እትዬ አበበችና ስዩም (የመሠረተ ትምህርት ትዝታዎች)  (ዘ-ጌርሣም)

Meserete tmhrtበህይወት ላይ ብዙ ገጠመኞች አሉ፤አብዛኞቹ ሲረሱ አንዳንዶቹ ደግሞ ሁልጊዜ አብረው ይኖራሉ።ትዝታዎች ጥሩም መጥፎም ሲሆኑ ገጠመኝ የራስ ወይም የሌሎች መታሰቢያ ነው።በህፃንነት ዕድሜ ጭቃ አቡክቶ ውሃ ተራጭቶ ተኮራርፎና ተደባድቦ ተመልሶም ጓደኛ በመሆን በክፉ ወይም በበጎ የሚታሰቡ ሆነው በትምህርትና  በስፖርት ተወዳድሮ ማሸነፍና መሸነፍ ራሱን የቻለ ገጠመኝና ትዝታዎች ናቸው።

የታሪክ ትረካወችም እንደ አቅራቢው ይለያዩ እንጅ የማይረሱና የህይወት ተጓዳኝ በመሆን ይቀጥላሉ።የታሪክ ትረካ ተሰጥዖ ይጠይቃል፥የራስን ወይም የሌሎችን ገፀ ባህሪያት ለመግለፅ ሥነ ጥበባዊ ስጦታ ይሻል፤ጥርስ የማያስከፍተውን ትረካ አሳምርው በማቅረብ ህይወት እየሰጡ የሚያዝናኑ ተራኪዎች የመኖራቸውን ያህል የደመቀ ህዝባዊ ትዕይንት የሚወጣውን ትረካ ባለቤቱን በማጣቱ አንገሸገሰኝ የሚሰኙ በርካታወች ናቸው።ሥነ ጥበብ መስታወት ነችና ባለቤት ትፈልጋለች።

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ የአንድ የትምህርት ቤትና የሥራ ባልንጀራዬ የነበረና በጣም የቀረበ ግንኙነት የነበረን በየጊዜው አኔንም ሆነ ሌሎች የጋራ ጓደኞቻችንን በልዩ ልዩ ትረካወቹ እያሳቀ ከሚያዝናናን መካከል አንዷንና ዘመን ተሻጋሪ ነች ብየ ያሰብኳትን መምረጥ ወደድኩ።

ስዩም ይባላል፤ንፍስ ይማርና  በህይወት የለም።ተወልዶ ያደገው በወቅቱ ምርጥ ሥጋና የፍራፍሬ ጭማቂ አላፊ አግዳሚውን በምታስተናግደው ዱከም ከተማ ሲሆን ዱከምን ለማታውቁ በአዲስ አበባና ደብረ ዘይት መካከል የምትገኘው ትንጥዬ ከተማ ነች፤ ምንም እንኳን ደብረ ዘይትና ዱከም በሁኑ ወቅት የገጠሙ ቢሆንም።

ስዩም ትረካውን እንዲህ ነበር የጀመረው፤በዘመነ ደርግ የዕድገት በህብረት ዘመቻ ተቋርጦ በምትኩ አስራ ሁለተኛ ክፍልን የጨረሱ ተማሪዎች ለጎልማሶች በመሠረተ ትምህርት አስተማሪነት ሲያገለግሉ ስዩም ተወልዶ በአደገባት ከተማ ዱከም ይመደባል።የስዩም ተማሪዎች አብዛኞቹ የጓደኞቹ እናቶችና አርስ በርሳቸው የሚተዋወቁ ሲሆን በተገናኙ ቁጥር አበክረው የሚያወጉት ስለ ኑሮ ውድነት፣ምን ተወደደ፣ ምን ረከሰ በሚሉት ዙሪያ ነው።ተማሪዎቹ ሁሉም እናቶችና ልጅ የሌላቸውም ካሉ ሁሉም ትልልቅ ሴቶች ናቸው።ትምህርት ቤት መግባት የተገደዱት ከቀበሌ ሱቅ ለሚገዙና ለሚሸመቱ የምግብ ቁሳቁሶች የፈቃድ ወረቀትና ቅድሚያ ለማግኘት ሲሆን ዋጋውም በጣም የረከሰና ከግል ነጋዴው ዋጋ ጋር ሲነፃፀር እጅግ የሚስብ ሁኖ በመገኝቱና አጋጣሚውን ለመጠቀም ነው። ታዲያ ይህን ዕድል ለማግኘት ደግሞ ”በእርጅና ቁንጅና” እንዲሉ ተማሪ ሆኖ ከመመዝገብ በተጨማሪ የፈተና ውጤት ማስረጃ ማቅረብ ግድ ይል ነበር።የተማሪዎቹ ስብጥር ከወጣት የቤት እመቤት እስከ ኦድሜ ጠገብ እናት ያካተተ ከመሆኑ በተጨማሪ  አስተማሪዎቹም ለብዙዎቹ ተማሪዎች ልጅ ፣ለዕድሜ ጠገቦቹ ደግሞ የልጅ ልጅ በሚሆን የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙና ከሁለቱም ፆታወች የተውጣጡ ነበሩ።

የስዩም ተማሪዎች አብዛኞቹ ትልልቆችና ሴቶች ብቻ ሲሆኑ ሥራውን በተገቢ ሁኔታ ለማካሄድ ይቸገር ነበር፤እሱን በማዳመጥ ፈንታ እርስ በአርሳቸው ስለቀበሌው ሱቅ፣ስለ ጉልት ገበያውና ስለሌሎች የገበያ ቦታወች ቡና እየጠጡ እንደሚያወሩት በሚመስል ያወራሉ።ከአናት ተማሪዎች መካከል በዚህ ፀባይ የታወቁት እትዬ አበበች የተባሉት ሲሆኑ ሌሎቹ አድማጫቸውና  አድናቂያቸው ነበሩ።ብዙ ጊዜ ስዩም ተማሪዎቹን የሚያነጋግራቸው በአክብሮትና በፍርሀት ስሜት ነበርና አንድ ቀን በዚህ ሁኔታ መቀጠሉ ተገቢ መስሎ ስለአልታየው ትንሽ ጠንከር ባለ አቀራረብ የክፍሉን ፀጥታ ለማርገብ ሙከራ በማድረግ፤እንዲህ በማለት ይጀምራል፥

ስዩም         ዛሬ ትምህርታችን የምንጀምረው በአማርኛ ትምህርት ነው

እትዬ አበበች          ከት ከት ከት ብለው ሳቁና ወይ ጉድ ”እግር ሂዶ ሂዶ የማይደርስበት የለም”                 እኔን አማርኛ የምታስተምር ደግሞ አንተ ሆንክ፣እኔ አበበች አንተ ገና በእናትህ        ሆድ ውስጥ ሳትረገዝ ነው አማርኛ የማውቀው

ሌሎች ተማሪወች      ክፍሉን በሳቅና በጩኽት አደመቁት

ስዩም          እትዬ አበበች እዚህ እኮ የመጡት እማራለሁ ብለው ነው

አትዬ አበበች           ተወኝ ወዲያ! ትምህርቱ እንኳን ለኔ ለአንተም አልጠቀመ፤ተማርን ያላችሁትም ስታውደለድሉ ከመዋል ያለፈ የሠራችሁት               የለም፤ሂድና የኔን ልጆች ጠይቅ፤ ወንዱም ሴቷም የአልጋ ሽቦ ሲያረግቡና ሶፋ ሲያለፉ ነው የሚውሉት

ስዩም          ታዲያ ሊማሩ ካልሆነ ለምን መጡ

እትዬ አበበች              አይ የኔ ልጅ ስኳርና ዘይት ለመግዛት የምትችይው ስትማሪ ብቻ ነው ብሎ የእናንተ አለቃ ተብየወ  የቀበሌ ተመራጮች ስለአስገደዱኝ  ነዋ! አይደለም እንዴ! እስኪ ሁላችሁም እውነቱን ተናገሩ

የክፍሉ ተማሪዎች      ትክክል ነው፣እውነቱን ነው ፍርጥ አርገው የተናገሩት፤እኛማ     እንደ እርስወ አንችል፤እንዲህ አርገው ያቅምሱልን እንጅ፤እኛማ ብንናገር አይደለም የቀበሌወቹ ተመራጮች ባል ተብየዎቹ ሳይቀሩ አያስቀምጡ      ንም ፤የነሱን ቁጣና ፍጥጫ ለመራቅ ብለን ነው ከዚህ ተጎልተን የምንውለ ው፤ከዚህ በኋላ ምን ልንሆን ድሮስ፣ወጉ አልቀረም።አዳሜ  ተማርኩ      ሰለጠንኩ ብሎ ሲቦጠጥና ሁሉም ሥራ ሲያጣ ቀበሌና  ካድሬ ብቻ ሆኖ አይደል የቀረው!! እኔ እንደሁ ጦሜን አድራለሁ እንጅ ካድሬ ሁኘ ወገኔን ሳስለቅስ አልኖርም

ስዩም                       ውይይቱ መስመር በመልቀቁ ስጋት ውስጥ ስለከተተውና አድማ አነሳሽ ሆንክ የሚለውን ተጠያቂነት ለማስወገድ ሲል ርዕሱን ለመቀየር ተገደደ

እንዲህም አለ፣አሽ እትዬ አበበች የአማርኛ ትምህርቱን እንተውና ሌላ ነገር እንማር ሲል

እትዬ አበበች                ድሮስ እኔ አልጠየኩህ አንተው አምጣኽው እንጅ ፤ደግሞ ሌላ ምን ልታመጣ ይሆን! ቀደም ብየ እንዳልኩህ አማርኛ አንተ እንደማታስተምረኝ ተግባብተናል፤ በዚህ የተነሳ አይደለም የቀበሌ ሱቅ ሽመታ የመርካቶ ገበያም ይቅርብኝ።ሳልሞት ደግሞ አንተ እኔን አማርኛ ላስተምርሽ ! ደፋር!

ይህ ደግሞ የአስተዳደግ ጉድለት ነው፤ብትፈልግ ሂድና ለአለቃህ አበበች እምቢ አማርኛ በአንተ አፍ አልማርም ብላለች ብለህ አቃስጥና ሁሉን ነገር ይከልክሉኝ ”ኩራት እኮ እራት ነው” አንተ!

ስዩም                       እትዬ አበበች አይቆጡ አባከዎት፣እኔ የተሰጠኝ ትዕዛዝና  መመሪያ ነው ካስቀይምኩ ይቅርታ

እትዬ አበበች                ኤዲያ መመሪያ የምትለኝ እኔይቷ አበበች ዓይነ ስውር መሰልኩህ ወይስ መንገድ ጠፋኝ አልኩህ።ታዝዠ ላልከው ግን ድሮስ አንተ ከመታዘዝ ሌላ ምን ልታደርግ ኑሯል! ምን አቅም አለህና ሌላ ምን ልትሠራ አሰብክ ይህም ሲበዛብህ ነው አልገባህም እንጅ፤አንተንስ ማዘዝ የሚያቅተው ማን አለና፤አሁን ዕድሜ ለጌቶችህ በልና ቀረ እንጅ ክፉ ልታናግረኝ አይደል! የዛሬ ዘመን ልጆች ሳይነካኳችሁ ትነካኩና አገር ታቃጥላላችሁ የሰው ጠባይም ታስገምታላችሁ፤አንተ ብዙ አታናግረኝ ይህችን ቀን ብናልፋት ይሻላል፤ለመሆኑ እናት የለህም አንዴ! ጥሎባቸው እንዲህ ዓይነቱን ደፋርና ዓይን አዉጣ ልጅ ከሚሰጠኝ መክኘ ብቀር ይሻለኛል

ስዩም                       ይቅርታ እኮ ጠይቄያለሁ እትየ አበበች ካጠፋሁ እንደገና ይማሩኝ ብሎ ወደ ጉልበታቸው ደፋ ማለት ሲጀምር

ከተማሪወቹ አንዷ           ወይ ጉድ አንተ ምን አቅም ኑሮህ ልጀ ታዘህ እንጅ፤ይበሉ እርስዎም ምርር ብለው አይዘኑበት፣ለልጆችዎ ግፉ እንዳይደስ የእናት አንጀተዎን ፈታ ያርጉት ሲሏቸው

እትዬ አበበች                ውይ ምን አረኳችሁ እንዲህ ዓይነቱስ  በልጆቸ አይድረስ ጠልዩልኝ፤በያመቱ የምዘክረው ቅዱስ ሚካኤልስ ምን ይሰራል።ይህ ልጅማ ምን አድርጎ መታዘዙንማ እኔም አውቃለሁ በምንስ አቅሙ ይህን ማድረግ ይችላል ተብሎ ይታሰባል! አንዲያው ነገሩ ቢበዛብኝ እንጅ።አውቃለሁ ማረር መትክኑ ለኔ ብቻ የመጣ አይደለም፣የአገራችን የቤት እመቤትና ሴት ወይዛዝርት ሁሉ ስቃዩን እያየ አይደል! ለማን አቤት ይባላል! ካድሬና ቀበሌ አንደሁ የቀን ጅብ ሁኗል፤መዝረፍ ማስጨነቅ እንጅ።ለመሆኑ አናትና እህት ያላቸው ይመስላሉ! ይህ ምስኪንማ በምን አቅሙ።እንደቤት ውሻ የሰው እጅ አይቶ የሚያድር አይደል በማለት ስዩምን በሃዘኔታ እየተመለከቱ የውስጥ በስጭቱን ከአበረዱለት በኋላ በል ልጀ ባልወልድህም ልጀ ነህና የታዘዝከውን አስተምረን ግን አማርኛን ተወው በሱ አንስማማም በማለት አረጋጉት

ስዩም                       አመሰግናለሁ እትዬ አበበች አማርኛውን ትተን ሂሳብ እንማር ሲላቸው ደስታ የተሞላበት ይሁንታ  አሳዩትና በል እሱ ጥሩ ነው ለኛም ይረዳናል፤እኔ እንዲያውም ይህን ዓይነቱን ትምህርት ድሮ ጀምሬ እፈልገው ነበር።መርካቶ ገብያ ሂጀ መልስ ሲሰጡኝ ሁልጊዜ ሳልጣላና ሳልጨቃጨቅ ተቀብየ አላውቅም፣ብዙዎችም ያታልሉኛል።ምንም እንኳን ሱቅ ከፍቸ ትርፍና ኪሳራ ባላሰላም መቀነቴ ላይ ያለውን ገንዘብ እንኳን በደንብ መቁጠርና ማስላት ያስፈልገኛል።የኔ ልጆች ሁልጊዜ ማዕድ ቤት ሁኘ ስሰማችው ሂሳብ ሲያሰሉ እሣት የላሱ ናቸው፣በተለይ ሴቷ ልጀ ስሌቱን በአየር ላይ ነው የምትቀልበው፤ወንዱ እንኳን ትንሽ እንዳንተ ፈዘዝ ያለ ስለሆነ ሂሳቡን ቢችለውም ትብት ብሎ በፍጥነት እንደ እህቱ አይናገረውም።በል አንተ አሁን እኛንም ፈጣን አስሊዎች እንድንሆን አስተምረን።ይህን ካደረክ ምርቃታችንም ለትልቅ እንጀራ ያበቃሃል፤የተመረቀ ልጅ ረደኤት አይለየውም

ስዩም                       በሉ አሁን ትምህርቱን እንጀምር አለ፤ወቅቱ አርባ ፆም የሚፆምበት ወቅት ነው፤በመቀጠልም እንዲህ አለ፥

አበበ ገበያ ሂዶ አስራ ሰባት ዕንቁላል ገዛ ሲል

እትዬ አበበች                ስብሃት ለአብ ስብሃት ለወልድ እመቤቴ ደግሞ ምን ልታሰሚኝ ነው! በማለት ማጉረምረም ጀመሩ፤ሌሎች ግን በፅሞና ያዳምጣሉ፤እትየ አበበች ግን ጀሮዬ አይስማው የለ፣ጉድ እኮ ነው እንደ እናት ዶሮ ታቅፎ ጫጩት ሊቀፈቅፍ ነው፣ደግሞስ ሁዳዴ ፆም መሆኑን ረሳው! አቡዬ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አባክወ ክፉ አያሰሙኝ በማለት ዝም አሉ

ስዩም                       በመቀጠልም ከአስራ ስባቱ ዕንቁላል ውስጥ ሁለት ወድቆ ተሰበረበት ሲል

እትዬ አበበች                ከርፋፋ ተጠንቅቆ አይዝም ነበር

ስዩም                       ሦስቱን ለጓደኛው ለከድር ሰጠው

እትዬ አበበች                ደግሞ እሱስ ምን ሊያደርገው ይሆን፤ከአበበ የባሰም አለ ለካ

ስዩም                       አራቱን ሸጠ

እትዬ አበበች                ለከስካሳ በሱ ቤት ስራ መስራቱ ነው፤ ይልቅ ሌላ ለወንድ ልጅ የሚስማማ ስራ ሰርቶ አይበላም! ስራው ተሰርቶ ተሙቷል! ”ሌባ ለአመሉ ዳቦ ይልሳል” ይባል የለ

ስዩም                       ሁለቱን ቀቅሎ በላ ሲል

እትየ አበበች                ትዕግስታቸው ወሰን አጣና ኡ ኡ ብለው እየጮሁ አቤት አቤት የጉግ ማንጉግ ጊዜ፣የጌታ ቃል ታጥፎ በአርባ ፆሙ ዕንቁላል የሚበላበት ጊዜ ደረስን።ፈረንጅ ነኝ ሊለን ይሆን! አፈር ያስብላህ ምኑን አሲድ በሆዱ ቀበረበት፤ስንት በፆም ጊዜ የሚበላ እንደ ድንች፣ ጎመን፣ ሽሮ፣ ክክ፣ ምስር፣ ሱፍ፣ ተልባ፣ ኑጉ፣ ባቄላው ስንቱ ተዘርዝሮ የባለሙያ ሴት እጅ ይቁጠረው እንጅ።ውሻ ይመስል የተገኘው ሁሉ የሚለቀምበት ጊዜ።አቤት አቤት ፈጣሪ አምላክ ስንቱን ልታሳየን ነው፤እረ ግፉና መዋረዱ በዛ በቃ በለን ምግብ ሳይጠፋ ዕንቁላል በፆሙ ምድር ይበላል! ለመሆኑ ይህ ጉድ በራዲወ ተነግሮ ያገራችን ህዝብ ቢሰማው ምን የሚያስከትል መሰለው።ይህ ሁሉ ጉድ የመጣው ይህ የቀበሌ ሱቅ የቀበሌ ጉድ ቢሉት ይሻል ነበር  የሚባል ከመጣ በሁዋላ እንጅ ይህን ያህል ዕድሜዬን ስኖር ይህን የመሰለ ጉድ ጀሮየን አሰምቶት አያውቅም፤ምን ይደረግ የራሱን ንጉሥ ገሎ የሰው አገር ንጉሥ የሚያወድስና የሚያከብር ጉግ ማንጉግ  ጥሎብን።ላደለው ምዕመናን በየገዳሙ እየዞሩ ሱባዔ በሚገቡበት ወቅት ካልሆነም እንደ አባት አደሩ በባቄላ አሹቅና ንፍሮ መሬት ላይ እየተኙ ማረኝ ማረኝ የሚባልበት ጊዜ ነበር።ታዲያ ምን ይደረግ አንድየም ሰለቸን መሰል አልሰማ አለ፤እሱማ ምን ያርግ የኛ ሃጢያታችን ስለበዛ ስንቱን ይታገሰን

ስዩም                       ይበሉ የሂሳብ ጥያቄው ይህን ይመስላልና በመጨረሻ አበበ ስንት ዕንቁላል ቀረው ብሎ ሲጨርስ ሁሉም ተማሪዎች እጃቸውን አወጡ

እትዬ አበበች                አሁን ይበልጥ ተናደዱና ወደ ሌሎቹ ተማሪዎች ዞር በማለት የት ነበራችሁ አስካሁን! እያንዳንድሽ አንደ ቆርበ ሰው አፍሽን ይዘሽ እንዳልነበር አበበችን ደንቆሮ ለማሰኘት ነው ይህ ሁሉ ማስመሰልና መጣደፍ! እኔ እኔ ማለት እስኪ እናንተን ምን አገባችሁ! መልሱን ነገራችሁ እንዴ! ወይንስ እያንዳንድሽ አፏን እንደዘጋች ቤቷ ተመለሳ ሄደች የምላችሁ መሰላችሁ! ሲሆን እኔና እሱ ስንጣላ መገላገል ሲገባችሁ ከንፈራችሁን ስትመጡ ዉላችሁ አሁን እኔ እኔ ትላላችሁ፤ለአበበች መልሱ ጠፋት ያላችሁ ማነው፤ያውም እኔይቷ አበበች ከእናንተ አንሸ!እንኳንስ የአስራ ሰባት ዕንቁላል ስሌት አንድ ዶንያ ጤፍ ብታመጡ እንኳን ቆጥሬና አስልቸ መስጠት እችላለሁ።ሌላው ቢቀር እሳት የላሱና በቃላቸው ትምህርቱን የሚያነበንቡ ልጆች አሉኝ፤ደግሞ ብዙዎቻችሁ ልጅ አንኳን አሳድጋችሁ አታውቁም፤አጉል አለሁ ለማለት ግን ማን ቀድሟችሁ።እግዚአብሔር ያሳድገውና ልጁ ጥያቄውን የጠየቀው እኔን ነው ግን የናንተን መውለብለብ ምን አመጣው! እስኪ ከመካከላችሁ ጥያቄው ለእኔ ነው የሚል አለ! አልገባችሁም እንጅ መኖራችሁን እንኳን ያስታወሰ እይመስለኝም።ምነው ሚካኤል ሻማህን እንኳን አብርቸልህ ነበር፤ የቀብሌው ሱቅ ሽመታ ይቅር እንጅ የማንም መቀለጃና መለማመጃ ልሆን አልመጣሁ።ልጁ እንኳን ጥፋቱን ተረድቶ ይቅርታ ጠይቆኛል፤እንዲያው ገና ለገና ከአንድ የግዳጅ ትምህርት ወንበር ላይ አብረን ተቀመጥን ተብሎ እንዲህ ይደረጋል እንዴ!!ለነገሩማ ይበለኝ ክብራቸውን የወደዱት ጓደኞቸማ ምኑም ምኑም ይቅርብኝ ብለው ከጎረቤቶቻቸው ጋር ደግ ደጉን እያወጉ ቡናቸውን እየተጠራሩ ሲጠጡ ይውላሉ፤እኔ ግን ልጅ አሳድጋለሁ ብየ ለውርደት በቃሁ።እኔ ተምሬ አገር አልገዛ፣መሃያ አላስቆርጥ፤ለስኳርና ዘይት ብየ ራሴን ላዋርደው! ብለው ምርር ባለ ስሜት ሲናገሩ

ስዩም                       ቀበል አደረገና  ወደ ሌሎቹ እይተመለከተ ጥያቄውን ያቀረብኩት ለእትዬ አበበች ስለሆነ እናንተ አዳምጡና እሳችቸው ካልቻሉት እናንተ ትሞክራላችሁ

እትዬ አበበች                አንተ ልጅ ተወኝ ብየሃለሁ ጤና የለህም እንዴ! ማንኛዋ ነች ለኔ አቅቶኝ እሷ ትመልሰዋለች የምትባለዋ፤ለብሰውና ተሽሞንሙነው ስላየሃቸው ሊቅና አዋቂ መሰሉህ እንዴ! አንተማ ምን ታደርግ! ልጅ አሳድጋለሁ በየ እንዲህ ወድቄና ተጎሳቁየ አይተኽኝ፤ነበርኩ ማለት አይጠቅምም እንጅ ከዚህ ከፊትህ ከምታያቸው ሁሉ የበለጥኩና አንች የተባልኩ የቆንጆዎች ቁንጮ ነበርኩ።እንዲህ ጎስቁዬ እያየኸኝ እንኳን ”የጥሩ ሸክላ ምስክሩ ገሉ” ነው እንዲሉ አስተውሎ ለተመለከተኝ ውበቴ አሁን ድረስ ማንንም የሚያስንቅ ነው።

አሁን አንተን የምጠይቅህ የሂሳብህን መልሱን ይዠዋለሁ፣እኔ ስናገር ጣልቃ እየገቡ ማደናቀፉን እንዲያቆሙ ንገርልኝና መልስህን አንድ ባንድ ምንዝርዝር ብጥርጥር አድርጌ እነግርሃለሁ፤ተግባባን! ሲሉ

ስዩም                       በሉ እባካችሁ ሁላችሁንም በአክብሮት የምጠይቀው የእትዬ አበበችን መልስ በፅሞና አብረን እናዳምጣቸው ሲል ሁሉም ዝም አሉ

እትዬ አበበች                ስዩምን አመስግነው በሉ ሁላችሁንም የምጠይቀው አስቀይሚያችሁ ከሆነ በእመቤቴ ስም ይቅርታ እየጠየቅሁ መልሴን በደንብ ስሙልኝ፤አንተም ብትሆን መልስህን ካገኘህ በሁዋላ ሳትውል ሳታድር ቢቻል ዛሬውኑ ለሁላችንም ካልሆነ እኔን በተመለከተ ጠቅላላ ትምህርቱን ሂሳብ የምትሉትን ሳይቀር በደንብ ስለቻለችው ከቀበሌው ሱቅ የምትፈልገውን ሁሉ መሸመት እንድትችል ይፈቀድላት ብለህ ሲሆን በጥሁፍ አለዚያም በቃልህ አንድትነግርልኝ ነው የምፈልገው፤ይህን ስልህም እንደልመና እንዳትቆጥረው መብቴንና ችሎታየን አውቀዋለሁ።ዲፕሎሙንም ሰኔ ወር ድረስ የምጠብቅበት ምክንያት ስለሌለ፤ደግሞስ አንተው ለምትጥፈው ነገር  ያን ያህል የሚያስጠብቀኝ አይመስለኝም፤የጎደለ ካለም ወደፊት ማስተካከል አያቅተኝም።ሰው በዱቤ ዕቃ ይገዛል አይደል! እንደዚያ አርገህ ቁጠረው።ዛሬውኑ ሰጥታችሁ ብታሰናብቱኝ ለእናንተም ረፍት ነው፤የሚቀርባችሁ ከእኔ ጋር ጭቅጭቁ ብቻ እንጅ የሚጎልባችሁ ነገር የለም።እኔ ብጎልባችሁ እንኳን ሌሎች የሚፈልጉና የምትናገሩትን ሳያላምጡ የሚውጡላችሁ ሞልተዋልና ለእኔ በሰላም ዲፕሎሜን ሰጥታችሁ አሰናብቱኝ።ይህን የምልህ ደግሞ በነፃ ስጡኝ ሳይሆን አሁን የጠየክኝን ከባድ የሂሳብ መልስ በደንብ አርጌ ከመለስኩልህ በሁዋላ ነው፤እኔ እንደሁ ከዚህ ወዲያ ተጨማሪ ትምህርት አያስፈልገኝም።ዩኒበርሲቲ አልገባ ወይም ፓርላማ ምረጡኝ ብየ አላስቸግር፤እኔይቷ አበበች እንደሁ ስሜንና የቤተሰቤን ስም እስከ አያት ቅድመ አያታቸው ድረስ ቁልጭ አድርጌ መፃፍ ችያለሁ።ቀበሌ ስብሰባ ላይ ግራ እጃችሁን አውጡ የሚለውን አስቸጋሪ ትምህርት አንኳን ቀኝ አጀ እንዳያስቸግረኝ በመቀነቴ ከወገቤ አስጠግቸ በማሰር ግራ እጀን ብቻ አለማምጀ ዛሬ ስንቱ ሴት ወይዛዝርትና መኳንንት በእጅ ማውጣት ሲደናበር እኔ ብቻ ያለችግር በመቻሌ ሰብሳቢዎቹ ሳይቀር ስሜን ከህዝቡ ፊት አጉልተው  እየጠሩ አመስግነውኛል።ስለዚህ ዛሬ ለእኔና ለአንተ የመጨረሻ ቀናችን ስለሆነች የጥያቄህን መልሶች በጥሞና አዳምጥ፥

  1. አበበ ገብያ ወጥቶ አሥራ ሰባት ዕንቁላል ገዛ ላልከው

መልሱ አቤት አቤት ያሰኛል፤በጣም የሚያሳፍር ሰው ነው፤ካልጠፋው ንግድ ያውም በሁዳዴው ፆም ሰው የዕንቁላል ነጋዴ ይሆናል! አይ አለመታደል አሳዳጊውን አሰዳቢ፤ለመሆኑ እናትና አባት ይኖረው ይሆን! ምናለበት ጥራጥሬውን ነግዶ ቢሆን! በዚያውም የፆመኞቹ ጾምና ፀሎት ምህላው ተጨምሮለት ረድዔቱ ይደርሰው ነበር

  1. ሁለቱን ለከድር ሰጠው ለምትለው የዛሬ ልጆች ከውሸት ሌላ ስላልተማራችሁ አንተው አይቻለሁ ብለህ የለመድከውን የውሽት ምስክርነት ስጥ እኔይቷ አበበች እንኳንስ በሁዳዴው ፆም ጊዜ የፋሲካ ዕለት እንኳን ባይ ሲሰጠው አይቻለሁ ብዬ አልመሰክርም፤ለመሆኑ ከድር እኮ የራሱ የፆም ጊዜ አለው፤እንዳንተም የሚዋሽ አይመስለኝም።ደግሞስ ይህን ዓይነቱን ቀልማዳ ወሬ የሂሳብ ትምህርት ብለህ ትጠራዋለህ!የመቀላመጃና የሃጢያት ትምህርት ብትለው በተሻለ ነበር።ሌላው ቢቀር በፆሙ ምድር የዕንቁላሉን ስሙን አንኳን ስትጠራ ኩነኔ እንደሆነ ይገባሃል! በየሻይ ቤቱ እየዞሩ ያንንም ያንንም መቅመስና መላስ ቁምነገር መስሎህ ነው! ምን ዓይነት ዘመን ላይ ደረስን፤በመሆኑም መልሴ ሲሰጥም ሲቀበልም አላየሁም፤ እረካህ!
  2. አራቱን ሽጦ በላ ብለሃል

እንዲህ ነው ነጋዴ! የሐረር ሰንጋ ነጋዴ! የጅማ ቡና ነጋዴ! የአዳ ነጭ ጤፍ ነጋዴ! የጎጃም ማር ነጋዴ! አቤት አቤት! ወጉ አልቀረም እሱም ከነጋዴዎች ቁጥር ሊገባ ፈለገ አይደል! የዕንቁላል ቱጃር ነጋዴ እንበላዋ! ያዉም የአራት ዕንቁላል ነጋዴ!! ተነግዶና ተከብሮ ተሙቷል፤ለመሆኑሳ አያፍርም!

ስለዚህ መልሴ ሲሸጥም ሲለውጥም አላየሁ፤ባይ እንኳን ያሳፍረኛል፤”ሌባ ለአመሉ ዳቦ ይልሳል” እንበለው እንዴ! እኔ አንተን ብሆን ይህን ጥያቄ ብየ አላቀርብም፤ለመሆኑማ አንተስ በሌሎች መጠሪያ አስተማሪ ተብልህ አይደል!

  1. ስንት ቀረው ላልከው

የኔ መልስ ስንት ኑሮት ስንት ሊቀረውስ ይችላል! አሥራ ሰባት ዕንቁላል ቁም ነገር ሆኖ ነበረኝ ይባላል እንዴ! ምን ዓይነት ሃፍረተቢስ ነው።

ተሰበረብኝ፣ለጓድኛዬ ሰጠሁ፣ስንት ቀረኝ! አሁን ይህ ጥያቄ ተብሎ ከሰው ፊት ይቀርባል!

ለአንተ ዓይነቱ በቀጣፊ ስርዓት ለአደገና በውሸት ትምህርት አንጎሉ ለደነዘዘ በሬ ወለደ እያለ የወሬ ታናሽና ታላቅ ብልት ለሚያወጣ ጤናማ ጥያቄ ሊመስል ችሏል፤ለእኔ ለአበበች ግን ከወሬ ድሪቶነት የሚያልፍ አይደለም፤በመሆኑም ለጥያቄህ መልሱ ያለው ክራስህ ከአንተ ጋር ስለሆነ ከአለቆችህ ጋር ተወያይተህ በለመደው የአሉባልታ ልምዳችሁ በየስብሰባው እሰጥ አገባ እያላችሁ እንድትደሰኩሩ እየመከርኩ ጠቅለል ያለው መልሴ፥

ሲወድቅበት   አላየሁ

ማበደሩን              አልሰማሁ

ሲሽጥም               አላዋዋልኩ

የተረፈው አንዳለ      የማይታሰብ

መሆኑን ፍርጥም አርጌ ልነግርህ እወዳለሁ ሲሉ በመመለስ በስዩምና በእትዬ አበበች መካከል የነበርው የሃሳብ አለመጣጣም በዚህ ተቋጨ።

 

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.