፡ አዲስ አበባ የ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ዋና መታገያ ከተማ ናት፡፡ ከባለቤትነት ጥያቄ ጋር በተያያዘም የመወዛገቢያ ከተማ ሆናለች፡፡ ኢዜማ ፣ ከከተማዋ የባለቤትነት ጥያቄ ጋር በተገናኘ ለሚነሳው ውዝግብም ሆነ የከተማዋን ችግሮች ለመቅረፍ መፍትሔው ምንድን ነው ይላል?
አዲስ አበባ ላይ ብዙ የባለቤትነት ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ እኛ የምናስበው በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ከተሞች ያሉ ሀብቶችም እና አካባቢዎች የሁሉም ሕዝቦች ነው ብለን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ ያሉ ከተሞች በሙሉ ባለቤትነቱ የኢትዮጵያ ዜጎች ነው፡፡ ከዛ ውጭ ማን ያስተዳድር? እንዴት ይተዳደር? የሚለው ነው ሊያነጋግረን የሚገባው፡፡
በፕሮግራማችን ውስጥ በግልጽ እንደተቀመጠው ተገቢ ብለን የምናምነው አወቃቀር ታችኛው መዋቅር (ወረዳ) ድረስ በግልጽ በሕዝቡ በቀጥታ የተመረጡ ኃላፊዎች ወረዳውን የሚያስተዳደሩበት ሁኔታ ሊኖር ይገባል፡፡ በዚህ ሂደት የተመረጡት ኃላፊዎችም ተጠያቂነታቸው ለመረጣቸው ሕዝብ ይሆናል፡፡ የሚሰሩትም የመረጣቸውን ሕዝብ ፍላጎት ለማሟላት የሚሰሩ ይሆናል፡፡
ከወረዳ ጀምሮ እስከ ላይኛው መዋቅር ድረስ ባሉ የመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሚሰሩ ኃላፊዎች መሾም ሳይሆን መመረጥ አለባቸው ብለን ነው የምናምነው፡፡ ያ ሲሆን (በሕዝብ የተመረጡ ሰዎች አካባቢያቸውን ሲያስተዳድሩ) ነው በወረዳ፣ በክፍለ ከተማና በከተማ ውስጥ ያሉ ችግሮች የሚፈቱት፡፡ የሚመረጡት ሰዎች የሕዝብን ችግር መፍታት ከቻሉ በሕዝብ ድምፅ ሥልጣናቸው ይራዘምላቸዋል፡፡ መፍታት የማይችሉ ከሆነ ደግሞ በሕዝብ ድምፅ በሌላ ይተካሉ፡፡ እንዲህ አይነት የፖለቲካ ሥርዓት ነው እንዲኖር የምንፈልገው፡፡ የመሬት አስተዳደር፣ የትራንስፖርት እጦት፣ የኑሮ ውድነት፣ የቤት አቅርቦት ችግር የመሳሰሉ ችግሮች አለ፡፡ እነዚህ ችግሮች ደግሞ የሚፈቱት በባለሙያዎች በተጠና ፖሊሲ ነው፡፡ እነዚህን ፖሊሲዎቻችንን ጊዜው ሲደርስ ለሕዝብ ይፋ የምናደርግ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ለሚቀጥሉት አምስት አመታት በተጨባጭ የምንሰራበትን ማኒፌስቶም ለሕዝብ ይፋ የምናደርግ ይሆናል፡፡
ጥያቄ፡ በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ ኢዜማ ከመሬት ወረራ ጋር ያቀረበው መረጃ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ እንደሚነሱ ስላወቁ ነው መረጃውን ያወጡት የሚሉ አሉ፡፡ ምክትል ከንቲባው መልስ መስጠት በማይችሉበት ቦታ ሆነው መቅረቡ እንዳሳዘናቸው ገልፀዋል፡፡ ኢዜማ ያቀረበበት ጊዜ ተገቢ ነው ብላችሁ ታምናለችሁ?
የአዲስ አበባን የመሬት ወረራ እና የጋራ መኖሪያ ቤት እደላ ጥናት የጀመርነው ሰኔ 15 ቀን 2012 ዓ.ም የኢዜማ ሥራ አስፈጻሚ ተሰብስቦ በወሰነው ውሳኔ መሠረት ነው፡፡ እሳቸው ከሥልጣናቸው ይነሱ አይነሱ ከሚለው ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ ጥናቱ የተጀመረው እሳቸው ከቦታቸው ከመነሳታቸው ከወራት በፊት ነው፡፡ ጥናቱ መች እንደተጀመረ እሳቸውም ያውቃሉ፡፡
ለምናካሄደው ጥናት መረጃ ልናገኝ የምንችለው ከመንግሥት መስሪያ ቤቶች፣ ከመገናኛ ብዙኃን፣ ጉዳት ከደረሰባቸው ነዋሪዎች ነው፡፡ ጥናቱን ስንጀምርም ይህንን ለይተን ነው ጥናቱን ያካሄድነው፡፡ በዚህም መሰረት መጀመሪያ ለከንቲባው ጽ/ቤት፣ ለመሬት አስተዳደር፣ ለቤቶች ልማት ኤጀንሲ፡- ለምናካሄደው ጥናት ግብዓት ስጡን ብለን ደብዳቤ ልከንላቸዋል፡፡ በወቅቱ ጥያቄያችንን ለመቀበል፤ ግብዓትም ለመስጠት ፍቃደኛ አልነበሩም፡፡ በኋላም የጥናት ውጤቱን አጠናቀን ምላሻችሁን እናካት ስንላቸው ፍቃደኛ አልነበሩም፡፡ ‹‹እኔ ምላሽ መስጠት በማልችለበት ቦታ ሆኜ ነው የወጣው›› የሚለው የምክትል ከንቲባው ምላሽ የእሳቸውን ቅንነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው፡፡ ምክንያቱም ምክትል ከንቲባው በሥራ ላይ እያሉ አስቀድመን ለቢሯቸው በፃፍንላቸው ደብዳቤ ለጥናታችን የሚሆን ግብዓት ስጡን ብለን ጠይቀናቸው ነበር፡፡ ለዚህ ጥያቄያችንም ምንም ምላሽ አልሰጡም፡፡
ጥያቄ፡ በአዲስ አበባ ከተማ በፊት የነበረው መሬት ወረራና ኢ-ፍትሃዊ የጋራ መኖሪያ ቤት አደላ አሁንም እንዳለ ነው፡፡ ይሄን ደግሞ ኢዜማም አረጋግጧል፡፡ በቀጣይ መንግሥት የማስተካከያ እርምት ባይወስድ የእናንተ ውሳኔ ምን ሊሆን ይችላል?
መጀመሪያ እንቅስቃሴያችን ሰላማዊና ሕጋዊ መሆኑን ማረጋገጥ እፈልጋለሁ፡፡ እንቅስቃሴዎቻችን የሌሎችን መብት ባከበረ መልኩ ነው የሚሆኑት፡፡ አሁን በሥልጣን ላይ የሚገኘው መንግሥት የዜጎችን ደኅንነትና የሀገርን መብት ማስጠበቅ ግዴታ አለበት ብለን እናምናለን፡፡ መንግሥት ግዴታውን እንዲወጣ በተለያየ መልኩ ግፊት እናደርጋለን፡፡ ይሄን የምናደርገው ጥናቶች እያጠኑ ክፍተት ያለባቸው ቦታዎች በማሳየት ነው፡፡ መንግሥት ከዚህ መነሻ ተነስቶ የእርምት እርምጃ ይወስዳል ከሚል ተስፋ ነው ይህን የምናደርገው፡፡ ያ ሳይሆን ሲቀር ደግሞ ባለፈው ባወጣነው ሪፖርት እንዳደረግነው ለሚመለከታቸው አካላት ፍትህንና የሕግ የበላይነት ለማስፈን የወንጀል ይጣራልኝ አቤቱታ እናስገባለን፡፡ ተቋማቱ አስፈጻሚው አካል ፍቃደኛ ባይሆን እንኳን አስገድደው የእርምት እርምጃ እንዲወስድ ጫና ማድረግ አለባቸው ብለን ስለምናምን ነው ይህንን የምናደርገው፡፡
ጥያቄ፡ ባለፈው ያስገባችሁትን የወንጀል ይጣራልኝ አቤቱታ ተከትሎ ምላሽ የሰጣችሁ ተቋም አለ?
ለፌዴራል ፖሊስ፣ ለፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እና ለጠቅላይ አቃቤ ሕግ ባስገባነው የወንጀል ይጣራልኝ አቤቱታ ላይ እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ አልደረሰንም፡፡ ተቋማቱ በዚህ ጉዳይ ምን እያደረጉ እንደሆነ የምናውቀው ነገርም የለም፡፡ ምላሽ እንዲሰጠን ባገኘነው አጋጣሚ መጠየቃችን አናቆምም፡፡
ጥያቄ፡ ችግሮቹ የሚቀጥሉ ከሆነና መንግሥት የእርምት እርምጃ የማይወስድ ከሆነስ ምንድነው ለማድረግ የምታስቡት?
መንግሥት የእርምት እርምጃ ለመውሰድ ፍቃደኛ ካልሆነ እነዚህን ችግሮች ማስቆም እንዳልቻለ፤ እኛ ደግሞ ተመርጠን ስልጣን ቢሰጠን እንዴት እንደምናስቆመው፤ ማስቆም ብቻ ሳይሆን በዚህ ሥራ ተሰማርተው አላግባብ ጥቅም ያገኙ ሰዎች የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድባቸው፤ በዚህ ሕገ ወጥ ሥራ ተሰማርተው የተበደሉ ሰዎች እንዴት ነው የሚካሱት የሚለውን በተግባር መሬት ላይ ሊወርዱ በሚችሉ አማራጮች በዝርዝር እናቀርባለን፡፡ ሕዝብ ደግሞ ሥልጣን ከሰጠን ቃል በገባነው መሠረት የእርምት እርምጃ ወስደን ማስተካከያ የምናደርግ ይሆናል።
ጥያቄ፡ ኢዜማ በቀጣይ ምርጫ አሸንፎ መንግሥት ቢሆን ምን አይነት የእርምት እርምጃ ሊወስድ ይችላል የጋራ መኖሪያ ቤቶችን እና የተወረሩ መሬቶችን በወሰዱ ሰዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመወስድ የሚያስችል ዝግጁነት አለው?
ተመርጠን ስልጣን የምንይዝ ከሆነ ሕዝቡ እኛ ቃል በገባንለት መሠረት ‹‹አስተዳድሩን›› ብሎ ይሁንታ የሚሰጠን ከሆነ መጀመሪያ የምናደርገው ሕገ ወጡን የመሬት ወረራ የማስቆም ሥራ ነው የምንሰራው፡፡ የመሬት ወረራው አሁንም እንደቀጠለ ነው። መቆም አለበት። በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚደረጉ ሕገ ወጥ ተግባራትና ኢ-ፍትሃዊ ሥራዎች በሙሉ መቆም አለባቸው። ለጤና ጣቢያና ለአረንጓዴ ቦታ የተተዉ በመሬት ባንክ ውስጥ የነበሩ ቦታዎች ጭምር ናቸው የተወሰዱት፡፡ እነዚህ መሬቶች ለተገቢው ባለቤቶች መመለስ አለባቸው። ያንን የማረጋገጥ ሥራ የምንሰራ ይሆናል፡፡
የጋራ መኖሪያ ቤቶች ደግሞ ያለ አግባብ የተላለፈላቸውን ሰዎች አማራጭ ሳናዘጋጅለቸው ከሚኖሩበት ቤት አውጥተን አንወረውራቸውም፡፡ እነዚህ ሰዎች ዜጎች ናቸው። የምንወስዳቸው የእርምት እርምጃዎች የዜጎችን ሰብዓዊ መብት በማይነካ መልኩ መሆን እንዳለባት እናምናለን፡፡ ምን አይነት የእርምት እርምጃ ነው መውሰድ የሚገባን የሚለውን በሚገባ ፈትሸን ነው የማስተካከያ እርምጃ የምንወስደው፡፡ በሰፊው የምናስብበትና የምንዘጋጅበት ነው የሚሆነው፡፡
ጥያቄ፡ ኢዜማ በአዲስ አበባ ጉዳይ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ተቀናጅቶ፣ ግንባር ፈጥሮ የመሥራት አቅድ አለው? ካለው በየትኛዎቹ ጉዳዮች ላይ ይሰራል?
ለፖለቲካ ፓርቲዎች ለፉክክርና ለትብብር በሚሆኑ ጉዳዮች ላይ ጥሪ ስናደርግ ነበር፡፡ በትብብር መሥራት ያለብን ነገሮች በጥቅሉ ሲታዩ በሦስት የሚከፈሉ ናቸው፡፡ ከሀገር አንድነት፣ ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ የዜጎችን ደኅንነት ከማስጠበቅ ጋር ተያይዞ ያሉ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመሥራት ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ ስናደርግ ቆይተናል፡፡
በብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ መሠረት የተቋቋመ አንድ ኮሚቴ አለ፡፡ ይህ ኮሚቴ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በዝርዝር በምን አይነት ጉዳዮች ላይ እና በምን መልኩ መሥራት አለብን የሚለውን እየፈተሸ ነው፡፡ በአዲስ አበባም ውስጥ ይሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚንቀሳቀሱ ከገዢውም ከተፎካካሪዎችም ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመሥራት ጥሪ የሚያደርግና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚያናግር ይሆናል፡፡ ከኢዜማ ጋር አብረን መሥራት እንፈልጋለን የሚሉ የምርጫ ወረዳዎችን በመቀላቀል ከዛ ጀምሮ ባለ የሥልጣን እርከን መሳተፍ ይችላሉ፡፡ ከዛ ውጭ ባለ ምርጫ ተኮር በሆኑ ቅንጅቶች ውስጥና ጥምረቶች ውስጥ በፍጹም የምንገባ አይሆንም፡፡ ምርጫው አልፎ የሚገኘው ውጤት አንደ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ብቻውን መንግሥት ለመመሥረት የማያስችል ከሆነ ከየትኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ነው አብረን መሥራት የምንችለው? የሚለውን ግን የምንመረምረው ይሆናል፡፡
ጥያቄ፡ የአዲስ አበባ ራስ ገዝነት ጥያቄ ጋር በተገናኘ ባልደራስ ለዴሞክራሲ ፓርቲ ለተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት መጥራቱ ይታወቃል። ሌሎች ፓርቲዎች ሊቀመንበራቸውንና ምክትል ሊቀመንበራቸውን ሲልኩ ኢዜማ ብዙም ትኩረት ስላልሰጠው መሪውን ወይም ምክትል መሪውን አላከም፡፡ ይሄም የሚያሳየው ኢዜማ ብዙም ትኩረት እንዳልሰጠው ነው በሚል አንዳንድ ወገኖች ትችት ያቀርባሉ። ለዚህ ትችት ምን ምላሽ አላቹህ?
ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የሚኖረን ግንኙነት ምን መመስል አለበት? በምን ጉዳዮች ላይ ነው በጋራ መሥራት ያለብን? የሚለውን የሚያጠና ራሱን የቻለ ኮሚቴ አቋቁመናል፡፡ ይሄ ኮሚቴ ማድረግ ያለበትን ዝግጅት አጠናቆ ከፓርቲዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ከመጀመሩ በፊት ‹‹በጋራ እንስራ›› የሚሉ ጥያቄዎችን ያቀርቡልናል፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች በደፈናው ኮሚቴው ዝግጅቱን አጠናቆ እስኪመጣ ድረስ ‹‹አንሳተፍም!›› ብለን መመለስ አንፈልግም፡፡ ምክንያቱም እንደዚህ የሚፈጠሩ ግንኙነቶች እያሳደግን በትልልቅ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ጅምር ሊሆነን ይገባል የሚል እምነት ስላለን ኮሚቴው ዝግጅቱን አጠናቆ ሥራውን ባይጀምርም የሚመጡልን ጉዳዮች ግን በአሉታዊ መንገድ መመለስ አንፈልግም፡፡ እንደዚህ አይነት ውይይቶች ሲመጡ በንቃት መሳተፋችንን እንቀጥላለን፡፡ አሁን የተነሳውን ጥያቄ በቅንነት ወስደን የብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የሆኑ ሦስት ሰዎችን በውይይቱ ላይ እንዲሳተፉ ልከናል፡፡ ኢዜማ የሚሳተፍባቸው ውይይቶች ላይ ‹‹እነማን ይሂዱ?›› የሚለውን የሚወስነው ኢዜማ ነው መሆን ያለበት፡፡ ከዛ ውጪ ሌሎች አካላት በዚህ ደረጃ ያለ ባለሥልጣን መጥቶ ካልተሳተፈ በቀር ለጉዳዩ ትኩረት አልሰጠውም ብለው የሚያቀርቡት ትችት ብዙም ተቀባይነት የለውም፡፡
ጥያቄ፡ ኢዜማ ከመሬት ወረራና ከኢፍትሃዊ መሬት እደላ ጋር በተያያዘ ያጠናውን ጥናት ሊያቀርብ ሲል በዛም ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሊወያይ ሲዘጋጅ መከልከሉ ይታወሳል፡፡ ኢዜማ ጉዳዩን ወደ ክስ ወስዶታል ምን ደረጃ ይገኛል?
መስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፍትሃ ብሔር ምድብ ችሎት ክስ መስርተናል፡፡ ክሱን የመሰረትነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ከተሰጠው የሕግ ስልጣን አልፎ ሕገ መንግሥታዊ የሆነ መብታችንን ተጋፍቷል፡፡ ይህ ሕገ ወጥ ተግባር በመሆኑ ‹‹ትዕዛዝ ይሰጥልን›› ብለን ነው ያመለከትነው፡፡ ከዚህ ወዲያም ቢሆን እንደዚህ ያለ ተግባር መፈፀም እንደማይችል ትዕዛዝ ይሰጥልን ስንል ነው በክሳችን ላይ ያመለከትነው፡፡ ክርክራችንን ለማቅረብ ፍርድ ቤት ቀጠሮ አልሰጠንም፡፡ ቀጠሮ በተሰጠን ጊዜ ቀርበን ክርክር የምናደርግ ይሆናል፡፡ ውጤቱንም ለሕዝብ ይፋ እናደርጋለን፡፡
ጥያቄ፡ ኢዜማ የተከለከለውን ውይይቱን ያካሂዳል? ወይስ ሌላ አማራጭ መንገድ ይጠቀማል? ከዛ ውጭስ ምን አይነት መንገዶችን ተጠቅሞ ውጤት ላይ ለመድረስ አስቧል?
ፍርድ ቤቱ እንዳናካሄድ የተከለከልነውን ውይይት ተከትሎ ለመሰረትነው ክስ በአፋጣኝ ትዕዛዝ የሚሰጥልን ከሆነ በዛ ትዕዛዝ መሰረት ሕገ መንግሥታዊ የሆነ መብታችንን ተጠቅመን ውይይቱን በፅህፈት ቤታችን የምናደርግ ይሆናል፡፡ ያ የማይሆን ከሆነና የፍርድ ሂደቱ ጊዜ የሚፈጅ ከሆነ ሌሎች አማራጮችን ማየት እንጀምራለን፡፡ ለምሳሌ ውይይቱን ለማካሄድ የግድ አንድ ቦታ ሰዎችን መሰብሰብ የማያስፈልግበት አማራጭ አለ፡፡ ይህን መሰል አማራጭ ተጠቅመን ውይይቱ እንዲደረግና የመፍትሔ ሀሳቦች የሚባሉት ላይ ውይይት እንዲደረግ መድረክ የማመቻቸት ሥራችንን የምንሰራ ይሆናል፡፡ እኛ የምናደርገው እንቅስቃሴ ሰላማዊና ሕጋዊ ነው የሚሆነው፡፡ እኛ እንቅስቃሴ ላይ እከል በመፍጠር የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት በፍፁም ውጤታማ አይሆንም፡፡ ችግሩ እንደሌለ አድርጎ ለመሸፈን የሚደረግ ጥረት ከሆነም አይሳካም፡፡ ይህንን ሊያውቁት ይገባል፡፡
ጥያቄ፡ ኢ-ፍትሐዊ የሆነ የጋራ መኖሪያ ቤት እደላ ለማከናወን የሚያስችል ሕገ ወጥ የሆነ ሕግ በከተማ አስተዳድሩ እንደወጣ ጠቅሳችኃል። ይህን ሕግ ተንተርሰው ኢ/ር ታከለም ሆነች ወ/ሮ አዳነች ቤት የሚያድሉት። ይህ ሕግ እስካልተሻረ ድረስ ኢፍትሐዊ እደላው ይቀጥላል። ይህ ሕግ እንዲሻር ኢዜማ ምን ያህል ርቀት ይሄዳል?
በጥናታችን ላይ የጠቀስነው የከተማ መስተዳድሩ ያወጣው መመሪያ የጋራ መኖሪያ ቤት ለማግኘት ከተመዘገቡና ከቆጠቡ ሰዎች ውጪ ምንም ቅድመ ሁኔታ ሳያስቀምጥ የከተማው ከንቲባና ካቢኔው ትዕዛዝ ከሰጡ ቤቶቹ ለሌሎች ሰዎች እንዲተላለፉ ተደርጎ ነው መመሪያው የተሻሻለው፡፡ ከተመዘገቡትና ከቆጠቡት ሰዎች ውጪ መሰጠት ያለበት አስገዳጅ ሁኔታ ከተፈጠረ እንኳን ለማን በምን ሁኔታና መቼ የሚለው በግልፅ ተቀምጦ ገደብም ሊጣልበት ይገባ ነበር፡፡ አሁን ላይ ያለው አሰራር ግን ከንቲባውና ካቢኔያቸው በፈለጉት ጊዜና ወቅት የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ላልተመዘገቡና ላልቆጠቡ ሰዎች መብት በሰጠ መልኩ ነው መመሪያው የተሻሻለው፡፡ ለኢ – ፍትሃዊ የጋራ መኖሪያ ቤት እደላ ይህን አንድ የችግሩ አካል ነው ብለን ለይተንዋል፡፡ የመፍትሔ ሀሳብ ሲባል ይህንንም መመሪያ መልሶ መፈተሸና ማሻሻልንም የጨመረ ነው መሆን ያለበት፡፡ እኛ ይህንን እንደ ችግር አንስተንዋል፡፡ የከተማ አስተዳድሩ ምን እያደረገ እንደሆነ በግሌ የማውቀው ነገር የለም፡፡ እውነተኛ መፍትሔ የሚሰጥ ከሆነና ፍትሃዊ የሆነ ውሳኔ የሚወሰን ከሆነና የሕግ የበላይነት የሚከበር ከሆነ ይህ መመሪያ መሻሻል እንዳለበት እናምናለን፡፡ የከተማ አስተዳድሩ ይህን መመሪያ የማያሻሽል ከሆነ እኛ የምንመረጥ ከሆነና ስልጣን የምንረከብ ከሆነ መጀመሪያ እርማት ከምንወስድባቸው መመሪያዎች ውስጥ ይሆናል፡፡
በራሳቹህ ፅ/ቤት የፓናል ውይይት ከመከልከላቹህ በፊት ከዚህ በራስ ሆቴል መግለጫ እንዳትሰጡ መከልከላቹህ ይታወቃል። የምርጫ ዘመቻ ሳይጀመር ከወዲሁ የመሰብሰብና ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታችሁ በዚህ መልክ እየተገፈፈ እንዴት ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል ብላችሁ ታምላችሁ?
6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ እስከዛሬ ካደረግናቸው ምርጫዎች ፍፁም የተለየ ነፃ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ መሆኑ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ሀገራችንን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለምታደርገው ሽግግር ጠንካራ መደላድል የሚጥል ወሳኝ ምዕራፍ ነው ብለን ነው የምንወስደው፡፡ ነፃ፣ ፍትሃዊና ሰላማዊ ምርጫ ማድረግ የሚቻለው ያንን ለማድረግ ሥልጣን የተሰጣቸው አካላት በአግባቡ ኃላፊነታቸውን መወጣት ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ ፍ/ቤት፣ ፖሊስ፣ ደኅንነት፣ መከላከያ፣ ምርጫ ቦርድ፣ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የመሳሰሉ… እዚህ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት በአግባቡ ሚናቸውን መወጣት የማይችሉ ከሆነ ምርጫው በፍፁም ነፃ፣ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ አይሆንም፡፡ አሁን በተጨባጭ እያየነው እንዳለነው የአስተዳደር መሥሪያ ቤቶች ለምሳሌ የከተማ አስተዳድሩን እዚህ ጋር መጥቀስ ይቻላል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዕለት ተዕለት ሥራቸው ውስጥ ማድረግ የሚገባቸውን ክንዋኔዎች መወሰን እንደሚችሉ አድርገው የሚያስቡና በእንደዚህ ያለ ሕገ ወጥ ተግባር ውስጥ እጃቸውን እንደሚከቱ በተጨባጭ አይተናል፡፡ ፍ/ቤቶች የሚሰጧቸውን ውሳኔዎች ፖሊስ በማን አለብኝነት በተደጋጋሚ እየጣሰ እንደሆነ እያስተዋልን ነው፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶች የሰው ሕይወትና ንብረት ላይ አደጋ ሲያደርሱ እያየን ነው፡፡ እነዛን ግጭቶች አስቀድሞ ተንብዮና ዝግጅት አድርጎ የመከላከልና ተከስቶ ሲገኙም በአፋጣኝ አስቁሞ የዜጎችን ሕይወትና ንብረት ከአደጋ መታደግ ላይ የፀጥታ አካላት ክፍተት እንዳለባቸው እያስተዋልን ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ሰላማዊና ሕጋዊ ከማድረግ አንጻር ክፍተት እንዳለባቸው አስተውለናል፡፡ እነዚህ ክፍተቶች በጊዜ የእርምት እርምጃ ተወስዶ ካልተስተካከሉ በስተቀር ምርጫው ነፃ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ይሆናል ማለት በፍፁም አይቻልም፡፡ አሁን የጠቀስኳቸው የመንግሥት አካላት፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ገለልተኛ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት የሚችሉበት ቁመና ላይ ቶሎ መድረስ አለባቸው ብለን እናምናለን፡፡ እነዚህ ተቋማት ላይ ያሉ ክፍተቶችን ከእኛ ምልከታ በዘለለ በጥናት ላይ ተመስርቶ ምንድነው ጉደለታቸው ምርጫውን ነፃና ፍትሐዊ ከማድረግ አንፃር ራሳቸውን ብቁ የሚያደርጉባቸው እርምጃዎች ምንድናቸው የሚለውን በጥናት ላይ የተመሰረተ ሪፖርት እያዘጋጀን ነው ያለነው፡፡ ጊዜው ሲደርስ ይፋ የምናደርገው ይሆናል፡፡
ጥያቄ፡ ኢዜማ፣ ለገዢው ፓርቲ ስስ ልብ አለው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የብልፅግና ተለጣፊ ነው ይሉታል፡፡ ይህ ገለፃ ቀላል የሚባል ቁጥር በሌላቸው ሰዎች ዘንድ እንደ እውነታ መታየቱ ኢዜማን ሊያሳስበው አይገባም? ኢዜማ ይህን ማጥራት ያቃተውስ ለምንድን ነው? ብልፅግናንስ በምን መልኩ ነው የምትገመግሙት?
ኢዜማ ከምሥረታው አንስቶ አራት ግቦችን አስቀምጦ የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ፓርቲ ነው፡፡ የመጀመሪያው ግቡ ራሱን ጠንካራና ዘመን ተሻጋሪ የፖለቲካ ፓርቲ ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው ግቡ በሕዝብ ዘንድ አመኔታ ያለው የፖለቲካ ፓርቲ መሆን ነው፡፡ ይህም ማለት ሀገር ማስተዳደር እንደሚችልና ሕዝብ የሚያምነው የፖለቲካ አማራጭ እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡ ሶስተኛ ግቡ በሀገር ደረጃ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲመሰረት እገዛ ማድረግ ነው፡፡ አራተኛውና የመጨረሻው ግባችን በምርጫ ተወዳድሮ ማሸነፍና ሥልጣን ይዞ ፖሊሲዎቻችንን በመተግበር በራዕያችን ላይ ያስቀመጥነውን ሀገር መፍጠር የምንችልበት እድል እንድናገኝ ማስቻል ነው፡፡ የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎቻችን በሙሉ እነዚህን አራት ግቦቻችንን መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ እነዚህን እንቅስቃሴዎች ስናደርግ ከብዙ አቅጣጫዎች እንቅፋቶች እንደሚያጋጥሙን እናውቃለን፡፡ ሀገራችን ውስጥ ያለው የፖለቲካ ስርአትና ልምምድ የተለያዩ ሀሳቦችን ለማስተናገድ ክፍት እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ ሕግን አክብሮና ሰላማዊ በሆነ እንቅስቃሴ ላይ ከሕግ ውጪ ሆነው መንቀሳቀስ እንደሚችሉ የተሰማቸው የፖለቲካ ሀይሎች እንቅፋት እንደሚሆኑ እንረዳለን፡፡ እንቅፋት የሚፈጥሩት ሀይሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ መንግሥትን የሚመራው ፓርቲና ከመንግሥት ተፅዕኖ ገለልተኛ ሆነው መሥራት የሚጠበቅባቸው ተቋማት ጭምር ያካትታል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን እንደ አዲስ እየመሠረትን ነው ያለነው፡፡ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ እነዚህ ተቋማት እንዴት ይንቀሳቀሳሉ የሚለውን መሠረት አድርገን አሁን የሚያጋጥሙን ችግሮች ተስፋ እንድንቆርጥ እንዲያደርጉን መፍቀድ የለብንም፡፡
እኛ የምናደርገው እንቅስቃሴ ፍፁም ኃላፊነት የተሰማው የሀገርና የሕዝብን ጥቅም የሚያስቀድም ነው፡፡ በዚህ ምክንያት እኛ የምናገኘው ጥቅም የሚቀር ከሆነ ራሱ እሱንም ለመቀበል ፍቃደኞች ሆነን ነው ስንንቀሳቀስ የነበረው፡፡ እኛ ሕግ ማክበራችንንና ሰላማዊ እንቅስቃሴ ማድረጋችንን ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ጥቅም/ብልጫ (Advantage) እየወሰዱ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የምንጎመጅ አይነት ሰዎች አይደለንም፡፡ ምክንያቱም የመጨረሻ ግባችን ስልጣን መያዝ አይደለም፡፡ የመጨረሻ ግባችን ሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የሁሉንም ዜጎች እኩል እድል ማክበር የሚችልና ለሁሉም ዜጎች እኩል መብት የሚሰጥ የፖለቲካ ስርዓት መዘርጋት ነው፡፡ ያንን የፖለቲካ ስርዓት ለመዘርጋት መክፈል የሚጠበቅብንን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል ሁላችንም ዝግጁ ነን፡፡ ያንን ደግሞ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ብልጣ ብልጥ ነን ብለው በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ወደ ተስፋ መቁረጥም ሆነ እነሱ እያደረጉት ስለሆነ እኛም እናደርገው ወደሚል ስሜት ውስጥ አንገባም፡፡ ስልጣን ላይ ያለው ፓርቲም ሆነ ሌሎች ፓርቲዎች በተቻለው አቅም ሕጋዊና ሰላማዊ እንቅስቃሴ እያደረጉ እንዲሄዱ ነው የምንፈልገው፡፡ ሁልጊዜም ስንናገረው የነበረውም ይህንኑ ነው፡፡ ሌሎች ያንን ባያደርጉም እኛ ሁልጊዜም እንቅስቃሴዎቻችንን ሕጋዊና ሰላማዊ እያደረግን መቀጠሉን አናቆምም፤ ተስፋም አንቆርጥምም፡፡
ጥያቄ፡ በመጨረሻ በውይይታችን ያላነሳናቸው ግን ለህዝቡ እንዲደርስ የሚፈልጉት ነገር ካለ እድሉን ልስጥዎት
ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ በሀገራችን ውስጥ ወሳኝ ምዕራፍ ነው፡፡ ሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመመስረት የሚያስችል ሂደት ውስጥ ትልቅ ሚና ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ጠንካራ መሰረት ላይ የምንጥልበት ሂደት ነው ብለን ነው የምናምነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በንቃት የምርጫውን ሂደት መከታተል አለባቸው ብለን እናምናለን፡፡ በሕግ የተፈቀደላቸውና በምርጫው መሳተፍ የሚችሉ ዜጎች በሙሉ በመራጭነትም፣ በእጩነትም በታዛቢነትም መሳተፍ አለባቸው፡፡ ምርጫው ነፃ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን ለማረጋገጥ ኃላፊነት የተሰጣቸው ተቋማት በሙሉ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በሚገባ መወጣት አለባቸው፡፡ ለዚህም ደግሞ ኃላፊነታቸውን ተረድተው እንቅስቃሴ ማድረግ አለባቸው ብለን እናምናለን፡፡ ተቋማት ስንል ደግሞ የመንግሥት ተቋማትን ብቻ አይደለም፡፡ የሲቪክ ተቋማትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫው ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ በታላቅ ትህትና መጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡ እንደ ኢዜማ ምርጫው ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን አባላቶቻችንን፣ ደጋፊዎቻችንን እናስተምራለን፡፡ በተጨማሪም ማንኛውም እንቅስቃሴዎቻችን የሌሎችን ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች መብት ባከበረ መልኩ እንዲሆን የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን፡፡ ይህንንም በዚህ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እፈልጋለሁ፡፡
ጥያቄ፡ ጊዜዎትን ሰውተው ከእኛ ጋር ቆይታ ስላደረጉ እኛም እናመሰግናለን፡፡
እኔም ስለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡

3 Comments

 1. Whoever he or she was asking the questions failed to introduce himself or herself, maybe on purpose because she or he failed to ask important questions such as

  -What is Ezema’s stand on the current arbitrary arrests of close to ten thousands people claiming it was done to quiet down the violence which took place right after Hachalu Hundessa was killed?

  – Does EZEMA feel it is just to arrest Eskinder Nega and charge him with terrorism?

  -Why did Ezema took time until the election was postponed to initiate a study about the handing out of the Addis Ababa Condos? Is it to give enough time for the government to handout enough condos?

  -What are the Ezema offices in Oromia and Benishsngul Gumuz region reporting about the ongoing slaughtering of people based on their ethnicities and based on their religions? Does Ezema think there is a crime against humanity ongoing genocide taking place?

  -What is Ezema’s stand on the GERD negotiation issues?

  -What is Ezema’s office in Tigray planing to do to bring the deteriorated relationship between the current Tigray region’s government and the central government?

  -Do Ezema’s leaders feel lucky or do Ezema’s leaders feel innocent for not being imprisoned while many other opposition political figures suffered imprisonments in the past few months ? Do they have suggestions for opposition politicians how to avoid being imprisoned as their leaders did? Are any of Ezema’s members imprisoned accused of participating or planing to participate in the violence that took place right after Hachalu’s death?

  Does Ezema feel Ethiopia currently got a failed state?

  Does Ezema feel Ethiopia is under a state terrorism?

 2. የኢትዮጵያ ህዝብ ግጭትና ጦርነት ስለሰለቸው እንደ ሕንዱ ጋንዲ ሰለማዊ ትግል ቢደገፍም በሕዝብ ውስጥ የሚነሱ ወዥንብሮችን ለማጥራት በኢዜማ በደንብ መሰራት አለበት፡፡
  አለባብሰው ቢያርሱ ሆነና ነገሩ ከምርጫ በፊት ገና ብዙ የሚሰሩ ነገሮች እንዳሉ ገሃድ ነው፡፡ ገና ምን ተይዞ ስለምርጫ፡፡ የገዥው ፓርቲ ቁርጠኝነት፣ የተቋማት ዝግጅት፣ የፓርቲዎች አቋምና ቅድመ ዝግጅት፣ የፍትህና ህግ አካላት ገለልተኝነትና ግልፀኝነት፣ የሚዲያዎች ገለልተኝነት … ወዘተ ፡፡ ህዝብ እኮ ማን ፓርቲ ምን እንደሆነ ምን እንደሚያደርግ ቀድሞም አውቆታል፡፡ አብዛኛው ዜጋ ጠግቦ መብላት ባይችልም እንኳ ቅድሚያ የሚፈልገው የሰላም ዋስትናና ፍትህ ነው፡፡ ታዲያ ማን ፓርቲ ነው በቅድሚያ እነዚህ መሰረታዊ ጥያቄዎች ታግሎ ሰላማዊ ምርጫ እንዲኖር የሚጋፈጥ፡፡ ከዛ እኮ የፖሊሲ ጉዳይ ቀጥሎ የሚመጣ ነው፡፡ የስልጣን ፍላጎት ወደ ጎን በመተው ለአገርና ለህዝብ አስባለው የሚል ፓርቲ (ብልፅግና ፓርቲ ጭምር) መጀመሪያ የእነዚህን ዋስትና ለህዝብ ማረጋገጥ ሲችል ነው ቅቡልነት የሚኖረው፡፡

  ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!

 3. የኢትዮጵያ ህዝብ ግጭትና ጦርነት ስለሰለቸው እንደ ሕንዱ ጋንዲ ሰለማዊ ትግል ቢደገፍም በሕዝብ ውስጥ የሚነሱ ወዥንብሮችን ለማጥራት በኢዜማ በደንብ መሰራት አለበት፡፡ አለባብሰው ቢያርሱ ሆነና ነገሩ ከምርጫ በፊት ገና ብዙ የሚሰሩ ነገሮች እንዳሉ ገሃድ ነው፡፡

  ገና ምን ተይዞ ስለምርጫ፡፡ የገዥው ፓርቲ ቁርጠኝነት፣ የተቋማት ዝግጅት፣ የፓርቲዎች አቋምና ቅድመ ዝግጅት፣ የፍትህና ህግ አካላት ገለልተኝነትና ግልፀኝነት፣ የሚዲያዎች ገለልተኝነት … ወዘተ ፡፡ ህዝብ እኮ ማን ፓርቲ ምን እንደሆነ ምን እንደሚያደርግ ቀድሞም አውቆታል፡፡ አብዛኛው ዜጋ ጠግቦ መብላት ባይችልም እንኳ ቅድሚያ የሚፈልገው የሰላም ዋስትናና ፍትህ ነው፡፡ ታዲያ ማን ፓርቲ ነው በቅድሚያ እነዚህ መሰረታዊ ጥያቄዎች ታግሎ ሰላማዊ ምርጫ እንዲኖር የሚጋፈጥ፡፡ ከዛ እኮ የፖሊሲ ጉዳይ ቀጥሎ የሚመጣ ነው፡፡ የስልጣን ፍላጎት ወደ ጎን በመተው ለአገርና ለህዝብ አስባለው የሚል ፓርቲ (ብልፅግና ፓርቲ ጭምር) መጀመሪያ የእነዚህን ዋስትና ለህዝብ ማረጋገጥ ሲችል ነው ቅቡልነት የሚኖረው፡፡

  ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.