በማንኛውም ዜጋ ላይ የሚፈፀም ኢፍትሃዊነት በሁላችንም ላይ እንደተፈፀመ ይቆጠራል

አንዱ አለም አራጌ
October 10, 2020
Andualemከዚህ ቀደም በጣም በአመዛኙ የፓርቲዬን አቋም ካልሆነ በስተቀር እምብዛም የግል አቋሜን አንፀባርቄ አላውቅም።
ብዙውን ጊዜ ተቋሞቻችን ህፀፃቸውን እያረሙ ሁላችንም የምንደገፍባቸው ተቋማት እንዲሆኑ እድልም ሆነ ጊዜ መስጠት ተገቢ መሆኑን አምናለሁ። ይሁንእንጂ ፣ ትናንት የኢትዮጵያ ህዝብ በነፍስና በስጋው ተወራርዶ መራር ህዝባዊ ትግል ያደረገው ዝቅ ብለን የምንመለከተውን አይነት ግፍ ለማስተናገድ አለመሆኑ እሙን ነው።
በ1993 ዓ.ም በጊወርጊስ የጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤት በተለያዩ ሁለት ችሎቶች፣ በተመሳሳይ እለት፣ በተመሳሳይ ሰዓት የተፈፀሙ ሁለት ውሳኔወችን ለማስታወስ እወዳለሁ።
አንደኛው ችሎት በሀቪየስ ኮርፐስ ክስ አማካኝነት፣ እነአቶ ታምራት ታረቀኝን ካሰረበት አምጥቶ ለፍርድ ቤቱ ያቀርብ ዘንድ ፓሊስን ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ ቢያዝም ትዛዙ ባለመፈፀሙ በወቅቱ የፍትህ ሚንስትር የነበሩት አቶ ወረደ ወልድ ወልዴ ታስረው እንዲቀርቡ ባዘዘው መሰረት ታስረው ቀረቡ። ፍርድ ቤቱም የአንድ ወር እስራት ፈረደባቸው።
በሌላ የዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ ችሎት አቶ ስዬ አብርሃ ቀርበው የወይዘሪቷ ችሎት አርነት ሰደዳቸው። ይሁን እንጂ ለቤታቸው ሊበቁ የተገባቸው አቶ ስዬ አብርሃ በአፈሙዝ አስገዳጅነት ወህኒ እንዲወርዱ ተገደዱ። ሚኒስትር ወረደ ወልድ ወልዴ ደግሞ ሳይገባቸው ለሞቀ ቤታቸው በቁ።
ይህን የሃያ ዓመት ታሪክ ያለምክንያት አላነሳሁትም። ከእልህ አስጨራሽ ህዝባዊ ትግል በኋላ የለውጥ ሽራፊ ለማየት ብንጓጓም ከሃያ ዓመት በኋላ ተመሳሳይ ለከት ያጣ ግፍ እያስተናገድን ነው። በ”ለውጡ” የመጀመሪያ ወራት ህዝቡ የተራበ አንጀቱን አስሮ ይስቅ የነበረው፣ ድጋፉንም የቸረው ከእንግዲህ በፍትህ ፣ በእውነትና በእኩልነት የምጠግብበት ዘመን ጠባ ብሎ በማመኑ ይመስለኛል። ከፈጣሪ በታች ተስፋችን በእጃችን መሆኑ የቀትር ያህል ግልፅ ቢሆንም፣ ከሃያ ዓመት በኋላ ተመሳሳይ የፍትህን መጨንገፍን ሳይ ጥልቅ ሀዘን አልተሰማኝም ብል ግን እውነቱን አልናገርም ።
በቅርቡ የኢዜማ ስራ አስፈፃሚ አባል ወይዘሮ ሂሩት ክፍሌ ፍርድ ቤት የዋስትና መብቷን ቢያከብርላትም ፓሊስ ላለመልቀቅ ያሳየውን ዳተኝነት እናስታውሳለን። በተመሳሳይ የአስራት ቴሌብዥን ጋዜጠኞችንም እንዲሁ በመከራ መልቀቁ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።
ዛሬ ብዕሬን እንዳነሳ ያደረገኝ ጉዳይ የአቶ ልደቱ አያሌው ጉዳይ ነው። ስለአቶ ልደቱ ከእኔ በላይ ብዙ ነገሮችን አጣቅሶ ማቅረብ የሚችል ሌላ ማን እንዳለ በእውነት አላውቅም ። በፓርቲዬም ላይ ቢሆን በተደጋጋሚ ምን ያደርጉ እንደነበር ፈፅሞ ዘንግቸው አይደለም። አቋማቸው ከአቋሜ ስለገጠመም አይደለም። ይልቅስ አቶ ልደቱ እራሳቸውን መከላከል በማይችሉበት በዚህ ሁኔታ አንዳች አሉታዊ ጉዳይ አንስቼ እሞግታቸው ዘንድ ፈፅሞ ህሊናዬ አይፈቅድልኝም።
በተወሰነ መልኩ የቀደመውን ለአንባቤ ያስታወስኩትም ቢሆን፣ የቆምኩበትን የሀሳብ ማዕዘን ለማሳየት ይረዳኝ ዘንድ ግድ ሆኖብኝ እንጂ ምቾት ተሰምቶኝ አይደለም። ይልቅስ ከላይ ከፍ ብዬ ከጠቀስኳቸው ወገኖቻችንም በከፋ ሁኔታ የ”ፓሊስ” ጢባጢቢ መጫወቻ ሆነው ሳይ እርሳቸውን የወጋ ጦር እኔንም እንደወጋኝ ተሰምቶኛል። በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ከእስር እንዲለቀቁ ቢያዙም በፓሊስ እንቢተኝነት ግን በእስር ላይ ይገኛሉ። ውርደቱ፣ መረገጡ፣ንቀቱና ኢፍትሃዊነቱ፣ የኢፍትሃዊነትን ስቃይ ለምናውቅ ዜጎች ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ነው።
በማንኛውም ዜጋ ላይ የሚፈፀም ኢፍትህአዊነት በሁላችንም ላይ እንደተፈፀመ የሚጠራጠር ካለ እርሱ ፍፁም ማስተዋል የጎደለው ነው።
በኢትዮጵያችን እየታየ ያለው ለከት ያጣ ግፍ ቅስም የሚሰብርና በምንም አይነት መንገድ ልንታገሰው የማይገባ ኢፍትሃዊ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ያዋረደ ወደር አልባ የነውረኝነት ተግባርም ነው።
በፈጣሪ እንደምትታመኑ ደጋግማችሁ የነገራችሁን ወገኖች በሚፈፀመው ግፍ ፈጣሪ የሚደሰትበት ይመስላችኋል? የሚሰራውን ኢፍትሃዊነት በአስቸኳይ እስካላስቆማችሁ የፈጣሪም ሆነ የህዝብም ቁጣ እሩቅ እንደማይሆን ለመናገር ነቢይነትን አይጠይቅም።
Free Lidetu Ayallew

8 Comments

 1. እኔም ያልከውን በሙሉ እጋራለሁ፡፡ ነገር ግን ለጉዳዩ ዶ/ር አቢይ መፍትሄ እንዲሰጥ የምትጠብቅ ከሆነ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም አሁን ባለው ህገ መንግስት መነጽር ካየነው አቢይ እንዲያውም ጭራሽ አያገባውም (እንደው ምናልባት በፓርቲው መስመር ካልሆነ?)፡፡ ምክንያቱም ድርጊቱ የተፈጸመው በኦሮሚያ ክልል እና የክልሉ መንግስት ተቋማት ነዋ፡፡ መጠየቅ ያለባችው ሽመልስ አብዲሳ እና መኣዛ አሽናፊ ይመስሉኛል፡፡ ጉዳዩን ደፈር ብሎ አጣርቶ ማቅረብ ደግሞ የሚዲያ እና ምናልባትም የተፎካካሪ ፓርቲዎች ሥራ ይሆናል፡፡ እንደው በግልህም ሆነ በኢዜማ መስመር ምንም ማጣራት ለማድረግ አልሞከርክም? ዳንኤል በቀለ እንዴት ዝም አለ? ወይስ እኔ አልሰማሁም፡፡

  • ወንድሜ እየቀለድክ ነው እንዴ? ኧረ ይጻፍከውን መልሰህ አንብበው፡፡ “ጭራሽ አያገባውም (እንደው ምናልባት በፓርቲው መስመር ካልሆነ?)፡፡ ምክንያቱም ድርጊቱ የተፈጸመው በኦሮሚያ ክልል እና የክልሉ መንግስት ተቋማት ነዋ፡፡ መጠየቅ ያለባችው ሽመልስ አብዲሳ እና መኣዛ አሽናፊ ይመስሉኛል፡፡ ”
   መቼ ነው አብይ እና አስተዳደሩ ሃላፊነት የሚወስደው? የውጪ ወራሪ ሲመጣ? መጀመሪያ የመንግሥትን ምንነትና ሃላፊነት ቆም ብልህ አስብበት፡፡
   እውነቱን ለመናገር አብይ የመሪነቱን ሃላፊነት ከወሬ መቦጥረቅ ሌላ የማይፈደው እንዳንተ አይነት በጭፍን እያሟሟቃችሁት ህዝብ ሲታረድ ፍርድ ሲገመደል እያየን አስተዳደሩ ተጠያቂ እንዳይሆን እያደረገቻሁ ይሄን ምስኪን ህዝብ እያሳለቃችሁት ነው፡፡

   • አይፈረድበህም። የለመድከውና የምታውቀው አንድ ሰው ከላይ የመንግስት መሪ ሆኖ ሁሉንም ሲያዝ ነው፡፡ ጃንሆይም፤ መንግስቱ ኃይለማርያም እና መለሰ (በፈደራል ስም የበለጠ አሃዳዊ)። እናም ወይ የፌዴራል ሥርአቱን አስቀይር ወይም የፈደራል ሥራዓት እንደት እንደሚሰራ ዕወቅና ተለማመድ፡፡

    • This is nothing to do with federalism. It is called accountability! The truth is that weather you like it or not the p/m Abiy and his leadership has been destabilizing Ethiopia…

 2. ሃሳብን በነፃነት መግለፅ ብቻ ፍትህና ዲሞክራሲ የሰፈነበት አገር ሊያስብል አይችልም፡፡ ላይ ላዩን ብቻ ዋጋ የለውም፡፡ እነአሜሪካን ስንት ስለዲሞክራሲ የሚያወሩ በአደባባይ በጥቁሮች ላይ የተፈፀመ ግፍ ምን ያህል የፍትህ ጉድለት በአለም ላይ እንዳለ አመላካች ነው፡፡ በመሰረቱ ፍትህ ካለ እኮ ፖሊስ ሲያጠፋ በፍርድ ቤት መታዘዝ ነበረበት፡፡ ህጉም ተጣያቂ ሊያደርገው ይገባ ነበር፡፡ ታዲያ አሁንም ያለው ከ1993 የፍርድ ቤት ችሎት ምን ለየው፡፡ አሁን እየታሰበ ያለው የፖሊስ መመሪያ/Policy/ እንደዚህ ያሉ ችግሮችንም መፍታት ከቻለ ጥሩ ነው፡፡

  ስለዚህ ይህቺ አገር የዲሞክራሲ መሰረት እንዲጣልባት ከታሰበ ፍትህ ከዚህ ነው የሚጀምረው፡፡ በዚህ ሂደት ቀጣይ ምርጫ ላይ በህግ ተቋማትና በፓርቲዎች ጣልቃ ላለመገባቱ ምን ዋስትና ይኖር ይሆን????????????? የፍትህ ስርዓት ከዚህ ነው የሚጀምረው፡፡ ይህ ለሚያልፍ ጊዜ ለቀጣዩ ትውልድ ጥሩ መሰረት ጥሎ ማለፍም አንድ ነገር ነው፡፡ አለዚያ አትፍረድ ይፈረድብሃል ይሆናል ነገሩ፡፡

 3. Kedir Setete

  The federal government is responsible to provide security and justice to all it’s citizens whenever the regional government is unwilling or unable to provide security and justice to its citizens. If the federal government is also unable then the federal government need to allow to form a caretaker government.

  The question would be is the mass arrest of nine thousand plus people including some opposition figures providing justice and security to the citizens or not? EXPERTS SAY IT IS NOT. Diminishing the ongoing genocide and pretending justice is being served and pretending the country is secured while the truth on the ground is saying otherwise is making the problem worst than it actually was, just for that reason only PM Abiy needs to be personally held accountable. History should document that the bloods of those citizens is in his hands. We need the Professor Meeting Woldemariams replacement (whoever he or she is ) to document it, that is if there is any replacement at all. Maybe the replacement is afraid too.

  • @Memex2
   አንተ/ቺ ደግሞ ወዴት ወዴት?፡ እኛ ያወራነው የአዳማ ፍርድ ቤት ትዕዛዝን ተቀብሎ ፖሊስ ለምን ልደቱን አልፈታውም ነው፡፡ ለማንኛውም አንተም ለሞቱት አዝነህ ሳይሆን የሥልጣን አቋራጯ ሥለተዘጋች ለአቢይ ያለህ ጥላቻ ጣራ ነክቶ ነው፡፡ በናትህ ይህንን “Caretaker govt” የሚባል የ”ፋራ” ፖለቲካ ሁለተኛ አታንሳ።

 4. Kedir Set Ete

  Yes you are right, I should use the word “technocrat” government instead. When I said care taker my ” in home care taker ” ( my domestic worker) thought I was going to order her to lead the government , she said “I will resign before you make me lead the country” . TRUE STORY

  That being said Adama’s court did not order to release Lidetu.

  Debre Zeit court ordered to release Lidetu since the trial went for months at the Debre Zeit court. but Shimeles Abdissa kept Lidetu hostage in jail defying the Debre Zeit court order to release Lidetu. After weeks past with Lidetu remaining hostage of Shimeles Abdissa then Shimeles brought Lidetu to Adama for intterogation , even the Adama court asked the police why Lidetu is still in custody after the Debre Zeit court ordered for his release? No answer yet by police because they are afraid to say Lidetu is held hostage illegally just like the Dembi Dollo University students. The sad thing is Lidetu is suffering from heart complications disease and need immediate medical treatment in Belgium or other countries outside Ethiopia. Shimelea is hoping if he keep him hostage long enough Lidetu will die or Lidetu will become incapacitated to ever function normally . Just like what Meles Zenawi did to the late Asrat Woldeyes

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.