ወንጀለኛ የህወሓት ሰዎችን ለመሸፈን አገር መተራመስ፣ የህዝብም ህልውና አደጋ ላይ መውደቅ የለበትም – አቶ አግዘው ህዳሩ

TPLF 1
ጥቂት ወንጀለኛ የህወሓት ሰዎች በህግ እንዳይጠየቁ ሽፋን ለመስጠት ሲባል አገር መተራመስና የህዝብ ህልውና አደጋ ላይ መውደቅ እንደሌለበት የራያ ራዩማ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አግዘው ህዳሩ አስታወቁ። አቶ አግዘው በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ ጥቂት ወንጀለኛ የህወሓት ሰዎች በህግ እንዳይጠየቁ ሽፋን ለመስጠት ሲባል አገር መተራመስ፣ አላስፈላጊ ቀውስና ግጭት መፈጠር፣ የህዝብም ህልውና አደጋ ላይ መውደቅ እንደሌለበትም አመልክተዋል።
የትግራይ ሕዝብ፣ የትግራይ ወጣቶች፣ የትግራይ ፖለቲከኞች በክልሉ የሚገኙ የጸጥታ ተቋም፣ ሚሊሻዎችና ልዩ ሃይል ከቡድኑ ጋር በመሰለፍ ህይወታቸውን፣ ህልውናቸውንና ኑሯቸውን በከንቱ አደጋ ላይ እንዳይጥሉ አሳስበዋል። ቡድኑ እየሄደበት ያለውን መንገድ እንዲፈትሽ ማስገደድና ማስጨነቅ እንዳለባቸውም መክረዋል። ህወሓቶች፤ ‹‹የአንድነት ሃይሉ ይፈረካከሳል፣ አገር ትፈርሳለች›› ብለው የያዙት አቋምና አስተሳሰብ ረብ የለሽ እንደሆነ አመልክተው ፣እነዚህ ጥቂት ወንጀለኛ በመጨረሻ በወንጀል ተጠያቂ መሆናቸው አይቀርም ብለዋል።
በክልል ደረጃ በህገ ወጥ መንገድ የተደራጀውን የህወሓትን አደረጃጀት ማቋረጡ ተገቢ መሆኑንም ጠቁመዋል። ለቀበሌ፣ ለወረዳ ምክር ቤቶችና ከተማ አስተዳደር ትብብር በማድረግና እውቅና በመስጠት በቀጣይነት የሚደረገውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ህጋዊ ውሳኔና አሰራርን እንደሚደግፉትም አስታውቀዋል። ፓርቲያቸው በፍትህ ትግሉ ምክንያት ባደራጀው የወረዳና የቀበሌ መዋቅር አማካኝነት መንግሥት ለሚያደርገው ተግባር ሁሉ ከጎን በመሰለፍ ለመደገፍም ሆነ ማናቸውንም መስዋዕት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የትግራይ ክልል ምክር ቤትና ከፍተኛ የህግ አስፈፃሚው አካል /ካቢኔ/ ህገመንግሥታዊ ቅቡልነት ስለሌላቸው ሁሉም የፌዴራል ተቋማት ምንም ዓይነት ህጋዊ ግንኙነት ማድረግ እንደማይችሉ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተላለፈው ውሳኔ ‹‹የምንቀበለው በከፍተኛ ሁኔታም የምንደግፈው መልካም አጋጣሚ›› ነው ሲሉም ተናግረዋል። ህወሓቶች በውይይት ችግሮቻቸውን መፍታት ሲገባቸው እያደረጉት ያለው 40 እና 50 ዓመታት እንደቆየ የፖለቲካ ድርጅት አይደለም ያሉት አቶ አግዘው፣ ህወሓቶች በኢትዮጵያና በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ ከፍተኛ ወንጀል ሲሰሩ መቆየታቸውንም ጠቁመዋል።
ሰላም፣ መረጋጋቱና ህዝባዊ አንድነቱ በመጨረሻ ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው ስለሚያስቡ በጥቂት ሰዎች ወንጀልና ሃጢያት ህዝቡ አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ እንዲገባና ከወገኖቹ ጋር ግንኙነቱን ለማበላሸት ከፍተኛ ሥራ እየሰሩ ይገኛሉ ሲሉም ከሰዋል። ‹‹የሰብአዊ መብት በመጣስ፣ በህገ ወጥ መንገድ ሕዝብን በማፈን ምርጫ በማካሄድ፣ ላካሄዱት ምርጫ ህጋዊ ነን ብለው መቀጠላቸው ትዝብት ላይ የሚጥላቸው መሆኑን አመልክተዋል።
ህወሓት እየሄደበት ያለው መንገድ ተንኳሽና ወደ እርስ በእርስ ግጭት የሚያስገባ መሆኑን ጠቁመው ፣ የፌዴራል መንግሥትና ሌሎች የክልል አካላትን ግጭት እንዲንቀሳቀሱ ሆነ ብሎ እየሰራ የሚገኝ መሆኑንም አስታውቀዋል። ህወሓት ውስጥ ያሉ አካላት በጸጥታው ስራና በደህንነት መዋቅሩ የነበሩ መሆናቸውን በማስታወስም፤ በመዋቅሩ የነበራቸውን ኔት ወርክ በመጠቀም ሀገርን ወደማያባራ ብጥብጥ ለመውሰድ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኙ አመልክተዋል። ክልሎች አካባቢ የሚታዩ ግጭቶች የህወኃት እጅ እንዳለበት ብዙ አመላካቾች አሉ፣ ይህም ድርጅቱ አገሪቱን ወደ ትርምስ ለማስገባት እያደረገ ያለውን ከፍተኛ ጥረት ያሳያል ብለዋል።
በትግራይ ክልል ተሰብስበው የፌዴራል መንግሥትን ረፍት በመንሳት፣ ሌሎች አካባቢዎችም ለመንግሥት ታዛዥ እንዳይሆኑ በመቀስቀስ፣ ሰላም እንዳይሰፍን፣ አገር እንዲፈርስ ጥረት በማድረግ እነርሱ የተከተሉትን አፍራሽ አካሄድ ሌላውም እንዲከተል፣ ለፌዴራል መንግስቱ ታዛዥነት እንዳይኖርና መልካም ግንኙነትና መስተጋብር እንዳይሰፍን ከፍተኛ ጥረት በማድረግ የትንኮሳና አገር የመበተን ስራ እየሰሩ መሆኑን አመልክተዋል። ሲጀመርም ተፈጥሯቸው ኢትዮጵያውያን ባለመ ሆናቸው ምክንያት የኢትዮጵያን መረበሽ ይፈልጉታል። የኤርትራ ህዝብ ከኢትዮጵያ መገንጠልና በውል ሳያስብበት እንደሄደ ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ ትርምስ ፈጥረው በትርምስ ውስጥ መንገድ ፍለጋ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ህወሓቶች በቅርቡ ያወጧቸው መግለጫዎችና ባለስልጣኖቻቸው የሚናገሩት ሲታይ እርስ በእርሳቸው የሚጋጩና አደገኛ መሆናቸውን አመልክተው ፣ ከውጭ ጉዳይ፣ ከመከላከያ፣ ከገቢዎችና መሰል ተቋማት ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ግን ደግሞ ተቋማቱን በበላይነት ከሚመራው መንግሥትና ከጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጋር ግንኙነት እንዲኖራቸው አለመፈለጋቸው አስገራሚ ነገር መሆኑን ጠቁመዋል ።
–ምንጭ፦ አዲስ ዘመን

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.